Friday, October 21, 2022

ከቅዱስ ሲኖዶስ ጽሕፈት ቤት የተሰጠ መግለጫ

 ጥቅምት ፲፩ ቀን ፳፻ ፲ወ፭ . አዲስአበባ -ኢትዮጵያ

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ቅዱስ ሲኖዶስ ምልዓተ ጉባኤ በዓመት ሁለት ጊዜ እንደሚያካሂድ ይታወሳል፡፡ይኸውም በወርኃ ጥቅምትና ግንቦት ነው፡፡ በእነዚህ ወራት በመንፈስ ቅዱስ መሪነት ምልዓተ ጉባኤውን በማካሔድ በቅድስት ቤተ ክርስቲያን ሁለንታዊ ጉዳዩች ወይም መንፈሳዊ፣ ማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ አገልግሎቶች ላይ በመምከር ልዩ ልዩ ውሳኔዎችን እንደሚያስተላልፍ ይታወቃል።

ቅዱስ ሲኖዶስ የሚያካሒዳቸው እነዚህ ጉባኤያት በተረጋጋ፣ በሰከነና በተሳካ መልኩ መካሔድ ይችላሉ ዘንድ የሚመለከታቸው አካላት ሁሉ አስፈላጊውን ትብብርና ድጋፍ ማድረግ ይኖርባቸዋል። በተለይም በተለምዶ ጉባኤው በሚካሔድበት ወቅት ልዩ ልዩ አቤቱታዎችን ሕጋዊውን አሠራር ባልጠበቀ መልኩ በግልና በቡድን በመሆን በቅዱስ ሲኖዶስ ጽሕፈት ቤት፣ በመንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ጽሕፈት ቤትና በብፁዓን አባቶች ማረፊያ ቤት በመገኘት ማቅረብ ሕጋዊነት የሌለው ተግባር ከመሆኑም በላይ የቅዱስ ሲኖዶስን ጉባኤን የሚያውክ ነው፡፡ በዚህም የተነሣ ፍጹም ተቀባይነትን የሌለው ተግባር መሆኑን ሁሉም ሊያውቀው ይገባል፡፡

አቤቱታና ጥያቄዎች ካሉም በሕጋዊው የቤተ ክርስቲያናችን አሠራር መሠረት መዋቅራዊ አሠራርን በጠበቀ መልኩ ማቅረብ ተቀባይነት ያለውና ሕጋዊ አሠራር ነው፡፡ በመሆኑም ማንኛውም ሕጋዊ አቤቱታና ጥያቄ ያለው ግለስብም ይሁን ተቋም ይህንን አሠራር መሠረት በማድረግ ጥያቄና አቤቱታውን ማቅረብ ይችላል። ይህም የሚሆነው ግን የቅዱስ ሲኖዶስ ጉባኤ የሚካሔድበትን ወቅት ጠብቆ መሆን የለበትም።

Tuesday, October 18, 2022

"ተናበን እንዳንሰራ እንቅፋት የሆነብን ምንድን ነው?" ሲሉ ብፁዕ አቡነ አብርሃም የጠቅላይ ቤተ ክህነት ዋና ስራ አስኪያጅ ጠየቁ ።

 

ጥቅምት 7 ቀን 2015 . (አዲስ አበባ) :- የጠቅላይ ቤተ ክህነት ዋና ሥራ አስኪያጅ እና የባሕር ዳር ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ አቡነ አብርሃም በባለፈው በጀት ዓመት የተሰሩ በርካታ ክንዋኔዎችን ዛሬ ጥቅምት 7 ቀን 2015 . 41ኛው የሰበካ መንፈሳዊ ጉባኤ በጠቅላይ ቤተ ክህነት በጽርሐ ተዋሕዶ አዳራሽ በተካሄደበት ላይ በሪፖርት አቅርበዋል ። ብፁዕነታቸው በሪፖርቱ የሀገር ውስጥ እና የውጭ ሀገር ሐዋርያዊ ክንውን ሐዋርያዊ ተልዕኮና መንፈሳዊ አገልግሎትን በተመለከተ የተሰሩ ሥራዎችን ፣በአስተዳደርና ፋይናንስ ዘርፍ የተሰሩ ስራዎችን ፣የምግባረ ሠናይ ዘርፍን በተመለከተ የልማት ድርጅቶችን እነዚህንና ሌሎችም መሰል ተግባራትን በተመለከተ በንባብ አሰምተዋል

ብፁዕነታቸው በመጨረሻም መሠረታዊ የመወያያ አጀንዳዎች የሚሆኑ መነሻ ሐሳቦችን አቅርበዋል። ብፁዕነታቸው ካቀረቧቸው መነሻ ሀሳቦች መካከልም


Ø  ስለ ሀገራችን ሰላም የቤተ ክርስቲያን አስተዋጽኦ ምን ይሁን ?

Ø  በቤተክርስቲያን እና በምእመናን የሚደርሰውን ግፍ በምን መልኩ ማስቆም ይቻላል ?

Ø  የቤተ ክርስቲያን ሕልውና ለማረጋገጥ (አብነት ትምህርት ቤት ለማስቀጥል፤ ሰንበት ትምህርትን ከማጠናከር አንጻር፤ ስብከተ ወንጌል ከማስፋፋት አንጻር ?)

Ø  በጀት አጠቃቀም ላይ ያለውን ችግር እንዴት እንፍታው?

Ø  የቤተ ክርስቲያንን ምጣኔ ሀብት እንዴት እንጠብቀው?

Ø  ከመንበረ ፖትርያርክ እስከ አጥቢያ ድረስ ተናበን እንዳንሰራ እንቅፋት የሆነብን ምንድን ነው ?ተናቦስ ለመሥራት ምን እናድርግ ?

Ø  የቤተ ክርስቲያንን ክብር እንዴት ጠብቀን እናስጠብቅ ?

Ø  ቤተ ክርስቲያናችን ለተጎዱት ከመድረስ ይልቅ ጉዳት ደረሰብኝ ባይ ሆናለች ስለዚህ ከዚህ ለመላቀቅ መፍትሄው ምንድን ነው ?

Ø  ሙስናን እንዴት አድርገን ከቤተ ክርስቲያን እናላቀው? የሚሉ መሰል ጥያቄዎች ከብፁዕ ጠቅላይ ሥራ አስኪያጁ ሪፓርት ቀጥሎ ለተሰብሳቢዎቹ የተሰጠ ሲሆን ከቀትር በኋላ ውይይት ይድረግባቸዋል ተብሎ ይጠበቃል፡፡