ከሚካኤል ጎርባቾቭ
- በነገረ ድኅነት፣ በነገረ ማርያምና በሥርዓተ ቤተ ክርስቲያን ላይ ሲነገሩ የነበሩትን የሰውዬውን ስህተት ችላ በማለት በይቅርታ ለማለፍ ብቻ ከተሞከረ ሃይማኖታዊ ለዘብተኛነት ከአባቶቻችን እየተማርን መሆኑ መዘንጋት የለበትም
- የኢትዮጵያ የቤተ ክርስቲያን ታሪክ ውስጥ ሃይማኖታዊ ስህተት ተገኝቶበት በይቅርታ የታለፈ አንድም ሰው የለም
(አንድ አድርገን ታህሣሥ 15 ፣ ታህሳስ 06 2006 ዓ.ም)፡- ይሄ ሰው በቤተ ክርስቲያን መድረክ ላይ እንዳሻው እንዲሆንና ብሎም በማወቅም ይሁን ባለማወቅ አንዳንድ ምዕመናን እንዲከተሉት ዕድልን ያገኘበት ሁለት ወሳኝ አጋጣሚዎች ነበሩት፡፡ የሰውዬው ታሪክም ከዚህ የሚጀምር ይሆናል፡፡ የመጀመሪያው ምርጫ 97ን ተከትሎ ቅንጅት በብዙኋኑ ሕዝብ ዘንድ ተዓማኒነት ማግኘቱና ሕዝቡም ገዢውን ፓርቲ ኢህአዴግን /መንግሥትን/ ተቋዋሚ በመሆኑ ወቅታዊውን ሀገራዊ ትኩሳት ተገን በማድረግ የቤተ ክርስቲያኒቱ ልጆችም እንደ ዜጋ የድጋፉና የተቃውሞው አካል መሆናቸውን ሰውዬው በመረዳቱ የአብዛኛውን ሕዝብ ስሜት የተከተለ የመንግሥት ተቃውሞን ማሰማቱ ነው፡፡
ሌላኛውና ዋነኛው ሰውዬው በምዕመኑ ዘንድ ተቀባይነትን እንዲያገኝ ዕድል የፈጠረለት አጋጣሚ ደግሞ የቤተ ክህነቱ ብልሹ አሠራርን ደካማነት በማጉላትና የቀድሞው 5ኛ ፓትርያርክ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ጳውሎስ ከመንፈሳዊነት ይልቅ ፖለቲካዊነቱ የሚበዛን ተግባር መፈጸማቸው ሕዝበ ክርስቲያኑን ያስቆጨው የነበረ መሆኑን የተረዳው ሰውዬ አጋጣሚውን ተጠቅሞበታል፡፡ በወቅቱ የቅድስት ሥላሴ መንፈሳዊ ኮሌጅ መደበኛ ተማሪ የነበረው ይህ ሰው የምርጫ 97ን ቅንጅታዊ ማዕበል በመደገፍና አቡነ ጳውሎስን በመቃወም ከመሳዮቹ ጋር በመሆን ወደ ሕዝብ ዘንድ ገባ፡፡ በዚህም ተግባሩ ከኮሌጁ የተባረረና ይቅርታን ጠይቀው ወደ ኮሌጁ እንዲመለሱ ተብለው አሻፈረኝ ያለ፤ ይህም ባይሆን ከሊቃውንተ ቤተ ክርስቲያን ጠጋ ብሎ የነገረ ሃይማኖት ዕውቀትን ያላስኬደ ዛሬም ድረስ ያለተማረ ባለ “ማዕረግ” ሆኖ ይኖራል፡፡ አቶ በጋሻው ደሳለኝ፡፡
ነገሩን እንዲህ እናቅልልለትና ….. ከላይ ያነሳሁትን ለሰውዬው ዕድል የሰጡትን ሁለት አጋጣሚዎች ትክክል ነበሩ ብለን በወቅቱ በነበረው ትኩሳት መጠን እናስብና ማለትም የአብዛኛው ሕዝብ ስሜት ናቸውና /በነገሬ ላይ…. የብዙኋኑ ድምፅ ሁሌም ትክክል ይሆናል ማለት ግን እንዳልሆነ ልብ በሉልኝ፡፡ ለአብነትም ያህል የብዙዎችን ፍላጎት የተከተለው ካህኑ አሮን ለማኅበረ እሥራኤል ጣዖትን አቆመ፤ የብዙዎችን ስሜት ያደመጠው ንጉሥ ጲላጦስ ክርስቶስ ተላልፎ እንዲሰጥ አደረገ/፡፡ ንግባዕኬ ኀበ ጥንተ ነገር /ወደ ቀደመው ነገራችን እንመለስ/ …. ስለዚህም የአብዛኛውን ሕዝብ ስሜት ተከትሎ አቶ በጋሻው የሕዝብ ድጋፍ አገኘ፡፡ መንግሥትን ተቃወመ፤ አባ ጳውሎስን ሰደበ፡፡ አሁን አላዋቂው ሰው ታዋቂ ሊሆን ጀመረ፡፡ የሕይወት ስብከት ብሎ በቅርቡ ካወጣው “ጥቁር ነኝ፤ ነገር ግን ውብ ነኝ” እስከሚለው ስብከቱ ድረስ የተለያዩ ስብከቶችን ለገበያ አቅርቧል፡፡ (በዚህ ርዕስ ከዚህ ቀደም በዲ/ን ዳንኤል ክብረት የተሰበከ ስብከት መኖሩን ልነግራችሁ እወዳለሁ)፡፡ ሰውዬው የሚኮርጅ እንጂ የሚኮረጅበት አለመሆኑን ከዚህ በፊትም ባሳተማቸው ካሴቶቹ መረዳት ይቻላል፡፡ በተለይም ከፕሮቴስታንት ሰባኪያን ትምህርቶችና የአነጋገር ዘይቤዎች የተቀዳ ነገር የሚበዛበት ኮራጅ ሊቅ መሆኑን አስመስክሯል፡፡ በርካታ የሆኑ የመዝሙር ግጥሞቹና ዜማዎቹም ቢሆኑ መገኛቸው የካህኑ ያሬድ ሳይሆኑ ምንጫቸው የታወቁ ነበሩ፡፡
ይህ ሰው በምስጢራተ ቤተ ክርስቲያን፣ በነገረ ድኅነት፣ በነገረ ማርያም፣ በሥርዓተ ቤተ ክርስቲያንና በግብረ ገብነት ላይ በርካታ ጥያቄዎችን የፈጠሩና ከቤተ ክርስቲያን ወገን ያልሆኑ ሐሳቦችን እንደልቡ ሲናገርም ቆይቷል፡፡ የቤተ ክርስቲያንን ትምህርተ ሃይማኖት በተሐድሶ መናፍቃን መንገድ ለመውሰድ ሞክሯል፡፡ ምዕመናንን በመከፋፈል፣ ካህናትን በመሳደብ፣ ሰንበት ት/ቤቶችንና ማኅበራትን በማጋጨት ለቆመለት ዓላማ ታግሏል፡፡ ከውጪ ሆነው ወደ ውስጥ ለሚገፉት አካላት ማንነቱን ሲያስመሰክር፣ ከውስጥ ላሉ የበግ ለምድ ለባሾች ደግሞ አውራ በመሆን አገልግሏል፡፡
ይሄ ሰው ገና ከጅምሩ በመንፈሳዊ ቅናትና ለቤተ ክርስቲያን በመጨነቅ የተነሳ ቢሆን ኖሮ የዛሬ ማንነቱ የትላንት ሰውነቱን አይገልጥበትም ነበር፡፡ …… ይሄ ጥያቄ በምዕመናን አዕምሮ ውስጥ ሁሉ እንዲመጣ አስባለሁ፤ ….ትላንት በጋሻው ቤተ ክህነቱን በማቃለል አቡነ ጳውሎስን ለምን ሰደበ? ፤ በኋላስ በጋሻው የአንጋፋው ድምፃዊ ሙሀሙድ አህመድን የቀድሞ ሚስት ወ/ሮ እጅጋየሁንና ግበረ አበሮችን አማላጅ በመያዝ ከፓትርያርኩ ጋር ለመታረቅ ለምን አሰበ? እንዲያውም ለዕርቁ እጅ መንሻ እንዲሆን ቦሌ መድኃኔ ዓለም ቤተ ክርስቲያን ግቢ ውስጥ አቡነ ጳውሎስ በሕይወት እያሉና ምዕመናንን ያስቆጣውን ሐውልት ሥራ እስከማሰራትስ ለምን ደረሰ?፡፡ በወቅቱ የመስቀሉ ሥር ቁማርተኞች እያለ ሲሰድባቸው የነበሩትን አቡን ኋላ ላይ “ሰማዕት እንበለ ደም” እያለ ለማሞገስስ ምን አነሳሳው? ……ምናልባትም አቡነ ጳውሎስን ሰድቦ የሰው ድጋፍ አግኝቷል፡፡ ነገር ግን በቤተ ክርስቲያን ዐውደ ምኅረት ላይ እንደፈለገው ለመሆን ረጅም ጉዞ እንደማያስኬደው ተረድቷል፡፡ በጊዜውም የአጉራ ዘለል ሰባኪያን አጀንዳ የቤተ ክህነት ከመሆኑም አልፎ የቤተ መንግሥት አጀንዳ መሆኑ አሳስቦታል፡፡ ስለዚህም አቡነ ጳውሎስን ይቅርታ መጠየቅ አስፈላጊ ሆኖ ስላገኘው እንጂ እሱ አስቀድሞ እንዳለውና እንደሰደባቸውም አባ ጳውሎስ በፍጹም መንፈሳዊ አባትነት ከፖለቲካው ርቀው ሕዝበ ክርስቲያኑን ስላስደሰቱት አይደለም፡፡ ከሥርዓተ ቤተ ክርስቲያን ውጪ ሆነዋል ሲላቸው የነበሩትን ፓትርያርክ፣ ከሥርዓተ ቤተ ክርስቲያን ውጪ ሐውልት ሲቆምላቸው “ሰማዕት እንበለ ደም” እያለ ከጀሌዎቹ ጋር ባላወደሳቸውም ነበር፡፡ ለዓላማው መሳካት መንገድ እንዲጠርግለት እንጂ፡፡
በሌላውም መልክ በጋሻው ከአነሳሱ ምርጫ 97 ላይ የቅንጅትን አካሄድ የደገፈና የመንግሥትን ተግባር በመቃወም ድምጹን ያሰማ ሰው ነበር፡፡ በኋላ ግን አዋጪውን መንገድ በመምረጡ አልተቀደመም፡፡ በተለያዩ ቦታዎች ላይ ከቤተ ክርስቲያን አካላትና ምዕመናን ለገጠመው ፈተና የመንግሥትን ጡንቻ መጠቀም እንደሚገባም በተግባር ሞክሮ አሳይቷል፡፡ ከዚህ ሲያልፍም “ተሐድሶ” የሚለውን ቃል በሃይማኖት ቋንቋ ሳይሆን በፖለቲካዊ ትርጉም አቀነባብሮ የመንግሥትን ድጋፍ ለማግኘት ጥሯል፡፡ መንግሥት ይህን ቃል በተረዳው መጠን የሚፈልገው ነውና፡፡ ስለዚህም በጋሻው ጊዜውን መስሏል፡፡ የቆመለት ዓላማ ግቡን እንዲመታ የመጣበት ስልትን ልብ ይሏል፡፡ በዚህ ሁኔታ ነገሮች መቀጠል የቻሉት ግን ጊዜው እስከፈቀደላቸው ወቅት ድረስ ነበር፡፡ ጊዜው ሲደርስ ግን ነገሮች መለወጥ ጀመሩ፡፡ የአጉራ ዘለል ሰባኪያን ጉዳይ መሥመር እየሳተ መጣ፡፡ የአቶ በጋሻው የምንፍቅናና የተሐድሶ ትምህርትና አካሄድ ጫፍ እየያዘ፣ የሰውዬውም ድፍረት በእጅጉ እየጨመረ መጣ፡፡ ጨዋው ባለ ማዕረግ (ጨዋ በቤተ ክህነት አነጋገር ያልተማረ እንደማለት ነው) ግልጽና ቀጥተኛ የሆኑ እንግዳ ትምህርቶችን በጽሑፎቹ፣ በስብከቶቹና በመዝሙር ግጥሞቹ ማሰራጨቱ ጎልቶ ታየ፡፡ የዜማ ድርሰቱም ቢሆን ከዓለማዊያን የዘፈንና ከፕሮቴስታንት የመዝሙር ዜማ የተቀዱ ነበሩ፡፡ ለአባቶችና ለምዕመናን የነበረው ንቀትና ራሱን ያስቀመጠበት ከፍታ ለየቅል ሆኑ፡፡ ሁከትና ብጥብጥን በቅድስት ቤተ ክርስቲያን ማስፋፋቱን ተያያዘው፡፡ ለታዋቂነት እንጂ ለዐዋቂነት ቦታ ያልነበረው ይህ ሰው ከተሐድሶው ዓለም የወረሰውን አካሄድ በማን አለብኝነት ሲዘራ ከቆየ በኃላ ግን ሁኔታው የፈጠረውን እሳት ለማስቆምና አደብ ለማስያዝ ምዕመናን፣ ሰንበት ት/ቤቶች፣ ማኅበራት፣ ካህናትና የአገር ሽማግሌዎች እንዲሁም የመንግሥት አካላት ባሳደሩት ጫና ቅዱስ ሲኖዶስ ጉዳዩን በማጤን በ2004 የግንቦቱ ስብሰባ ተቀመጠ፡፡
በስብሰባውም ቅዱስ ሲኖዶስ ባደረገው ማጣሪያና በቀረበው መረጃ መሠረት በሌሎች የተሐድሶ መናፍቃን ላይ ውሳኔ ሲያስተላልፍ የአቶ በጋሻው ጉዳይ ግን ያልተሟላ መረጃ አለ በሚልና ሰውዬውም ተጠርቼ ሀሳቤን አልተጠየኩም በማለቱ የተነሳ ለ2005 የጥቅምቱ ስብሰባ ተቀጠረ፡፡ ይህ ሳይሆን ግን በመሐል ነሐሴ 2004 ላይ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ጳውሎስ ከዚህ ዓለም በሞት ተለዩ፡፡ የ2005ቱም የጥቅምቱ የቅዱስ ሲኖዶስ አጀንዳም አዲስ ፓትርያርክ መምረጥ ላይ ትኩረቱን አደረገ፡፡ ዕድል ወደ መድረክ ያመጣው በጋሻውም ዕድለኛ ሆነና በቀጠሮው ጉባኤ የእሱ ጉዳይ በአጀንዳነት ሳይታይ ከዛም በኃላ ሁለት የቅዱስ ሲኖዶስ ጉባኤዎች ተደርገው አለፉ፡፡ አሁን የአዲሱ ፓትርያርክ ሢመት የተደላደለ ይመስላል፡፡ መንፈቅ አልፎታልና፡፡ ስለዚህም ያለፉ አጀንዳዎች መነሳታቸው አይቀሬ ይሆናል፡፡ ይሄም በጋሻው በሥጋት የሚጠብቀው ጉዳይ ብቻ ሣይሆን ምዕመናንም ጭምር ተገቢውን ውሳኔ የሚጠብቁበት አጀንዳ ነው፡፡ ለዚህም ይመስላል አቶ በጋሻው ጉዳዩ በይቅርታ ቀድሞ እንዲዘጋ አቋራጭ መንገድ የመረጠው፡፡ ዘማሪት ፋንቱ ወልዴን ጨምሮ ብፁዓን አበው በተገኙበት የዕርቅ ጉባኤ ተብሎ በአዋሳ ደብረ ምኅረት ቅዱስ ገብርኤል ቤተ ክርስቲያን መከናወኑም ተሰምቷል፡፡
ከላይ እንደተመለከትነው በጋሻው ከቅድስት ሥላሴ ኮሌጅ ከተባረረ በኋላ ፓትርያርኩን ጨምሮ ሲሳደባቸው የነበሩትን አካላት ይቅርታ ጠይቆ ወደ ትምህርቱ እንዲመለስ ሲጠየቅ አሻፈረኝ ያለ ሲሆን፤ ከቆይታ በኋላ ደግሞ ወቅታዊ ሁኔታዎች እሱ በፈለገው መልኩ እንዲፈነጭ ዕድል ስላልሰጡት አቡነ ጳውሎስን ይቅርታ ለመጠየቅና እስከማሞጋገስ በቅቷል፡፡ ሆኖም የእሱና የግብረ አበሮቹ የአጉራ ዘለለ ሰባኪነትና ዘማሪነት ጫፍ እየያዘ ሲመጣና ለተሐድሶ መናፍቃን በርን ሲከፍት ከየአቅጣጫው ያሉ የቤተ ክርስያን አካላት ባደረጉት ተጋድሎ በጋሻውና ቡድኑ ቅዱስ ሲኖዶስ ውሳኔ እስኪሰጥባቸው ድረስ ከማንኛውም መንፈሳዊ አገልግሎት እንዲታገዱ ተደርጓል፡፡ ይህ ሲሆን ግን የቅዱስ ሲኖዶስን ውሳኔ በማያከብሩና የበጋሻውና የቡድኑ ደጋፊ በሆኑ አንዳንድ አካላት መድረክ ሊሰጧቸው ሞክረዋል፡፡ ራሱም ሆነ ቡድኑም ቢሆን ለቅዱስ ሲኖዶስ ውሳኔ ተገዢ ባለመሆን የተለያዩ የስብከትና የመዝሙር ካሴቶችን አውጥተዋል፡፡ በኢቢኤስ የቴሌቪዥን ጣቢያም አሁንም ድረስ የሚታየው አጉራ ዘለልነታቸው አልቆመም፡፡ ሆኖም ግን ራሱን ከሚገባው በላይ ያመጻድቅ የነበረው እንደበፊቱ የምዕመኑን ጭብጨባና ዕልልታ አላገኝም፡፡ ስለዚህም ሌላ ስልት ይዞ መምጣት አማራጭ የማያሻው ተግባሩ ሆነ፡፡ አቡነ ገብርኤልንና የአዋሳ ምዕመናንን ይቅርታ መጠየቅ፡፡ በነገሬ ላይ … ይቅርታ መጠየቅና ይቅርታም ማድረግ ተገቢና ፍጹም መንፈሳዊ የሆነ ተግባር ሲሆን ከብፁዓንነት ደረጃም የሚያደርስ ሃይማኖታዊ ምግባር ነው፡፡ ነገር ግን የአቶ በጋሻውና ጓደኞቹ ይቅርታ ጠያቂነት አጋጣሚና ሁኔታዎችን እየጠበቁ ለራስ አካሄድ እንደሚመች የሚያደርጉት መሆኑን ካሳለፈው የሰውዬው ህይወት ለማየት ችለናል፡፡
በመሠረቱ በአዋሳ ቅዱስ ገብርኤል ቤተ ክርስቲያን የተደረገው የዕርቅ ጉባኤ ተገቢውን ቀኖናዊ አካሄድ ያልተከተለ ከመሆኑ ባሻገር በማወቅም ይሁን ባለማወቅ እነበጋሻውን ተከትለው የወጡ የቤተ ክርስቲያን ልጆችን ለመመለስ መልካም አጋጣሚ ሊሆን እንደሚችል ይታሰባል፡፡ ይህ ቢሆንም ግን በይቅርታ ብቻ የማይታለፉ በርካታ የሰውዬው ሃይማኖታዊ ሕፀጾች አሉ፡፡ እነዚህ ሕፀጾች ደግሞ የእምነት ተሐድሶን የሚያመጡና ምንፍቅናም ጭምር ናቸው፡፡ ይህም በተጨባጭ መረጃ ውሳኔ የሚተላለፍባቸው የቅዱስ ሲኖዶስ አጀንዳዎች ሆነው የተያዙ ናቸው፡፡ ታዲያ ይህ ጉዳይ ከይቅርታ በላይ ነው፡፡ ሃይማኖት ነው፡፡ ቀኖናዊ ውሳኔ የሚገባው ነው፡፡ የዚህ ሰው ጥፋት ስህተት አንድ በአንድ እየተዘረዘረ ለምዕመኑ ሳይነገር ውሳኔም ሳይሰጥ ምን አደረገ ተብሎ ነው እንዲሁ በመሸፋፋን ይቅርታ የሚደረገው?፡፡ ከፈረሱ ጋሪው ይሏችኋል ይሄ ነው፡፡
ባሳለፍናቸው የኢትዮጵያ የቤተ ክርስቲያን ታሪክ ውስጥ ሃይማኖታዊ ስህተት ተገኝቶበት በይቅርታ የታለፈ አንድም ሰው የለም፡፡ ከእንዲህ ዓይነቱ ስህተት መመለስን የሚሻ ሰው ቢኖር ተገቢውን ሃይማኖታዊ ቀኖናና ውሳኔ በመስጠት ያንንም ከልቡ መቀበሉንና ተግባራዊ ማድረጉን በማረጋገጥ ሊታለፍ ይገባዋል፡፡ የአቶ በጋሻውም ጉዳይ በዚህ መልክ የሚታይ እንጂ ሌላ መሥመርን እንዳይከተል በትኩረት መከታተል ይገባል፡፡ ቀድሞ የዕርቅ ጉባኤ ተብሎ አዋሳ ላይ መደረጉ መልካም ነው ተብሎ ቢታሰብ እንኳ የተሐድሶ አካሄዱ፣ የቤተ ክርስቲያን ያልሆኑ እንግዳ ትምህርቶቹ፣ በድፍረትና በንቀት ያፈረሳቸው የቤተ ክርስቲያን ሥርዓቶች፣ ከጻፈው ጽሑፍ፣ ካሳተመው ካሴት፣ በመድረክ ካስተማረው፣ በመዝሙር ግጥምና ዜማ ከደረሰው ሁሉ ተጠቅሶ የአቶ በጋሻው ስህተት ይሄ ነበረ ተብሎ መገለጥና ለዚህም ጥፋቱ የቅዱስ ሲኖዶስ ውሳኔ ይሄ ነው መባል አሁንም ይኖርበታል፡፡ ይህ ባልሆነበት ወይም ይህ ሳይሆን ቢቀር ግን ማንም ደፋር እንደእሱ ብድግ እያለ ያሻውን በድፍረት እየተናገረ የቅዱስ ሲኖዶስን የውሳኔ አፈጻጸምና ብቃት ጥያቄ ውስጥ እንዲከት ሲያደርገው የቅድስት ቤተ ክርስቲያንንም ክብር የሚነካ ይሆናል፡፡
በሌላውም በኩል በእነ በጋሻው እብሪት የተጎዱ ምዕመናንና የባከኑ የአገልግሎት ጊዜያት እንዲሁም የተከፈሉ መሥዋዕቶችን ዋጋቢስ ማድረግም ነው፡፡ ከምንም በላይ ደግሞ በነገረ እግዚአብሔር፣ በነገረ ድኅነት፣ በነገረ ማርያምና በሥርዓተ ቤተ ክርስቲያን ላይ ሲነገሩ የነበሩትን የሰውዬውን ስህተት ችላ በማለት በይቅርታ ለማለፍ ብቻ ከተሞከረ ሃይማኖታዊ ለዘብተኛነት ከአባቶቻችን እየተማርን መሆኑ ነው፡፡ ስለዚህም አበው ሊቃነ ጳጳሳት፣ ካህናትና ምዕመናን ቆም ብለው ሊያስቡበት ይገባል እላለሁ፡፡ ምክንያቱም በይቅርታ የሚታለፍ ተሐድሷዊነት ወይም ምንፍቅና በቤተ ክርስቲያን ታሪክ ውስጥ የለምና፡፡ ታይቶም ተሰምቶም አይታወቅምና፡፡ ዳሕፀ ልሳን ካልሆነ በቀር፡፡
perfect description.God bless you.
ReplyDeletetebarek
ReplyDeleteእርቅ የሚጠላ ዲያቢሎስ ብቻ ነው አፈርኩባችሁ
ReplyDeleteEgziabhear feraj neaw, ke alkaida gar endemnm manekakat neaw yekerachu. Edilegna neaw ende Kirstean, diabilos gin liayew endaemayfelg enji lelaw ende seaw yetedegageme mikneat neaw. Egziabhear Tsadk neaw ye hulunm Lib, andebet, tsihuf,.. Yemeremral, ...
ReplyDeleteቃለ ህይወት ያሰማልን
ReplyDeleteየቤተክርስቲያን፡ ቀኖና፡ ይጠበቅ።
ቸሩ፡ አምላካችን፡ ማስተዋልን ፡ ያድለን።
አሜን።
asgerami new yihin yaderegu sewoch yetarik tewekashoch nachew
ReplyDeleteperfect description.God bless you.
ReplyDeleteBewnet egzabeher lebonawen yemleselet my heart was bern!
ReplyDeletesew lemen wedebetkerstian agelegelot temelse belo yehie hulu kenate gieta yeker yebeleh.
ReplyDeleteአትፈር ።የቤተክርስትያን የእርቅ አይነቶች ሳይገባው ፣ወይም እየተረዳው ፣ምንተ ግዲ በማለት ከነ ዲያብሎሳዌ ሥራው ይቅርታ መጠየቅ ፣ቆም፣ ተብሎ ከታየ ለዳግም ጥፋት ሌላ የቤተክርስቲያኗ የበር መክፈቻ ቁልፍ ስጡኝ እንደማለት ይመስለኛል ። ስለዚህ ጉዳዩ ትኩረት ተስጥቶበት ፣ በሰነድወስ በኩል ቢያልቅ ለሁሉም ትምህርት ሰጭ ይሆናል ። የድንግል ልጅ በምህረት ይጓብኘን ።አሜን!
ReplyDelete