Friday, February 3, 2012

ጾመ ነነዌ!!

እንኳን አደረሳችሁ!! 
ነነዌ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ታሪካቸው በስፋት ከተጻፈላቸው የሜሶፖታምያ ከተሞች አንዷ ናት፡፡ ብዙ የሥነ መለኰት ምሁራን ከዛሬዋ የሞሱል ከተማ በተቃራኒ ከባግዳድ ሰሜን ምዕራብ 350 ኪ.ሜ. ርቀት ላይ እንደ ነበረች ይስማማሉ፡፡ ምንም እንኳን በ4000 ቅ.ል.ክ. ገደማ በናምሩድ በኵል ብትቆረቆርም /ዘፍ.10፡11-12/ የአሦራውያን ዋና ከተማ የሆነችው ግን በ1400 ቅ.ል.ክ. ነው /2ነገ.19፡36/፡፡ በከተማዋ በጣም ታዋቂ የነበረው የጣዖት ቤተ መቅደስ የአስታሮት ቤተ መቅደስ ይባላል፡፡
በዚህች ከተማ የሚኖሩት ሰዎች የሚሠሩት ክፋትና ኃጢአት እጅግ ከመብዛቱ የተነሣ ጽዋው ሞልቶ መጥፊያቸው ስለ ደረሰ ለፍጥረቱ ርኅራኄ ያለው እግዚአብሔር ግን ንስሐ ይገቡ ዘንድ ነብዩ ዮናስን ልኮላቸዋል፡፡ ይህ ነብይ ወደ አሕዛብ መንደር የተላከ ብቸኛ ነብይ ነው፡፡ አላላኩም አንድ ነብይ ወደ እስራኤላውያን ተልኮ እንደሚያደርገው ለመገሰጽ ሳይሆን ወደ ንስሐ ይጠራቸው ዘንድ ነበር፡፡ ነገር ግን ነብዩ ወደዚያች ከተማ እንዲሄድ በእግዚአብሔር ቢታዘዝም ወደ ተርሴስ ሲኮበልል እንመለከተዋለን፡፡ ቅዱስ ጄሮም ነብዩ ለምን እንዲህ እንዳደረገ ሲናገር፡- “ዮናስ አሕዛብን ከመጥላቱ የተነሣ ሳይሆን መዳን ከእስራኤል እየራቀ መሆኑን በትንቢት መነጽር ሲመለከት ወደ ነነዌ አልሄድም አለ፡፡ ይኸውም ሙሴ ይህን ሕዝብ ከምታጠፋው እኔን ከሕይወት መጽሐፍህ ደምስሰኝ ያለው ዓይነት ነበር /ዘጸ.32፡31-32/፡፡ ቅዱስ ጳውሎስም ስለ እነርሱ እርሱ ቢረገም እንደሚመርጥ እንደሰማነው” ብሏል /ሮሜ.9፡3/፡፡ በእርግጥም በዘመነ ሐዲስ አሕዛብ በክርስቶስ አምነው ሲጠመቁ እስራኤል ግን መጻሕፍትን ብቻ ይዘው ቀርተዋል፤ እስራኤል ነብያትን ብቻ ይዘው ሲቀሩ አሕዛብ ግን የነብያቱን የትንቢት ፍጻሜ ይዘዋል /ማቴ.12፡42/፡፡
ልብ ያመላለሰውን ኩላሊት ያጤሴውን የሚያውቅ አምላክ ግን ዮናስ ላለመታዘዝ ብሎ እንዳላደረገው ስላወቀ በልዩ ጥበቡ ሲወስደው እናያለን፡፡ አስቀድሞ ታላቅ ነፋስን በመርከቢቱ ላይ አመጣ፤ ዮናስን የሚውጥ ታላቅ ዓሣ አሰናዳ፤ ሲቀጥል ደግሞ ዓሣው በየብስ እንዲተፋው አደረገ፡፡ ኦ! አምላኬ! የእግዚአብሔር ፍቅር እንዴት ዕፁብ ድንቅ ነው?! 
ዮናስ ወደዚያች ከተማ ከደረሰ በኋላ ግን ምንም እንኳን የሦሰት ቀን መንገድ ዙሮ መስበክ ቢጠበቅበትም የአንድ ቀን መንገድ ያህል ወደ ከተማይቱ ውስጥ ሊገባ ጀመረ፤ ጮኾም። በሦስት ቀን ውስጥ ነነዌ ትገለበጣለች አለ። የነነዌም ሰዎች እግዚአብሔርን አመኑ፤ ለጾም አዋጅ ነገሩ፥ ከታላቁም ጀምሮ እስከ ታናሹ ድረስ ማቅ ለበሱ። ወሬውም ወደ ነነዌ ንጉሥ ደረሰ፤ እርሱም ከዙፋኑ ተነሥቶ መጐናጸፊያውን አወለቀ ማቅም ለበሰ፥ በአመድም ላይ ተቀመጠ። አዋጅም አስነገረ፥ በነነዌም ውስጥ የንጉሡንና የመኳንንቱን ትእዛዝ አሳወጀ፥ እንዲህም አለ፡- “ሰዎችና እንስሶች ላሞችና በጎች አንዳችን አይቅመሱ፤ አይሰማሩም ውኃንም አይጠጡ፤ ሰዎችና እንስሶችም በማቅ ይከደኑ፥ ወደ እግዚአብሔርም በብርቱ ይጩኹ፤ ሰዎችም ሁሉ ከክፉ መንገዳቸውና በእጃቸው ካለው ግፍ ይመለሱ። እኛ እንዳንጠፋ እግዚአብሔር ተመልሶ ይጸጸት እንደ ሆነ፥ ከጽኑ ቍጣውም ይመለስ እንደ ሆነ ማን ያውቃል?” ሰው ወዳጁ ጌታም ከክፉ መንገዳቸው እንደተመለሱ ሥራቸውን አየ፤ ያደርግባቸው ዘንድ በተናገረው ክፉ ነገር ተጸጽቶ አላደረገውም። በእርግጥም እግዚአብሔርን የሚፈራ ልቡና የትምህርት ጋጋታ አያስፈልገውም፤ የቀናት ብዛት አያስፈልገውም፡፡
እኛ ክርስቲያኖችም ይህን በማዘከር “ንስሐ ብንገባ እንደ ነነዌ ሰዎች ከተቃጣው ማንኛውመ መቅሰፍት እንድናለን” በማለት በየዓመቱ ከዓብይ ጾም መግቢያ ሁለት ሳምንት አስቀድማ ካለችው ሰኞ ጀምሮ እስከ ረቡዕ ድረስ “ጾመ ነነዌ” በማለት እንጾማታለን፡፡ ዘንድሮም ዓብይ ጾም የካቲት 12 ስለሚገባ የአሁኑ ሰኞ ጥር 28 እስከ ረቡዕ ጥር 30 እንጾማታለን፡፡
እግዚአብሔር የመረጠውን ዓይነት ጾም እንድንጾም ከተቃጣው ማንኛውም ዓይነት ፈተናም እንድናመልጥ ሰውን በመውደድ ሰው የሆነው ክርስቶስ ይርዳን አሜን!!

From Gebregziabher Kide  face book address

1 comment:

  1. ENQUAN ABERO ADERESEN! ...የነነዌን ሕዝብ ጾም የተቀበለ እግዚአብሔር የኛንም ይቀበለን.

    ReplyDelete