Wednesday, February 12, 2014

ኦ ብእሲት - አንቺ ሴት


በዲያቆን አባይነህ ካሴ
 (አንድ አድርገን የካቲት 06 2006 ዓ.ም)፡- ሴት የሚለው ቃል በመጽሐፍ ቅዱስ የተሰጠው ቦታ እጅግ ከፍ ያለ ነው፡፡ ቃሉን ለመጀመሪያ ጊዜ የተጠቀመበት አባታችን አዳም ነው፡፡ እግዚአብሔር ከአዳም ግራ ጎን አንዲት አጥንት ወስዶ እጅግ ውብ እና ድንቅ የሆነች ሔዋንን ፈጥሮ ቢሰጠው በተደምሞ "ይህች አጥንት ከአጥንቴ ናት፥ ሥጋም ከሥጋዬ ናት እርስዋ ከወንድ ተገኝታለችና ሴት ትባል።" ሲል ጠራት፡፡ ዘፍ ፪፥፳፫። ሴት የሚለውን መጥሪያ አዳም የሰጠበት ዋናው ወይንም ዐቢይ ምክንያት ምን እንደሆነ እዚሁ ተገልጦልናል፡፡ 

እርሱም "አጥንቷ ከአጥንቴ ሥጋዋም ከሥጋዬ" ስለሆነ የሚለው ነው፡፡ የቃሉ ጥንት ከመነሻው ይኽን ይመስላል፡፡ ከቃሉ አብነት የምንረዳው የሰው ሁሉ አባት አዳም እጅግ አቅርቦ የራሱ እንደሆነች ሲያመለክት ቃሉን እንደተጠቀመበት ነው፡፡ ለዚህ አባባል ማጠናከሪያ የሚሆነን ሦስተኛ ወንድ ልጁን ለአቤል ምትክ የሚሆን ተሰጠኝ ሲል "ሴት" ብሎ መሰየሙ ነው፡፡ "ልጅንም በምሳሌው እንደ መልኩ ወለደ ስሙንም ሴት ብሎ ጠራው።" እንዲል፡፡ ዘፍ ፭፥፫። እርሱን ከመምሰል ጋር እንዴት እንዳያያዘው ስንረዳ ቃሉ የማቅረብ እንደሆነ ያስገነዝባል፡፡ በምሳሌው እንደ መልኩ መወለዱ ሴት የሚለውን ስያሜ ከአባቱ እንዲያገኝ በአመክንዮነት ሰለቀረበ በዚህ እንረዳለን፡፡


በእርግጥ ከእመቤታችን ውጪ ሌሎች ሴቶችን ጌታችን በዚህ አጠራር አልጠራም ማለት አይደለም፡፡ ለምሳሌ ከነናዊቷን ሴት፣ ስታመነዝር የተገኘቸውን ሴት እና መግደላዊት ማርያምን በመቃብሩ ስፍራ በተመሳሳይ እንደጠራቸው እንረዳለን፡፡ ታዲያ ይህ ከሆነ ለእመቤታችን ሲሆን እንዴት የተለየ ነው ልንል እንችላለን? ሚል ጥያቄ ሊነሣ ይችላል፡፡ አንድ ልጅ የወለደችውን እናቱን "እማማ" እንደሚላት ሁሉ በእናቱ ዕድሜ እንዳሉ ያሰባቸውን ሌሎች እናቶችንም "እማማ" ብሎ ሊጠራቸው ይችላል፡፡ ይህ ማለት ግን ሁሉም በሥጋ እናቶቹ ናቸው ማለት እንዳልሆነው ሁሉ ጌታችን እመቤታችንን በዚህ ሲጠራት እና ሌሎችን ሲጠራም እንዲሁ ይለያያል፡፡ ዳግማዊ አዳም ኢየሱስ ክርስቶስ ወደዚህ ዓለም በመጣ ጊዜ መጻሕፍት እንዳስረዱን "አንቺ ሴት" የሚለውን ቃል ለእመቤታችን ሁለት ጊዜ ተናግሮታል፡፡ የመጀመሪው ጌታችን በቃና ዘገሊላ በቤተ ዶኪማስ በጉባኤ በአደባባይ ሰው ሁሉ እየሰማው የተናገረው ነው፡፡ ይኽም እመቤታችን የወይን ጠጅ ማለቁን ማንም ሳይነግራት በተሰጣት ሀብት ዐውቃ (ምልዕተ ጸጋ ናትና) "የወይን ጠጅ እኮ የላቸውም" ባለችው ጊዜ ተገቢውን መልስ ሲመልስላት ነው፡፡ ያን ጊዜ "አንቺ ሴት" ሲል እናቱን ጠራት፡፡ ዮሐ ፪፥፬። እንግዲህ ምን ማለቱ ይሆን?ሌላ ጥያቄ እንዳናነሣ እርሱ ቅሉ ሐጋጌ ሕግጋት (ሕግጋትን ደንጋጊ) የባሕርዪ አምላክ በመሆኑ "አባትህን እና እናትህን አክብር" ብሎ ቅድመ ሥጋዌ (ቅድመ ተዋሕዶ ወይንም ሰው ከመሆኑ በፊት) ያዘዘ ነውና እናቱን ክብር ነፈጋት ማለት ይሆንብናል፡፡ ማክበሩንማ እናውቅ ዘንድ "ከእነርሱም ጋር ወርዶ ወደ ናዝሬት መጣ፥ ይታዘዝላቸውም ነበር።" ብሎ መጽሐፍ ነገረን፡፡ ሉቃ ፪፥፶፩፡፡ እርሱን በዚህ መጠርጠር እርሱን አለማመን ይሆንብናል፡፡ እኛ ደግሞ አምላከ አማልክት፣ እግዚእ ወአጋእዝት፣ ንጉሠ ነገሥታት፣ አልፋ ዖሜጋ፣ ብለን እናምነዋለን እናመልከዋለንም፡፡ ራእይ ፲፯፥፲፬፣ ፲፱፥፲፮ ጢሞ ፮፥፲፭፡፡

ቃል ሥጋን የተዋሐደው ከሰማይ አምጥቶ አይደለም፡፡ ቢያደርግ የሚቸግረው ሆኖ ሳይሆን ፍጹም ሰው ለመሆን የአዳምን ሥጋ መዋሐድ የግድ ስለሆነ ነው፡፡ ዳግማዊ አዳም የተባለውም በአማን የእኛን ሥጋ ስለተዋሐደ ነው፡፡ ቆሮ ፲፭፥ ፵፭። የዳዊት ልጅ ለመባልም አልገደደውም፡፡ ዘመን የማይቆጠርለት መለኮት በዚህ ጊዜ ነበረ በዚህ ጊዜ አልነበረም የማይባለው ቃል ለተዋሕዶ የመረጠው የእመቤታችን የቅድስት ድንግል ማርያምን ሥጋ ነው፡፡ እርሷን በንጽሕና አጊጣ እና ተሸልማ ቢያገኛት ለተዋሕዶ መረጣት፡፡ ከሥጋዋ ሥጋ ከነፍሷ ነፍስ ነሥቶ ሰው ሆነ፡፡ ስለዚህም አንቺ ሴት አላት፡፡ 

ቀዳማዊው አዳም ይህች አጥንት ከአጥንቴ ሥጋዋም ከሥጋዬ ሲል ሴት እንዳላት ሁሉ ዳግማዊው አዳም ደግሞ ከሰማይ ሥጋ አላመጣሁም ሥጋዬ ከሥጋሽ አጥንቴም ከአጥንትሽ ሲል "አንቺ ሴት" ብሎ እናቱን ቅድስት ድንግል ማርያምን በወግ በማዕረግ ጠራት፡፡ ይህ አጠራር ድንቅ ነው! ይህ አጠራር በአማን ልዩ ነው! መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ማክበሩን ብቻ ሳይሆን የመታዘዙን ወሠን እስኪ እንመልከተው፡፡ ለዚህ ትኅትናውስ ምን ቃል እናገኝለታለን

ጌታችን አንቺ ሴት ማለቱ ሰው በተሰበሰበበት በአደባባይ እናትነቷን ማረጋገጡ ነው፡፡ ሌሎች እናቶች እናትነታቸው በአባት የታጀበ ነው፡፡ የእርሷ እናትነት ግን ያለ አባት እንበለ ዘርዐ ብእሲ ነው፡፡ የልዩነቱን ርቀት እስኪ እንለካው፡፡ ይህ በኅሊናችን ዘወትር ተስሎ ይኖር ዘንድ "አንቺ ሴት" ብሎ ጠራት፡፡ በሌላ አጠራር ለመጥራት ገድዶት አይደለም፡፡ ይኽኛውን ወድዶት እንጂ፡፡ "ኩሎ ዘፈቀደ ገብረ እግዚአብሔር በሰማይኒ ወበምድር በባሕርኒ ወበቀላያት - በሰማይም በምድርም በባሕርም በጥልቆችም እግዚአብሔር የወደደውን ሁሉ አደረገ" እንዲል የወደደውን ለማድረግ ማን ከልካይ አለበት? መዝ ፻፴፬፥፮። ይህን አጠራር በተለየ ጌታችን ወድዶታል ለማለት እንችላለን ወይ? ብንል እርሱ ራሱ እመቤታችንን በድጋሚ በዚሁ አጠራር መጥራቱ ያረጋግጥልናልና መልሳችን አዎ ብቻ ነው፡፡ እርሱም በቀራንዮ በመስቀል ላይ ሆኖ በጠራት ጊዜ ነው፡፡ "አንቺ ሴት እነሆ ልጅሽ" ያለበት ድምጽ ልዩ ቃና ያለበት ነው፡፡ ዮሐ ፲፱፥፳፮። ሁለቱም ሁኔታዎች በተመሳሳይ ያስተላለፉት ዐቢይ መልእክት አለ፡፡ የእመቤታችንን ክብር! ምክንያቱም፡- በአደባባይ መናገሩ ነው፡፡ ጌታችን በሁለቱም ጊዜያት እመቤታችንን "አንቺ ሴት" ያለው በጣይ በጉባይ ነው፡፡ በቃናው ሠርግም እድምተኞች ነበሩ፣ በቀራንዮ አደባባይም እንዲሁ ሰዎች ነበሩ፡፡ የእመቤታችን እናትነት እንዲህ በአደባባይ መነገሩ ሁሉም በሚገባ ያውቀው ዘንድ የተደረገ ታላቅ ዐዋጅ ነው፡፡ እመቤታችን እንዲህ ከፍ ባለ መድረክ በሚሰማ ድምጽ የተሰጠችን  ናት፡፡ 

እስኪ እናስተውል ጌታችን በተለይ በዚያች የጭንቅ ጭንቅ ሰዓት በተደራረበ መከራ መስቀል ውስጥ ሆኖ ይህን ቃል እንደምን ተናገረው? ሁኔታው የማይታለፍ ደረጃው ከፍ ያለ መሆኑን የምናየው ከተናገራቸው ጥቂት ንግግሮች መሀል የእናቱን ነገር በመጨመሩ ነው፡፡ ከሰባቱ አጽርሐ መስቀል አንዱ "አንቺ ሴት" የሚለው ነውና፡፡ የቃላቱ ጥቂት መሆን፣ የሰዓቲቱ አስጨናቂ መሆን፣ የእርሱ እጅግ በደከመ ጊዜም ቢሆን ከፍ ባለ ድምጽ መናገር ለጉዳዩ ልዩ ትኩረት እንድንሰጥ ያስገድደናል፡፡ እናቱን መቼም ቢሆን ሊተዋት እንደማይችል ከዚህ በላይ እንዴት ይገለጣል፡፡ ወደዚህ ዓለም ሲመጣ ያነጋገረችው እርሷ ናት፡፡ የመጣበትንም የቤዛነት ሥራ ፈጽሞ ወደ ቀደመ መንበሩ ወደ የማነ አብ ዘባነ ኪሩብ ሲሄድም የተነጋገረው ከእርሷ ጋር ነው፡፡ ስለሆነም እመቤታችን ራሷ ምሥጢር ናት፡፡ መጠሪያዋ እንደ አሸዋ የበዛው እንዲሁ እንዳልሆነ የማያውቅ ክርስቲያን መኖር የለበትም እና ስለእርሷ ተናግሮ መድከም አይኖርም፡፡ ጌታችንም በሕማም በደከመ ጊዜ እንኳ ስለ እርሷ ነግሮናልና፡፡ 

ይኽንን እናውቅ ዘንድ የረዳን አምላካችን እግዚአብሔር ይመስገን፡፡

1 comment:

  1. ስለሆነም እመቤታችን ራሷ ምሥጢር ናት፡፡ መጠሪያዋ እንደ አሸዋ የበዛው እንዲሁ እንዳልሆነ የማያውቅ ክርስቲያን መኖር የለበትም እና ስለእርሷ ተናግሮ መድከም አይኖርም፡፡ ጌታችንም በሕማም በደከመ ጊዜ እንኳ ስለ እርሷ ነግሮናልና፡፡
    D/n Abayneh, excellent explanation that really nourish our sole and flesh. God bless you

    ReplyDelete