Monday, September 10, 2012

‹‹ርእሰ ዐውደ ዓመት›› በኢትዮጵያ



ዛሬ ያመቱ፣ 2004 .. 364 ቀን ነው፡፡ ዓመቱ ሊያበቃ፣ ዘመኑ ሊካተት አሮጌ ኾኖ ሊያልፍና አምና የሚለውን ካባ ለመደረብ 24 ሰዓት ወይም 1,440 ደቂቃ ወይም 86,400 ሰከንድ ቀርቶታል፡፡
ርእሰ ዐውደ ዓመት (የዓመት ዙር ዋና መነሻ) በፀሐይ መስከረም 1 ቀን 2005 .. በፀሐይና ጨረቃ ጥምር ኢትዮጵያዊ አቆጣጠር 2013 ዓመት ሊብት ዘመኑም ሊሞሸር፣ ዓመቱም ሊቀመር በናፍቆት እየተጠበቀ ነው፡፡ በባህላዊውና ዓለማዊው ትውፊት ‹‹እንቁጣጣሽ›› በኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን ትውፊት ‹‹ቅዱስ ዮሐንስ›› እየተባለም ይጠራል፡፡ ቤተ ክርስቲያኒቷ እያንዳንዱን ዓመት ለአራቱ ወንጌላውያን በመስጠቷ ምእመኖቿና ካህኖቿ የተረኛውን ወንጌላዊ ስም በመጥራት መልካም ምኞታቸውን ይገላለጹበታል፡፡


እያንዳንዱ ዓመት ለአራት እያካፈሉ ቀሪው አንድ ከሆነ ዘመኑ የማቴዎስ፣ ሁለት የማርቆስ፣ ሦስት የሉቃስ፣ እኩል ከሆነ ዮሐንስ እያሉ ይጠሩታል፡፡ እየተገባደደ ያለውን የዘንድሮ ዓመት ዘመነ ዮሐንስ ሲሉት የሚመጣውን አዲሱን ዓመት ደግሞ ዘመነ ማቴዎስ ይሉታል፡፡

በአገር ውስጥና በዓለም ዙርያ በሚገኙ አጥቢያ ቤተ ክርስቲያናት በዕለተ ማክሰኞ መንፈሳዊ ሥነ ሥርዓት ያከናውናሉ፡፡ በየዓመቱ የሚውሉትን ተዘዋዋሪዎቹን አጽዋማትና በዓላት ሁዳዴንና ፋሲካን የመሳሰሉትን በዓዋጅ ይገልጻሉ፡፡ ዘንድሮ የካቲት 12 ቀን የተያዘው ሁዳዴና ሚያዝያ 7 ቀን የዋለው ፋሲካ፣ ለከርሞ ሁዳዴ መጋቢት 2 ቀን፣ ፋሲካ ሚያዝያ 27 ቀን 2005 .. እንደሚውል የባሕረ ሐሳብ ሊቁ ያውጃሉ፡፡

‹‹
ውስተ ርእሰ ዐውደ ዓመት ተጽሕፈ ተዝካርከ
ባርከኒ እንሣእ በረከትከ›› 

(
የስምህ መታሰቢያ በዓመቱ መጀመርያ ተጽፏል፤ በረከትህን አገኝ ዘንድ ባርከኝ መርቀኝ) እያሉም ያወድሳሉ፡፡ የዘንድሮው መጨረሻ የአንድ ዓመት ብቻ ሳይሆን ሦስተኛው ሚሌኒየም ከገባበት 2001 .. ዘመነ ማቴዎስ ተነሥቶ የተጀመረው የአራት ዓመት ዐውድ (Cycle) የሚፈጸምበት ነው፡፡ መጪው 2005 ደግሞ 1987 .. የተጀመረው 19 ዓመት ዐውድ የሚጠቃለልበት ዓመት ይሆናልና በልዩ ዓመትነቱ ይጠቀሳል፡፡

የክረምት የጨለማው ወራት ተፈጽሞ የበጋው፣ የመፀው (አበባ) የጥቢው ብርሃን የሚፈነጥቅባት መስከረም፣ ኢትዮጵያዊው እንደ ሃይማኖቱ ወደየቤተ አምልኮቱ እየሔደ ለዚህች ዕለት ላደረስከኝ አምላኬ ተመስገን፣ የከርሞ ሰው በለኝ፣ ተርፎ ለሚቀረው ዕድሜ አትንፈገኝ ብሎ ፈጣሪውን ይለምናል፡፡ የክብረት ሰው ይበለነ፡፡

መስከረም አንድ በልዩ ልዩ አቈጣጠር
ከነገ ወዲያ ማክሰኞ መባቻው የሆነው የኢትዮጵያ አዲስ ዓመት በልዩ ልዩ አቈጣጠሮች እንዲህ ይገለጻል፡፡

•   
መስከረም 1 ቀን 7505 ዓመተ ዓለም (ከአዳም ተነሥቶ የሚቈጥር)
•   
የጨረቃ መስከረም 24 ቀን 7734 ዓመት 9 ወር 22 ቀን
•   
መስከረም 1 ቀን 2005 ዓመተ ሥጋዌ (ከክርስቶስ ልደት ተነሥቶ በፀሐይ የሚቈጥር)
•   
መስከረም 1 ቀን 2013 ዓመተ ምሕረት (ከክርስቶስ ልደት ተነሥቶ በፀሐይና ጨረቃ ጥምር አቈጣጠር የሚቆጥር)
•   
የጨረቃ መስከረም 24 ቀን 2065 ዓመት 11 ወር 13 ቀን
•     
ሸዋል 24 ቀን 1433 ዓመተ ሒጅራ (ከነቢዩ መሐመድ ከመካ ወደ መዲና ስደት ተነሥቶ የሚቈጥር)
•   
ኢሉል 24 ቀን 5772 ዓመተ ፍጥረት (የአይሁድ ቤተ እሥራኤል አቈጣጠር)
•   
ኦገስት 29 ቀን 2012 (በዩሊየሳዊ አቈጣጠር)
•   
ሴፕቴምበር 11 ቀን 2012 (በጎርጎርዮሳዊ አቈጣጠር)

ከአዘጋጁ፡- ጸሐፊው ባሕረ ሐሳብ የሚባለው የኢትዮጵያ ዘመን አቈጣጠር ትምህርት ባለሙያ ነው፡፡ የጸሐፊው የኢሜይል አድራሻ ayamaru100@yahoo.com ነው፡፡

በሔኖክ ያሬድ(http://www.ethiopianreporter.com/ )

3 comments:

  1. adisu amet sint seat lay new yemigebaw? segno mata 12 seat yemilu alu, yih tikikil new?
    thanks,

    ReplyDelete
  2. http://ewenetaw.blogspot.de/
    Be Germany Yalew gemena sigalet yeh yemselale

    ReplyDelete
  3. http://ewenetaw.blogspot.de/
    Be Germany Yalew gemena sigalet yeh yemselale

    ReplyDelete