- ቤተ ክርስቲያኑ እንዲፈርስ የተደረገው ለሶስተኛ ጊዜ ነው፡፡ ከዚህ በፊት ቀበሌው ቤተክርስቲያኑን አፍርሶ ታቦታቱን በግብረ ሃይል(በኢ-አማንያን) እንዲነሱ ካደረገ በኋላ በቀበሌ መጋዘን ውስጥ እንዲቀመጡ አድርጓል፡፡
- የቅዱስ ሩፋኤል ፤ የበአታ ለማርያም ፤ የቅዱስ ገብርኤል እና ኤዎስጣጢዎስ ታቦታት በሚያሳዝን ሁኔታ ከነ መንበራቸው ሜዳ ላይ ተጥለዋል፡፡
- ‹‹ቀበሌው በራሱ ፍቃድ ነው ቤተክርስቲያኑን ያፈረሰው›› የቤተክርስቲያኑ አስተዳዳሪ
(ከቆንጆ መጽሄት)፡-ቦሌ ሰሚት ኮንዶሚኒየምና በአካባው የሚገኙ የኦርቶዶክስት ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን እምነት ተከታዮች
እንዲገለገሉበት የተተከለው የቦሌ ለሚ ቅዱስ ሩፋኤል ወአውስጣጢዎስ
ቤተ ክርስቲያን ከተተከለበት ከ2001 ዓ.ም ጀምሮ የአካባቢው ማኅበረ ካህናትና ምዕመናኑ ሃይማኖታዊ ስርዓትና መንፈሳዊ አገልግሎት
እያገኙ ስርዓተ አምልኮትን በነጻነት እያከናወኑ ባሉበት ሰዓት ባልታወቀና ባልተጠበቀ ሁኔታ ቅድመ ማስጠንቀቂያ ሳይሰጥበት የወረዳ
11 ስራ አስፈጻሚ በቀን 09/08/05 ዓ.ም በተጻፈ ደብዳቤ ማስጠንቀቂያ ከሰጠ በኋላ በነጋታው እንዲፈርስ ተደረገ፡፡
የቦሌ ክፍለ ከተማ ወረዳ 11 ስራ አስፈጻሚ የሆኑት ወ/ሮ ኤልሳቤጥ መንግስቱ ለብጹዕ አቡነ ዳንኤል በቀን
09/08/05 በቁጥር በቦ/ክ/ከ/ወ 11/001/22/15 በጻፉት ደብዳቤ ላይ ‹‹በወረዳ 11 ቦሌ ለሚ ኢንደስትሪ ዞን በተተከለ መንግሥት ካሳ በከፈለበት
ቦታ ላይ ቅዱስ ሩፋኤል ቤተክርስቲያን በሕገወጥ መገንባቱ ይታወቃል ፡፡ ይህ ቤተ ክርስቲያን ለኢንደስትሪ ልማቱ በአሁኑ ሰዓት ትልቅ
እንቅፋት በመሆኑ ከዚህ በፊት ለቤተክርስቲያን እና ለሃይማኖቱ ክብር በመስጠት በተደጋጋሚ ቤተ ክርስቲያኑን እንዲያሱ ስንጠይቅ መቆየታችን ይታወቃል፡፡ ይሁንና እሰከ ዛሬ ድረስ ቤተ
ክርስቲያኑን ለማንሳት ፈቃደኛ አልሆኑም፡፡ በዚህ መሰረት ቅዱስ ሲኖዶስ በ09/08/2005 ዓ.ም በግብረ ሃይል የምናነሳ መሆኑን አውቆ
በቤተክርስቲያኑ ውስጥ ያለውን ጽላት እና ንዋየ ቅድሳት እንዲያነሱልን ለቤተክርስቲያኑ አስተዳደርም መመሪያ እንዲሰጡልን
በጥብቅ እናሳስባለን›› ይላል፡፡