የሀገራችን ሕገ መንግሥት መሠረታዊ መርኾች ከሚባሉት መካከል አንዱ አንቀጽ ፲፩ ነው፡፡ መሠረታዊ መርሕ ማለት ሕገ መንግሥቱ ራሱን ያዋቀረበት አስኳል ፍሬ ነገር ማለት ነው፡፡ በዚህ አንቀጽ ላይ ሕገ መንግሥቱ የሃይማኖት እና የመንግሥትን መለያየት በተመለከተ የደነገገ ሲኾን በተለይም አንቀጹ ከያዛቸው ሦስት ንዑሳን አናቅጽ መካከል የመጀመሪያው እና ሦስተኛው እንዲህ ይነበበባሉ፡፡
- መንግሥት እና ሃይማኖት የተለያዩ ናቸው፡፡
- መንግሥት በሃይማኖት ጉዳይ ጣልቃ አይገባም፡፡ ሃይማኖትም በመንግሥት ጉዳይ ጣልቃ አይገባም፡፡
የመጀመሪያው ንዑስ አንቀጽ እንደሚያመለክተው መንግሥት ሃይማኖታዊ ቁመና ተላብሶ ወይም ሃይማኖት መንግሥታዊ ቁመና ተላብሶ የሚገኝበት ወይም የሚመሠረትበት አመክንዮ እንደሌለ ያሳያል፡፡ ስለኾነም እነዚህ ሁለት አካለት ተጠባብቀው እና ተናብበው እንዲሄዱ የሚያደርግ ሁኔታ እንዲመቻች ሕገ መንግሥቱ የሰጠው መፍትሔ የለም፡፡ ተገነዛዝበው መሥራት የሚኖርባቸው እጅግ በርካታ የጋራ አጀንዳዎች በመካከላቸው እንደሚኖሩ ስለሚገመት ነው፡፡ ለምሳሌ አንድ ሃይማኖታዊ ቅርስ እንዴት ሊተዳደር ይችላል? የሚለውን ብናነሣ የሁለቱን መገነዛዘብ ግድ የሚል ኾኖ እናገኘዋለን፡፡ በአንድ አቅጣጫ ያ ቅርስ የሀገር ሀብት ነውና መንግሥት ያገባኛል ሊል ሲችል በሌላ በኩል ደግሞ የእምነት ተቋሙ ያፈራው ወይም ያካበተው ቅርስ በመኾኑ ይህኛውም ያገባኛል የማለት መብት አለው፡፡