Tuesday, March 13, 2012

በሰፈሩት ቁና

(አን አድገን መጋቢት 4 2004.)-የቦረና ጉጂና ሊበን ዞኖች ሃገረ ስብከት በፖሊስ ተደብድበው ላለፉት 13 ቀናት እስር ላይ የነበሩት ክርስቲያኖች ጥቂቱ በነጻ የተቀሩትም በዋስትና መለቀቃቸውን መዘገባችን ይታወቃል፡፡ ታዲያ አነዚህ ክርስቲያኖች ከእስር እንደተለቀቁ ወደ ቤት የሄደ አንድም ሰው አልነበረም፡፡ ሁሉም በመኪና ተሳፍረው በጋራ እየዘመሩ ወደ ስላሴ ቤተክርስቲያን (ታፍሰው የተወሰዱበት ) ነበር ያመሩት ፤ እግዚአብሔርን የምናመሰግነው ሲመቸን ብቻ መሆን የለበትም ፤ በፈተና ውስጥም ብንሆን አምላካችንን ማመስገን ይገባናል ፤ ‹‹ነገሩ ሁሉ ለበጎ ነው›› በማለት ለአምላካችው የምስጋና ጸሎት አድርሰው ስለ ቀጣይ እርምጃዎችና የወደፊት አቅጣጫዎች ውይይት አድርገዋል፡፡ እነዚሁ ታሳሪዎች በእስር በመቆየታቸውየአባቶቻችን በረከት ደርሶናልና እግዚአብሄር ምስጋና ይገባዋልማለታቸውን ከቦታው ከደረሰን መረጃ ለማወቅ ተችሏል ክርስትያን እንደ ሚስማር ሲመቱት ይጠብቃል፤ እውነት ያለው እኛ ጋር ነው በደሙ የዋጃትን ቤተክርስትያንን እንጠብቃለንም ብለዋል ፡፡




በተያያዘ ዜና በህገወጥ መንገድ የተጻፈላቸውን ደብዳቤ በመያዝ የሃገረ ስብከቱ ስራ አስኪያጅ ነኝ በማለት በፈጠሩት ውዝግብ ከነጌሌ ቦረና ከተማ ተባርረው ክብረመንግስት ላይ ህገወጥ ሌላ  የሃገረ ሰብከት ጽ/ቤት ከፍተው በህገወጥ መንገድ ባሳተሙት ማህተም ክርስቲያኖቹን በወህኒ ያሳጎሩት ተሾመ ሃይለማርያም በወንጀል ተከስሰው ከነጌሌ ቦረና ፍርድ ቤት በወጣባቸው የመያዣ ትእዛዝ መሰረት ከነጌሌ ቦረና በተላኩ ሁለት ፖሊሶች ተይዘው  በክብረመንግስት ከተማ ፖሊስ ጣቢያ እንዲያድሩ የተደረገ ሲሆን ፤ በወንጀል ወደሚፈለጉበት ነጌሌ ቦረና ከተማ እንደሚወሰዱ ታማኝ ምንጮች ከቦታው የላኩልን መረጃ ያሳየል፡፡

በእሳቸው ቀድሞ የተጠነሰሰ ሴራ 40 ክርስትያኖችን ወህኒ ያሳጎሩት እኝህ ሰው በስተመጨረሻ የሰሩት ስራ ገሀድ በመውጣቱ በሰፈሩት ቁና ሊሰፈሩ ችለዋል፡፡ እስር ቤት ፈርተን ቤተክርስትያንን ለቀን ጅቦች አሳልፈን አንሰጥም ፤ የመጣውን ሁሉ በእርሱ ለመቻል ራሳችንን በእምነት አጠንክረን ቤተክርስትያን እንጠብቃለን ፤ 1ኛ የጴጥሮስ መልእክት 314 ላይ እንዲህ ይላል ‹‹ነገር ግን ስለ ጽድቅ እንኳ መከራን ብትቀበሉ ብፁዓን ናችሁ። ማስፈራራታቸውንም አትፍሩ አትናወጡም፥›› ፤ 1ኛ የጴጥሮስ መልእክት 3፥16 ላይ ደግሞ ‹‹ክርስቲያን እንደሚሆን ግን መከራን ቢቀበል ስለዚህ ስም እግዚአብሔርን ያመስግን እንጂ አይፈር።›› ይላል ፤ እኛም መሪያችን የእግዚአብሔር ቃል መሆን መቻል አለበት ፤ ከስርአተ ቤተክርስትያን ውጪ የሚደረግን ማንኛውንም እንቅስቃሴ አጥብቀን እንቃወማለን ፤ የቅዱስ ሲኖዶስ መመሪያ ተግባራዊ እንዲሆን ሁላችንም የበኩላችንን ሃላፊነት መወጣት መቻል አለብን ፤ ትላንት በሀሰተኛ ደብዳቤ ህጋዊ የመሰሉት ሰዎች ዛሬ እስር ቤት ይገኛሉ ፤ ትላንት በሀሰት የታሰሩ ክርስትያኖች እውነት ስላላቸው ቀኑ ሲደርስ ነፃ ናችሁ ተብለዋል፡፡

ማንም ይሁን ማን በመታሰሩና በመቸገሩ የምንደሰት ባይሆንም ‹‹የግፍ ጉድጓድ አትቆፍር ብትቆፍርም አታርቀው ..ቀድሞ የሚገባበት አይታወቅምና›› የሚለውን የሃገራችንን ምክር ማስታወሱ ሳይጠቅም አይቀርም፡፡ ትናንት ወገኖቻቸውን አሳፍሰው ባሳደሩበት እስር ቤት ዛሬ ደግሞ እሳቸው ቀምሰዉታል፡፡ በሰፈሩበት ቁና...እንዲሉ ፤ የጉዳዩን መጨረሻ ተከታትለን እናሳውቃችኋለን፡፡ እግዚአብሔር ለቤተክርስቲያናችን ሰላሙን ያድልልን፡፡ ለቤተክርስቲያናችን “መሪዎችም” እግዚአብሔር መልካም ልቡና ይስጥልን፡፡



አቡነ ጎርቶርዮስ ካልዕ በሕይወት በነበሩበት እንዲህ ብለው ነበር
ቤተክርስቲያን ስለ ሁሉ ሰላም ስለፀለየች ክፉዎች በእርሷ ላይ ተነሳሱባት ክብሯን ሲገፉባት አጥሯን ሲወዘውዙባት ክዳኗን ሲያነሱባት ክርስቶስ ይናገር ዘንድ እሷ ዝም ማለቷን ቢያዩ ይበልጥ ተበረታቱባት ስለክርስቶስ ሁሉን በማክበሯ ክፉ መሪ ደግ መሪ ሳትል መልካም ሰው ክፉ ሰው ሳትል ስለሁሉ በመፀለየዋ ስለሁሉ ምህረትን በማድረጓ ክፉወች ይቅር ባይነቷን ትእግስቷን መጠቀሚያ አደረጉት ሁሉ ተነሳሱባት የወላድ መካን እንደሆነች ጥቃቷን የሚመክትላት ልጅ እንደሌላት ሁሉ በሷ ላይ ተነሱ ልጆቿ ሁሉ አድር ባዮች መሰሉ ለሆዳቸው የሚጋደሉ ለስጋቸው የሚጨነቁ የመንፈስ ባይተዋሮች መሰሉ ስለዚህም ፉወች የምድር ፈራጆች ጠላቶች የድፍረት እጃቸውን አነሱባት ይበልጥም በገዳም ያሉ አባቶቻችን ረሃብ ጥሙን ቻሉ የስጋ ስሜትን ቻሉ የአራዊትን ክፋት ቻሉ ሙቀት ቁሩን ቻሉ የሰይጣንን ተንኮል ቻሉ ሁሉን ቻሉ ሁሉን ስለክርስቶስ በክርስቶስ ቻሉ የቤተክርስቲያንን ነገር ግን እንደምን ይችላሉ? ስለክርስቶስ ሲሉ በዱር በገደል አለም እንዳልተገባቸው ተቅበዘበዙ አብዝቶ ስለመፆም ሳያቁርጡ ስለመፀለይ ለምስጋና ስለመቆም ደክመው ከስተው ባዩአቸው ጊዜ ገፍተው ይጥሏቸው ዘንድ ተነሳሱ መንፈሳውያን ናቸውና ጋሻና ጦር ወጥመድና ቀስት እንደሌላቸው ባዩ ጊዜ ክብራቸውን ያሳጧቸው ዘንድ ተበረታቱባቸው፡፡ ገዳማውያን አባቶቻችን ግን ምን አድረጉ ዘወትር ስለኢትዮጵያ ስለፀለዩ? ስለ ሐገር መሪው ስለ ወታደሩ ስለ ሁሉ ቀን ሳያስታጉሉ በባዶ ሆዳቸው ስለለመኑ? ደመወዝ ክፈሉን አላሉ ግለጡን ስበኩን አስተዋውቁን አላሉ ቤታችሁ ወስዳችሁ መግቡን አላሉ ምን አደረጉና ይናቁ? ምን አደረጉና ከቤታቸው ይባረሩ? ምን አደረጉና ትምክህታቸው ትፍረስ? ምን አድረጉና የአባቶቻቸው ክብር ይነካ? ጌታችን መድሃኒታችን አምላካችን ኢየሱስ ክርስቶስ ሆይ በሁሉ መገፋታችንን አስብ፡፡ ክርስቶስ ሆይ አባቶቻችን እንዳስተማሩን አንተ ትናገር ዘንድ እኛ ዝም ብለናልና ትእግስታችንን አፅናልን የቤተክርስቲያንንም ለቅሶ ሰምተህ ቸል አትበል፡፡ አሜን፡፡




3 comments:

  1. Thanks to God for releasing those innocent chrisitians. What a wonderful messaage from His Grace Abune Gorigoreos!!! It is a timely message.

    Nabute

    ReplyDelete
  2. "ክርስቶስ ሆይ አባቶቻችን እንዳስተማሩን አንተ ትናገር ዘንድ እኛ ዝም ብለናልና ትእግስታችንን አፅናልን ፡ የቤተክርስቲያንንም ለቅሶ ሰምተህ ቸል አትበል፡፡ አሜን፡፡" The words from our Father is coming from the one whose soul is ready to be sacrifice for true religion and true church. Let it be heard by our God these days too.
    Thanks to the Almighty God since our brothers and sisters are free and the truth is on the way to be revealed by God.

    ReplyDelete
  3. Amlake Kidusan Wagachihun yikfelachihu ayzoachihu selfu ye EGZIABHER new. Atsirare betechristianin yastagsilin.


    Ye Enatachin miljana bereket ayileyachihu.

    ReplyDelete