Tuesday, September 4, 2012

“የፈርዖን ልብም ደነደነ” ኦሪት ዘጸአት 7፤14



 (አንድ አድርገን ነሐሴ 29 2004 ዓ.ም)፡- እግዚአብሔርም ሙሴን ተናገረው፦ ወደ ፈርዖን ግባ እንዲህም በለው። እግዚአብሔር እንዲህ ይላል። ያገለግለኝ ዘንድ ሕዝቤን ልቀቅ። ለመልቀቅ እንቢ ብትል ግን እነሆ እኔ አገርህን ሁሉ በጓጕንቸሮች እመታለሁ ፤ ወንዙም ጓጕንቸሮችን ያፈላል፥ ወጥተውም ወደ ቤትህ፥ ወደ መኝታ ቤትህ፥ ወደ አልጋህም፥ ወደ ባሪያዎችህም ቤት፥ በሕዝብህም ላይ፥ ወደ ምድጆችህም፥ ወደ ቡሃቃዎችህም ይገባሉ ፤ ጓጕንቸሮችም በአንተ በሕዝብህም በባሪያዎችም ሁሉ ላይ ይወጣሉ። ኦሪት ዘጸአት 8  ፤ 1-4 አሁንም እግዚአብሔር እየተናገረ ይገኛል ፤ ከወራት በፊት በዋልድባ ላይ የተከሰተውን ነገር ሰምቶ ያላዘነ ሰው የለም ፤ በቦታው የሚገኙ መነኮሳትም ከአቅማቸው በላይ ሲሆን “ይግባኝ ለክርስቶስ” ብለው አሳልፈው ሰጥተዋል ፤ መንግስትና ቤተክህነቱ በአቋማቸው በመጽናታቸው እግዚአብሔር በሚናገርበት መንገድ ተናግሯል ፤ አሁንም  በተደረገው ነገር ከመማር ይልቅ እልህ የመጋባት ነገር እየተመለከትን እንገኛለን ፤ ይህ ለማንም አይጠቅምም፡፡

“ፈርዖንም ጸጥታ እንደሆነ ባየ ጊዜ ልቡን አደነደነ እግዚአብሔርም እንደተናገረ አልሰማቸውም። እግዚአብሔርም ሙሴን አለው፦ አሮንን፦ በትርህን ዘርጋ፥ በግብፅም አገር ሁሉ ቅማል እንዲሆን የምድሩን ትቢያ ምታ በለው። እንዲሁም አደረጉ አሮንም እጁን ዘረጋ፥ በበትሩም የምድሩን ትቢያ መታው፥ በሰውና በእንስሳም ላይ ቅማል ሆነ በግብፅ አገር ሁሉ የምድር ትቢያ ሁሉ ቅማል ሆነ። ጠንቋዮችም በአስማታቸው ያወጡ ዘንድ እንዲሁ አደረጉ፥ ነገር ግን አልቻሉም ቅማሉም በሰውና በእንስሳ ላይ ነበረ።ጠንቋዮችም ፈርዖንን፦ ይህስ የእግዚአብሔር ጣት ነው አሉት የፈርዖን ልብ ግን ጸና፥ እግዚአብሔርም እንደ ተናገረ አልሰማቸውም።  ኦሪት ዘጸአት 8  ፤ 15-19 ፈርዖን በእግዚአብሔር ላይ ልቡን አደነደነ ፤ እግዚአብሔር እንደተናገረም አልሰማቸውም ፤ እግዚአብሔር ይስተዋለሁ በፍጥረቱ ሁሉ ይናገራል ፤ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከመሞታቸው ከ4 ቀናት በፊት ግዙፍ የሆነ ዋርካ በቤተመንግስት ወድቋል ፤ ይህን ብዙ ሰው እንደፈለገው ትርጓሜ ሰጥቶታል ፤ ፈርኦር እግዚአብሔር ያደረገውን ነገር በመገዳደር ልቡን አደንድኗል ፤ የሆነውንም ነገር በስልጣኑ በመመከት ለመገዳደር ሞክሯል ፤  “የሠራዊት ጌታ የእግዚአብሔር” መጽሐፈ ነገሥት ካልዕ 19፤ 31 እንደተናገረም ማንም አላስተዋለም ፤ “እግዚአብሔርም ምድሩን በትቢያ መታው ፤ ጠንቋዮችም እጁን መቋቋም አልቻሉን እነርሱም ይህ የእግዚአብሔር እጅ ነው አሉት ፤ ፈርኦን ሊሰማ አልወደደም” ፤ አሁንም እየሆነ ያለው ነገር ይህ ነው ፤ ፈርኦን ከክርስቶስ ልደት በፊት የነበረ ገናና ንጉስ ነው ፤ ፈርኦን ወደፊት የሚነሱ አሁንም ያሉ የብዙ ነገስታት ምሳሌ ነው ፤ የእግዚአብሔርን ኃይል የሚፈታተኑ የብዙዎች ተምሳሌት ነው ፤ አሁንም በዋልድባ ገዳም የሚደረገውን የስኳር ልማት በመቃወም ብዙዎች መነኮሳት ተቃውሟቸውን በአደባባይ አሰምተዋል ፤ ፈርኦናውያን ግን በጉልበታቸው ተማምነው ሊሰሟቸው አልወደዱም ፤ ጉልበትም የእግዚአብሔር መሆኑን አላወቁም ፤ እነዚህ መነኮሳት ጉዳያቸውን ከቤተክህነት እስከ ቤተመንግስት በራፍ ይዘው መጡ ፤ አሁንም የሚሰማቸው ግን አልተገኝም ፤ ቤተመንግስቱ “እናንተ ደፋሮች” ብሎ ቀልባቸውን ነሳቸው ፤ ቤተክህነቱ በዝምታ አለፋቸው ፤ እነዚህ አባቶች በፍልሰታ አንባቸውን ወደ አምላክ አፈሰሱ ፤ “መልስ ካልሰጠህን ይህን ዳዊት እና ይህን መቋሚያ ተመልሰን አናነሳም” ብለው አምርረው ጥለው ወደ በዓታቸው አመሩ ፤ የንጹዓን  አባቶችን እንባ መሬት እንዳትወድቅ የማይፈቅድ አምላክ …..፣… ፤…..

ፈርኦናውያን ሁል ጊዜ በሰራዊቶቻቸው ብዛት ይተማመናሉ ፤ የእግዚአብሔርን እጅ ግን ከመጤፍ አይቆጥሩም ፤ “እግዚአብሔርም ሙሴን አለው፦ ወደ ፈርዖን ዘንድ ገብተህ ንገረው። የዕብራውያን አምላክ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ ያገለግሉኝ ዘንድ ሕዝቤን ልቀቅ። ልትለቅቃቸውም እንቢ ብትል ብትይዛቸውም፥ እነሆ የእግዚአብሔር እጅ በሜዳ ውስጥ ባሉት በከብቶችህ፥ በፈረሶችም በአህዮችም በግመሎችም በበሬዎችም በበጎችም ላይ ትሆናለች ብርቱ ቸነፈርም ይወርዳል። እግዚአብሔርም በእስራኤልና በግብፅ ከብቶች መካከል ይለያል ከእስራኤልም ልጆች ከብት አንዳች አይጠፋም። እግዚአብሔርም፦ ነገ እግዚአብሔር ይህን ነገር በምድር ላይ ያደርጋል ብሎ ጊዜን ወሰነ። እግዚአብሔርም ያንን ነገር በነጋው አደረገ፥ የግብፅም ከብት ሁሉ ሞተ ከእስራኤል ልጆች ከብት ግን አንድ ስንኳ አልሞተም። ፈርዖንም ላከ፥ እነሆም ከእስራኤል ልጆች ከብት አንድ ስንኳ አልሞተም። የፈርዖን ልብ ግን ደነደነ፥ ሕዝቡንም አልለቀቀም።” ኦሪት ዘጸአት 9 1፤7

የነገስታት ልብ ከእግዚአብሔር ጋር ከጥቁር ድንጋይ ይልቅ በርትቶ ይጠነክራል ፤ነዋይ ፤ ሀብትና ስልጣንም በስራቸው እንዳመጡት ተመልክተው ፈጣሪን ይዘነጋሉ ፤ አንዱም ግን ነፍሳቸውን ከተቆረጠላት ቀን ማሳለፍ አይቻላቸውም ፤ ራሳቸውን ከሰው በላይ የማይሞቱ ፍጡራን አድርገው ያስቀምጣሉ ፤ ፈርኦን የሆነውን የተደረገውን ነገር እያየ ህዝቡን መልቀቅ ግን አልፈለገም ፤ አሁንም ይህ መንግስት በሳምንት የሆነውን እያየ ዋልድባ ላይ ስኳር ልማቱን ማቋረጥ  አልፈለገም ፤ ይባስ ብሎ አባቶቻችንን “እናንተ መተተኞች” እስከ ማለት ደርሷል ፤ ሰብአዊ መብታቸውን ነጥቆ ያለጥፋታቸው የማሰር የማንገላታትና ፤ ከገዳሙ በረው እንዲጠፉ የማድረግ ስራ እየሰራ ይገኛል ፤ እስከ አሁንም በመጀመሪያ 6 አባቶች ከገዳሙ ሲሰደዱ ተጨማሪ 7 አባቶች ከቀናት በኋላ መሰደዳቸው ታውቋል ፤ “የደበቃችኋውን አባት አውጡ” በማለት እያስጨነቃቸው ይገኛል ፤ በአሁኑም ሰዓት በገዳሙ የቀሩት አባቶች ላይ ይህ ነው የማይባል እንግልት እየፈጸመ ይገኛል ፤ እግዚአብሔር በአንድም በሌላም መንገድ ሰው እንዲማር እንዲመለስ ምልክት ይሰጣል ፤ ነገር ግን አልመለስ ያለውን ይቀጣል ፤ እግዚአብሔር የፈርኦናውያንን ከብቶች ከእስራኤላውያን ለይቶ መግደል ይችላል ፤ ይህንም የተመለከቱ ፈርኦናውያን የሆነውና የተደረገውን ነገር እየተመለከቱ እግዚአብሔር ባደረጋቸው ተዓምራት ማመን አይፈልጉም ፤ እንዲህ አይነት ተዓምር በተመለከቱ ጊዜ ልባቸውን ከበፊቱ እጅጉን ያደነድናሉ፡፡ እግዚአብሔር ግን ህዝቡን የሚጠብቅበት መንገድ አለው፡፡

እግዚአብሔርም ሙሴን አለው፦ ማልደህ ተነሣ፥ በፈርኦንም ፊት ቆመህ በለው። የዕብራውያን አምላክ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ እንዲያገለግሉኝ ሕዝቤን ልቀቅ። በምድር ሁሉ እንደ እኔ ያለ እንደሌለ ታውቅ ዘንድ በሰውነትህ በባሪያዎችህም በሕዝብህም ላይ መቅሠፍቴን ሁሉ አሁን እልካለሁ። አሁን እጄን ዘርግቼ አንተን ሕዝብህንም በቸነፈር በመታሁህ ነበር፥ አንተም ከምድር በጠፋህ ነበር ፤ ነገር ግን ኃይሌን እገልጥብህ ዘንድ ስሜም በምድር ሁሉ ላይ ይነገር ዘንድ ስለዚህ አስነሥቼሃለሁ። እንዳትለቅቃቸው ገና በሕዝቤ ላይ ትታበያለህን? እነሆ ነገ በዚህ ጊዜ፥ ከተመሰረተች ጀምሮ እስከ ዛሬ ድረስ እንደ እርሱ ያለ በግብፅ ሆኖ የማያውቅ፥ እጅግ ታላቅ በረዶ አዘንብብሃለሁ።” ኦሪት ዘጸአት 9 13-18 ይህ የሆነው ከዘመናት በፊት ነው ፤ አሁንም ይህ  እንዳይሆን የሚይዘው ነገር የለም ፤ በዘመናችን አይተነው የማናውቀውን ነገር እርሱ በዘመናችን ማከናወን ይችላል ፤ በዘመናችን አንድ ፓትርያርክና አንድ ጠቅላይ ሚኒስትር በአንድ ሳምንት ውስጥ ቀብረን አናውቅም እርሱ ካለ ግን በአንድም ቀንም ይሆናል ፤ የሚያስተውል ካለ መልካም ነው ፤ የአንዳቸውን ሀዘን በአግባቡ ሳንጨርስ ሌላውን የደገመበት ምክንያት ምንድነው ? ብለን መጠየቅ መቻል አለብን ፤  አሁንም መንግስት እጁን ከስኳር ልማቱ ላይ ካላነሳ እግዚአብሔርን ከዚህም በላይ እንዳያደርግ የሚከለክለው ማነው ?

አሁንም በዋልድባ ገዳም ላይ የሚደረግን የመነኮሳት አባቶችን ማንገላታት ከዚህ በላይ ጉዳት እንደማያመጣ እርግጠኞች ሆነን መናገር አንችልም ፤ የላመ እና የጣመን በመተው እርሱን ብለው እድሜ ዘመናቸውን በዱር በገደል ያሳለፉ አባቶቻችንን አምላክ ጸሎታቸውን ዝም አይላቸውም ፤ ጤዛ ልሰው ድንጋይ ተንተርሰው ያሉትን አባቶች እንዳሉ እንወቅ ፤ ላስተዋለ የሆነው እና የተደረገው ነገር በቂ ነው ፤ ላላስተዋለ ግን የዚህን አስር እጥፍ ቢደረግ ያው ነው ፤ 21 ዓመታት በስልጣን ሳላችሁ ከዚህ የከፋ ጊዜ አይታችኋል ብለን አናስብም ፤ እጃችሁን ከገዳማትና ከአብያተክርስትያናት ላይ ካላነሳችሁ ግን ከዚህ የባሰ ነገር ሊመጣ ይችላል ፤ እርሱ ሁሉን ማድረግ ሁሉን ማከናወን ይችላል ፤ እንባችሁ ጎርፍ ከመሆኑ በፊት የቆማችሁበትን ቦታ አስተውሉ “ማንም የቆመ ቢመስው እንዳይወድቅ ይጠንቀቅ” 1ኛ ወደ ቆሮንቶስ ሰዎች 10፤12 ቃሉ እንዲህ ይላል ፤ የአባቱ የዳዊትን እና የልጁን የሰለሞንን ስርወ መንግስትን የመሰረተው ጊዜው ሲደርስም ያሳለፈ እርሱ እግዚአብሔር ነው ፤ አሁንም እናንተን እዚህ ወንበር ላይ ያስቀመጣችሁ የሚያወርዳችሁም እርሱ ነው ፤ ዘመናችሁ እንዲረዝም የምትፈልጉ ከሆነ እጃችሁን ከገዳማትና ከአብያተ-ክርስትያናት ላይ አንሱ ፤ እርሱን ታግሎ ያሸነፈ በዘመናችን የለም ፤ ወደፊትም አይኖርም ፡፡

የዋልድባ ገዳም አባቶችን በገዳማቸውና በበዓታቸው ሱባኤ እንዳይዙ ብታደርጓቸው እንኳን እርሱ እነርሱን ለመስማት ቦታ እንደማይገድበው እወቁ ፤ ከዚህ ተግባራችሁ ካልተገደባችሁ ይባስ እንዳያመጣባችሁ ስጋት አለን ፤ ቆም ብላችሁ አስቡ ፤ አስተውሉ ፤ የሆነውን እና የተደረገውን ነገር ተመልከቱ ፤ ከመንገዳችሁም ተመለሱ፡፡ ያለበለዚህ እናንተ ሟቾች እኛ አልቅሶ ቀባሪዎች እንዳንሆን ስጋት አለን ፤ እኛ ቆጣሪዎች እናንተ ተቆጣሪዎችም አንዳትሆኑ እንሰጋለን ፤ የቆምንበትንና ያለንበትን ዘመን እንድናስተውል አምላክ ይርዳን፡፡

ለቤተክርስቲያናችን መልካም ፓትርያርክ ለሀገራችን ጥሩ መሪ እግዚአብሔር ይስጠን……. አሜን

ቸር ሰንብቱ

7 comments:

  1. Amen kale hiwot yasemalen!
    tebarku

    ReplyDelete
  2. Amen Amen Amen Amen!!! Well Stated! Rightfully Stated and truthfully based on the very essence of the holy bible teachings! I really hope the authoritarians will listen to God's message and escape the rage that's forthcoming - lest it is inconceivable anything less would happen if they choose not to listen. I am looking forward to the retreat (Subae) orders given by our holy synod. The only solution is to offer our supplications to God in great depths and emotions. God is STILL a merciful God.

    ReplyDelete
  3. Amen leb yestachew egzabher eko eytenagere new gen yemsema tefa ahunm ebackachehu semu yewaldeba sequar project terf yelwem leb yestachu amen

    ReplyDelete
  4. TIKIKIL !
    ዘመናችሁ እንዲረዝም የምትፈልጉ ከሆነ እጃችሁን ከገዳማትና ከአብያተ-ክርስትያናት ላይ አንሱ ፤ እርሱን ታግሎ ያሸነፈ በዘመናችን የለም ፤ ወደፊትም አይኖርም፡፡
    KALE HIWOTIN YASEMALIGN!

    ReplyDelete
  5. “የፈርዖን ልብም ደነደነ” ኦሪት ዘጸአት 7፤14

    ReplyDelete
  6. wow well said

    May GOD bless u all Andadrgen

    የዋልድባ ገዳም አባቶችን በገዳማቸውና በበዓታቸው ሱባኤ እንዳይዙ ብታደርጓቸው እንኳን እርሱ እነርሱን ለመስማት ቦታ እንደማይገድበው እወቁ ፤ ከዚህ ተግባራችሁ ካልተገደባችሁ ይባስ እንዳያመጣባችሁ ስጋት አለን ፤ ቆም ብላችሁ አስቡ ፤ አስተውሉ ፤ የሆነውን እና የተደረገውን ነገር ተመልከቱ ፤ ከመንገዳችሁም ተመለሱ፡፡ ያለበለዚህ እናንተ ሟቾች እኛ አልቅሶ ቀባሪዎች እንዳንሆን ስጋት አለን ፤ እኛ ቆጣሪዎች እናንተ ተቆጣሪዎችም አንዳትሆኑ እንሰጋለን ፤ የቆምንበትንና ያለንበትን ዘመን እንድናስተውል አምላክ
    ይርዳን፡፡

    Amen Amen Amen Amen!!! Well Stated! Rightfully Stated and truthfully based on the very essence of the holy bible teachings! I really hope the authoritarians will listen to God's message and escape the rage that's forthcoming - lest it is inconceivable anything less would happen if they choose not to listen. I am looking forward to the retreat (Subae) orders given by our holy synod. The only solution is to offer our supplications to God in great depths and emotions. God is STILL a merciful God.

    ReplyDelete
  7. AMEN AMENNNNNNNNN Ye sefra ye tekeds nwna chamhne ke egerh lay awleke

    ReplyDelete