Monday, April 1, 2013

‹‹ሃይማኖቱን ጠልተው መቃብሩን መናፈቅ አያስኬድም›› አቡነ ገብርኤል


(አንድ አድርገን መጋቢት 23 2005 ዓ.ም)፡- አቡነ ገብርኤል ከ14 ዓመት በፊት ከጦቢያ ጋዜጣ ጋር ያደረጉትን ቃለ መጠይቅ ስለ ተሃድሶያውያን ፤ በወቅቱ ስለተነሱ መናፍቃን ፤ ስለኢትዮጵያ እና ኤርትራ ሁኔታ ፤ የኤርትራ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን እንዴት ከእናት ቤተክርስቲያ ተለይታ ራሷን እንደቻለች ፤ በወቅቱ ሲያስተዳድሩ ስለነበረው ስለ ኢየሩሳሌም ገደማት እና ሌሎች ጉዳዮች ብፅዕ አቡነ ገብርኤል ያስቃኙናል፡፡ ሙሉውን በPdf ያንብቡ

ከቃለ መጠይቁ የተወሰደ
በመንግሥት ለውጥ ጊዜ
ደርግም አለፈ ፤ ኢህአዴግም ተተካ፡፡ ኢህአዴግ ከአቡነ መርቆሪዮስ ጋር አብሬ አልሰራም አለ፡፡ ኢህአዴግ በግንቦት ወር 1983 ዓ.ም ሥልጣን ከያዘ በኋላ በሐምሌ ወር ወደ 22 የሲኖዶስ ሊቃነ ጳጳሳት ከከፍተኛ ባለስልጣናት ጋር ጉባኤ አድርገን ነበር፡፡ ያንን ጉባኤ የመሩት አሁን በእስር ላይ የሚገኙት የቀድሞ ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ ታምራት ላይኔ ነበሩ፡፡ እሳቸው በወቅቱ አቡነ መርቆሪዮስ ከደርግ ጋር የወገኑ ብዙ ገንዘብም የሰጡ እና ዓላማቸውን የሳቱ አባት ስለሆኑ በምንም አይነት ከእሳቸው ጋር አንሰራም” ነበር ያሉት፡፡ በዚህ ምክንያት እሳቸው እስኪወርዱ ድረስ  ለጳጳሳቱ ደመወዝ ፤ ለቤተ ክርስቲያኒቱ የስራ ማስኬጃና  ለሠራተኛው ደመወዝ እንዲሆን ከመንግሥት ይሰጥ የነበረው በጀት እንዲቆም ተደረገ፡፡ ከዚያ በኋላ ደግሞ በየቦታው እሳቸውን የሚቃወም ሰላማዊ ሰልፍ ተደረገ፡፡ ፓትርያርኩ እስከ መጨረሻው ድረስ እንደ አቡነ ቴዎፍሎስ ተጎትተው አልወረዱም፡፡ ራሳቸው በገዛ ፈቃዳቸው ይቅርብኝ ብለው ሥልጣናቸውን ተዉ፡፡የወር ደመወዝ እየተቀበሉ ፤ መኪናም ተመድቦላቸው ብሥራተ ገብርኤል አካባቢ እንዲቀመጡ ተደረገ፡፡


የኤርትራ ቤተ ክርስቲያን በተለየችበት ጊዜ
የግብጽ ፓትርያርክ አቡነ ሺኖዳ ከመጀመሪያ ጀምሮ የሚወስዱት ርምጃ ሁሉ አፍራሽ ነው፡፡ በመጀመሪያ ከአስመራ መነኮሳትን ጋብዘው ጳጳሳት ብለው ሾሙ፡፡ ለምን ሾሙ? ብለን ስንጠይቃቸው ‹‹በውጭ ሀገር ለሚገኙ ኤርትራውያን ነው›› ብለው ምክንያት ሰጡ ፡፡ እሳቸው ጳጳሳት ብለው የሾሟቸው መነኮሳት ያመነኮስናቸው እኛ ስለሆንን የእኛ አይደሉም ወይ? ስንላቸው ደግሞ ‹‹እናንተስ የእኔ አይደላችሁም ወይ ?›› የሚል መልስ ሰጡ፡፡ በእኩልነት ላይ በተመሰረተ ግንኙነት እንጂ እኛ ከ1951 ዓ.ም ጀምሮ የራሳችንን ፓትርያርክ እየሾምን ያለን ፤ ራሳችንን የቻልን ነን ብለን ተከራከርን፡፡ ይህ ጭቅጭቅ እያለ ይግረማችሁ ብለው በማን አለብኝነት ሌሎች መነኮሳትን ጠርተው የጳጳስነት ማዕረግ ሰጡ፡፡ ፓትርያርክም ሾሙ፡፡ ፓትርያርኩ ይህን በማድረጋቸው በኤርትራ ለተፈጠረው የግንጠላ ችግር ሁሉ የራሳቸውን አስተዋጽኦ ያበረከቱ ነው የሚመስለኝ፡፡ ፓትርያርኩ አንድ መጥፎ ስራ ሰርተዋል፡፡ የሊባኖስንና የእስራኤልን ፓትርያርኮች ጠርተው የኤርትራ ቤተ ክርስቲያን ነጻ ነችና እወቁልኝ ብለው ጉባኤ ሰብስበዋል፡፡ለእኛም ጽፈውልናል፡፡ እኛ በወቅቱ ይህን ስብሰባ አድርገን በጥብቅ ተቃውመናል፡፡ ስለዚህ ፓትርያርክ ሺኖዳ በጥፋት ላይ ጥፋት ሰርተዋል፡፡ በአጠቃላይ ኤርትራን በሚመለከት በየጊዜው የሚወስዷቸው እርምጃዎችና መልዕክቶች ሁሉ በሙሉ አፍራሽ ናቸው፡፡
በወቅቱ ስለ ተነሱ መናፍቃንና ተሃድሶያውያን
ሃይማኖቱን ጠልተው መቃብሩን መናፈቅ የሚያስኬድ አይደለም ፤ ሃይማኖት አንድ ያላደረገን መቃብር አንድ ሊያደርገን አይችልም ፤ መስቀልን የሚቃወሙና የመላዕክትን አማላጅነት የማይቀበሉ ከኦርቶዶክሶች ጋር እኩል አንድ ላይ መቃብር እንጋራ ማለቱ ሁከት ከመፍጠር ውጪ ሌላ ትርጉም ሊኖረው አይችልም፡፡
 
ቤተ ክርስቲያኒቱ ተሃድሶ ማድረግ አለባት የሚሉ መናፍቃን ናቸው፡፡ እነዚህ ሰዎች ቀድሞ የእኛ እምነት ተከታዮች የነበሩና በኋላ በልዩ ልዩ  ምክንያ ወጥተው ሃይማኖታቸውን በመቀየር ኦርቶዶክስ አርጅቷል ፤ አፍጅቷልና መታደስ አለበት የሚሉ ናቸው፡፡ እነዚህ መናፍቃን ከቤተክርስቲያናችን ማኅበር  የወጡ እና እንዲህ ያለውን ቅስቀሳ የሚያደርጉት፡፡ይህን የሚያደርጉት የኦርቶዶክሱን ስም ይዘው ምዕመናኑን ለመከፋፈል ፤ ትርምስ ለመፍጠርና ቤተ ክርስቲያኒቱን ለማዳከም የሚንቀሳቀሱ ወገኖች ስለሆኑ ትክክለኛ የኦርቶዶክስ ተዋህዶ ተከታዮች ከእነዚህ ዓይነቶቹ ተኩላዎች ራሳቸውን መጠበቅ ይኖርባቸዋል፡፡
ሌሎች


  • ቤተክርስቲያኒቱ 450 ያህል ቤቶች አሁን ከመንግስት አልተመለሰላትም

  • እንደሚታወቀው በአሁኑ ሰዓት ትግራይ ከወሎም ከጎንደርም ብዙ ቦታዎች በመውሰድ ትልቅ ሀገር ሆናለች ፡፡ በታላቋ እና በኢህአዴግ ዘመን ሰፊ ለሆነችው የትግራይ ክልል ለአምስቱም ዞኖች አምስት ኤጲስ ቆጶሳት መሾም አለባቸው ብለው ፓትርያርኩ ለመወሰን አሰቡ…….ሙሉውን  ቃለ መጠይቅ  በPdf ያንብቡ

1 comment:

  1. ሰላም ጤና ይስጥልኝ እንደምን ዋላችሁ።
    መድኃኔዓለም የተመሰገነ ይሁን።

    አቡነ ሽኖዳ ነፍሳቸውን ይማር። ብዙ ኢትዮጵያውያን የግብጽ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ከኛ የተለየ እየሆነ እንደመጣ አያውቁም። እነዚህ ኢትዮጵያውያን አቡነ ገብርኤልን ቢያዳምጡ መልካም ነበር። የኒቅያው ቅዱስ ጎርጎሬዎስ፣ የቆስጠንጢኖሱ ቅዱስ ዮኃንስ ቅርሦስጦሞስ እንዲሁም አባ ሕርያቆስ ዓለም በሙሉ ከክርስትና መንገድ ሲወጣ እውነተኛዋን መንገድ ይዛ የምትቀረው ኢትዮጵያ ብቻ ናት ብለው በትንቢት እንደተናገሩት አሁን ከኢትዮጵያ ሌላ እውነተኛዋን መስመር የሚከተል አገር የለም። እኛም ቢሆን ሰዎቹ ስተናል ክርስትናዋ ግን መስመርዋን አልለቀቀችም። (አንዳንዶች የአባ ሕርያቆስ ትንቢት በግእዙ ላይ አይታይም የሚሉ አሉ። ነገር ግን ቅዳሴ ማርያም እራሱ የትንቢቱ መግለጫ ነው።) ግብጾች ስለ ድንግል ማርያም የሚሉት መልካም አይደለም። ከነሱ ጋር ተራርቀናል። ኤርትራ ብለው ገንጥለው በተሳሳተ መንገድ ሊወስዱ ፍላጎት ነበራቸው። አቡነ ገብርኤል ጥበብ ያለው ነገር ነበር የተናገሩት።

    አቡነ ገብርኤል ቃለ ሕይወት ያሰማልን። ይፍቱኝ።

    እግዚአብሔር ይስጥልኝ።
    ኃይለሚካኤል።

    ReplyDelete