Saturday, December 21, 2013

ፖለቲካና ሃይማኖተኝነት የሚያቃርናቸው ነገር አለን?

ሠዓሊ አምሳሉ ገ/ኪዳን አርጋው
                                            amsalugkidan@gmail.com 
(አንድ አድርገን ታህሳስ 13 2006 ዓ.ም)፡-ፖለቲካ የሚለው ቃል የባዕድ ቃል ነው እምነተ-አሥተዳደር ማለት ነው፡፡ ከባዕድ ከመምጣቱም ቃሉንና ተግባሩን በመልካም ጎኑ ቀምሰን ሳናጣጥመው ወዲያውኑ ምሬቱን ስላሳየን ለቃሉና ለተግባሩ መልካም ስሜት የለንም፡፡ አንድ አባባልም ፈጥረንለት ከሥነ-ቃሎቻችን ቀላቅለንለታል ‹‹ፖለቲካንና ኮረንቲን በሩቁ ነው›› የሚል፡፡ በእርግጥ ግን ፖለቲካን ርቆ መራቅ ይቻላል? ለዚህ ቃልና ለተግባሩ ባለን ጥሩ ያልሆነ አመለካከት የተነሣ ፖለቲካ ያለውን የሀገርንና የሕዝብን እጣ ፈንታ የመወሰንን ያህል ግዙፍ አቅምና ሚና ዘንግተን ፖለቲካንና ፖለቲከኛነትን ጭንቅላታችን ውስጥ የጭራቅ ምስል ሥለን በመፍራት በመጥላትና በመሸሽ በዜግነታችን ለሀገራችን ልናበረክተው የሚገባንን ተግባርና አገልግሎት እንዳናበረክትና ሀገሪቱም በፖለቲካ ምክንያት ከሚከሰቱ ትብትብ ችግሮች እንዳትወጣ አድርጓታል፡፡

        በሌላ በኩል ደግሞ ይህ ሁኔታ ማለትም ሕዝቡ ፖለቲካን መጥላቱ ከፖለቲካ መራቁ መገለሉ ገዥዎች በመድረኩ ላይ ያለጠያቂ እንደፈለጉ እንዲፋንኑ ምቹ ሁኔታን ፈጥሮላቸዋል፡፡ ይህ ሁኔታ ሕዝቡን ለፖለቲካ በሚሰጠው የተሳሳተ ግንዛቤ ሊያስጨብጠው ከሚችሉት ልፈፋዎች (propaganda) ከሚፈጠር ፍርሐት የተነሣ በርከት ያሉ የመገለያ ሰበቦችን እንዲፈጥር አስገድዶታል፡፡ 
        ሕዝባችን አሁን ያለበትን አስቸጋሪ ሁኔታ ማየት ለዚህ በቂ ምሥክር ነው፡፡ ሕዝቡ ሀብታም ከድሀ ሳይለይ የግፍ አገዛዙ ከልክ በላይ ያንገፈገፈው ቢሆንም ሊከፍለው የሚገባውን ዋጋ ከፍሎ የተነጠቀውን ነጻነት በእጁ ለመጨበጥ ያለው ቁርጠኝነት እጅግ ደካማ ሆኗል፡፡ ከዚያ ይልቅ በዝምታ ግፍን ተንጋሎ መጋት የመረጠ አስመስሎታል፡፡  ይህ ግምት የተጋነነ መስሎ የሚታየው ዜጋ ይኖራል ብየ አልገምትም፡፡ ነገር ግን ሁሉም ሊባል በሚችል ደረጃ ይህ ሁኔታ እንዳለ ያምንና ለድካማችን ለስንፍናችን ለፍርሐታችን ለዳተኝነታችን ምክንያት የእናታችንን ቀሚስ የምንጠቅስ ነን፡፡ ይሄንን ጉዳይ ተጨባጭነት ባለው ምሳሌ ለማስረዳት ልሞክር፡፡ 
        እኔ ለአቅመ አዳም ከመድረሴ በፊት ጀምሮ ብዙ የታዘብኳቸው ነገሮች አሉ እንደኔና እኔን እንደመሰሉ ሁሉ የሚፈጸሙ ግፍና በደሎችን እነሱም ይቃወሙ ዘንድ ከምንጠይቃቸው ወገኖች ከፊሎቹ “አይ እኔ ፈሪ ነኝ፣ ራስ ወዳድ ነኝ፣ የግል ጥቅሜን አሳዳጅ ነኝ የሌላው አይገደኝም ” ላለማለት ዘወትር የሚናገሩት ነገር ነበር አለም፡፡ ‹‹አይ ይሄ ፖለቲካ ነው አያገባኝም›› የሚል በተለይ ቤተክርስቲያን አካባቢ ያሉትና ሃይማኖተኛነትን በተሳሳተ መንገድ የተረዱ ሰዎች፡፡ ይመስለኛል በሌሎች ሃይማኖቶች ተከታዮችም ዘንድ ተመሳሳይ ሁኔታ አለ፡፡
       
 እነኝህ ሰዎች በደሉን ያደረሱት ፖለቲከኞች እንደሆኑና በደሉም የደረሰው በቤተክርስቲን ላይ ሆኖም እንኳ እለ ያንን በደል መቃወም እንዴት ፖለቲካ ሆኖ እንደሚታያቸው አስገራሚ ነው፡፡ እንግዲህ ይህ ችግር የሚፈጠረው አንደኛው ከላይ እንዳልኩት ራስን ከኃላፊነት ለማሸሽ ሲሆን ሁለተኛው ደግሞ ፖለቲካ ማለት ምን ማለት እንደሆነ ካላመረዳትም ነው፡፡ እንደ እውነቱ ከሆነ ማንኛውም ዜጋ ወዶም ይሁን ተገዶ በቀጥታም ይሁን በተዘዋዋሪ ፖለቲካዊ ጉዳይ ይመለከተዋል ይገደዋል፡፡ ፖለቲካ ነው አያገባኝም ብሎ ማለት በሌላ አማርኛ እኔ ዜጋ አይደለሁም ሀገርንም ሆነ ሕዝብን እራሱን ጨምሮ እንደፈለጉ እንዳሻቸው ቢያደርጉ አይመለከተኝም ማለት ነው፡፡ እንዲህ ብሎ የሚል ሰው ደግሞ በዜግነቱ ሊያገኛቸው የሚችላቸውን ወይም የሚገባውን ማለትም የመሥራት፣ የመማር፣ የመኖር ወዘተ መብቶች ለእኔ አይገቡኝም አልጠይቅም ማለቱ እንደሆነ ያለመረዳትን ያህል ድንቁርና የተጫነው አባባልና አስተሳሰብም ነው፡፡
        
 አንድ ሃይማኖተኛ ወይም መንፈሳዊ ሰው ሃይማኖተኛ ወይም መንፈሳዊ ቢሆንም በሌላ በኩል ደግሞ ዜጋም ነው፡፡ ሃይማኖተኛነቱ ዜጋነቱን አይከለክለውም ዜጋነቱም ሃይማኖተኛነቱን አይከለክለውም፡፡ እነዚህ ጉዳዮች በተለይ በኢትዮጵያ ሲሆን ደግሞ ምክንያቱም ኢትዮጵያ በመጽሐፍ ቅዱስና በፍልስፍና መጸሐፍትም ጭምር ሀገረ እግዚአብሔርነቷ እንደመመስከሩ ተጣጥመው ያሉ እንጅ የሚቃረኑ አይደሉም፡፡ እንግዲህ ይህ ሰው ሊወጣቸው የሚገባቸው ሁለት የማንነት መገለጫዎች አሉት ማለት ነው፡፡ የሃይማኖት ሰው ቢሆንም እንደዜጋነቱ ደግሞ ሀገሪቱ እንዲያደርግላትና እንዲወጣላት ከሱ የምትጠብቀው ብዙ ግዴታዎች ደግሞ አሉ፡፡ ይሄም ስለገባቸው ነው አባቶቻችን ለሀገራቸው ታቦት ተሸክመው ጦርነት ይወጡ ይዋደቁ ይሞቱላትም የነበሩትና የሀገራችንን ነጻነት ሉዓላዊነትና ክብር አስጠብቀው ሊቆዩ የቻሉት፡፡
      ከሁለት ሦስት ዓመታት በፊት ጀምሮ ስደተኛውን ሲኖዶስ ለመመለስ ወይም ሀገር ቤት ካሉ አባቶች ጋር ለማስታረቅ ሰፊ እንቅስቃሴ እየተደረገ በነበረበት ጊዜ በመሀሉ አባ ጳውሎስ ዐረፉ፡፡ አይ አግዚአብሔር ባወቀ ነገሩን አስተካከለው ተብሎ ሲታሰብ የሀገር ቤቶቹ አጋጣሚው የፈጠረው ነገር አልተመቻቸው ሆኖ የእርቅ ድርድሩን ለማሰናከል አንድ ሰበብ ፈጠሩ በመግለጫም ‹‹ስደተኞቹን አባቶች ከቤተክርስቲያን ጋር ግንኙነት የሌለውን ፖለቲካዊ ጉዳይ ያነሣሉ ስለሆነም የእርቅ ድርድሩ መሰናክል ገጥሞታል ወይም ወደፊት ማስቀጠል አልቻልንም›› አሉ ፡፡  
        በወቅቱ ይህ መግለጫ እጅግ ካስቆጣቸውና ካሳዘናቸው ወገኖች አንዱ ነበርኩና ወዲያውኑ በመጽሔት፣ በመካነ ድሮች ይሄንን የተሳሳተና ሸፍጥ ያዘለ ፍረጃ የሀገር ቤቶቹ አባቶች የዘነጉትን የታሪክ እማኝነት በማንሣት እርቃኑን ያስቀረ ጽሑፍ ለንባብ አበቃሁ፡፡ ለራሳቸው ለስደተኛው ሲኖዶስም በመካነ ድራቸው በኩል እንዲደርሳቸው በማድረግ እነዚህ የዛሬዎቹ ‹‹አባቶች›› ፖለቲካ ብለው ያሉት ነገር የኢትዮጵያ ቤተክርስቲያን ባለባት ታሪካዊ ኃላፊነት ወይም ባለ አደራነት ከኦሪት ጀምራ ከዚያም በፊት ከሕገ ልቡና ጀምራ ስትወጣው ስትከውነው የኖረችው የተቀደሰ ተግባር መሆኑን፣ ነገሥታትን በዕውቀትና በጥበብ በሥነ-ምግባር አሳድጋ ቀብታ ስታነግሥ የኖረች መሆኗን ወደ ኋላ ደግሞ ማለትም በ13ኛው መቶ ክፍለ ዘመን ሲሦ መንግሥት ተሰጥቷት እስከ ቅርብ ጊዜ 20ኛው መቶ ክፍለ ዘመን ቆይቶ ለየት ባለ መልኩ ሀገሪቷ በፈተናዎች የተዋጠች ብትሆንም፤ ከሀገሪቱ ነጻነት እስከ ሥልጣኔዋ የማይተካ ቁልፍ ሚና የተጫወተች ኃላፊነቷን በሚገባ የተወጣች መሆኗን፤ አሁን በስደት ላይ ያሉ አባቶችን የሀገር ጉዳይ በማንሣታቸው ፖለቲከኞች ብለው የሚነቅፏቸው የሚኮንኗቸው ከሆነ እየነቀፉ ያሉት እነሱን ብቻ ሳይሆን በስንክሳሩ የሚዘከሩ ቅዱሳን አባቶቻችንን፣ የቤተክርስቲያኗን ተጋድሎ እና ታሪክ መሆኑን “ድሀ ተበደለ ፍርድ ተጓደለ” ብሎ ስለ ተበደሉ ፍትሕ ስለተነፈጉ ወገኖች መጮህ መሟገት አምላካዊ ኃላፊነትን መወጣትና ሐዋርያዊ ግዴታ መሆኑን፣ ከሐዋርያት ሕይዎትና ከክርስቶስ ቃል ጋር በማመሳከር ለዚያ የደነቆረ ፍረጃና ነቀፋ አጥጋቢ ምላሽ እንደሰጠሁ ብዙ ሳይቆዩ ማለትም ከሁለት ሳምንታት በኋላ እስከዚያ ጊዜ ድረስ ፖለቲከኛ ሲሏቸው ይሸማቀቁና በዜግነታቸው የሚሰማቸውን ሁሉ አፋቸውን ሞልተው በሀገራዊ ጉዳይ ላይ ለመናገር ይሳቀቁ የነበሩ ስደተኞቹ አባቶች የጽሑፌን ሐሳብ ሙሉ ለሙሉ በማካተት እንዲህ እንዲህ በማለታችን ፖለቲከኞች ተባልን፤ እንዲህ እንዲህ ማለት ፖለቲከኛነት ሳይሆን ሐዋርያነት ነው የሚል መግለጫ አወጡና ለብዙኃን መገናኛዎች ለቀቁ፡፡ እኔም በእውነት እንዲያ ብዙ ስደክምለት የኖርኩትን አስተሳሰብ ያውም በሲኖዶስ ደረጃ ሲንጸባረቅ የተሰማኝ ደስታ የላቀ ነበር፡፡ ከዚያ በኋላማ እንዲያውም በተለይ ከሀገር ውጭ ያሉ ሰባክያን ይሄንን አስተሳሰብ በደንብ እያንጸባረቁት እንደሆነ በመገናኛ ብዙኃን ሳይቀር እየሰማናቸው ነው፡፡ ጎሽ እንዲያ ነው ከዚህ በኋላ ፈሪውና ራስ ወዳዱ ለዳተኝነቱ የዜግነት ኃላፊነቱን ላለመወጣቱ የሚጠቅሰው ሌላ ምክንያት ምን እንደሆነ እንግዲህ ደሞ እንሰማለን፡፡ 
        በእርግጥ እነኝህ አባቶች ይሄንን እውነታ አተውት ወይም ሳያውቁት ቀርተው ነው ማለቴ አይደለም፡፡ ልቦናቸው ይሄንን ሀቅ ስለሚያውቅማ ነው በቂም ባይሆን አምነውበት ለመተግበር ሲሞክሩ የቆዩት፡፡ ነገር ግን በሀገራችን ፖለቲካን ወይም ሀገራዊ ጉዳይን ከዜግነት ግዴታና ከቤተክርስቲያን ለመነጠል ከፋሽስት ጣሊያን ጀምሮ በደርግ በተለይም ደግሞ በወያኔ የተሰበከው ማወናበጃና ማምታቻ በሁሉም ኢትዮጵያዊያን አስተሳሰብ ላይ እንዳጠላ ሁሉ ይህ ሁኔታ ከባድ ጫና ፈጥሮባቸው በዜግነታቸው ለሀገራችን ልናበረክት ይገባል ብለው የያዙትን ቀናና ትክክለኛ አስተሳሰባቸው ከልብ ወጥቶ ወደ አንደበት ስላልደረሰ ነበር በሀገራዊ ወይም በፖለቲካዊ ጉዳይ ላይ በሚጠሩና በሚከወኑ መድረኮች ተገኝተው ያለ ሀፍረትና መሸማቀቅ እንደ ቀድሞዎቹ ሁሉ የቅርብ የሆኑትንም ማንሣት እንችላለን እንደ አርበኛው አቡነ ጴጥሮስ ሁሉ በግንባር ቀደምትነት በወኔና በስሜት ምላት መናገር ያለባቸውን ለመናገር ተሳትፏቸውንም ለማበርከት ይቸገሩ የነበሩት፡፡ አሁንም ቢሆን ገና ይቀራል ይቀራል፡፡ እንደ ሐዋርያትና ሠማዕታት ሁሉ ባለ 30,60,100 ፍሬ ባለ አዝመራ መሆን የፈለገ አባት ወይም የሃይማኖት ሰው ቢኖር መንገዱ ይሄው ነው ሌላ የለምና ያለ ማመንታት በልበ ሙሉነትና በወኔ ውጡ ተሳተፉ ተጋደሉ፡፡ 
        ከዚሁ አካባቢ ካሉ ሰዎች ከሕዝቡም ቢሆን የሚነሣው ሌላኛው ሰበብ ደግሞ ‹‹እግዚአብሔር ያመጣውን ምን ማድረግ ይቻላል እሱ ያመጣውን እሱ እስኪመልሰው ዝም ብለን መቀበል ነው እንጅ›› የሚል ነው፡፡ ለአሁኑ ባጭሩ ለመመለስ አንደኛ ነገር ‹‹ማንም ሲፈተን  በእግዚአብሔር እፈተናለሁ አይበል እግዚአብሔር በክፉ አይፈትንምና፤ እርሱ ራሱስ ማንንም አይፈትንም፡፡ ነገር ግን እያንዳንዱ በራሱ ምኞት ሲሳብና ሲታለል ይፈተናል፡፡ ከዚህ በኋላ ምኞት ፀንሳ ኃጢአትን ትወልዳለች ኃጢአትም ካደገች በኋላ ሞትን ትወልዳለች፡፡ ያዕ. 1÷13-15 ተብሎ መጻፉን ልብ ይሏል፡፡ ሁለተኛ ስኬት የሚገኘው ከጥረት ከግረት ከልፋት መሆኑን አዳምን ጥረህ ግረህ በግንባርህ ወዝ ብላ እደር ዘፍ. 3÷19 ባለውና ሊሠራ የማይወድ አይብላ  2ኛተሰ. 3÷8-13 ባለው ቃል እጅና እግርን አጣምሮ ቁጭ ብሎ በማየት የሚገኝ ነገር እንደሌለ እንቅጩን ተናግሯል፡፡ በዚህም ላይ የሚሠሩ እጆችና እግሮች የሚያስብ ጭንቅላት የሰጠን የሚበጀንን ነገር እንደወደድን እንድናደርግበት መሆኑ ይታወቃል፡፡ እስከዛሬም ድረስ በዓለም ታሪክ ያለውን ብንመለከት ሰዎች በጥረታቸው አንዱ አንዱን ይጥላል አንዱ አንዱን ያነሣል እንጅ እግዚአብሔር እራሱ ወርዶ እናንተ ይበቃቹሀል ወግዱ እናንተ ተቀመጡ ብሎ አያውቅም፡፡ ነገር ግን በእያንዳንዱ ነገር ላይ የእርሱ ፈቃድ እንዳለበትና አድራጊውም ሥራውን በርትቶ እየሠራ በሚሠራው ነገር ሁሉ የእሱ ፈቃድና እረድኤት እንዲኖርበት መለመን መጠየቅ ማሳሰብ እንዳለበት እሙን ነው፡፡ 
        የሀገራችንንም የቅርብ ጊዜ ታሪክ ብናይ ያለው እውነታ ይሄው ነው፡፡ ደርግን የሸኘው እግዚአብሔር መሆኑ ግልጽ ነው ፡፡ ይሁን እንጅ እግዚአብሔር እራሱ ወርዶ ደርግን ከመንበሩ አውርዶ ወያኔን ደግሞ ና ተቀመጥ ብሎ አስቀምጦ አይደለም፡፡ ወያኔን ምክንያት አድርጎ ደርግን ሸኘው እንጅ፡፡ 
        በደርግ የተማረሩ ወያኔዎች ወተው ባይታገሉ ኖሮ ለነገሩ ወያኔ ብቻም አልነበረም ምርኩዙ መጠቀሚያው የሆኑ ሌሎችም ነበሩ አሉም፡፡ ለማንኛውም እነሱ ‹‹አይ እግዚአብሔር ያመጣውን እኛ ምን ማድረግ እንችላለን? ›› ብለው እጅ እግራቸውን አጣምረው ቁጭ ቢሉ ኖሮ ደርግን ታግለው ለመጣልና ሥልጣን ለመጨበጥ ለመቆናጠጥ መቻላቸው የማይታሰብ በሆነ ነበር፡፡ በይነ ሕዝባዊ (ዲሞክራሲያዊ) ሥርዓት ኖሮ ተመርጠው ለሥልጣን ካልበቁ በስተቀር፡፡ በመሆኑም ቁጭ ብሎ ዓይንን በማቁለጭለጭ የሚገኝ ምንም ነገር የለም፡፡ ሰው ማግኘት የፈለገውን ነገር የእግዚአብሔር ፍቃድ ታክሎበት በልፋት በጥረት ይገኛል እንጅ እጅና እግርን አጣምሮ ቁጭ ካሉበት ከሰማይ ዱብ የሚል ነገር ጨርሶ የለም፡፡ 
                ሦስተኛው የሰበበኞች ሰበብ ደግሞ በመሠረተ ሐሳብ ደረጃ ከሁለተኛው ጋራ ተመሳሳይ ሆኖ ነገር ግን ብልጠት አይሉት ድንቁርና የተሞላበት አስገራሚ ሰበብ ነው፡፡ ሐዋርያው ጳውሎስ በሮሜ መልእክቱ 13÷1-7 ያለውን ይጠቅሱና ሰጥ ለበጥ ብለን የመገዛት አምላካዊ ግዴታ አለብን ይላሉ፡፡ እጅግ አሳፋሪና ነውረኛነትም ነው፡፡ ቃሉን እንይ “ ነፍስ ሁሉ በበላይ ላሉ ባለ ሥልጣኖች ይገዛ ፡፡ ከእግዚአብሔር ካልተገኘ በቀር ሥልጣን የለምና፤ ያሉትም ባለሥልጣኖች በእግዚአብሔር የተሾሙ ናቸው፡፡ ስለዚህ ባለ ሥልጣንን  የሚቃወም የእግዚአብሔርን ሥርዓት ይቃወማል የሚቃወሙትንም በራሳቸው ላይ ፍርድን ይቀበላሉ፡፡ ገዥዎች ለክፉ አድራጊዎች እንጅ መልካም ለሚደርጉት የሚያስፈሩ አይደሉምና ፡፡ ባለ ሥልጣንን እንዳትፈራ ትወዳለህን? መልካሙን አድርግ ከእርሱም ምስጋና ይሆንልሀል፡፡ ለመልካም ነገር ለአንተ የእግዚአብሔር አገልጋይ ነውና፡፡ በከንቱ ግን ሰይፍ አይታጠቅምና ክፉ ብታደርግ ፍራ ቁጣውን ለማሳየት ክፉ አድራጊውን የሚበቀል የእግዚአብሔር አገልጋይ ነውና፡፡ …. ለሁሉም የሚገባውን አስረክቡ ግብር ለሚገባው ግብርን፣ቀረጥ ለሚገባው ቀረጥን፣ መፈራት ለሚገባው መፈራትን፣ ክብር ለሚገባው ክብርን ስጡ ” ይላል ቃሉ እንግዲህ ይሄንን ቅዱስ ቃል እንዴት ለፍላጎታቸው አጣመው እንደተጠቀሙበት አያቹህ? ቃሉ ምንም በማያሻማና ጥርት ባለ መልኩ ነው የቀረበው፡፡ ቁጥር 3-4 ያለውን ቃል ልብ ብለው ቢመለከቱት ቅዱስ ጳውሎስ ስለ የትኞቹ ባለ ሥልጣኖች እየተናገረ እንደሆነ በተረዱ ነበር፡፡ “ገዥዎች ለክፉ አድራጊዎች እንጅ መልካም ለሚያደርጉ የሚያስፈሩ አይደሉምና፡፡ ባለ ሥልጣንን እንዳትፈራ ትወዳለህን? መልካሙን አድርግ ከእርሱም ምስጋና ይሆንልሀል” ይሄንን ቃል በሚገባ መረዳት እንድንችል አሁን ካለንበት ሥርዓት ሥራ ጋር እንይ ፡፡ ቃሉ እንዳለው ‹‹ገዥዎች ለክፉ አድራጊዎች እንጅ መልካም ለሚያደርጉ የሚያስፈሩ አይደሉምና›› በሚለው ቃል ግልጽ ባለ መልኩ ስለ የትኞቹ ገዥዎች እንደተናገረ አሳይቷል፡፡ በዘመንኛ አገላለጽ ለፍትሕ ለቆሙ ወይም ዲሞክራት ለሆኑ ማለቱ እንጅ እጃቸውን በንጹሐን ደም ለሚያጥቡ ግፈኞች ማለቱ እንዳልሆነ ግልጽ ነው ምክንያቱም ‹‹መልካም ለሚያደርጉ የሚያስፈሩ አይደሉምና›› ብሏልና ለፍትሕ የቆሙ ወይም ዲሞክራት መሪዎች መልካም ለሚያደርጉት ማለትም ለሕግ የበላይነት ለሚታገሉት፣ ለሰብአዊ መብቶች ለሚጮሁት፣ ፍርድ ተጓደለ ደሀ ተበደለ እያሉ ስለተበደሉትና መብታቸውን ስለተነፈጉት ለሚጮሁት፣ ግፉና ጭቆናን ለሚቃወሙት ለሚሟገቱት የሚያስፈሩ አይደሉምና ብሏልና፡፡ እንኳን ሊያስፈሩ ይሄንን በማድረጋቸው ማለትም መልካም ሥራ በመሥራታቸው ፍትሕ እንዲሰፍን በመታገላቸው እንዲያውም ከእነሱም ምስጋና ይሆንልሀል፡፡ በማለት እያወራላቸው ያላቸው ባልሥልጣናት ስለ የትኞቹ ዓይነቶች እንደሆነ ግልጽ አድርጓል፡፡ ይሄንን ጉዳይ በሀገራችን ላይ ባለው ተጨባጭ ሁኔታ ብናየው ነገሩ የተገላቢጦሽ ሆኖ እናገኘዋለን ምክንያቱም የኛ ባለሥልጣናት የሚያስፈሩት ክፉ ለሚያደርጉት ማለትም ሰብአዊ መብትን ለሚረግጡት ፍርድ ለሚያጓድሉት፣ ለሚጨቁኑት፣ ግፍ ለሚያበዙት ፣ ለሚመዘብሩት፣ በደል ለሚያደርሱት፣ ፍትሕ ለሚነፍጉት፣ ለሚያንገላቱት ሳይሆን ለሕግ የበላይነት ለሚታገሉት፣ የፍትሕ ያለሕ፣ የመንግሥት ያለህ፣ የዳኛ ያለህ፣ የሕግ ያለህ ለሚሉት ለተጨቆኑት የሰብአዊ መብት እረገጣ ለደረሰባቸው ወገኖች ለሚጮሁት፣ ፍርድ ተጓደለ ድሀ ተበደለ ለሚሉት፣ ግፉና በደል ስለ ደረሰባቸው ምስኪኖች ለሚጮሁት፣ ለሕዝብ ሁለንተናዊ ነጻነት ለሚታገሉት፣ እውነት ለሚናገሩት እንደሆነ አእምሮ ላለው ሁሉ ግልጽ ነው፡፡ በመሆኑም እራሳቸው ክፉ አድራጊዎችና መልካም የሚያደርጉትንም የሚያመሰግኑ ሳይሆኑ የሚሳድዱ የገቡበትም ገብተው ድራሻቸውን የሚያጠፉ መሆናቸው ግልጽ ነው በመሆኑም ይህ የአገዛዝ ሥርዓት ቃሉ ከሚልላቸው ባለሥልጣናት ዓይነቶቹ በተቃራኒ ያለ መሆኑ ግልጽ ነውና ይሄንን ቃል ለሚጠቅሱ አባዮችና እራሳቸውን ለሚያታልሉ የዋሀን በቃሉ የሚያምኑ ከሆነ ጥቅሱ ላይ በቁትር 4 ላይ ያለውን ማለትም ‹‹ቁጣውን ለማሳየት ክፉ አድራጊውን የሚበቀል የእግዚአብሔር አገልጋይ ነውና›› እንዳለ ሁሉ በሀገርና በሕዝብ በቤተክርስቲያንም ላይ ክፉ የሚያደርገውን በመበቀል የእግዚአብሔር አገልጋይ ለመባል እንዲተጉ ማሳሰብ እወዳለሁ፡፡ 
        እናም ቃሉ ምንም የሚያምታታ ነገር የሌለበት ጥርት ባለ መልኩ እንዳስቀመጠው ቅን ፈራጅ ለሆኑት ለሕዝብ ልብ በሉ “ለሕዝብ” ሁለንተናዊ ደኅንነት ሰላምና ጤና ለቆሙት ባለሥልጣናት ማለቱ እንጅ እንደነ ዲዮቅልጥያኖስ ፣ መክስምያኖስ በሀገራችን ደግሞ ዮዲት ጉዲት፣ ግራኝ መሐመድ፣ በወረራ መጥቶ ለነበረው ለፋሺስት ጣሊያን ዓይነቶች ሁሉ ተገዙ ማለቱ አይደለም፡፡ ለእንደነዚህ ዓይነቶቹ እንኳን ልንገዛላቸውና ክብር ልንሰጣቸው የእግዚአብሔር ሰላምታ እንኳን እንዳንሰጣቸው ሐዋርት በበርካታ ቦታዎች ላይ እያለቀሱም ጭምር አበክረው አስጠንቅቀዋል፡፡ ቸር ይግጠመን፡፡
                                            ሠዓሊ አምሳሉ ገ/ኪዳን አርጋው
                                            amsalugkidan@gmail.com

3 comments:

 1. ሰላም ጤና ይስጥልኝ እንደምን ከረማችሁ።

  ይድረስ ከሰዓሊ አምሳሉ።

  እኛ ባሁኑ ዘመን የምንኖር ኢትዮጵያውያን ብዙ ተምታቶብናል። በተለይ አዕምሯችን በምእራባውያን ትምህርትና ባህል ከተመረዘ ወዲህ እምነትንም ቢሆን የያዝነው በማስመሰል ነው። በርግጥ የቁጭትህ መንስኤ በደልን መጥላት ቢሆንም አንተ ያቀረብከው አማራጭ እራሱ “አልሸሹም፤ ዘወር አሉ።” እንደሚባለው ነው። አንዳንዶቹን የተደበላለቁትን አስተያየቶችህን ጠቁሜ አንተም ሆነ እኔ ጥበብን እንድንሻት ላሳስብ እወዳለሁ።

  በመጀመሪያ “ፖለቲካ” እውነተኛ ትርጉሙ አንተ ያልከው ሳይሆን የኛ አገር ባላገሮች እንደሚሉት ነው። “ፖለቲካ” ማለት ገቢራዊ ትርጉሙ (true sense) ውሸት ማለት ነው። ፖለቲካ ምን ማለት እንደሆነ ለማወቅ የፈረንጆችን መዝገበ ቃላት በማገላበጥ ትርጉሙ ይህ ነው ማለት የጉዳዩን ምስጢር ለማወቅ ለሚፈልጉ ሰዎች ፍትህ ያለው መልስ አይሆንም። ትርጉሙን ለማወቅ ጉዳዩን የፈለሰፉት ሰዎች እንዴት እንደሚሚጠቀሙበት መመርመር ያስፈልጋል። በምእራባውያን አገሮች ፖለቲካ ምንድን ነው? በትረ መንግሥትን ስለመጨበጥ የሚንቀሳቀሱት ፓርቲዎች በትረ መንግሥት ለመጨበጥ የሚያስችላቸውን ሸፍጥ ሁሉ መሥራት ፖለቲካ ይባላል። ሁሉም የፖለቲካ ፓርቲዎች አላማቸው በትረ መንግሥት መጨበጥ እንጂ እውነትን ማራመድ ባለመሆኑ ዘወትር መንገዳቸውን ሲቀያይሩ እናያለን። በትረ መንግሥትም ከጨበጡ በኋላ ብዙ ክፋትን ይሠራሉ ይህን ክፋት መልካም አስመስለው የሚናገሩበት ቋንቋ ፖለቲካ ይባላል። ለምሳሌ “ብሔራዊ ጥቅም” (national interest) የሚባለውን ፖለቲካ ማየት በቂ ነው። በሩቅ ያሉ የራሳቸውን ሥራ እየሠሩ የእለት ኑሯቸውን የሚገፉ ሌሎች አገሮችን በማመስ፣ በማበጣበጥና በማዋጋት ከሚኖረው የሌሎች አገሮች ውድቀት ትርፍ ማግኜትን ነው ምእራባውያን “ብሔራዊ” ጥቅም” የሚባል የፖለቲካ ልብስ ያለበሱት። “ብሔራዊ ጥቅም” ብለው ሲነግሩት የአገራቸው ሰው ወኔው ይቀሰቀሳል። እንደምታያው ባጭሩ ፖለቲካ ማለት ዝርፊያ ወይም ቅሚያ ወይም ማጋደል ወይም መግደል “ብሔራዊ ጥቅም” ተብሎ የሚሰየምበት የሃሰት ዘይቤ ነው። ፖለቲካ በኮርፖሬት ሥራዎችም ውስጥ አለ። ብዙ ጊዜ በአንድ ባለስልጣን የሚመራ ቡድን በሌላው ባለሥልጣን የሚመራውን ቡድን ለመጣል የሚደረግ የውስጥ ለውስጥ የማጣጣል ቁርቁስ ነው። ብዙ ጊዜ አንዱ የሌላውን ሥራ - ትክክለኛ የሆነውን ሙከራ ሳይቀር ያጣጥላል። አላማው የአንዱን ቡድን ባለ ስልጣን ጥሎ የሌላውን ቡድን ባለስጣን በስልጣን ከፍ ማድረግ ነው። በመስሪያ ቤት ፖለቲካ ውስጥ እውነት ቦታ የላትም። ፖለቲካ በሳይንስ ውስጥም አለ። በተለያየ “የመጠቁ የምርምር ጣቢያዎች” ውስጥ የተሰማሩ “የሳይንስ ተመራማሪዎች” የፖለቲካ ቡድን አላቸው። በሳይንስ በተለይም በፊዚክስ ውስጥ ጎሳዎች ተብለው ይጠራሉ። የትኛውም “ተመራማሪ” የአንዱ ጎሳ አባል ካልሆነ ምንም ያህል ቢመራመር ሥራው ከቆሻሻ መጣያ ውጭ ሌላ እጣ አይኖረውም። ለምሳሌ የሉፕ ኳንተም ግራቪቲ ጎሳዎች የስትሪንግ ቲዮሪን ጎሳዎች ያጣጥላሉ። አዲስ ተመራማሪ ሌላ ነገር ይዞ ቢመጣ ከንዱ ጎሳ ካልወገነ እንኳን ሃሳቡን የሚቀበልለት ጽሁፉን የሚያነብለትም አያገኝም። ይህ የሳይንስ ፖለቲካ ነው። በነገራችን ላይ ፊዚክስ እራሱ ፖለቲካ ሆኖ ቀረ እንጂ እውነትን አላገኛትም።

  አንተን ወዳሳሰበህ “ፖለቲካ” ብለህ ስለጠራኸው ወደ አገራችን ጉዳይ እንምጣ። ለአገራችን ለኢትዮጵያ ቅዱሳን መጻህፍት የሚያዙላት በንጉሥ መተዳደርን እንደሆነ ታውቃለህን? የጥንት ቅዱሳን መጻሕፍትንማ ተዋቸው፤ ሌላው ቀርቶ በአዲስ ኪዳን ትርጓሜ ሰፍሯል። እንዲያውም የቅዱሳን ትንቢት በኢትዮጵያ ቀደም ያለው ፍካሬ ኢየሱስ በትንቢቱ የኢትዮጵያ ውድቀት የሚመጣው ኢትዮጵያውያን የንጉሥ አስተዳደርን ሲጥሉ እንደሆነ ይናገራል። እንደትንቢቱም ተፈጸመ። ብጹዕ ወቅዱስ አቡነ ባስሊዮስ የነ መንግሥቱ ንዋይን መፈንቅለ መንግሥት ሲያወግዙ የተናገሩት ቃልም ይህ ነው። ኢትዮጵያ የምትተዳደረው ከጥንት ጀምሮ እግዚአብሔር በቀባው ንጉሥ እንጂ በመፈንቅለ መንግሥት ወይም በሰው ሹመት አይሆንም። የኢትዮጵያ በትረ መንግሥት በቅዱስ አብርሃና አጽብሃ ዘመን ለንጉሠ ነገሥቱ ለኢየሱስ ክርስቶስ በመባነት ተሰጥቷል። ለእግዚአብሔር የተሰጠን መባ ሰው መልሶ ሊወስድ ይችላልን? የቅዱስ ዳዊት ትውልድ ያላቸው ነገሥታት በቤተክርስቲያን እየተቀቡ የሚነግሱት በቦታ ያዢነት እንጂ እውነተኛው የኢትዮጵያ ንጉሠ ነገሥት ኢየሱስ ክርስቶስ ነው። ሞዓ አንበሳ ዘእምነገደ ይሁዳ የሚባለውም ስልጣኑ የክርስቶስ መሆኑን ለማመልከት ነው። (ይቀጥላል)

  ReplyDelete
 2. (የቀጠለ) ....ነገስታት ህዝብን በደሉ፣ የእግዚአብሔርን መንገድ አልተከተሉም ብሎ አምጾ ከስልጣን እንዲወርዱ ማድረግና በምትካቸው እግዚአብሔርን የሚፈራ፣ በቤተክርስቲያን የተቀባ ንጉሥ እንዲሾም ማድረግ ከጥንት ከአባቶቻችን የነበረ ነው። ለምሳሌ ንጉሱ ሓጸኒ መልአክ ሰገድ (ሱስኒዮስ) እምነታቸውን በመቀየራቸው ምክንያት ኢትዮጵያውያን ከየቦታው ተሰባስበው በተለይ ደንቀዝ ላይ በማመጽ ሐጸኒ መልአከ ሰገድ እንዲወርዱና ጥር ፲፪ ቀን ፲፮፻፳፬ (1624) ዓ.ም. ሐጸኒ ዓለም ሰገድ (ፋሲል) በቤተክርስቲያን ተቀብተው እንዲነግሡ አደረጉ። እግዚአብሔርም የኢትዮጵያውያንን ፍትሕና እግዚአብሔርን መሻት ተመልክቶ ለሚቀጥሉት አንድ መቶ አምሳ አመታት ለኢትዮጵያ ብልጽግናና በረከትን አትረፈረፈላት። ውድቀት የጀመረው ከአንድ መቶ አምሳ አመት በኋላ ከጥጋብ የተነሳ ሃጢአትና ክፋት በመብዛቱ ነበር።

  እንደምናየው በኢትዮጵያ በትረ ስልጣን የክርስቶስ ነው ሆኖም ግን ሐጸኒ ኃይለስላሴ በእንግሊዞች አማካሪነት “ሃገር የጋራ ነው፣ ኃይማኖት የግል ነው” በማለት ክርስቶስን ከአስተዳደራቸው ሲያወጡት አለቃ አያሌው በፊታቸው ቀርበው “እንዚህ አሁን ሃይማኖት የግል፤ ሃገር የጋራ ይባል እያሉ የሚያማክርዎ የውጭ አገር ሰዎች ነገ እርስዎ በወደቁ ጊዜ ባጠገብዎት አይገኙም። አሁን ጥለውት በወደቁ ጊዜ እግዚአብሔርን ቢፈልጉት ከየት ያገኙታል” እንዳሏቸው አንተም ቢሆን ሳትሰማ አትቀርም። እንዳሉትም ንጉሱ ሲወድቁ ያማከሯቸው ካጠገባቸው አልተገኙም። አሁን አንተና በውጭ ሲኖዶስ ነን የሚሉት “ፖለቲክ” የምትሉን ያን አባቶቻችን ያቆዩልንን ትውፊት፣ እሱም በትረ ስልጣን የክርስቶስ መሆኑን አይደለም። ስለ መንግሥት አትናገሩ የሚሉትም በመልክ ክርስቲያኖች ይምሰሉ እንጂ የመረጡት ሞዓ አንበሳ ዘእምነገደ ይሁዳ ክርስቶስን ሳይሆን በስነደቅ አላማው ላይ “የብሄሮች መብት” የሚል የሃሰት ትርጎም የተሰጠውን የሉሲፈርን ፔንታግራም ነው። አሁን ኢትዮጵያ የምትመራው በክርስቶስ ጠላቶች ነው። በውጭ አገር ያሉ “የፖለቲካ ፓርቲዎች” በሙሉም የክርስቶስ ጠላቶች ናቸው። የክርስቶስን መንበር በአመጽም ሆነ “በዲሞክራሲ” የሚሻ የክርስቶስ ጠላት ብቻ ነው። በነገራችን ላይ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ተጠብቃ የኖረችው፣ እስልምናና ክርስትናም “ተቻችለው ኖሩ” የሚባለው ኢትዮጵያ የክርስቶስ አገልጋይ በሆኑ ነገሥታት ስለተዳደረች ነበረ። እስኪ ንግረኝ ሰዓሊ አምሳሉ፥ ዴሞክራሲ እያሉ በሚታገሉ ፓርቲዎችና እኔ ነኝ ዴሞክራሲ እያለ በሚመራው ፓርቲ መካከል ምን ልዩነት አለ? ሁሉም ክርስቶስን አይፈልጉም። ክርስቶስን የሚፈልግ አንድ ፓርቲ ልትጠራ ትችላለህ? በርግጥ ነው እንደጥንቱ የክርስቶስን መንበር እንመልስ፣ እግዚአብሔር በቀባው ንጉሥ መተዳደር አለብን እያለ የሚታገል ቡድን ወይም ድርጅት ካለ እሱን መደገፍ በርግጥ እግዚአብሔር የሚወደው ሥራ ነው። እንደዚህ አይነት ቡድን አለ ወይ? ሌላው ቀርቶ የዘውድ ምክር ቤት እያለ እራሱን የሚጠራው እንኳን ሰውን ከፍ ከፍ ስለማድረግ፣ ስለ ማስመሰልና፣ ለራሳቸው ክብርን ከመፈለግ ውጭ እግዚአብሔርን ሲፈልጉ አይታዩም። እነሱም እንደሌሎቹ “ፓርቲዎች” የክርስቶስ ተቃዋሚዎች ናቸው። “ዴሞክራሲ ዴሞክራሲ”ም ትላለህ። ዴሞክራሲ ምን እንደሆነ የምታውቀውም አትመስልም። ዴሞክራሲ ምእራባውያን የሌሎች አገሮችን በር ለመክፈትና ጥሬ ሃብታቸውን ለመመጥመጥ የሚጠቀሙበት ስልት እንጂ ፍትህ ማለት አይደለም። ምእራባውያን የማይዘርፉት የአፍሪካ አገር የለም። ምእራባውያን ባገራቸው ውስጥ አንድ ሰው፤ በውጭ አገር ደግሞ ሌላ ሰው መሆን ይችላሉን? በግብራቸው ውጭ አገር ሄደው የሚዘርፉ ሆነው እያየሃቸው በፍልስፍናቸው እውነተኞች ናቸው እንዴት ልትል ትችላለህ? ዴሞክራሲንስ ከፈጣሪዎቹ ከምእራባውያን በላይ ማን ሊያውቀው ይችላል? በኢትዮጵያ የሚገኘውን ገዢ ፓርቲ እነሱው ኮትኩተው አሳድገው ነው ለስልጣን ያበቁት። ዴሞክራሲ ማለት የራስን እድል በራስ የመወሰን መብትን ማስከበርና መገነጣጠል ነው ብለው ለገዢው ፓርቲ ማህተም አድርገውለታል። በ”ዴሞክራሲ” የምታምን ከሆነ እነሱ ማህተም ያደረጉበትን ሥርአት መቀበል አይኖርብህምን?

  ወንድሜ ሆይ፥ አባቶቻችን ለእግዚአብሔር የሰጡትን መባ ለእግዚአብሔር እንመልስ ብለህ ከተነሳህ እኔ ከጎንህ እቆማለሁ። ጥበብን በዛ መንገድ አንተም ሆነ እኔ እንሻት። ያለዛ ግን ከጭቃ ወደ ጭቃ ለመንቦራጨቅ “ፖለቲካ ፖለቲካ” ማለት በእግዚአብሔርም ቤት ቦታ የለውም በአካላዊ ምድርም ትርፍ አይገኝበትም።

  እግዚአብሔር የተመሰገነ ይሁን።
  ኃይለሚካኤል።

  ReplyDelete
 3. God Bless you Hailemichael! This person always wites randomly. let's write what can help others to be more bright.

  ReplyDelete