(አንድ አድርገን ጥቅምት 19 2006 ዓ.ም)፡- ዛሬ ማለዳ ከጠዋቱ 11 ሰዓት ላይ ከሰሜን ሆቴል ወደ ጊዮርጊስ ቁልቁል ሲሄድ የነበረ አንድ ከባድ የጭነት ማመላለሻ(SINO TRUCK) መኪና ባጋጠመው የፍሬን ችግር ምክንያት ሹፌሩ መኪናውን መቆጣጠር አቅቶት ቀጥታ ገነተ ጽጌ ቅዱስ ጊዮርጊስ ቤተክርስቲያን ቅጽርን ደርምሶ በመግባት ከፍተኛ አደጋ አድርሷል ፡፡ በወቅቱ በቦታው ላይ በእቅልፍ ላይ የነበሩ ሁለት ጎዳና ተዳዳሪዎች ወዲያውኑ ሕይወታቸው ሲያልፍ ተጨማሪ ሶስት ሰዎች ላይ ከባድ የሆነ አደጋ ደርሶባቸዋል ፤ ከፍተኛ አደጋ የደረሰባቸው ሶስቱ ሰዎች ወዲያውኑ በእሳት አደጋ ሰራተኞች እና አካባቢው ላይ ባሉ ሰዎች ጥረት ራስ ደስታ ሆስፒታል ተልከው ጊዜያዊ እርዳታ ከተደረገላቸው በኋላ ጉዳቱ ከፍተኛ በመሆኑ ወደ ጥቁር አንበሳ ሆስፒታል ተወስደዋል ፡፡ በአደጋው የቤተክርስቲያኑ መግቢያ በር እና ግንብ ከፍተኛ አደጋ የደረሰበት ሲሆን በተጨማሪ ሰው በፍርስራሽ ውስጥ ይኖራል ተብሎ በመገመቱ በአደጋ ጊዜ ሰራተኞች ፍርስራሹን የማንሳት ስራ ሲያከናውኑ ተስተውሏል፡፡ የደረሰው አደጋ አሰቃቂ መሆኑን በቦታው የነበሩ ሰዎች ተናግረዋል፡፡
ከአደጋው በኋላ የመኪናው ሹፌር በሰጠው ቃል መሰረት የመኪናው ንፋስ እምቢ በማለቱ አደጋው የደረሰ መሆኑን ተናግሯል፤ በአሁኑ ሰዓት ፖሊስ የመኪናው ሹፌር ላይ ተጨማሪ ምርመራ እያካሄደ መሆኑን ለማወቅ ተችሏል፡፡
No comments:
Post a Comment