Sunday, March 25, 2012

ታሪክን የኋሊት «የደርግ ውድቀት ዋዜማና ሚያዚያ ጊዮርጊስ»


(አንድ አድርገን መጋቢት 17 2004 ዓ.ም )- በአሁኑ ሰዓት በዋልድባ ገዳመ ላይ መንግስትም ሆነ ቤተክህነቱ አንድ አይነተ አቋም ይዘዋል ፧ ስራው ከገዳሙ ጋር የሚያገናኝው ነገር የለም ብለዋል ፡ ከፕሮጀክቱ እስከ ዋልድባ ገዳም ድረስ የስድስት ሰዓት መንገድ ያህል ርቀት አለው ብለውናል ፡ ይህ ማለት አንድ ሰው በሰአት በአማካይ 4 ኪሎ ሜትር መሄድ ይችላል ብለን ብናስብ 24 ኪሎሜትር ያህል ልዩነት አለው ማለት ነው ። ይህ ማለት ከመሀል አዲስ አበባ አቃቂ በሰቃ ድረስ ርቀት አለው ማለት ነው ፡ እንዲህ ቢሆን መልካም ነበር ፡ ድንበሩንም ባይነካው ጥሩ  ነበር ፡ የሆነው ወይም እየሆነ ያለው ነገር ግን የዚህ ተገላቢጦሽ ነገር ነው ፡ ይህ ደግሞ ለቤተክርስትያን መልካም አይደለም ፡ እስኪ የዛሬ 20 ዓመት መንግስትና ቤተክህነት ሁለቱም የተሳሳተ ጎዳና ላይ ሳሉ አለቃ አያሌው ታምሩ በቅዱስ ጊዮርጊስ አውደ ምህረት ላይ ያስተማሩትን ትምህርት እንመልከት

1983 ዓ.ም ደርግ በህዝቡ ላይ ሲሰራ የነበረው ግፍ ሁሉ ዘንግቶ ከመጣበት የውድቀት ጥሪ ለመዳን በከፍተኛ ደረጃ በተፍጨረጨረበት ዓመት ነበር ።። በቀደሙትዓመታት ሙልጭ አድርጎ ሲሰድባቸው የነበሩት ቀደምት የኢትዮጵያ ነገስታት ይልቁንም እነ አጤ ቴዎድሮስን ፡ እነ አጤ ዮሐንስን ፣ አጤ ምንይልክን በተለያዩ የመገናኛ ብዙሀን እያነሳ የህዝቡን ወኔ መቀስቀሻ እና የዘመቻ ማዘጋጃ ዘዴ ብሎ ይዞተ ነበር።። ነጋ ጠባ ስለ እነዚህ ቀደምት ነገስታት ጀብዱና ሀገር ወዳድነት አትንኩኝ ባይነት ብዙ ይባል ነበር።።

ሚያዚያ 23 ቀን 1983 የሰማዕቱ ቅዱስ ጊዮርጊስ በአል በአራዳ ጊዮርጊስ ቤተክርስትያን በሚከበርበት ጊዜ አለቃ አያሌው ታምሩ በቤተክርስትያኑ ተገኝተው እንዲያስተምሩ ተጋብዘው ነበር። እሳቸው ስለ ሰማዕቱ ተጋድሎና በሀይማኗት ስላገኝው የድል አክሊል ዘርዝረው አስተማሩ። ዛሬ በከፍተኛ አዘቅት ውስጥ የወደቀችው አገራችሁን ኢትዮጵያን እና ሀይማኖታችሁን ለመታደግ በሀይማኖት ጸንታችሁ መንፈሳዊ ተጋድሎ አድርጉ ፡ የቴዎድሮስ ነኝ የምንሊክ ነኝ የዮሐንስ ነኝ ማለት ጉራ መንዛት አያዋጣም። እነርሱ በጊዜአቸው መስራት የሚገባቸውን ሰርተው የማይጠፋ ስም ተክለው ሄደዋል። ዛሬም እናንተ የራሳችሁን ግዴታ መወጣት አለባችሁ ፡ ቤተመንግስትና ቤተክህነት ተባብረው የካዱት እግዚአብሔር ፡ በድለውናል ጨቁነውናል ብለው ያንቋሸሿቸውን ነገስታትን ስም ዛሬ የጦርነት ነጋሪት መጎሸሚያ ማድረጋቸው ተገቢ አይደለም ፡ እናንተም እነሱ የሚሏችሁን ተከትላችሁ ራሳችሁንና ሌላውን ወገናችሁን መጨረሻ ወደ ሌለው እልቂት መክተት  የለባችሁም ፡ በአሁኑ ሰዓት ከግራ ከቀኝ የሚጎሰመው የጦር ነጋሪት አገራችንንም ራሳችንንም ወደ ማያባራ ተጨማሪ መከራ የሚያስገባ ነው ።። ንስሀ አልገባችሁም የበደላችሁትን እግዚአብሕርን ይቅርታ አልጠየቃችሁም ፡  ባለፈው 17 ዓመት የተሰራው በደል ከባድ ነው፡ እግዚአብሔር ጨርሶ የለም ተብሎ ተክዷል መንግስት ህዝብም ተባብረው ካዱት ፡መንግስት አሮጌዋ ቤተክርስትያን ትውደም ፡ እግዚአብሔር የሚባል አምላክ የለም ብሎ በካድሬዎቹ አማካኝነት ሰበከ ፡ ብዙ ህዝብም እግዚአብሔርን ክዶ በሶሻሊዝም ጸበል ተጠመቀ። በለውጥ ስም ልጆች ወላጆቻቸውን ፡ ወንድም ወንድሙን ገደል ። እናቶች የልጆቻቸውን እርም በሉ ብዙ እልቂትም በሀገሪቱ በሞላ ተካሄደ ። ቤተክርስትያን በራሷ ካህን ተዋረደች ። ካህናት የፖለቲካ ካድሬዎች፣ የአብዮት ጠባቂዎች ሆነው ሰሩ። በእጃቸው የወገኖቻቸውን ደም አፈሰሱ ። ደም ባፈሰሱበት እጅ ወደ ቤተ መቅደስ ገብተው የወልደ እግዚአብሔርን ስጋው ደሙ አቀረቡበት ። ጳጳሳት መምህራን ሶሺያሊዝምና ክርስትና አንድ ናቸው ፤ ማርክስ እንዲህ አለ ፤ሌኒን እንዲህ አለ ብለው በእግዚአብሔር እና በቤተክርስትያን ላይ አፌዙ ከግፈኞች ጋር በአደባባይ በየፖለቲካ ሸንጎ ተሰልፈው የግፍ ድግስ አድናቂዎች ሆኑ ፤ በቤተክህነቱ የስብከተ ወንጌል አዳራሽ ውስጥ በስመ ማርክስ ኤንግልስ ወሌኒን እየተባለ ፌዝ ተነገረበት ። እግዚአብሔር በሆነው ነገር ሁሉ አዘነ ። የህዝቡም የመንግስትም ልብ ባለመመለሱ አሁንም ወደ ተከታይ አዘቅት እየወረድን እንገኛለን። ስለዚህ እዘኑ ፣ ልባችሁን በፍጹም ንስሀ ሀዘን ለእግዚአብሔር ስጡ.. በማለት አስተማሩ

ጊዜውን የደረሳችሁበት ታውቁታላችሁ ፡  ህዝቡም  ቤተክህነቱም ሆነ መንግስት አንድ ላይ በእግዚአብሔር ላይ ያመጹበት ጊዜ ነበር ፡ በዚህም የተነሳ በመላው ኢትዮጵያ ከዚህ በፊት ተከስተው የማያውቁ በርካታ ነገሮች በ100 ዓመት ያልተከሰቱ ነገሮች በ17 ዓመት ተከስተዋል ፡ አሁንም በቤተክርስትያናችን ላይ መንግስት እያደረሰ ያለው ተጽህኖ ከሰዎች ጆሮ የማይገባ እና የማይሰማ አይደለም ፡ ቤተክህነቱም ከመንግስት ጎን መቆሙን በመግለጫቸው አቋማቸውን በይፋ ነግረውናል፡የተሰጠው ጋዜጣዊ መግለጫ  ለዋልድባ ገዳምም ሆነ ለህዝበ ክርስትያን የማይበጅ ነው።የቤተክህነት ሰዎች ከመንግሰት ጋርም ጸብ ውስጥ መግባት የፈለጉ አይመስሉም ፣ እንቢ ብለን ብንቃወምም መንግስት ወደ ኋላ የሚልም መስሎም አልታያቸውም፣ተቃውመን ምንም ለማናመጣው ነገር መቃወም ትርፉ ገብስ ነው ብለው ያሰቡ ይመስላሉ ፣ ነገር ግን በእምነት ያለ ሰው ስለ ቤተክርስትያን ብሎ መቃወም ያለበትን ነገር መንግስትን ሳይፈራ መቃወም መቻል አለበት የሚል እምነት አለን ። አቡነ ሺኖዳ ከ30 ዓመት በፊት የማርቆስ መንበር ላይ ከተቀመጡ በኋላ ከግብጽ መንግስት ጋር ከፍተኛ እሰጣ ገባ ውስጥ ገብተው ነበር ፣ በጊዜው መንግስት እያደረገው ያለውን ነገር በግልጽ ተቃውመዋል ፣ ይህ አካሄዳቸው ያልተመቸው የወቅቱ የግብጽ መሪ አንዋር ሳዳት ከፓትርያርክነት ወንበር አስነስቶ አሁን የተቀበሩበት ገዳም በግዞት እንዲቀመጡ አድርጓቸው ነበር ፣ እሳቸውም ስለ ህዝበ ክርስትያን ብለው ፡ ስለ ቤተክርስትያን እና ስለ ነበራቸው አቋም በደስታ ተቀብለውታል ፡ ይህ የሚያሳየን እውነተኛ እረኝነታቸውን ማንንም ሳይፈሩ እንደተወጡ ነው ። አሁን ግን እኛ ጋር እየተመለከትን ያለነው ከፓትርያርኩ ጀምሮ በሀላፊነት የተቀመጡ ሰዎች መቃወምም ሆነ ድምጻቸውን ማሰማት አለመቻላቸውን ነው ።  እኛ አቅሙ ኖሮን ታግለን ማስቆም ባንችል እንኳን እግዚሐብሔር የበደል ጽዋው እስኪሞላ ጠብቆ እጁን እንደሚሰነዝር እናውቃለን ። አባታችን አለቃ አያሌው ታምሩ በዚያን እሳት ዘመን ፡ ካድሬዋች የሰውን ነፍስ ከዶሮ ነፍስ አሳንሰው በሚመለከቱበት ወቅት ፣አይደለም ሰው ከአንደበቱ ቃል ተናግሮ አስበሀል ተብሎ ተዘቅዝቆ በሚገረፍበት በግፍ በሚገደልበት ሰዓት ፣ በዚያንአስቸጋሪ ወቅት በአውደምህረት ላይ ቆመው ህዝቡ ምን ማድረግ እንዳለበት ማንንም ሳይፈሩ ማንንም ሳያፍሩ ስለ አምላካችን ክብር ብለው ምዕመኑን አስተምረዋል ። አሁን ግን አብረውን ያሉት ዋልድባ ድረስ ሄደው ሁኔታውን አይተው በአብዮታዊ ዲሞክራሲ አይዲዎሎጂ ከተጠመቁ ሰዎች ጋር ድምጻቸውን በመደረብ መንግስትን ፈርተው ለቤተክርስትያን የማይበጃትን የማይጠቅማትን የነገውን ዋልድባ ገዳም አደጋ ላይ የሚጥል ውስኔ አብረው አጨብጭበው ባለ ስድስት ነጥብ የአቋም መግለጫ አውጥተው መጥተው ተመልሰውልናል። እኛም ስለ ቤተክርስትያናችን በጮህን ሌላ ስም ተሰጥቶናል ፡ የእኛ በደል እንጂ የማያንቀላፋ አምላክ እንዳለን እንናውቃለን ።

አባታችን ሲያስተምሩ ዛሬ በከፍተኛ አዘቅት ውስጥ የወደቀችው አገራችሁን ኢትዮጵያን እና ሀይማኖታችሁን ለመታደግ በሀይማኖት ጸንታችሁ መንፈሳዊ ተጋድሎ አድርጉ ብለው ደርግ ሊንበረከክ ኢህአዲግ መንበሩን ሊይዝ ሲል አስተምረዋል፡ ቀጥለውም ቀደምት አባቶቻችን ስራቸውን ሰርተው አልፈዋል አሁን ያለነው ክርስትያኖች ክርስትያናዊ ግዴታችንን መወጣት መቻል አለብንም ብለዋል ፡ ይህ ለዛሬ 20 ዓመት አማኞች ብቻ የተነገረ አይደለም ፡ አሁን ላለነው በጣም የሚስማማ መስሎም ይታየኛል ፡ ፈተናችን ሲከብድ እንጂ ሲቀል ለማየት አልቻልምን፣ ስለዚህ ከእኛ የሚጠበቀው ፈተና ቢበረታብንም ከቤተክርስትያናችን ጎን ሆነን ሀላፊነታችንን መወጣት መቻል አለብን ።

ንስሀ አልገባችሁም የበደላችሁትን እግዚአብሔርን ይቅርታ አልጠየቃችሁም ፡ባለፈው 17 ዓመት የተሰራው በደል ከባድ ነው። በማለት አስተምረዋል ፣ አዎን ይህን ወደ እኛ ዘመን ብናመጣው ባለፉት 20 ዓመታት በቤተክርስትያኒቱ ውስጥ የተሰሩት ስራዎች በደሎች ብናስባቸው ጆሮ የሚያስይዙ ለማየት የሚከብዱ ነገሮች ተከናውነዋል ፣ እግዚአብሔርም ምህረቱ የበዛ አምላክ ስለሆነ ፡ ለቁጣ የማይፈጥን አምላክ ስለሆነ ዝም ብሎ ይማራሉ ይስተካከላሉ ንስሀም ይገባሉ ብሎ አልፎናል ፣የተሰሩትን ነገሮችን ዘርዝሮ መናገር የሚያስፈልግ አይመስለንም ፡ እኛም ንስሀ ገብተን ወደ እግዚአብሔር መመለስ አለመቻላችን ፈተናችንን ከቀን ቀን እያባሰው ይገኛል ። ቀን አልፎ ቀን ሲተካ ደግሞ ዛሬ ምን አዲስ ነገር ተፈጠረ? ብለው የሚጠይቁ ሰዎች እየበዙ ይገኛሉ ፣ የእኛም ጆሮ አንድ በጎ ነገር ፣ አስር ደግሞ መልካም ያልሆኑ ነገሮችን መስማትን ለምደነዋል ፣ ባለፈው ሳምንት በዝቋላ ፣ በአሰቦት እና በዋልድባ ገዳሞች ያሳለፍነውን ጊዜ ምሳሌ ሊሆነን ይገባል። የነገን አናውቅም

ቤተክርስትያን በራሷ ካህን ተዋረደች ። ይህ አሁንም ምናየው ነገር ነው ፣ ጠላቶቻችን ከሩቅ የሚመጡ ሆነው አይደለም ፣ እዚህው አጠገባችን ያሉ ክደው ለማስካድ የተቃረቡ ሰዎች ናቸው ፣ ለዘመናት ታይቶ የማይታወቅ ከስርአተ ቤተክርስታን ውጪ የሆነ ሀውልት ፡ እኛን በመሰሉ ሰዎች ተሰርቶ የቀረበልን ጊዜ ፡ምዕመን በመንፈሳዊ አባቶች ላይ እምነት ያጣበት ፤የቅዱስ ሲኖዶስ ውሳኔ ተፈጻሚ የማይሆንበት ፤ የቅዱስ ሲኖዶስ ልዕልና በአቡነ ጳውሎስ ጋሻ ጃግሬዎች የተገረሰሰበት ፣ ከብጹአን ሊቃነ ጳጳሳት ይልቅ የአንዲት ሴት ድምፅ ጎልቶ የሚሰማበት ፤ ያለ አግባብ የቤተክርስትያኗን የጥምቀት ቦታ ያለ አግባብ የሚሸጥበትና ሌሎች እዚህ ላይ ቢጠቀሱ ቦታ የማይበቃቸው ነገሮች እየተከናወኑ ያሉት ካህን ብላ ባስቀመጠቻቸው ሰዎች አማካኝነት ነው። ስለዚህ ቤተክርስትያን እየተዋረደች ያለችው ከሀገር ውጪ የጦርመሳሪያ ታጥቆ በመጣ ጦር አይደለም ፣ ስለዚህ የአባታችን ምክር በዚህ ዘመን የምንገኝ ምዕመናንም የሚመለከተን ይመስለናል ።

ጊዜው 1976 ዓ.ም የታህሳስ ገብርኤል በዓል በሚከበርበት ወቅት በጥቁር አንበሳ ሆስፒታል አካባቢ የመንግስቱ ኃ/ማርያም ምስል ያለበት ሐውልት ተሰርቶ ቆሞ ይታያል። አለቃ አያሌው በብስራተ ገብርኤልቤተክርስትያን ተገኝተው እንዲያስተምሩ ተጋብዘው በዚያም ተገኝተው ነበር ። ቅዳሴ እና የታቦት ዑደት ከተፈጸመ በኋላ በቦታው ለተገኝው ብዙ ህዝብ ትምህርት መስጠት ጀመሩ ። ስለ በአሉ ታላቅነት አስተማሩ ከዚያም ቀጥለው ወደ ህዝቡ የእለት ህይወት በመግባት ፡ በጊዜው የነበሩ የሀገሪቱ መሪዎች የሀውልት መታሰቢያ ለማቆም የሚበቃ አንድም የረባ ነገር ሳይሰሩ ምስላቸው ያለበትን ሀውልት ማቆማቸው ከናቡከደነጾር ስራ ጋር የሚመሳሰል መሆኑን ፡ ምእመናን ለዚህ ሀውልት ሳይሆን ለአምላካቸው ለእግዚአብሔር ብቻ ክብርን ሊሰጡ እንደሚገባ የሚገልጽ ቅኔ ለበስ ተግሳጽ ይናገራሉ። ይህ ከሆነ በኋላ መንግስት ይዟቸው እንዲህ አይነት ነገር በአውደምህረት ላይ እንዳይናገሩ ማስጠንቀቂያም ተጨምሮላቸው ሊለቀቁ ችለዋል ፡ እሳቸው ግን በጊዜው የተሰራውን ሀውልት በግልጽ አውግዘዋል ፤ የሰሩት ስራ ሳይኖር ሀውልት ማቆማቸው ተገቢ አይደለም ብለውም አስተምረዋል ፤ እኛም አሁን ማድረግ ያለብን ነገር ሁሉንም ነገር ጊዜው ሳያልፍ በጊዜው ከስርአተ ቤተክርስትያን ውጪ ሲሆን መቃወም መቻል አለብን ፤ ገዳሞቻችንን ሲነኩብን መቃወም መቻል አለብን ፣ እጃቸውን ቤተክርስታየናችን የውስጥ ጉዳይ ላይ ሲያስገቡብን መቃወም መቻል አለብን ፣ እውነታውን መሰረት ያላደረገ መግለጫ ሲሰጥም መቃወም መቻል አለብን ፣ ተባባሪያችሁ አይደለንም ማለትም አለብን ፤ ዝምታ ግን መስማማትን ይወክላልና ዝም ማለት የለብንም ፣ ዛሬ ዝም ብለን ያሳለፍነው ጉዳይ ነገ አድጎ እና ተመንድጎ መልኩን ቀይሮ ሲመጣ ወይኔ የዛኔ ብቃወም ኖሮ ብንል ዋጋ የለውም ።

አለቃ አያሌው ታምሩ የመንግስቱ ኃ/ማርያምን ሀውልት ነበር የተቃወሙት ፡ አሁን እኛ የአቡነ ጳውሎስን ሐውልት መቆም ስንቃወም ፡ እኛው ጋር ቤተክህነት ውስጥ ያሉ ሰዎች ደግሞ እንደሚገባቸው እና ሲያንስባቸው እንጂ እንደማይበዛባቸው ፡ ሽንጣቸውን ይዘው በመጽሄትና በጋዜጣ የሚከራከሩ እንደነበሩ የዛሬ ዓመት ትውስታችን ነው ፣ አሁንም አንዳንድ ወይዛዝርት መጽሀፍ ጽፈው በጥብቅና ቆመው ሲከራከሩላቸው እየየን ነው ፣ከ3 ቀናት በፊት ቤተክህነቱ ዋልድባ ገዳምን በሚመለከት ያወጣውን መግለጫ መቃወምም መቻል አለብን ፣ እውነታው የተገላቢጦሽ ነው ፣ ኢቲቪ ላይ በተቀነባበረ ዜና የማይመለከታቸው መነኮሳትን ሰብስበው ዶክመንተሪ ቢሰሩ ስራቸው የነገሩን እውነትነት አያረጋግጥልንም ፣ ይህ ጉዳይ በአባቶች ቀጣይ የሲኖዶስ ስብሰባ ላይ ተነስቶ የመወያያ አጀንዳ መሆንም መቻል አለበት ብለን እናስባለን ፣ የቅዱስ ሲኖዶስ አባቶችም አስቸኳይ ስብሰባ መጥራት ካለባቸው ጊዜው አሁን ነው ፣ የቤተክህነቱን አቋም እና መንግስትን አቋም ተመልክተናል ፡ ከአንድ ወር በኋላ በግንቦት ወር በሚካሄደው የቅዱስ ሲኖዶስ ስብሰባ ላይ የአባቶቻችንንም አቋም ማወቅ እንፈልጋለን ፡ ጠባቂ ተብለው እስከተሾሙ ድረስ በነገሩ ላይ ጣልቃ ገብተው የመፍትሄ አቅጣጫ ማስቀመጥ መቻል አለባቸው ፣ የዋልድባ ገዳምን የመንግስት የስኳር ልማት ምንም አይነት ተጽህኖ እንደማያደርስበት ተወካዮችን ልከው ማረጋገጥ አለባቸው የሚል እምነት አለን ።  አቡነ ጳውሎስ በላኳቸው ሰዎች እምነት የለንም ፣ መግለጫውም ነባራዊ ሁኔታን ያገናዘበ እውነት ነው የሚል አቋምም እምነትም  የለንም ።  ቅዱስ ሲኖዶሱ በሚልከው አጣሪ ቡድን ጉዳዩ ዳግም ይታይልን ። ብለንጥያቄያችንን በወቅቱ ማቅረብ አለብን። ቤተመንግስትና ቤተክህነት ስህተት ቢሰሩ ፣ ሁለቱም በተሳሳተ ጎዳና ላይ ቆመው ብንመለከታቸው እኛም የእነሱ ተባባሪ መሆን መቻል የለብንም ።

አቡነ ሺኖዳ ባለፈው አመት የጌታችን የመድሀኒታችን የኢየሱስ ክርስቶስን ልደት አክብረው ከቤተክርስትያን ሲወጡ በሞቱት 32 ንጹሀን ክርስትያኖች ላይ የተደረገውን ነገር ለመቃወም የሄዱት ወደ መንግስት ባለስልጣናት ቢሮ አልነበረም። ከዚህ ሰቅጣጭ የአክራሪዎች ጥቃት በኋላ ቀጥታ ለሱባኤ ወደ ገዳም አመሩ ፣ የሱባኤያቸው መልስ ግን 30 ዓመት ግብጽን  ሲያስተዳድራት የነበረው የሁስኒ ሙባረክ መንግስት በ18 ቀን የህዝብ ተቃውሞ ከስልጣኑ ወርዶ ነበር ያገኙት ፣ እግዚአብሔር እውነተኛ አባቶችን «አቤት» ብሎ ነው የሚሰማቸው። ለእኛም ስለ ቤተክርስትያናችን ፈተና አምላክ ፊት አቤቱታችንን የሚያቀርብልን አባት ይስጠን እንላለን። ለምንስ አምላክ አቡነ ጎርጎርዮስን የመሰለ አባት አያስነሳልንም?


7 comments:

  1. ወይዛዝርቱ መፅሐፍ ‹‹ፅፈው›› የሚለው ‹‹አስፅፈው›› በሚለው ቢስተካከል፡፡

    ኤልዛቤል እንኳን መፅሐፍ መፃፍ አረፍተ ነገርም መስራት አትችልም፡፡

    መፅሐፉን የጻፈው እኮ በጌ መናፍቁ ነው፡፡

    ReplyDelete
  2. ቅዱስ ሲኖዶሱ በሚልከው አጣሪ ቡድን ጉዳዩ ዳግም ይታይልን::
    ለምንስ አምላክ አቡነ ጎርጎርዮስን የመሰለ አባት አያስነሳልንም?

    From Hawassa

    ReplyDelete
  3. አቡነ ሺኖዳ ባለፈው አመት የጌታችን የመድሀኒታችን የኢየሱስ ክርስቶስን ልደት አክብረው ከቤተክርስትያን ሲወጡ በሞቱት 32 ንጹሀን ክርስትያኖች ላይ የተደረገውን ነገር ለመቃወም የሄዱት ወደ መንግስት ባለስልጣናት ቢሮ አልነበረም። ከዚህ ሰቅጣጭ የአክራሪዎች ጥቃት በኋላ ቀጥታ ለሱባኤ ወደ ገዳም አመሩ ፣ የሱባኤያቸው መልስ ግን 30 ዓመት ግብጽን ሲያስተዳድራት የነበረው የሁስኒ ሙባረክ መንግስት በ18 ቀን የህዝብ ተቃውሞ ከስልጣኑ ወርዶ ነበር ያገኙት ፣ እግዚአብሔር እውነተኛ አባቶችን «አቤት» ብሎ ነው የሚሰማቸው። ለእኛም ስለ ቤተክርስትያናችን ፈተና አምላክ ፊት አቤቱታችንን የሚያቀርብልን አባት ይስጠን እንላለን። ለምንስ አምላክ አቡነ ጎርጎርዮስን የመሰለ አባት አያስነሳልንም?

    thank you my brother.

    ReplyDelete
    Replies
    1. Egizabiher Masitewalhun Yadilen yedegaguch geta yekidusan amilak lenesu yadelewen bereket ena tsenat legnam yadelaen!!!

      Delete
  4. አቡነ ሺኖዳ ባለፈው አመት የጌታችን የመድሀኒታችን የኢየሱስ ክርስቶስን ልደት አክብረው ከቤተክርስትያን ሲወጡ በሞቱት 32 ንጹሀን ክርስትያኖች ላይ የተደረገውን ነገር ለመቃወም የሄዱት ወደ መንግስት ባለስልጣናት ቢሮ አልነበረም። ከዚህ ሰቅጣጭ የአክራሪዎች ጥቃት በኋላ ቀጥታ ለሱባኤ ወደ ገዳም አመሩ ፣ የሱባኤያቸው መልስ ግን 30 ዓመት ግብጽን ሲያስተዳድራት የነበረው የሁስኒ ሙባረክ መንግስት በ18 ቀን የህዝብ ተቃውሞ ከስልጣኑ ወርዶ ነበር ያገኙት ፣ እግዚአብሔር እውነተኛ አባቶችን «አቤት» ብሎ ነው የሚሰማቸው።

    ReplyDelete
  5. እስኪ እግዚአብሄር እንዲሰማን እንፀልይ፣ የድርሻችንን ለቤተክርስቲያን የምናበረክትበት ጊዜ ይመስለኛል፡፡ አሁን ጊዜው ነው አካሄዳችንን ከፖለቲካ፣ ከዘር፣ወዘተ ልዩነት ሳናገናኝ ፣ በአንድነት፣ በተጠና እና በተደራጀ መልኩ ለመታገል ሁላችንም ስለቀጣይ አካሄራችን እንወያይ፡፡ እኛ ባሪያዎቹ ከተነሳን እርሱ ያከናውንልናል፡፡እስኪ እግዚአብሄር እንዲሰማን እንፀልይ፣ የድርሻችንን ለቤተክርስቲያን የምናበረክትበት ጊዜ ይመስለኛል፡፡ አሁን ጊዜው ነው አካሄዳችንን ከፖለቲካ፣ ከዘር፣ወዘተ ልዩነት ሳናገናኝ ፣ በአንድነት፣ በተጠና እና በተደራጀ መልኩ ለመታገል ሁላችንም ስለቀጣይ አካሄራችን እንወያይ፡፡ እኛ ባሪያዎቹ ከተነሳን እርሱ ያከናውንልናል፡፡

    ReplyDelete
  6. Diakon asmelash ze-rayaMarch 27, 2012 at 6:28 AM

    "Egnas abat atan yehaymanot jegna, weld wahid bilo be'eminetu yetsena." ahun bete kihnetoch yayit miskir dinbit mehonachihu new? Tarik yiweksachihual.

    ReplyDelete