Monday, November 2, 2015

የመምህር ግርማ ቤት ተበረበረ
(ሪፖርተር ጥቅምት 21 2008 ዓ.ም)፡- በማታለል ወንጀል ተጠርጥረው ጥቅምት 17 ቀን 2008 .. በፖሊስ ቁጥጥር ሥር የዋሉት መምህር (አጥማቂ) ግርማ ወንድሙ፣ አያት የሚገኘው መኖርያ ቤታቸው በፖሊስ መበርበሩ ታወቀ፡፡ 

ፖሊስ ቤታቸውን ሲበረብር ያገኘው ነገር ባይገለጽም፣ ለተጠረጠሩበት የወንጀል ድርጊት ማስረጃ የሚሆነውና ሌሎች ተጨማሪ ነገሮች ፍለጋ ሳይሆን እንዳልቀረ ምንጮች ለሪፖርተር ተናግረዋል፡፡ መምህር ግርማ ከሁለት ወራት በፊት የእስር ትዕዛዝ ተሰጥቶባቸው እንደነበር ተጠቁሞ፣ አንድ ቀን ፖሊስ ጣቢያ አድረው ጥቅምት 18 ቀን 2008 .. በፌዴራል የመጀመርያ ደረጃ ፍርድ ቤት አራዳ ምድብ አንደኛ ወንጀል ችሎት ቀርበዋል፡፡ በወቅቱም ፖሊስ 14 ቀናት ተጨማሪ የምርመራ ጊዜ ጠይቆባቸው ነበር፡፡ የፖሊስን ጥያቄ በመቃወም የዋስትና መብታቸው ተጠብቆ ከእስር እንዲፈቱ በጠበቃቸውና በራሳቸው የጠየቁ ቢሆንም፣ ፍርድ ቤቱ አልተቀበላቸውም፡፡ 


መምህር ግርማ የተጠረጠሩበትን የማታለል ወንጀል የፈጸሙት፣ በመስከረም ወር 2006 .. እንደሆነና በየካ ክፍለ ከተማ ወሰን ግሮሰሪ አካባቢ ነዋሪ መሆናቸው ከተጠቆመው አቶ በላይነህ ከበደ መኖርያ ቤት ጋር የተገናኘ መሆኑ በምርመራው ተገልጿል፡፡ 

ፖሊስ በምርመራው እንዳረጋገጠው አቶ በላይነህ ከትዳር አጋራቸው ጋር የሚኖሩበት 400 ካሬ ሜትር ቦታ ላይ ያረፈ መኖርያ ቤት ነበራቸው፡፡ አቶ በላይነህ ቤታቸውን በአጭር ጊዜ ውስጥ ካልሸጡ ሊሞቱ እንደሚችሉ መምህር ግርማ ሲነግሯቸው፣ ከፍተኛ ዋጋ ያወጣላቸው የነበረ ቤታቸውን 800 ሺሕ ብር ለመሸጥ መገደዳቸውን የፖሊስ ምርመራ ይጠቁማል፡፡ 

መምህር ግርማ ቤቱን ማሸጥ ብቻ ሳይበቃቸው፣ ገንዘቡ እንዲበረክትላቸው እንዲፀለይበት እንዲሰጧቸው የተጠየቁት አቶ በላይነህ፣ ገንዘቡን መስጠታቸውን ፖሊስ ለፍርድ ቤት አስረድቷል፡፡ ሊፀለይበት ወደ መምህር ግርማ ቤት ተወስዷል የተባለው ገንዘብ ውሎ በማደሩ፣ አቶ በላይነህ ወደ መምህር ግርማ ቤት ስልክ ሲደውሉ ስልኩ አልሠራ እንዳላቸውና ወደ ውጭ አገር መሄዳቸውን እንደሰሙ መግለጻቸው በፖሊስ ተጠቅሷል፡፡ 

ተጠርጣሪው መምህር ግርማ ለፍርድ ቤቱ ከሳሻቸውን ቀይ ይሁኑ ጥቁር እንደማያውቋቸውና ሆን ተብሎ የተሸረበባቸው ሴራ መሆኑን አስረድተዋል፡፡ የተጠረጠሩበት ወንጀል ዋስትና የማያስከለክል መሆኑን በመግለጽ በዋስ እንዲለቀቁ ቢጠይቁም፣ ፍርድ ቤቱ አልተቀበላቸውም፡፡ ፍርድ ቤቱ ፖሊስ የጠየቀውን 14 ቀናት የምርመራ ጊዜ ባለመቀበል ሰባት ቀናትን በመፍቀድ ለጥቅምት 25 ቀን 2008 .. ቀጠሮ ሰጥቷል፡፡ 

1 comment:

  1. የእኛ ሀገር ፖሊስ በቃ እንደዚህ ሆኖ ቀረ፤ የማንም ወሬ እየለቃቀመ ሰው መክሰስ ጀመረ፡፡ የ ዜ ግ ነ ት ክ ብ ር መቼ ይሁን በእኛ ሀገር ተፈጽሞ የምናየው??????????????????????????????????????????????? ወይኔ ሀገሬ ስንት ቅዱሳን እንዳላፈራሽ ዛሬ የማንም መጫወቻ ትሆኚ፤ እስኪ ይሁን ጌታ ሆይ አንተ ታውቃለህ!!!!!!!!!!!!!!!!!!!!!!!!!!!!!!!!!!!!!!!!!!!!!!!!!!!! አሁን ይህ ጉዳይ ወደ እራሳችን እንምጣውና ጥላቻችን እንተወውና እሳቸውን ምንም ይሁኑ ቢያንስ በትንሹ በእድሜ ይበልጡናል፡፡ አደረጉ ብለን የምንከሰውን እንተወው፡፡ ሁሉንም የሚያውቀው እግዚአብሔር ስለሆነ ለእርሱ እንተውውና፡፡ በእውነት እኚህ አባት እንደክርስትና ወይም እንደባለህሊና ስንመለከተው እየደረሰባቸው ያለው ግፍ ትክክል አይደለም፡፡ ምክንያቱ ፖሊስ የፈለገ ቢሮጥ ይህ ጉዳይ መፈጸሙን የሚገለጽ ማስረጃ ሊያገኝ አይችልም፡፡ ምክንያቱም ከሳሹ በእምነት አስታኮ ስለመጣ፡፡ ድርጊቱ ሲፈጸም ማንም ሰው ሊኖር ስለማይችል፤ ካለም መረጃ ሊሆን የሚችለው ሁለቱም ገንዘቡን ሲቀባበሉ የሚገልጽ የፎቶ ወይም የቪዲየ መረጃ አለበለዚያ እንደአባቶቻችን በፊርማ የተገለጸበት መረጃ፣ እነዚህ እንኳን በአሁን ሰዓት ተቀባይነት አይኖራቸውም ምክንያቱም ይህ ሁሉ ፎርጅድ መሰራት ስለሚችል፡፡ ይህ ሁሉ ነገር ያለባት ዓለም እንዴት ነው አንድ ሰውን ብቻ ተቀብሎ እንደዚህ ማቀንቀን እኔ አልገባኝም፡፡ወይ ክርስትና!!!!!!!!!!!!!!!!!!!! እኔ ማንንም እልደግፍም አያደርጉም፣ አላደረጉም፣ እያልኩ አይደለም፡፡ እኔ አላውቅም ይህንን እውነት የሚያውቀው አንድ እግዚአብሔር ብቻ ነው የሚያውቀው፡፡ ወይ ተከሳሹ አምኖ ሲቀበል፡፡ አለበለዚያ ማንም ባላየበት፣ ገና ለገና ሊሆን ይችላል ተብሎ ጥቃቅን ነገር ተለቃቅሞ ሰውን መክሰስ፡፡ በዚህ ዘመን የሰው ክብር ተብሎ በሚነገርባት አለም!!!! እንደዚህ ዓይነት ነገር መታየቱ የሚያሳዝን ነው፡፡ ለማንኛውም መጨረሻውን መመልከት ነው፡፡ ማስተዋል ይስጠን፡፡

    ReplyDelete