Monday, April 8, 2013

ላፍቶ ሌንቃ መድኃኔዓለም ቤተክርስቲያን 
(አንድ አድርገን ሚያዚያ 1 2005 ዓ.ም) ፡- በአሁኑ ሰዓት የገጠር አብያተ ክርስቲያናት ተመልካች በማጣት የከፋ ችግር ውስጥ የሚገኙ ጥቂቶች አይደሉም ፡፡ አንዳንዶች የካህናትና የዲያቆናት ችግር አላላውስ ሲላቸው ሌሎች ደግሞ ጧፍ ፤ እጣን ፤ ዘቢብ እና መሰል መገልገያዎች እጦት ይስተዋልባቸዋል፡፡ ዛሬ እስከ አሁን ከሰማነው ችግር ለየት ያለ ነገር የሚታይበትን ከገጠር አብያተክርስቲያናት አንዱን ላፍቶ ሌንቃ መድኃኔዓለም ቤተክርስቲያን ያለውን ወቅታዊ ሁኔታ ለማስዳሰስ እንሞክራን፡፡ላፍቶ ሌንቃ መድኃኔዓለም ቤተክርስቲያን በሀዲያ እና ስልጢ ሀገረ ስብከት ውስጥ  ከአዲስ አበባ 210 .ሜ ርቀት ላይ ከምትገኘዋ ላፍቶ ሌንቃ የምትባል የገጠር ከተማ ሲደርሱ ወደ ቀኝ የሚገነጠለውን  ወደ ስልጤ ዞን ቄልጦ ከተማ የሚወስደውን ኮረኮንቻማ የገጠር መንገድ ይዘው  በግምት ከ5 .ሜ በኋላ ያገኙታል፡፡  

በታሪክ ቤተክርስቲያኑ የተመሰረተበትን ዘመን በእርግጠኝነት ለማወቅ እና እና ለመናገር የሚያስችል በቂ መረጃ የሌለ ቢሆንም ዘመናትን እንዳስቆጠረ የሀገር ሽማግሌዎች  ይናገራሉ፡፡ ቦታው በአካባቢው ላይ ያሉ የጥንት አባቶች ሲጠቀሙበት የነበሩ ዋሻዎች ፤ በውስጣቸው የተገኘው የመስቀል ምልክት እና ፅሁፍ ለዕድሜ ጠገብነቱ ምስክሮች ናቸው፡፡  ላፍቶ ሌንቃ መድኃኔዓለም አካባቢ ምዕመናን ልጅ ወልደው ክርስትና የሚያስነሱበት ፤ በስርዓተ ቤተክርስቲያን የሚያሳድጉበት ፤ ቅዳሴ የሚያስቀድሱበት ፤ ለራሳቸውም ይሁን ለልጆቻቸው ስጋወ ደሙ የሚቀበሉበት ፤ የወንጌል አግልግሎት የሚያገኙበት ፤ በአላትን የሚያከብሩበትና መሰል አገልግሎት የሚያገኙበት ቤተ ክርስቲያን የላቸውም ፡፡ ከመካከላቸው አንድ ሰው በሕይወተ ስጋ ሲለይ እንኳ ጸሎተ ፍትሀት የሚያደርግ አባት በአካባቢው ባለመኖሩ ፍትሀት ሳይደረግለት ቀድሞ ቤተክርስቲያኑ የተቃጠለበት ቦታ በማምጣት ሲቀብሩ ኖረዋል፡፡ አስከ አሁንም ድረስ በላፍቶ ሌንቃ የሥላሴ ልጅነት ጥምቀት ያልተጠመቁ ህፃናት እና ወጣቶች ያሉ ሲሆን አንገታቸው ላይ ማህተብ በማሰር ‹‹እኔ ክርስቲያን ነኝ›› በማለት በአህዛብ መካከል እየመሰከሩ ይኖራሉ፡፡ ላፍቶ ሌንቃ መድኃኔዓለም እንደ ቤተክርስቲያን የሚያገለግለው ዋርካ/ዛፍ/ ሲሆን ከስሩ ስዕለ መድኃኔዓለምን በማስቀመጥ ይጠቀሙበታል፡፡ በፊት የነበረው ቤተክርስቲያን በተለያየ ጊዜ የተነሱ አፅራረ ቤተክርስቲያን ለሦስት ጊዜ ያፈረሱት ሲሆን ለመጨረሻ ጊዜ በ1971 .ም በአህዛብ ተቃጥሏል፡፡


በአካባቢው ያሉት 7ዐ የማይሞሉ ክርስቲያኖች ሃይማኖታችንን አንክድም ማተባችንን አንበጥስም በማለት ያለ መምህር በመፅናት ለአስርት ዓመታት ቆይተዋል፡፡ እነዚህ ምዕመናን በአንዲት እምነታቸው  ምክንያት ባለፉት 33 ዓመታት ያሳለፉትን መከራ ተናግሮ መጨረስ የማይቻል መሆኑን በቦታው በህይወት ያሉ የሀገር ሽማግሌዎች ይናገራሉ፡፡ የቤተክርስቲያኑን ይዞታ አንሰጥም በማለታቸው ምክንያት ለበርካታ ጊዜያት ታስረዋል ፤  ተገርፈዋል ፤ ብዙም መከራም ደርሶባቸዋል፡፡

ላፍቶ ሌንቃ ሁሉም ኦርቶዶክሳዊ በእለተ ሰንበት ተኝቶ አያረፍድም ከህጻን እስከ አዋቂ ድረስ ነጠላቸውን አጣፍተው ፤ ጋቢያቸውን አደግድገው ቤተክርስቲያኑ የተቃጠለበት ቦታ የምትገኝ አንድ ዛፍ ስር የመድኃኔዓለምን ስዕል በማኖር/በማስቀመጥ/ ጸሎት ያደርሳሉ ፤ ይሰግዳሉ ፤ ይማፀናሉ ፣ ይለምናሉ ሥርዓተ አምልኮታቸውንም ይፈፅማሉ፡፡ ወር በገባ በ27 የመድኃኔዓለም ዕለት ተራ ይዘው ዳቦ በመጋገር ጠላ በመጥመቅ ጠበል ፀዲቅ በማዘጋጀት መድኃኔዓለምን ይዘክራሉ፡፡ በአጠቃላይ በአህዛብ ተከበው ሃይማኖትን በማፅናት አስደናቂ ተጋድሎ በመፈፀም ላይ ይገኛሉ፡፡

ተአምራት፡- በቦታው ላይ የተገለጡት  ተአምራት ጥቂቶቹ

 1. ቤተክርስቲያኑን ያቃጠሉት ሁለት ወንድ እና አንድ ሴት አህዛብ ሲሆኑ፡- ሴቲቱ እሳት በእንስራ ደብቃ ይዛ በመምጣት ቤተክርስቲያኑ በር ላይ ይጠብት ለነበሩ ሁለት ወንዶች በመስጠት ተባብረው ካቃጠሉት በኋላ በተለያየ ወር የመድኃኔዓለም እለት ያቃጠሉት ሰዎች በመብረቅ የተቀጡ /የሞቱ/ መሆናቸው፡፡ሴቲቱም ከብቶችዋ በሙሉ በመብረቅ ማለቃቸው፤
 2. ቤተክርስቲያኑ ሲቃጠል የነበሩ አገልጋይ መልሶ ለማሰራት የተሰበሰበውን ብዙ ገንዘብ በእጃቸው አድርገው ከአገልጋያቸው ጭምር ወደ እስልምና በገቡ በእለቱ አይነስውር መሆናቸው አገልጋዩም ሽባ መሆኑ እና እስከዛሬ በህይወት መኖራቸው፤
 3. ቤተክርስቲያኑ በተቃጠለበት ቦታ እና አፀዶች መካከል ዝማሬ ቃጭልና እና ከበሮ የሚሰማ ዕጣን /ማዕጠንት/ የሚሸት መሆኑ
 4. ጥንታውያን ዋሻዎች /ሰው የሚገባባቸው እና የማይገባባቸው/ ሲኖሩ በድፍረት የገቡት አንደበተ-ዲዳ ፤ ዓይነ ስውር መሆን እና በእሳት እየተቃጠሉ መውጣት በተጨማሪም ዝማሬ ቅዳሴ በዋሻዎቹ ውስጥ መሰማት ዋና ዋናዎቹ ሲሆኑ በተጨማሪም በተለያዩ ቅዱሳት/ቅዱሳን/ ስም የተሰየሙ ፍል/ሙቅ/ጠበሎች ያሉ ሲሆን ህዝብም አህዛብም እየተጠቀሙባቸው በመፈወስ ላይ መገኝታቸው፡፡በቦታው ላይ ካሉት ተዓምቶች ከብዙ ጥቂቶቹ ናቸው፡፡


በሀዲያ እና ስልጢ ሀገረ ስብከት ውስጥ ያሉትን ችግሮች እና በምእመናኑም ላይ የሚደርሰውን መከራ እንደ እግዚአብሔር መልካም ፈቃድ ለማስወገድ በማሰብ የቤተክርስቲያን ልጆች በመሰባሰብ እና በመምከር ከሀገረ ስብከቱ ጋር በመነጋገር አብሮ በመስራት እና እውቅና በመውሰድ በመጀመሪያ ደረጃ የላፍቶ ሌንቃ መድኃኔዓለም ቤተክርስቲያንን በተገቢው ሁኔታ እና በአጭር ጊዜ ለማቋቋም ፤ በቀጣይነት ሀገረ ስብከቱን ማዕከል ባደረገ ሁኔታ ያሉትን ችግሮች ለዘለቄታው ለመቅረፍ እና ለማስወገድ በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን በሀዲያ እና ስልጤ ሀገረ ስብከት ቅዱስ እንጦንስ መንፈሳዊ የአገልግሎት ማኅበር ተቋቁሞ የተለያዩ ተግባራት በማከናወን ላይ ይገኛል፡፡ ይህም ማኅበር የመድኃኒዓለምን ቤተክርስቲያ ለማሳነጽ መሰረት ድንጋይ ጥሎ ስራ ጀምሯል በመሆኑም ማንኛውም የቤተክርስቲያን ነገር የሚያሳስበው አካል ማኅበራትም ሆኑ ምእመናን በኅብረት በመሆን ዘለቄታዊ መፍትሄ እንድንሰጥ ሁላችንም የምንችለውንና የሚጠበቅብንን እንድናደርግ በእግዚአብሔር ስም ጥሪያችንን እናቀርባለን፡፡


‹‹ቅዱስ እንጦንስ መንፈሳዊ የአገልግሎት ማኅበር››  ህንፃ ቤተክርስቲያኑ እየተሰራ ሲሆን የቤተ ክርስቲያኑን ግንባታ በአጭር ጊዜ ውስጥ ለማጠናቀቅ ይስችለን ዘንድ ምዕመኑ የበኩሉን አስተዋጽኦ ያደርግ ዘንድ በእግዚአብሔር ስም እንጠይቃለን በማለት ጥሪውን ያቀርባል፡፡


‹‹የሰማይ አምላክ ያከናውንልናል፥ እኛም ባሪያዎቹ ተነሥተን እንሠራለን ›› መጽሐፈ ነህምያ  2 ፤ 20


ቅዱስ እንጦንስ መንፈሳዊ የአገልግሎት ማኅበር

Commercial Bank of Ethiopia,

Bomb Tera Branch.

Account no. 1000017080249

Mobile +251911143653, +251911780816, +251910016008
ክብር ምስጋና ለመድኃኔአለም ይሁን፡፡ለፍፃሜው አድርሶ የበረከቱ ተካፋይ ለመሆን ያብቃን፡፡

ወስብሐት ለእግዚአብሔር ወለወላዲቱ ድንግል ወለመስቀሉ ክቡር አሜን!

4 comments:

 1. ሰላም ጤና ይስጥለኝ እንደምን ዋላችሁ።
  መድኃኔዓለም የተመሰገነ ይሁን።

  ሁላችንም በተለይ ውጭ አገር የምንኖር ለዚህ የተቀደሰ ዓላማ ብንረዳ በረከት እናገኝበታለን።

  ከአሜሪካን አገር ኢትዮጵያ ወዳለው ከላይ ወደተጠቀሰው የባንክ ቁጥር እንዴት ነው ማስገባት የሚቻለው? ወይስ መድረሱና ሥራ ላይ መዋሉ የሚረጋገጥበት ሌላ አማራጭ የአላላክ ዘዴ አለ ወይ?

  ምስጋና ለመድኃኔዓለም።
  ኃይለሚካኤል።

  ReplyDelete
  Replies
  1. awon ale melak yemichalebet Addis Ababa bomb tera Commercial Bank of Ethiopia kidus entons blachu btlehu account kuter ale.

   Delete
  2. Commercial Bank of Ethiopia,

   Bomb Tera Branch.

   Account no. 1000017080249

   Mobile +251911143653, +251911780816, +251910016008
   ክብር ምስጋና ለመድኃኔአለም ይሁን፡፡ለፍፃሜው አድርሶ የበረከቱ ተካፋይ ለመሆን ያብቃን፡፡

   ወስብሐት ለእግዚአብሔር ወለወላዲቱ ድንግል ወለመስቀሉ ክቡር አሜን!

   Delete
 2. እንዴት ነው ማስገባት የሚቻለው? ወይስ መድረሱና ሥራ ላይ መዋሉ የሚረጋገጥበት ሌላ አማራጭ የአላላክ ዘዴ አለ ወይ????????

  ReplyDelete