(አንድ አድገን ህዳር 28 ፤
2005 ዓ.ም)፡- መጽሐፍ ቅዱስ እንዲህ ይላል “ለሰው ሁሉ ከሚሆነው በቀር ምንም ፈተና አልደረሰባችሁም፤ ነገር ግን ከሚቻላችሁ መጠን ይልቅ ትፈተኑ ዘንድ የማይፈቅድ እግዚአብሔር
የታመነ ነው። ትታገሡም
ዘንድ እንድትችሉ
ከፈተናው ጋር መውጫውን
ደግሞ ያደርግላችኋል።” የፍቅር
እጦት እንጂ ሰውም በወንድሙ ላይ በክፋትና በአመፅ
አይነሳምና ቃየል አቤልን
በምቀኝነትና በጥላቻ
ተነሳስቶ እንደገደለው ሁሉ ዛሬም ብዙ ቃየላውያን በወንድሞቻቸው ላይ በትዕቢት እና በእብሪት ተነሳስተው የሚሞት
ስጋቸውን ለመግደል ያሴራሉ።
መግደል ለእነርሱ
እጅግ የቀለለ ተግባር
ነው፤ ቀድመው
ህሊናቸውን ገድለዋልና። ነገር ግን ዛሬም አሁንም በዚች ቅጽበትም
በንስሃ ለተመለሰ
ሁሉ ምህረት አለ።
ከጥፋት መንገድ
ዘወር ላለ መዳን ይሆንለታል። ነገር ግን እንደቀደመው ጊዜ በክፋትና በተንኮል
ለመመላለስ ልቡን ያደነደነ፣
ፍቅርን የገፋ፣
ምህረትን የናቀ፣ ለወገኖቹ
መጥፊያ ያሴረ፣
ጥላቻን ያነገበ እርቅን
የጠላ ሰው ወይም ቡድን የኋላ ኋላ በታላቅ አወዳደቅ መንኮታኮቱ
አይቀርም።
እርቅና ሰላም ያልተጠጋው ጉልበትና ሃይሉን ፤
ሴራና ተንኮሉን ፤ የተመካም
ሲምስ በዋለው
ጉድጓድ ገብቶ እስከወዲያኛው
ማለፉን ታሪክ ይነግረናል። በግርማቸው አስፈሪ
የነበሩትም ነገሥታት እስከጭፍራ
ሠራዊቶቻቸው በውሃ ሙላት ሲወሰዱ፣ እንደ እንስሳ በጫካ ሲቅበዘበዙ፣ እና ከነመታሰቢያቸው
ትቢያ ሲሆኑ ዓለም ታዝባለች።
ሃይልን እና እብሪትን በፍቅር
እና ርህራሄ፣ በይቅርታ
እና ታጋሽነት፣
በትህትና እና ጨዋነት
የሚመክቱ ግን በስተመጨረሻ አሸናፊዎች ናቸው።
እስከመጨረሻዋ አስፈሪ ቅጽበትም
ባመኑበት ነገር ፀንተው የሚቆሙ፣ የመጨረሻዋን
ጽዋ ለመጐንጨት
የታመኑ፣ በህይወታቸውም ባይሆን
በህልፈታቸው ዛሬም ፍቅር
ህያው እንደሆነ
የሚሰብኩ ሰማዕታት በየዘመኑ
መነሳታቸው ደግሞ ለሰው ልጆች ሁሉ ተስፋ ነው። በሰው ልጅ ላይ ያለንን የመልካምነት እምነትም ያጠናክርልናል።
ዛሬም በመተዛዘን፣ በመዋደድ፣ በአንተ ትብስ አንቺ መከባበር፣ ራስን አሳልፎ በመስጠት፣ በመረዳዳት፣ ደስታና
ሀዘን በመካፈል፣ ያለንን
ሁሉ በማካፈል፣
ለወገንና ለቤተክርስቲያን
በመቆርቆር የወደፊቱን ትውልድ ህይወት የእኛንም
ጭምር ብሩህ ማድረግ እንችላለን። እኛ
ከተዋደድን ብዙዎቹ
ተራሮቻችን በፊታችን ደልዳላ
ሜዳ ይሆናሉ። ፍቅር
ሃያል ነው፤ ፍቅር ያላቸውም ኃያላን
ናቸው። በመሆኑም ፍቅር
ያላቸው ሁሉ የኃያላን ተግባራትን ይከውናሉ።
በልበ-ሙሉነት
እና በፍፁም በራስ-መተማመን ስሜት ሊገላቸው ጭምር ከመጣው
ሰው ፊት የፍቅር ምላሽ ይሰጣሉ። ሰይፍን በሰይፍ
አይመልሱም፤ ሰይፍን የሚያነሱ
በሰይፍ እንደሚጠፉ
ያውቃሉና! ይልቁንም
ግራ ጉንጫቸው
ሲመታ ቀኙን ለማዞር
ይዘጋጃሉ። ሊገላቸው
የመጣውን ሰው በክፋት
አይተባበሩትም። የገዳይ
ግብረ-አበርም አይሆኑም፤
ለመሞት ይመቻቹለታል
እንጂ። በዚህም ተግባራቸው
የፍቅርን ሃያልነትና ረቂቅነት
ይገልጣሉ! እየሞቱ፡-
‹‹አባት ሆይ፡ -
የሚሠሩትን አያውቁምና
ይቅር በላቸው!››
እያሉ ስለገዳዮች
ይማፀናሉ። ምክንያቱስ
ቢሉ፡ ‹‹ፍቅር ይታገሣል፣ ቸርነትንም ያደርጋል፣
ፍቅር አይቀናም፤
ፍቅር አይመካም፣ አይታበይም፤
የማይገባውን አያደርግም፤ የራሱንም
አይፈልግም፤ አይበሣጭም፤ በደልን
አይቆጥርም፣ ከእውነት
ጋር ደስ ይለዋል
እንጂ ስለዓመፅ
ደስ አይለውም፤ ሁሉን
ይታገሣል፣ ሁሉን ያምናል፣ ሁሉንተስፋ
ያደርጋል፣ በሁሉ ይፀናል።›› ይህም የተገለፀው
በመጽሐፍ ቅዱስ ነው።
ታዲያ ዛሬ ሕይወታችንን መለስ ብለን
ስንቃኘው፣ ወደውስጣችን
ስንመለከት፣ ጓዳችንን ስንመረምረው፣
ልባችንን ስንፈትሸው ፍቅርን
እናገኘው ይሆን? ወይስ በቦታው ጥርጣሬ፣ አለመተማመን፣ ፍርሃት፣
ቂም በቀል እና ጥላቻ ነግሶበታል? ቀስ-በቀስ ውስጣችንን እየቦረቦረው እና እየገደለው ያለውን ይህንን
መርዘኛ ሰንኮፍ
የምንነቅለውስ በምንድን ነው? ምንም መልካም እንዳንሠራ ብቻ ሳይሆን
የምንሠራው ሁሉ ጥፋት እንዲሆን ከሚያንደረድረን
ጥላቻስ የምንወጣው በምን
መላ ነው? ከራሳችን፣ ከቤተሰባችን፣ ከጐረቤቶቻችን፣ ከአባቶቻችን ጋር ተጣልተንስ የምንኖረው
እስከመቼ ነው? መቼስ እርቅ እናወርዳለን? መቼስ የቀደመውን ፍቅር ከወደቀበት
እናነሳዋለን?
ለመሆኑ “እርቅ” ማለትስ ምንድነው?የፕ/ር መስፍን ወልደ ማርያም “አገቱኒ” ላይ እንዲህ ይነበባል፡- ‹‹እርቅ ማለት ጠብን በሰላም፣ ጥላቻን በፍቅር፣ አለመግባባትን በስምምነት፣ ጥርጣሬን በመተማመን፣ መራራቅን በመቀራረብ፣ ኩርፊያን በመነጋገርና በመወያየት መለወጥ ነው፤ እርቅ ማለት የበደለ ጥፋቱን አምኖና ካሣ ከፍሎ፣ የተበደለ ቂሙን ከልቡ ፍቆ ለአዲስ ግንኙነት በንጹሕ መንፈስ መታደስ ነው።
እርቅን የሚፈልግ
ማን ነው? እርቅን የሚፈልግ
ሰላምን የሚፈልግ
ነው፤ እርቅን የሚፈልግ
ከራሱ በላይ የአምላክም ሆነ፣ የሕግም
ሆነ፣ እግዚአብሔየር
ኃይል መኖሩን የሚያምንና
አርቆ የሚያስብ
ሰው ነው፤ እርቅን የሚፈልግ ዘመን ተሸጋሪ እይታ ያለው ሰው ነው ፤ እርቅን የሚፈልግ ያለ
ሰላም የተጓዘበትን መንገድ ዞር ብሎ መመልከት የሚችል ሰው ነው :: ምንም
ዓይነት ተጠያቂነት
የሌለበት መስሎ የሚታየው፣
እያጠቃሁ ለመኖር
የሚያስችለኝ ጉልበት አለኝ ብሎ የሚያምን ሰው፣ ከጉልበቱ ውጭ የሚተማመንበት ምንም ኃይል ስለሌለ እርቅን የሚፈልግበት ምክንያት
አይታየውም፡፡ ተበዳይም ቢሆን አቅሙን አሳንሶ
ገምቶ “ደሀ ተበድሎ ማሩኝ ይላል ቶሎ” እንደሚባለው አለመቀየሙንም ለመግለጽ
ሲል ራሱን በደለኛ አድርጎ በማቅረብ
ጉዳዩን በዳዩ እንዲረሳለት ይሞክራል፤ ነገር ግን በዳዩም ሆነ ተበዳዩ ከሚያቆራኛቸው የበደል ሰንሰለት
አይላቀቁም፤ በዳዩ ተበዳዩ
አይተኛልኝም ብሎ በስጋትና በፍርሃት ይኖራል፤
ተበዳዩም የበዳዩን ፍርሃትና
ስጋት ስለሚያውቅ
ሲመቸው ያጠፋኛል ብሎ በስጋትና በፍርሃት
ይኖራል፤ እርቅ የሚያስወግደው
ይህንን በሁለቱም በኩል
ያለውን ስጋትና
ፍርሃት ነው፤ እውነት ነጻ ያወጣል
የሚባለው የሚሠራው
ለዚህ ነው፤ ሽምግልና
በእውነት ላይ እንዲቆም የሚያስፈልገውም ለዚህ ነው።
እርቅ ማለት እግዚአብሔር ነው፤ እርቅ የእግዚአብሔር ባሕርይ
ነው፤ እግዚአብሔር ማለት እርቅ ነው፤ በክርስትና የመስቀል ትክክለኛ
ትርጉሙ እርቅ ነው፤ ክርስቶስ ሰው ሆኖ መከራውን የተቀበለውና የተሰቀለው ለእርቅ
ነው፤ አዳም በበደለ መድኃኔዓለም ካሠ የሚባለው ለዚህ ነው፤ እርቅ
የእግዚአብሔር በመሆኑ
ነው ትንሽና ትልቅ፣
አለቃና ምንዝር፣
ሴትና ወንድ፣ ሽማግሌና
ወጣት፣ ንጉሠ ነገሥትና ሎሌ የማይለየው፤
ለዚህ ነው በጦርነት ድልን የተጎናፀፈውና
የተሸነፈው በእርቅ
ደማቸውን የሚያጥቡት፣ ለዚህ ነው ማራኪና ምርኮኛ ቂማቸውን በእርቅ
የሚፍቁት፣ ለዚህ ነው አሳሪና ታሳሪ ከሁለቱም ለበለጠ
ፋይዳ በእርቅ የሚስተካከሉት፤
እርቅ የእግዚአብሔር በመሆኑ
አይናቅም፤ እርቅ የእግዚአብሔር በመሆኑ አይደበቅም፤
እርቅ የእግዚአብሔር
በመሆኑ ያስከብራል
እንጂ አያሳፍርም፤ እርቅ
የእግዚአብሔር በመሆኑ
ጽድቅ ነው፤ እውነት
ነው፤ ክቡር ነው፤ እርቅ ክቡር በመሆኑም ያስከብራል። በዳይና ተበዳይ መሀል እርቅ ሲወርድ
እግዚአብሔርን ደስ ማሰኝት ነው ፡፡
ዛሬ በደቡብ አፍሪካ ኩራት የሆኑ ትልልቅ ሰዎች የሚገኙት እርቅ የእግዚአብሔር መሆኑን በመገንዘባቸው
ነው፤ አሳሪ ደክላርክና ታሳሪ ኔልሰን
ማንዴላ ከሁለቱም
በላይ የደቡብ አፍሪካ
ሕዝብ፣ ደቡብ አፍሪካ የሚባል
አገር፣ ሰላምና ብልጽግና፣
እግዚአብሔር ከነሱ በላይ እንዳሉ በማወቃቸው
ለእርቅ ልባቸውን በመክፈታቸው
ነው፤ ታሳሪውን
ኔልሰን ማንዴላን በደቡብ
አፍሪካ ብቻ ሳይሆን በዓለም ጭምር
ለትልቅነት ያበቃው
አሳሪው ደክላርክ ነው፤
የደክላርክ ትልቅነት
በእምነትና በተስፋ የጉልበት
አስተሳሰቡን ለውጦ ልቡን ለእርቅ በመክፈቱና በተጨባጭም የእርቁን
መንፈስ ለመግለጽ ማንዴላን
ከእስር አውጥቶ
እኩያው ማድረጉ ነው፤ በእርቅ ትልቅ ሰው ትልቅ ሰውን ወለደ፤ ጉልህ መንፈሳዊ ወኔን አሳየ።››
ሁላችንም የምናሸንፈው
ፍቅር ሲያሸንፍ ነው።
ፍቅር ሲያሸንፍ
አባት ያሸንፋል!
ፍቅር ሲያሸንፍ እናት ታሸንፋለች! ፍቅር ሲያሸንፍ ልጆች ያሸንፋሉ!
ፍቅር ሲያሸንፍ
አባቶች ያሸንፋሉ! ፍቅር ሲያሸንፍ
ህዝበ ክርስቲያን
ሁሉ ያሸንፋሉ!
ፍቅር ሲያሸንፍ
የሰው ልጆች ሁሉ
ያሸንፋሉ! ፍቅር ሲያሸንፍ ለሁላችን ሰላም አንድነትና
እና ብልጽግና
ይሆናል!
ነገር ግን ፍቅር ያለ እውነት
ሽንገላ ነው ፤
እውነት ያለ ፍቅር
ዱላ መሆኑን መዘንጋት አያስፈልግም! በመላ ህዝበ ክርስቲያን መጨረሻው ምን እንደሆነ በጉጉት የሚጠበቀው በዳላስ በአባቶቻችን መካካል የተጀመረውን እርቀ ሰላም
የፍሬ ያደርግልን ዘንድ የእግዚአብሔር መልካም ፍቃድ ይሁንልን፡፡
“አንድ አድርገን
ጌታ ሆይ
አንድ አድርገን……….”
ዘለዓለሙ ሥላሴ የአባቶቻችንን ልብ አለዝቦ በፍቅር አንድ ያድርግልን።
ReplyDeleteለተዋህዶ ቤተክርስቲያናችን ለተዋህዶ ሃይማኖታችን በአንድ ቃል ተናጋሪ
በአንድ ቃል ፈፃሚ ይሁኑልን።
እግዚአብሔር ሀገርችንን ኢትዮጵያን በረድኤቱ ይጠብቅልን።
ወስብሐት ለእግዚአብሔር!
ይድረስ በአገር ውስጥና በውጭ አገር ለምትገኙ ለውድ አባቶቻችን ብጹአን ሊቀ ጳጳሳት።
ReplyDeleteከሁሉ አስቀድሜ የማክበር ትትና የተሞላበት የልጅነት ሰላምታየን ዝቅ ብየ ከጫማችሁ ስር ተደፍቸ አቀርባለሁ። ቡራኬአችሁ ለእኔና ለመላው የአለም ሕዝብ ይድረሰን እያልሁ በመልመን ከዚህ በታች የማቀርበውን አቤቱታየን ትሰሙልኝ ዘንድ በማክበርና በትትና እለምናለሁ።
ስሜ ዳንኤል እባላለሁ፤ እድሜየ 20 ነው፤ የትውልድ ቦታ ሰሜን አሜሪካ ነው፤ ስራየ ተማሪ ነው፤ እምነቴ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ነው።
በጉጉት መልካም ውጤቱን እየተጠባበቅን ያለው የአባቶች ዕርቀ ሰላም ውይይት በአሜሪካዋ የቴክሳስ ግዛት ዳላስ ከተማ እየተካሄደ መሆኑን ይታወቃል። ይህ በእንዲህ እያለ ኣባታችን ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ናትናኤል ለ VOA እንደተናገሩት ፓትርያርኩ (አቡነ መርቆሬዎስ) ወደ ሀገራቸው ገብተው በመረጡት ቦታ መቀመጥ እንደሚችሉ እንጅ ከዚያ የተለየ ምንም ሌላ ነገር እንደሌ ገልጸዋል።፣ በውጭም ሆነ በዉስጥ ያለነው ብዙዎቻችን የቤተ ክርስቲያኒቱ ልጆች እንደጠበቅነው፥ የተጣሰው ቀኖና ተስተካክሎ በአንድ ቅዱስ ሲኖዶስና በአንድ ቅዱስ ፓትርያርክ የምትመራ አንዲት ቤተ ክርስቲያን ትኖረናለች ብለን አስበን በጸሎትና በስግደት አምላካችንን ፈጣሪያችንን ያስጨነቅነውን ተስፋ ያጨለመብን ይመስላል። ምንም እንኳን የእግዚአብሔር ሃሳብና የሰው ልጅ ሀሳብ አንድ ባይሆንም የነበረው እንዳልሆነ ነው መረጃዎች የሚጠቁሙት።
ቤተ ክርስትያኗ የምትመራው በአንድ ፓትርያርክ ነው፤ በፓትርያርክ ላይ ፓትርያርክ አይሾምም፤ ቀኖና ተጥሷል፤ ውግዘት ይንሳ፤ እርቅና ሰላም ይውረድ እንዲሁም የመሳሰሉትን መንፈሳዊ ጥያቅይዎች መልስ ልማግኘት እውነት ከዚህ የሻለ ጊዜ አለን?
አቡነ መርቆሬዎስ በህይዎት አሉ፤ ስልጣናቸው መንፈስ ቅዱስ የሰጣቸው ስልጣን ነው፤ ከሃገር የወጡት ተገፍተው ነው፤ ሕዝባቸውን በሙያቸው እያገለገሉ ናቸው። ምእመናን የምናውቀው፥ የምናየውና የምንሰማው ሀቅ ይህ ሆኖ እያል፤ ታድያ ለምን ሌላ ፓትርያርክ መምረጥ አስፈለገ? ውድ አባቶቻችን ከኰሚዩኒዝም ጀምሮ እስከ ቅርብ ጊዜ እግዚአብሔር በሀገራችን ላይ ያደረገው ለእናንተ ግልጽ ሳይሆንላችሁ ቀርቶ አይደለም፤ እግዚአብሔር ያረመውን እኛ ፍጡሮቹ እንዳናበላሽ እናስተውል እንጂ፤ በማቴ ፮፥፲፬ -፲፭ ያዘዘው እናንተን አይመለከታችሁም?
ሁሉም ለማለት ብቸገርም፤ አብዛኛው ምእመናን ዛሬ ይቅር ለእግዚአብሔር እያል ይገኛል። ከአባቶቻችንም ይህንኑ ይጠብቃል። በጐች ተቅበዘበዙ፥ በጐች ጥሩ እረኛ ፈለጉ፥ የበግ ለምድ የለበሱ ተኩላዎች ሰግስገው ገብተው በጐችን እያመሱ ናቸው፤ የተኩላው መንጋ ራቅ ብሎ በጐች እስኪበተኑ ይጠብቃል። ልጆቻችሁ ተኩላውን እናሸንፍ፤ አባቶቻችን እርዱን? ይህን አድርጉልን?
አቡነ መርቆሬዎስ ፈቃደኛ ከሆኑና በቀራቸው የእድሜ ዘመን መንጋውን ለመጠበቅ ፈቃደኛ ከሆኑ:-
፩ ወደ ኢትዮጵያ ይግቡ፣
፪ ማእረጋቸው ፬ኛው ፓትርያርክ እንደሆነ ይጠበቅ፣
፫ አሜሪካ ከ፬ ባላነሰ አህጉረ ስብከት ትከለል፣
፬ ቃለ አዋዲ በመላው የውጭ አገር ላሉ የኢኦተቤክ ባስቸኳይ ይሰራጭ፣
፭ የኢ/ኦ/ተ/ቤ/ክ ከሙስናና ከዘረኝነት ባስቸኳይ ትንጻ፣
፮ ስራችን ሁሉ ክርስቶስን ይምሰል፤ ቅድስትና ብጽእት ማርያምን እናስብ፥ የመላይክትን አገልጋይነት እንይ፥ ጻድቃንና ሰማእታት ትተውልን እንዳለፉ ጠብቀን እናስተላልፍ።
የቅዱሳን አምላክ ቅድስት ቤተክርስቲያናችንን ይጠብቅልን፤ አሜን።