Monday, December 9, 2013

በዋልድባ ላይ ለሚሰራው የሥኳር ፕሮጀክት ነዋሪዎች መነሳት ጀመሩ



የቆራሪት ከተማ
(አንድ አድርገን ታህሳስ 01 2006 ዓ.ም)፡- በሀገሪቱ ሰሜናዊ ክፍል በዋልድባ ገዳም ላይ ለሚገነባው የስኳር ልማት ፕሮጀክት በመጀመሪያ ዙር 1800 አባወራዎች ከቦታቸው መነሳታቸው ታወቀ፡፡ ለተነሱ አርሶ አደሮቹ 127.5 ሚሊዮን ብር የካሳ ክፍያ ተሰጥቷል፡፡ ለእነዚህ ተነሺዎች ከወራት በፊት የገጠር ከተማ መልክ በመያዝ በተገነባችው የቆራሪት ከተማ ላይ የማስፈር ስራ ተከናውኗል ፡፡ ለዚች ከተማ ምስረታ ምክንያት ደግሞ በዋልድባ ገዳም ላይ የሚሰራው የስኳር ልማት ፕሮጀክት መሆኑ ታውቋል፡፡ በአሁኑ ሰዓት ከቦታው የተነሱት 1800 ነዋሪዎች ከወልቃይት ወረዳ ፤ ከቃሌማ እና ፅምሪ ቀበሌ ይኖሩ የነበሩ አርሶ አደሮች ናቸው፡፡ መንግሥት እንደሚለው ለእነዚህ የልማት ተነሺዎች ለተነሱበት ቦታ በምትኩ የእርሻ ፤ የመኖሪያ  ቤት ፤ ሙሉ የቤት እና የሰብል ካሳ ክፍያ ፈጽሜያለሁ ብሏል፡፡ ለአርሶ አደሮቹ ነዋሪዎች መንግሥት 127.5 ሚሊየን ብር ካሳ መስጠቱ ታውቋል ፤ በሁለተኛ ዙር የሰፈራ ፕሮግራሙ ላይ 4ሺህ ሰዎች ከቦታው ይነሳሉ ተብሎ ይጠበቃል፡፡ ሰፈራው የሚቀጥል ሲሆን ለሚነሱት ከ13 ለማያንሱ አብያተ ክርስቲያናት ምትክ አዳዲስ ቤተክርስቲያን በቆራሪት ከተማ መሰራት መጀመራቸውን ለማወቅ ተችሏል፡፡
የዚህ ፕሮጀክት እሳቤ መነሻው 1991 ዓ.ም ቢሆንም አሁን ላይ ግን ወደ እውነታው እየተቃረበ ያለ ይመስላል ፤ ከዓመት በፊት ብዙ ሲያነጋግር የነበረው ይህ የሥኳር ፕሮጀክት አሁን ላይ የቁርጥ ቀኑ የቀረበ መስሏል ፤ መንግሥት ገዳሙን አልነካሁም በማለት አይኔን ግንባር ያድርገው እያለ ቢምልም መሀላው እውነታው ሊደብቀው አልቻለም፡፡ ገዳማውያኑም የሚደርስባቸው መከራ ከቀን ቀን እየጨመረ መምጣቱ ከቦታው የሚገኙ መረጃዎች ያመለክታሉ ፤ ጥቂት የማይባሉት መከራውን በመቋቋም የሚመጣውን ነገር ሁሉ በጸጋ ለመቀበል በአቋማቸው ፀንተው አሁንም ድረስ ያሉ ሲሆን ፤ ጥቂት መነኮሳት ግን የመንግሥትን የአምስት አመት የእድገትና ትራንስፎርሜሽን እቅድ ከግብ ለማድረስ ቀን ከሌት ከመንግሥት ሹማምንት ጋር ዳገት ሲወጡ ቁልቁለት ሲወርዱ ተስተውሏል፡፡
የ2005 ዓ.ም በጀት ዓመት የሥኳር ኮርፖሬሽን ዓመታዊ አፈጻጸም ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በቀረበበት ጊዜ መንግሥት በበጀት እጥረት  የሰፈራ ፕሮግራሙን በአግባቡ ለማስኬድ እንቅፋት እንደሆነበት ሚኒስትሩ ለምክር ቤቱ ማቅረባቸው ይታወሳል ፤ ከዚህ በተጨማሪም ቦታው ድረስ በመሄድ ስራውን የሚያከናውን የተማረ የሰው ኃይል እጥረት እና ቦታው ላይ ረዥም ጊዜ አለመቆየት መቻልን ለፕሮጀክቱ መጓተት እንደ ሁለተኛ ምክንያት አቅርበው ነበር፡፡
አንድ አድርገን ከውስጥ ሰዎች ባገኝችው መረጃ መሰረት በአሁኑ ሰዓት ዋልድባ ላይ እየተሰራ ላለው የሥኳር ፕሮጀክት የወራት ዝምታ መንስኤው ባለሙያዎች ቦታው ላይ ይህን ሥራ ለመስራት ፍቃደኛ አለመሆናቸው መሆኑን ለማወቅ ችላለች፡፡ በተለያዩ ጊዜም ለሥራ ወደ ቦታው ያቀኑ ባለሙያዎች በራሳቸው ፍቃድ ስራውን ያለደመወዝ  እየለቀቁ መሆኑን ለማወቅ ተችሏል፡፡



እኛስ የኃያሉን የአምላክን እጅ እጠብቃለን

3 comments:

  1. እኛስ የኃያሉን የአምላክን እጅ እጠብቃለን, yes we are helpless except dropping our tears and see the power of God as He did a year before. Still some people are still with their rigid heart like the Ferraho who finally was sunk in the Red Sea river. Let them have a repenting heart and learn from others.

    ReplyDelete
  2. ባለቤት የሌላት ሀገርና ቤተ ክርስቲያን ፤ ተቆርቋሪና ተንከባካቢ የሌላቸዉ የሀገር ቅርሶች። እጅግ ራስ ወዳድና ለእኔ ካልሆነ በስተቀር ሳር አይብቀልብሽ የሚሉ ከዚች ቅድስት ሃገር የበቀሉ ይሁዳዎች የበዙበት ዘመን።
    ያባቶቻችን አምላክ ልብ ይስጣቸው፤ ሃገራችንና ቤተክርስቲያናችንን በቸርነቱ ይታደግልን አሜን።

    ReplyDelete
  3. አንድ አድርገኖች "ሰፈራው የሚቀጥል ሲሆን ለሚነሱት ከ13 ለማያንሱ አብያተ ክርስቲያናት ምትክ አዳዲስ ቤተክርስቲያን በቆራሪት ከተማ መሰራት መጀመራቸውን ለማወቅ ተችሏል፡፡" ማለት ምን ማለት ነው ?

    ReplyDelete