በታደሰ ወርቁ ተጻፈ
- ዛሬ ሊቃውንቱ የቤተክርስቲያኗ መቁሰል አልታይ ብሏችዋልና ቤተክርስቲያን አለቃ አያሌውን ከሙታን መንደር ትጣራለች፡፡
(አንድ አድርገን ግንቦት 23 2006 ዓ.ም)፡- በዚህ ዐውድ(Context)ምሁር የምለውን ከቤተ ክርስቲያኒቱ የአብነት
ትምህርት ቤቶች ሊቅነታቸውን ያስመሰከሩ ፤ ከመንፈሳዊ ኮሌጆች የተመረቁ እንዲሁም በቤተ ክርስቲያኒቱ ዙሪያ ጥናትና ምርምር አድርገው
የጥናት ወረቀቶቻቸውን ያበረከቱ ፤ መጻሕፍትን ያሳተሙትን ጭምር ነው፡፡ በጥቅሉ በቤተ ክርስቲያኒቱ በአዕምሮ ሥራ ላይ የተሰማሩትን
ነው፡፡
በዚህ መልኩ ያስቀመጥናቸው ሊቃውንት ቁጥር በአንጻራዊነት እያደገ ቢሄድም በቤተ ክርስቲያኒቱ እና በምእመኑ ውስጥ ቀድሞ
የነበራቸው ቦታና የኑሮ ደረጃ በማሽቆልቆል ላይ ይገኛል፡፡ አንዳንዶቹም ሊቃውንት በቤተ ክርስቲያኒቱ አገልግሎታቸውን እየሰጡ ቢሆኑም በአሁን ጊዜ በቤተ ክርስቲያኒቱ ውስጥ እንደሚታየው የቀድሞውን የመንፈስ ልዕልና
እና ሐሳባዊ መሪነት አጥተዋል፡፡ ለመኖር የሚያስፈልጋቸውን ከማድረግ በተረፈ ምሁር የሚያሰኛቸውን ተግባር የሚፈጽ አሉ ብሎ ለመናገር
አያስደፍርም፡፡