Sunday, August 24, 2014

‹‹በያዛችሁትን ስልጣን ቤተክርስትያንን ከውድቀት ልታነሱበት ይገባችኋል ፤ ይህ ሳይሆን ከድጡ ወደ ማጡ የምትወስዷት ከሆነ ከታሪክ ተወቃሽነት አትተርፉም›› አለቃ አያሌው ታምሩ


አንድ አድርገን ነሐሴ 17 ፤ 2004 ዓ.ም 
፡- 
ቀኑ ህዳር 6 1985 ዓ.ም ነበር ፡፡ በአዲስ አበባ ከተማ ሰሜን አቅጣጫ በምትገኝው በመንበረ መንግስት ቁስቋም ቤተክርስትያን ብዙ ህዝበ ክርስትያን ተሰብስቧል ፡፡ ምክንያቱ በዓለ ቁስቋምንና የጾመ ጽጌን ፍቺ በዓል ለማክበር ነበረ ፡፡ የዕለቱም አስተማሪ አለቃ አያሌው ታምሩ ነበሩ፡፡ አለቃ ‹‹በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሀዱ አምላክ አሜን›› ብለው ጀመሩ፡፡ በትምህርታቸውም ስለ እመቤታችን ስደት ፤ ስለ ቁስቋም ታሪክ ፤ ወደ እየሩሳሌም ስለ መመለሷ ፤ ከእመቤታችን 300 ዓመት በኋላ በግብጽ ስለተሰራው የመታሰቢያ ቤተክርስትያን ፤ በዚህ በዓል ምክንያት ኢትዮጵያውያን ነገስታትና ንግስታት ስላደረጓቸው መንፈሳዊ ተሳትፎዎች ፤ ስመ ጥሩዋ ኢትዮጵያዊት ንግስት እቴጌ ምትዋብ በጎንደር ስላሰሯት የደብረ ቁስቋም ቤተክርስትያን  ፤ ስለ ጾመ ጽጌ ፤ ስለ ማህሌተ ጽጌ በዝርዝር አስተማሩ፡፡ ከዚያም በመቀጠል ፤ በእመቤታችን በቅድስት ማርያምና በልጇ ስደት በረከትን ካገኙ የኢትዮጵያ አውራጃዎች አንዱ የሆነው ምድረ ትግራይ ከሌሎች ቅዱሳን የኢትዮጵያ መካናት ጋር የተጣመረ የታሪክ ተዛምዶ ያለው ከመሆኑ ባሻገር ከታቦተ ጽዮን ጀምሮ ለኢትዮጵያ ለተሰጡ ልዩ ልዩ ስጋዊ እና መንፈሳዊ በረከቶች ምንጭና ቦይ ሆኖ የኖረ ነው ፡፡ ዋልድባ ገዳምም ይህን መንፈሳዊ በረከት ከሚገኝባቸው ቦታዎች አንዱ ነው ፤  በአሁኑ ወቅት ህዝቡ የተሰጠውን  ስጋዊ ስልጣን አገሪቱንና ቤተክርስትያንን ከውድቀት ለማንሳት ሊሰራበት ይገባል፡፡ ይህ ሳይሆን ቀርቶ ህዝብና እግዚአብሔርን የሚያሳዝን ስራ ቢሰራ ግን ትዝብትና የታሪክ ተወቃሽነትን ያተርፋል ፤ ያለው ሰፊት ትምህርት ሰጥተዋል ፡፡(የአለቃ አያሌው ታምሩ የመንፈቅ መታሰቢያ ገጽ 26)

Thursday, August 21, 2014

‹‹ከዚህ በኋላ ያሉት ዘመናት ሰው ትንሳኤ ልቡና የሚነሳባቸው ማንም ሳያስተምረው ከመንፈስ ቅዱስ የተማረና ፈጣሪውን ያወቀ የሚሆንባቸው ናቸው፡፡›› መምህር ተስፋዬ ሸዋዬ


(አንድ አድርገን ነሐሴ 16 2006 ዓ.ም)
በኦሪት ዘፍጥረት እንደተጻፈው በድርሳነ ጽዮንም እንደተተረጎመው ብርሃን ከመፈጠሩና ማታና ጠዋት ፤ ቀንና ሌሊት ከመለየቱ አስቀድሞ ሰማይና ምድር ሳይለያዩ በአንድ ሁነው በጨለማ ይኖሩ እንደነበር ምድርም በውኃ ተሸፍና በላይዋ ላይ የእግዚአብሔር መንፈሰ ይሰፍን እንደነበር ተብራርቷል፡፡ ከዚያ በኋላ እግዚአብሔር ብርሃን ይሁን ባለ ጊዜ ማታና ጠዋት ፤ ቀንና ሌሊት ሆነ ሰማይና ምድርም እንዲለያዩ በባለቤቱ ቃል ታዘዙ ተለያዩም፡፡ ከመላእክት በዓለሙ ካለውም ሥነፍጥረት በኋላ የሥነ ፍጥረት ፍጻሜ አዳምና ሔዋን ተፈጠሩ፡፡ ግዙፍ ሥጋና ረቂቅ ነፍስ ያላቸውም እንዲሆኑ እግዚአብሔር የሕይወትን መንፈስ እፍ አለባቸው፡፡ ልብ ንባብ እስትንፋስ ያላት ነፍስ ተሰጠቻቸው፡፡ በዚህም በተፈጠረው ፍጥረት ሁሉ ገዥነት ተሰጣቸው፡፡

Saturday, August 2, 2014

''ትናንትን ያሻገረን እግዚአብሔር ዛሬንም ያሳልፈናል''

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን ለሀገራችን ስልጣኔ በር ከፋች ሆና የኖረች ከመሆንዋም በላይ ዛሬ ላለው የዘመናዊ ስልጣኔም መሠረት የጣለች ባለውለታ ናት፡፡ ቀደምት የቤተ ክርስቲያን አበው ደከመን ሰለቸን ሳይሉ ዕረፍ ዘመን እስከገታቸው ድረስ ሲያገለግሉ ኖረው ቤተ ክርስቲያኒቱ አሁን ከምትገኝበት የዕድገት ደረጃ አድርሰዋታል፡፡
በዚህ ዘመንም የሚገኙ የቤተ ክርስቲያኒቱ ልጆች ሁሉ ይህን አስበው የተማሩትን ሃይማኖትና ሥርዓት ጠብቀውና አስጠብቀው ለሚመጣው ትውልድ ለማቆየት ኃላፊነት ያለባቸው መሆኑ ግልጽ ነው፡፡ በእርግጥ ይህንን ሥርዓተ ቤተ ክርስቲያን የማስጠበቅ ሂደት በውስጥም ሆነ በውጭ ሆነው ለማደናቀፍ ሌት ተቀን የሚዳክሩ ጠላቶች መኖራቸው እሙን ነው፡፡