Thursday, July 26, 2018

‹‹ኦርቶዶክስ ሀገር ናት ፤ በጣም ደስ ብሎኛል እንኳን ደስ አላችሁ ›› ጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር አብይ አሕመድ

  • ሀገራችን ካለ እናንተ ጸሎት ውጪ ሰላሟም ልማቷም ሊረጋገጥ አይችልም
  • ዛሬ በኢትዮጵያ ወገኖቻችን ላይ ተገንብቶ የኖረው የመጀመሪያው የጥላቻ ግንብ ዋንኛው ምሰሶ በይፋ ተንዷል


(አንድ አድርገን ሐምሌ 19 2010 ዓ.ም)፡- ጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር አብይ አሕመድ በእርቀ ሰላም ጉባኤ ላይ የተናገሩትን እንዲህ አቅርበነዋል


‹‹በጣም ደስ ብሎኛል እንኳን ደስ አላችሁ ፤ ኢትዮጵያ ከዚች ታላቅ ቤተ ክርስቲያ ውጪ አትታሰብም ፤ እርቁ እንዲመጣ ያስፈለገበት ምክንያት ኦርቶዶክስ ሀገር ስለሆነው ነው ፤ ታላቅ ታሪክ ፣ ዝና እና ክብር ያላት ቤተክርስቲያን ናት ፤ እዚህ ሰላም ሲሆን ሁላችንም ሰላም እንሆናለን ፤ እዚህ ሰላም ሲጠፋ ደግሞ በቀጥታም ይሁን በተዘዋዋሪነት እያንዳንዳችንን ይነካናል ፤ አንድነቷ ከተጠበቀ ሌሎችን መርዳት ትችላለች ፤ የታሪክና የትውፊት ባለቤት የሆነች ቤተ ክርስቲያን ራሷ አንድነቷን በማጣቷ እሷ እያለች ሌሎች እኛን ሲያግዙን ኖረዋል ፤ የእሷ አንድነት ከምስራቅ አፍሪካ አልፎ ለአፍሪካ ትልቅ ዜና ፣ ትልቅ ብስራት እንደሆነ ይሰማኛል ፣ በተግባርም የምናየው ይሄንኑ ነው ፤ በህብረት ውስጥ የሚገኝ ትርፍ ፣ ሥምና ዝና አጥተናል ፤ ኦርቶዶክስ አንድ ሆና ቢሆን ኖሮ የኢትዮጵያ እና የኤርትራ ጉዳይ እርቀ ሰላም እስከ አሁን ባልዘገየ ነበር፡፡ ኢትዮጵያ ውስጥ ሰው ከራሱ እንዲጣላ ፣ ከጎረቤትና ከሃይማኖቱ እንዲጣላ ፤ የሃይማኖት አባቶችን እንዳያከብር ፤ ሲገሰጽ እንዳይመከር ያደረገው አንዱ ነገር በዚች ታላቅ እና ቅድስት ቤተክርስቲያ ያጋጠመው ጸብ ነበር ማለት ይቻላል፡፡ እኛ አንድ ስንሆን ለክርስትና እምነት ብቻ ሳይሆን ለእስልምናና ኢትዮጵያ ውስጥ ላሉ ዜጎች በሙሉ ክብር ፣ አንድነትና ሰላም የሆነ ዜና መስማት እጅጉን የሚያስደስት ነገር ስለሆነ ዛሬ ለኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን ምዕመናት ብቻ ሳይሆን የኢትዮጵያ ሙስሊሞችም እንኳን ደስ አላችሁ ማለት እፈልጋለሁ፡፡

Saturday, July 21, 2018

እርቀ ሰላም( አንድ አድርገን  ሐምሌ 15 ፤ 2010 ዓ.ም ) መጽሐፍ ቅዱስ እንዲህ ይላል “ለሰው ሁሉ ከሚሆነው በቀር ምንም ፈተና አልደረሰባችሁም ፤ ነገር ግን  ከሚቻላችሁ መጠን ይልቅ ትፈተኑ ዘንድ የማይፈቅድ እግዚአብሔር የታመነ ነው ። ትታገሡም ዘንድ እንድትችሉ ከፈተናው ጋር መውጫውን ደግሞ ያደርግላችኋል።” 

የፍቅር እጦት እንጂ ሰውም በወንድሙ ላይ በክፋትና በአመፅ አይነሳምና ቃየል አቤልን በምቀኝነትና በጥላቻ ተነሳስቶ እንደገደለው ሁሉ ዛሬም ብዙ ቃየላውያን በወንድሞቻቸው ላይ በትዕቢት እና በእብሪት ተነሳስተው የሚሞት ስጋቸውን ለመግደል ያሴራሉ። መግደል ለእነርሱ እጅግ የቀለለ ተግባር ነው፤ ቀድመው ህሊናቸውን ገድለዋልና። ማሳት ለእነርሱ እጅግ የቀለለ ተግባር ነው፤ ቀድሞ ህሊናቸውን ስተዋልና። ነገር ግን ዛሬም አሁንም በዚች ቅጽበትም በንስሃ ለተመለሰ ሁሉ ምህረት አለ። ከጥፋት መንገድ ዘወር ላለ መዳን ይሆንለታል። ነገር ግን እንደቀደመው ጊዜ በክፋትና በተንኮል ለመመላለስ ልቡን ያደነደነ፣ ፍቅርን የገፋ፣ ምህረትን የናቀ፣ ለወገኖቹ መጥፊያ ያሴረ፣ ጥላቻን ያነገበ እርቅን የጠላ ሰው ወይም ቡድን የኋላ ኋላ በታላቅ አወዳደቅ መንኮታኮቱ አይቀርም።