(አንድ አድርገን ታህሳስ 23 2005 ዓ.ም)፡- የእርቀ ሰላሙ ኮሚቴዎች እርቁ ዳር እንዲደርስ ጊዜያቸውንና ጉልበታቸውን
በመሰዋት ከፍተኛ እንቅስቃሴ እያደረጉ መሆኑ ይታወቃል ፤ ቤተክርስቲያን ከነበረችበት መከፋፈል ወደ አንድ እንድትመጣ በሁለቱም ሲኖዶሶች
መካከል በመሆን የንግግር መንፈሱ እንዲጀመርና በአባቶች መካከል ያለው ያለመነጋገር እና ያለመወያት መንፈስ እንዲርቅ አድርገዋል፡፡
ከቀናት በፊት ከአሜሪካ የእርቀ ሰላም ኮሚቴውን በመወከል አዲስ አበባ
የመጡት ሊቀ ካህናት ኃ/ሥላሴ አለማየሁ በመንግስት የደህንነት ሰዎች አማካኝነት ወደ መጡበት እንዲመለሱ ተደርጓል ፡፡ ከቀናት በፊት
የፌደራል ጉዳዮች የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ ለፋና ብሮድካስት በሰጡት አስተያየት “መንግሥት በኦርቶዶክስ ተዋህዶ ፓትርያርክ ምርጫ
እና እርቀ ሰላሙ ላይ እጁን አላስገባል ፤ በየ ድረ-ገፅ የሚወራው ወሬ ሀሰት ነው ፤ ሕገ መንግሥቱ መንግሥትና እምነትን ስላለያየ
መንግስት በእምነቶች ላይ ጣልቃ አይገባል” በማለት ተናግረዋል ፡፡ የቅዱስ ሲኖዶስ ጸሀፊም “መንግስት በመካከላችን ጣልቃ አልገባም ፤ ጭራሹን አልደረሰብንም ፤ የሚወራው ወሬ ሀሰት ነው” በማለት
አስረድተዋል፡፡ አቡነ ሕዝቅኤል ለእርቀ ሰላም የመጡት አባት በማን አማካኝነት
ከሀገር እንዲወጡ ስለመደረጉ ተጠይቀው ለአሜሪካ ድምጽ በሰጡት መልስ “ መምጣታቸውን እናውቃለን ፤ በአካልም አግኝቼ አናግሬአቸው
ነበር ፤ በምን ምክንያት እንደተመለሱ ግን የማውቀው ነገር የለም ፤ ነገ ስለምንሰበሰብ ቅዱስ ሲኖዶስ ይነጋገርበት ይሆናል” ብለዋል፡፡
አሁን ግን እየተደረገ እና እየተወራ ያለው ነገር ምዕመኑን ይባስ ግራ መጋባት ውስጥ እየከተተው ይገኛል፡፡ አባቶቻችን
መንግስት ጣልቃ አልገባም ብለው በአደባባይ ሲናገሩ ፤ መንግስት ደግሞ ለእርቀ ሰላሙ የመጡትን አባት ወደ መጡበት ወደ አሜሪካ እንዲመለሱ
ቲኬት ቆርጦ እንደሰጣቸው ለማወቅ ተችሏል፡፡ መንግሥት
የቀጣይ ፓትርያርኩን ምርጫ በቅርበት ሆኖ የሚከታተል ኮሚቴ በፌደራል ጉዳዮች ሚኒስቴር አማካኝነት እንዳቋቋመ ከወር በፊት መጻፋችን
ይታወቃል፡፡ ( ይህን ይጫኑ )አሁን በግልጽ እየታየ ያለው ነገር ቢኖር መንግሥት ከአሜሪካ በሚመጡት አባቶች ወይም
በእርቀ ሰላሙ ላይ ፍላጎት እንደሌለው ነው ፤ ይህ የእርቀ ሰላም ጉዳይ ያለ መንግሥት መልካም ፍቃድ ጫፍ የማይደርስበት ሁኔታ እየተስተዋለ
ነው ፤ የውጭ ጫናዎች እንዳሉ ሆነው አባቶች ያላቸውን አቅም አሰባስበው
የውስጥ ስምምነታቸውን አጠንክረው በአንድ አቋም እና በአንድ
ሀሳብ ለቤተክርስቲያኒቱ የተሻለው ሁሉ ቢያደርጉ መልካም ነው እንላለን፡፡ እድሜም ይገፋል ፤ ስልጣንም ያልፋል ፤ ሞትም ይፈጥናል ትውልድ ግን ይቀጥላል ፤ በትውልዱ የምትወቀሱበት ስራ እንዳትሰሩ እግዚአብሔር
ይርዳችሁ፡፡
No comments:
Post a Comment