Tuesday, December 24, 2013

በኩክ የለሽ ገዳም ሁከት የፈጠረው የኤልያሳውያን ተከታይ በገንዘብ ተቀጣ



(አንድ አድርገን ታህሣሥ 16 2006 .)- አቶ አበበ ነጋሽ የሚባል ሰው በደብረ ብርሃን በምትገኝው ኩክ የለሽ ገዳም ውስጥ ትውልድ አልቋል› ፤ ‹8ተኛው ሺ ደርሷል› ፤ ‹ትውልድ ሊቀጠፍ ነው› ፤ ‹ኤልያስ ወደ ምድር ወርዷል› ብሎ ሲሰብክ ተይዞ ‹የሌላ ሃይማኖት ተከታይ ሆኖ ሳለ በኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን ገዳም ስብከት በማከናወንና የሃይማኖት ተከታዮች ውስጥ ሁከት በማነሳሳት›› እና ተያያዥ ክሶች ቀርበውበት ደብረ ብርሃን ፍርድ ቤት መቅረቡን መዘገባችን ይታወሳል፡፡ ይህ ሰው በወቅቱ ሃይማኖታዊ ስነሥርዓቱ እንዲታወክ እና ረብሻ እንዲፈጠር አድርጎ ነበር፡፡ ከቦታው በደረሰን መረጃ መሰረት አቶ አበበ ነጋሽ ላይ የተመሰረተው ክስ የተመለከተው ፍርድ ቤት ጥፋተኝነቱን በማረጋገጥ ባሳለፍነው ሳምንት በእስር የቆየባቸውን 40 ቀናት ከግምት ውስጥ በማስገባት የአንድ ሺህ ብር የገንዘብ ቅጣት ፈርዶበታል፡፡
“የማህበረ ስላሴ ዘደቂቀ ኤልያስ” ማህበር አባላት አሁንም ድረስ ከፌደራል ጉዳዮች ሚኒስቴር ሕጋዊነቱን የሚያረጋግጥና በመንግስት ዘንድ እውቅና ያለው የእምነት ተቋም ሳይሆን ስሙን ከመሬት በማንሳት በኦርቶዶክስ ተዋሕዶ አብያተክርስቲያናት እና ገዳማት ላይ አስተምህሯቸውን ለመጫን እየሰሩ ይገኛሉ፡፡ በአሁኑ ሰዓት በባለፉት ሦስት ዓመታት በሰሩት ስራ ባፈሯቸው ጭፍራዎቻቸው አማካኝነት ጊዜን እየጠበቁ በየቦታው ሁከት እያስነሱ ይገኛሉ፡፡ ቤተክርስቲያኒቱ እነዚህ ሰዎች በተለያዩ ቦታዎች ላይ እያደረሱት ያለውን ጉዳት ከግምት ውስጥ በማስገባት በሕጋዊ መንገድ የምትጠይቅበት ምዕመኑንም ከውዥንብር የምትታደግበት ጊዜ እስኪመጣ ድረስ ሁሉም በያለበት እነዚህን ሰዎች ሊቃወማቸውና ከተቻለም እንደ ደብረ ብርሃን ወጣቶች ከነሥራቸው ወደ ፍርድ አደባባይ ሊያቀርባቸው ይገባል እንላለን፡፡

እግዚአብሔር ቤተክርስቲያንን ይጠብቅልን

No comments:

Post a Comment