Monday, December 9, 2013

በፔርሙዝ ተለውጦ አሜሪካ የተሻገረው የ400 ዓመቱ ብራና


08 December 2013 ተጻፈ   ፍቅር ለይኩን
  •  የቅርሶቻችን ዋጋ ምን ያህል ነው?

(ሪፖርተር ጋዜጣ):-  የተባበሩት መንግሥታት የትምህርት፣ የሳይንስና የባህል ድርጅት (ዩኔስኮ)...በዓለም ጥንታዊ ቅርስነት ከመዘገባቸው የሥነ ጽሑፍ ውጤቶች መካከል በኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን ባለቤትነት የተመዘገቡና በብራና ላይ የተጻፉ የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍሎች የነገረ ሃይማኖት ጽሑፎች ይገኙበታል፡፡


 እነዚህ እስከ ሺሕ ዓመታት ዕድሜን ያስቆጠሩ ብርቅና ውድ የሆኑ የሥነ ጽሑፍ ቅርሶች በተለያዩ ጊዜያት በአገሪቱ በደረሱ ተፈጥሮአዊና ሰው ሠራሽ አደጋዎች ምክንያት ውድመት፣ ጥፋትና ዝርፊያ እንዳጋጠማቸው ይታወቃል፡፡ከዚህም በተጨማሪ በጥናትና በምርምር ሰበብ ከአገር የወጡ ጥንታዊ ብራናዎች አያሌ ናቸው፡፡ በአውሮፓና በአሜሪካ በሚገኙ ትላልቅ ዩኒቨርሲቲዎችና አብያተ መጻሕፍት፣ እንዲሁም በግለሰቦች፣ በቅርስ አሻሻጮች እጅም ማግኘት የተለመደ ነው፡፡

በኢትዮጵያ ጥንታዊ የሥነ ጽሑፍ ቅርሶች፣ ጥንታዊ የብራና መዛግብት፣ መጻሕፍትና ጠልሰሞች (Magical Scrolls) ላይ በተለያዩ ጊዜት ሰፋ ያለ ምርምርና ጥናት ያደረገው አሜሪካዊው ምሁር ፕሮፌሰር ስቲቭ ከሰባት ዓመት በፊት በዋሽንግተን ዲሲ፣ በዓመታዊው ‹‹ለሶሳይቲ ኦፍ ባይብሊካል ሊትሬቸር›› ዓለም አቀፍ ስብሰባ ላይ ‹‹Scribal Practice in Ethiopian Psalters as Expression of Identification and Differentiation›› በሚል ርእስ በርካታ ተሳታፊዎችን ያስገረመና ያስደመመ አንድ እውነተኛ ገጠመኙን በማስቀደም ሰፋ ያለ ጥናታዊ ጽሑፍ አቅርቦ ነበር፡፡
ስቲቭ በዚህ ጥናታዊ ወረቀቱ ላይ በተለይ በኢትዮጵያ ጥንታዊ ጽሑፎችና መዛግብት ላይ የበለጠ ትኩረት ሰጥቶ እንዲያጠና ያደረገውን አንድ ለየት ያለ ገጠመኙን ለተሳታፊዎቹ ገልጾ ነበር .. ከስምንት ዓመት በፊት ከአንድ በአካል ከማያውቀው ሰው ዘንድ የስልክ ጥሪ ይደርሰዋል፡፡ ጥሪውም ስቲቭ ከሚኖርበትና በመኪና 45 ደቂቃ ጉዞ ከሚፈጀው ከአሜሪካዋ የኦሬገን ክፍለ ግዛት ነበር፡፡ ደዋዩም አሜሪካዊ ለስቲቭ ስልክ እንዲደውልለት ያስገደደውን ምክንያቱን በአጭሩ ገለጸለት፡፡
‹‹39 ዓመት በፊት (.. 1966) ከአሜሪካ የሰላም ጓድ ሠራዊት አባል ሆኜ በባሕር ዳር ከተማ ለጥቂት ወራት ቆይታ አድርጌ ነበር፡፡ በአንድ የዕረፍቴ ቀንም ከባሕር ዳር ከተማ ባሉ ገጠራማ ቀበሌዎች ወጣ ብዬ ስንሸራሸር ድንገት በመንገዴ ላይ አንድ ዕድሜው በጎልማሳነት ደረጃ ከሚገኝ የገጠር ሰው ጋር ተገናኘሁ፡፡ 
እንደ ሀገሩ ባህልም ከዚህ ፊቱ በፈገግታ ከተሞላ ጎልማሳ ሰው ጋር ሰላምታ ከተለዋወጥን በኋላ ቋንቋችን ለየቅል በመሆኑ የተነሣ መግባባት ቢያዳግተንም እንደምንም በምልክት ለመግባባት ጥረት አደረግን፡፡ ከአፍታ ቆይታም በኋላ ጎልማሳውን ሰው በአካባቢያችን ከሚገኘው የዛፍ ጥላ ሥር አረፍ እንድል በምልክት ነገርኩት፡፡ በፈገግታ ፈቃደኝነቱን በአንገቱ በማወዛወዝ ገልጾልኝ አብረን ተቀመጥን፡፡ ከዚያም በእጄ በያዝኩት የሻይ መያዣ ፔርሙዝ ግሩም ሻይ ቀድቼ ለእንግዳዬ ጋበዝኩት፡፡ እንግዳውም ሰው በግብዣዬ ተደስቶ በብዙ ካመሰገነኝና ከመረቀኝ በኋላ ዓይኑን በሻይ መያዣ ዕቃዋ ላይ ሲንከራተት ደጋግሜ አስተዋልኩት፡፡ 
‹‹እኔ በበኩሌ ገና ስንገናኝ ጀምሮ ይህ ሰው ባነገተውና በእጅጉ በተዋበችው የቆዳው ቦርሳው ላይ ዓይኔን ጥዬ ነበር፡፡ እናም ይህን ሰው አግባብቼና በምልክትም ቢሆን ተስማምተንና ተግባብተን በሻይ መያዣ ዕቃዬ/ፔርሙዜ ላይ አስር የኢትዮጵያ ብር ጉርሻ ጨምሬለት ባነገተው ቦርሳ ተቀያየርን፡፡ ይህችን በውስጧ በግሩም ሁኔታ የተደጎሰች መጽሐፍ የያዘችው የቆዳ ቦርሳ (ማኅደርም) የኢትዮጵያን ምድር ተሻግራ በአሜሪካ ይኸው ከእኔ ጋር ላለፉት 39 ዓመታት ቆይታለች፡፡
‹‹አሁን ግን ቦርሳው ውስጥ ያለው በከፍተኛ ጥንቃቄ የተዘጋጀውና በተዋቡ ሐረጎች ያሸበረቀው ይህ ጥንታዊ የሚመስል መጽሐፍ ምን መሆኑን አንተና መሰል ምሁራን ትመረምሩት ዘንድ ልሰጥህ እፈልጋለሁና እባክህ እንገናኝ በማለት ጠየቀኝ፡፡ስቲቭ በዚሁ ጥናታዊ ወረቀቱ ላይ ትረካውን ሲቀጥል፡- ‹‹እኔም አድራሻውን ከተቀበልኩት በኋላ በጉጉትና በፍጥነት ወዳለበት ድረስ በመሄድ ያን 39 ዓመታት ከዚህ አሜሪካዊ የሰላም ጓድ ጋር የቆየውን መጽሐፍ ከነቆዳ ማኅደሩ ከታላቅ ምስጋና እና ጠቀም ካለ ጉርሻ ጋር በደስታ ተቀበልኩት፡፡
በአሜሪካዊው ምሁር ፕሮፌሰር ስቲቭ አገላለጽ፣ አስደናቂው ነገር እጅግ ባማረ ሁኔታ በኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን ሊቃውንት አስደናቂ ዕውቀትና ጥበብ የተዘጋጀ፣ በእጅጉ የተዋበና የዘመን መለዋወጥ በጭራሽ ያላስረጁት ትንግርተኛ መጽሐፍ 17ኛው መቶ ክፍለ ዘመን ‹‹መዝሙረ ዳዊት›› ሆኖ ነበር የተገኘው፡፡ 400 ዓመታት ገደማን ያስቆጠረ መዝሙረ ዳዊት ነበር፡፡
ስቲቭ በዚሁ ጥናታዊ ወረቀቱ እንደገለጸው፣ .. 2005 እስከ 2006 ከአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ የኢትዮጵያ ጥናትና ምርምር ተቋም፣ የጥንታዊ መዛግብትና የብራና ጽሑፎች ክፍል ጋር በመተባበር ባደረገው አሰሳና ጥናት፣ በአንድ ዓመት ውስጥ ብቻ በዓለም ዙሪያ 240 በላይ የሚሆኑ በተለያዩ ዘመናት የተጻፉ ጥንታዊ የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን ብራናዎችና ጠልሰሞችን አሰባስቦ ከኢትዮጵያውያንን ከሌሎች አገሮች ምሁራን ጋር ካታሎግ ለማድረግ መቻሉን ይገልጻል፡፡
በተለያዩ ዘመናት በተለያዩ ጉዳዮችና ሰበቦች ወደኢትዮጵያ የመጡ የውጭ ሰዎች በዚህ መልኩ መንፈሳዊና ታሪካዊ ቅርሶችን ወደ አገራቸው አሻግረውታል፡፡ ዛሬ ዓለም የሚደነቅበትና በኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን ጥንታዊ ቋንቋ በኾነው በግእዝ የተዘጋጀው ‹‹መጽሐፈ ሔኖክ፣›› የዓባይን መነሻ አስሳለኹ ብሎ 17ኛው መቶ ክፍለ ዘመን  ወደ ኢትዮጵያ በመጣው ስኮትላንዳዊው ተጓዥ ጀምስ ብሩስ ወደ አውሮፓ ለመሻገር የበቃው፡፡
ፕሮፌሰር ስቲቭ በዚሁ ጥናታዊ ወረቀቱ በተለያዩ ጊዜያትና አጋጣሚዎች ከኢትዮጵያ ወጥተው በውጭ ሀገራት የሚገኙ የኢትዮጵያን ጥንታዊ የብራና መጻሕፍትና መዛግብትን እንደሚከተለው በዝርዝር አቅርቦታል፡፡ በብሪትሽ ቤተ መጻሕፍት 598 በጀርመን ዩኒቨርስቲዎችና ቤተ መጻሕፍት 545 በኦክስፎርድ ዩኒቨርሰቲ 115 በካምብሪጅ ዩኒቨርስቲ ቤተ መጻሕፍት 69 በአይርላንድ ዱብሊን በሚገኘው ረይላንድ ቤተ መጻሕፍት 58 በማንችስተር ዩኒቨርስቲ 45 በሩሲያ ቅዱስ ፒተር ስፐርግ 275 በአሜሪካ 133 በዱክ ዩኒቨርስቲ 33 ጥንታዊ ብራናዎች እንደሚገኙ ጠቁሟል፡፡
በተጨማሪም በእንግሊዟ ንግሥት ቤተ መንግሥት ውስጥ በሚገኘው ሮያል ቤተ መጻሕፍት ውስጥ 150 አብዛኞቹ በመቅደላ ወረራ ጊዜ ከኢትዮጵያ የተዘረፉ እጅግ ውብና ጥንታዊነ የሆኑ የሥነ ጽሑፍ ቅርሶቻችን ይገኛሉ፡፡ እነዚህን ጥንታዊ ብራናዎች ለማየትም ሆነ ለመመርመር ከንግሥቲቱ ዘንድ ልዩ ፈቃድ እንደሚያስፈልግ ምሁራን ያስረዳሉ፡፡
በእርግጥ ፈረንጆቹ ሰርቀውም ሆነ ገዝተው ወይም በስጦታ አግኝተው ወደ ሀገራቸው የወሰዷቸውን ጥንታዊ የሥነ ጽሑፍ ቅርሶችን በክብር በማስቀመጥ፣ በመንከባከብ፣ በልዩ ጥንቃቄ በሳይንሳዊ መንገድ አጥንተውና አስጠንተው ለዓለም ማስተዋወቃቸው አልቀረም፡፡በእጃችን የሚገኙ ጥንታዊ የሥነ ጽሑፍ ቅርሶችን አያያዝና አጠባበቅን፣ እንዲሁም ያሉበትን ሁኔታ የታዘቡ ሰዎች አንድ አበክረው የሚሉት ነገር አላቸው፡፡ ይኸውም ለታሪካችንና ለቅርሶቻችን ክብር፣ ዋጋና ጠቀሜታ ምን ያህል መሆኑ በቅጡ እስኪገባን ድረስ እነዚህ በተለያዩ ጊዜያትና አጋጣሚዎች ከአገራችን የወጡ ብርቅዬና ውድ የሆኑ ቅርሶቻችን በሚገኙበት ውጪ አገሮች እንዳማረባቸው ተጠብቀውና ተከብረው ቢኖሩ ይሻላል በማለት አስተያየታቸውን ይሰጣሉ፡፡
በእነዚህ ሰዎች አስተያየት በከፊል የሚስማሙ አሉ፡፡ በርካታ አስተያየት ሰጪዎች ወደ ውጭ ስለወጡትና እየወጡት ስላሉት የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን ጥንታዊ መጻሕፍት ሲቆጩና ለምን ሲሉ ይሰማሉ፡፡ ግን እዚሁ በአገሪቷ ውስጥ እየጠፉና እየወደሙት ስላሉት በርካታ መዛግብትና ቅርሶች እምብዛም የሚቆረቆር አይታይም፡፡ የአገሪቱ መንፈሳዊ፣ ጥንታዊና ታሪካዊ ቅርሶችን በተመለከተ አሁንም በሚመለከታቸው የመንግሥት አካላት፣ የሃይማኖት ተቋማት፣ የታሪክ ምሁራን፣ የቅርስ ባለሙያዎች፣ በቱሪዝም ኢንዱስትሪ ውስጥ ያሉ የግል ባለሀብቶችና ድርጅቶች ትኩረት ሰጥተው መሥራት እንደሚገባቸው የሚወተውቱት ቁጥር ቀላል አይደለም፡፡

2 comments:

  1. ባለቤት የሌላት ሀገርና ቤተ ክርስቲያን ፤ ተቆርቋሪና ተንከባካቢ የሌላቸዉ የሀገር ቅርሶች። እጅግ ራስ ወዳድና ለእኔ ካልሆነ በስተቀር ሳር አይብቀልብሽ የሚሉ ከዚች ቅድስት ሃገር የበቀሉ ይሁዳዎች የበዙበት ዘመን።
    ያባቶቻችን አምላክ ልብ ይስጣቸው፤ ሃገራችንና ቤተክርስቲያናችንን በቸርነቱ ይታደግልን አሜን።

    ReplyDelete