- የቅርሶቻችን ዋጋ ምን ያህል ነው?
(ሪፖርተር ጋዜጣ):- የተባበሩት መንግሥታት የትምህርት፣ የሳይንስና የባህል ድርጅት (ዩኔስኮ)...በዓለም ጥንታዊ ቅርስነት ከመዘገባቸው የሥነ
ጽሑፍ ውጤቶች መካከል በኢትዮጵያ ቤተ
ክርስቲያን ባለቤትነት የተመዘገቡና በብራና ላይ
የተጻፉ የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍሎች የነገረ ሃይማኖት ጽሑፎች ይገኙበታል፡፡
እነዚህ እስከ
ሺሕ ዓመታት ዕድሜን ያስቆጠሩ ብርቅና ውድ የሆኑ የሥነ ጽሑፍ ቅርሶች በተለያዩ ጊዜያት በአገሪቱ በደረሱ ተፈጥሮአዊና ሰው ሠራሽ አደጋዎች ምክንያት ውድመት፣ ጥፋትና ዝርፊያ እንዳጋጠማቸው ይታወቃል፡፡ከዚህም በተጨማሪ በጥናትና በምርምር ሰበብ ከአገር የወጡ ጥንታዊ ብራናዎች አያሌ
ናቸው፡፡ በአውሮፓና በአሜሪካ በሚገኙ ትላልቅ ዩኒቨርሲቲዎችና
አብያተ መጻሕፍት፣ እንዲሁም በግለሰቦች፣ በቅርስ አሻሻጮች እጅም ማግኘት የተለመደ ነው፡፡
በኢትዮጵያ ጥንታዊ የሥነ
ጽሑፍ ቅርሶች፣ ጥንታዊ የብራና መዛግብት፣ መጻሕፍትና ጠልሰሞች (Magical Scrolls) ላይ በተለያዩ ጊዜት ሰፋ ያለ ምርምርና ጥናት ያደረገው አሜሪካዊው ምሁር
ፕሮፌሰር ስቲቭ
ከሰባት ዓመት
በፊት በዋሽንግተን ዲሲ፣ በዓመታዊው ‹‹ለሶሳይቲ ኦፍ ባይብሊካል ሊትሬቸር›› ዓለም አቀፍ ስብሰባ ላይ ‹‹Scribal Practice in Ethiopian Psalters as Expression of
Identification and Differentiation›› በሚል
ርእስ በርካታ ተሳታፊዎችን ያስገረመና ያስደመመ አንድ እውነተኛ ገጠመኙን በማስቀደም ሰፋ ያለ ጥናታዊ ጽሑፍ
አቅርቦ ነበር፡፡
ስቲቭ በዚህ ጥናታዊ ወረቀቱ ላይ
በተለይ በኢትዮጵያ ጥንታዊ ጽሑፎችና መዛግብት ላይ የበለጠ ትኩረት ሰጥቶ እንዲያጠና ያደረገውን አንድ ለየት ያለ ገጠመኙን ለተሳታፊዎቹ ገልጾ ነበር እ.ኤ.አ ከስምንት ዓመት በፊት ከአንድ በአካል ከማያውቀው ሰው ዘንድ የስልክ ጥሪ
ይደርሰዋል፡፡ ጥሪውም ስቲቭ ከሚኖርበትና በመኪና የ45 ደቂቃ
ጉዞ ከሚፈጀው ከአሜሪካዋ የኦሬገን ክፍለ
ግዛት ነበር፡፡ ደዋዩም አሜሪካዊ ለስቲቭ ስልክ እንዲደውልለት ያስገደደውን ምክንያቱን በአጭሩ ገለጸለት፡፡
‹‹ከ39 ዓመት በፊት (እ.ኤ.አ በ1966) ከአሜሪካ የሰላም ጓድ ሠራዊት አባል ሆኜ በባሕር ዳር
ከተማ ለጥቂት ወራት ቆይታ አድርጌ ነበር፡፡ በአንድ የዕረፍቴ ቀንም ከባሕር ዳር ከተማ ባሉ ገጠራማ ቀበሌዎች ወጣ
ብዬ ስንሸራሸር ድንገት በመንገዴ ላይ
አንድ ዕድሜው በጎልማሳነት ደረጃ ከሚገኝ የገጠር ሰው
ጋር ተገናኘሁ፡፡
እንደ ሀገሩ ባህልም ከዚህ ፊቱ በፈገግታ ከተሞላ ጎልማሳ ሰው ጋር ሰላምታ ከተለዋወጥን በኋላ ቋንቋችን ለየቅል በመሆኑ የተነሣ መግባባት ቢያዳግተንም እንደምንም በምልክት ለመግባባት ጥረት አደረግን፡፡ ከአፍታ ቆይታም በኋላ ጎልማሳውን ሰው
በአካባቢያችን ከሚገኘው የዛፍ ጥላ ሥር አረፍ እንድል በምልክት ነገርኩት፡፡ በፈገግታ ፈቃደኝነቱን በአንገቱ በማወዛወዝ ገልጾልኝ አብረን ተቀመጥን፡፡ ከዚያም በእጄ
በያዝኩት የሻይ
መያዣ ፔርሙዝ ግሩም ሻይ ቀድቼ ለእንግዳዬ ጋበዝኩት፡፡ እንግዳውም ሰው በግብዣዬ ተደስቶ በብዙ
ካመሰገነኝና ከመረቀኝ በኋላ ዓይኑን በሻይ
መያዣ ዕቃዋ
ላይ ሲንከራተት ደጋግሜ አስተዋልኩት፡፡
‹‹እኔ በበኩሌ ገና ስንገናኝ ጀምሮ ይህ ሰው ባነገተውና በእጅጉ በተዋበችው የቆዳው ቦርሳው ላይ
ዓይኔን ጥዬ
ነበር፡፡ እናም
ይህን ሰው
አግባብቼና በምልክትም ቢሆን ተስማምተንና ተግባብተን በሻይ መያዣ ዕቃዬ/ፔርሙዜ ላይ
አስር የኢትዮጵያ ብር ጉርሻ ጨምሬለት ባነገተው ቦርሳ
ተቀያየርን፡፡ ይህችን በውስጧ በግሩም ሁኔታ
የተደጎሰች መጽሐፍ የያዘችው የቆዳ ቦርሳ (ማኅደርም) የኢትዮጵያን ምድር ተሻግራ በአሜሪካ ይኸው ከእኔ ጋር ላለፉት 39 ዓመታት ቆይታለች፡፡
‹‹አሁን ግን ቦርሳው ውስጥ
ያለው በከፍተኛ ጥንቃቄ የተዘጋጀውና በተዋቡ ሐረጎች ያሸበረቀው ይህ
ጥንታዊ የሚመስል መጽሐፍ ምን መሆኑን አንተና መሰል
ምሁራን ትመረምሩት ዘንድ ልሰጥህ እፈልጋለሁና እባክህ እንገናኝ በማለት ጠየቀኝ፡፡ስቲቭ በዚሁ ጥናታዊ ወረቀቱ ላይ
ትረካውን ሲቀጥል፡- ‹‹እኔም አድራሻውን ከተቀበልኩት በኋላ በጉጉትና በፍጥነት ወዳለበት ድረስ በመሄድ ያን ለ39 ዓመታት ከዚህ አሜሪካዊ የሰላም ጓድ ጋር የቆየውን መጽሐፍ ከነቆዳ ማኅደሩ ከታላቅ ምስጋና እና ጠቀም ካለ ጉርሻ ጋር በደስታ ተቀበልኩት፡፡
በአሜሪካዊው ምሁር ፕሮፌሰር ስቲቭ አገላለጽ፣ አስደናቂው ነገር
ያ እጅግ
ባማረ ሁኔታ
በኢትዮጵያ ቤተ
ክርስቲያን ሊቃውንት አስደናቂ ዕውቀትና ጥበብ
የተዘጋጀ፣ በእጅጉ የተዋበና የዘመን መለዋወጥ በጭራሽ ያላስረጁት ትንግርተኛ መጽሐፍ የ17ኛው መቶ ክፍለ ዘመን ‹‹መዝሙረ ዳዊት›› ሆኖ ነበር የተገኘው፡፡ 400 ዓመታት ገደማን ያስቆጠረ መዝሙረ ዳዊት
ነበር፡፡
ስቲቭ በዚሁ ጥናታዊ ወረቀቱ እንደገለጸው፣ እ.ኤ.አ ከ2005 እስከ
2006 ከአዲስ አበባ
ዩኒቨርስቲ የኢትዮጵያ ጥናትና ምርምር ተቋም፣ የጥንታዊ መዛግብትና የብራና ጽሑፎች ክፍል ጋር በመተባበር ባደረገው አሰሳና ጥናት፣ በአንድ ዓመት ውስጥ ብቻ በዓለም ዙሪያ
ከ240 በላይ
የሚሆኑ በተለያዩ ዘመናት የተጻፉ ጥንታዊ የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን ብራናዎችና ጠልሰሞችን አሰባስቦ ከኢትዮጵያውያንን ከሌሎች አገሮች ምሁራን ጋር
ካታሎግ ለማድረግ መቻሉን ይገልጻል፡፡
በተለያዩ ዘመናት በተለያዩ ጉዳዮችና ሰበቦች ወደኢትዮጵያ የመጡ የውጭ ሰዎች በዚህ መልኩ መንፈሳዊና ታሪካዊ ቅርሶችን ወደ አገራቸው አሻግረውታል፡፡ ዛሬ
ዓለም የሚደነቅበትና በኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን ጥንታዊ ቋንቋ
በኾነው በግእዝ የተዘጋጀው ‹‹መጽሐፈ ሔኖክ፣›› የዓባይን መነሻ አስሳለኹ ብሎ በ17ኛው
መቶ ክፍለ
ዘመን ወደ ኢትዮጵያ በመጣው ስኮትላንዳዊው ተጓዥ ጀምስ ብሩስ ወደ አውሮፓ ለመሻገር የበቃው፡፡
ፕሮፌሰር ስቲቭ በዚሁ ጥናታዊ ወረቀቱ በተለያዩ ጊዜያትና አጋጣሚዎች ከኢትዮጵያ ወጥተው በውጭ
ሀገራት የሚገኙ የኢትዮጵያን ጥንታዊ የብራና መጻሕፍትና መዛግብትን እንደሚከተለው በዝርዝር አቅርቦታል፡፡ በብሪትሽ ቤተ መጻሕፍት 598፣
በጀርመን ዩኒቨርስቲዎችና ቤተ መጻሕፍት 545 በኦክስፎርድ ዩኒቨርሰቲ 115፣ በካምብሪጅ ዩኒቨርስቲ ቤተ
መጻሕፍት 69፣
በአይርላንድ ዱብሊን በሚገኘው ረይላንድ ቤተ
መጻሕፍት 58፣
በማንችስተር ዩኒቨርስቲ 45፣ በሩሲያ ቅዱስ ፒተር ስፐርግ 275፣ በአሜሪካ 133፣ በዱክ ዩኒቨርስቲ 33 ጥንታዊ ብራናዎች እንደሚገኙ ጠቁሟል፡፡
በተጨማሪም በእንግሊዟ ንግሥት ቤተ መንግሥት ውስጥ
በሚገኘው ሮያል
ቤተ መጻሕፍት ውስጥ 150፣ አብዛኞቹ በመቅደላ ወረራ
ጊዜ ከኢትዮጵያ የተዘረፉ እጅግ ውብና ጥንታዊነ የሆኑ
የሥነ ጽሑፍ
ቅርሶቻችን ይገኛሉ፡፡ እነዚህን ጥንታዊ ብራናዎች ለማየትም ሆነ ለመመርመር ከንግሥቲቱ ዘንድ
ልዩ ፈቃድ
እንደሚያስፈልግ ምሁራን ያስረዳሉ፡፡
በእርግጥ ፈረንጆቹ ሰርቀውም ሆነ ገዝተው ወይም
በስጦታ አግኝተው ወደ ሀገራቸው የወሰዷቸውን ጥንታዊ የሥነ ጽሑፍ ቅርሶችን በክብር በማስቀመጥ፣ በመንከባከብ፣ በልዩ
ጥንቃቄ በሳይንሳዊ መንገድ አጥንተውና አስጠንተው ለዓለም ማስተዋወቃቸው አልቀረም፡፡በእጃችን የሚገኙ ጥንታዊ የሥነ ጽሑፍ ቅርሶችን አያያዝና አጠባበቅን፣ እንዲሁም ያሉበትን ሁኔታ
የታዘቡ ሰዎች
አንድ አበክረው የሚሉት ነገር አላቸው፡፡ ይኸውም ለታሪካችንና ለቅርሶቻችን ክብር፣ ዋጋና
ጠቀሜታ ምን
ያህል መሆኑ
በቅጡ እስኪገባን ድረስ እነዚህ በተለያዩ ጊዜያትና አጋጣሚዎች ከአገራችን የወጡ ብርቅዬና ውድ
የሆኑ ቅርሶቻችን በሚገኙበት ውጪ አገሮች እንዳማረባቸው ተጠብቀውና ተከብረው ቢኖሩ ይሻላል በማለት አስተያየታቸውን ይሰጣሉ፡፡
ባለቤት የሌላት ሀገርና ቤተ ክርስቲያን ፤ ተቆርቋሪና ተንከባካቢ የሌላቸዉ የሀገር ቅርሶች። እጅግ ራስ ወዳድና ለእኔ ካልሆነ በስተቀር ሳር አይብቀልብሽ የሚሉ ከዚች ቅድስት ሃገር የበቀሉ ይሁዳዎች የበዙበት ዘመን።
ReplyDeleteያባቶቻችን አምላክ ልብ ይስጣቸው፤ ሃገራችንና ቤተክርስቲያናችንን በቸርነቱ ይታደግልን አሜን።
አሜን!
ReplyDelete