Monday, December 10, 2012

ምርጫ ይቅደም ወይስ እርቀ ሰላም ?




ከዲ/ን አባይነህ ካሴ
(አንድ አድርገን ታህሳስ 1 2005 ዓ.ም) ፡- የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን የዘወትር ተግባሯ ከሆነው መንግሥተ እግዚአብሔርን ከማስፋፋት ባሻገር በአሁኑ ወቅት ሁለት አበይት የቤት ሥራዎች ከፊቷ ተደቅነዋል፡፡ “እርቀ ሰላም” እና ቀጣይ “የፓትርያርክ ምርጫ” ፡፡ እነዚህ ሁለቱ አጀንዳዎች የሕዝበ ክርስቲያኑን አይንና ጆሮ  ሰቅዘው ይዘዋል፡፡ መረጃው ለደረሳቸው ከበረሀ እስከ ከተማ ፤ ከሀገር ቤት እስከ ውጭ ሀገር ያሉ የቤተክርስቲያን ልጆች ሁሉ የልብ ትርታ ሆኗል ቢባል ማጋነን አይሆንም፡፡
ቅድስት ቤተክርስቲያን ከእነዚህ ከሁለቱ ለየትኛው ቅድሚያ ልትሰጥ ይገባታል ? የሚለው ጥያቄ እየተብላላ ፤ በየአእምሯችን እየተጉላላ ፤ ወደ ህሊናችን እየተመላለሰ ፤ ቀንን ቀን እየወለደ ከዛሬ ደርሰናል፡፡ የጥቅምቱ ቅዱስ ሲኖዶስ የፓትርያርክ የምርጫ ሕግ እንዲዘጋጅ ያሳለፈው ውሳኔ እና በተለያዩ መገናኛ ብዙሃን “አምስት ብሎ ስድስት እንጂ አራት የለም” የሚለው መግለጫ እያነጋገረ ቀጥሏል፡፡ ከዚሁ ጎን ለጎን በአሜሪካ የሚገኙት አባቶች ደግሞ “4ተኛው ፓትርያርክ ወደ መንበራቸው ይመለሱ” ማለታቸው የውይይት አጀንዳ ሆኖ ሰነባብቷል፡፡

በየትኛውም የምድር ጫፍ እና ጠረፍ የሚገኙ አባቶች ሊያስቡበት የሚገባ አንድ ትልቅ እውነት አለ፡፡ የቅድስት ኦርቶዶክሳዊት ተዋህዶ ምዕመናን በገዛ አባቶቻቸው ፍጭትና ግጭት እንዲሁም ንትርክ  መፈተን እየገለመማቸው መምጣቱ ! ዝሆኖች ሲጣሉ የሚደርቁት ሳሮች ናቸው ፡፡ ዝሆኖቹ ለመጣላት ሆነ ለመታገል አንድ ሺህ አንድ ምክንያት ሊኖራው ይችላል፡፡ የእነሱ መጎዳት ሳያንስ አካባቢያቸውን የሚያተራምስ ከሆነ ላደረሱት ጉዳትም ሆነ ጥቃት ከተጠያቂነት አያመልጡም፡፡ በእኛም አባቶች ዘንድ የተከሰተው ሁኔታ የሳሮቹ አምሳያ የሆኑትን ምዕመናንን ክፉኛ እያጎሳቆላቸው ይገኛል፡፡
በመሆኑም እነርሱ ሲታገሉ እየደረቀ ያለው ልምላሜ ጨርሶ እንዲጠፋ መፍቀድ አይኖርባቸውም፡፡ ጠቡ ፤ ክርክሩ ሰልችቷቸው  ዓለምን ትተው የመነኑ  አባቶች የገጠሙት ግብግብ አመክንዮ ባይዋጥላቸው ሽሽት እየመረጡ ከድጡ ወደ ማጡ የገቡ ምዕመናን ስንት ይሆኑ ?
የብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ጳውሎስ ሞት ለቅድስት ቤተክርስቲያን ምን እድል ይዞ መጣ ? የሚለው በአግባቡ እና በሥርዓቱ መፈተሽ ይኖርበታል፡፡ ብዙዎቻችን ቤተክርስቲያን ያገኝችውን መልካም እድል በጥንቃቄ እና በመንፈሳዊነት ልትጠቀምበት ይገባል ብለን እናምናለን፡፡ አባቶቻችንም በየትም ይሁኑ በየት ይህንን  መመርመር ይሳናቸዋል አንልም፡፡ ስለዚህ ከእርቀ ሰላሙ እና ከሲመተ ፓትርያርክ ሊቀድም የሚገባው የትኛው ነው ? በምንስ ምክንያት ?  የሚለው በቅድሚያ መመለስ የሚገባው ጥያቄ መሆን አለበት፡፡
ፓትርያርክ ቢመረጥ ምን ጥቅምና ጉዳት ይረዋል?
1 . ጥቅሙ
ሀ.መንበሩ ጦም አያድርም፡- አሁን በውስጥና በውጭ ሀገር ያለውን ወቅታዊውን ሁኔታ ረስተን የተከፈለ ሲኖዶስ በሌለበት ሁኔታ ማሰብ የምንችል ብንሆን ኖሮ አንድ ፓትርያርክ አልፎ ተተኪው በጊዜ ካልተሰየመ መንበሩ ጦም ማደሩ ይጎዳል የሚል ነበር፡፡ ምክንያቱም በቀጥታም ይሁን በተዘዋዋሪ በሰው ሰውኛ አስተሳሰብ በመንበሩ ላይ ለመቀመጥ የሚመኙ ሰዎች እና  አካላት የሚፈጥሩት ሽኩቻ በቤተክርስቲያኒቱ አስተዳደር ላይ ያጠለሻልና፡፡ እንዲሁም በተለያዩ መንገድ እጃቸውን ለማስገባት ለሚሞክሩት አካላት ሰፊ እድል ይሰጣቸዋል፡፡ ለዚህም በቶሎ ፓትርያርክ መሰየም የራሱ ጥቅም ይኖረዋል፡፡ ይህ ማለት ግን እጃቸውን በረጅሙ ለማስገባት የሚፈልጉትን አካላት ሙሉ በሙሉ በዚህ መንገድ  በተፋጠነ ምርጫ መቋቋም ይቻላል ማለት አይደለም፡፡
ለ. ቤተክርስቲያን በባለ ሙሉ ስልጣን ትመራለች፡- በጊዜያዊ ወይም በሽግግር ወቅት የሚፈጠሩ ዓይነታቸው ብዙ የሆኑ ችግሮች ይኖራሉ፡፡ እነዚህን ችግሮች በጊዜያዊ ወይም በባለ አደራ ስልጣን የመጨረሻ ውሳኔ መስጠት ያዳግታል፡፡ ምንም ይሁን ምን አቃቢ መንበሩ ያለው ስልጣን የፓትርያርኩን አያክልምና፡፡
ሐ. ቡራኬው ፡- በመንፈሳዊ መለኪያዎች ፤ በስርዓቱ እና በአግባቡ የተመረጠ ፓትርያርክ ቢሰየም ምዕመናን በእግዚአብሔር የተወደደ እና የተመረጠ ነው ብለው እንዲያምኑ ስለሚያደርጋቸው ቡራኬውን እና ቃለ ምዕዳኑን አሜን ብለው በፍጹም ልባቸው ለመቀበል ይችላሉ፡፡ ይሁን እንጂ የምርጫው  ስርዓት ፍጹም ቀኖናዊ እና ቅንነት የተሞላበት እስከሆነ ድረስ በተፋጠነ መንገድ መሆኑም ቆይቶ መምጣቱ ምዕመናን የሚያገኙት ጥቅምን አያስቀርባቸውም፡፡
2. ጉዳቱ
ሀ. የቤተክርስቲያንን አንድነት ተስፋ ያጨልማል ፡- የቆምንበት የታሪክ ክፍለ ዘመን የሚያሳየን እውነታ በአሁኑ ወቅት ከሁለት የተከፈለ  ሲኖዶስ  መኖሩን ነው፡፡ በጓዳም ይሁን በጎድጓዳ  የማንደብቀው እያነቀን የምንውጠው ደረቅ ሀቅ ሆኖብናል ፤ የማንፈልገውን እንድናምን ተገደናል ፡፡ በመሆኑም  በሀገር ቤት ያለው ሲኖዶስ 6ተኛ ፓትርያርክ ወደ መምረጥ  የሚያዘነብል ከሆነ ፤ አሁንም እንደገና በሁለት ፓትርያርክ  የምትመራ አንዲት ቤተክርስቲያን  ባለቤቶች ልንሆን ነው፡፡ አንድ ከመሆን ይልቅ ሁለትና ከዚያም በላይ መሆንን የሚያመጣ ነውና ስህተቱ የማይጠገን ንስሐም የማይገኝለት ይሆናል፡፡ እየተደከመበት ያለው የእርቀ ሰላም ጉዳይ ወማ ይበላዋል፡፡ የአንድነቱን ተስፋ ያጨልማል፡፡
ለ. የቀኖና ልዩነት ይፈጠራል፡- ሁለት ሲኖዶስ እንዲኖር እስከተፈቀደ ድረስ በተለያዩ አርእስት የሚደነገጉ ቀኖናዊ ድንጋጌዎች ፤ የሚሰሩ ስርአቶች ልዩነት እያመጡ ይሄዳሉ፡፡ እነዚህ በቀኖና የሚጀመሩ ልዩነቶች እየዋሉ እያደሩ የዶግማ ልዩነት ሊያመጡ እንደማይችሉ እርግጠኛ መሆን አይቻልም፡፡ ከዚህ የከፋ ጉዳት ደግሞ ሊኖር አይችልምና ጉዳዩ በቀላሉ የሚታይ አይደለም፡፡
ሐ. ምዕመናን ይከፋፈላሉ፡- ከአብራከ መንፈስ ቅዱስ ከማየ ዮርዳኖስ የተወለዱ የአንዲት ቤተክርስቲያን ልጆች በአስተዳደር በተከፈለች ቤተክርስቲያን ምክንያት አነ ዘኬፋ ወአነዘ አጵሎስ እየተባሉ ይከፋፈላሉ፡፡  በመሆኑም የአንድ አገር ልጆች አንድነታቸው ይመነምናል፡፡ ለወግ ለማዕረግ ፤ ለትዳር የተጫጩ የማይፈልጉት ፈተና ውስጥ ይወድቃሉ፡፡
መ. ጥፋትን በጥፋት ይመልሳል፡- መጽሐፋችን “ክፉውን በበጎ ተቃወሙ” የሚል መርህ አስቀምጦልናል፡፡ ክፉውን በክፉ እንድንቃወም አልተፈቀደልንም፡፡ ከዚህ ቀደም የተጣሰ ቀኖና አለ፡፡ ጥፋቱ አሁን እንደምንሰማው የአንዱ ወገን ብቻ አይደለም፡፡ በሁለቱም በኩል የጠፋ እንጂ አንዱ ንጹህ ሌላኛው በደለኛ የሆነበት አይደለም፡፡ ያንን ጥፋት የምንክሰው ሌላ አነጋጋሪ  እና አጠያያቂ  ድርጊት ከመፈጸም ሳይሆን በሌላ ደረጃው ከፍ ባለ ምግባረ ሰናይ መሆን መቻል አለበት፡፡
“እግዚአብሔር ዓለምን ከፈጠረበት ይልቅ ያዳነበት ጥበቡ ይደንቃል” እንዲሉ አበው እኛም ከፊተኛው ይልቅ በሁለተኛው የበለጠ ልናደርግ ይጠበቅብናል፡፡  ባለፈው ያዘነውን ምዕመን በአሁኑ ልንክሰው ያስፈልጋል ፡፡ ይህን በማድረግ ፋንታ እዚህም እዚያም ጠንክሮ በመቅረት 6ተኛ ፓትርያርክ በመምረጥ ጥፋትን በጥፋት መመለስ እጅግ አደገኛ ይሆናል፡፡
እነዚህም ጥቅምና ጉዳቶች በማመዛዘን መሠረታዊ የቤተክርስቲያንን ችግር ለመፍታት የምንረባረብበት ወሳኝ ወቅት ላይ እንደመገኝታችን ውሳኔያችንንና ድርጊታችን ከስሜታዊ የጸዳ ፤ ለግለኝነትና ከእኔ ብቻ ልሰማ የተላቀቀ እንዲሆን ያስፈልጋል፡፡ አባቶች  ከራሳቸው ይልቅ ወንድሞቻቸውን የሚስቀድሙበት “ከእኔ ይልቅ ባልንጀራዬ” የሚለው መጽሐፍ ቅዱሳዊ ይትበሀል የሚተረጎምበት ወርቃማ ጊዜ ላይ ቆመናል፡፡
አባቶች ታሪክ ሰርቶ ታሪክ ሆኖ ለማለፍ ምቹ አጋጣም ከፊታቸው ይጠብቃቸዋል፡፡  እንደዚህ ያሉ መልካም ዕድሎች  የሚገኙት ከእልፍ አንድ ጊዜ ነው፡፡ በዘመነ ሰማዕታት ጊዜ ክርስቲያኖች ያ የሰማዕትነት እድል እንዳያልፋቸው ወደ መከራው ድግስ በጥብዐት እየዘለቁ በመግባት ታሪክ ሰርተዋል፡፡ በጣልያን ወረራ ወቅትም ከደብረ መዊ  ማርያም እስከ ደብረ ሊባኖስ ኅልቆ መሳፍርት የሌላቸው አበው የአባቶቻውን ታሪክ ደግመዋል፡፡ ዛሬ በሕይወት ስጋ ያሉ አባቶቻችንም የራሳቸውን ፈቃድ በመተው እና በመሰዋት ለቤተክርስቲያን የሚበጀውን ለማድረግ አስር ጊዜ አስበው አንድ ጊዜ ሊቆርጡ ይገባቸዋል፡፡
መቅደም ያለበት የቱ ነው?
አስር ጊዜ ተጠይቆ የማያወላውል መልስ የሚፈልገው ጉዳይ ይህ ነው ፡፡ ፓትርያርክ ለመምረጥ መሟላት የሚገባቸው ቅድመ ሁኔታዎች አሉ፡፡ ከእነዚህ መካከል የተወሰኑትን መመልከታችን ለጉዳዩ የሚኖረው ምልከታ ሊያቃናው ይችላል፡፡
1.    ፍቅርና አንድነት

ቅዱሳን ሐዋርያት ከመካከላቸው በጎደለው በይሁዳ ምትክ ማትያስን ከመተካታቸው በፊት ሁሉም በአንድ ልብ በአንድ ሀሳብ  ተስማምተው ያለመከፋፈል እና ያለመነጣጠል ይኖሩ እንደነበር ከግብረ ሐዋርያት  መረዳት ይቻላል፡፡ “እነዚህ ሁሉ ከሴቶችና ከኢየሱስ እናት ከማርያም ከወንድሞቹም ጋር በአንድ ልብ ሆነው ለጸሎት ይተጉ ነበር።  የሐዋርያት ሥራ 1፤14  ይህ አንድነታቸው እና ፍቅራቸው ሐዋርያው ማትያስን ከመረጡ በኋላም መቀጠሉ እንዲህ ተጽፏል፡፡ “በየቀኑም በአንድ ልብ ሆነው በመቅደስ እየተጉ በቤታቸውም እንጀራ እየቈረሱ፥ በደስታና በጥሩ ልብ ምግባቸውን ይመገቡ ነበር፤ እግዚአብሔርንም እያመሰገኑ በሕዝብ ሁሉ ፊት ሞገስ ነበራቸው። ጌታም የሚድኑትን ዕለት ዕለት በእነርሱ ላይ ይጨምር ነበር።” የሐዋርያት ሥራ 2፤46




ቅዱስ ሲኖዶስ የሚመራው በመንፈስ ቅዱስ  መሆኑ አንድና ሁለት የለውም፡፡ መንፈስ ቅዱስ ስንል ከሶስቱ አካል አንዱ ብቻውን ማለታችን ሳይሆን ከአብና ከወልድ  ጋር ማለታችን ነው፡፡ “ደግሞ እላችኋለሁ፥ ከእናንተ ሁለቱ በምድር በማናቸውም በሚለምኑት ነገር ሁሉ ቢስማሙ በሰማያት ካለው ከአባቴ ዘንድ ይደረግላቸዋል። ሁለት ወይም ሦስት በስሜ በሚሰበሰቡበት በዚያ በመካከላቸው እሆናለሁና። ” እንዲል ማቴዎስ 18 ፤ 19-20
ስለዚህ መንፈስ ቅዱስ በመካከል እንዲኖር የአባቶች መስማማት ቀዳሚ መሆኑን እናያለን፡፡  በተከፈለ ልብ ወይም ልዩነት ሆኖ መንፈስ ቅዱስ በመካከላችን ይገኛል ብሎ መገመት ይከብዳል፡፡ “አርነት መውጣታችሁን ለሥጋ ምክንያት አይስጥ”  እንዲል ሐዋርያው ቆም ብሎ በረጋ መንፈስ በሰከነ ስብእና ማሰብ ይገባል፡፡ የፈለገውን ለማድረግ አርነት የወጣን ቢሆንም ቅሉ ለስጋ ስሜታችን እያደላን መሆን እንደሌለበት ሐዋርያው መክሮናል፡፡
ከዚህ በመነሳት ፓትርያርክ መሰየምን ፍቅርና አንድነት ይቀድመዋል እንላለን፡፡ ስለሆነም አባቶቻችን ከሲመተ ፓትርያርክ በፊት በውጭ እና በውስጥ የተከፈለውን ሲኖዶስ በፍቅር የመፈወስ ስራን ሊያስቀድሙ ይገባል እንላለን፡፡
2.   በመባዕ በፊት ይቅርታ

በወንጌል ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ እንዳስተማረን አምሀ ይዞ በእግዚአብሔር ፊት ከመቅረብ በፊት ሊደረግ የሚገባ ምግባረ ሰናይ አለ፡፡ መባዕን ይዞ ወደ ቤተመቅደስ የሚመጣ ቢኖር ድንገት ግን በወንድሙ ላይ አንዳች ትዝ ቢለው መባውን ትቶ ወደ ወንድሙ ይሂድ ፡፡ እርሱንም ይቅርታ ይጠይቅ ፤ ከዚያም ተመልሶ መባውን ይስጥ ይላል፡፡ ከዚህ የምንረዳው ለእግዚአብሔር የምናቀርበው  ማናቸውም አምሃ ፤ መባዕ ፤ ጸሎትና ምስጋና ተቀባይነት የሚኖረው ከጀርባ ንጽህና ሲኖር ብቻ መሆኑን ነው፡፡
በዚህኛው ጉዳይ እግዚአብሔር ሁሉንም የሚያስምረው ከምርጫ በፊት እርቀ ሰላም ሲሰፍን መሆኑን እንገነዘባለን፡፡ የእኛ ክርስትና የሚያስተምረው ክርስትያኖች የሚበልጠውን እንዲያደርጉ ነው፡፡ ጌታችን ይህንን ብታደርጉ ምን ብልጫ አላችሁ ፡፡ አሕዛብስ እንዲህ ያደርጉ የለምን? ያለን በማንኛውም ዘርፍ ተሽለን መገኝት ስላለብን ነው፡፡ “የሚወዱአችሁን ብትወዱ ምን ዋጋ አላችሁ? ቀራጮችስ ያንኑ ያደርጉ የለምን ?” ማቴዎስ 5፤ 46 ፤ ተሽሎ መገኝት ደግሞ ከማንም ይልቅ ከአባቶች ይጠበቃል፡፡
3.   ተቀባይነትን (Legitimacy) ይሰፋል

እርቀ ሰላም ከተከናወነ በኋላ ሁሉም አባቶቻችን በጋራ መክረውና ዘክረው የሚወስኑት ውሳኔ የማያሳምነው ሰይጣንን ብቻ ነው፡፡ እኛን የናፈቀን እነዚህ የተራራቁ አባቶች በአንድነት ተቀምጠው ማየት ነው፡፡ “ናሁ ሰናይ ወናሁ አዳም ሶበ ይሄሉ አኃው ኅቡረ” (ወንድሞች በኅብረት ቢቀመጡ እነሆ ያማረ ነው) የሚለው ቃል ተግባራዊነት ለማየት እጅግ የጓጉ ምዕመናን ባሉበት ጊዜ በጋራ በአንድ ጽርሐ ሲኖዶስ ተሰይመው ለማየት ሁላችንም ናፍቀናል፡፡ በዚህ ሁኔታ አባቶች ተሰባስበው ቢፈልጉ አዲስ ፓትርያርክ ቢመርጡ ያለበለዚያ ሌላም አይነት አሰራር ቢያመጡ ወይም ቢደነግጉ ሁሉንም ወገን ያስማማል፡፡ ተቀባይነቱም ከአድማስ አድማስ ይሆናል፡፡ ሁላችንም በድለናል ከእኛ ማንም ንጹህ የለም ብለው ጀምረው በፍቅርና በእንባ ተራጭተው የትናንትናውን ትተው በአዲስ መንፈስ ጉዟቸውን ሲጀምሩ ሰልፋቸው ያማረ ውጤታቸው የሰመረ ይሆናል፡፡
አሁን በልዩነቱ እንዳሉ የሚወስኑት ውሳኔ ግን ተቀባይነቱ በጠባብ ወሰን (Narrow jurisdiction) ላይ የተንጠለጠለ ይሆናል፡፡ ይህም ከተቀባይነቱ ይልቅ ተቃውሞን ይጋብዛል፡፡ የገበያ ግርግር ለሌባ ያመቻል እንዲሉ፡፡ ይህንን የተሰበሰበ ግርማ ሞገስ የተላበሰ ቅዱስ ሲኖዶስ ላለማየት ቀንና ለሊት ለሚተጉ ጠላቶቻችንም የበለጠ የተደላደለ መንገድ ይነጠፍላቸዋል፡፡ የተበተነው አንድነት ተመልሶ  የሚሰራው ስራ ጠላትን ከማድከሙ በላይ  የተቀባይቱ መሰረት እጅግ ሰፊ በመሆኑ ለቤተክርስቲያን ይበጃል ፡፡ የሚሰማ ፤ የሚደመጥ በስልጣኑ የሚሰራ ቅዱስ ሲኖዶስ እጅግ ያስፈልጋታል፡፡ ቤተክርስቲያን መወሰን ማድረግና ማዘዝ የሚችል ሲኖዶስ ሊኖራት የሚችለው እርቀ ሰላሙ ሲከናወን ነው፡፡ ይህ ሳይሆን የቀረ እንደሆነ ግን ተሰሚነቱ የመነመነ ፤ ተቃውሞ የበዛበት ፤ እዚህም እዚያም የተበታተነ ከአንድነቱ ይልቅ መለያየትን የሚሰብክ ቁመና ይላበሳል፡፡ ይህ ደግሞ ተቀባይነቱን በእጅጉ ይሸረሽረዋል፡፡
4.    ያላደረጉትን አድርጉ ማለት ይቸግራል

መጽሐፍ “አንተ ሌላውን የምታስተምር ራስህን አታስተምርምን ? ሌላውን አትስረቅ የምትል ትሰርቃለህን ? እንዲል ሌሎችን ታረቁ ለማለት አባቶች መታረቅን ማስቀደም አለባቸው፡፡ አሠረ ፍኖታቸውን የምንከተላቸው ቅዱሳን በሄዱበት መንገድ መጓዝ ይጠበቅብናል፡፡ መጽሐፍ ያለውን ብቻ መናገር ፈሪሳዊነት ነው፡፡ እነርሱ የመጽሐፉን ቃል ያዝዛሉ እንጂ አያደርጉትምና፡፡
እኛ ክርስትያኖች ደግሞ ሕገ ወንጌልን በተግባር ለመተርም የምንወጣ የምንወርድ ነን እንጂ በቃላችን ብቻ እያነበነብን የምናሙለጨልጨ አይደለንም፡፡ ሲመቸን የእግዚአብሔርን ቃል እየጠቀስን ለአፍ ጅምናስቲክ ብቻ የምናውል ልንሆን አልተጠራንም፡፡ በመሆኑም አርአያ የመሆን ኃላፊነታችን ከፍ ይላል፡ ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ የመንፈስ ልጆቹን ደጋግሞ ያስጠነቀቃቸው ምሳሌ የሚሆን ራሳቸውን በተግባር እንዲያሳዩ መሆኑን ከመልዕክቱ እንረዳለን፡፡ ዛሬ ያሉ ብጹዓን አባቶቻችንም መታረቅ ከምንም በላይ በማስቀደም ሌላውን ታረቁ ብለው ለመምከር ያላቸው የሞራል ልዕልና ሊያስመሰክሩ ይገባቸዋል፡፡ በመሆኑም ከሲመት በፊት እርቅ መቅደሙ ግዴታ ይሆናል፡፡
5.   አርአያ ክርስቶስን መከተል

ጌታችን መድኃኒታችን እየሱስ ክርስቶስ  ከመንበረ ጸባኦት (ከየማ አብ ከዘባነ ኪሩብ) እስከ መስቀል ሞት የተጓዘው እርቅ ለመፈጸም መሆኑ አይጠረጠርም፡፡ በልደቱ የተዘመረው “ስብሐት ለእግዚአብሔር በሰማያት ወሰላም በምድር  ስምረቱ - ለእግዚአብሔር በሰማያት ወሰላም  በምድር  ስምረቱ ለሰብእ - ምስጋና ለእግዚአብሔር በሰማይ ለሰውም በጎ ፍቃድ ሰላምም ሆነ በምድር” የሚለው የተጠናቀቀው “ገብረ ሰላም በደመ መስቀሉ  - በመስቀሉ ደም ሰላም አደረገ” ተብሎ ነው፡፡ ከቤተልሔም እስከ ቀራንዮ የተከፈለው መስዋዕትነት ለሰላም ነው፡፡ የደቀ መዛሙርቱን እግር ካጠበ በኋላ “እናንተም እንዲሁ ታደርጉ ዘንድ” በማለት ያደረገውን ሁሉ እንድንከተል  ደግሞ “ምሳሌ ሰጥቻችኋለሁ” ሲል አስረድቶናል፡፡ ዮሐንስ 13፤15 ፡፡ በመሆኑም የእርቀ ሰላምን  መንገድ በመከተል አርአያ ክርስቶስን መከተል ያስፈልጋል፡፡ ጌታችን እኛን ለማስታረቅ ምንም አይነት ቅድመ ሁኔታ እንዳላስቀመጠ ሁላ እኛም ያለምንም  ቅድመ ሁኔታ የሁለቱን ሲኖዶስ አንድነት ለመመለስ የሚከፈለውን ሁሉ ለመክፈል መዘጋጀት አለብን፡፡

በመጨረሻም
እርቀ ሰላሙን መፈጸም ለፓትርያርክ ምርጫው መንገድ ጠራጊ ነው፡፡ ስለሆነም ወደ መንበራቸው እንመልስ የሚለው ሆነ ስድስተኛው ፓትርያርክ እንምረጥ  የሚለውን ሃሳብ በመተው እርቀ ሰላሙን ለመፈጸም ብቻ መነጋገር ያስፈልጋል፡፡ በሕይወት ያሉት የብጹእ ወቅዱስ  አቡነ መርቆርዮስም ጉዳይ መታየት ያለበት በቅድመ ሁኔታነት  ሳይሆን ከእርቀ ሰላም በኋላ  በተሰየመ ጉባኤ መሆን ይገባዋል፡፡ እርሳቸውም አንዱ የጉባኤ ተሳታፊ የሚሆኑበት ያ መድረክ  ይዞት የሚመጣው መፍትሔ ለቤተክርስቲያን የሚበጅ ይሆናል ተብሎ ይጠበቃል፡፡  ወይ ሁሉም “ይደልዎ” ይሏቸዋል ፤ ወይ ራሳቸው በቡራኬ መወሰኑን እና በሕይወተ ስጋ እስካሉ ድረስ አስተዳደሩን በሙሉ እንደራሴ ተሾሞ ይመራ ይሉ ይሆናል፡፡  ወይ ሌላ የጋራ ግን የሚጠቅም ውሳኔ ይመጣ ይሆናል፡፡ በራችንን ከፍተን እግዚአብሔር ያመጣልንን ለመቀበል መጠበቅ ይኖርብናል፡፡ አንቀጿ (በሯ) ጠባብ ብትሆንም ከመግባት አትከለክልምና በዚች በር እንግባ፡፡ የምርጫ ሕግ መዘጋጀቱ የግድ መምረጥ አለብን የሚል ትርጓሜ አይሰጥም፡፡ መሠራቱ ለነገ ይበጃልና ይሰራ ፤ ግን አሁን ለመምረጥ አይሁን ፡፡
ቸር ያሰማን
“አንድ አድርገን

ጌታ ሆይ

አንድ አድርገን  … .”

8 comments:

  1. አንድ አድርገኖች እግዚአብሔር ይባርካችሁ ፡፡ ድንቅ መልዕክት

    ReplyDelete
  2. Nicely articulated! I like the ending paragraph,

    አንቀጿ (በሯ) ጠባብ ብትሆንም ከመግባት አትከለክልምና በዚች በር እንግባ፡፡ የምርጫ ሕግ መዘጋጀቱ የግድ መምረጥ አለብን የሚል ትርጓሜ አይሰጥም፡፡ መሠራቱ ለነገ ይበጃልና ይሰራ ፤ ግን አሁን ለመምረጥ አይሁን ፡፡

    ReplyDelete
  3. አንድ አድርገን

    ReplyDelete
    Replies
    1. ወንጌል ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ እንዳስተማረን አምሀ ይዞ በእግዚአብሔር ፊት ከመቅረብ በፊት ሊደረግ የሚገባ ምግባረ ሰናይ አለ፡፡ መባዕን ይዞ ወደ ቤተመቅደስ የሚመጣ ቢኖር ድንገት ግን በወንድሙ ላይ አንዳች ትዝ ቢለው መባውን ትቶ ወደ ወንድሙ ይሂድ ፡፡ እርሱንም ይቅርታ ይጠይቅ ፤ ከዚያም ተመልሶ መባውን ይስጥ ይላል፡፡ ከዚህ የምንረዳው ለእግዚአብሔር የምናቀርበው ማናቸውም አምሃ ፤ መባዕ ፤ ጸሎትና ምስጋና ተቀባይነት የሚኖረው ከጀርባ ንጽህና ሲኖር ብቻ መሆኑን ነው፡፡

      Delete
    2. ጽሐፍ “አንተ ሌላውን የምታስተምር ራስህን አታስተምርምን ? ሌላውን አትስረቅ የምትል ትሰርቃለህን ? እንዲል ሌሎችን ታረቁ ለማለት አባቶች መታረቅን ማስቀደም አለባቸው፡፡ አሠረ ፍኖታቸውን የምንከተላቸው ቅዱሳን በሄዱበት መንገድ መጓዝ ይጠበቅብናል፡፡ መጽሐፍ ያለውን ብቻ መናገር ፈሪሳዊነት ነው፡፡ እነርሱ የመጽሐፉን ቃል ያዝዛሉ እንጂ አያደርጉትምና፡፡

      Delete
  4. ወንጌል ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ እንዳስተማረን አምሀ ይዞ በእግዚአብሔር ፊት ከመቅረብ በፊት ሊደረግ የሚገባ ምግባረ ሰናይ አለ፡፡ መባዕን ይዞ ወደ ቤተመቅደስ የሚመጣ ቢኖር ድንገት ግን በወንድሙ ላይ አንዳች ትዝ ቢለው መባውን ትቶ ወደ ወንድሙ ይሂድ ፡፡ እርሱንም ይቅርታ ይጠይቅ ፤ ከዚያም ተመልሶ መባውን ይስጥ ይላል፡፡ ከዚህ የምንረዳው ለእግዚአብሔር የምናቀርበው ማናቸውም አምሃ ፤ መባዕ ፤ ጸሎትና ምስጋና ተቀባይነት የሚኖረው ከጀርባ ንጽህና ሲኖር ብቻ መሆኑን ነው፡፡

    ReplyDelete
  5. ወንጌል ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ እንዳስተማረን አምሀ ይዞ በእግዚአብሔር ፊት ከመቅረብ በፊት ሊደረግ የሚገባ ምግባረ ሰናይ አለ፡፡ መባዕን ይዞ ወደ ቤተመቅደስ የሚመጣ ቢኖር ድንገት ግን በወንድሙ ላይ አንዳች ትዝ ቢለው መባውን ትቶ ወደ ወንድሙ ይሂድ ፡፡ እርሱንም ይቅርታ ይጠይቅ ፤ ከዚያም ተመልሶ መባውን ይስጥ ይላል፡፡ ከዚህ የምንረዳው ለእግዚአብሔር የምናቀርበው ማናቸውም አምሃ ፤ መባዕ ፤ ጸሎትና ምስጋና ተቀባይነት የሚኖረው ከጀርባ ንጽህና ሲኖር ብቻ መሆኑን ነው፡፡

    ReplyDelete
  6. This is a good holy message that provides spiritual thrust of all followers of
    christ in relation to the existing debatable issue that has formed two campus
    inside and outside Ethiopia.we all want to learn more if men of God like D.
    Abaineh helps us learn by feeding us the truth relating it to the rules of the
    synodos.some may dislike the unity and may exert utmost effort to be stumbling
    block for the reconcilation.however,truth never dies before it kills its enemies .
    So,we should unite our hears but not our tongues.

    ReplyDelete