(የዮሐንስ ወንጌል ሁለተኛ ሳምንት )!!
“በመጀመሪያው ቃል ነበረ፥ ቃልም በእግዚአብሔር ዘንድ ነበረ፥ ቃልም እግዚአብሔር ነበረ።ይህ በመጀመሪያው በእግዚአብሔር ዘንድ ነበረ።” ዮሐ.1፡1-2
ዓሣ አጥማጁ ሐዋርያ ጌታ ከእመቤታችን ከቅድስት ድንግል ማርያም የተወለደውን ደኃራዊ ልደቱ በሌሎች ወንጌላውያን የተነገረ ስለሆነ ቀዳማዊ ልደቱን ይነግረን ዘንድ ይቻኰላል /ቅ.ዮሐንስ አፈወርቅ/፡፡ በእርግጥም “የድንግል ማርያም ልጅ” ብሎ የሚያቆም ካለ እኛ እርሱን አንሰማውም፤ “በመጀመሪያው ቃል ነበረ፥ ቃልም በእግዚአብሔር ዘንድ ነበረ” ሊለንም ይገባዋል እንጂ /ሄላሬዎስ/፡፡ አንዳንድ ሰዎች “ወልድ ልጅ ሆኖ ሳለ እንዴት ከአባቱ አያንስም?” ብለው ይጠይቁናል፡፡ እኛም የማይመረመር መሆኑንና የነብዩን ቃል ጠቅሰን እንዲህ ብለን እንመልስላቸዋለን፡- “መኑ ይነግር ልደቶ- ከአብ ያለ እናት የተወለደበት ቀዳማዊ ልደቱን ማን ይናገራል? እንዴትስ ሊመረመር ይችላል? እኛ፡ አብ ለልጁ አባት ሲባል አገኘነው እንጂ እንደምን እንደወለደው አናውቅም” /ኢሳ.53፡9፣ አውግስጢኖስ፣ አባ ጊዮርጊስ ዘጋሥጫ/፡፡ ሐዋርያው “በመጀመርያው” ብሎ ሲነግረንም ከእርሱ በፊት ማንም እንዳልነበረ ለመግለጽ ነውና /ቅ.ቄርሎስ/፡፡ ምንም እንኳን “በመጀመርያ” የሚለው አገላለጽ በመጽሐፍ ቅዱስ የተለያየ ትርጕም ቢኖረውም አሁን ወንጌላዊው እየነገረን ያለው ግን ቀዳማዊ ቃል ተራሮች ሳይወለዱ፥ ምድርም ዓለምም ሳይሠሩ፥ ከዘላለም አንሥቶ እንደ ነበረ ነው /መዝ.90፡2፣ አርጌንስ/፡፡ ዮሐንስ “በመጀመርያው” የሚል ደካማ አገላለጽ ከመጠቀም ውጪ ሌላ የተሻለ ቋንቋ ማግኘት አልቻለም /ቅ.ቄርሎስ/፡፡
ሊቀ ነብያት ሙሴ “በቀዳሚ ገብረ እግዚአብሔር ሰማየ ወምድረ- በመጀመርያ እግዚአብሔር ሰማይንና ምድርን ፈጠረ” ካለው ጋር ንባብ ቢያሳብረውም ምሥጢር አያሳብረውም፡፡ ነብዩ “በቀዳሚ ዕለት፣ በቀዳሚ ሰዓት ሰማይና ምድር ተፈጠሩ” እያለን ነው፡፡ ይህም ማለት ለእነዚህ ፍጥረታት በዕለተ እሑድ መነሻ፣ መጀመርያ አላቸው፤ ቀዳማዊ ቃል ወልደ እግዚአብሔር ግን ለዘመኑ ጥንት፣ መነሻ፣ መጀመርያ ለሕይወቱም ፍጻሜ የለውም፤ እርሱ አልፋና ኦሜጋ ነው /ዕብ.7፡3፣ ራዕ.22፡13፣ ቴዎዶር ዘሜውፕሳስትያ/፡፡ ለዚህም ነው ሐዋርያው “ቃልም በእግዚአብሔር ዘንድ ነበረ” በማለት ለዓይን ጥቅሻ ታህል ቅጽበት እንኳን የባሕርይ አባቱ የባሕርይ ልጁን በዘመን እንደማይቀድመው የነገረን /ቅ.ቄርሎስ፣ አባ ጊዮርጊስ ዘጋሥጫ/፡፡ መሴም ቢሆን “በመጀመርያ እግዚአብሔር ሰማይንና ምድርን ፈጠረ” አለን እንጂ (ሎቱ ስብሐትና) “ወልድን ፈጠረ” አላለንም /ዘፍ.1፡1/፡፡ አካለዊ ቃል ወልድማ ሁሉንም የፈጠረ እግዚአብሔር ነው /ቆላ.1፡16/፡፡ የማያምኑበት ባያምኑበትም እኛስ ሙሴ ስለ እርሱ የጻፈለትን ቀዳማዊ ቃል ያህዌ-Johovah እንደ ሆነ እናምናለን /ዮሐ.5፡46፣ ዮሐ.8፡25፣ አውግስጢኖስ/፡፡
ይህ የተሰወረባቸው ሰዎች የማይቀላቀለውን ሲቀላቅሉ “ነበረ” እና “ተፈጠረ” አንድ ነው ሊሉን ይሞክራሉ፡፡ ነገር ግን “ነበረ” የሚለው አገላለጽ ለሰዎች ሲቀጸል ኃላፊ ጊዜን የሚያመለክት ሲሆን ለእግዚአብሔር ሲቀጸል ግን ዘላለማዊነትን የሚያለመክት መሆኑን እንነግራቸዋለን፡፡ ምክንያቱም እግዚአብሔር ከጊዜና ከቦታ ቀመር ውጪ ነውና /ቅ.ዮሐንስ አፈወርቅ/፡፡ ይህንንም የምናውቀው ሐዋርያው “በመጀመሪያው ቃል ነበረ” እያለን መልሶ ደግሞ “ቃልም በእግዚአብሔር ዘንድ ነበረ፤ ቃልም ራሱ እግዚአብሔር ነበረ” ስለሚለን ነው /አርጌንስ/፡፡
ወንጌላዊው እየነገረን ያለው ዓይነት “ቃል” እኛ እንደምንናገረው ዓይነቱ ዝርው (ብትን) ቃል ሳይሆን አካል ያለውን ቃል ነው /ቅ.አግናጥዮስ ምጥው ለአንበሳ/፡፡ የእኛ ቃል ወዲያው እንደተናገርነው ወደ አለመኖር ይለወጣል፤ አካላዊ ቃል ወልደ እግዚአብሔር ግን ሁሌ ያው ነው፤ አይለወጥም /ሚል.3፡6፣ ቅ.አትናቴዎስ/፡፡ የእኛ ዝርው ቃል ከልብ ተገኝቶ ህልው ሆኖ ሲኖር አማርኛም ይሁን ትግርኛ አይታወቅም፡፡ ነገር ግን ልገለጽ ባለ ጊዜ በአንደበት እንደሚገለጽ ሁሉ አካላዊ ቃል ወልድም ከአብ ተገኝቶ በአብ ህልው ሆኖ ሲኖር ልገለጽ ባለ ጊዜ በሥጋ ተገልጧል /ዮሐ.14፡9፣ ገላ.4፡4፣ ቅ.ኤፍሬም/፡፡ እግዚአብሔር ወልድ ከዘላለም አንሥቶ ከባሕርይ አባቱ ጋር አለ /ቅ.ጐርጐርዮስ ዘእንዚናዙ/፤ ነገር ግን አሁን እየተመለከትን ያለነው በሥልጣን ሳይሆን በአካል ከአባቱ የተለየ መሆኑን ነው /ቅ.ቄርሎስ/፡፡
እንዴት ይደንቃል?! ሙሴ በጊዜ ውስጥ ተወስኖ ይጽፋል፤ ይህ ዓሣ አጥማጅ ሐዋርያ ግን ከምናየው ሰማይና ምድር ያልፍና በደቂቃና በሴኮንድ ወደማይቆጠረው ዘላለማዊነት ያስገባናል፤ ሙሴ ከነገረን መጀመርያ አስወጥቶም መጀመርያ ወደሌለው መጀመርያ ይወስደናል /ሄላሬዎስ/፡፡ ወደዚያ ስንሄድም አካላዊ ቃል አምላክ ወልደ አምላክ፣ ከብርሃን የተገኘ ብርሃን፣ ከጥበብ የተገኘ ጥበብ፣ ከእውነት የተገኘ እውነት፣ ከማይቸገር የተገኘ የማይቸገር፣ ከማይጠፋ የተገኘ የማይጠፋ፣ ከማይፈርስ የተወለደ የማያረጅ፣ ከማያንቀላፋ የተገኘ የማይተኛ፣ ከማይጨልም የተገኘ የማይጠቁር፣ ከማይመረመር የተወለደ የማይለይ፣ ድካም ከሌለበት የተወለደ የማይደክም፣ ከማይበቀል የተወለደ የማይቀየም፣ ከማይጐድል የተወለደ የማይጐድል፣ ከማያድፍ የተገኘ የማይረክስ መሆኑን እንረዳለን /አባ ጊዮርጊስ ዘጋሥጫ/፡፡ ይህ ምን ማለት እንደ ሆነ ግን በእኛ ደካማ ቃላት መግለጽ አይቻለንም /አውግስጢኖስ/፡፡ የምናውቀው ሁሉ በከፊል ነውና /1ቆሮ.13፡12/፡፡ በእምነት መሠላል ብቻ ወደዚህ እንደርሳለን /ቅ.ጐርጐርዮስ ዘኑሲስ/፡፡
“ሁሉ በእርሱ ሆነ፥ ከሆነውም አንዳች ስንኳ ያለ እርሱ አልሆነም። በእርሱ ሕይወት ነበረች፥ ሕይወትም የሰው ብርሃን ነበረች። ብርሃንም በጨለማ ይበራል፥ ጨለማም አላሸነፈውም።” ዮሐ.1፡3-5
አዎ! የወንጌላዊው ዓላማ ሥነ-ፍጥረትን ሳይሆን የየሥነ-ፍጥረት ሁሉ ምንጭ ማን እንደሆነ ማስተዋወቅ ነው፡፡ እነዚህ ፍጥረታት ከመፈጠራቸው በፊት አልነበሩም፤ እርሱ ግን ከዘላለም አንሥቶ በእግዚአብሔር ዘንድ አለ /ዘጸ.3፡14፣ ቴዎዶር ዘሜውፕሳስትያ/፡፡ ሁሉንም የፈጠረ ፈጣሪ “ፍጡር ነው” ይሉት ዘንድ አንዳንዶች እንዴት ደፈሩ?! /አውግስጢኖስ/፡፡ ወልድ ፍጡር ከሆነስ ከእርሱ በፊት የነበረችውን ጊዜ ማን ሊፈጥራት ነው? ወንጌላዊው ግን “ከተፈጠረውም አንዳች ስንኳ ያለ እርሱ የተፈጠረ የለም” ነው ያለን፡፡ በአመክንዮም (By Logic) ሸክላ ከሸክላ ሠሪው አይቀድምም /ዕብ.1፡8፣ ቅ.ዮሐንስ አፈወርቅ/፡፡
አንድ ነገር ግን ታስተውሉ ዘንድ እንማልዳችኋለን፡፡ ወንጌላዊው፡-“ሁሉ በእርሱ ተፈጠረ፥ ከተፈጠረውም አንዳች ስንኳ ያለ እርሱ አልተፈጠረም” ስላለ ጣዖት፣ ኃጢአትና ክፋት ሁሉ በእግዚአብሔር ተፈጠሩ ማለት አይደለም /አርጌንስ/፡፡ ምክንያቱም እነዚህ ሁሉ የኃጢአት ውጤቶች ናቸውና /ቅ.አትናቴዎስ/፡፡ ስለዚህ ፈጣሬ ዓለማት አካላዊ ቃልን ማመን ሕይወትን ይሰጣል /አርጌንስ/፡፡ አዎ! እርሱ ከሕይወት የተገኘ የሕይወት ሁሉ ምንጭ ነው /ቅ.ዮሐንስ አፈወርቅ/፤ ከእውነት የተገኘ እውነት እንጂ እውነትን ቆይቶ የተማረ ፍጡር አይደለም /ሄላሬዎስ/፡፡ እርሱ፡ ሲሞት እንኳን ሕይወትን የሚሰጥ ዕፀ ሕይወት ነው /አውግስጢኖስ/፡፡ ዕፀ ሕይወቱም እንበላው ዘንድ አደለን፤ ይኸውም እኛን ስለ መውደድ መጥቶ ያዳነን ቅዱስ ሥጋውና ክቡር ደሙ ነው /ቅ.ኤፍሬም/፤ በበላነው ጊዜም ክፋንና ደጉን የምናውቅበት ዕውቀትን አገኘን /አርጌንስ/፡፡
እርሱ ብርሃን ብቻ ሳይሆን ብርሃን ሰጪም ነውና /ቅ.ቄርሎስ/ በአካላዊ ቃል ሞትና ትንሣኤ ብርሃን ወጣልን /ቅ.ዮሐንስ አፈወርቅ/፡፡ ዐይነ ስውር የሆነ ሰው (የማያምን) ፀሐይ ብትኖርም እርሱ ስለማያያት እስከ አሁን ድረስ በጨለማ ውስጥ አለ /አውግስጢኖስ/፡፡ እኛም ቅዱስ ጳውሎስ እንደነገረን ቀድሞ ጨለማ ነበርን፥ አሁን ግን በጌታ ብርሃን ነን /ኤፌ.5፡8፣ አርጌንስ/፡፡ ስለዚህ ከእንግዲህ ወዲህ “ወልድ ፍጡር ነው” ከሚሉት ጋር በጨለማ ውስጥ አንኖርንም፡፡ አካላዊ ቃልን ስናምን ጨለማ ከእኛ ተገፎ ይጠፋል፤ ሞት ከእኛ ይርቃል፣ ክህደት ከእኛ ይወገዳል፤ በአማናዊው ብርሃን ተሸንፏልና ሞት በእኛ ላይ ድል የሚያደርግበትን ሥልጣን ያጣል /1ቆሮ.15፡55-57፣ ቅ.ማር ይስሐቅ፣ ቅ.ጐርጐርዮስ ዘእንዚናዙ፣ ቅ.ቄርሎስ/፡፡
እንግዲያስ ተወዳጆች ሆይ! ይህ አካላዊ ቃል፣ ከዘላለም አንሥቶ ከአባቱ ጋር የነበረው ወልድ፣ ከጊዜና ከቦታ ከመታየትም ውጪ የሆነው አምላክ፣ አሁን ስለ እኛ ብሎ የእኛን ሥጋ ለብሶ ስለ ታየ፤ ልዑል ሲሆን ዝቅ ስለ አለ፤ ያድነንም ዘንድ በጊዜና ቦታ ተወስኖ ስለ መጣ፤ ከፀሐይና ከጨረቃ አቆጣጠር ውጪ ሆነን ከእርሱ ጋር ለዘላለም እንኖር ዘንድ ዘመን ስለ ተቆጠረለት በእርሱ ዘንድ ጽርፈትን (ስድብን) ከመናገር እንቆጠብ /ቅ.ቄርሎስ/፡፡
ሰላም ወሰናይ! (በሦስተኛው ጥናት እንገናኝ!)
(አዘጋጅ፡- ገብረ እግዚአብሔር ኪደ)
egzabhar ystelen
ReplyDelete