ጻድቃን ፤ ሰማዕታት

ሰኔ 26 
በዚህች ቀን ታላቁ መስፍን ፤ ካህን ፤ ነቢይ የሆነው የነዌ ልጅ ኢያሱ አረፈ፡፡ ሙሴ ከሞተ በኃላ እስራኤላውያንን መርቶ ምድረ ርስት ያወረሰ በገባኦን ምድር በኤሎን ቆላ ፀሐይን ያቆመ የዮርዳኖስን ባህር ከፍሎ ያሻገረ ፤ የአህዛብንም ነገስታት ድል የመታ ታላቅ ነቢይ ነው፡፡ አባ ሕርያቆስ እመቤታችንን የኢያሱ የምስክር ሐውልት ይላታል ኢያ 24 26 ይህች የኢያ ሐውልት እስራኤላውያን እግዚያብሔርን እንዳይክዱ ትዕዛዛቱን እንዳይተላለፉ ከህዝቡ ጋር ተማምሎ ከቤተመቅደሱ አጠገብ ከአድባር ዛፍ በታች ያቆማት ህያው ምስክር ናት፤ ሐውልቷ ፍጹም የማትንቀሳቀስ እንደሆነች ሁሉ እመቤታችንም በድንግልናዋ በንህጽናዋ ጥርጥር የሌለባት ፍጹም የጸናች ናትና፡፡ ይህ ነቢይ ለእግዚያብሔር ታዛዥ ሆኖ ህዝቡንም በመልካም መርቶ በፍቅር አስተዳድሮ 110 ዓመቱ በበጎ እርጅና በመልካም ሽምግልና ሰኔ 26 በዛሬዋ ቀን አንቀላፋ በተራራማውም አገር በገዓስ ተራራ ባለችው በርስቱ ዳርቻ ቀበሩት። ኢያ 24 29 በረከቱ ይደርብን፡፡

ሰኔ 25

(በውብሸት ተክሌ፡-  )አንድ አምላክ በሆኑ በአብ በወልድ በመንፈስ ቅዱስ ስም ሰኔ 25 በዚህች ቀን ከሰባ ሁለቱ አርድዕት አንዱ የሆነው የእመቤታችን ጠባቂ የነበረው የጸራቢው የዮሴፍ ልጅ ሐዋርያው ይሁዳ በሰማዕትነት አረፈ፡፡ ይህ ሐዋርያ በብዙ አገራት ተዘዋውሮ ወንጌለ መንግስተ ሰማያትን ሰበከ፤ ብዙ አህዛብንም ወደ ቀናችው ሓይማኖት መለሰ፤ ህሙማንን ፈወሰ አጋንንትንም አወጣ በመጨረሻም ሐራፒ ወደሚባል አገር ገብቶ ክርስቶስ ወረደ ተወለደ ሞተ ተሰቀለ ተነሳ አረገ ዳግም ለፍርድ ይመጣል፤ መንግስተ ሰማያት ቀርባለችና ንስኃ ግቡ ብሎ ሲሰብክ አገረ ገዢው ይዞ ጽኑ ስቃይን አሰቃየው ችንካር ያለው ጫማ አድርጎ አስሮጠው ሰቅሎ በፍላጻ ነደፈው ቅድስት ነፍሱንም ሰጠ፡፡ ይህ ሐዋርያ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የይሁዳ መልዕክት የሚለውን የጻፈልን ሐዋርያ ነው፡፡ ለእግዚያብሔር ምስጋና ይሁን እኛንም ከሐዋርያው በረከት ያሳትፈን፡፡


አባ ሙሴ ጸሊም
(by Wubishet Tekle …  ) ሰኔ 24 በዚህች ቀን ኢትዮጵያዊው ጻድቅ አባ ሙሴ ጸሊም አረፈ፡፡ አስቀድሞ ሽፍታ፣ ወንበዴ፣ ዘማዊ ፣ጣኦት አምላኪ ነበር፤ በኃላ እንደ አብርሃም አምላኬ ማን ነው? ብሎ ተመራመረ፤ ወደ አስቄጥስ ገዳም ብትሄድ አምላክህ ማን እንደሆነ ይነግሩሃል የሚል ራዕይ አየ፣ ተመለከተ፤ ተነስቶም ሄደ አባ ኤስድሮስን አገኛቸው፤አጽናንተው አረጋግተው ወደ አባ መቃርስ ወሰዱት አባ መቃርስም ንስሃውን ተቀብለው ቀኖና ሰጡት ኋላም አመነኮሱት የሽፍቶች አለቃ የነበረው የመነኮሳት አለቃ እስከመሆን ደረሰ፤ ሰይፉን ወርውሮ ከፍቅር ጋር ተወዳጀ፤ሌሊት እየተነሳ ለሁሉም መነኮሳት ውኃ ይቀዳላቸው ነበር፤ ለሁሉም ይታዘዛቸው ነበር ትንሹም ትልቁም ሙሴ ይህን አድርግሊኝ ይሉታል አርሱም ሁሉንም እሺ ይላል፤ ራሱን ዝቅ አደረገ ትሁትም ሆነ፤ በጸሎቱ ዝናብ ያዘንም ነበር፤ እድሜው መጨረሻ አካባቢ ቡራኬ ሊቀበል ከመነኮሳት ጋር ሆኖ ወደ አባ መቃርስ ሄደ አርሳቸውም ልጆቼ ከእናንተ መካከል በሰማእትነት የሚሞት አለ ብለው ትንቢት ተናገሩ ሙሴ ጸሊምም አባቴ ሰው እኔ ነኝ ሰይፍ የሚያነሱ በሰይፍ ይጠፋሉ የሚል ቃል አለ ይህን ጊዜ በጉጉት ስጠባበቀው ነበር አላቸው፤ እንደተባለውም የበርበር ሰዎች ገዳሙን ሊያጠፉ መጡ መነኮሳቱ ሲሸሹ ሙሴ እዚያው ቀረ ሌሎች ሰባት መነኮሳት ከአባታችን ጋር እንሞታለን ብለው አብረውት ሆኑ የበርበር ሰዎች ደረሱ ሁሉንም በሰይፍ ገደሏቸው፤ ይህም ሰኔ 24 ቀን ነው፤ የአባታችን የሙሴ ጸሊም ስጋው በገዳመ አስቄጥስ በክብር ይገኛል፤ ግብጻውን ቤተ ክርስቲያን ሰርተውለት ታቦት ቀርጸውለት በየዓመቱ በድምቀት ያከብሩታል ገድሉን ጽፈውለታል ፊልምም ሰርተውለታል ይህን ፊልም የኛ ሰዎች ግሩም አድርገው ወደ አማርኛ መልሰውታል፤ የዛሬዋን ቀን ስለ ተክለ ሃይማኖት ብቻ ብለን አንመጽውት ስለ አባ ሙሴ ጸሊምም እያልን ይሁን እንጂ፤ አምላከ ተከልዬ ጠብቀኝ ስንል አምላከ ሙሴ ጸሊም አትርሳኝ ማለትንም አንርሳ የዚህ ድንቅ አባት ታሪክ የማይረሳ ነውና፡፡

 ሙሴ ጸሊም ማለት ጥቁሩ ሙሴ ማለት ነው፤ መልኩ ጥቁር ስለሆነ ነው ጥቁሩ ሙሴ ተብሎ የተጠራው፤ በነገራችን ላይ ከዕለታት በአንዱ ቀን በዚሁ በጥቁረቱ የተነሳ አባቶች አንድ ፈተና አቅርበውለት ነበር፣ አባ ኤስድሮስ ይጠሩትና ሙሴ ዛሬ ቀድሰክ ታቆርባለህ ይሉታል እርሱም እሺ አባቴ ብሎ ይወጣል በዚህን ጊዜ አባ እስድሮስ ካህናቶችን ይጠሩና ዛሬ ሙሴ ቅዳሴ ሊቀድስ ወደ መቅደስ ሲገባ ሰድባችሁ አባሩት ብለው ትዕዛዝ ይሰጣሉ እንደተባለው ሙሴ ሊቀድስ ልብሰ ተክህኖ ለብሶ ወደ መቅደስ ሊገባ ሲል አንተ ጥቁር ብለክ ብለክ ከኛ ጋር መቀደስ አማረክ ወግድ ከዚህ ብለው ያባርሩታል እርሱም ምንም ሳይናገር አንገቱን አቀርቅሮ ትክክል ናቸው ያለ ቦታክ ለምን ገባክ እያለ እራሱን እየወቀሰ ተመለሰ የሚገርመው ቂም ሳይዝባቸው በነጋታው ውኃ ሊቀዳላቸው ሄደ ይህን የተመለከቱ አባ እስድሮስ ጠርተው ሙሴ ያቀረብንልክን ፈተና አልፈካል እግዚአብሔር ካንተ ጋር ይሁን ብለው መርቀውታል። መጽሐፈ መነኮሳት 2ኛው ከአባ ሙሴ ጸሊም ከጻድቁ ተክልዬ በረከት ያሳትፈን።
 ------------------------------------ 
አቡነ ገሪማ
(by Wubishet Tekle …  ) ሰኔ 17 በዚህች ቀን ከዘጠኙ ቅዱሳን አንዱ የሆነው አቡነ ገሪማ አረፉ። ዘጠኙ ቅዱሳን በአምስተኛው መቶ ክፍለ ዘመን ወደ አገራችን ኢትዮጵያ መምጣታቸው የሚታወቅ ነው። ይህ አቡነ ገሪማ በአባቱ መንግስት በሮም ለሰባት ዓመት ከነገሰ በኃላ ንግስናውን ትቶ በቅዱስ ገብርኤል መሪነት ወደ ኢትዮጵያ መጣ ከስምንቱ ባልንጀሮቹ ጋር ተቀላቀለ። ለአቡነ አረጋዊ የእህት ልጅ ነው። ሲመነኩስ እድሜያቸው 28 ነበር። የእኚህ አባት የመጀመሪያ ስማቸው ይስሐቅ ነበር ፤ በኃላ ነው ተአምራቱን አይተው ገሪማ ያሉት። ታሪኩ እንዲህ ነው ካህናቱ ተሰብስበው ምግብ በልተህ ቅዳሴ ቀድሰካል ብለው ያወግዙታል እርሱም እሺ ካላችሁ ብሎ ከተቀመጠበት ነስቶ ሲሄድ በዙሪያው ያሉት ዛፎች፣ ሳር ቅጠል ድንጋዮች እየተፈነቃቀሉ ተከትለውት ሄዱ፤ ይህን ያዩ ካህናት ሳር ቅጠሉ የሚታዘዙለት ይህ ማነው ብለው ተገረሙ በተአምራቱ በጣም ተደነቁገሪማ ገረምከነ” “ገሪማ ገረምከነአሉት አስገረምከን ማለት ነው፡፡ በዚህ የተነሳ ነው አቡነ ገሪማ የተባለው ዘወትር በማኅበር ለማዕድ ሲቀመጡ የሚበላ ይመስላል እንጂ ምግቡን ኮሮጆው ውስጥ ከቶ ለጦም አዳሪዎች ይመጸውት ነበር፤ ካህናቱ የተመገበ መስሏቸው ነው ለማውገዝ የተነሳሱት። አቡነ ገሪማ አድዋ አካባቢ መደራ በተባለ ቦታ ታላቅ ገዳም አላቸው ከዚህም በተጨማሪ አገራችን ውስጥ በስሙ የታነጹለት 27 አብያተ ክርስቲያናት እንዳሏቸው ሊቀ ብርሃናት መርቆሪዎስ አረጋ የቅዱሳን ታሪክ በሚለው መጽሐፋቸው ተቅሰውታል ብጹዕ አቡነ ጳውሎስ የኢትዮጵያ አምስተኛው ፓትርያርክ በወጣትነታቸው ትምህርታቸውን የተከታተሉት በዚሁ በአቡነ ገሪማ ገዳም ነው። አቡነ ገሪማ በርካታ ታአምራትን አድርገዋል ፤ በምራቁ ጸበል አፍልቋል እንደ ኢያሱ ጸሐይን አቁሟል ወይን ጠዋት ተክሎ ለዘጠኝ ሰዓት ለምስዋት አድርሷል፣ በርካታ ድውያንን ፈውሷል፣ በመጨረሻም በተወለዱ 99 ዓመት 1 ወር 3 ቀኑ ሰኔ 17 በዛሬዋ ቀን እንደ ቀደሙት አባቶቹ ሄኖክና ኤሊያስ ሞትን ሳይቀምሱ ተሰውረዋ። በረከታቸው ይደርብን።
------------------------------------  

ቅዱስ ገላውዲዎስ
(by Wubishet Tekle …  ) ሰኔ 11 በዚህች ቀን ከሰባቱ ዓበይት ሰማዕታት አንዱ የሆነው ሰማዕቱ ቅዱስ ገላውዲዎስ አረፈ። ስንክሳሩ የመልአክት አርአያ ያለው ይለዋል ንጽህናውን ቅድስናውን ሲያጠይቅ፤ የሮም የነገስታት ልጅ ነው ዓለምን ክብሩን ሁሉ ንቆ ወጣ በፍጹም ተጋድሎም ኖረ ለጣኦት አልሰግድም አልሰዋም ብሎ ሰው ሊሰማው የሚከብድ ጽኑ መከራዎችን በትእግስት ተቀበለ በዛሬዋ ቀንም አንገቱ ተቆርጦ በሰማዕትነት አረፈ። ሰኔ 11 ቀን የሚነበበው ስንክሳር ታሪኩን በሰፊው ጽፎታል፤ ሊቀ ብርሃናት መርቆርዮስ አረጋ ይህ ሰማዕት በተለይም በጎንደር ልዩ ክብር እንዳለውና በስሙ ታላላቅ ገዳማት እንደታነጹለት በአጠቃላይ ኢትዮጰያ ውስጥ 16 የማያንሱ አብያተክርቲያናት እንዳሉትየቅዱሳን ታሪክበሚለው መጽሐፋቸው ጠቅሰውታል፤ በነገራችን ላይ በዚሁ ስም የሚጠሩ ታላቅ የኢትዮጰያ ጻድቅ ንጉስም አሉ ዓጼ ገላውዲዎስ ግራኝ መሐመድን ድል የነሱ ናቸው ቤተክርስቲያን መታሰቢያቸውን መጋቢት 27 ቀን ታከብረዋለች። የዲያቆን ዳንኤል ክብረትን የቤተክርስቲያን ማረጃዎች የሚለውን መጽሕፍ ይመልከቱ ።ከበዓሉ በረከት ያሳትፈን።
------------------------------------  



ዓፄ ገላውዴዎስ 
መጋቢት 27 የጌታችን ጥንተ ስቅለቱ ነው። ዳግመኛ በዛሬዋ ቀን በኢትዮጵያ ምድር ታላቅ አባት በሰማእትነት አርፏል ይህም ዓፄ ገላውዴዎስ ነው፤ ይህ አባት ቤተክርስቲያን የቅድስና ማእረግ ሰጥታ ከምታዘክራቸው ነገስታት የመጨረሻው ንጉስ ነው። ከዚህ በኃላ በኢትዮጵያ ምድር የነገሱት ነገስታት ምን ደግ ስራ ቢሰሩ የቅድስና ማዕረገ አላገኙም። ዓፄ ገላውዴዎስ የዓፄ ልብነ ድንግል ልጅ ናቸው፤ ግራኝ መሐመድ ኢትዮጵያን ሲወር ከአባታቸው ጋር ሸሽተው ወደ ደብረ ዳሞ ሄዱ በዚያም 17 ዓመት ቆዩ አባታቸው ዓፄ ልብነ ድንግል ሲሞቱ ወራሽ ሆነው ነገሱ ጦራቸውን አደራጁ ከፖርቹጋሎች ጋር ሆነው ግራኝን ገጠሙት ለየካቲት ማርያም 1543 / ወይና ደጋ በተባለ ቦታ ላይ ድል አደረጉት ግራኝ ሞተ የቀሩት ሸሹ ይላል፡፡ በጦርነቱ ማግስት ፖርቹጋሎችአባትህ ቃል በገባልን መሰረት አገር ቆርሰህ ስጠን ሃይማኖታችሁንም ለውጣችሁ የካቶሊክን እምነት ተቀበሉአሏቸው፤ዓፄ ገላውዴዎስም ሲመልሱአገር ቆርሰን አንሰጥም ሃይማኖትም አንለውጥም፤ ለዋላችሁልን ውለታ ግን ወርቅ ብር እንሰጣቹሃለን አሏቸው !!! ብልህ መሪ ይሉሃል ይህ ነው፤ ኢይኀድጋ እግዚአብሔር ለብሔር ዘእንበለ አሐዱ ሄርየሚለው አባባል እዚህ ጋር የተመቸ ነው።እግዚአብሔር አገርን ያለ አንድ ጠባቂ አይተዋትም ማለት ነው። በዓፄ ገላውዴዎስ መልስ የፖርቹጋሉ ጦር አዛዠ ቤርሙዳ ተቆጣ በስውርም ሊያስገድሏቸው አስቦ አልተሳካለትም። ከዚህ በኃላ ግራኝ ያጠፋውን አገር ማቅናት፤ የተጎዳ የተሰደደውን ህዝብ ማጽናናት ጀመሩ ከአቡነ ዮሳብ ጋር ሆነው ስርዓተ ቤተክርስቲያንን አጸኑ ብዙ አብያተክርስቲያናትን አነጹ። ከዚህ በኃላ እንዲህ ሆነ የሐረሩን ገዢ ኑር መሐመድን ጦሩን አደራጀቱ መጣ ዘመኑ 1552 / ወርሃ መጋቢት በሃያ ሰባተኛው ቀን ዕለቱ ደግሞ ዓርብ ነው ከሶስት ቀን በኃላ ፋሲካ ነው፤ በዙሪያቸው ያሉት መኳንንት መሳፍንቱ አማካሪዎቻቸው ፋሲካን አክብረን ጦርነቱን ብንጀምር ይሻላል አሏቸው፤ ዓፄ ገላውዲዎስ ሲመልሱ እንዲህ አሉ እኔስ ፋሲካን ከጌታዬ ጋር በሰማይ አከብራለሁ ጦርነቱ መጀመር አለበት አሉ ትንቢታዊ ንግግር ነበር፤ ጦርነቱ ተጀመረ ከፊት ሆነውም ሲዋጉ ሲያዋጉ ውለው ማምሻውን በጥይት ተመትተው ወደቁ አንገታቸውንም ቆርጠው ገደሏቸው። ታዲያ ህዝቡ እንዲህ ብሎ አለቀሰላቸው፤
ዓፄ ገላውዴዎስ ጌታን ተከተለ
ፋሲካውን ሳይውል አርብ ተሰቀለ፤
በረከታቸው ይደርብን። ስንክሳር፤ የቤተክርስቲያን መረጃዎች(ዳንኤል ክብረት)

------------------------------------  

ቅዱስ አባ ቴዎቅሪጦስ 
(by Wubishet Tekle …  )መጋቢት 17 በዚህች ቀን የአገረ ሮሜው ቅዱስ አባ ቴዎቅሪጦስ በሰማዕትነት አረፈ። ገና 15 ዓመት ብላቴና ሳለ ዓላውያን ለጣኦት እንዲሰዋ ግድ አሉት፤ ከጌታዬ ከእየሱስ ክርስቶስ በቀር አምላክ የለም አላቸው፤ እየደበደቡ ንጉሱ ጋር አቀረቡት፤ ንጉሱም ለጣኦት ስገድ አለው፤ ንጉሱንም ጣኦታቱንም ዘለፋቸው፤ ንጉሱ ተቆጣ አፍንጫውን ቆረጠው፤ ወደ ገደል ወረወረው፤ ስጋው እስኪበጣጠስ አጥንቶቹ እስኪሰባበሩ አስደበደበው፤ እንዲያውም የሰደባቸው የዘለፋቸው አማልክቶቻችንን ተበቅለው ያጥፉት ብሎ ጣኦት ቤት አስገብተው ዘጉበት፤ ይህ ቅዱስ ግን ጣኦቶቹ ላይ ያለውን ወርቅ እያወለቀ በስውር ወጥቶ ለጦም አዳሪዎችና ለምስኪኖች ከፋፍሎ ይመለሳል፤ በሩ እንደቀድሞ ይዘጋል ሐዋ 1626 ጳወሎስና ሲላስ የወህኒ ቤቱ በር በመዝሙር እንደከፈቱት ልብ ይሏል። ከአንድ ሳምንት በኃላ ሊያየው ቢመጣ ጣኦታቱ ተሰባብረው ወድቀው ቅዱሱ ሲዘብትባቸው አገኘው 1 ሳሙ 54 በዚህም ተቆጣ የሆድ እቃው እስኪታይ አስደበደበው፤ ወደ መጫወቻ ቦታ አስገቡት አንበሶች ለቀቁበት፤ አንበሶቹ ግን ቁስሉን ላሱለት ዳን 622 ዳግመኛ ልዩ ልዩ መከራ አደረሰበት በመጨረሻም በዛሬዋ ቀን አንገቱን ቆርጠው ገደሉት እርሱም የሰማዕትነትን አክሊል ተቀዳጀ ለእግዚያብሔር ምስጋና ይሁን እኛንም ከሰማዕቱ በረከት ያሳትፈን።አሜን !!!
------------------------------------  

መጋቢት 13 በዚህች ቀን ፵ ሐራ ሰማይ በሰማዕትነት አረፉ።


by Wubishet Tekle … ዘመኑ ዘመነ ሰማዕታት ነው በወቅቱ በሮም ነግሶ የነበረው ደግሞ አረመኔው ንጉስ ሉክያኖስ ነው፤ መኮንኑ ግሪኮልዮስ ይባላል። ክርስቶስን ክዶ ለጣኦት እንዲሰግድ ህዝቡ ላይ የመከራ ቀንበር ጫኑበት፤ ብዙዎች ሞቱ ብዙዎችም ካዱ። የንጉሱ ወታደሮች የነበሩት በጀግንነታቸው የሚታወቁት አገራቸውን በውትድርና ያገለገሉት ሐራ ሰማይ ግን እኛ የሰማያዊው ንጉስ የእየሱስ ክርስቶስ ወታደሮች ነን ለጣኦት አንሰግድም አሉ። ለዚህም ነው ሐራ ሰማይ የተባሉትየሰማያዊ ንጉስ ወታደር ተከታይማለት ነው፤ ብዛታቸው 40 ነው። ከዚህ በኃላ ልዩ ልዩ ጸዋትኦ መከራ አጸኑባቸው ይህን ሁሉ ታገሱ፤የመጨረሻ መከራቸው ግን ለየት ያለ ነበር፤ ሰውነትን የሚቆራርጥ እጅግ ቀዝቃዛ ወደሆነ የበረዶ ባህር ውስጥ መጣል መወርወር፤ ተጣሉ ተወረወሩም ስቃዩ ቅዝቃዜው እጅግ ጸናባቸው፤ ቀናት፤ ሳምንታት፤ ወራት ተቆጠሩ ወታደሮች ዙሪያውን ከበው እየተመለከቷቸው ነው፤ የሚገርመው የመጨረሻው ቀን ላይ አንዱ ስቃዩ ሲጸናበት ከባህሩ ወጣ 39 ቀሩ ነገር ግን 40 የብርሃን አክሊላት ወርዶ በራሳቸው ላይ አረፈ አንዷ ብቻ አየር ላይ ተንጠልጥላ ቀረች፤ ይህንን የተመለከተ ወታደር ሮጦ ወደ ባህሩ ገባ ከሰማዕታቱ ጋርም ተቀላቀለ፤በበነጋው ሁሉንም በሰይፍ ገደሏቸው ይህም መጋቢት 13 ቀን ነው። ከሰማዕታቱ በረከት ያሳትፈን።
ስንክሳር፤ ገድለ ሰማዕታት
------------------------------------  
አቡነ ገብረመንፈስ ቅዱስ 
ቀኑ መጋቢት 5 ዕለቱ ቅዳሜ ለእሁድ አጥቢያ ሰዓቱ ከሌሊቱ ስድስት ሰዓት ሆኗል፤ አሁንም ህማሙን እየታገለ እያላበው በድካም ለፍጥረቱ ሁሉ ይለምናል፤ “አቤቱ ህዝብህን አድን ርስትህን ኢትዮጰያንም ባርክ” ይላል። ህመም የጀመረው መጋቢት 3 ዓርብ ቀን ነው፤መታመሙን የሰሙ እንደርሱ ቅዱሳን የሆኑት ዘርአ ቡሩክ፤ ፍሬ ቅዱስ፤ያዕቆብ፤ብንያምና ዮሴፍ እንዲሁም በወቅቱ የኢትዮጰያ ንጉስ የነበረው እንድርያስ ሊጠይቁት ተሰብስበዋል ወደ አጠገቡ መድረስ ግን አልተቻላቸውም አባታችን ገብረመንፈስ ቅዱስ የሚጋርደው እንጨት ዛፍ በሌለበት በርሃ እንደ አንበሳ ተኝቶ አዩት በላዩ ያረፈው የእግዚያብሔር ጸጋ ከፊቱ የሚወጣው ብርሃን ቀይ መልኩ ረዥም የራስ ጠጉሩ እንደ ነጭ ሐር የሚሆን ጽሕሙ አስደነቃቸው። ከሌሊቱ ሰባት ሰዓት ሲሆን ከሰማይ ታላቅ ነጎድጓድ ድምጽ ተሰማ ጌታችን መላአክትን አስከትሎ ወደ አባታችን ወረደ፤ ከሰማይ ወደ ምድር ህብሩ አምሳያው ልዩ ልዩ የሆነ እንደ ጸሐይና እንደ ጨረቃ የሚያበራ እንደ ወንጪፍ ድንጋይ ይወረወር ነበር ከዚያ የነበሩ ሁሉ ፈሩ ወደ ኃላም ሸሹ ምድር ራደች ተራሮች ኮረብቶች ተናወጡ ብርቱ ጩኸት ንውጽውጽታ ሆነ። “ወዳጄ ገብረመንፈስ ቅዱስ ሰላም ላንተ ይሁን” እነሆ የማይታበል ቃል ኪዳን እገባልኃለው ስምህን የጠራ መታሰቢያህን ያደረገውን፤ እጣን ቋጥሮ ግብር ሰፍሮ መባ ይዞ ቤትህ የመጣውን እምርልኃለው አንተ ከገባህበት ገነት መንግስተ ሰማያት አገባዋለሁ አለው፤ አባታችንም “አቤቱ ጌታ ሆይ የኢትዮጰያን ህዝብ ማርልኝ” አለው፤ እነሆ ምሬልኃለው አስራት በኩራት አድርጌም ሰጥቼሃለው፤ ከመጋቢት አምስት ቀን ጀምሮ ዝክርህን ያድርጉ በአማላጅነትህም ይማጸኑ አለው። ከዚህ በኃላ ሰባቱ ሊቃነ መላክት የአባታችንን ነፍስ ሊቀበሉ ወረዱ በታላቅ ምስጋናም ወደ ሰማይ አሳረጉት ስጋውንም ይዘውት ሄዱ የት እንደተቀበረ ግን እስካሁን አይታወቅም አንዳንዱ በእየሩሳሌም ነው ይላሉ፤ ሌላው በምድረ ከብድ ነው ይላል ግን እስካሁን ልክ እንደ ሊቀ ነብያት ሙሴ ስጋ የት እንደተቀበረ አይታወቅም። ገድሉ ትሩፋቱ ከሰማይ ከዋክብት ከምድር አሸዋ ይበዛል ኢትዮጰያን አብዝቶ ይወዳታል፤ ምድራዊ ምግብ አልተመገበም የእናቱን ጡት እንኳን አልጠባም፤ ልብስ፤ መጠለያ አልፈለገም፤ የክረምት ቁር የበጋ ሐሩር እየተፈራረቀበት በተጋድሎ 562 ዓመት ኖረ፤ በዛሬዋ ቀን ሩጫውን ጨረሰ። ለእግዚያብሔር ምስጋና ይሁን እኛንም ከአባታችን በረከት ያሳትፈን። ታሪክ:- አዲስ አበባ የሚገኘው ሳሪስ አቦ ቤተክርስቲያን ከዕለታት በአንዱ ቀን ጻደቁ አባታችን ወደ ዝቋላ ሲሄዶ ለጥቂት ቀናት ቦታው ላይ አርፈውበት እንደነበር ይነገራል፤ይህ ከሊቃውንቱ አንደበት ያገኘነው ቃል ነው።
------------------------------------
መጥምቁ ዮሐንስ
"እውነት እላችኋለሁ፥ ከሴቶች ከተወለዱት መካከል ከመጥምቁ ዮሐንስ የሚበልጥ አልተነሣም፤" ማቴ 1111 ዛሬ የካቲት 30 የከበረች የመጥምቁ ዮሐንስ ራስ ተገለጸችበት ቀን ነው ሄሮድስ አንገቱን ለአንዲት ጋለሞታ ዘፈኝ ሲል አስቆረጠው፤ ማር 627 በዚህን ጊዜ ጣፋጭ መዓዛ አካባቢውን አወደው በዚህም ብዙ ድውያን ተፈወሱ ይላል። የተፍጻሚተ ሰማዕት ቅዱስ ጴጥሮስን አንገቱን ሲቆርጡት ለሁለት ሰዓት አንገቱ አየር ላይ ቀጥ ብላ ቆመች ይላል፤ ግሩም ነው፤ ቅዱስ ጳውሎስ በጥላው ድውያን ይፈውስ ነበር፤ ቅዱስ ዮሐንስ ደግሞ በሰውነቱ መዓዛ የሚገርም ነው ከዚህ በኃላ በወጪት አድርጎ ለወለተ ሄሮዲያዳ ሰጣት የቅዱስ ዮሐንስ አንገት ክንፍ አውጥታ በረረች በደቡብ ዓረቢያ አስራ አምስት ዓመት ወንጌልን ሰበከች ሚያዚያ 15 ቀን አረፈች፤ ከዘመናት በኃላ ነጋዴዎች እዚያ ቦታ አደሩ ከነዚህም ሁለቱ ደጋግ ክርስቲያኖች ነበሩበት ቅዱስ ዮሐንስ በህልማቸው ተገለጸላቸው የከበረች እራሱንም እንዲያወጡ ነገራቸው ሲነጋም እንዳዘዛቸው አደረጉ ይህም የካቲት 30 ቀን ነው፤ ከቀሪ ስጋው ጋር ቀበሩት ቀድሞ ስጋው የተቀበረው በታላቁ ነብይ በኤልሳ መቃብር ነበር፤ ቅዱስ ዮሐንስ ሰኔ 30 ልደቱ ነው፤መስከረም 2 አንገቱ የተቆረጠበት ሚያዚያ 15 ያረፈበት፤የካቲት 30 ራሱ የተገለጸበት ነው። ከነዚህ ውስጥ መስከረም 2 እና ሰኔ 30 ቤተክርስቲያን ሰማዕቱን በደማቁ ታዘክረዋለች። ከቅዱስ ዮሐንስ በረከት ያሳትፈን።
(
ስንክሳር፤ገድለ ዮሐንስ መጥምቅ የካቲት ወር የሚነበብ)

ሮማዊው ቅዱስ ቴዎድሮስ
የካቲት 28 በዚህች ቀን ሮማዊው ቅዱስ ቴዎድሮስ አረፈ። በዚህ ስም የሚጠሩ ብዙ ቅዱሳን አሉ፤የሰራዊት አለቃ የተሰኘውና በዲዮቅልጥያኖስ ዘመን በሰማዕትነት የሞተው ቴዎድሮስ ዋነኛው ነው እረፍቱ ሐምሌ 20 ሲሆን በአገራችን በስሙ አብያተክርስቲያናት ታንጸውለታል፤ ቢሾፍቱ መስመር የረር በዓታ ጽላቱ አለ። በየዓመቱ ግንቦት 21 ቀን ግብጽ በደብረ ምጥማቅ እመቤታችን ለክርስቲያኑ ለአህዛቡ ተገልጻ ትታይ ነበር፤ ታዲያ ህዝቡ የተለያየ ጥያቄ ይጠይቃታል አባታችን አዳምን አሳዪን ሲሏት አዳምን ታሳያቸዋለች፤ ሄዋንን፤ ዳዊትን ሙሴን አብርሃምን... የጠየቋትን ከገነት እየጠራች ታሳያቸው ነበር ይላል ተአምረ ማርያም፤ ሰማዕታትን አሳዪን ሲሏት ደግሞ ቅዱስ ጊዮርጊስን ቅዱስ መርቆርዮስንና ይህንን ቅዱስ ቴዎድሮስን ነበር ጠርታ ይምታሳያቸው ስለዚህም በ3ኛ ደረጃ ያለ ሰማዕት ነው። ምስራቃዊ ቴዎድሮስ የሚባል ሰማዕትም አለ፤ ቴዎድሮስ ሳልሳይም ( ቴዎድሮስ 3ኛው) ኢትዮጰያዊ ነው ታሪኩን ግን እዚህ መጻፍ የተመቸ አይደለም ምነዋ ቢባል ዘመኑ ክፉ ነውና፤ ዳሩ ግና ታሪኩ ገድለ ፊቅጦር፤ድርሳነ ኡራኤል፤ትልቁ ፍካሬ እየሱስ ላይ በስፋት ተጽፏል። ነገርን ነገር ያነሳዋል እንዲሉ ስለ ቴዎድሮሶች ይህንን አልን፤ ለመሆኑ ዛሬ መታሰቢያውን የምናደርግለት ቴዎድሮስ ታሪኩ እንዴት ነው ቢሉ፤ በመክሲሞስና መክስምያኖስ ዘመን የነበረ ነው አገሩ ሮም ነው፤ እንሾምሀለን እንሸልምሀለን ለጣኦት ስገድ አሉት፤ ሹመት ሽልማታችሁ ለጥፋት ይሁንባችሁ ከእግዚያብሔር በቀር አምላክ የለም አላቸው ዘለፋቸው እረገማቸውም፤ ዘቅዝቀው ሰቀሉት ደሙ እንደ ውኃ እስኪፈስ ገረፉት ደሙ የነካቸው ብዙ በሽተኞች ዳኑ ይህንንም ያዩ ብዙዎች አመኑ፤ዳግመኛ የእሳት ምድጃ ውስጥ ከተቱት ነፋስ ነፈሰ ነጎድጓድም ሆነ ምንም ሳይነካው ከእሳት ወጣ፤ ዳግመኛ አፉን ለጎሙት እጆቹን እግሮቹን ቸንክረው ለአንበሳ ጣሉት፤ አንበሳው እንባውን አፈሰሰ ይላል ተንበርክኮ ሰገደለት ዳን 6፤22። በዚህ ጊዜ ጌታችን ተገልጾ “ስምህን የሚጠራ መታሰቢያህን የሚያደርገውን እምርልሃለው” ሲል ቃል ኪዳን ገባለት ማቴ 10፤41 ፤ ከዚህ በኃላ የሁለት መቶ ሸክም እንጨት መቶ ልጥር ባሩድ፤የዶሮ ማር፤ነሐስ አመጡ፤ እጅግ እስከሚግል አነደዱት እሳት ውስጥ ወረወሩት፤ምስክርነቱን በዚህ ፈጸመ፤ ቅዱስ ሚካኤልና ገብርኤል ነፍሱን ተቀብለው በሶስት አክሊል አቀዳጇት፤ስጓውንም አውሳብያ የተባለች የመኮንን ሚስት ወስዳ በገላትያ ቀበረችው ቤተክርስቲያንም ሰራችለት። ለእግዚያብሔር ምስጋና ይሁን እኛንም ከሰማዕቱ በረከት ያሳትፈን።
------------------------------------
ጥር 18 የቅዱስ ጊዮርጊስ ዝርዎተ አጽሙ
by Wubishet Tekle …ዳግመኛም ያ ከሃዲ ንጉስ ዱድያኖስ ግንድ አምጥተው ቅዱስ ጊዮርጊስን በግንዱ ላይ እንዲቸነክሩት አዘዘ፤በላዩም ላይ ሰም አፍስሰው እሳት እንዲያነዱበት አደረገ ፤ ከዚህም በኃላ እንደመጭመቂያ ሆኖ ከተሰራ የስቃይ መሳሪያ ላይ አወጡት ሰውነቱን እንዲሰነጥቁት እንዲጨምቁት አዘዘ፤አንጀቱ ሁሉ ወጥቶ ከምድር ላይ እስኪዘረገፍ ድረስ እንዲሁ አደረጉበት ነፍሱ ከስጋው ተለየች የሰማእቱን ሰጋ አቃጠሉት ፈጩት አመድም ሆነ በቀፎ አድርገው ይድራስ ወደሚባል ተራራ ላይ በነፋስ ዘሩት ደብረ ይድራስ ማለት ምድረ በዳ ነው ወታደሮቹ የታዘዙትን ፈጽመው ተመለሱ። ያንጊዜም መብረቅ ነጎድጓድ ታላቅ ንውጽውጽታ ሆነ ምድርም ከመሰረቷ እስክትናወጽ ድረስ ከሰማይ ድምጽ ተሰማ ጌታችን መድሐኒታችን እየሱስ ክርስቶስ መላእክትን አስከትሎ በብሩ ደመና ወረደ በተራራውም ላይ ተቀመጠ አራቱን የምድር ነፋሳት የሰማእቱን ስጋ እንዲሰበሰቡ አዘዛቸው ከሞትም አስነሳው ኃይሉን አሳደረበት ባርኮትም ወደ ሰማይ አረገ፤ ከዚህ በኃላ ቅዱስ ጊዮርጊስ እየሮጠ ወታደሮቹን ተከተላቸው ወንድሞቼ ቆዩኝ ከናንተ ጋር ልሂድ እያለ ተጣራ የነዚህ የወታደሮች ቁጥር አራት ነው ስማቸው ህልቶን፤አግሎሲስ፤ሶሪስና አስፎሪስ ነው፤ ይህንን ታላቅ ተአምራት አይተው አምነዋል፤ በኃላም በሰማእትነት ሞተዋል፤ ይህ የሆነው ጥር 18 በዛሬዋ ቀን ነው ይህንንም ቀን " ዝርዎተ አጽሙ " ስትል ቤተክርስቲያን ሰማእቱን አዘክራ ትውላለች፤ በስሙ በታነጹለት አብያተክርስቲያናት በሙሉ ታቦተ ህጉ ውጥቶ በደማቁ ተከብሮ ይውላል። አራዳ ጊዮርጊስን የተከሉት ደጉ ንጉስ እምዬ ምኒሊክ ናቸው ታዲያ የዚህን ታላቅ ደብር መሰረቱን ሲጥሉ የቅዱስ ጊዮርጊስ መቃብር ከሚገኝበት ቦታ አፈሩን በመርከብ አጓጉዘው በበቀሎ በፈረስ አስጭነው መሰረት አድርገውታል፤ይህንን ከአባቶቻችን የሰማነው ነው፤ ከበዓሉ በረከት ያሳትፈን።

ገድለ ቅዱስ ጊዮርጊስ ምዕራፍ 6 ፤ 15 - 18
------------------------------------
ብፁእ አባታችን አቡነ ዘርዐ ቡሩክ
በረከታቸዉ ይደርብንና ብፁእ አባታችን አቡነ ዘርዐ ቡሩክ ከአባታቸዉ ከቅዱስ ደመ ክርስቶስ ከናታቸዉ ከቅድስት ማርያም ሞገሳ 8 ኛዉ መቶ /ዘመን መጨረሻ በክብር ተወለዱ ከመወለዳቸዉ አስቀድሞ ቅድመ አያታቸዉ ከኔ ዘር 7 ትዉልድ አንዲት ሴት ትወልዳለች ከርሶም አለምን በጸሎቱ የሚያድን ይወለዳል ብለዉ ትቢት ተናግረዉላቸዉ ነበር፡፡  በተወለዱ 7 አመታቸዉ ይህን አለም ክፋቱን እንዳላይ አይኖቸን አሳዉርልኝ ብለዉ ጸለዪ አይኖቻቸዉም እስከ 12 አመታቸዉ ማየት አይችሉም ነበር፡፡  ከዛም በኋላ የዓለምን ክብር በመናቅ በትምህርት ምክንያት ከሃገር ወደ ሃገር ከገዳም ደ ገዳም እየተዘዋወሩ ብዙ ታምራትን ሲያደርጉ ቆይተዋል፡፡  ከአቡነ ገብረ መንፈስ ቅዱስ ጋር መጋቢት 27 ቀን ዲያቆን ሆነዉ ቀድሰዋል ፤ በአቡነ ገብረ መንፈስ ቅዱስ ሞት ጊዜም ተገኝተዋል በአቡነ ገብረ መንፈስ ቅዱስ ገድል መጽሃፍ ላይም ሰፍረዉ ይገኛሉ  12 ክንፎችም ተሰተዋቸዋል በግዮን ምንጭ ግሽ አባይ በተባለዉ ቦታ 30 አመታት ጸልየዋል አሁንም በዛዉ ግሺ አባይ ፈለገ ግዮን ቅዱስ ሚካኤል እና አቡነ ዘርአ ቡሩክ ቤተክርስቲያን በጸበላቸዉ ታምራት እየተደረገ ነዉ ፡፡
ታህሳስ 13 አባታችን አቡነ ዘርዐ ቡሩክን የምናስብበት ቀን ነዉ ከበረከታቸዉ ያካፍለን አሜን 
ምንጭ : ገድለ ዘርዐ ቡሩክ እና ተአመረ ዘርዐ ቡሩክ በግዕዝና በአማርኛ
ይህ የምታዪት ደብር  ፈለገ ግዮን ግሽ አባይ አቡነ ዘርዐ ቡሩክ እና የቅዱስ ሚካኤል ቤተክርስቲያን ነዉ
------------------------------------

አባ ሳሙኤል ዘዋልድባ

(by Wubishet Tekle  )ታሀሳስ 12 በዚህች ቀን ታላቁ ኢትዮጰያዊው ጻድቅ አባ ሳሙኤል አረፈ። የትውልድ ቦታው አክሱም ነው፤ 18 ዓመቱ ከአቡነ መድሐኒነ እግዚ እጅ ምንኩስናን ተቀበለ በዚያው በደብረ ባንኮል 13 ዓመት በተጋድሎ ኖረ፤ከዚያም ወደ ጎንደር ደምቢያ ሄደ 3 ወር ከዘረጋ ሳያጥፍ ከቆመ ሳያርፈ እህል ውኃ ሳይቀምስ በተጋድሎ ኖረ፤ከድካም ብዛት አጥንቱ ተሰብሮ ወደቀ ጌታችን ተገለጸለት አበረታው ያንተ ክፍልህ እዚህ አይደለም ወደ ዋልድባ ሂድ አለው፤ ወደ ዋልድባ ሄደ በዚያም ግርማ ሌሊቱን ድምጸ አራዊቱን ታግሶ ማቅ ለብሶ ድንጋይ ተንተርሶ በተጋድሎ ኖረ። ይህ አባት ለእመቤታችን ልዩ ፍቅር ነበረው ውዳሴዋንና ቅዳሴዋን በቀን 64 64 ጊዜ ይጸልይ ነበር፤ውዳሴዋን እየደገመ መንገድ ሲሄድ ከምድር ክንድ ከስንዝር ከፍ ይላል፤ እመቤታችን እንደ ጓደኛ ታነጋግረው ነበር ይላል። ውኃ ላይ ውዳሴ ማርያም ሲደግም ውኃው ተለውጦ ህብስት ይሆንለት ነበር፤ ከቦታ ቦታ የሚጓጓዘውም በአንበሳ ላይ ተቀምጦ ነበር፤ ከመሞቱ በፊት ጌታችን ብዙ ቃል ኪዳን ገብቶለታል፤ 100 ዓመቱ ታህሳስ 12 ቀን አርፏል። ታሪክን ታሪክ ያነሳዋል እንዲሉ፤ ስለ ዋልድባ ገዳም ገናንነት በድርሳነ ኡራኤል ላይ እመቤታችን እንዲህ ብላ ተናገረች:-     " ከኤሮድስ ፊት ሸሽቼ በተሰደድኩኝ ጊዜ ልጄ በእጁ ደመና ጠቀሰ በዚያች በምታበራ ደመና ላይ ተቀምጠን መጀመሪያ ወደ ናግራን ( የዛሬዋ የመን) ሄድን ከዚያም ወደ ሐማሴን (ኤርትራ) አክሱምን ጎብኝተን፤ የተከዜን ወንዝ ተሻግረን ታላቅ ጫካ የለበሰ ገዳም አገኘን በዚያም አረፍን ያቺ ቦታ ዋልድባ ትባላለች፤ ልጄ ስለዚያች ገዳም እንዲህ አለኝ እናቴ ሆይ በኃላኛው ዘመን ለኔ የሚገዙ ባንቺም ፍቅር የነደዱ ቅዱሳነ መነኮሳት በዚህች ገዳም ይበዛሉ፤ የጣመ የላመ አይበላበትም የሞቀ የደመቀ አይለበስበትም፤   ምግባቸው ይህ መራራ የዛፍ ስር ነው ብሎ አሳየኝ አለች። ይህ የነገራት ትንቢት የተፈጸመው 485 / ነው። ይህ የሚገርም ሰፊ ታሪክ ቢኖረውም በአጭሩ እንዲህ ይነበባል፤ ከሸዋ ቡልጋ ብዙ መነኮሳት ወደ እየሩሳሌም እንሄዳለን ብለው ተነሱ፤ አዲስ አበባ መጡ ፉሪ ወጨጫንና እንጦጦን በማቋረጥ ወሎ አማራሳይንት አቋርጠው በጎንደር ሊቦ አድርገው ከምከም በለሳና ደባርቅን ጨርሰው የሊማሊሞን ጠመዝማዛ ተራራ በማቋረጥ ዋልድባ ደረሱ ይላል። እዚያም ጌታ ተገለጸላችው የናንተ ክፍላችሁ እዚህ ነው፤ በምጽአት እስክመጣ በዚህ ነው የምትኖሩት ለበቁ አባቶች እየተገለጻችሁ የገዳሙን ስርዓት ንገሩ ብሎ ሰውሯቸዋል፤ እነዚህ ስውራን መነኮሳት ዛሬም ድረስ አሉ፤ይህ በምን ይታወቃል  ቢሉ ዋልድባ  ጸጥ  ረጭ ብሎ የጸናጽል የደወል ድምጽ ይሰማል ልብን የሚማርክ የእጣን መአዛም ይሸታል፤አልፎ አልፎ እነዚህ ስውራን ቅዱሳን እንደኔ ኃጢያተኛ ያልሆነ በጾም በጸሎት የበረታ ሰውን ተገልጸው አነጋግረውት ይሰወራሉ፤ይህንንም እዚያ የሚኖሩ አባቶች መሰከሩልን። ጻድቁ ተክልዬ ከነዚህ ስውራን ቅዱሳን ጋር 3 አርባ ማለትም 120 ቀን አብረው እንደኖሩ ገድለ ተክልሃይማኖት ላይ ተጽፏል።  ከመልአኩ ከቅዱስ ሚካኤል  ከአባታችን  ከአቡነ  ሳሙኤል  በረከት ያሳትፈን ይህንን ገዳም ለመሳለም ያብቃን።
------------------------------------

ቅድስት ስርስት 
ታህሳስ 10 በዚህች ዕለት ቅድስት ስርስት አረፈች፤ አገሯ ቁስጥንጥንያ ነው ወላጆቿ በሀብት በዘመድ የከበሩ ናቸው፤ 12 ዓመት ሲሆናት ለአንድ ታላቅ ባለጸጋ ሊድሯት አሰቡ እርሷ ግን ገዳማትን ተሳልሜ ልምጣ ብላ ከቤት ወጣች አልተመለሰችም፤ አንድ ማቅ የለበሰ ግርማው የሚያስፈራ መነኩሴ አገኘች፤ በምናኔ መኖር እንደምትፈልግ የልቧን ነገረችው የእግዚያብሔር ፈቃድ ይሁን ብሎ ጸጉሯን ላጭቶ አመነኮሳት፤ ከዚህ በኃላ አናብስት አናምርት አክይስት አቃርብት ካሉበት ነቀዐ ማይ ልምላሜ ዕጽ ከሌለበት ዘር ተክል ከማይገኝበት ከጽኑ በርሃ ሄደች፤ ሰው ሳታይ 27 ዓመት በተጋድሎ ኖረች፤ አንድ የበቃ አባት ነበር ሲላስ ይባላል፤ ዛሬ እናቶቻችን ስንቅ ቋጥረው መባ ይዘው ግብር ሰፍረው በገዳም ያሉ አባቴን ጠይቄ ልምጣ ብለው እንደሚሄዱት፤ ይህም አባት ስንቅ ይዞ በበርሃ የሚኖሩ አባቶችን ለመጠየቅ ራቅ ወዳሉ ገዳማት ሄደ፤ አንድ ወሻም አገኘ፤ ወደ ውስጥም ዘለቀ፤ ሰው እንዳለ አውቆ አባቴ ባርኩኝ አለ፤ ቅድስት ስርስትም አባ ሲላስ አንተ ካህን ስትሆን እንዴት ባርኩኝ ትላለህ አለችው፤ ደነገጠ ስሜን እንዴት አወቀችው ካህን መሆኔንስ ማን ነገራት አለ፤ አረፍ በል አለችው ጨዋታ ጀመሩ እንጀራ ሰጣት አልበላችም፤ አመጣጥህ መልካም ነው ብላ ታሪኳን ሁሉ ነገረችው እርሱም ጻፈው በዚያኑ ቀን አረፈች፤ ይህም ታህሳስ 10 ነው፤ ገንዞ በዚያው በገዳሟ ቀበራት፤ ለእግዚያብሔር ምስጋና ይሁን። ዳግመኛ በዛሬዋ ቀን ሃይማኖታችንን ካቀኑት አርዮስን አውግዘው ከለዩት 318 ሊቃውንት አንዱ የሆነው አባ ኒቆላዎስ ያረፈበት ቀን ነው፤ ይህ አባት በህጻንነቱ እሮብና አርብ ቀን 9 ሰዓት ካልሆነ የእናቱን ጡት አይጠባም ነበር፤ 9 ዓመቱ ቅስና ተቀበለ፤ ታላቅ ጸጋ ድንቆችን የማድረግ ሀብት...

 ------------------------------------
ኤልያስ
እነሆ የተባረከ የታህሳስ ወር ባተ፤ ይህ ወር ቀኑ 9 ሰዓት ነው ሌሊቱ 15 ሰዓት፤ ቀኑ በጣም አጭር ነው ፤ ቶሎ ይመሻል ሌሊቱ በጣም ረጅም ነው፤ ታህሳስ 1 በዚህች ቀን በገለዓድ ይኖር የነበረው ቴስብያዊው ኤልያስ የተወለደበት ቀን ነው፤ ታሪኩ 1ኛ ነገስት 17፤1 ላይ በስፋት ይገኛል፤ በእሳት ሰረገላ የተሰወረው ጥር 6 ቀን ነው፤ እነዚህን ሁለት ቀናት ቤተክርስቲያን ነብዩን አስባ ትውላለች፤ ይህ ነብይ በአገራችን በስሙ የታነጹለት አብያተክርስቲያናት አሉት::  ከነዚህም በመዲናችን አዲስ አበባ እንጦጦ ጋራ ላይ የሚገኘው ቤተክርስቲያን አንዱ ነው፤ ኤርትራ ውስጥም አንድ ቤተክርስቲያን አለው፤ ዛሬ በደማቁ ተከብሮ ይውላል፡፡ አክአብና ኤልዛቤል ምሰኪኑን ናቡቴ ከአባቶቹ እርስት አፈናቅለው በግፍ በገደሉት ጊዜ፤ ንጉሱን ሳይፈራና ሳያፍር በግልጽ የዘለፈ ነብይ ነው፤ ዝናብ እንዳይዘንብ ሰማይንም የለጎመ ነው ይህንንም ያዕቆብ በመልእክቱ እንዲህ ሲል መስክሯል ያዕ 5 ፤ 16 "የጻድቅ ሰው ጸሎት በሥራዋ እጅግ ኃይል ታደርጋለች። ኤልያስ እንደ እኛ የሆነ ሰው ነበረ፥ ዝናብም እንዳይዘንብ አጥብቆ ጸለየ፥ በምድርም ላይ ሦስት ዓመት ከስድስት ወር አልዘነበም፤ ሁለተኛም ጸለየ፥ ሰማዩም ዝናብን ሰጠ ምድሪቱም ፍሬዋን አበቀለች"

ከበዓሉ በረከት ያሳትፈን፡፡

 ------------------------------------
ቅዱስ ጴጥሮስ
ህዳር 29 በዚህች ቀን ተፍጻሚ ሰማዕት ቅዱስ ጴጥሮስ አረፈ። በዚህች ሴት ታሪክ እንደርደር ሳራ ትባላለች አገሯ አንጾኪያ ነው ፤ ደግ ክርስቲያን ነች ፤ ጣኦት አምልኮ በተስፋፋበት ወራት ሁለት ልጆች ወልዳ ነበር ፤ የክርስትና ጥምቀትን ልታስጠምቃቸው ግን አልቻለችም ፤ ምነው ቢባል ካህንም ቤተክርስቲያንም ከዚያች አገር ተሰደው ነበርና፤ እስክንድርያ ወስጄ ላስጠምቃቸው ብላ መርከብ ተሳፍራ ጉዞ ጀመረች፤ ታላቅ ሞገድ ተነሳ መርከቧ ልትገለበጥ ደረሰች በዚህ ጊዜ ልጆቼ ሳይጠመቁ ሊሞቱ ነው ብላ ፈራች፤ ምላጭ አውጥታ ጡቷን ሰነጠቀች በደሟም የልጆቿ ግንባር ላይ መስቀል እየሰራች በአብ በወልድ በመንፈስ ቅዱስ ስም ብላ አጠመቀቻቸው፤ ወዲያውኑ ወጀቡ ማዕበሉ ጸጥ አለ እስክንድርያ በሰላም ደረሱ ወደ ሊቀ ጳጳሱ ገባች ፤  የዚህ አባት ስም ተፍጻሜ ሰማዕት ጴጥሮስ ይባላል፤ ልጆቿን ሊያጠምቅ ወደ ጸበሉ ሲጠጋ ጸበሉ እንደ ሰም ይረጋል፤ ሌሎች ህጻናት ሲመጡ መፍሰስ ይጀምራል ፤ ለሁለተኛ ጊዜ ልጆቿ ሲመጡ ጸበሉ እንደ ሰም ይረጋል ሶስት ጊዜ እንዲሁ ሆነ ነገሩ ምንድን ነው ብሎ ጠየቃት የሆነውን ሁሉ ነገረችው፤ በጣም ተደነቀ እግዚያብሔርንም አመሰገነ ይላል። ተፍጻሜ ሰማዕት ጴጥሮስ 3 ደቀ መዛሙርት ነበሩት አርዮስ፤አኪላስና እለእስክንድሮስ ይባላሉ፤ ለአርዮስ ክህነት ሰጥቶ የሾመው ይህ አባት ነው፤ ምን ዋጋ አለው አርዮስ አጥብቆ ተመራመረ ወልድ ፍጡር ነው ብሎ ወደቀ፤ ይህንንም በድብቅ ለሰው ማስተማር ጀመረ፤ በዚህ ጊዜ ጌታችን ለተፍጻሚተ ሰማዕት ጴጥሮስ የተቀደደ ልብስ ለብሶ ተገለጸለት አንተ ማን ነህ ይለዋል ፤ የናዝሪቱ እየሱስ ነኝ ፤ ታዲያ ልብስህ ለምን ተቀደደ ይለዋል “አርዮስ ሰጠጣ ለልብስየ” ይለዋል አርዮስ ልብሴን ቀደደው ማለት ነው፤ ከባህሪ አባቴ ከአብ ከባህሪ ህይወቴ ከመንፈስ ቅዱስ ለይቶ ፍጡር ነው አለኝ ይለዋል፤ ይህን ራዕይ እይቶ ብዙም ሳይቆይ አርዮስ መጣ ቁጭ አድርጎ መከረው “በልብህ ያለውን ኑፋቄ ካሰብክ እንዳትናገር ከተናገርክ እንዳትደግመው ብሎም ያስጠነቅቀዋል፤ ሊሰማው ግን አልቻለም፤ አውግዞ ይለየዋል፤ ጓደኞች አኪላስና እለእስክንድሮስ ሊማልዱለት ይመጣሉ፤ አባታችን አርዮስ ተመልሻለው እያለ ነው ከግዝቱ ፍታው ይሉታል፤ እርሱም እንደማይመለስ ጌታ በራዕይ ነግሮኛል ፤ አሁን እኔ የምሞትበት ጊዜ ደርሷል ፤ ከኔ በኃላ አኪላዎስ ሊቀ ጳጳስ ትሆናለህ ጓደኝነት በልጦብህ አርዮስን ከግዝቱ ትፈታዋለህ ነገር ግን ብዙ አትቆይም ትሞታለህ ብሎ ትንቢት ይነግራቸዋል፤ የእረፍቱ ቀን እንደደረሰም አውቆ “ጌታ ሆይ የኔን ሞት የሰማእታት መጨረሻ አድርግሊኝ ከኔ በኃላ የእንድስ እንኳን ሰማእት ደም እይፍሰስ” ብሎ ጸለየ፤ህዳር 29 ቀን የዲዮቅልጥያኖስ ጭፍሮች አንገቱን ቆርጠው ገድለውታል፤ለዚህም ነው ቤተክርሰቲያን “ተፍጻሚ ሰማዕት ጴጥሮስ” ብላ የምትጠራው የሰማእታት መጨረሻ ማለት ነው፤ ለእግዚያብሔር ምስጋና ይሁን እኛንም ከአባታችን በረከት ያሳትፈን።
------------------------------------

አባ እየሱስ ሞአ
( by Wubishet Tekle ) ገድለኛው አባ እየሱስ ሞአ ህዳር 26 አረፉ። የተወለዱት ጎንደር ጎርጎራ ልዩ ስሙ ዳህና ሚካኤል በ 1196 ዓ/ም ነው፤ በ 30 ዓመታቸው መንነው ደብረ ዳሞ ሄዱ ፤ በአባ ዮሐኒ እጅ መነኮሱ በተጋድሎም ኖሩ፤ ከዚያም ቅዱስ ገብርኤል እየመራቸው ሐይቅ እስጢፋኖስ መጡ፤ ሐይቅ እስጢፋኖስ ማለት ከደሴ 30 ኪሎ ሜትር ርቆ የሚገኝ ሲሆን የመሰረቱት ካልዕ ሰላማ የተባሉ ግብጻዊ ጻድቅ ናቸው፤ ገዳሙን ከሰሩ በኃላ የማንን ታቦት እናስገባ ብለው ሲያስቡ ቶራ የምትባል እንስሳ ጭነት ተጭና ከመካከላቸው ተገኘች፤ ጭነቱን አውርደው ቢያዩት በሐር ጨርቅ የተጠቀለለ ሁለት ታቦት አገኙ አንዱ የእስጢፋኖስ አንዱ የጊዮርጊስ " ይህንን ታቦት በእየሩሳሌም የሚኖሩ የተሰወሩ ቅዱሳን ከእግዚያብሔር ታዘው የላኩት ነው" የሚል ጽሑፍም አገኙ ይላል። 

ይህ ከሆነ ከ 400 ዘመን በኃላ ነው አባ እየሱስ ሞኣ ወደዚህ ቦታ የመጡት ለ 52 ዓመት ቀን ቀን መንፈሳዊ ስራቸውን ይሰራሉ ሌሊት ሌሊት ሐይቁ ውስጥ ቆመው ሲጸልዩ ያድራሉ፤ በእንዲህ ያለ ፍጹም ተጋድሎ ኖረው ህዳር 26 በዛሬዋ ቀን አርፈዋል፤ በነገራችን ላይ ተክልዬን ያመነኮሱ አባት ናቸው። እንደዚህ ነው የመነኮሳት አባት እንጦንስ ነው እንጦንስ መቃርስን ወለደ መቃርስ ጳኩሚስን ፤ ጳኩሚስ አቡነ አረጋዊን አቡነ አረጋዊ አባ ዮሐኒን ፤ አባ ዮሐኒ የሐይቁን አባ እየሱስ ሞአን ወለዱ፤  አባ እየሱስ ሞኣ ደግሞ ተክልዬን ወለዱ። በዚህ ገዳም የሚከበሩ በዓላት መስከረም 15 የእስጢፋኖስ ፍልሰተ አጽሙ፤ ህዳር 26 የአባታችን እረፍት እንዲሁም ጥር 1 የእስጢፋኖስ እረፍቱ ናቸው፤ በእውነቱ የሚገርም ገዳም ነው ፤ ገነት እንጂ ምድር አይመስልም። ቦታውን ለማየት ያብቃን የጻድቁ በረከትንም ያሳትፈን።
------------------------------------ 
ቅዱስ መርቆሪዎስ
( by Wubishet Tekle ) ህዳር 25 ቀን ቅዱስ መርቆሪዎስ በሰማዕትነት አረፈ፤ አገሩ ሮም ነው፤ በወጣትነቱ ከሃዲው ንጉስ ኡልያኖስ ላቆመው ጣኦት አልሰግድም ብሎ የሰው ልጅ ሊሸከመው የማይችለውን መከራ ተቀበለ፤በመጨረሻም ህዳር 25  ቀን አንገቱን ቆርጠው ገደሉት ደም ውኃና ወተት ከአንገቱ ፈሰሰ። ይህ ሰማዕት በአገራችን በስሙ በርካታ ገዳማትና አብያተክርስቲያናት አሉት በተለይም ቅዱስ ላሊበላ ካነጻቸው 11 ውቅር አብያተክርስቲያናት አንዱን ቤተ መርቆሪዎስ ብሎ ሰይሞለታል፤ በዚህ በሰሜን ሸዋ ደግሞ የሚገርም ገዳም አለው፤ ካህናት በማህሌት ወረብ ሲያቀርቡ ስዕሉ ያሸበሽባል ይዘላል፤ ይህንንም አይቶ ማረጋገጥ ይቻላል፤ በመዲናችን አዲስ አበባ ቅዱስ ኡራኤል ቤተክርስቲያን ውስጥ ታቦቱ አለ:: ዛሬ በደማቁ ተከብሮ ይውላል። መርቆሪዎስ ከሞተ በኃላ ፈረሱ ለሰባት ዓመት ወንጌልን አስተምሯል፤ በኃላም አንገቱን ቆርጠው ገድለውታል እንዴት ብሎ የሚገረም የበልአምን አህያ ይጠይቃት፤ እኛስ እስመ አልቦ ነገር ዘይሳኣኖ ለእግዚያብሔር ብለን እንመልሳለን፤ ዘኁልቁ 22፤28 ቅዱስ ጴጥሮስም እንዲህ አለ ቃል የሌለው አህያ በሰው ቃል ተናግሮ የነብዩን እብድነት አገደ ይላል 2ጴጥ 2፤16። ከሰማዕቱ በረከት ያሳትፈን።
------------------------------------
ሐዋርያው ፊሊጶስ 
( by Wubishet Tekle )ህዳር 18  ቀን ከአስራ ሁለቱ ሐዋርያት አንዱ የሆነው ሐዋርያው ፊሊጶስ አረፈ፤ ጥቅምት 14 ቀን መታሰቢያውን የምናከብርለት ኢትዮጰያዊውን ጀንደረባ ያጠመቀውን ዲያቆኑ ፊሊጶስ ነው ። ይህ የዛሬው ግን ቁጥሩ ከ 12ቱ ሐዋርያት ነው ዮሐ 1፤44 በነገው ኢየሱስ ወደ ገሊላ ሊወጣ ወደደ፥ ፊልጶስንም አገኘና። ተከተለኝ አለው።ፊልጶስም ከእንድርያስና ከጴጥሮስ ከተማ ከቤተ ሳይዳ ነበረ ይላል። ሐዋርያት ዓለምን ዞረው ለማስተማር ዕጣ ሲያወጡ ለፊሊጶስ ከወርቅ የተሰራ ኦሞራ የሚያመልኩ ሰዎች ያሉበት አገር ደረሰው ፤ ገድለ ሐዋርያት ላይ አፍራቅያ ይለዋል፡፡ የአገሩን ስም ቱርክ አካባቢ የሚገኝ ነው፤ ወደ ከተማው ገብቶ ወንጌለ መንግስተ ሰማያትን ሰበከ ብዙዎችንም አሳመነ አጠመቃቸው፤ አቆረባቸውም፤ ቤተክርስቲያን ሰራላቸው፤ ካህንና ዲያቆንም ሾመላቸው፤ ነገር ግን ጥቅማቸው የጎደለባቸው የጣኦት ካህናት ከንጉሱ ጋር ነገር ሰርተው አጣሉት፤ አስረው ደበደቡት፤ ሰቅለውም ገደሉት ፤ ይህም የሆነው በዛሬዋ ቀን፤ የሐዋርያው በረከት ይደርብን፤
------------------------------------ 

ታሪክ ያልዘከረው አባት፤ የመናገሻው አባ ኤልያስ
( by Wubishet Tekle ) ህዳር 6 በዚህች ቀን እመቤታችን ከልጇ ጋር 3 ዓመት ከ 6 ወር በስደት ከተንገላታች በኃላ ወደ አገራቸው የተመለሱበት ቀን ነው፤ ከግብጽ ሲመለሱ ጌታችን በእመቤታችን ጀረባ ላይ ሆኖ እነዚያ እውራንን ባበሩ ጣቶቹ ወደ ኢትዮጵያ ይጠቁም ያመለክት ነበር፤ እመቤታችንም ልጄ ሆይ ለምንድነው ጣትህን የምታመለክተው ብትለው "ያቺ የተባረከች አገር ናት እኔን የሚያመልኩ አንቺን የሚማልዱ በፍቅርሽ የነደዱ ቅዱሳን መነኮሳት የሚፈልቁባት አገር፤ ያንቺ ዘመዶች ሰቅለው ይገድሉኛል በዚህች አገር ያሉ ግን ሳይዩኝ ያምኑኛል፤ አስራት በኩራትሽ ትሁን ብሎ ሰጥቷታል፡፡ በኪደተ እግራቸውም ጣና ሐይቅን፤ ዋልድባንና ሌሎችንም ቦታዎች ዞረው እንደባረኩ ድርሳነ ኡራኤልና ተአምረ ማርያም ላይ በስፋት ተጽፏል፡፡ እምቤታችንን ከሐና ማህጸን ፈጥሮ ከፍጥረተ ዓለም ለይቶ ከሁሉ አልቆ የእናት አማላጅ ትሁናችሁ ብሎ የሰጠን እግዚያብሔር ይመስገን። 

ዳግመኛም በዛሬዋ ቀን በኢትዮጰያ ምድር ታላቅ አምድ ወደቀ ይህም የመናገሻው ባህታዊ አባ ኤልያስ ነው፤ በ 400 ዓመት እድሜው ህዳር 6 1874 ዓ/ም አረፈ፤ በአጼ ምኒሊክ ዘመነ መንግስት ማለት ነው፤ የቅርብ ጊዜ ነው፤ ይህ አባት በግራኝ መሐመድ ወረራ ጊዜ የነበረ ነው፤ በዚያን ጊዜ በተለይ ኦሮሞዎች "አያና ውቃቢ" እያሉ በጣም ያከብሩት ነበር፤ ከመናገሻ እንጦጦ ኪዳነምህረት እየተመላለሰ ሱባኤ እየገባ ጸሎት ያደርግ ነበር፤ በዛሬዋ ቀን ይህ አባት ሲሞት በኢትዮጰያ ሰማይ ላይ ከዋክብት ሲበታተኑ ሲራወጡ ታየ የተጉለቱ አባ በላይነህም ይህንን ምልክት አይቶ የአባ ኤልያስን መሞት ተረዱ ወደ መናገሻ ቢመጡ ሞቶ ተቀብሮ አገኙት፤ጎንደር ላይም በተመሳሳይ ከዋክብት ሲበታተኑ እነ አለቃ ወልደ ቂርቆስ በአይኔ አየው ሲሉ መስክረዋል ይላል መርስሄ ሐዘን ''ትዝታዬ ስለራሴ የማስታውሰው" በሚለው መጽሐፋቸው የከተቡልን። የሚግርመው ይህ አባት ከቤተመንግስት ወገን ሲሆን ተድላ ደስታን ንቆ 400 ዓመት በቅድስና በተጋድሎ የኖረ መናገሻንና እንጦጦ ኪደነምህረትን በጸሎቱ የባረከ ይህንን የመሰለ ቅዱስ አለመዘከሩ ታሪኩ አለመጻፉ የታሪክ ጸሐፍት ወዴት አሉ ሊቃውንቱስ ወዴት ተደበቁ ያሰኛል፤ ከእመቤታችንንና ከመናገሻው አባ ኤልያስ በረከት ያሳትፈን። አሜን
------------------------------------
ንጉስ ነአኩቶ ለአብ 
ህዳር 3  ቀን ጻድቁ ንጉስ ነአኩቶ ለአብ አረፈ፤ ይህ ጻድቅ የቅዱስ ላሊበላ የወንድም ልጅ ነው አባቱ ሐርበይ እናቱ መርኬዛ ይባላሉ፤ቅዱስ ነአኩቶ ለአብ ክህነትን ከንግስና ይዘው ኢትዮጰያን ከመሩ አራቱ የዛጌ ነገስታት አንዱ ነው፤ ቤተክርስቲያን ለነዚህ አራት ነገስታት ጽላት ቀርጻላቸው ቤተክርስቲያን አንጻላቸው የቅድስና ስም ሰጥታቸው ታከብራቸዋለች፤ ይምርሃነ ክርስቶስ፤ላሊበላ ነአኩቶ ለአብና ገብረ ማርያም ፤ ቅዱስ ነአኩቶ ለአብ በነገሰበት 40 ዓመት ሙሉ አርብ አርብ ቀን የጌታን ህማም እያሰበ በዘውዱ ፋንታ የእሾህ አክሊል ደፍቶ፤5 ጦር ዙሪያውን ተክሎ እየደማ እያለቀሰ ሲጸልይ ሲሰግድ ይውል ነበር፤ከእለታት በአንዱ ቀን ጌታችን ተገለጸለት እንዲህም አለው  ወዳጄ ነአኩቶ ለአብ እኔ ለዓለም ደሜን ያፈሰስኩት አንድ ቀን ነው፤ አንተ ግን 40 ዓመት ሙሉ ደምህንንና እንባህን ስታፈስ ኖርክ ይበቃሃል አሁን ወደ እኔ ልወስድህ ነው ይለዋል፤ነአኩቶ ለአብም ጌታችንን “ጌታዬ ሆይ እዚህ ቦታ እኔን ብለው የሚመጡ ወገኖቼን ማርልኝ ይለዋል” ጌታም እውነት እልሃለው ቦታህን ባይረግጥ ዝክርህን ባያዘክር እንኳን ዝናህን ሰምቶ ያሰበህን ኃጢያቱ ምን ቢበዛ እምርልሃለው፤ ዳግመኛም እልሃለው 40 ዓመት ሙሉ እንባህን ያፈሰስክባት ይህች ድንጋይ እስከ እለተ ምጽአት እያነባች ትኖራለች ከዚህ ለሚጠጡ ለሚጠመቁ ድህነት ይሁናቸው ብሎታል፤ ዛሬም ድረስ የነአኩቶ ለአብ ቤተክርስቲያኑ ባለበት ከጣራው ስር ጻበሉ እየቆየ ጠብ ጠብ ይላል፤ክረምት ከበጋ እይለይም እንዲያውም በበጋ መጠኑ ይጨምራል ይህ ጸበል እጅግ መድሐኒት ነው፡፡ ቅዱስ ነአኩቶ ለአብ አሸተን ማርያምን አንጾ ከጨረሰ በኃላ ማዕጠንት ይዞ ቤተክርስቲያኑን ሲያጥን ብዙ ቅዱሳን እጣኑን አሽትተው ቤተክርስቲያን ውስጥ ጥቅጥቅ ብለው ቆሙ፤ እናንተ ደግሞ እንዴት መጣችሁ አላቸው እነርሱም እጣኑን አሽትተን መጣን አሉት በዚህም የተነሳ “አሸተን ማርያም ” ተብላለች፤ቅዱስ ነአኩቶ ለአብ በ70 ዓመቱ ህዳር 3 ቀን እንደነ ሄኖክ ተሰውሯል። በረከቱ ይደርብን፡፡ 
ምንጭ የይምርሃነ ክርስቶስና የነአኩቶ ለአብ ገድል
------------------------------------
ሐዋርያው ቅዱስ ማርቆስ 
(By Wubishet Tekle )ጥቅምት 30  ቀን ሐዋርያው ቅዱስ ማርቆስ የተወለደበት ቀን ነው፤ በመዲናችን አዲስ አበባ ጨምሮ በስሙ በታነጹለት አብያተ ክርስቲያናት ታቦተ ህጉ ወጥቶ በደማቁ ተከብሮ ይውላል፤ ሚያዚያ 30 እረፍቱ ነው። ቅዱስ ማርቆስ ቁጥሩ ከ 72ቱ አርድእት ነው፤ የእናቱ ስም ማርያም ይባላል ቁጥሯ ከ 36ቱ ቅዱሳት አንስት ነው፤ በ 50ኛው ቀን መንፈስ ቅዱስ ለሐዋርያት የወረደላቸው በዚህች ቅድስት እናት ቤት ሆነው ሲጸልዩ ነው፤ ሐዋ 2፤1 12፤12 ፤ ይህ ሐዋርያ ወንጌሉን የጻፈው ጌታ ባረገ በ 11ኛ ዓመት በሮማይስጥ ቋንቋ ሮም ላይ ሆኖ ነው፤ ምንም እንኳን ቅዱስ ጴጥሮስንና ቅዱስ ጳውሎስን ተከትሎ በተለያዩ ቦታዎች ወንጌልን ቢሰብክም በዋናነት ግብጽ በመዘዋወር ጣኦታት አፈራርሷል፤ ወልድ ዋህድ ብላ እንድትጸናም አድርጓል፤ ኢትዮጵያም ድረስ መጥቶ ወንጌልን ሰብኳል፤ መንበረ ጰጰስናው ግብጽ እስክንድርያ ነው፤ ኢትዮጵያ በዚህ በማርቆስ መንበር የተሾሙ 111 ጳጳሳትን ከግብጽ ስታስመጣ ኖራለች፤ እስክንድርያ እናቴ ማርቆስ አባቴ የምትለውም ለዚህ ነው፤ ቅዱስ ማርቆስን ሚያዚያ 30 ቀን ጣኦት አምላኪዎች በበሬ አስጎትተው ገድለውታል። ስለ ደብረ ማርቆስ ከተማ ጥቂት ልበል ከአባቶች የሰማሁት ነው፤ በዚህች ከተማ የነበሩት ጳጳስ የቅዱስ ማርቆስን ቤተክርስቲያን ከነጹ በኃላ ታቦተ ህጉን ለማስገባት አገሬው ይሰበሰባል፤ እናም ሽማግሌዎች ተነስተው ጳጳሱን ይመርቃሉ እንዲህ ብለው አባታችን ይህንን ደብር እንደሰሩልን እርሶንም እግዚያብሔር ይደብሮት ብለው መረቁ በዚህን ጊዜ በዙሪያው የነበሩት ጎረምሶች ከት ብለው ሳቁ፤ ግን ምን አሳቃቸው እግዚያብሔር ይደብሮት ማለት እኮ ታላቅ ሰው ያድርጎት ማለታቸው ነው ደብር ማለት ተራራ ማለትም አይደል። ከበዓሉ በረከት ያሳትፈን።
 
------------------------------------
ሙሴ
(By Wubishet Tekle )የነቢያት አለቃ የሆነ የዋህ፤ቅን፤ጻድቅ የሙሴ መታሰቢያው ነው። ከእግዚያብሔር ጋር 570 ቃላትን ተነጋግሯል፤ ከባለሟልነቱ የተነሳ ከዕለታት በአንዱ ቀን እግዚያብሔርን መቼ ነው የምሞተው ብሎ ይጠይቀዋል፤ ዐርብ ቀን ነው ብሎ ይመልስለታ ፡፡ ሙሴም ዐርብ ቀን ሁሌም ራሱን ገንዞ ተዘጋጅቶ ይጠብቃል ሰባት ዓመት አለፈው፤ ከዛ በኃላ ቀኑን ረሳው መዘጋጀቱንም ተወው፤ ነገር ግን ዐርብ ቀን ሁለት መላዕክት በሰው ተመስለው መቃብር ሲቆፍሩ አገኛቸው ምን እየሰራችሁ ነው አላቸው፤ እነሱም ሰው ሞቶብን መቃብር እየቆፈርን ነው አሉት፤ ላግዛችሁ ብሎ ቆፈረላቸው፤ እነሱም የሞተው ሰው አንተን ነው የሚያህለው ውስጥ ግባና ለካልን ይሉታል እርሱም ውስጥ ገብቶ በጀርባው ጋደም አለ፡፡  ጣር ሳይኖርበት ህማም ሳይሰማው በዛው አሸለመ መላእክት አፈር አልብሰውት ያርጋሉ፤የሙሴ መቃብር እሰካሁን የት እንዳለ አይታወቅም፤ ምነዋ ቢባል እስራኤል በጣም ይወዱት ነበርና ስጋውን እንዳያመልኩት ነው። እንደ ሙሴ ደግ የዋህ ቅን የሆነ ነቢይ እንዳልተነሳና እንደማይነሳ መጽሐፍ በእውነት መሰከረ። ፍቅር እንደ ሙሴ ቸርነት እንደ አብርሃም ጥበብን እንደ ሰሎሞን ስጠን አይደል የምንለው። በረከቱን ያድለን
------------------------------------
  አቡነ መብአ ጽዮን
(By Wubishet Tekle)ጥቅምት 27  ቀን ኢትዮጵያዊው ጻድቅ አቡነ መብአ ጽዮን የእረፍት ቀናቸው ነው፤ ትውልዳቸው ሸዋ ትጉለት ውስጥ ነው:: እመቤታችን ያወጣችላቸው ስም ተክለ ማርያም ነው፤እኚህ ጻድቅ በጣም የሚታወቁበት ተጋድሎ አላቸው፤ ይህም አርብ አርብ ቀን የጌታችንን ሞቱን ለማሰብ ትልቅ ድንጋይ በጀርባቸው አዝለው እልፍ እልፍ እየሰገዱ ማታ ላይ ኮሶ ይጠጡ ነበር፤ ሀሞት መጠጣቱን ለማሰብ፤ ከጽድቃቸው ብዛት የተነሳ መቋሚያቸውን ቢተክሉት ሎሚና ትርንጎ አፈርቷል፤ጻደቁ የእረፍት ቀናቸው ሲደርስ ጌታችን ተገልጾ በርካታ ቃለ ኪዳን ገብቶላቸዋል፤ የእረፍታቸውን ቀን በእረፍት ቀኑ አድርጎላቸዋል፤ ዳግመኛ በዛሬዋ ቀን ቤተክርስቲያን የመድሐኒያለምን በዓል በደማቁ ታከብራለች፤ ይህም የለውጥ በዓል ነው፤ ጌታችን መድሐኒታችን እየሱስ ክርስቶስ ደሙን ያፈሰሰው ስጋውን የቆረሰው አንዴ ብቻ ነው እርሱም መጋቢት 27 ቀን፤ ይህ ግን በአብይ ጾም ስለሚውል በአብይ ጾም ሀዘን እንጂ ደስታ ስለሌለ በዓል ማክበርም ስለማይፈቀድ፤ ወደ ጥቅምት 27 ተዛውሮ ደስ ብሎን ከድሆች ጋር እንድናከብረው ቤተክርስቲያ ስርዓት ሰርታለች፤
------------------------------------
አባ ዮሴፍ 
(By Wubishet Tekle)ጥቅምት 23  ቀን የእስክንድርያው ሊቀ ጳጳስ አባ ዮሴፍ አረፈ፤ ይህ አባት ከደጋግ ክርሰቲያኖች ወገን ነው፤ ወላጆቹ በመልካም አስተዳደግ አሳደጉት፤ ዲቁናን ቅስናን ተቀበላ በ20 ዓመቱ መነኮሰ ፤ ገዳመ አስቄጥስ ገብቶ ለ 39 ዓመት በተጋድሎ ኖረ። ከዚህ በኃላ እንዲህ ሆነ 51ኛው የእስክንድርያ ሊቀ ጳጳስ ሲሞት አባቶች ማንን እንሹም ብለው አሰቡ፤ አባ ዮሴፍንም ለመሾም ከእግዚያብሔር ምልክትን አገኙ ወደ ገዳሙ ሄደው ተገናኙት፤ በመልካም መስተንግዶ በበዓቱ አስተናገዳቸው፤ የእስክንድርያ ሊቀ ጳጳስ አድርገን ልንሾምህ ነው አሉት፤ እኔ ኃጢያተኛ ነኝ አይሆንም ይላቸዋል፤ ስንክሳሩ እንደሚለው በግድ አስረው ወደ እስክንድርያ ወሰዱት 52ኛ ሊቀ ጳጳስም አድርገው ሾሙት ይላል፤ የሚገርም ነው ፡፡የዚህ ዘመን ፍጹም ተቃራኒ ማለትም አይደል ባልንጀራን እስር ቤት ከቶ  እኔ ልሾም እኔ ልሾም የምንል ትውልዶች የበቀልንበት ዘመን፤ አባ ዮሴፍ አስረው እንደሾሙት እርሱም በእግዚያብሔርና በሰው ፍቅር ታስሮ ለ19 ዓመት መንጋውን ተግቶ ጠበቀ ድሆችን እረዳ፤ ሀይማኖቱን አጸና በ 78 ዓመቱ ጥቅምት 23  ቀን አረፈ። ከቅዱስ ጊዮርጊስና ከአባ ዮሴፍ በረከት ያሳትፈን።
---------------------------------
አባ ዘካርያስ 
(By Wubishet Tekle)ጥቅምት 13 ቀን ገድለኛው አባ ዘካርያስ የእረፍቱ መታሰቢያ ነው፤ ይሀ አባት በ 7 ዓመቱ ገዳም ገብቶ መነኮሰ፤ መልኩ እጅግ ውብ መልከ መልካም ነበር ፤ ወንድሞቹ መነኮሳት እስከመሰናከል ደርሰውበት ነበር ይላል መጽሐፈ መነኮሳት፤ አጉረመረሙበት ይህንን የመሰለ መልክ ይዞ እንዴት ከእኛ ጋር ይኖራል አሉት፤ አባ ዘካርያስ ይህን ባወቀ ጊዜ ናጥራን ወደሚባል በርሃ ወረደ ልብሱንም አውልቆ የጨው ባህር ውስጥ ይተኛል ሰውነቱ አባበጠ፤ ቆዳው ተመላለጠ፤ ስጋው ተነፋፋ፤ ለረጅም ጊዜ በደዌ ኖረ፤ ጠቋቁሮ ወደ ገዳሙ ይመለሳል ማንም አላወቀውም፤ ነገር ግን በኃላ ላይ እግዚያብሔር ለአባ ኤስድሮስ ስራውን ገለጸለት አባ ኤስድሮስም ለመነኮሳቱ ነገራቸው፤ እነርሱም አባ ዘካርያስን እንዲህ ይሉታል አባታችን ቀድሞ ሰው ሆነህ ወደ ገዳማችን መጣህ ዛሬ ደግሞ እንደ እግዚያብሔር መልአክ ሆነህ መጣህ አሉት፤ የሚገርም ነው፤ ይህ አባት ለ 48 ዓመት በፍጹም ተጋድሎ ኖሮ በ 52 ዓመቱ በዛሬዋ ቀን አረፈ፤ በጾሎቱ የሚገኝ በረከት ከሁላችን ጋር ይኑር።
------------------------------------
አባ ዲሜጥሮስ
(By Wubishet Tekle)ጥቅምት 12  ቀን አባ ዲሜጥሮስ አረፈ፤ይህ አባት ያልተማረ ገበሬ ነበረ ይላል ስንክሳሩ፤ እንዲህም ሆነ በዚያን ወቅት የእስክንድርያ ሊቀ ጳጳስ የነበረው ዩልያኖስ የእረፍቱ ቀን ሲደርስ የታዘዘ መልአክ ተገልጾ ዛሬ የወይን ዘለላ ይዞ የሚመጣ ምዕመን አለ፤ ካንተ በኃላ ሊቀ ጳጳስ የሚሆነው እርሱ ነውና ተቀበለው ይለዋል፤ ዲሜጥሮስ ወደ ተክል ቦታው ሲገባ ያለወቅቱ ያፈራ ወይን ያገኛል በጣም ተገርሞ ይህንንማ ለሊቀ ጳጳሱ ነው የምሰጠው ብሎ ይዞ ይሄዳል፤ አባ ዩልያኖስ መልአኩ የነገረውን ተረዳ እንደተባለውም አደረገ፤ አባ ዲሜጥሮስ ከሹመቱ በኃላ በመንፈስ ቅዱስ ተቃኝቶ በርካታ መጽሀፍትን ደረሰ ከነዚህም ዋንኛው የአጽዋማትንና የበዓላትን ቀን የሚደነግገው ባህረ ሐሳብ የተሰኘው ግሩም መጽሀፍ አንዱ ነው። የሚገርመው ይህ አባት ከብቃቱ የተነሳ የሰዎችን ኃጢያት ያይ ነበር፡፡ ሊቆርቡ ሲመጡ አንተ አልበቃህም ንስሀ ግባ ፤ አንተ በቅተሃል እያለ ያቆርብ ነበር፤ በዚህም ገሚሶቹ ጠሉት ፤ እርሱ ደግሞ ማነውና ጳጳስ ድንግል መሆን ሲገባው ሚስት አግብቶ እየኖረ የአባቶቻችንን ወንበር አረከሰ ብለውም አሙት፤ በዚህም የታዘዘ መልአክ ተገልጾ እራስህን ግለጽላቸው ይለዋል፤ እንደተባለውም ህዝቡ የደመራ እንጨት ይዞ እንዲመጣና ያመጣውን እንጨት እንዲነድ ያደርጋል፤ በሚነድ እሳት ውስጥም ገብቶ ለረጅም ጊዜ ይቆማል ሚስቱንም ይጠራታል ፡ እርሷም እሳት ውስጥ ትገባለች ፍሙን እያነሳ ይሰጣታል በቀሚሷ ትቀበለዋለች፤ የአገሬው ህዝብ ይህንን አይቶ እጹብ እጹብ አለ፡፡ ምስጉን እግዚአብሔርንም አመሰገነ። ከእሳቱ ወጥቶ እንዲህ ይላቸዋል እኔ ይህን ያደረኩት ውዳሴ ከንቱ ሽቼ አይደለም በሐሜት እንዳትጎዱ ብዬ እንጂ ይህቺ የአጎቴ ልጅ ነች ከተጋባን 48 ዓመታችን ነው ፡፡ አንድ አልጋ ላይ እንተኛለን በግብረ ስጋ አንተዋወቅም ሁለታችንም ድንግል ነን አላቸው፤ ህዝቡ ተንበርክኮ ይቅርታ ጠይቆታል፡፡ አባ ዲሜጥሮስ ሸምግሎ ሳለ ህዝቡ በአልጋ ተሸክሞት ቤተክርስቲያን እየወሰደው እስኪመሽ አልጋ ላይ ተኝቶ ያስተምር ነበር፤ በንጽህና በቅድስና ኖሮ በ 107 ዓመቱ ጥቅምት 12 ቀን አርፏል። ዳግመኛ በዛሬዋ ቀን ወንጌልን የጻፈልን ሐዋርያው ማቴዎስ የእረፍት ቀኑ ነው፤ይህ ሐዋርያ ኢትዮጰያ መጥቶ ወንጌልን እንደሰበከ በርካታ መጽሐፍት ላይ ተጠቅሶ ይገኛል፤ የመልአክት አለቃ ቅዱስ ሚካኤልም ዳዊትን ቀብቶ እንዲያነግሰው ወደ ሳሙኤል የተላከበት ቀን ነው፡፡ የመልአኩንም የቅዱሳኑን በረከት ያድለን፡፡   
----------------------------------------------
አቡነ ጰንጠሌዎን 
(By Wubishet Tekle)ጥቅምት 6  ቀን ከዘጠኙ ቅዱሳን አንዱ የሆኑት አቡነ ጰንጠሌዎን አረፉ፤ እኚህ ጻድቅ ልክ እንደነ አቡነ አረጋዊ ከሮም ከነገስታት ወገን ናቸው መንግስታቸውን ክብራቸውን ትተው ወደ ኢትዮጰያ መጡ ለጥቂት ጊዜ ዘጠኙም አብረው ኖሩ ከዚያ በኃላ ለየብቻ መኖር ይሻለናል ብለው ሁሉም ተበታተኑ አቡነ አረጋዊ ወደ ደብረ ዳሞ አቡነ ገሪማ ወደ መደራ ሌሎችም በየአቅጣጫው ሄዱ እኚህ አቡነ ጰንጠሌዎን ደግሞ አክሱም አቅራቢያ ተራራ ላይ ወጥተው የራሳቸውን ገዳም አበጁ ርዝመቱ 5 አግድመቱ 2 ስፋቱ 3 ክንድ ነው በር የለውም ቀዳዳ እንጂ በዚህ ገዳም ውስጥ ሳይቀመጡ ሳይተኙ ያለመብልና መጠጥ ቆዳቸው ከአጥንታቸው እስኪጣበቅ 45 ዓመት በተጋድሎ ኖረዋል፤ ብዙ በሽተኞች ወደ እርሳቸው እየመጡ ይፈወሱ ነበር። አጼ ካሌብ በየመን ናግራን ክርስቲያኖችን ነጻ ለማውጣት ሲዘምቱ እኚህ አባት ጋር መጥተው ተባርከው ዘመቱ ድል አድርገው ሲመለሱም መንግስቴን አልፈልግም ብለው በእኚሁ አባት እጅ ነው የመነኮሱት። አቡነ ጰንጠሌዎን የእረፍት ቀናቸው ሲደርስ ጌታችን ተገልጦ በርካታ ቃል ኪዳን ገብቶላቸዋል ጥቅምት 6 ቀንም አርፈዋል፤ ዛሬ ገዳማቸው የበረከት ቦታ ብቻ ሳይሆን የቱሪስትም መስህብ ነው።  ከጻድቁ በረከት ያሳትፈን
-----------------------------------------------------------------------
አባ አትናስዮስ
(by Wubishet Tekle)በጥቅምት 9 ዕለት አባ አትናስዮስ አረፈ፤ይህ አባት በልጅነቱ መነኮሰ በገዳም በተጋድሎም ኖረ፤ አባቶች ቅድስናውን ባዩ ጊዜ ከየአህጉረ ስብከታቸው ተሰባሰቡ የአንጸኪያ ሊቀ ጳጳስ አድርገውም ሾሙት፤ነገር ግን የሰልቅ አህጉረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ በዚህ ጉባዬ አልተገኘም ነበር፤ እኔ ባልተገኘሁበት እንዴት ይሾማል ብሎ ተቆጣ እንዲህም አለ በቅዳሴ ጊዜ የአባ አትናስዮስን ስም የሚጠራ መስቀሉንም የሚሳለም የተወገዘ ይሁን አለ፤ አባ አትናስዮስ ይህን በሰማ ጊዜ የጵጵስናውን ልብስ አወለቀ አሮጌ እራፊ ልብስ ለብሶ ራሱን ለውጦ ወደ አወገዘው ጳጳስ በእግሩ ሄደ ዘበኛውን አስፈቅዶ ይገባል፤ ምን ትፈልጋለህ ይለዋል አባቴ እኔ ደሃ ነኝ እንዲያስጠጉኝ ነው ይላል፤ዲያቆን ነህ ቄስ ይለዋል ሁለቱንም አይደለሁም ይለዋል፤ ከመነኮሳቱ ጋር እንዲኖር ፈቀደለት፤ አባ አትናስዮስ ራሱን ዝቅ አድርጎ ማገልገል ጀመረ የከብቶችን አዛባ ይጠርጋል፤ካባድ ስራዎችን ሁሉ ይሰራል መነኮሳቱን ሁሉ በትህትና ይታዘዛቸዋል፤ ይህንን አይቶ ጳጳሱ ዲቁና ሊሾመው አሰበ አባ አትናስዮ ግን አይሆንም አለ ግድ ባለው ጊዜ ግን አባቴ ድቁናስ አለኝ አለው፤ከ 7 ወር በኃላ ቅስና ሊሾመው አሰበ አባ እትናስዮ አሁንም አይሆንም አለው ግድ ባለው ጊዜ ግን አይ አባቴ ቅስናስ አለኝ አለው፤ከረጅም ጊዜ በኃላ አስተዋይነቱን የአንደበቱን ጣዕም የተደራረበ አገልግሎቱን አይተው ጵጵስና ሊሾሙት ይሰበሰባሉ በዚህ ጊዜ አትናስዮስ አይሆንም ብሎ አለቀሰ ግድ ብለው ባስጨነቁት ጊዜ ግን የአንጾኪያ ሊቀ ጳጳስ እንደሆነ ገለጠላቸው አመጣጡንም ነገራቸው፤ በዚህ ጊዜ ጳጳሱ ደነገጠ አክሊሉን አውልቁ አመድ ነሰነሰ የበቅሎዎችን ጉድፍ ሲጠርግ የነበረው ሊቀጳጳሱ ነበር ወዮልኝ ወዮታ አለቢኝ አለ፤ወድቆ ይቅርታም ጠየቀው፤ ከዚህ በኃላ በታላቅ አጀብ ወደ አንጾኪያ መለሱት፤ አባ አትናስዮስ መንጋውን በፍቅር እየጠበቀ በተጋድሎ ኖሮ ጥቅምት 9 ቀን ወደ ወደደው አምላኩ ሄደ፤በረከቱ ይደርብን፤የእርሱን ትህትና ለእኛም ያድለን፤ ስንክሳር
-----------------------------------------------------------------------
አባ ህርያቆስ
(By Wubishet Tekle)ጥቅምት 2  ቀን ደገኛው አባት አባ ህርያቆስ አረፈ። ይህ አባት ትውልዱ ብህንሳ ነው፤አልተማረም ግን በትሩፋት የጸና ደገኛ አባት ነው፤ የገዳሙ አበ ምኔትም ነበር፤ ልክ እንደ ቅዱስ ኤፍሬም የእመቤቴ ምስጋናዋ እንደ ባህር አሸዋ እንደ ሰማይ ኮከብ በዝቶልኝ እንደ ምግብ ተመግቤው እንደ መጠጥ ጠጥቼው እንደ ልብስ ለብሼው በኖርኩኝ እያለ ይመኝ ነበር። በብህንሳ ያሉ አብዛኞቹ መኖኮሳት ይጠሉት ይንቁት ነበር ምነዋ ቢሉ ስርዓት ያጸናባቸው ነበር፤ከዕለታት በአንዱ ቀን በምን እንሻረው ብለው አሰቡ አስበውም አልቀሩም ቀድሰህ አቁርበን አሉት፤እመቤታችንን አደራ እንዳታሳፍሪኝ ብሎ ሊቀድስ ገባ፤ የለመኗትን የማትነሰ እመቤታችን አዲስ እንግዳ ድርሰት ገለጸችለት ጎሳ ልብየ ቃለ ሰናየ ልቦናዬ በጎ ነገርን አወጣ ብሎ ወይእዜኒ ንሰብሖ እስከሚለው ድረሰ ሰተት አድርጎ ተናገረ፤ በዙሪያው ያሉት የሚወዱት መንፈስ ቅዱስ ነው እንጂ እንዲህ ያለ ሚስጢር ከሩቅ ብእሲ አይገኝም አሉ፤ ገሚሶቹ የሚጠሉት ደግሞ አናናቁበት በዚህም ተከራከሩ ጽፈው ደጉሰው ከህሙም ላይ ጣሉት ድውይ ፈወሰ ይልቁንም ሙት አስነስቷል። 14ኛ ቅዳሴ አድርገው ይዘውታል። አባ ህርያቆስ ከአቡነ አረጋዊ ጋር ሆነው በርካታ መጽሐፍትን ይዘው ወደ ኢትዮጰያ እንደመጡ ህዝቡንም እንዳስተማሩ የጥር ድርሳነ ኡራኤል ላይ ተጽፎ ይገኛል፤ በድጋሚ ከቅዱስ ኤፍሬም ጋር እመቤታች አዛቸው አክሱም መጥተው ከቅዱስ ያሬድ ጋር ተገናኝተዋል አንተ ቅዳሴየን አንተ ደግሞ ውዳሴየን ነግራቹት በዜማ ያድርስ ብላቸው እነሱም ነግረውት አድርሶታል፤ አባ ህርያቆስ በንጽህና በቅድስና ኖሮ ጥቅምት በባተ በሁለተኛው ቀን በክብር አረፈ ፤ የዚህ ደገኛ አባት በረከት ይደርብን።
-----------------------------------------------------------------------
አቡነ ተክለሐዋርያት
በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን !!!
አባታችን አቡነ ተክለሐዋርያት ከሌሎች ፃድቃን ለየት የሚያደርጋቸዉ አንድ ዓመት የታመመ ህመምተኛ ሥጋወደሙ ወስዶ (ተቀብሎ ) ከህመሙ የተነሳ አስመለሰዉ ዲያቆኑ ያስመለሰዉን በእቃ ተቀበለዉ ። ደምና መግል የተቀላቀለበት ነበር አባታቺን አቡነ ተክለሐዋርያት ሰለ ስጋወ ደሙ ክብር በእለተ አርብ ሃሞትና ሆምጣጥዉን እንደ አጠጡት የወልድን የመስቀሉን መከራ አስበዉ ፈጣሪአቸዉን ከመዉደዳቸዉ የተነሳ ያንን ያስመለሰውን  ግጥም አደርገዉ ጠጡት በዘያን ጊዜ ጌታችን ወደሳቸዉ መጥቶ ወዳጄ ተክለሐዋርያት ሆይ በሰዉ ፊት እዳከበርከኝ በሰማያዊ መላአክትና በምድራወዊ ፃድቃን ሰማእታት ፊት አከብርሃለሁ ብሎ ጣቱን አንስቶ በጣቱ ፊታቸዉን በባረከዉ ግዜ ፊታቸዉ እንደ ፀሐይ አበራ በፊቱም ላይ ያለዉ የፀሐይ ብረሃን በምድር ላይ ሁሉ ታየ ።

አንድ ዶሮ በሰበት ቀን ከባለቤቱ አምለጦ መጥቶ አስጥለኝ ብሎ ለመናቸዉ አሳቸዉ የዶሮዉን ባለቤት ሰንበት ነዉ አትረደዉ ቢሉት አልሰማ ሰላላቸዉ ያላቸዉን ሸማ (ልብስ ) ሰጥተዉ ከመታረድ አድነዉታል በስእሉ ላይ አንደሜታየዉ ።

ክብር ይግባዉና የኛ አምላክ የቅዱሳንን ሥራ አይተን ሰምተን አንብበን እነሱ የሰሩትን መስራት ባንችል እንኳን ተስፋ እድንቆርጥ አልተወንም ምንም እንኳን እነሱ የተጋደሉትን ተጋድሎ መጋደል ባንችል ደካሞች ብንሆን ይልቁንም እነሱን ብንቀበል በነሱ ስም አንድ ጽዋ ቀዝቃዛ ዉሃ ብንሰጥ የነሱን ዋጋ እደሚሰጠን ቃል ገባልን አንጂ ማቴ ፲ : ፬፩ አቡነ ተክለ ሐዋሪያት መድህን ዓለም ኢየሱስ ክርስቶስ ግንባራቸው ላይ ጸሐይ ያተመባቸው ታላቁ አባት ናቸው ቅድስት ቤተክርስቲያንም ወር በገባ በ27 አስባቸው ትውላለች፡፡የጻድቁ በረከታቸው ይደርብን

ስብሐት ለእግዚአብሔር ኪያነ ዘፈጠረ ከመ ናምልኮ!
ስብሐት ለማርያም እመ አምላክ እግዝእትነ ወመድኃኒትነ!
ስብሐት ለመስቀለ ክርስቶስ ዕፀ መድኃኒት ኃይልነ ወፀወንነ! አሜን!

-----------------------------------------------
የቅድስት አርሴማ ታሪክ በአጭሩ

እናታችን ቅድስት አርሴማ እግዚአብሔርን በቅንነት ያገለግሉ ከነበሩ ከከበሩ ካህናት ወገን ከሆኑ ከቅዱስ ቴዎድሮስና ከእናቷ ቅድስት አትናሲያ በስዕለት ተወለደች፡፡

ሰማዕቷ ቅድስት አርሴማ ብሉይን ሐዲስን ተምራ እያነበበች እንዲሁም በተግባር እየተረጎመች ዘወትርም በጸሎት ትተጋ እንደነበር ገድሏ ይተርካል፡፡ በዚህ ዘመን ድርጣድስ የሚባል በአርመን የነገሠ አረማዊ ንጉሥ ለጣዖት የሚሰግድ' ፀሐይንም የሚያመልክ' ክርስቲያኖችንም እኔ ለማመልከው አምላክ መስገድ አለባችሁ በማለት መከራ ያጸናባቸው ነበር፡፡

እናታችን ቅድስት አርሴማም ተጋድሎዋን የጀመረችው የዚህ ጨካኝ ንጉሥ አገልጋይ ወይም ሹም ፳፯ ክርስቲያኖችን እንደልማዱ እየደበደበ' እየገረፈና ልዩ ልዩ ስቃይ እያደረሰባቸው ሲወስዳቸው በማየቷ ነበር፡፡

ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ‘‘ለእነርሱና ለአሕዛብ ምስክር እንዲሆን ስለኔ ወደገዢዎችና ወደ ነገሥታት ትወሰዳላችሁ፡፡’’ (ማቴ. ፲፡፲፮፡፲፱)፡፡ ያለውን በማሰብ ቅድስት አርሴማም ገና በሃያ ዓመቷ የዚህን ዓለም ንጉሥ እኩይ ግብሩን በመንቀፍ ስለ ክርስቶስ ከሚሰቃዩ ወገኖቿ ጋር ግንባር ቀደም በመሆን ትመሰክር ጀመር፡፡ የንጉሡም አገልጋይ በደም ግባቷና በንግግሯ ማማር ተደንቆ በዚች በፈቃዷ ልትሠዋ በወደደች ሴት ምንም ሊያደርግባት ስላልወደደ ወደ ንጉሡ ወደ ድርጣድስ ከሃያ ሰባቱ ክርስቲያኖች ጋር ወሰዳት፡፡ ንጉሡም ብዙ የተነገረላትን ወጣት ሲያይ በውበቷና በንግግሯ ተማርኮ ለዓለማዊ ደስታውና ፍላጎቱ ተመኛት፡፡ ለእርሱም ሙሽራ እንድትሆን ብዙ ወተወታት፡፡ ቅድስት አርሴማ ግን ናቀችው ‘‘እኔ የሰማያዊው ንጉሥ የክርስቶስ ሙሽራ እንጂ የዚህን ዓለም አላፊ ጠፊ የሆነውን ገንዘብና ደስታ የምሻ አይደለሁም፡፡’’ በማለትም መለሰችለት፡፡

ንጉሡም ይህንን ከእርሷ በመስማቱ እጅግ ተቆጣ፤ በመናቁም ተበሳጨ፤ አሽከሮቹንም ጠርቶ በቤተ መንግሥቱ የታሰሩትን አንበሶች እንዲለቀቅባቸው አዘዘ፡፡ አንበሶቹ ግን ይደሰቱ ነበር፡፡ በኋላም ፊታቸውን ወደ ንጉሡና አገልጋዮቹ በማዞር ሩጠው እስኪደበቁ ድረስ አሳደዷቸው፡፡ ንጉሡ ይበልጥ ነደደው ክርስቲያኖቹ በረሃብ እንዲያልቁ እንዲታሰሩ አዘዘ፡፡ እግዚአብሔርም በአምስተኛው ቀን በብርሃን ቤቱን ሞልቶት የሚበሉትን በመሶብ የሚጠጡትን በጽዋ ከሰማይ አወረደላቸው፡፡ ንጉሡም ይህንን በማየቱ ከዚያ አውጥቶ በእሳት ውስጥም አስገባቸው፡፡ ሠለስቱ ደቂቅን የጠበቀ አምላክ እነርሱንም አዳናቸው፡፡ በሌላም በብዙ መንገድ ሊያጠፋቸው እንደሞከረ ገድሏ ይተርካል፡፡ በመጨረሻም ከአማካሪዎቹ ጋር ተማክሮ በሰይፍ እንዲያልቁ ይወስናሉ፡፡

እያንዳንዳቸውን ተራ በተራ ሲሰይፋቸው ቅድስት አርሴማ ለሚሰየፉት ሁሉ የድል አክሊል ከሰማይ ሲወርድላቸው ትመለከት ስለነበር የእርሷን ተራ በጉጉት ትጠብቀው ነበር፡፡ በመደሰቷም እየጸለየች አይዟችሁ ጽኑ ትላቸው ነበር፡፡

በመጨረሻም ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ጽናቷን ተመልክቶ ቃል ኪዳን ይገባላታል፡፡ ንጉሡም ሌሎቹን አሰይፎ ሲያበቃ ወደሷ ዞሮ በቁጣ እየጮኸ አንቺን እንደ ባልንጀሮችሽ በቀላሉ አልገልሽም ስቃይሽን አጸናብሻለሁ ብሎ ለአገልጋዮቹ ትእዛዝ በመስጠት አይኗን አስወጥቶ በእጇ ያሲዛታል፤ ጡቷን ያስቆርጣል፤ በኋላም አንገቷን አሰይፏታል በዚሁ ሁኔታ እናታችን ሰማዕትነትን ተቀበለች፡፡

ይህንን ሁሉ መከራ ስለአምላኳ ስትል እራሷን አሳልፋ የሰጠች ድንቅ ሰማዕት ናት፡፡ ነቢዩ ዳዊት በመዝሙሩ ‘‘ከመረጥኳቸው ጋር ቃል ኪዳኔን አደረግሁ’’ (መዝ.) እንዳለ ለእናታችንም የገባላት ቃል ኪዳን ‘‘በእኔ ስም አምነሽ የዚህ ዓለም ተድላና ደስታ ሳያታልልሽ አንገትሽን ለሰይፍ ሰጥተሽ ተሰይፈሻል፤ የሰማዕትነት ተጋድሎ ፈጽመሻልና ስምሽን የጠራ፤ በዓልሽን ያከበረ፤ ዝክርሽን የዘከረ፤ ገድልሽን የጻፈና ያጻፈ፤ የሰማና ያሰማም እስከ ፲፪ ትውልድ ድረስ እምርልሻለሁ’’ ሲል ቃል ኪዳን ገብቶላታል፡፡ በዚህም መሠረት በሷ አማላጅነት አምኖ እገዳሟም ሄዶ በጸሎት የተማጸናት ሁሉ ለችግሩ መፍትሄ አግኝቶ እንደሚመለስ እሙን ነው፡፡ የቅድስት አርሴማ ረድኤት በረከት ጸሎትና ምልጃ ከእኛ ጋር ይኑር፡፡ አሜን አሜን አሜን
-----------------------------------------------
አቡነ ተክለሃይማኖት

የአባታችን የአቡነ ተክለሃይማኖት አባት ቅዱስ ፀጋዘአብ በሸዋ ቡልጋ ደብረ ጽላልሽ ቅዱስ ሚካኤል ቤተክርስቲያን አገልጋይ ካህን ነበሩ፡፡ መጋቢት 24 ቀን አባታችን ተክለሃይማኖት ተፀነሱ በታህሣስ 24 ቀን በ1190 ዓ.ም አባታችን ጻድቁ አቡነ ተክለሃይማኖት ከእናታቸው ከቅድስት እግዚሐሪያ እና ከአባታቸው ከቅዱስ ፀጋዘአብ ተወለዱ፡፡ በተወለዱ በ3ኛው ቀን አሐዱ አብ ቅዱስ፣ አሐዱ ወልድ ቅዱስ፣ አሐዱ ውእቱ መንፈስ ቅዱስ ብለው ፈጣሪያቸውን አመሠገኑ፡፡

 በተወለዱ በ40ኛው ቀን ክርስትናን በመነሳት ፍስሐ ጽዮን “የጽዮን ደስታ” ተበለው ተጠሩ፡፡ አባታችን 7 ዓመት እስከሞላቸው ድረስ ከአባታቸው ከፀጋዘአብ ዘንድ እየተማሩ አደጉ፡፡ አባታችን በ15 ዓመታቸው ዲቁናን ከጌርሎስ ዘንድ ተቀበሉ፡፡ አባታችን በ22 ዓመታቸው ከአቡነ ጌርሎስ ዘንድ ቅስናን ተቀበሉ፡፡ በከተታ አውራጃ 3 ዓመት ወንጌልን እያስተማሩ ብዙ ድንቅ ነገርን አደረጉ፡፡ 

አባታችን በዳዊት ፀሎት ከነቢያት ምስጋና ሌሊቱን ሙሉ ይተጉ ነበር በያንዳንዱ መዝሙርም 10፣ 10 ስግደትን ይሰግዱ ነበር፡፡ በሕዳር 24 ቀን ቅዱስ ሚካኤል ወደ ላይ ነጠቃቸው (አወጣቸው) ከ24ቱ ካህናተ ሰማይ ጋር 25ኛ ካህን ሆነው የሥላሴን መንበረን “አሐዱ አብ ቅዱስ አሐዱ ወልድ ቅዱስ አሐዱ ውእቱ መንፈስ ቅዱስ” በማለት አጥነዋል፡፡ በሐይቅ 10 ዓመት በደብረዳሞ 12 ዓመት ኖረዋል፡፡ አባታችን አቡነ ተክለሃይማኖት በ1267 ዓ.ም ደብረ ሊባኖስን በአት አድርገው ኖሩ፡፡ ለ22 ዓመት ቆመው በመፀለይ የአንድ እግራቸው አገዳ ተሠበረ ደቀ መዝሙሮቻቸው በጨርቅ ጠቅልለው ቀበሩት፡፡ በአንድ እግራቸው ለ7 ዓመት በፀሎት ቆሙ በጠቅላላው ለ29 ዓመት በፀሎት ከቆሙ በኋላ በ99 ዓመት ከ10 ወር ከ10 ቀን ነሐሴ 24 ቀን 1290 ዓ.ም አረፉ አባታችን ባረፉ 54 ዓመታቸው በ1354 ዓ.ም ለአባታችን ለአቡነ እዝቅያስ ተገልጸው አጽማቸው ከደብረ አስቦ ወደ ደብረ ሊባኖስ ግንቦት 12 ቀን እንዲፈልስ አድርገዋል፡፡ 
  • ህዳር 24 ቀን 25ተኛ ካህናተ ሰማይ ሆነው በሠማይ የሥላሴን መንበር ያጠኑበት
  • ታህሳስ 24 ቀን የአባታችን ልደት 
  • ጥር 24 ቀን የአባታችን ስባረ አጽም 
  • መጋቢት 24 ቀን የአባታችን ጽንሠት 
  • ግንቦት 12 ቀን የአባታችን ፍልሰተ አጽም 
  • ነሐሴ 24 ቀን የአባታችን እረፍት
የአባታችን ቡራኬ ይድረሰን አሜን!

21 comments:

  1. በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሃዱ አምላክ አሜን
    አቤቱ ይህንን ድንቀ ድንቅ የአባቶቻችን ሥራ እና ገድል ጽፋችሁ ላስነበባችሁን እግዚአብሔር አምላክ ቃለ ሕይወት ያሰማችሁ አቤቱ ከክፉ ይሰውራችሁ አሁን እኔ በተለይ ስለቅድስት አርሴማ ምንም የማውቀው ነገር የለም ነበር በእናንተ በጻድቃን ሰማዕታት ጽሁፍ በቀረበው አንብቤ ብዙ ተረዳሁ እንዲሁም የማላውቀውን አወቅሁ እባካችሁ እንዲህ እንዲህ ያለውን ትምህርት አዘል ቁም ነገር ጻፉበት ቀጥሉበት አሳውቁን ያስተማረ ይማራል የብዙሃኑን ሕይወት ከክፋት ይመልሳል እና እባካችሁ አንድ አድርገን ስለፀብ ትታችሁ ስለክስ ትታችሁ ይህንን አስተምሩን የማናውቀውን አሳውቁን አምላከ እግዚአብሔር ይባርካችሁ የተሰቀለው ንጉሥ ይምራችሁ ልቦናችሁን ይመልሰው እላለሁ

    ወለዕተ ገብርኤል
    ከአዲስ አበባ
    አመሰግናለሁ ስለትምህርቱ

    ReplyDelete
  2. kale hiwot yasemachu !!

    ReplyDelete
  3. በርታ ወንድማችን እጅግ ደስ ይላል

    ReplyDelete
  4. በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሃዱ አምላክ አሜን፡፡
    እጅግ በ