Monday, December 16, 2013

በጠወለገው የዘመናችን የሃይማኖት አባቶች ምግባር ፊት ፡- የአራቱ አባቶች ገድል


ከብርሀኑ ደቦጭ

(የቀድሞ የአዲስ ነገር ጋዜጣ ቋሚ ጸሐፊ እና የታሪክ ምሁር)
  • የሞራል ስብዕናቸው ምሣሌነት የሚያንሰው የዘመናችን የሃይማኖት አባቶችም ስለ ሃይማኖቱ መሪዎች የሚያደክመውን ብቻ በመስማት የተዳከመውን ምዕመናንን ዘወር ብለው ትላንትን እንዲመለከቱ በር የሚከፍት ነው፡፡
  • በግዕዝ የተጻፉትን  በአማርኛ እንድናገኛቸው በማድረጉ ባሻገር ራሳቸው ገድላት ያላቸውን ዋጋ እንድናስብና እንድንነጋገር አድርጎናል፡፡
  • ዲ/ን ዳንኤል ገድላቱን እንድናገኛቸው ያደረገ ብቻ ሳይሆን ከተለያዩ ምንጮች ባሰባሰባቸው መረጃዎች አማካኝነት የምናውቃቸውን አካባቢዎች ፤ በምናውቃቸው ማሳያዎችና ፤ በታወቁ ማመሳከሪያዎች ወደ ተጨባጭ ዕውቀት ለመቀየር ያደረገው ጥረት ጥሩ ነው፡፡
  • በሸዋ እና በትግራይ የነበረውን ግንኙነትና  ቅርበት ብዙ የሚያስታውስና  አሁን በተወሰኑ የሁለቱ አካባቢ ሰዎች  ነን የሚሉ ቀንደኞች የሚቀነቀነውን ልክ የለሽ ሽኩቻ ለመታዘብ ዕድል የሚሰጥ ነው፡፡
  • አቀራረቡ በዘመኑ የታሪክ ጥናት ያለብንን ክፍተት ለመሙላት የታሪክን የፊሎሎጂ ስነ ዘርፍ ጥናቶች የመተጋገዝን ጥቅም ልብ እንድንል ያደርገናል፡፡
  • በቤተክርስቲያን አካባቢ በሚፈጠሩ ችግሮች ዙሪያ አዘውትሮ ሃሳቡን ሲያካፍለን የቆየበት የእሱም ሆነ  ሌሎች ልፋት ብዙም ለውጥ ያመጣ ስላልሆነ የነዚህን ሰዎች ታሪክ በገድላቸው አማካኝነት  በመዘከር ፤ የሚጠብቀውን የሞራል ስነ-ልክ በማሳያ ያመላከተ ነው
  • የፕ/ር ጌታቸው ኃይሌን ጨምሮ በግርጌ ማስታወሻ የሚያነሳቸውና የሚከተላቸው ሙግቶች  ፤ ክርክሮችና ማስረገጫዎች ዲ/ን ዳንኤል  የነ ፕ/ር ታደሰ ታምራትን  ፈለግ ለመከተል የሚሻ መሆኑን ያመለክታሉ፡፡
  • ዲ/ን ዳንኤል ገድላቱን የተጻፉበት ምክንያት ከሃይማኖት አይን በዘለለ አለማየቱ ሌሎች ምክንያተ ጽሕፈቶችን ለመቃኝት ጥረት አላደረገም ፤ ስለዚህም ከተጠቀሱት አባቶች ታሪክ የዘለለ ፋይዳ ሲፈልግ አናይም፡፡
  • በየገድላቱ እንደ ተዓምራት የሚቆጥሩትን አማኞች እንዳለ ሊወስዱት ይችላሉ፡፡ በአንጻሩ ሌሎች ደግሞ መጽሐፉን የማንበብ ፍላጎታቸውን ሊፈታተን ይችላል፡፡
(አንድ አድርገን ታህሳስ 08 2006 ዓ.ም)፡- ዲ/ን ዳንኤል ከጋዜጦች ፤ መጽሔቶችና ድረ-ገጾች ያሰባሰባቸውን ጽሁፍ ያሳተመባቸውን መጻፍት ጨምሮ  በርካታ ስራዎችን  (በአብዛኛው በሃይማኖት ላይ  ያተኮሩ) ለህዝብ አቅቧል፡፡ በዚህም ምክንያት ይህንን ሁሉ በምን ጊዜ ሰርቶት  ነው የሚሉና የሚደነቁ አሉ፡፡ ከጋዜጣና መጽሔት ያሰባሰባቸውን  እየደጋገመ ማሳተሙ  ደስታ ባይሰጠኝም ፤ እኔም በዚህ ምክንያት  ከሚገረሙት መካል ነኝ ፡፡ በእርግጥ ከጋዜጣ እና መጽሔት  ወስዶ በማሳተሙ ተቆራርጦ  የወጣውን በአንድ ቦታ  እንዲገኝ የማድረግ  ፋይዳውን አልዘነጋሁም ፡፡ ለማንኛውም አዲሱን የዲ/ን ዳንኤል መጽሐፍን የጽሐፊው ልፋት ከመቼውም በበለጠ መሆኑንና  የሥራውም ዋጋ  የዛኑ ያህል  ከፍ ያለ እንደሆነ ለማስተዋል ችያለሁ፡፡ የዛሬው አጠቃላይ አስተያየቴ  በዚሁ መጽሀፍ ዙሪያ ይሆናል፡፡

መጽሐፉ ሁለት ክፍል አለው፡፡ አንደኛው(ከገጽ 13-114) አጠቃላይ ጉዳዮች በሚል ርዕስ  የቀረበው በዓምደ ጽዮንና ሠይፉ አርዕድ  ዘመን የነበረው የቤተክርስቲያን  ሁኔታ ፤  ቤተክህነትና ቤተ-መንግሥት በዐፄ አምደ ጽዮንና  በዐፄ ሰይፈ አርዕድ  ዘመን ፤ አምስቱ ጳጳሳት ፤ ካህናት ደብተራና ገዳማውያን  አባቶች ፤ የቅጣት አይነቶች  ፤ የመካከለኛው ዘመን መነኮሳት  ዋና ዋና እሴቶች  በሚል ርዕስ ታሪኩን ለመከተብ የተደረጉ ጥረቶች ውጤት ናቸው፡፡ ይህ የመጽሐፉ አጭሩ ክፍል ሲሆን  ታሪኩን ጨምቆ ለማውጣት  ከፍተኛ ጥረት የተደረገበትና አራቱ አባቶች  በኖሩበት ዘመን ስለነበረው አጠቃላይ  የቤተክርስቲያን ሁኔታ  ከላይ በተዘረዘሩት  አጫጭር ምዕራፎች  ርዕሰ ጉዳይ አንጻር የቀረበበት ነው፡፡ እንደ እኔ አይነት  ሙሉ ለሙሉ ማስታወሻ  እየያዘ  የሚያነበው የመጽሐፍ ዕፍታ ነው፡፡
ሁለተኛው ክፍል (ገጽ 115-435)  በዓምደ ጽዮንና  ሠይፈ አርዕድ  ዘመን የነበሩ አራቱ አባቶች ገድላት ትርጉም የያዘ ነው፡፡  የገድላቱ ትርጉም  ለየአቡኑ ካሏቸው  ምልከታዎች  ዲ/ን ዳንኤል በዘረዘራቸው ምክንያቶች  የመረጣቸው ሲሆኑ ፤ በሌሎቹ ምልከታዎች  የተለየ ነገር ካለ  በግርጌ ማስታወሻ  እያጣቀሰ  ልዩነቱን  በማመልከት  በመጽሐፉ የተሟላ መረጃ የቀረበበት ነው፡
በአጠቃላይ ሁለቱ ክፍሎች  በአፈጣጠራቸው የታሪክ ፊሎሎጂ አቀራረብን  የያዙ ናቸው ማለት ነው፡፡ የገድሉ ትርጉም ሌሎች  ከዚህ በፊት  በዚህ ረገድ ቅድምና የሚወስዱትን የሚያስታውስ ቢሆንም  የዲ/ን  ዳንኤል አስተዋጽኦ  ከፍተኛ የሚያደርገው  አንድም ታሪኩን የሚነካው ክፍል አንድ ነው፡፡ ሌላው የትርጉም ክፍል የአራቱ አባቶች ገድላት የአንደኛው መጽሐፍ ፍልሰቱ ተጨምሮበት  በአንድ ላይ መተርጎሙ ነው፡፡  አቀራረቡ ምንጮችን በዕለት ተዕለት ቋንቋ ለፈለገው ሁሉ የሚዳረስበት  መልኩ የማዘጋጀት አካሄድ ነው፡፡ እንዲህ አይነቱን ለታሪክ ጥናት እጅግ ጠቃሚ የሆነ ሥራ በአግባቡ የሚያካሄደው ተቋም ባለመኖሩ  የዲ/ን ዳንኤል አስተዋጽኦ ከፍተኛ ዋጋ ያለው ነው፡፡ እንደ እምነቱ ተከታይም ዲ/ን ዳንኤልን ቤተክህነቱ ሊያስብበት የሚገባው ጉዳይ  ባለማድረጉ  የሚያካክሱ እርምጃዎችን በግል እየወሰዱ ስላሉ ሰዎች ከዋና ዋና ማሳያዎች አንዱ አድርገን እንድንወስደው የሚያደርግ ነው፡፡
የግዕዝ ምንጮችና የገድላት ዋጋ
የግዕዝ ምንጮች ወደ ተለያዩ ቋንቋዎች መተርጎም በአብዛኛው በውጭ ሰዎች የሚደረግ ተግባር ነው፡፡ ከእነዚህ የግዕዝ ምንጮች  መካከል የነገሥታቱ ዜና መዋዕልና ገድላት ይኙበታል፡፡ ለሕዝብ የማዘጋጀት ሙከራ ቢኖርም እዚህም እዚያም የተበጣጠሰ ሙከራ እንጂ የተቀናጀ አይደለም፡፡ አልፎ አልፎ በትንሳኤ ማተሚያ ቤት የታተሙ ቢኖሩም በተቋም ደረጃ  የኢትዮጵያ ኦርዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን  የእነዚህ ገድላትና ዜና መዋዕል አስቀማጭና ባለቤት ብትሆንም ተርጉሞ ለማቅረብ ብዙም አለመትጋቷን  ማስታወስ ይገባል፡፡ በብሔራዊ ደረጃም በአቶ አለሙ ኃይሌ አማካኝነት የቅርስ ምርምርና ማዕከላዊ ዶክመንቴሽን መምሪያ ዜና መዋዕሎችን ለማሳተም ቢሞክሩም ከዚያ የገፋ እንቅስቃሴ አልተደረገም፡፡ 
የታሪክ ምሑራኑም በራሳቸው በዚህ በኩል ያደረጉት እንቅስቃሴ አለ፡፡ ለዚህም እነ ፕሮፌሰር ሥርገው  ኃ/ሥላሴ  ፤ ታደሰ ታምራትና ጌታቸው ኃይሌን  በፊት አውራሪነት መጥቀስ ይቻላል፡፡  ብዙ ባይገፋበትም  እንደ ማኅበረ ቅዱሳን ያሉ ተቋማትን መጥቀስ ይቻላል፡፡ በዚህ አጋጣሚ በግለሰቦች ጥረት እነዚህን አይነት ሰነዶች በአንድ ቦታ( የኢትዮጵያ ጥናትና ምርምር ተቋም)  ከውጭ በማይክሮ ፊልም  ቅጂነት ተሰብስበው  እንዲገኙ ጥረት የመደረጉን ያህል አሳዶ የማሻሻጡን ሁኔታን የሚያቀላጥፉ መኖራቸውም መጠቀስ አለበት፡፡
እንግዲህ  ዲ/ን ዳንኤል በዚህ መጽሐፍ ያቀረበልን ከተለያዩ ቦታዎች  ያሰባሰባቸው ገድላት ተርጉሞ  ነው ፡፡ ይህን በማድረጉም በግዕዝ የተጻፉትን  በአማርኛ እንድናገኛቸው በማድረጉ ባሻገር ራሳቸው ገድላት ያላቸውን ዋጋ እንድናስብና እንድንነጋገር አድርጎናል፡፡  መቼም አንደዚህ አይነቶቹን ምንጮች  በቀጥታ ያለዋጋ ለማስቀረት የሚዳዳቸው እንዳሉ ይታወቃል፡፡ የቄሶች ዋጋ ስለሆኑ አንዳች የሚረባ ነገር እንደሌላቸው የሚቆጥሩና በእነርሱ ላይ ተመስርተው የተሰሩትን ሁሉ ያለማወላወል ለማጣጣል የሚሞክሩ  በእውቀት ማነስ የተፈጠረ የጥላቻ ስሜት ውስጥ የገቡ ወገኖች መኖራቸው ይታወቃል፡፡ በዚህ አጋጣሚ ዘመናት የየራሳቸውን ምንጮች ሲተውልን ፤ ምጮቹም የራሳቸው ባህርያት እንደሚኖራቸው እነሱን መጠቀም የግድ እንደሆነ ፤ ነገር ግን እንከን የሌለው ምንጭ የለምና እንደየባሕሪቸው ችግራቸውን  ቀድሞ በመለየት ከውስጣቸው ተጨምቆ ሊገኝ የሚችለውን መረጃ ለማውጣት የሚያስችል አጠቃቀም እንዳላቸው መግለጽ ያሻል፡፡ ገድላት በውስጣው የሚይዟው ክፍሎች አሉ ፡፡ ከእነዚህ ውስጥ የሰማዕቱን /ጻዲቁ አጠራር ፤ የሰማትነቱን አፈጻጸምና የተሰጠው ቃል ኪዳን ናቸው፡፡ ጸሐፊው ለእነዚህ ሽፋን ሲሰጥ የመረጠውን  አቀራረብ ከነምክንያቱ በምንጭ ትንተና ልንለይ እንችላለን፡፡ ስለዚህ ገድላትን ለታሪክ ምንጭነት እንጠቀማለን ሲባል የተባለውን ሁሉ እንወስዳለን ማለት እንዳልሆነ ሊታወቅ ይገባል፡፡ በአንድ አካባቢ ስሚታወቁ ሁለት ቅዱሳን የሚጻፉ ገድላት በታሪክ አጥኚው ሲፈተሹ በደብሮቹ መካከል የበለጠ ምዕመናንን ለማገናኝት ከሚደረግ ጥረት ጀምሮ የየትኛው ተዓምር ከየትኛው ጋር ይመሳሰላል እስከሚሉ ጥያቄዎች ድረስ የሚዘልቅ መሆኑን መዘንጋት የለበትም፡፡ እንግዲህ ዋናው አስፈላጊው ጉዳይ  እንዲህ አይነቶቹን ምንጮች ለመጠቀም የሚያስችለው ስነ-ዘዴ መካን ነው፡፡
ከዚህ ውስጥ አንዱ በተለያዩ ሰዎችና አጋጣሚዎች የተገለበጡ የተለያዩ ገድሎችን አንድነትና ልዩነት  መለየትና ትርጉማቸውን ማውጣትና ከእነርሱ የሚገኙትን መረጃዎችንም ከሌሎች ጋር ማመሳከር ነወ፡፡ በዚህ ረገድ ዲ/ን ዳንኤል ልዩነቶችን ለመለየት ያደረገው ጥረትና በገድላቱ ውስጥ የሚጠቀሱ ፍሬ ነገሮችን በዝርዝር ማብራሪያ መግለጫና ማመሳከሪያ ለማጠናከር የሄደበት ርቀት በጉዳዩ ዙሪያ አጠቃላይ ፍላጎት ያለውንም ሆነ ልዩ አትኩሮት የሚያደርገውን የሚያስብ ነው፡፡ ዲ/ን ዳንኤል ገድላቱን እንድናገኛቸው ያደረገ ብቻ ሳይሆን ከተለያዩ ምንጮች ባሰባሰባቸው መረጃዎች አማካኝነት የምናውቃቸውን አካባቢዎች በምናውቃቸው ማሳያዎችና በታወቁ ማመሳከሪያዎች ወደ ተጨባጭ ዕውቀት ለመቀየር ያደረገው ጥረት እንገነዘባለን፡፡ በእርግጥ እነዚህን ቦታዎች በካርታ ማሳየት ቢቻል የዲ/ን ዳንኤል ትረካ ብቻ ሳይሆን አዲስ የለያቸው አካባቢ ስሞችና አቅጣጫቸውን እንዲሁም ግምቶቹን በቀላሉ ለመረዳት ይጠቅመን ነበር፡፡
ገድላት በተፈጥሯቸው ከባለገድላቱ ሕይወት በኋላ የሚጻፉ ናቸው፡፡ ይህም በመሆኑ በውስጣቸው የሚይዙት መረጃ የባለገድላቱን  ዘመን ብቻ ሳይሆን የተጻፉበትን ዘመንም የሚወክሉ እና የዘመናቸውን ዕሳቤም የያዙ መሆናቸው አይቀርም፡፡ ለምሳሌ በአቡነ አኖሬዎስ የተጻፈው አቡነ አኖሬዎስ ካረፉ ከ127 ዓመት በኋላ ነው(ገጽ 368) ፡፡ ስለዚህ ገድላቱ ስሚያወሩላቸው ቅዱሳን ብቻ ሳይሆን ስለ ጸሐፊዎቹም ዘመን የሚነግሩን ይኖራል፡፡ ስለዚህ የገድላትን የታሪክ ምንጭነት በሁለት ተለያዩ ዘመኖች የመሆኑን እድል ያበዛዋል፡፡ በእርግጥ ዲ/ን ዳንኤል የተጻፉበት ምክንያት ከሃይማኖት አይን በዘለለ አለማየቱ ሌሎች ምክንያተ ጽሕፈቶችን ለመቃኝት ጥረት አላደረገም ፤ ስለዚህም ከተጠቀሱት አባቶች ታሪክ የዘለለ ፋይዳ ሲፈልግ አናይም፡፡
ሌሎች አገራዊና ማኅረሰባዊ ፋይዳዎች
በቆየው ዘመን የኢትዮጵያ ታሪክ ጠቢብ ለመሆን ቢያንስ ቢያንስ የግዕዝ ፤ የጣሊያንና እግሊዝኛ ቋንቋም ማወቅ ግድ ይላል፡፡ ይህንን አይነቱን የቆየውን ዘመን ማጥናት በእጅጉ አስቸጋሪ የሚያደርገው የቋንቋን ጉዳይ አልፈው ለየሚያጠኑበት ዘመን ሊቅ ለመሆን የቻሉ ጠበብቶች ቁጥር በጣም አናሳ ነው፡፡ እነርሱም በሞት እያለፉ በመሄዳቸው አሁን ነገሩ ሁሉ እየጨለመ ነው፡፡ ከዚህ አንጻር ነው በቆየው ዘመን ላይ የቻሉትን ያህል የሠሩትንና ስለ ዘመኑ ያለንን ዕውቀት የገነቡልንን ሰዎች በአልሠሩም ስም ሲተቹ ማድመጡ ተቺዎቹን ምክንያት የራቃቸው እንደሚያሰኝ የምንረዳው፡፡ ምስጋና ይግባውና ዲ/ን ዳንኤል የግዕዝ ቋንቋን በማወቁ ምክንያት አሁን የገባበት ዘርፍ በጠቀስኩት መልኩ ያለብን ችግር ለመቅረፍ ሊወሰድ የሚገባውን እርምጃ መሆኑንና ሌሎችንም የሚያበረታ እንደሚሆን መመስከር የሚያስገድድ  ነው፡፡ አቀራረቡ በዘመኑ የታሪክ ጥናት ያለብንን ክፍተት ለመሙላት የታሪክን የፊሎሎጂ ስነ ዘርፍ ጥናቶች የመተጋገዝን ጥቅም ልብ እንድንል ያደርገናል፡፡
መቼም በሕዝባዊ ታሪክ ዙሪያ የዕውቀት ክፍተትን ከመሙላት ያለፈ የታሪኩ ዋጋ ግምት ውስጥ መግባቱ አይቀርም፡፡ እውነትም ወደ ኋላ እና ወደ ፊት ስናነብና አንድምታዎችን ስንፈትሽ የመጽሐፉን መጻፍ አንዳንድ ፋይዳዎች እንረዳለን፡፡ እርግጥ ነው መጽሐፉ ለዕምነቱ ተከታይ ሰዎች አገልግሎትህ ይባርክልህ ብለው የሚቀበሉት እንደሚሆን መናገር አይከብድም፡፡ በዚህ ረገድ ትርጉሞችን በሃይማኖቱ ማስተማሪያና ማብራሪያ መጻሕፍት ላይ ተመስርቶ እንደ ቤተክርስቲያን እምነት የሰጣቸውን ትንተና መመልከት ይበቃል፡፡ በየገድላቱ እንደ ተዓምራት የሚቆጥሩትን አማኞች እንዳለ ሊወስዱት ይችላሉ፡፡ በአንጻሩ ሌሎች ደግሞ መጽሐፉን የማንበብ ፍላጎታቸውን ሊፈታተን ይችላል፡፡ ይህም ቢሆን ግን መጽሐፉ በአጠቃላይ የፖለቲካ እና ታሪክ አረዳዳችን ዙሪያ ያለውን የሚያጠፋ አይሆንም፡፡ የመንግሥትና የሃይማኖት ግንኙነት አስመልክቶ ማጥናት የተለመደ ነው፡፡ ፕ/ር ታደሰ ታምራት ፤ ፕ/ር ዶናልድ ክራሜን ፤ አንዳርጋቸውን ወዘተ መጥቀስ ይቻላል፡፡ የፕ/ር ጌታቸው ኃይሌን ጨምሮ በግርጌ ማስታወሻ የሚያነሳቸውና የሚከተላቸው ሙግቶች  ፤ ክርክሮችና ማስረገጫዎች ዲ/ን ዳንኤል  የነ ፕ/ር ታደሰ ታምራትን  ፈለግ ለመከተል የሚሻ መሆኑን ያመለክታሉ፡፡እግረ መንገዱን ግን የራሱን አላማና አቀራረብ  መከተሉንም በግልጽ ማየት ይቻላል፡፡ ከዚህ ውስጥ አንዱ ሌሎች የስቴቱን(የሃገረ-መንግሥቱን) ታሪክ ከቤተክርስቲያን አንጻር ለማየት ሲሞክሩ እርሱ ደግሞ የቤተክርስቲያንን ታሪክ ከመንግሥታቱ አንጻር ለማየት የሚሞክር መሆኑ ነው፡፡
የመጽሐፉ መታተም አንዱ አንድምታ ከዚያው በቤተክርስቲያኗ አምልኮት ዙሪያ ያለውን ሁነት የመንጸር አዝማሚያ እንዳለው መገመት ይቻላል፡፡ ይህንንም ገድላቸውን በሚዘረዝርላቸው የሃይማኖት አባቶች ትሩፋት ላይ ተመስርቶ  አሁን የሚታዩት የሞራል ዝቅጠቶች  እንዴት እንደተፈጠሩ የሚጠይቅበት (ገጽ 111) እንደሆነ ያመለክታል፡፡ ዲ/ን ዳንኤል በይፋ ባይናገረውም ለመጽሐፉ የመረጣቸው አባቶች ለዕምነታቸው ቀጥተኛነት የታገሉትን መሆኑን ስናስብ ምሳሌነታቸው በእምነቱ ውስጥ  የሚነሱ ሁነቶችን ለመፈተሸ ማንፀሪያ እንዲሆን ያሰበ ቢያስመስለው አይደንቅም፡፡ በገዳማውያኑና በካህናተ ደብተራዎቹ መካከል ስላለው ልዩነት የተካተተው ምዕራፍ ዋናው የልዩነት ምንጭ እንደሆነ እንደ አንዳመላካች  ልንወስደው እንችላለን፡፡ በመጀመሪያ ክፍልም ሆነ በቅዱሳኑ ታሪክ የተገለጹት የቅጣት አይነቶችም(ገጽ 92-101) ኢትዮጵያውያን ለአስተዳደራቸው ያልተመቿቸውን የሚያሰቃዩበት መንገድ ወደ ኋላ ስድስትና ሰባት መቶ ዓመታት ሄደን እንድናሰላስል የቅርሶቹን ድርጊያ እንድናስብ የሚያደርገን ነው፡፡ ያለፈ ታሪካችን ነቅ እንደሌለበት በጭፍን ሁሉን ነገር በጭፍን እንድገመው ለሚሉት በተለይ በዚህ ረገድ  ምን ያህል ርቀት  እንጓዝ (ራቁት ማስቀረትን ፤ ሐፍረተ ስጋን መንጨትን ጨምሮ መንደቅ ማስገባት) እንደነበር የሚጠቁም ነው፡፡
ዲ/ን ዳንኤልንም በቤተክርስቲያን አካባቢ በሚፈጠሩ ችግሮች ዙሪያ አዘውትሮ ሃሳቡን ሲያካፍለን የቆየበት የእሱም ሆነ  ሌሎች ልፋት ብዙም ለውጥ ያመጣ ስላልሆነ የነዚህን ሰዎች ታሪክ በገድላቸው አማካኝነት  በመዘከር ፤ የሚጠብቀውን የሞራል ስነ-ልክ በማሳያ እያመላከተ ነው ብንል ስህተት አይሆንም ይሆናል፡፡ በሃይማኖት መሪዎች ዘንድ አንባቢም ሆነ የሚነሸጥ ልብ ቢገኝ መጽሐፉ ድንቅ ማስተማሪያ ይሆን ነበር፡፡  ለምዕመኑም የስነልቦና ጥንካሬ ይሆንለታል፡፡ ምክንያቱም ሕዝብ ሲበደል ፤ ግፍ ሲሰራ እና ፍትህ ሲጠፋ የሃይማኖት አባቶች ለእውነትና ሀቅ መቆም ቢያቅታቸው እንኳን እምነታውን የሚፈታተን ለመንግሥታቱን ድርጊት ለመከላከል እያቃታቸው በመንግሥታት ፊት ሲልመዘመዙ እያየ የሚያዝነው ምዕመን  ስለነበሩት አባቶች እያሰበ የሚጽናናበት ይሆናልና ነው፡፡ እውነትም ስለ ቤተክርስቲያኗ ታሪክ ሲወሳ የነገሥታቱን ጠባይ ለማረቅ ቤተክርስቲያኗ ስለወሰደቻቸው እርምጃዎች መነሳቱና በዚያም ረገድ የአራቱ አባቶች ሁኔታ ሰፊ ቦታ ይዞ መነገሩ የማይቀር ፤ ለዚህም ዲ/ን ዳንኤል ነገረ ጉዳዩን ከሕዝብ ጋር በማስተዋወቅ  ደረጃ ይበል  የሚያሰኝ ሥራ እንደሠራ ስሙ የሚጠቀስለት መሆኑን በድፍረት መናገር ይቻላል፡፡
ሌላው ፋይዳውም ኢትዮጵያዊ ብሔርተኝነትን መስክ ነው ልንል እንችላለን፡፡ ይህንንም ‹‹ቤተክርስቲያኗ  በመጸሐፈ ስንክሳሯ ከምታውቃቸው ቅዱሳን ብዙዎቹ የውጭ ቅዱሳን ናቸው ›› የሚለን ዲ/ን ዳንኤል ገድል ከተጻፈላቸው ከሶስት መቶዎቹም አካባቢም 30ዎቹ ብቻ ናቸው በአማርኛ የተተረጎመላቸው  በማለት ይቆጫል(ገጽ  112)፡፡ እንደ ዲ/ን ዳንኤል ለዚህ ምክንያቱ ተገቢ ትኩረት ለኢትዮጵያውያን ሰማዕታት አለመሰጠቱ ነው፡፡ ሁኔታው ስለ ኢትዮጵያውያን አባቶች በቂ እውቀት አለመፈጠሩም የሚስረግጥ ነው፡፡ ይህን አስቀድሞ ማድረግ የተሳነው  ቤተክህነትም የቤት ስራውን የማይሰራ  መሆኑን የሚረጋግጥበት ነው፡፡ እንግዲህ ከዚህ አንጻር ነው ፤ በከተሞች በአንድ ጻዲቅ ስም አምስት ስድስት ቤተክርስቲያን መሠራቱን የሚተቸው፡፡
ስለ ሕዝቦች ግንኙነት ማመልከቱ ሌላኛው  የመጽሐፉ ፋይዳ ተደርጎ ሊወሰድ የሚችል ነው፡፡ ምንም እንኳን ቤተክርስቲያንና መንግሥት አንዱ የአንዱ ግልባጭ ለመሆን እስኪዳዳቸው የሚደጋገፉ እንደነበሩ ቢወሳም ፤ ቢያንስ በሃይማኖቱ ጉዳይ ነገሥታቱን ካልተገባ መንገድ ለመከላከል ሳይፈሩ የሚገስጹ  የሃይማኖት አባቶች እንደነበሩ አመልክቷል፡፡ ከዛ ባለፈም የሃይማኖት አባቶች ምግባረ- ስሁት መሪዎችን በመገሰፃቸው ሲሰደዱም የሚሄዱበት አካባቢ ሕዝብ ማንነታቸውን ሳያስጨንቀው ተቀብሏቸው የሚሉትን ሰምቶ በእምነት ጸንቶ ስለመኖሩ የሚገኝው ፍንጭም የራሱ ትርጉም አለው፡፡ ጥያቄው የት ተወለድክ ? ሳይሆን  የትና ምን ተማርክ?  ነበርና (ገጽ 99) ፡፡ በተለይ በሸዋ እና በትግራይ በዚህ መልኩ የነበረውን ግንኙነትና  ቅርበት ብዙ የሚያስታውስና  አሁን በተወሰኑ የሁለቱ አካባቢ ሰዎች  ነን የሚሉ ቀንደኞች የሚቀነቀነውን ልክ የለሽ ሽኩቻ ለመታዘብ ዕድል የሚሰጥ ነው፡፡  
የአርትኦት ግድፈት
ስለዚህ መጽሐፍ ከአርትኦት ጋር የተያያዘ አክል ለማንሳት ያቀድኩ ባይሆንም ከመጽሐፉ ዋና ፋይዳ ጋር የተያያዘውን አክል ማለፍ ግን አልቻልኩም፡፡ ይህም በግርጌ  ማስታወሻ  አዘገጃጀት  ጋር የተያያዘ ጉዳይ ነው፡፡ ብዙ መጻሕፍት ጨርሶ እንዲህ አይነት ነገር አስፈላጊ መሆኑን ይረሱታል፡፡ ምናልባት ሕዝቡ ቀለል ያለ ነገር ሳየጨነቅ ለማበብ ነው የሚፈልገው ተብሎ ሊሆን ይችላል፡፡ አንዳንድ ርዕሰ ጉዳዮችና አቀራረቦች ግን የግድ የግርጌ ማስታወሻ ይፈልጋሉ፡፡ ስለዚሀ ጸሐፊዎቻቸው እንደ ዲ/ን ዳንኤል እንዲህ ጉዳዩን ሲያስበት አሰየው ማለታችን አይቀርም፡፡ መሠረታዊ ጥንቃቄ የሚሹ ጉዳዮች እንዳሉት ግን መዘንጋት አይገባም፡፡በዘመናችን በኮምፒዩተር እርዳታ አሠራሩን አቅሎታል፡፡ በአንድ ትዕዛዝ ከመጀመሪያ እስከ መጨረሻ እያስተካከልን ስለሆነ ማለቴ ነው፡፡ ችግሩ ግን መሰል ትዕዛዝ የማያስተካክላቸው ነገሮች አሉ፡፡ ከእነዚህ አንዱ በድጋሚ ማብራሪያ የሚፈልጉ ነገሮች እንደገና ሲገጥሙ የቀደመውን ለማታወስ ግርጌ ማታወሻ ‹ሀ› ተመልከት የሚሉ ትዕዛዞችን ልብ የሚል አለመሆኑ ነው፡፡ እንዲህ አይነት አጠቃቀም የመጽሐፉ ረቅቅ የመጨረሻ ደረጃ ላይ ሲደርስ ካልሆነ በስተቀር በስቀር በየጊዜው በግርጌ ማስታወሻ ላይ መጠን መጨመር ወይም ለውጥ ማድረግ ቁጥሮቹን ስለሚያዛባ ዝርዝሮቹን በተባለው ቁጥር ላይ  ያለማግኝት አጋጣሚ መፍጠሩ አይቀሬ ነው፡፡ በዚህ ምክንያት ከተፈጠሩ ስህተቶች በተጠቆሙት ገጾቻቸው የማይገኙት የግርጌ ማስታወሻ ቁጥር  1122 ስለ ዳሞት ግርጌ ማታወሻ ቁጥር 707ን  ተመልት የሚለውና ስለ አስኬማ ገጽ 404 ተመልከት የሚለው የግርጌ ማስታወሻ ቁጥር 104 ተመልከት የሚለው የግርጌ ማስታወሻ ቁጥር 691 መጥቀስ ይቻላል፡፡ 
በግርጌ ማስታወሻ እንዲህ ሲሆን የተባሉትን ማስረጃዎች ለማግኝት ይከብዳል፡፡ ለቸኮለማ ጭራሽ ማግኝት አይቻለውም ፤ በግርጌ ማስታወሻዎቹ በዚሁ መጽሐፍ ገጽ ‹እከሌ. የተባሉትን የተቀመጡትንም መመልከትም ያሻል ፡፡ ለምሳሌ የግርጌ ማስታወሻ 316 ላይ ገጽ 249 ተመልከት ቢልም የተባለው መረጃ የሚገኝው ከአንድ ገጽ በኋላ ነው፡፡ እንዲህ አይነት ስህተቶች የግርጌ ማስታወሻውን ጥቅም ሊያደበዝዝበት ይችላል፡፡ እንዲያውም በግርጌ ማስታወሻ 400 ላይ ግርጌ ማስታወሻ ቁጥር ተመልከት ብሎ ቁጥሩን ከማይሰጠው በምን እንደሚለይ መናገር ሊከብደው ይችላል፡፡ ሁኔታው በመጠቁምም ላይ ተመሳሳይ ዕክል ፈጥሯል፡፡ ለምሳሌ ጌታቸው መረሳን በመጠቁም ገጽ 6 ላይ እንደሚገኝ የተጠቆመ  አንባቢ በተባለው ገጽ ላይ አያገኝውም፡፡ ስለዚህ ወደፊት ወደ ኋላ እየሄደ እንዲያነብ ሊገደድ ነው ማለት ነው፡፡ ይህ ግን እጅግ ብዙ የተለፋበትን የግርጌ ማስታወሻ ዝርዝር የሚያጠቃልል አስተያየት አይደለም፡፡
በተረፈ በመጀመሪያው ክፍል ሰፋ ቢልልን ከመሻታችንና ግርጌ ማስታወሻውን እንደገና እንዲመለከተው ከመጠየቃችን ውጪ የሁለተኛውን ክፍል አገራዊና ማኅበራዊ ፋይዳ እያሰብን እንዲህ አዳዲስና ወጥ ነገር ጀባ እንዲለን ጸሐፊውን በርታ ማለት እንወዳለን፡፡ የሞራል ስብዕናቸው ምሣሌነት የሚያንሰው የዘመናችን የሃይማኖት አባቶችም ስለ ሃይማኖቱ መሪዎች የሚያደክመውን ብቻ በመስማት የተዳከመውን ምዕመናን /አጠቃላይ ዜጋ እጃችሁ ከምን የሚል ጥያቄ ማንሳት እንወዳለን፡፡

1 comment: