Sunday, November 25, 2012

ቤተክህነት የቱሪዝም ተቋም ልትመሠርት መሆኗን አስታወቀች


በሔኖክ ያሬድ(From Reporter )
የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን በአገር ውስጥና በውጭ አገር በተለይም በኢየሩሳሌም የሚገኙ ገዳማቷንና የቱሪስት መዳረሻዎቿን የሚያስተዋውቅ የቱሪዝም መምርያ ለመመሥረት በእንቅስቃሴ ላይ መሆኗን አስታወቀች፡፡ በተለይም ወደ ኢየሩሳሌም የሚደረጉ የምዕመናን ጉዞዎችን በኃላፊነት ለመምራትም አቅዳለች፡፡

በጠቅላይ ቤተክህነት የውጭ ግንኙነት መምርያ ኃላፊ መምህር ሰሎሞን ቶልቻ ለሪፖርተር እንደገለጹት፣ ቤተ ክርስቲያኒቱ በያዘችው ዋና ዓላማ ከመንፈሳዊ አገልግሎቷና አገራዊ ልማት ተሳትፎ ባሻገር፣ በቱሪዝሙ መስክ ከአገልጋይነት ባለፈ ተጠቃሚ ባለመሆኗ የቱሪዝም መምርያን ለመመሥረት በእንቅስቃሴ ላይ ትገኛለች፡፡ ቤተ ክርስቲያኒቷ እምነቷ፣ ቀኖናዋና ሥርዓቷም ሳይፋለስ ተከብሮ ትውልድ ተሻጋሪ እንዲሆን ለማስቻል የቱሪዝምና ቅርስ አገልግሎት ተጠናክሮ እንዲቀጥል በቅዱስ ሲኖዶስ መወሰኑን መምህር ሰሎሞን አስታውሰዋል፡፡ ለዚህም ተግባራዊነት የቱሪዝም መምርያ ማቋቋም አስፈላጊ በመሆኑ ቅድመ ጥናቶች እየተሠሩ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡

በዓመት ሁለቴ በኢየሩሳሌም የሚደረገው የምዕመናን ጉዞ ቤተ ክርስቲያኒቱ በባለቤትነት ለመያዝና በተመጣጣኝ ዋጋ አገልግሎት የሚሰጥ የአስጎብኚ ድርጅት ለመክፈት የሚያስችል ቅድመ ጥናት ለማድረግ፣ በቅዱስ ሲኖዶስ ዋና ጸሐፊ ብፁዕ አቡነ ሕዝቅኤል የተመራ ቡድን ከኅዳር 14 እስከ 22 ቀን 2005 ዓ.ም. ድረስ ኢየሩሳሌም ውስጥ እየተወያየ ነው፡፡

‹‹በአገሪቷ ላለው ቱሪዝም መዳረሻ ከሆኑት ሥፍራዎች ሰፊውን ሽፋን የምትሰጠው ራሷ ናት፡፡ ባህላዊ ተጠቃሚ እንጂ ኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታ አግኝታበታለች ማለት አይቻልም፤ ከእርሷ ይልቅ በእርሷ ስም ተጠቃሚዎች ሌሎች ናቸው፤›› ያሉት ኃላፊው፣ በኢየሩሳሌም ርስት ካላቸው የምሥራቅና የምዕራብ አብያተ ክርስቲያናት ጋር የኢትዮጵያ ሲነፃፀር ደከም ያለ በመሆኑ ትኩረት ሰጥቶ መንቀሳቀስ አስፈላጊ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

በሚቋቋመው የቱሪዝም መምርያ አማካይነት በገና እና ትንሣኤ ለሚከናወነው የኢየሩሳሌም ጉዞ የኢትዮጵያ አየር መንገድ አብሮ እንዲሠራ ቤተ ክርስቲያኒቱ መጠየቋንና በጎ ምላሽና ተስፋ ሰጪ ውጤት መገኘቱንም ገልጸዋል፡፡

ክርስትና በኢትዮጵያ በመጀመርያው ምእት ዓመት መግባቱና በአራተኛው ምእት ዓመትም የኢትዮጵያ ኦርቶዶስ ቤተ ክርስቲያን መመሥረቷ ይታወቃል፡፡ በኢየሩሳሌም ቅዱሳት መካናት ካሏቸው ጥቂት አገሮች አንዷ የሆነችው ኢትዮጵያ የዴር ሱልጣን ገዳሞቿ ከክርስቶስ ልደት በፊት ከንግሥተ ሳባ ጊዜ ጀምሮ ባለርስት እንደሆነች የቤተ ክርስቲያኗ ታሪክ ያመለክታል፡፡

1 comment:

  1. ርብቃ ከጀርመንNovember 25, 2012 at 9:20 AM

    እሰየው ይበል ይበል የሚያሰኝ ነገርነው ነገርግን በእቅድብቻ እንዳይቀር አደራ ለፍጻሜ አብቁት መቸም በዚህ ስድስት ወርብቻ ስንት እቅድና ውሳኔ ቤተክህነት ወይም ቅዱስ ሲኖዶስ እንድስተላለፈ የምናውቀው ነገር ነው ስንቱ ግን ተፈጻሚይሆናል የሚለውን እግዚያአብሄር ያውቃል ነገርግን ተስፋባለመቁረጥ አሁንም ....!

    ReplyDelete