Monday, June 17, 2013

‹‹ይህ ቤተክርስቲያን ለኢንደስትሪ ልማቱ ትልቅ እንቅፋት ነው›› የቦሌ ክፍለ ከተማ ዋና ስራ አስፈጻሚ



  •  ቤተ ክርስቲያኑ እንዲፈርስ የተደረገው ለሶስተኛ ጊዜ ነው፡፡ ከዚህ በፊት ቀበሌው ቤተክርስቲያኑን አፍርሶ ታቦታቱን በግብረ ሃይል(በኢ-አማንያን) እንዲነሱ ካደረገ በኋላ በቀበሌ መጋዘን ውስጥ እንዲቀመጡ አድርጓል፡፡
  •  የቅዱስ ሩፋኤል ፤ የበአታ ለማርያም ፤ የቅዱስ ገብርኤል እና ኤዎስጣጢዎስ ታቦታት በሚያሳዝን ሁኔታ ከነ መንበራቸው ሜዳ ላይ ተጥለዋል፡፡
  • ‹‹ቀበሌው በራሱ ፍቃድ ነው ቤተክርስቲያኑን ያፈረሰው›› የቤተክርስቲያኑ አስተዳዳሪ

(ከቆንጆ መጽሄት)፡-ቦሌ ሰሚት ኮንዶሚኒየምና በአካባው የሚገኙ የኦርቶዶክስት ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን እምነት ተከታዮች እንዲገለገሉበት የተተከለው  የቦሌ ለሚ ቅዱስ ሩፋኤል ወአውስጣጢዎስ ቤተ ክርስቲያን ከተተከለበት ከ2001 ዓ.ም ጀምሮ የአካባቢው ማኅበረ ካህናትና ምዕመናኑ ሃይማኖታዊ ስርዓትና መንፈሳዊ አገልግሎት እያገኙ ስርዓተ አምልኮትን በነጻነት እያከናወኑ ባሉበት ሰዓት ባልታወቀና ባልተጠበቀ ሁኔታ ቅድመ ማስጠንቀቂያ ሳይሰጥበት የወረዳ 11 ስራ አስፈጻሚ በቀን 09/08/05 ዓ.ም በተጻፈ ደብዳቤ ማስጠንቀቂያ ከሰጠ በኋላ በነጋታው እንዲፈርስ ተደረገ፡፡

የቦሌ ክፍለ ከተማ ወረዳ 11 ስራ አስፈጻሚ የሆኑት ወ/ሮ ኤልሳቤጥ መንግስቱ ለብጹዕ አቡነ ዳንኤል በቀን 09/08/05 በቁጥር በቦ/ክ/ከ/ወ 11/001/22/15 በጻፉት ደብዳቤ ላይ ‹‹በወረዳ 11 ቦሌ ለሚ ኢንደስትሪ ዞን በተተከለ መንግሥት ካሳ በከፈለበት ቦታ ላይ ቅዱስ ሩፋኤል ቤተክርስቲያን በሕገወጥ መገንባቱ ይታወቃል ፡፡ ይህ ቤተ ክርስቲያን ለኢንደስትሪ ልማቱ በአሁኑ ሰዓት ትልቅ እንቅፋት በመሆኑ ከዚህ በፊት ለቤተክርስቲያን እና ለሃይማኖቱ ክብር በመስጠት በተደጋጋሚ ቤተ ክርስቲያኑን  እንዲያሱ ስንጠይቅ መቆየታችን ይታወቃል፡፡ ይሁንና እሰከ ዛሬ ድረስ ቤተ ክርስቲያኑን ለማንሳት ፈቃደኛ አልሆኑም፡፡ በዚህ መሰረት ቅዱስ ሲኖዶስ በ09/08/2005 ዓ.ም በግብረ ሃይል የምናነሳ  መሆኑን አውቆ  በቤተክርስቲያኑ ውስጥ ያለውን ጽላት እና ንዋየ ቅድሳት እንዲያነሱልን ለቤተክርስቲያኑ አስተዳደርም መመሪያ እንዲሰጡልን በጥብቅ እናሳስባለን›› ይላል፡፡

ይህ በእንዲህ እያለ ማስጠንቀቂያ በደረሳቸው በተመሳሳይ ቀን ቤተ ክርስቲያኑ በአፍራሽ ግብረ ሃይል እንዲፈርስ መደረጉን የቤተክርስቲያኗ ጠባቂ ለዝግጅት ክፍላችን የፈረሰውን ቤተክርስቲያን ለመመልከት በሄደበት ወቅት ተናግረዋል፡፡

ለቤተክርስቲያኑ ጠባቂ መሬቱን አስመልክቶ ላቀረበላቸው ጥያቄ ምላሻቸው ‹‹ የግለሰብ መሬት ነው ፤ በመሬት በኩል ጭቅጭቅ የለም ፡፡ የመሬት ይዞታ ማረጋገጫ አለን ፤ አቶ ቦኬ እና አቶ ገመቹ ከእርሻ መሬታቸው ላይ 1000 ካሬ ሜትር በመስጠታቸው ቤተ ክርስቲያኑ እንዲሰራ ተደረገ፡፡›› ያሉን ሲሆን በውሉ መሰረትም የመሬት ርክክብ ውሉ 2001 ዓ.ም የተደረገ ሲሆን ፤ በውል ሰጪዎች አቶ ገመቹ ወርዶፋ እና አቶ ቦኩ ገመቹ ለስጦታ ተቀባይ ለተከስተ ካሳሁን (በኋላም የቦሌ ለሚ ቅዱስ ሩፋኤልና ጻድቁ አቡነ አውጣጢዮስ ቤተክርስቲያን አስተዳዳሪ) በተዋዋሉት መሰረት በአዲስ አበባና በቦሌ ክፍለ ከተማ  ቀበሌ 16/18/21/22 ክልል ውስጥ የሚገኝውን 1000 (አንድ ሺህ ካሬ ሜትር) ቦታ ለቅዱስ ሩፋኤል ቤተ ክርስቲያን መገልገያ የሰጡ ሲሆን መሬቱ የራሳቸው መሆኑን ገልጸው ‹‹ይህን መገልገያ ቦታ በእዳ ይዥዋለሁ አይሰጥብኝም  ባይ ተከራካሪ ወገን ቢመጣ በራሳችን ወጪ ተከራክረን የምንመልስ ሲሆን ይህን የስጦታ ውል ከመዋዋላችን በፊት ከመዋዋላችን  በፊት የተጠቀሰውን ቦታ በተመለከተ የመንግሥት ግብርንም ሆነ ማኛውንም እዳ ቢኖር ተጠያቂዎች እና ከፋዮች እኛ የስጦታ ውል ሰጪዎች  መሆናችንን በዚህ ውል ግዴታ ገብተናል፡፡ መስጠታችንንም  በፊርማችን እናረጋግጣለን›› ይላል በውል ሰጪ እና በውል ተቀባይ መካከል የተገባው ውል፡፡ 

አቶ ቡኬ ገመቹ ለስምዓ ጽድቅ ጋዜጣ በሰጡት ቃል ‹‹ቦታው ከአባቴ ጋር የምንጠቀምበት የእርሻ መሬት ነበረ በአካባበቢው ምንም ቤተ ክርስቲያን ሰላልነበረ ከአባታችን ጋር ተመካክረን የቅዱስ ሩፋኤል ቤተክርስቲያን እንዲሰራ መጋቢት 3 ቀን 2001 ዓ.ም ሰጥተናል ቤተ ክርስቲያኑ ከተሰራ ከ6 ወር በኋላ በአዲስ አበባ አስተዳዳር የቦሌ ክፍለ ከተማ ቀበሌ 16/18 ግብረ ሃይል ልኮ አስፈረሰው ፤ ምክንያቱን ‹‹ሲገልጹ ሳታስፈቅዱ በሕገ ወጥ መንገድ የሰራችሁት›› ነው አሉን ፤ ነገር ግን መሬቱን እኛ ስንጠቀመንበት የነበረ ሲሆን ለመንግሥትን ግብርን ስንከፍልበት የነበረ መሬት ነው ፤ በስማችን የሚገኝውን ለቤተ ክርስቲያን መስሪያ ብለን በውል ተፈራርመን ሰጥተናል ብለዋል፡፡

ውል ከተዋዋሉ በኋላ ለቤተክርስቲያኑ አገልግሎት ውሎ በ2001 ዓ.ም ተሰጥቶ የነበረ ቢሆንም ከዚያ በኋላ ቀበሌው በድጋሚ አስፈርሶታል ፤ በ2001 ዓ.ም የቤተክርስቲያኑ መፍረስ አስመልክቶ ብጹእ አቡነ ዳንኤል ለቦሌ ክፍለ ከተማ ወረዳ 11 ጽ./ቤት በጻፉት ደብዳቤ ላይ 

‹‹ የአዲስ አበባ ሃገረ ስብከት ጽ/ቤት ለቦሌ ክፍለ ከተማ ለወረዳ አስዳደር ጽ/ቤት በጻፈው ደብዳቤ መሰረትም በቦሌ ክፍለ ከተማ በቀድሞ ቀበሌ 19/18 አስተዳደር ስር የሚገኝውንና መንፈሳዊ አገልግሎቱን በመስጠት ላይ የነበረውን የቦሌ ለሚ ቅዱስ ሩፋኤል ቤተ ክርስቲያን በወቅቱ የቀበሌው አስተዳደር ጽ/ቤት የነበሩትን ጸሀፊዎች በራሳቸው ሃሳብ ተነሳስተው ሚያዚያ 5 ቀን 2002 ዓ.ም ከቀኑ 3፡30 ሲሆን ቤተክርስቲያኑን በአፍራሽ ግረ ሃይል ቡድን አፍርሰው ከታቦተ ሕጉ ጀምሮ ያለውን ንብረትና ነዋየ ቅድሳትን በሙሉ በጠቅላላ ጣሪያወን ግድግዳውን ሳይቀር በመውሰድ በቀበሌው ጽ/ቤት የተቀመጠ መሆኑን ከቀረበልን ሪፖርት ተረድተናል፡፡  በመሰረቱ አንድ ቤተክርስቲያን ተተክሎ ስርዓተ ቅዳሴው እየተከናወነ ባለበት ቤተክርስቲያኑን በማፍረስ ከታቦተ ሕጉ ጀምሮ ነዋየ ቅድሳቱን ጀምሮ በመውሰድ ቀበሌ ጽ/ቤት እንዲቀመጥ ማድረጉ የእምነት ነጻነት እንደማሳጣት ይቆጠራል፡፡

ስለዚህ አሁን ለወረዳው ጽ/ቤት የምናሳስበው የተፈጸመው ግፍ በመመልከት በቀበሌው ጽ/ቤት ውስጥ እዲቀመጥ የተደረገው ከታቦተ ሕጉ ጀምሮ በአጠቃላይ ንዋዬ ቅድሳቱን በሙሉ እንዲመለስ ተደርጎ በፈረሰው ከታቦተ ሕጉ ጀምሮ  በቦታ ላይ ቤተክርስቲያኑ ተተክሎ የተቋረጠውን መንፈሳዊ አገልግሎቱን እንዲቀጥል ይደረግል ዘንድ በቅድስት ቤተ ክርስቲያናችን ስም የተለመደውን ትብብር በአክብሮት እንጠይቃለን›› ይላል፡፡

‹‹ከዚህ በኋላ ቤተክርስቲያኑ የተሰራ ቢሆንም እንደገና በ09/08/05 ዓ.ም በአፍራሽ ግብረ ሃይል ሊፈርስ ችሏል ፤ ከዚያ በኋላም እንደገና ተሰራ ይህንንም ይህው አፈረሱብን›› ያሉን በወቅቱ በቦታው ስናገኛቸው ከሀዘን ብዛት እስከ አሁን የፋሲካን ጾም እንዳልፈቱ የነገሩን የቤተክርስቲያኑ አስተዳዳሪ መልአከ ብርሃን ተከስተ ካሳሁን ናቸው ፤ አያይዘውም ሕዝቡ ተረባረበ ፤ በጋዜጣም ወጣ መንግስት ራሱ ወስኖ ያፈረሰውን ቤተክህነት ነገሩን ይዛዋለች ከፈረሰ ከአንድ ወር ከ19 ቀን በኋላ ብጹዕ አቡነ ማቲያስ መጥተው ሊጎበኙት መሆኑን ሰምተናለ ፤ በ11/08/05 አጣሪ ኮሚቴ አይቶ ሄዷል፡፡ 

 የቤተክርስቲያኑ ድጋሚ መፍረስ አስመልክቶ ብጹዕ አቡነ ዳንኤል ለቦሌ ክፍለ ከተማ በቀጥር 925/90/05 በቀን 15/08/05 ዓ.ም የጻፉት ደብዳቤ እንዲህ ይላል፡፡

ለ፡- ቦሌ ክፍለ ከተማ ዋና ስራ አስፈጻሚ

ጉዳዩ ፡- ስለ ለሚ ቅዱስ ሩፋኤል ቤተክርስቲያንን መፍረስ ይመለከታል

በቦሌ ሰሚት ኮንዶሚኒየምና በአካባቢው የሚገኝውን የኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያንና ተከታዮች እንዲገለገሉበት የተተከለውን የለሚ ቦሌ ቅዱስ ሩፋኤል ቤተ ክርስቲያንን ከተተከለበት ከ2001 ዓ.ም  ጀምሮ የአካባቢው ማኅበረ ካህናት እና ምዕመኑ ሃይማኖታዊ መብታቸውን ተከብሮ እና ተጠብቆ መንፈሳዊ አገልግሎት እያገኙ ስርዓተ አምልኮት በነጻነት እያከናወኑ ባለበት ሰዓት ባልታወቀና ባልተጠበቀ ሁኔታ ቅድመ ማስጠንቀቂያ ሳይሰጥበት የወረዳ 11 ስራ አስፈጻሚ ቤተክርስቲያኑን እንዲፈርስ 09/08/05 ዓ.ም በተጻፈ ደብዳቤ ማስጠንቀቂያ ከሰጠ በኋላ በዚያው ቀን እንዲፈርስ አድርጎታል፡፡

በእኛ በኩል ጉዳዩን ወደ ቅዱስ ፓትርያርኩ በማቅረብ ለመነጋገር ጊዜ እንዲሰጥ ወረዳው በወከላቸው ሃላፊ አማካኝነት እየተነጋገረ ባለንበት ሰዓት ወዲያውኑ በዚያው ቀን ቤተክርስቲያኑ በአሳዛኘ ሁኔታ እንዲፈርስ በመደረጉ የሕዝበ ክርስቲያኑ መንፈሳዊ ሕይወት በእጅጉ ተጎድቷል ፤ ጽላቱ አና መንበሩ ብቻ በሜዳው ላይ ሲቀር ሌላው ንብረት ወዴት እንደደረሰ አይታወቅም ማኀበረ ካህናቱ እና ምዕመኑ እስከ አሁን ድረስ በፈረሰው ቦታ ላይ በሀዘንና በለቅሶ ላይ ይገኛሉ፡፡

ስለዚህ ክፍለ ከተማው የምንጠይቀው ስለ አጠቃላይ ሁኔታ ቅዱስ ፓትርያርኩ ከክቡር ከንቲባው ጋር ተነጋግረውበት የመጨረሻ እልባት ወይም መፍትሄ እስኪሰጥበት ድረስ የታላቁ ጾምና ጸሎት እና የቅዳሴ ጊዜ እስኪፈጸም ቤተ ክርስቲያኑ በነበረበት ሁኔታ እንዲቆይ ትብብር እንዲደረግላቸው ለወረዳ 11 ስራ አስፈጻሚ ጽ/ቤት ጥብቅ መመሪያ እንዲተላለፍ ይደረግልን ዘንድ በአክብሮት በሕዝበ ክርስትያኑ ስም እንጠይቃለን፡፡

እግዚአብሔር ከሁላችን ጋር ይሁን
የሰሜንና ምስራቅ አህጉረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ

 በ09/08/05 ደብዳቤ ከተሰጣቸው በኋላ የደብሩ አስተዳዳሪ ጉዳዩን ለአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ሊያስረዱ በሄዱበት ሰዓት እየፈረሰ መሆኑን መረጃ ሲደርሳቸው ተመልሰው እንደሄዱ ተናግረዋል፡፡

በአካባቢው የሚገኙ ምዕመናን በስፍራው ባገኝናቸው ወቅት በታላቅ ሃዘንና ለቅሶ ውስጥ የነበሩ ሲሆን የሚመለከተው የመንግስት አካል በሕጉ መሰረት ከማፍረስ የተሻለ አማራጭ መኖር እንደነበረበት ገልጸውልናል፡፡ እኛም በቦታው ተገኝተን ባየነውም መሰረት የቅዱስ ሩፋኤል ፤ የበአታ ለማርያም ፤ የቅዱስ ገብርኤል እና ኤዎስጣጢዎስ ታቦታት በሚያሳዝን ሁኔታ ከነ መንበራቸው ሜዳ ላይ ተጥለው ተመልክተናል ፡፡ ይህንን ጉዳይ አስመልክቶ የቦሌ ክፍለ ከተማ ዋና ስራ አስፈጻሚ የሆኑት ወ/ሮ ኤልሳቤት ለማናገር በተደጋጋሚ ቢሮ ብንሄድ ሳናገኛቸው ቀርተናል፡፡
……
አሁን አሁን ጆሮዎቻችን የአብያተ ክርስቲያናትን መፍረስ ዜና እየተለማመዱ ይገኛሉ ፤ በተለያዩ የልማት ምክንያቶች ፤ በአንድም ይሁን በሌላ መንገድ አብያተ ክርስቲያናት እየተነሱ ይገኛሉ ፤ ይህ አብያተ ክርስቲያናትን የማፍረስ ሁኔታ እና የምዕመኑ ዝምታ በዚሁ የሚቀጥል ከሆኑ ቤተክርስቲያኒቱ ላይ የሚደርሰውን አደጋ የከፋ ያደርገዋል፡፡ ይህ ከመንግሥት ጋር ፤ ከበታች የመንግስት አለቆች ጋር በየጊዜው የሚነሳው የቤተክርስቲያን የቦታ ችግር መፍትሄ ያሻዋል……

እግዚአብሔር ቤተክርስቲያንን ይጠብቅልን

3 comments:

  1. Egziabher yafrsachew!

    ReplyDelete
  2. egz/r ensun yafersachewal lenegeru eyaferasachew neber algebachew bilo new enji

    ReplyDelete
  3. Enzih leboch. Errr tedfernal. Mametse miyasfleg yemslegnale. Egziabher yebtatnachew! Demo lezih yewshet poltica....

    ReplyDelete