Thursday, February 6, 2014

የዘመናችን ተሀድሶያውያን የቀድሞ ‹‹አልፎንዙ እሾኾች››

  • ‹‹ማስተማር ያለባችሁ ስለ እመቤታችን ነው›› የወላይታ ሶዶ  ቅድስት ማርያም ቤተ ክርስቲያን አስተዳዳሪ
  • ‹‹ይህን ሁሉ ኪሎ ሜትር አቋርጠን የመጣነው ስለጌታ ለመመስከር ነው! ጳውሎስ በእብራውያን ላይ ሰለነዮፍታሄ እንዳልተርክ ጊዜ ያንሰኛል ያለው ዓላማው ጌታን መስበክ ስለነበረ ነው›› አልፎንዙ እሾኾች
(አንድ አድርገን ጥር 29 2006 ዓ.ም)፡- የቅድሰት ቤተክርስቲያን ፈተናዎች ሁለት አይነት መልክ ያላቸው ናቸው፤ የመጀመሪያው ቁሳዊ ዕሴቶቿን ማጥፋት ሲሆን ሁለተኛውና ከባዱ ደግሞ መንፈሳዊ ዕሴቶቿን ማጥፋት ነው፡፡ እነዚህ ጥፋቶች በጦርነትም ያለ ጦርነትም ተፈጽመዋል፡፡ በሀገራችን የመንፈሳዊ ዕሴቶች ጥፋት ተጠናክሮ መታየት የጀመረው በዐፄ ሱሲንዮስ ፡፡ ዐፄ ሱሲንዮስ በፖርቹጋል ሚሲዮናውያን አማካኝነት የሀገሪቷን ብሔራዊ ሀይማኖት ወደ ካቶሊክነት ለመቀየር በሞከረበት ግዜ በርካታ የቅድስት ቤተክርስቲያን መንፈሳዊ ዕሴቶች ተበርዘዋል፡፡ የዚህ የቅሰጣና የጥፋት እንቅስቃሴ ዋና ተሳታፊና ነገር ሰሪ ከነበሩት መካከል በዋናነት ፖኤዝ እና አልፎንዙ የተባሉ ሚሲዮናውያን ቄሶች ይገኙበታል፡፡ ለሰባት አመታት ያህል ለቆየው የሀይማኖት ጦርነት እና በአንድ ጀንበር በሱሲንዮስ አደባባይ በግፍ ለተሰውት 8 ሺህ በላይ ንፁሀን የተዋህዶ ልጆች ዕልቂት ምክንያት የሆነው ሚሲዮናዊው ቄስ አልፎንዙ ሜንዴዝ በሱሲኒዮስ ልጅ በዐፄ ፋሲል ትዕዛዝ ከሀገር እንዲወጣ በተፈረደበት ግዜ እንዲህ ብሎ ነበር ከሀገር የወጣው ‹‹ በኢትዮጵያ ሁለት እሾህ ተክዬባታለሁ›› አልፎንዙ በቀደሙት ነገስታት ላይ ይታይ የነበረውን ያለመጠን የበዛ ደግነትና የዋህነትን በመጠቀም ከሀገር ሳይወጣ አሞኛል በማለት የተወሰነ ቀን ትግራይ አካባቢ በመቀመጥ ከጎንደር ላመጣቸው ሁለት ኢትዮጵያውያንቅብዓትና ፀጋ” ብሎ አዲስ እምነት አስተማራቸው፡፡ አልፎንዙ ሁለት እሾህ ያላቸው ቅብዓተ እና ፀጋ የተሰኙትን በእርሱ የተፈለፈሉትን ኑፋቄዎች ነበር፤ ይህ ሚሲዮናዊ ቄስ የኢትዮጵያውያን የእምነት ፅናት ገብቶታል፣ የአንድ ክርስቲያን ደም በሺህ የሚቆጠሩ ክርስቲያኖችን እንደሚፈጥር በታሪክም ሰምቷል በአይን በብሌኑም አይቷል፣ የአብያተ ክርስቲያናት መቃጠል የንዋያተ ቅዱሳት መውደም ኢትዮጵያውያንን ከእምነታቸው አንዲት ጋት ፈቀቅ እንደማያደርጋቸው ተረድቷል፣ የብራናዎቻችንና የመጻህፍቶቻችን መቃጠል ኢትዮጵያውያንን ስለሀይማኖታቸው ከማወቅ እንደማያግዳቸው ተገነዘቧል፤... 

አዎ አንድ ክርስቲያን ሺህ ክርስቲያኖችን በደሙ ሲወልድ በብራና ያሉ ቅዱሳት መፅሐፍቶቻችንና ታሪካዊ መዝገቦቻችን በእያንዳንዱ ኦርቶዶክሳዊ አዕምሮ ውስጥ ሲታተም፣ ከእንጨት እና ከጭቃ የተሰሩት አብያተ ክርስቲያኖቻችን በልባቸው ውስጥ እንደማይፈርሱና እንደማይቃጠሉ ሆነው ሲገነቡ አልፎንዙ አንድ መደምደሚያ ላይ ደረሰ፤... የኢትዮጵያውያንን ቁሳዊ ዕሴቶች ማጥፋት ለተቀሩት ብርታትና ጥንካሬ እየሆናቸው እንደሆነ ተረዳ በዚህም አላበቃም አንድ ዘዴን ዘየደ... መንፈሳዊ ዕሴቶቻችንን የማይጨበጡት የማይዳሰሱት ሀብቶቻችንን ለማጥፋት ለመበረዝ ወሰነ ለዚህም ይረዳው ዘንድ ጎንደር ሳለ አብረውት የነበሩትን ሁለት ለሆዳቸው ያደሩ ደብተራዎችን ተጠቀመ አንዱን ቅብዐት ብሎ አንዱን ፀጋ ብሎ በዘመናት እየበዙ የሚሄዱ እሾሆችን ዘራባቸው፡፡ አልፎንዙ ከአሁን በኋላ ኢትዮጵያ ውስጥ መቀመጥ አላስፈለገውም ደግሞም እርግጠኛ ነበር የዘራቸው ኑፋቄዎች ዕለቱን ባይሆን እንኳን ግዜያቸውን ጠብቀው ቅድሰት ቤተክርስቲያንን እሾህ ሆነው እንደሚወጓት... ያኔ ታዲያ ደረቱን ነፍቶ ‹‹ በኢትዮጵያ ሁለት እሾህ ተክዬባታለሁ›› ብሎ እሾሆቹ ሺህ ሆነው እንደሚበቅሉ በመተማመን ከሀገር ወጣ፡፡ 

ከዚያን ግዜ በኋላ የአልፎንዙ እሾሆች በተለያየ መልኩ የቅድስት ቤተክርስቲያን መንፈሳዊ ዕሴቶች ማጥፋት ወይም መበረዝ ዋነኛ አላማቸው አድረገው ተንቀሳቀሱ ፤እንቅስቃሴያቸውም ዘመኑን የመሰለ ነበር... አዎ በእርግጥም ነው፡፡ የአልፎንዙ የግብር ልጆች የዘመኑን ምቹ ሁኔታ እና የእኛን ግዴለሽነት በመጠቀም የተለየ በሚመስል መልኩ አሁንም ወረውናል፡፡ አልፎንዙ ዛሬም አንደዛ ለሆዳቸው ያደሩ የጎንደር ደብተራዎች በቅድሰት ቤተክርስቲያን ውስጥ ያሉ የሷን ጡት የጠቡ... ሀሁ ብላ ፊደል ያስቆጠረቻቸውን ... መልዕክተ ዮሐንስ አስብላ ንባብ ያስተማረቻቸውን ከሀዲ ልጆችዋን በመጠቀም ከውስጧ ሆነው እንዲወጓት እያደረገ ነው፡፡ 

በየዘመኑ የተለያየ ስም እና አካሄድን በመያዝ ቅድስት ቤተክርስቲያንን የሚወጋው የአልፎንዙ እሾህተሐድሶ” የሚል ስም በመያዝ በእኛ ዘመንም በቅሏል፡፡ተሐድሶ” ቃሉ በደፈናው ሲታይ መልካምነት እና አውንታዊ ትርጉም ያለው ይመስላል አንድን ነገር ማደስ ማስተካከል ማረም የሚል አይነት፤ ይህ ፍቺ ለቅድሰት ቤተ ክርስቲያን ፈፅሞ አይስማማትም ምክንያቱም እሷ አቡነ ፊሊጶስ እንዳሉት ታድሳለች እንጂ አትታደስም፣ እሷ የተበላሸውን ታስተካክላለች እንጂ አትስተካከልም፣ እሷ የተሳሳተውን ታርማለች እንጂ አትታረምም”  እርግጥ ነው ተሐድሶያውያኑ ቅዳሴው ረዝሞባቸዋል፣ ፆም ፀሎቱ ያለመጠን በዝቶባቸዋል፣ ገድሉ ደርሳናቱ ቆርቁሯቸዋል፣ የእነዚያ ቅዱሳን አባቶቻችን ድምፅ ሻክሮባቸዋል፣ የቁርባኑና የንስሐው ነገር አቅለሽልሿቸዋል፣ እንደ ስምኦን መሰሪው ፀጋ መንፈስ ቅዱስን በገንዘብ ይሸጡታል፣ የሰበኩትንና ያስተማሩትን መኖር አቅቷቸው ትምክህታቸው ጌታችን ሳይሆን እነዚያ ተራ የአራት ኪሎ ወይዛዝርት እና ምድራዊ ባለስልጣናት ናቸው ፣ መዝሙሩን ከዘፈን ደባልቀው ምዕመኑን ግራ አጋብተውታል፣ የሚሲዮናውያኑ ገንዘብ አቅላቸውን አስቷቸዋል፣ እንደ አለቃቸው አልፎንዙ በየመንደሩ እና በየአዳራሹ በግል እና በቡድን ኑፋቄን እየዘሩ ነው ፤ ለጥቂት ጊዜያትም ቢሆን ገለል ያሉበትን አውደ ምህረት ዳግም በእጃቸው ለማስገባት ድንጋዮችን እየፈነቀሉ ነው ፤የአልፎንዙ እሾሆች ከምንግዜውም በላይ በእኛ ዘመን እየተሳካለቸው ይገኛል፡፡ ይህ የቅሰጣ ተግባር በዚሁ ከቀጠለ ቅድሰት ቤተክርስቲያንን ከነሙሉ ክብሯ እና አቅሟ ለቀጣዩ ትውልድ መተላለፏ አጠራጣሪ ይሆናል፡፡
 
እነዚህ የአልፎንዙ እሾኾች ከተገለሉ በኋላ የመጀመሪያውን ጉባኤ  በወላይታ ሶዶ  ቅድስት ማርያም ቤተ ክርስቲያን ባካሄዱበት ወቅት ምእመኑን እጅግ ማናደዳቸውንና በሁለት የተከፈለ ጉባኤ ማካሄድ መቻላቸውን ለማወቅ ተችሏል፡፡ ከቤተክርስቲያኑ አስተዳዳሪ ‹‹የመጣችሁባት ቤተ ክርስቲያን የእመቤታችን ናት ፤ ማስተማር ያለባችሁ ስለ እመቤታችን ነው›› ተብለው በተጠየቁበት ወቅት ‹‹ይህን ሁሉ ኪሎ ሜትር አቋርጠን የመጣነው ስለጌታ ለመመስከር ነው! ጳውሎስ በእብራውያን ላይ ሰለነዮፍታሄ እንዳልተርክ ጊዜ ያንሰኛል ያለው ዓላማው ጌታን መስበክ ስለነበረ ነው›› የሚል መልስ ሰጥተዋቸዋል፡፡ አውደ ምህረቱን እኛው ፈቅደን እንዲህ አይነት ነገር የድፍረት ቃላቶች እየመጡብን ይገኛሉ ፤ ቀድመው ለማይገባቸው አውደ ምህረቱን ፈቅደው ስለ እመቤታችን መስበክ ማለት ስለነዮፍታሄ መተረክ ጋር አያያዙልን፡፡  በዚህ የድፍረት መልሳቸው ያልጠበቁት አስተዳዳሪ በነገሩ እጅጉን መናደዳቸውን በዚህም የተነሳ  እንደታመሙ እና በወቅቱ ይህን ሲናገሩ በአካባቢው ላይ የነበሩ የአይን ምስክሮችን በመያዝ ለበላይ አካል አቤት ለማለት እንደተዘጋጁ ለማወቅ ተችሏል፡፡ 
አሁንም ሃሳባችን አንድና አንድ ነው ፤ በዚች ቤተክርስቲያን የጀመሩት ሕገወጥ ጉባኤ በሌላ ላይ መደገም ስለሌለበት አውደ ምህረት ፈቃጆች ልታስቡበት ይገባል ፤ የሰላም አየር ሲተነፍስ የነበረውን ምዕመን ዳግም ወደማያባራ ቀውስ ውስጥ የመክተቻ ቀላሏን እርምጃ አታለማምዱት ፤ አሁንም የሰዎቹ ጉዳይ በቅዱስ ሲኖዶስ የተያዘ ስለሆነ ከቅዱስ ሲኖዶስ ውሳኔን መጠበቅ ስለሚያስፈልግ በጓሮ በር የተደረገ ይቅርታን መሰረት አድርጎ  አውደ ምህረቱን መፍቀድ ወደፊት ያልታሰበ ዋጋ እንደሚያስከፍል ተረዱት፡፡ አውደ ምህረቱን ለሆዳቸው ካደሩ ሰዎች መጠበቅ ያስፈልጋል ፡፡ የአልፎንዙ የግብር ልጆች የዘመኑን ምቹ ሁኔታ እና የእኛን ግዴለሽነት በመጠቀም የተለየ በሚመስል መልኩ መንፈሳዊ ዕሴቶችን ፤ ሃይማኖታዊ ትምህርቶችንና አይከኖቻችንን  ማቃለል ፤ ማጥፋትና መበረዝ ዋንኛ አላማቸው ነው፡፡  አሁንም ሌላ የድፍረት ቃል ላለመስማት አውደ ምህረቱን ለማን እንደምትፈቅዱ አስተውሉ፡፡ 
እግዚአብሔር ቤተክርስቲያንን ከአልፎንዙ እሾኾች ይጠብቅልን

No comments:

Post a Comment