Thursday, November 7, 2013

የማኅደረ ስብሐት ልደታ ለማርያምና ደብረ መድኃኔዓለም ቤተ ክርስቲያን በሶስት ዓመት ውስጥ 4.6 ሚሊየን ብር መመዝበራቸው ተገለጠ


  •  የታገድነው በደብሩ የተፈጸመውን ከፍተኛ የገንዘብ ምዝበራ በማጋለጣችን ነው (ሰበካ ጉባኤው)
  • ጉዳዩን አዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን የልዩ ልዩ ወንጀሎች ምርመራ ዲቪዚዮን ተይዟል፡፡ 

(አንድ አድርገን ጥቅምት 28 2006 ዓ.ም)፡- በአዲስ አበባ ደቡብ ክፍለ ከተማ የሚገኝው የማኅደረ ስብሐት ልደታ ለማርያምና ደብረ መድኃኔዓለም ቤተ ክርስቲያን የሰበካ ጉባኤ ጳግሜ 3 ቀን 2005 ዓ.ም ሕገ ወጥ ተግባር ፈጽሟል  በሚል በመታገዱ ችግር መፈጠሩ ተገለጸ፡፡

በአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ዋና ስራ አስኪያጅ የመጋቢ ሐዲስ ቀሲስ ይልማ ቸርነት ፊርማና ማኅተም ያለበት በቁጥር 450/25/06 በቀን 03/01/2006 ዓ.ም የተጻፈ ደብዳቤ እንደሚያመለክተው የደብሩ ሰበካ ጉባኤ የታገደው የሥራ ዘመኑን መጋቢት 12 ቀን 2005 ዓ.ም ቢያጠናቅቅም ሌላ የሰበካ ጉባኤ ሳይመረጥ በመቅረቱ በተለያየ ጊዜ ጭቅጭቅ ንትርክና ሁከት እንዲፈጠር በማድረጉ ማታገዱ ይገልጣል፡፡


የሰበካ አስተዳደር መንፈሳዊ ጉባኤ የደብሩ ምዕመናንና አገልጋይ ካህናት  በተገኙበት ሐምሌ 14 ቀን 2005 ዓ.ም በተደረገው ስብሰባ በሦስት ዓመት ውስጥ ከአራት ሚሊየን ስድስት መቶ ሺህ ብር በላይ  ገንዘብ በላይ የተመዘበረ መሆኑ ተገልጧል፡፡ 17 ጥራዝ ሞዴል የት እንደገባ እደማይታወቅ የሰበካ ጉባኤው ምክትል ሊቀመንበር አቶ ተስፋሁን በቀለ ማጋለጣቸውን ለማወቅ ተችሏል፡፡

ከአስር ዓመት በኋላ የቀረበ የደብሩ የሰበካ ጉባኤ ሪፖርት በሚል በደብሩ በሚዘጋጀው “ዜና ማኅደረ ስብሐት” ጋዜጣ ደግሞ የቀድሞ የደብሩ ጸሐፊ የደብሩን ማኅተም እና የቢሮ ቁልፍ ለማረከብ ፍቃደኛ ባለመሆናቸው የሙዳየ ምጽዋት ቆጠራ ለማካሔድ ፍቃደኛ ባለመሆናቸው ቃለ ጉባኤዎችንና የሞዴል ደረሰኞችን በመውሰዳቸው ደብሩ ለልደታ ክፍለ ከተማ ፖሊስ መምሪያ በማሳወቁ ምክንያት የተወሰኑትን መመለሳቸውን መረጃው ያመለክታል፡፡

ገንዘብ በትክክል ገቢ መሆኑን ለማረጋገጥ በምክትል ሊቀ መንበሩ Bank Statement ወጥቶ ሲመረመር ተቆጥሮ እንዲገባ  የተባለው ገንዘብ በትክክል ባንክ አለመግባቱን ለማረጋገጥ ተችሏል፡፡ ገንዘቡ ገቢ ባለመደረጉም በአስተዳዳሪዎችና በሒሳብ ሰራተኞች መካከል ውዝግብ ሲፈጠር ቆይቷል፡፡ በደብሩ እየተፈጠረ ያለውን ችግር በቅርብ ሲከታተሉ የቆዩ ምዕመናን ጳግሜ 3 2005 ዓ.ም የደብሩን ንብረት የመዘበሩ አካላት ጉዳይ ከምን ደረሰ ? የቤተክርስያኒን ገንዘብን ዘርፈው ጠፉ የተባሉት ሦስት ግለሰቦች ላይ ሀገረ ስብከቱ ምን ያከናወነው ተግባር አለ? በማለት ጥያቄ ሲያነሱ ቆይተዋል፡፡

ችግር ፈጥረዋል የተባሉ የደብሩ ሠራተኞች ሰበካ ጉባኤው በተለያዩ ጊዜ ለሚመለከታቸው አካላት ማሳወቁን የሰበካ ጉባኤ ምክትል ሊቀ መንበር የነበሩት አቶ ተስፋሁን በቀለ አስታውቀዋል፡፡ጉዳዩን የያዘው የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን የልዩ ልዩ ወንጀሎች ምርመራ ዲቪዚዮን  ኃላፊ ም/ኮር አበራ ቡሊና በቁጥር አ15/ወ/መ/04/1464/05 በቀን 02/12/05 ዓ.ም ለደብሩ በጻፉት ደብዳቤ በእነ አብርኽት ተክሉ የክስ መዝገብ ስድስት ሰዎች ሰነዶችን በማጥፋት ወንጀል መከሰሳቸውን ይገልጣል፡፡

አቶ ዮሐንስ በርሄ ፤ ሊቀ ስዩማን ኃ/ማርያም አብርሃም ፤ መ/ስ/ሀ/ጊዮርጊስ ዕዝራ የተባሉ ግለሰቦች ከሙዳየ ምጽዋት ተሰብስቦ በደብሩ ሰበካ ጉባኤ  ተረጋግጦ ቃለጉባኤ የተያዘ ገንዘብ ሞዴል እና ልዩ ልዩ የሒሳብ ሰነዶችን ሳያስረክቡ እና ሳያሳውቁ ወደ ሌላ ደብር መቀየራቸው ምክንያት ቤተክርስቲያኒቷ ወጪዋንና ገቢዋን እንዳታውቅ ፤ ገንዘብ ኦዲት ሳይደረግ ቀርቶ ያለ አግባብ እንዲባክን አድርገዋል ተብሏል፡፡ የተጠቀሰውን ጥፋት ሊያረጋግጥ የሚችል ማስረጃ የደብሩ ሰበካ ጉባኤ እና የደብሩ አስተዳደር እንዲልኩ በደብዳቤ ተጠይቀዋል፡፡

ስምዐ ጽድቅ ጋዜጣ የጥቅምት 2006 ዓ.ም ዕትም

(በቤተክርስያኒቱ የነገሰውን ብልሹ አሰራር የሚገልጥ መጽሐፍ ታትሞ ከዓመት በፊት በገበያ ላይ መዋሉ ይታወቃል፡፡ አስፈላጊ ከሆነ  ‹‹አንድ አድገን›› መጽፉን በመንተራስ ወደፊት የማኅደረ ስብሐት ልደታ ለማርያምና ደብረ መድኃኔዓለም ቤተ ክርስቲያንን ችግር ለምዕመኑ የምታደርስ መሆኑን ለመግለጥ እወዳለን፡፡)





1 comment:

  1. የሚገርም ዜና ነው። የድንግል ልጅ ዓን ዓማንያንን ፤ ለሆድ አደርን ልቦና እንዲሰጥ አበክረን የምንጸልይበት ዘመን ስለሆነ በጾሎት ስዓታቾ እባካችሁ እናስበው።

    ReplyDelete