ከሳምሶን ኃ/ሚካኤል
(አንድ አድርገን የካቲት 3 2006 ዓ.ም)፡- ነገ የሚገባው የነነዌ ጾም መቼም ለኢትዮጵያውያን ክርስቲያኖች ከታላቁ ከጌታ ጾም በፊት በእየአመቱ የሚጾም ጾም ነውና በደንብ ይታወቃል ይልቁን አባቶቻችን እናቶቻችን ‹‹ የነይነይ ጾም›› አስከማለት ደርሰው ስም አውጥተውላታል፡፡ ስያሜው ከጾመ ነነዌ ወደ ነይነይ የተቀየረው…በንባብ ተፋልሶ ይሁን ወይም ቶሎ ቶሎ ነይ ለማለት ተፈልጎ …. በእርግጥ አላውቅም፡፡ ወደ ዋናው አሳቤ ስገባ..የብጹዕ ወቅዱስ አቡነ ሺኖዳ ሶስተኛ መጽሀፍ የሆነውን ስለ ነቢዩ ዮናስ የተጻፈውን ‹‹CONTEMPLATIONS
ON THE BOOK OF JONAH THE PROPHET ›› የተባለውን መጽሀፍ ሳነብ ለface book ወዳጆቼስ ትንሽ ባካፍል ብዬ እንዲህ በውርስ ትርጉም አቀረብኩት፡፡
መጽሀፍ ቅዱሱ ታሪኩን እንዲህ ብሎ ይጀምራል…..‹‹የእግዚአብሔርም ቃል ወደ አማቴ ልጅ ወደ ዮናስ እንዲህ ሲል መጣ።ተነሥተህ ወደዚያች ወደ ታላቂቱ ከተማ ወደ ነነዌ ሂድ፥ ክፉታቸውም ወደ ፊቴ ወጥቶአልና በእርስዋ ላይ ስበክ።ዮናስ ግን ከእግዚአብሔር ፊት ወደ ተርሴስ ይኰበልል ዘንድ ተነሣ ወደ ኢዮጴም ወረደ፥ ወደ ተርሴስም የምታልፍ መርከብ አገኘ ከእግዚአብሔርም ፊት ኰብልሎ ከእነርሱ ጋር ወደ ተርሴስ ይሄድ ዘንድ ዋጋ ሰጥቶ ወደ እርስዋ ገባ።››ትንቢተ ዮናስ 1፡1
1. ‹‹ነቢዩ ዮናስ ራስ ወዳድ ነበር ››
ወደ ነነዌ ሂድና ስበክ ሲባል እምቢ ያለው እንዲህ ብሎ አስቦ ነበር፡፡ ‹‹በአገሬ ሳለሁ የተናገርሁት ይህ አልነበረምን? አንተ ቸርና ይቅር ባይ ፥ ታጋሽም ፥ ምሕረትህም የበዛ ፥ ከክፉው ነገርም የተነሣ የምትጸጸት አምላክ እንደ ሆንህ አውቄ ነበርና ስለዚህ ወደ ተርሴስ ለመኰብለል ፈጥኜ ነበር።›› ትንቢተ ዮናስ 4፡3 እኔ ሄጄ ከተማዋ ትገለባበጣለች ብዬ ብሰብክ አንተ መሐሪ ነህና አትቀጣቸውም ያኔ እኔ ደግሞ ሐሰተኛ ነቢይ ፤ቃሉ የማይፈጸም ተብዬ እዋረዳለው ብሎ ራስ ወዳድ ሆኖ ኮበለለ….
2. ነቢዩ ዮናስ ከእግዚአብሔር ፊት በመኮብለል ጌታ ሲጠራው በዛፎች ስር እንደተሸሸገው የእግዚአብሔርነት ሁሉን አዋቂነትን እንደረሳው አዳም ሆነ
በመዝ139፡7‹‹ከመንፈስህ ወዴት እሄዳለሁ? ከፊትህስ ወዴት እሸሻለሁ? ወደ ሰማይ ብወጣ፥ አንተ በዚያ አለህ። ወደ ሲኦልም ብወርድ ፥ በዚያ አለህ። እንደ ንስር የንጋትን ክንፍ ብወስድ፥ እስከ ባሕር መጨረሻም ብበርር ፥ በዚያ እጅህ ትመራኛለች ፥ ቀኝህም ትይዘኛለች። በውኑ ጨለማ ትሸፍነኛለች ብል ፥ ሌሊት በዙሪያዬ ብርሃን ትሆናለች ጨለማ በአንተ ዘንድ አይጨልምምና፥ ሌሊትም እንደ ቀን ታበራለችና እንደ ጨለማዋ እንዲሁ ብርሃንዋ ነው።›› ተብሎ ቢጻፍም ቃሉን እንደማያውቅ ነቢይ ሆኖ በመኮብለል የእግዚአብሔርን የገዢነት ክልል እንደማያውቅ ሰው ሆነ፡፡
3. መርከብ ላይ ለመሳፈር ዋጋ ከፍሎ ገባ
በዚያን ዘመን መርከብ ላይ ለመሳፈር ብዙ ገንዘብ ይጠይቅ ነበር ዮናስም ጌታን የምድር ብቻ ጌታ አድርጎ ከሱ በመኮብለል በባህር ላይ ለመሳፈር ዋጋ ከፍሎ መርከብ ላይ ወጣ በዚህም ምክንያት በገንዘቡ ምክንያት ንጽህናውን ቅድስናውን እንደሚያጣ ደካማ ሰው ሆነ፡፡
4. ከዮናስ ክፋት በላይ የሚደነቀው የእግዚአብሔር ደግነት ዮናስን ተቀይሞ ዝም አላለውም የሱን ክፋት ለደግነት ተጠቀመው ……መርከበኞችም ከእሱ የተሻሉ ሆኑ
ዮናስ ባለመታዘዙ ምክንያት መርከበኞቹ ዳኑ ፤ ቀጥሎ ደግሞ በግድም ቢሆን ታዞ ነነዌ እንዲድኑ ሆነ ፤
ፈጣሪ
ነቢዩ ዮናስ አልታዘዝ ሲለው ግዑዙን ፍጥረታት አዘዘ ፤ ንፋሳት ታዘዙት….‹‹እሳትና በረዶ አመዳይና ውርጭ ፥ ቃሉን የሚያደርግ ዐውሎ ነፋስም…የእግዚአብሔርን ስም ያመስግኑ›› መዝ 148፡8 ተብሎ እንደተጻፈ ቃሉን የሚያደርገው አውሎ ንፋስ መጣ ፤ ‹‹እግዚአብሔርም በባሕሩ ላይ ታላቅ ነፋስን አመጣ፥ በባሕርም ላይ ታላቅ ማዕበል ሆነ፥ መርከቢቱም ልትሰበር ቀረበች።›› ትንቢተ ዮናስ 1፡4
ነገር ግን ዮናስ በመርከቧ ከገባ በኋላ ምንም የኃጢአተኝነት ስሜት ሳይሰማው እንቅልፉን ተኝቶ ስለ ነበር ይልቁን በሱ ምክንያት መርከቧ ስትናወጥ አሱ ግን ምንም ያወቀው ነገር አልነበረም ፡፡ በጥልቅ እንቅልፍ ውስጥ ነበር እነዛ አህዛብ መርከበኞቹም ፈሩ፥ እያንዳንዱም ወደ አምላኩ ጮኸ መርከቢቱም እንድትቀልልላቸው በውስጥዋ የነበረውን ዕቃ ወደ ባሕር ጣሉት ፡፡በዚያን ሰዓት የማይጸልየው ብቸኛው ሰው የእግዚአብሔር ነቢይ ዮናስ ነበር፡፡እንዴት ከዚህ ሁሉ በደል በኋላ የሰላም እንቅልፍ ይልቁን ጥልቅ እንቅልፍ ሊተኛ ቻለ ቢባል ምክንያቱ በራሱ ድርጊት ትክክል ነኝ ብሉ ስለሚያምን ነበር :: የመርከቡም አለቃ ወደ እርሱ ቀርቦ። ምነው ተኝተሃል? እንዳንጠፋ እግዚአብሔር ያስበን እንደ ሆነ ተነሥተህ አምላክህን ጥራ አለው።….አርሱም ከእግዚአብሔር ሲኮበልል አግዚአብሔር ደግሞ አህዛቡን አስነስቶ ወደ አምላክህ ጸልይ አለው፡፡ ነቢዩ ወደ ፈጣሪው እንዲጸልይ በአህዛቡ ተሰበከ፡፡
ነገር ግን መርከቧ አልተረጋጋችም እነሱ የዕምነት ሰዎች ነበሩ ፤ ፈጣሪ የችግሩን ምክንያት እንደሚገልጥላቸው አምነው ዕጣ ተጣጣሉ ዕጣው ለነቢዩ ዮናስ ላይ ወጣ፡፡ ወዲያውም አልፈረዱበትም ምንም ክፉ ነገር አልተናገሩትም ራሱን እንዲከላከል በስርዓት እንዲህ ብለው ጠየቁት ይህ ክፉ ነገር በማን ምክንያት
እንዳገኘን እባክህ ንገረን ሥራህ ምንድር ነው? ከወዴትስ መጣህ? አገርህስ ወዴት ነው? ወይስ ከማን ወገን ነህ? አሉት።እርሱም፦
እኔ ዕብራዊ ነኝ በሕሩንና የብሱን የፈጠረውን የሰማይን አምላክ እግዚአብሔርን እመልካለሁ እነዚያም ሰዎች ከእግዚአብሔር ፊት
እንደ ኰበለለ እርሱ ስለ ነገራቸው አውቀዋልና እጅግ ፈርተው። ይህ ያደረግኸው ምንድር ነው? አሉት።››ትንቢተ ዮናስ 1፡8-10
ብዙ አማልክት የነበራቸው የሰማይና የምድር ጌታ እሱ አገልጋዩ ሲኮበልል እንዲህ አደርጎ በድንቅ መለሰው ብለው ፈሩት፡፡ አወቁትም… ‹‹ባሕሩንም ሞገዱ አጥብቆ ያናውጠው ነበርና። ባሕሩ ከእኛ ዘንድ
ጸጥ እንዲል ምን እናድርግብህ? አሉት።እርሱም፦ ይህ ታላቅ ማዕበል በእኔ ምክንያት እንዳገኛችሁ አውቃለሁና አንሥታችሁ ወደ
ባሕር ጣሉኝ፥ ባሕሩም ጸጥ ይልላችኋል አላቸው።›› ትንቢተ ዮናስ 1፡11….አሱ ለብዙ ሺ የነነዌ ህዝብ ማሰብ ሲያቅተው መርከበኞቹ ለአንድ ለሱ ተጨንቀው ባላቸው አቅም ሁሉ ጥረው አቃታቸው ፤ የሚገርም ጥረት ነበር አደገኛ ጥረት ሕይወታቸውን ነበር የሰጡት ምክንቱም እሱን ለማዳን በሚደርጉት ጥረት መርከቧ ልትሰበር ትችል ይሆናል ብለው በመፍራት እሱን ወደ ባህር ለመጣል አልተሸቀዳደሙም ፤ ወደ ምድሩ ሊመለሱ አጥብቀው ቀዘፉ ዳሩ ግን ባሕሩ እጅግ አብዝቶ ይናወጥባቸው ነበርና አልቻሉም ሲያቅታቸው….‹‹ስለዚህ ወደ እግዚአብሔር ጮኸው። አቤቱ፥ እንደ ወደድህ አድርገሃልና እንለምንሃለን አቤቱ፥ ስለዚህ ሰው ነፍስ እንዳንጠፋ ንጹሕም ደም በእኛ ላይ እንዳታደርግ እንለምንሃለን አሉ።ዮናስንም ወስደው ወደ ባሕሩ ጣሉት ባሕሩም ከመናወጡ ጸጥ አለ።ሰዎችም እግዚአብሔርን እጅግ ፈሩ፥ ለእግዚአብሔርም መሥዋዕትን አቀረቡ፥ ስእለትንም ተሳሉ። ››ትንቢተ ዮናስ 1፡14 ፡፡
የሚስገርመው የነዚህ ሰዎች ንግግር ነበር ለዛ ሁሉ መከራ ችግር ሀብትና ንብረታቸውን ወደ ባህር ለመጣል ምክንያቱ ዮናስ ሆኖ….. በእጣ የችግሩ ባለቤትን ሲያገኙ ሊፈርዱበት አልፈለጉም ለማትረፍ የአቅማቸውን ሁሉ ጣሩ ፤ በመጨራሻም ሲያቅታቸው ‹‹የንጹሕም ደም በእኛ ላይ እንዳታደርግ እንለምንሃለን››ለው የዮናስን ደም ንጹህ ብለው ጠርተው ወደባህር ጣሉት ፤ መርከቧም ጸጥ አለች ፤ እነሱም በፈጣሪ አመኑ ለሱም መሰዋዕት አቅራቢ በመሆን ዳኑ ፤ መርከበኞቹ ይገርሙ ነበር መርከቧ እየተናወጠች የመርከቧን መናወጥ ችግር አውቀው በነውጡስ ሆነው እሱ ለማትረፍ ሞከሩ ፤ ማነው እንዲህ ሚያደርግ ????
5. ዮናስም ወደባህር ሲጣል አሳ አንበሪ ሆድ ለሶስት ቀን በመቆየት የጌታ ምሳሌ ሆነ
ዮናስ ነነዌን ትቶ ተርሴስ የሄደው ከእግዚአብሔር በመኮብለል ነበር ፤ አሱ ሰብኮ ሕዝቡን የእግዚአብሔር ምህረት ከሚያድነው……በውጤቱም ክብሩን ከሚያጣ ውሸተኛ ከሚባል… ብሎ ሲሸሽ መርከቧ ተናውጻ ወደ ባሀር ሲጣል…ሕዝቡን ለማዳን ክብሩን አዋርዶ በሞቱ ሊያከብረን ለመጣው ለጌታ ሞት እና ትንሳዔ ምሳሌ ሆነ፡፡ ‹‹እርሱ ግን መልሶ እንዲህ አላቸው፦ ክፉና አመንዝራ ትውልድ ምልክት ይሻል፥ ከነቢዩም ከዮናስ ምልክት በቀር ምልክት አይሰጠውም። ዮናስ በዓሣ አንባሪ ሆድ ሦስት ቀንና ሦስት ሌሊት እንደ ነበረ፥ እንዲሁ የሰው ልጅ በምድር ልብ ሦስት ቀንና ሦስት ሌሊት ይኖራል።››ማቴ 12፡40
6. ዮናስን ሊያርመው…. አስተምሮ ሊልከው የወደደ ጌታ ባህር ውስጥ አሳ አንበሪን አዘጋጀለት
መጽሀፍ ቅዱስ በግልጽ እንደሚነግረን ትልቁ አሳ አንበሪ ዮናስን ዋጠው፡፡የአሳ አንበሪው ሆድ ሌላ ጊዜ የዋጠውን እንደሚፈጭ ያይደለ ጨጓራውም ሌላ ጊዜ እንደሚያመነጨው ዳጄስቲቭ እነዚያም ሳይሆን ለሱም የሶስት ቀን ቤት ሆነለት ፤ በዛም በእምነት ድንቅ የሆነ ጸሎት ጀመረ እንዲህም አለ፦ በመከራዬ ሳለሁ ወደ አምላኬ ወደ እግዚአብሔር ጮኽሁ፥ እርሱም
ሰማኝ በሲኦልም ሆድ ውስጥ ሆኜ ጮኽሁ፥ ቃሌንም አዳመጥህ።… በዛለችብኝ ጊዜ እግዚአብሔርን አሰብሁት ጸሎቴም ወደ አንተ ወደ ቅዱስ
መቅደስህ ገባች።…..እኔ ግን በምስጋና ቃል እሠዋልሃለሁ የተሳልሁትንም እከፍላለሁ። ደኅንነት ከእግዚአብሔር ዘንድ ነው። እግዚአብሔርም ዓሣውን አዘዘው፥ እርሱም ዮናስን በየብስ ላይ ተፋው።››ትንቢተ ዮናስ ምዕራፍ 2
7. ዮናስ ነነዌ ገብቶ በጣም በሚያስገርም መልኩ አጭር የሆነ ስብከት ሰበከ
ከአሳ አንበሪ ሆድ ከሶስት ቀን በኋላ የተተፋው ዮናስ ወደ ነነዌ ከተማ በቀጥታ ሄደ..ነነዌ የሶስት ቀን ያህል ጊዜ የምትወስድ ታላቅ ከተማ ነበረች…አሱም በሚያስገርም መልኩ ብዙ ስብከት መስበክ ሲችል ስለንስሀ ማስተማር ሲችል ወደ ከተማ የአንድ ቀን ያህል መንገድ ከገባ በኋላ አጭር ቃል ብቻ ተናገረ…‹‹በሦስት ቀን ውስጥ ነነዌ ትገለበጣለች አለ።›› ትንቢተ ዮናስ 3፡4
8. የነነዌ ሰዎች ታላቅ ጾም አወጁ
ንጉሱ ታላቅ አዋጅ አወጣ እኛ በበደልነው በደል ሕጻናት ሆኑ እንሰሳት መቀጣታቸው አይቀርምና ሁሉም ይጹሙ በእጃቸው ካለው ግፍ ይመለሱ ፤ የሚያስገርም የጾም አዋጅ .. የጾም ትክክለኛ ትርጉም የታየበት..ንስሀ እና ጦም የተዋሀዱበት አዋጅ….. ‹‹ንጉሱም ከዙፋኑ ተነሥቶ መጐናጸፊያውን አወለቀ ማቅም ለበሰ፥ በአመድም ላይ ተቀመጠ›› ትንቢተ ዮናስ 3፡1
9. ፈጣሪ ጦመ ንስሀቸውን ተቀበለ ዮናስ ተበሳጨ በቅል ፤ በጸሀይ ፤ በንፋስ አስተማረው
‹‹እግዚአብሔርም ከክፉ መንገዳቸው እንደተመለሱ ሥራቸውን አየ እግዚአብሔርም ያደርግባቸው ዘንድ በተናገረው ክፉ ነገር ተጸጽቶ አላደረገውም።››ትንቢተ ዮናስ 3፡10 ዮናስ ግን ተበሳጨ ‹‹ አቤቱ፥ እለምንሃለሁ በአገሬ ሳለሁ የተናገርሁት ይህ አልነበረምን? አንተ ቸርና ይቅር ባይ፥ ታጋሽም፥ ምሕረትህም የበዛ፥ ከክፉው ነገርም የተነሣ የምትጸጸት አምላክ እንደ ሆንህ አውቄ ነበርና ስለዚህ ወደ ተርሴስ ለመኰብለል ፈጥኜ ነበር።››ትንቢተ ዮናስ 4፡2 ፈጣሪም የከተማውን መቃጠል ለማየት ተራራ ላይ የተቀመጠውን ዮናስን በዕለት በቅላ ከጸሀይ ሙቀት ኣሳርፋው በዕለት በደረቀችው ቅል ሲበሳጭ እንዲህ ብሎ አስተማረው……‹‹ አንተ ትበቅል ዘንድ ላልደከምህባት ላላሳደግሃትም፥ በአንድ ሌሊት ለበቀለች፥ በአንድ ሌሊትም ለደረቀችው ቅል አዝነሃል።እኔስ ቀኛቸውንና ግራቸውን የማይለዩ ከመቶ ሀያ ሺህ የሚበልጡ ሰዎችና ብዙ እንስሶች ላሉባት ለታላቂቱ ከተማ ለነነዌ አላዝንምን? አለው።››ትንቢተ ዮናስ 4፡10
አባቶቻችን ስንጾም አለንስሀ መጾም እንደማይገባን ለማሳየት ከታላቁ ጦመ ሁዳዴ በፊት ንስሀ ጎልቶ የወጣበትን የነነዌን ጾም ለዝግጅት እንድንጾም አደረጉን
ከጾሙ አንድንጠቀም የነነዌን ሰዎች የንስሀ ልብ ይስጠን!!!
No comments:
Post a Comment