Monday, May 19, 2014

አቡነ ማትያስ ለቅዱስ ሲኖዶስ ያቀረቡት ተግሳጽ ፤ ምክር፤ አቤቱታና ጩህት



  •  ‹‹የእግዚአብሔር ባለ አደራ መሆን ቀላል ስላይደለ እያንዳንዳችን በእግዚአብሔር ፤ በታሪክና በሃይማኖት በምንመራቸው ምዕመናን ዘንድ በኃላፊነት እንጠየቃለን፡፡››
  • ‹‹ፓትርያርኩ በተቃራኒ መንገድ በመጓዝ ምን አይነት ጥቅምና የኅሊና ደስታ እንደሚሰጣቸው በፍጹም ሊገባን አልቻለም፡፡ ›› አቡነ ማትያስ ለአቡነ ጳውሎስ
  • ቆቡ እንደው አንድ ጊዜ ከተሰቀለ በኋላ በቀላሉ የሚወርድ ወይም የሚሻሻል አይደለም፡፡ “ታሞ ከመማቀቅ አስቀድሞ መጠንቀቅ” (የጳጳሳትን ሹመትን በተመለከት ለቅዱስ ሲኖዶስ ያሳሰቡት)
  • በስመ ሲኖዶስ  የሚጠቀሙት ባለስልጣኖች ሲኖዶሱን ባያሰድቡ መልካም ነው፡፡

(አንድ አድርገን ግንቦት 12 2006 ዓ.ም)፡-  በአሁኑ ሰዓት ስድስተኛ ፓትርያርክ አድርጋ ቤተክርስቲያን የሾመቻቸው አባት ከአመታት በፊት የሰሜን አሜሪካ ሊቀ ጳጳስ ሆነው ማገልገላቸው ይታወቃል፡፡ ከ14 ዓመት በፊት በርካታ አስተዳደራዊ ግድፈቶችን ተመልክተው ማለፍ ያልቻሉት አቡነ ማትያት ለቅዱስ ሲኖዶስ የሚደርስ 20 ገጽ ደብዳቤዎችን ከበርካታ አባሪ ማስረጃ ደብዳቤዎች ጋር ለወቅቱ የቅዱስ ሲኖዶሱ ዋና ጸሀፊ ለብጹዕ አቡነ ኒቆዲሞስ ጥቅምት 12 1992 ዓ.ም አድርገው ልከው ነበር፡፡ ይህ የተላከው ሰነድ ቅዱስ ሲኖዶስ ተነጋግሮበት ውሳኔ እንዲሰጥበት መሆኑን አቡነ ማትያስ በመልዕክታቸው ይገልጻሉ ፡፡ ነገር ግን ከቅዱስ ሲኖዶስ ጽ/ቤት ያገኙት መልስ ቢኖር አልደረሰንም የሚል ነበር፡፡ ይህ በሴራ ለቅዱስ ሲኖዶስ ጉባኤ እንዳይቀርብ የተደረገው ደብዳቤ የግል ጋዜጦች እንዲያወጡትን በቀድሞ ፓትርያርኩ እና በዙሪያቸው ያሉ ሰዎች  እያደረጉት ያለውን ነገር ህዝቡ እንዲያውቅ ለማድረግ በአስቸኳይ የፖስታ አገልግሎት በወቅቱ ህትመት ላይ ለነበረው “ኢትኦጵ” መጽሄት ዋና አዘጋጅ ለአቶ ተስፋዬ ተገኝ ከተላከው ሰነድ እና በጊዜው ለህትመት ከበቃው ጋዜጣ ላይ መለስ ብለን ምን አይነት ስሞታዎችንና ቅሬታዎችን ለቅዱ ሲኖዶስ እንዳቀረቡ ለማየት እንሞክራለን፡፡

     
በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን
ለኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን ቅዱስ ሲኖዶስ
አዲስ አበባ ፤ ኢትዮጵያ

“ወይእዜኒ ዕቀቡ ርዕሰክሙ ወኩሉ መራዕየ ዘሎቱ ሤመክሙ መንፈስ ቅዱስ ጳጳሳተ ከመትርዐዩ ቤተክርስቲያኑ ለክርስቶስ እንተ አጥርያ በደሙ፡፡” ዮሐንስ 20፤28
ይህ ጽሁፍ በቤተክርስቲያናችን የበላይ ባለስልጣኖች በኩል በየጊዜው የሚደርሱብንን የአስተዳደር ፈለግና ሥነ ሥርዓት ያልተከተሉ የካህናት ጥሪዎችንና ልዩ ልዩ አግባብ የሌላቸው የአስተዳደር ጣልቃ ገብነትን የሚመለከት ሆኖ ይህን በተመለከተ ሰፋ ያለ መግለጫ እና ማስረጃዎችን ይዘዋል፡፡

በቅድሚያ ቅዱስ ሲኖዶሳችን ኃይል መንፈሳዊና የመንፈስ ቅዱስ መሪነት እንዳይለየው እግዚአብሔር ለኦርቶዶክሳዊት ተዋህዶ ሃይማኖታችን ጽንአትንና ብርታትን እንዲሰጣት የርቱዓነ ሃይማኖት አባቶቻችን ጸሎትና ረድኤትም እንዳይለየን የዘወትር ጸሎታችን መሆኑን እንገልጻለን፡፡ይህ ማመልከቻ ለቅዱስ ሲኖዶስ ምልዓተ ጉባኤ ቀርቦ እንዲታይና ከፍተኛ ትኩረት እንዲሰጥበት በታላቅ ትህትና አጥብቀን እናሳስባለን፡፡

ካለፉት በርካታ ዓመታት ጀምሮ በነበሩብን ችግሮች ላይ ችግርን እየጨመሩብን የቆዩትና አሁንም በመቀጠል ላይ የሚገኙት ሕግንና ስርዓትን  ያልተከተሉ አሰራሮች በቀጥታም ይሁን በተዘዋዋሪ ወደ ግለሰቦች የሚተላለፉ የቃል ፤ የቴሌፎን ጥሪዎችና የጽሁፍ ትዕዛዞች ሁሉ እንዲቆሙ ተደርጎ ከበላይ የሚተላለፉ ትዕዛዞችና ውሳኔዎች በሙሉ የአስተዳደርን ፈለግ ተከትለው በአገረ ስብከቱ አስተዳደር ስር እንዲተላለፉ እንዲደረግልን በአክብሮት እንጠይቃለን፡፡ 

ከነበሩብን ሌሎች ከባድ ውጥረቶች አንጻርና ከዛሬ ነገ ይሻል ይሆናል በሚል ተስፋ በትዕግስት ለአመታት ተሸክመነው ቆየን እንጂ የዚህ አይነቱ አሰራር ዛሬ የተጀመረ ሳይሆን ከ1987 ዓ.ም ጀምሮ እያተራመሰ በአስተዳደራችንና በዕለታዊ ተግባራችን ላይ መሰናክልና ቀውሶችን እያስከተለ ሲያስቸግረንና ሲያስጨንቀን ኑሯል፡፡ በመንፈሳዊነት ፤ በቅንነት በሐቅ በሰላምና በመተማመን  በአንድነት ተሰልፈን  ቤተክርስቲያናችን መንፈሳዊ ፍሬ የምታፈራበትን ሥራ በመስራት በመፋጠን ፈንታ ፤ ፓትርያርኩ በተቃራኒ መንገድ በመጓዝ ምን አይነት ጥቅምና የኅሊና ደስታ እንደሚሰጣቸው በፍጹም ሊገባን አልቻለም፡፡

“በዚህ ባለንበት በአሜሪካ አገር በታሪካችን ታይተው የማይታወቁ የዘርና ፖለቲካ ልዩነቶች በአብያተክርስቲያናት ውስጥ ሰርገው ገብተው የምዕመናንን አዕምሮ እየበጠበጡ እና እየከፋፈሉ ባስከተሉብን ጸዋትወ መከራዎች ምክንያት ወሰንና መለኪያ በሌለው ችግር ተወጥረን እንደምንገኝ እየታወቀ ቤተክርስቲያኒቱ ከእንዲህ አይነት የታሪክ ጠባሳ የምትወጣበት ፈሊጣዊ መንገድ በመቀየስና በመረዳዳት ፈንታ “በዕንቅርት ላይ ጆሮ ደግፍ” እንዲሉ  እጅግ የበጠበጠን ጉዳይ ቢኖር  በትልቁም በትንሹም  ማለትም በጣም አነስተኛ ጥቃቅን  በሆኑ ጉዳዮች  ላይ ሳይቀር ፤ በአገረ ስብከቱ የሥራ ድርሻዎች  ላይ ፓትርያርኩ በሚያደርጉት ጣልቃ ገብነቶችና የቀውስ ስራዎች ናቸው፡፡ ቅዱስ ሲኖዶስን በአጠቃላይ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያንን ወክሎ የሚሰራው የሰሜን አሜሪካ አገረ ስብከቱ ሳያውቃቸው በቅዱስ ሲኖዶስ ስም የሚተላለፉ ትዕዛዞች የሚጻፉት ደብዳቤዎች የሚለወጡት ውሳኔዎችና ፤ ድንገተኛ የቴሌፎን ጥሪዎች ከአሁን በኋላ መቆም ይገባቸዋል፡፡ የአስተዳደር መስመር በመስበር በየጊዜው የተፈጸሙት ቅጥ የለሽ ተግባሮች ዝርዝር መግለጫዎች ከነማስረጃዎቻቸው ከዚህ በታች ይተነተናሉ፡፡” በማለት አቡነ ማትያስ ከአቤቱታቸው  ጋር በየጊዜው የተደረጉ ህገ ወጥ አሰራሮችን የሚያጋልጡ ኮፒ ሰነዶችን ለማስረጃት በማጣበቅ  በአባሪ መልክ አያይዘው ለቅዱስ ሲኖዶስ ልከው ነበር፡፡

ፓትርያርኩ የሚያደርጉትን ሕገወጥ የካህናት ጥሪን በመቃወም ‹‹ጥሪው ለሹመት ከሆነ ይደልዎ ፤ እግዚአብሔር ያስችላቸው እያልን ከመጸለይ ጋር›› ነገር ግን ሀገረ ስብከት ሳያውቅ ፓትርያርኩ ብቻቸውን በመወሰን ካህትን ከቦታ ወደ ቦታ ማዘዋወር ተገቢ እንዳልሆነ  ፓትያርኩ እና በፓትርያርኩ ዙሪያ ያሉ ሰዎች የሚሰሩትን ስራ ክፉኛ በመውቀስ ተቃውሟቸውን ገልጸዋል፡፡

አቡነ ማትያስ ቀጥለውም….
 ‹‹ባለንበት አገር ያሉት ካሕናት በጣም የተወሰኑ ስለሆኑ  አንድ ካህን ለአንድ ቤተክርስቲያን ብቻ እንጂ ትርፍ የሰው ኃይል የለንም፡፡ ይህንንም ችግር ፓትርያርኩ አሳምረው ያውቁታል  ፤ የኖሩበት አገር ነውና፡፡ ስለዚህ አንድ ካህም ለአጭርም ይሁን ለረዥም ጊዜ  ቦታውን ትቶ በሚንቀሳቀስበት ጊዜ ቤተክርስቲያን እንዳይዘጋና ምዕመናን እንዳይበታተኑ አሱን ተክቶ ቤተክርስቲያኗን የሚጠብቅ ካህን አስቀድሞ ማዘጋጀት ስለሚኖርብንና ካህናት ሲጠሩ አገረ ስብከቱ አስቀድሞ ማወቅ ይኖርበታል፡፡›› በማለት አቤቱታቸውን ይቀጥላሉ፡፡

 የተጠሩት አባት የሚያገለግሏቸው ምዕመናን ከእሳቸው በቀር ሌላ ቀድሶ የሚያቆርብ እንደሌለ እየታወቀ  በቅድሚያ መፍትሄ ሳይፈለግ በሚሄዱት ካሕን ሌላ አባት ሳይተኩ ፓትያርኩ በድንገተኛ ጥሪ ነጥቀው ሲወስዱ ለምዕመናኑ ምንም አላሰቡም፡፡ አሜሪካ ከኢትዮጵያ በሺህ ማይሎችን የሚርቅ ክፍለ ዓለም እንደመሆኑ መጠን ማንኛውም ነገር ሁሉ በአጭር ጊዜ ውስጥ ለማከናወን የማይቻል መሆኑ ለማንም ስውር አይደለም፡፡ ስለዚህ እንዲህ አይነቱ ጥሪ በሚደረግበት ጊዜ ለዝግጅት ጊዜን ይጠይቃል፡፡ ያለንበት ቦታ ካህን ለማስመጣት ረዥም ደጅ ጥናት ይጠይቃል፡፡ ይህን ሁሉ አስቀድሞ ማሰብ አስፈላጊ ነበር፡፡

ጥሪው ለኤጲስ ቆጶስነት ሹመት ከሆነም ደግሞ ኤጲስ ቆጶሳት ማለት የቤተክርስቲያኗ የመጨረሻ ወሳኝ አካላት እንደመሆናቸው መጠን ፤ የምርጫ ሁኔታ በዕለታትና በሰዓታት የሚወሰን ሳይሆን ብዙ ወራትና አመታትን የሚወስድ ጥናት ፤ ምርምርና ማተዋልን የሚጠይቅ የቤተክርስቲያኒቱ አብይ ጉዳይ ነው፡፡ ለድንገት ሞት ድረስ እንደተባለ ነገር እንደዚህ በቅጽበት የሚሰራበት ምክንያት ምንድነው? ነገሩ በጣም የሚያስፈራና ለቤተክርስቲያናችንም የሚያሰጋ ጉዳይ ነው፡፡

‹‹……… በውኑ ቤተክርስቲያን የጳጳሳት እጥረት ኖሮባት ነው? ቤተክርስቲያኒቱ አሁን ለተሾሙት ጳጳሳት የጵጵስና ክብራቸውንና ማዕረጋቸውን ጠብቆ የሚንቀሳቀስ የተሟላ በጀት አላት? ወይስ እንዲሁ በባዶ ሜዳ ላይ በመጣል የቤተክርስቲያንን ክብር ለማዋረድ ሆን ተብሎ የሚሰራ ስራ ነው? እንደ እውነቱ ከሆነ ቆቡና መስቀሉ የቤተክርስቲያን አርማዎች እንደመሆናቸው ሌሎች አብያተክርስቲያናት የሚያደርጉትን ሁሉ መንፈሳዊ ክብራቸው መጠበቅ ይኖርበታል፡፡ ከማዕረጉ ጋር አብሮ የሚሄድ መንፈሳዊ  ክብሩን የሚጠብቅበት መሳሪያ ካልተሰጠው በቀር ብጹዕ ፤ ቅዱስ ተብሎ በስም ብቻ ቢከበር ምን ይጠቅማል? ምንስ ትርጉም ይሰጣል? አንድ ወታደር በቂ የሆነ ትጥቅና ስንቅ ሳይሰጠው የጀነራልነት ማዕረግ ብቻ አሸክመው ወደ ጦር ሜዳ ቢልኩት ከጠላት ጋር ተፋልሞ የአገር ዳር ድንበር ማስከበር አይችልም፡፡ (ዝኒ ከማሁ) መንፈሳዊ ወታደርም ከዚህ የተለየ አይለም፡፡ ተከታዩ ምዕመናንም ቢሆን ክብሩ የተጠበቀ  መንፈሳዊ አባት ማየት ይፈልጋል፡፡ “ባለቤቱ ያቀለለውን አሞሌ ባለ ዕዳ አይቀበለውም”  ተብሏል፡፡ ቆቡ እንደው አንድ ጊዜ ከተሰቀለ በኋላ በቀላሉ የሚወርድ ወይም የሚሻሻል አይደለም፡፡ ታሞ ከመማቀቅ አስቀድሞ መጠንቀቅ……›› በማለት ምክር ተክሳጽ አቤቱታቸውን ይቀጥላሉ፡፡

‹‹….. ለዓመታዊ ሲኖዶስ ጉባኤ በፋክስ የሚደረግልን ጥሪም ሁል ጊዜ የመጨረሻዋ ደቂቃ ስትቀር ሲሆን ፤  ጥሪው የግብር ይውጣ መሆኑን ብንረዳውም ሁኔታዎች ስላልተመቻቹና አቅምና ሁኔታ ስለማይፈቅድልን ለጊዜው መሳተፍ አልቻልንም፡፡ ስለዚህ የጥሪው ጊዜ አጠረ ረዘመ በማለት ምን አነታረከን  ? ብለን ሁል ጊዜ በትዝብት እናልፈዋለን፡፡ ከላይ እንደተጠቀሰው እኛ ያለንበት በሰዓትና በተወሰኑ ደቂቃዎች ፈጥኖ የሚደረስበት ቦሌ ወይም እንጦጦ አይደለም ፤ በብዙ ሺህ ማይልስ  ከአገር ርቀን ነው የምንገኝውና ይህ ሁሉ በቅድሚያ መታሰብ ይኖርበታል ነው የምንለው፡፡….››

·        አቡነ ማትያስ ለአንድ ተራ ግለሰብ ሲኖዶሱ የጻፈውን ደብዳቤ ተቃውመው የሰጡት መልስ
ቅዱስ ሲኖዶስ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን ሕግ አውጪና የመጨረሻው አካል እንደመሆኑ መጠን እጅግ በጣም ከፍተኛ ጉዳዮች ካልሆነ በቀር ተራና ዝርዝር ጉዳዮች ውስጥ ገብቶ  ይዘባርቃል ብለን ባናምንም ፤ ‹‹በስመ ሲኖዶስ  የሚጠቀሙት ባለስልጣኖች ሲኖዶሱን ባያሰድቡ መልካም ነው›› ለማለት ያህል ነው፡፡ በቅዱስ ሲኖዶስ አርማና ማህተብ የሚበሩ ደብዳቤዎች እጅግ ከፍተኛ ለሆኑት ጉዳዮች ብቻ መሆን ይገባቸዋል፡፡ አለበለዚያ ግን ነገሩ ሁሉ ጨዋታ መሆኑ ነው፡፡

‹‹ግለሰብና ራሱን የቻለ ነጋዴ ደርሶ መልስ የመጓጓዣ ቲኬት ፤ አዲስ አበባ የሚቆዩበትን ጠቅላላ ወጪ በመሸፈን በሲኖዶስ ስም መክፈል ሃላፊነት የማይሰማውና አስተሳሰብ የጎደለው አሰራር ነው፡፡ ነገሩ እንቆቅልሽ ሆኖብን ነበር ነገር ግን ቆይተን ስንመረምረው ጉዳዩ ከግል ጥቅም ጋር የተያያዘ መሆኑን ማስረጃዎች አመላክተውናል፡፡” በማለት በሲኖዶስ ስም ያለ አግባብ የሚወጡትን ደብዳቤዎች ስርዓት እንዲበጅላቸው በቅዱስ ሲኖዶስ ማሳሰብ ችለው ነበር፡፡

·        ከሃይኖት ውጪ ለሆኑት  ካህናት ከሲኖዶስ የተላለፉ ደብዳቤዎችን በሚመለከት ያቀረቡት አቤቱታ
“በቅዱስ ሲኖዶስ አርማ ደብዳቤ ተጽፈው የቅዱስ ሲኖዶስ ማህተብና የዋና ጸሀፊው ፊርማ አርፎባቸው ተመሳሳይ መልዕክት ይዘው በተመሳሳይ ቀን የተጻፉ አራት ደብዳቤዎች የልዩ ልዩ እምነት  ተከታይ ለሆኑት አራት ቀሳውስት በቀጥታ ሲላክላቸው እኛም በግልባጭ እንድናውቀው ተደርጓል፡፡ ቅዱስ ሲኖዶስ በእነዚህ ደብዳቤዎች አማካኝነት ቀሳውስቱን የሚጠይቀው ቲኔስ ኒውጀርሲ በሚባል ስቴት ላቋቋምነው አዲስ የቅዱስ ሚካኤል ቤተክርስቲያን ምዕመናን መጸለያ ቤተ መቅደስ እንዲለግሱን ነው፡፡ ቀሳውስቱ ከኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን ቅዱስ ሲኖዶስ እንዲህ አይነት ደብዳቤ በቀጥታ ሲጻፍላቸው በጣም ሳይገርማቸውና ግራም ሳይገባቸው አልቀረም አንድም መልስ ሳይሰጡበት የቀሩት፡፡  እረ ለመሆኑ የወዴት አገር ቤተክርስቲያን ሲኖዶስ ነው ደረጃውንና ማዕረጉን ዝቅ አድርጎ በትምህርተ ሃይማኖት  በቀኖና ለማይመስሉት ያውም ለተራ ቀሳውስት በቀጥታ ደብዳቤ የሚፅፍ ? ተደርጎ የማይታወቅ ነገር ነው፡፡

እነዚህ ደብዳቤዎች የተጻፉት በማን ጠያቂነት እንደሆነ ባናውቅም ፤ ያመለከተ ግለሰብም ካለ ሀገረ ስብከቱ አውቆት ማከናወን የሚገባው ስራ ሆኖ ሳለ ፤ በትንሹም በትልቁም ጉዳዮች ላይ ያውም በሲኖዶስ ስም ጥልቅ እያሉ በመግባት ሀፍረትን መከናነብ ቤተክርስቲያንን ማዋረድ ምን ይጠቅማል? በእንደዚህ አይነት ጉዳዮች ላይ ቅዱስ ሲኖዶስ እንዲያስብበት ይገባል፡፡” በማለት በወቅቱ ሀገረ ስብከቱ ሳያውቀው ቀጥታ ለሌሎች እምነት ተከታዮች ቤተ መቅደስ እንዲለግሱን በማለት የተጻፈውን ደብዳቤ ተቃውመዋል፡፡

 የአቡነ ማትያስ ማጠቃለያ
‹‹……… ይህ ከዚህ በላይ በንኡስ አንቀጾች ተንትነን የቀረበው ስሞታና ዝርዝር መግለጫ ከላይ እንደተገለጸው  ሁሉ ከፓትርያርኩ የሚተላለፉ ቅጥ ያጡ ቅጽበታዊ ትዕዛዞች ፤ ከስነ ስርዓት ውጪ የሆኑ የቴሌፎን ጥሪዎችና ልዩ ልዩ ተጽህኖችን ፤ ለአስተዳደራችን ቀውስና  መሰናክል እየሆኑብን ስለተቸገርን ብንታገሰው በመሻሻል ፋንታ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ በመሄዱ ጉዳዩን ለሲኖዶስ ለማቅረብ ተገደናል፡፡ የቤተክርስቲያኒቱ እውነተኛ መጋቢ (አስተዳዳሪ) እግዚአብሔር ብቻ ቢሆንም ከእሱ በታች ቤተክርስቲያኒቱን እንድንመግብ ኃላፊነቱን ለእኛ ለውሉደ ክህነት ሰጥቷል፡፡ ሊዘነጋ የማይገባው አብይ ነገር የተቀበልነውን ምግብና የጸጋ እንጂ የባሕርይ ስላይደለ የሰጪው የእግዚአብሔር ባለአደራዎች መሆናችንን ነው፡፡ ይህንን በሚገባ ሳንረዳ ስልጣኑን የባሕርይ አድርገነው ከሆነ አጉል ቦታ ላይ ነው የተቀመጥነው ማለት ነው፡፡ ጌታ ቅዱስ ጴጥሮስን “ለዐይኬ አባግዕ” በማለት እየደጋገመ አደራ ያለው ምግብናውን በቀላሉ እንዳያየውና ቸልተኛ ሆኖ አደራውን እንዳይዘነጋ ነው፡፡ስለዚህ የእግዚአብሔር ባለ አደራ መሆን ቀላል ስላይደለ እያንዳንዳችን በእግዚአብሔር በታሪክና በሃይማኖት የምንመራቸው ምዕመናን ዘንድ በኃላፊነት እንጠየቃለን፡፡   የተቀበልነውን ከባድ አደራ በሚገባ ለመወጣት ሰብአዊ ችሎታችንን በምንችለው ሁሉ መሞከር ይኖርብናል፡፡ አባቶቻችንስ በበኩላቸው “አደራ ጥብቅ ሰማይ ቁቅ ነው” ይላሉ፡፡….. ስለዚህ እኛ የአሜሪካ ነዋሪዎች ብቻ ሳንሆን በዚች ቅድስት ቤተክርስቲያን ጥላ ስር የተጠለለ ሁሉ  ካህኑም ፤ ምዕመኑም በያለበት እውነተኛ መጋቢና ምግብና(ፍትሕ ርትዕን) ይጠብቃል፡፡ ይበልጡን ግን በብዙ መከራ ውስጥ ተዘፍቃ የምትገኝው በአሜሪካ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን ሀገረ ስብከት ሲኖዶሳዊ ፍትሕ ርትዕን ትጠብቃለች፡፡ ……….. ›› በማለት ከ20 ገጽ ያላነሰ ምክር ፤ ተግሳጽ ፤ አቤቱታ እና ጩህታቸውን እንዲህ በማለት አጠቃለዋል፡፡
“ወአምላክ ሰላም ይቀጥቅጦ ለሰይጣን በታሕተ እግሪክሙ ፍጡነ ጸጋሁ ለእግዚእነ ኢየሱስ ክርስቶስ የሃሉ ምስሌክሙ” አሜን (ሮሜ 16፤20)  


  የአንድ አድርገን ሃሳብ
አቡነ ማቲያስ ቤተክህነቱን ፤ ቅዱስ ሲኖዶሱንና ቅዱስ ፓትርያርኩ በጊዜው ያከናወኗቸውን ሕገ-ወጥነት መቃወም በመቻላቸው የሚያስመሰግናቸው ተግባር ነው፡፡ ማንኛውም ምዕመን በቤተክርስቲያኒቱ ውስጥ የሚካሄዱ ኢ-ሃይማኖታዊም ሆነ ብልሹ አስተዳደሮችን ተመልክቶ ዝም ብሎ ማለፍ እንደሌለበት አስተምረውናል ፡፡ ዛሬ በቀላሉ ስህተቱን ነግረን ማስተካከል የምንችላቸው ነገሮችን ነገ ችግሮቹን ለመፍታት የማይቻሉበት እጅግ ውስብስብ የሆነ ደረጃ ላይ ሊደርሱ እንደሚችሉም ማሰብ መቻል አለብን፡፡ ከምዕመኑ አንስቶ እስከ ቤተክርስቲያኒቱ የበላይ አስተዳዳሪ ቅዱስ ሲኖዶሱ ጭምር በደረጃ ሁሉም በአቅሙ ሕገ-ወጥነትንና ኢፍትሃዊነትን አጥብቆ የመቃወም ባህሉን ማዳበር ይገባዋል እንላለን ፡፡ ስብሰባ ረግጦ በመውጣት ተቃውሞን ብቻ በመግለጽ እውነታውን ለራስ ደብቆ ማቆየት ምዕመኑ ያሸከሙትን ሃላፊነትን መወጣትን አያመለክትም ፡፡ ሰዎች ጥሩ ሲሰሩ ሊመሰገኑ ፤ ጥሩ ሳይሰሩ ሲቀሩ ደግሞ ስህተታቸውን በመንገር እና ወደ ትክክለኛው መንገድ መመለስ አስተዋይነት ነው፡፡ አቡነ ማትያስ በጊዜው ችግሮቻቸው መፍትሄ ባያገኙም  ለቅዱስ ሲኖዶስ ለማቅረብ እንዲህ አቅርበው ነበር፡፡

መጮህ ፤ ጥያቄና አቤቱታ  ማቅረብ ቀላል ሊሆን ይችል ይሆናል፡፡ አቤቱታዎችን የሚሰማ እና ለጩህቶች መልስ የሚሰጥ አባት ወይም አካል ማግኝት ግን ቀላል አይደለም፡፡ በወቅቱ የአቡነ ማትያስ አቤቱታ ፓትርያርኩ እጅ ገብቶ ‹‹አልደረሰም›› የሚል መልስ ተሰጥቷቸው ነበር፡፡ አሁንም ቢሆን በርካታ ጥያቄዎች በርካታ አቤቱታዎች መልስ ያግኙም አያግኙም ለበላይ አካል በየቀኑ ይነጉዳሉ፡፡ መልስ የሚያገኙት ችግራቸው የሚፈታላቸው ግን ጥቂቶች ሆነው እናገኛቸዋለን፡፡ ቀድሞ ስለ አንድ አገልጋይ ያለ አግባብ ከቦታ ቦታ መዛወር ይቆረቁራቸው የነበሩት አባት ከሦስት ወራት በፊት በማኅበረ ቅዱሳን አስተባባሪነት በየሦስት ዓመቱ የሚካሔደው በመቶዎች የሚቆጠሩ ከበርካታ ገዳማትና ፤ አድባራትና አብያተ ክርስቲያናት ተማሪ ቤታቸውን ዘግተው በመጡ የአብነት መምህራን የምክክር ጉባኤ ከፓትርያርኩ በተሰጠ መመሪያ መሠረት እንዳይካሔድ በእሳቸው ፊርማ የወጣ ደብዳቤ መመልከት ግራ ያጋባል፡፡ ከዚህ በተጨማሪ ‹‹ማኅበረ ቅዱሳን በጥንታዊ የብራና መጻሕፍት አያያዝና አጠባበቅ ላይ የጠራውና በጠቅላይ ቤተ ክህነቱ ጽ/ቤት የተፈቀደው ጥናታዊ ጉባኤ በፓትርያርኩ ውሳኔ ተከለከለ›› የሚል ዜና መስማት ለጆሮም ይከብዳል፡፡ ‹‹እያንዳንዳችን በእግዚአብሔር በታሪክና በሃይማኖት የምንመራቸው ምዕመናን ዘንድ በኃላፊነት እንጠየቃለን›› የሚለው ቃላቸው ከወዴት እንዳለ ማወቅ ከባድ የሆነ ይመስላል፡፡

እንደ እኛ ሃሳብ አቡነ ማትያስ በጊዜው የጻፉትን አቤቱታ ደግመው አሁን ቢያነቡት ለራሳቸውም ጥያቄ አሁን ላይ መልስ ቢሰጡ መልካም ነው እንላለን፡፡ ለምን ቢባል እርሳቸው የጠቀሱት ችግሮች ሁላ አሁንም ላይ በቤተክርስያቱ ያሉ ስለሆኑ ፤ እርሳቸው የችግሮቹ ቁልፍ ቦታ የተቀመጡ አባት በመሆናቸው ለችግሮቻቸው መፍትሄ ነው የሚሉትን መንገድ ቢያመላክቱ ሸክሟ የከበዳት ቤተክርስቲያን ሊቀልላት ይችል ይሆናል፡፡ ‹‹በመንፈሳዊነት ፤ በቅንነት በሐቅ በሰላምና በመተማመን  በአንድነት ተሰልፈን  ቤተክርስቲያናችን መንፈሳዊ ፍሬ የምታፈራበትን ሥራ በመስራት በመፋጠን ፈንታ ፤ ፓትርያርኩ በተቃራኒ መንገድ በመጓዝ ምን አይነት ጥቅምና የኅሊና ደስታ እንደሚሰጣቸው በፍጹም ሊገባን አልቻለም፡፡›› (ከአቡነ ማትያስ አቤቱታ መልዕክት ላይ የተወሰደ)፡፡  እኛም አሁን በእርሳቸው ፊርማ የሚወጡ ደብዳቤዎች እየገቡን አይደሉም፡፡
   
አሁንም ቢሆን በቤተክርስያቱ ባለፉት አስተዳደሮች ጥያቄ ያልተሰጣቸው በርካታ ችግሮች በውስጥም ይሁን በውጭ እንዳሉ ይታወቃል፡፡ ጎጠኝነት ፤ ሙሰኝነት ፤ የሰበካ ጉባኤ እና የምዕመና አለመስማማት ፤ የአንድነት ማጣት  ፤ አስተዳደራዊና ሃይማኖታዊ መልስ የሚያስፈልጋቸው ችግሮች ፤ በአይን የማይታዩ ውስጣዊ አሰራር እንከኖች ፤ የአብነት ትምህርት ቤቶች ደብዛቸው የመጥፋትና የተተኪ ችግር ፤ ገዳሞች በመናንያን የመራቆት ችግር ፤ ተመልካች ያጡ በየገጠሪቱ ክፍል የሚገኙ አብያተክርስቲያናት ላይ አገልጋይ የማጣት ችግርና ሌሎች መሰል ነገሮች ቤተክርስያኒቱን ከውስጥም ከውጭም ወጥረው የያዙበት ጊዜ ላይ እንገኛለን፡፡  እነዚህ ችግሮች አይናቸውን አፍጥጠው እስኪመጡ ድረስ መጠበቅ ሃላፊነት የሚሰማው አካል ተግር መሆን መቻል የለበትም፡፡ ወይም ችግሮቹ በፈጣን መልዕክት ተልከው የፓትርያርኩ ጽ/ቤት መድረስ አለባቸው ብለንም አናምንም ፡፡ የቀድሞውን አስተዳደራዊም ሆነ ሃይማኖታዊ ችግሮችና አቤቱታዎች ለመፍታት ወንበሩ ብቻውን ምንም አይሰራም፡፡ ችግሮቹ እንደ ብዛታቸው የአፈታት ደረጃቸውም ሊለያይ ይገባል፡፡ ከባለፈው አስተዳደር ተንከባለው የመጡ በቀላሉ መፍትሄ የሚሰጣቸው በርካታ ችግሮችና ጊዜ ፤ ገንዘብና የሰው ኃይልን የሚፈልጉ ችግሮችን በመለየት ቀላሎቹን በአፋጣኝ የመፍታት ፤ ከበድ ያሉትን ችግሮቹ ጊዜ ወስዶ ከሊቃውንት መክሮ  የሚፈቱበት መንገድ ቅዱ ሲኖዶሱ መቀየስ አለበት ብለን እናምናለን፡፡  አሁን ያለው አስተዳደር ከባለፈው የሚሻልበትን ነገሮች  በሚታይና በሚዳሰስ መልኩ ሰርቶ ለምዕመኑ ማሳየት መቻል አለበት ብለን እናምናለን፡፡ በቤተክርስያኒቱ የቅዱስ ሲኖዶስ አባላት አባቶች አማካኝነት የሚደረጉ ጉባኤዎች የቤተክርስቲያኒቱን መሰረታዊ ችግሮችን በሚፈቱ መልኩ ፤ ሸክሟን ሊያቀሉ በሚችሉ መልቁ መቃኝት መቻል አለባቸው፡፡
ቸር ሰንብቱ

11 comments:

  1. Betam yegermal Abune Matias bergtem yeminagerut betam yetemtatana ers berasu yemigach kal newu. Ewunet yegel kiberena tekim kelelebet lemin bebetekrestiyan wuset yemiserawun yekenona teset eysemuna bemaserega yetegeleselachewu negerun lemadbesbes yemokeralu. bewunet ye Orthodex hayemanotachin ayenachin eyaye eyetefa selehone hulachinem korten bemenesat meftehe lemagget mesewaetenet mekfel yenorbenal bebetekirestiyan abatocho nen bayoch bebetekerstiyan wuset tenkolana zemut sefesem eyayu zeme mallet yemot mot newu

    ReplyDelete
  2. betam des yilal tiru mereja silesetachhun

    ReplyDelete
  3. ብጹ አባታችን አቡነ ማትያስ እውነተኛና ቀትተኛ መንገድን የሚከተሉ አባት ናቸው። እናንተ ግን የአይሁድ ፈንፈስ ስለተጸናወታችሁ መልካም ነገርን ማየት አትችሉም። በህይወት ያሉትን አባቶች በቁም እየቀበራችሁ አባቶቻችን አባቶቻችን አባቶቻችን ......የምትሉ የዘመናችን አስመሳዮች። ምን ይሻላችሁ ይሆን???? እባካችሁ ንስሓ ግቡ።

    ReplyDelete
    Replies
    1. ANTE TADISO MENAFIK- TEMAMAWU SIRAH YETEFETSEMELEH SILEMESELE NEWU?
      TESASTEHAL; BETEKIRISTIYAN LE ENNENTE AYINETU TELELFA ATTISETIM

      ANTE RASIH NISEHA GIBA

      Delete
  4. Chigru yalew meqemechaw lay yimeslehnal. Ye patriarch'u biro tselot ena tsebel sayasfelgew ayqerm. Aymeslafhihum?

    ReplyDelete
  5. Chigru yalew meqemechachew lay yimeslegnal. Birowachew tsebel ena tselot yasfeligewal.

    ReplyDelete
  6. "Kebro besew eji Yamir siyizut Yadenager" ale Yagerie sew.

    ReplyDelete
  7. Does anyone know the present status of the case of Deacon Begashaw? He was supposed to appear in front of "YeLiqawunt Gubae", and the Synod to determine whether he's in heresy or not. Please let me know.

    ReplyDelete
  8. hulu lebego new melkam abat nachew beagbabu tekula saygebabachew enyazachew. sew silehonu yisasatalu weyim mikniyat yinorachewal metages melkam new .zim malet sigeban zim enibelina sira enisra mastekakeya. sedbo lesedabi anit, kemahiberu garmagachetim melkam new biye alamnin. eski melkamun nigerun kiftetunim bemelkam menged nigerun esachew yeegziabher enderase nachew .miemenum beabatoch lay tiritare endiyadiribet atedirgu. lekiftetoch lela media tetekemu ameseginalehu bertu egziabiher kenante gar yihun. negerochinim lemakilel mokiru!!!

    ReplyDelete
  9. በመሠረቱ በአንድአድርገን የተሰጠው የማጠቃለያ ሀሳብ በጣም በጣም ትክክል ነው ፡፡ አንዳንድ አስተያየት ሰጭዎች ለምን የተጣመመ ሀሳብ አንደሚሰነዝሩ አይገባኝም ፡፡ ብጹእ አባታችን በአንዳንድ ጉዳዮች ላይ አስተላለፉ እተባለ ያለው ውሳኔ መንፈሳዊነት እና ወጥነት የጎደለው እንደሆነ መገመት ይቻላል ፡፡ አብኣኞቹ ሀሳቦች የሶስተኛ ወገን ግፊት እና ጫና እናዳለባቸው አመላካች ነገሮች አሉ ፡፡ እውነትን መሰረት በማድረግ ስለቤተክርስቲያን እና ስለምእምናን ጥቅምና ክብር ተብሎ የሚሰራ ስራ እምብዛም አይታይም፡፡ የቤተክርስቲያኒቱን አሰራር በመከተል ያለምንም አድሎና ልዩነት ቢሰራና ፈሪሀ-እግዚአብሄር ቢኖር መልካም ነው ፡፡ ገዳማትሲደፈሩና ንብረታቸው ሲፈርስ በዝምታ በማለፍ ፣ ለቤተክርተሲያን ከብር ፣ ምእምናንን በወንጌል ለማነጽ እና በእምነት ለማጎልበት የሚተጉ አካላትን አሳልፎ በመስጠት ፣ ብዙ አማንያን በተሀድሶ ሰርጎ ገቦች ሲበረዙ በዝምታ በማለፍ እና እነዚህን አካላት ከላለ በመስጠት፣ እና በአጠቃላይ ስለቤተክርስቲያኒቱ ጉዳይ የሌላ ወገንን ጣልቃ ገብነት በመፍቀድ አባቶች ለፈተና እንዲጋለጡና ምእምናኑ እናዳይረጋጋ በር መክፈት ተገቢ አይደለም ፡፡ ሁላችንም የእምነቱ ተከታዮች እየተፈጠረ ባለው ችግርና የቤተክርስቲያን ፈተና መፍተሔ እንዲያገኝ ወደ ፈጣሪ መጸለይና አወቅም የቻለውን ሁሉ እገዛ በማድረግ የበኩላችንን መወጣት ይገባናል ፡፡ እግዚአብሔር ለሁላችንም ቅን፣ አስተዋይና በጎ ህሊና ይስጠን ፡፡ ሁል ጊዜ ስለ ሰላም እናስብ ፡፡ አሜን ፡፡

    ReplyDelete