Tuesday, April 23, 2013

‹‹ተዓምሯን አንቀብርም›› በሚል አርዕስ ታላቅ የቅኔ ምሽት ተካሄደ ፤ ከእሳት የተረፉት ንዋየ ቅድሳትም ለምዕመኑ ለእይታ ቀረቡ

(አንድ አድርገን ሚያዚያ 15 2005 ዓ.ም)፡- በአጉስታ ደብረ ጽዮን ቅድስት ማርያም ቤተክርስቲያን “ተዓምሯን አንቀብርም”በሚል አርዕስ ታላቅ የቅኔ ምሽት ባሳለፍነው እሁድ ሚያዚያ 13 2005 ዓ.ም የመንፈሳዊ ኮሌጅ መምህራን ፤ ታላላቅ የቅኔ ድጓ እና የአቋቋም ምሁራን በተገኙበት ተካሄደ፡፡ በጊዜው የደብሩ ሰበካ ጉባኤ እና የስብከተ ወንጌል ጽ/ቤቱ አንድ ላይ ሆነው ባዘጋጁት መርሀ ግብር ላይ በርካታ አዲስ አበባ ውስጥ አሉ የሚባሉ በተለያዩ የአገልግሎት ዘርፎች በቤተክርስቲያኒቱ ውስጥ የሚያገለግሉ ሊቃውንት ተገኝተዋል፡፡ የጉባኤው ዋናው ዓላማው ከእሳት ቃጠሎ የተረፉ ንዋየ ቅድሳትን ለምዕመኑ ለማሳየት መሆኑ ለማወቅ ተችሏል፡፡ በጉባኤው ላይ በቦታ ሄደን እንደተመለከትነው ባየነው ነገር እጅግ ተገርመናል ፤ የእግዚአብሔርንም ተዓምር አድንቀናል ፤ ከእሳት ቃጠሎ የተረፉ በቦታው ላይ የተደረገው የእግዚአብሔርን ተዓምር የሚመሰክሩ በርካታ መጻህፍት ፤ ወደ ዘጠኝ የሚጠጉ የእንጨት መስቀሎች ፤ መጎናጸፊያ እና መሰል በርካታ ንዋየ ቅድሳትን ለመመልከት ችለናል፡፡ በጊዜው የተገኝው የጉባኤው ተካፋይ ምዕመን በሁኔታ እጅጉን መገረሙን ሲገልፅ አስተውለናል፡፡ የመርሀ ግብሩ አስተባባሪና የደብሩ የቁጥጥር ክፍል ኃላፊ መጋቢ ስርዓት ያዕቆብ እንደገለጸው የእመቤታችን ተዓምር እዚህው ተቀብሮ መቅረት ስለሌለበት ወደፊት ቦታውን የረገጠ ምዕመን ሁሉ ይመለከተው ዘንድ ግቢው ውስጥ ትንሽ ሙዚየም በሰበካ ጉባኤው አማካኝነት በማሰራት ከእሳት የተረፉትን ንዋየ ቅድሳት በውስጡ ለማስቀመጥ እንደታሰበ ገልጿል፡፡በተጨማሪም በአሁኑ ሰዓት ምዕመኑ በዚህ ሳምንት ውስጥ እስከ ሚያዚያ 21 2005 ዓ.ም ድረስ በቦታው ላይ በመገኝት ተዓምሯን ይመለከት ዘንድ አስጎብኚ በመመደብ በደብሩ ቅጥር ግቢ ውስጥ የማሳየት ተግባር እየተከናወነ ይገኛል ፤ እነዚህን ንዋየ ቅድሳት በቪዲዮ የተቀረጹ ሲሆን በቅርብ ቀንም ቦታው ላይ ድረስ ሄደው መመልከት ላልቻሉት ምዕመናን ለማድረስ መታሰቡን ለማወቅ ችለናል፡፡

የተቀረጸው ቪሲዲ ሲለቀቅ ለተመልካች ለማቅረብ እንሞክራለን

ስለ ሁኔታው የተሻለ መረጃ ለማግኝት እና ለተጨማሪ ጥያቄዎች የደብሩን ቁጥጥር ክፍል ኃላፊ መጋቢ ስርዓት ያዕቆብ በዚህ  ቁጥር ማግኝት ይችላሉ፡፡
0912-629177

No comments:

Post a Comment