Thursday, November 5, 2015

መንፈሣዊነት እና ሰይጣንን ማባረር ፡ መምህር ግርማ Vs ዳንኪረኛው ጥበቡ ወርቅዬ

በጥበቡ በለጠ 
 •  ጠያቂና አሳቢ አእምሮ ከሌለን ሰው የመባላችን ምስጢርም አጠራጣሪ ይሆናል።
 • የሰይጣን ማስወጫው ምንድን ነው? መስቀል? መቁጠሪያ? መዳፍ? ፀሎት? እምነት?
 • መምህር ግርማ ወንድሙ እና ጥበቡ ወርቅዬ ሰይጣን ሲያያቸው እንዲህ የሚርበተበትላቸው ከሆነ ለምንስ በጋራ ተቀናጅተው ይህን ሁሉ ህዝብ የሚያሰቃዩትን ሰይጣኖች አያስወጡልንም?
 •  የቅስና ማዕረግ ሲፈለግ የሚነሳ ፤ ሳይፈለግ የሚደበቅ ማዕረግ ነውን?(  መምህር ግርማ በአንድ ወቅት ስልጣነ ክህnት ሳይኖርዎት እንዴት ያጠምቃሉ? ተብለው ሲጠየቁ ‹‹አይ ደብቄው ነው እንጂ የቅስና ማዕረግ አለኝ ›› ብለው ቆባቸው አድርገው መምጣታቸው የምናስታውሰው ጉዳይ ነው፡፡)


(አንድ አድርገን ጥቅምት 26 2008 ዓ.ም)፡-     በተለምዶ መምህር ግርማ ወንድሙ በመባል ስለሚጠሩት፣ በማዕረግ ስማቸው ደግሞ “መልአከ መንክራት ግርማ ወንድሙ” ፣ ጥያቄ አዘል መጣጥፍ አቅርቤ ነበር። እኚህ አባት በየአውደምህረቱ ከሰዎች ላይ ስለሚያስወጧቸው ሰይጣኖች ርዕሰ ጉዳይ ለመወያያ የሚሆኑ ጥያቄዎችን ነበር የሰነዘርኩት፡ በነዚሁ በተነሱት ጥያቄዎች ዙሪያ በሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎች በድረ-ገፅ አማካይነት አንብበዋል። አያሌ አንባቢዎች መልስ ሲሰጡበት ቆዩ። አብዛኛዎቹ ሰዎች ለተጠየቀው ጥያቄ ተገቢውን መልስ አልሰጡም። እንደውም የተነሳውን ጥያቄ ራሱ የሚቃወሙ በርከት ያሉ አንባብያን ገጥመውኛል። አንዳንዱ ጥያቄውን ራሱ መስማት የዘገነነው አለ። ሌላው ደግሞ ፅሁፉን ጨርሶ ያነበበ የማይመስልም አለ። ምክንያቱም የሚሰጠው መልስ ከጥያቄው ጋር ፈፅሞ አይገናኝምና ነው። ጥቂት የሚባሉ ሰዎች ደግሞ በሚገባ አንብበው ተገቢውን ምላሽ ሰጥተዋል። ለኔ ግን ትልቁ ጉዳይ በዚህ ሁሉ ሺ ሰው ውስጥ ጥያቄውን ማንሸራሸሩ ነበር።

     መምህር ግርማ ወንድሙ ስለሚያባርሯቸው ሰይጣኖች ጉዳይ ጠይቄ ሳልጨርስ በአናቱ ላይ ደግሞ አንድ አስገራሚ ነገር ገጠመኝ። የቀድሞው ጎበዝ ድምጻዊ (ዘፋኝ) የነበረው ጥበቡ ወርቅዬ፣ እሱም እንደ መምህር ግርማ ወንድሙ የሰይጣን መንፈስ እያተረማመሰ ሲያስወጣ ተመልክቼ ማሰብ ማሰላሰሌን፣ መጠየቄንም ቀጠልኩበት።

     ጥበቡ ወርቅዬ የፕሮቴስታንት ሃይማኖት ተከታይ መሆኑን እና ከዘፈን፣ ከዳንኪራ ብሎም ከሃጢያት መንገድ መውጣቱ በቅርቡ በልዩ ልዩ ሚዲያዎች ሲነግረን ሲያጫውተን ቆይቷል። ጥበቡ ወርቅዬ ዘፈን ማቆሙና ሃይማኖቱን መቀየሩ ብሎም መንፈሳዊ ሰው መሆኑ ገርሞኝ ሳላበቃ ይሔው የቀድሞ ድምፃዊ ዛሬ ደግሞ ፈጣሪያችንን ተፈታታኝ የሆነውን ሰይጣን፣ የሰው ልጆችን ሁሉ ለመከራና ለስቃይ የሚዳርገውን ሰይጣን፣ አለምን ለእርኩሰትና ለሀጢያት የሚያጋልጠውን ሰይጣን አባራሪ፣ አስወጪና የኢትዮጵያዊያን ሕሙማን ፈዋሽ ሆኖ ተመርጧል።

     ጥበቡ ወርቅዬም ሰይጣኑን እያነጋገረው፣ እያስጨነቀው፣ እያስጓራው፣ እያስጮኸው፣ እያንከባለለው፣ እያንደፋደፈው ሲያስወጣ በየመድረኩ እያየን ነው። ጥበቡ ወርቅዬን ከሰይጣኑ ጋር ሲያወራም አየሁት፡ ሰይጣኑን “እኔን አታውቀኝም?” እያለ ይጠይቀው ነበር። በዚህ ጊዜ ሰይጣኑ ጥያቄውን ፈርቶ ይርበተበት ነበር። ድሮ አንተ ዘንድ ነበርኩ፤ ዛሬ ደግሞ አንተን አባራሪ ሆኛለሁ እያለ የቀድሞው ድምጻዊና ዳኪረኛ ጥበቡ ወርቅዬ በአዲሱ የመንፈሣዊነት ጎዳና ላይ አየሁት። መቼም ለዚህ ወግና ማዕረግ መብቃት፣ መመረጥ ያስደስታል። ግን ደግሞ ሰው ስለሆንን የሚያስብ የሚጠይቅ አእምሮ ስላለንም አንዳንድ ጥያቄዎች በውስጣችን ብቅ ማለታቸው አይቀርም።

     እኔ በበኩሌ ለመምህር ግርማ ወንድሙ ያቀረብኳቸውን ጥያቄዎች አይነት በጥበቡ ወርቅዬ ላይም እጠይቃለሁ። የሚመልስልኝ የሃይማኖት መሪ፣ አዋቂ ካለም እሰየሁ። ከሌለም ደግሞ ከአንባቢዎቼ ጋር ብንወያይበት ጥቅሙ ለሁላችንም ነው። የቢላ ስልቱ የሚወጣው እርስ በርሱ ሲፋጭ ነው። የረጋ ወተትም ቅቤ የሚወጣው ሲናጥ ነው። እኛም በሃሳብ ሽርሽር ተፋጭተን አእምሯችን ውስጥ አንድ ነገር እናስቀምጥ። ጠያቂና አሳቢ አእምሮ ከሌለን ሰው የመባላችን ምስጢርም አጠራጣሪ ይሆናል። ስለዚህ እስኪ እንጠይቅ።

     ጥበቡ ወርቅዬ አሁን በቅርቡ ድምጻዊ የነበረ፣ ከመንፈሳዊ ሕይወት ራቅ ብሎ በአለማዊው ሕይወት ጎልቶ ይታይ የነበረ ድምፃዊ እንደነበር እሱ ራሱ ከሰጣቸው መልሶች መገንዘብ ይቻላል። ይህ በሀጢያት ጎዳና እንደነበር ሲገልፅልን የነበረ ድምጻዊ ድንገት ተነስቶ ኢትዮጵያዊያንን ከሰይጣን ቁራኛ የሚያላቅቅ ታላቅ መንፈሣዊ ሆኖ ስናየው ያስገርማል። “እግዚአብሔር ከሐጢያተኞች መሀል መርጦት ለታላቅ ክብር አበቃው፤ ይህ ደግሞ የእርሱ ስራ ነው” ብዬ በመመለስ ይህን ጉዳይ ማለፍ አልቻልኩም። እግዚአብሔር ከመረጠ ለአያሌ ዘመናት ወይም እድሜ ልካቸውን በመንፈሳዊ ሕይወት ውስጥ የኖሩ፣ ለዘመናትም ለሕዝብ ኑሮና ብልጽግና ሲፀልዩ፣ በፈጣሪያቸው ሲያምኑ የኖሩ ሰዎች ለምን አልተመረጠም ብዬ እጠይቃለሁ፡ እግዚአብሔር ለፈውስ የሚመርጠው ማንን ነው? ብዬ ጠይቃለሁ።

     በጥቂቱ ተቀርፆ ያየሁት የጥበቡ ወርቅዬ የፈውስ መርሃ-ግብርም ጥያቄ እንዳነሳ ገፋፍቶኛል። በፕሮቴስታንት ቤተ-ክርስትያን ለዚያውም በአንዲት የማምለኪያ ስፍራ ከተገኙት አማኒያን ውስጥ ይህ ሁሉ ሰይጣን አለ ወይ ፤ 90 በቶው በእርኩስ መናፍስት በጫወጫ ነው ወይ ብዬ እንድጠይቅ አድርጎኛል። ምክንያቱም የጥበቡ ወርቅዬን የፈውስ መርሃ-ግብር ሲካሔድ ሰይጣን ትርምስምሱ ሲወጣ ፊልሙ ያሳያል። እዚህች ኢትዮጵያችን ውስጥ በአንዲት ቦታ ላይ ብቻ በዚህ ሁሉ ሰው ውስጥ ሰይጣን ከሰፈረ መፍትሔው ምንድን ነው? ለመሆኑ ሕዝቡን እንዲህ የሚያወራጨውና የሚያንደባልለው ሰይጣን ነው ወይ? ወይስ ከባድ መተት?

     በኦርቶዶክስ ቤተ-ክርስቲያን በኩል ያሉት መምህር ግርማ ወንድሙ ሰይጣንን በመቁጠሪያ እና በመስቀል አስጨንቀው ሲያስወጡት ይታያል። ከፕሮቴስታንት በኩል ያለው ጥበቡ ወርቅዬ ደግሞ ሰይጣንን እስኪ እየኝ እያለው ትክ ብሎ እየተመለከተው፣ በእጆቹ መዳፍም የሕሙማንን ሰውነት እየደባበሰ ሰይጣንን ያባርራል። ለመሆኑ ሰይጣኖች የኦርቶዶክስና የፕሮቴስታንት ተብለው ይከፈላሉ ወይ? ልዩነትስ አላቸው ወይ? የሰይጣን ማስወጫው ምንድን ነው? መስቀል? መቁጠሪያ? መዳፍ? ፀሎት? እምነት? ሌላም ካለ እንነጋገርበት።

     መምህር ግርማ ወንድሙ እና ጥበቡ ወርቅዬ ሰይጣን ሲያያቸው እንዲህ የሚርበተበትላቸው ከሆነ ለምንስ በጋራ ተቀናጅተው ይህን ሁሉ ህዝብ የሚያሰቃዩትን ሰይጣኖች አያስወጡልንም?
     ሌላው ጥያቄዬ የሰይጣን መገኛው የት ነው የሚለው ነው? ድሮ ልጅ ሳለን በመቃብር ስፍራ በጠራራ ፀሐይ እና በምሽት አትጓዙ ሰይጣን አለ እንባል ነበር። በጠንቋይ ቤት፣ ባዕድ አምልኮ በሚሰራባቸው ቦታዎች፣ ሌሎችም የሰይጣን መገኛዎች ናቸው ተብለው የተፈረጁ ቦታዎች ነበሩ። ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ደግሞ የክርስትያን የማምለኪያ የተቀደሱ ቦታዎች ናቸው የሚባሉት ላይ ይህ ሁሉ ሰይጣን ሲወጣ እያስተዋልን ነው። ሰይጣን የአምልኮ ቦታ ላይ የመቆም ሃይል አለው ወይ? ለመሆኑ መኖሪያው የት ነው?

      ታላቁ ፕሮፌሰር መስፍን ወልደማርያም በ1985 ዓ.ም ያሳተሙት ኢትዮጵያ ከየት ወደየት የተሰኘ ግሩም መፅሐፍ አላቸው። በዚህ መፅሐፍ ውስጥ ልዩ ልዩ መጣጥፎች የሚገኙ ሲሆን፣ ከነዚህ ውስጥ ደግሞ “እግዚአብሔርና እኛ” የተሰኘው ፅሁፍ አንዱ ነው። ፕሮፌሰር መስፍን፣ በዚህ ፅሁፋቸው እኛ ኢትዮጵያዊያን ከፈጣሪያችን ጋር ያለን ግንኙነት እንዴት ነው? አምልኳችን በምን ላይ የተመሰረተ ነው? እምነት ራሱ ምንድን ነው የሚሉትንና የመሳሰሉትን ሃሳቦች የያዘ ርዕሰ ጉዳይ ነው።

     እንደ ፕሮፌሰር መስፍን አፃፃፍ ከሆነ እኛ ኢትዮጵያዊያን በተለይ አሁን ያለነው ትውልዶች፣ ሁሉንም ነገር ፈጣሪና መላዕክት አልያም ሌላ አካል እንዲሰጠን እንጠብቃለን። እኛ እግዚአብሔር ብርታትና ጥንካሬ ሰጥቶን ያሰብነው ያለምነው ቦታ ላይ ለመድረስ ጥረት አናደርግም፤ ሁሉንም ነገር የሚሰጠንን ኃይል እንጠብቃለን የሚል ጭብጥ ያለው ጽሁፍ ነው። እውነት ግን እምነት እና እኛ ግንኙነታችን እንዴት ነው ብለን እስኪ እንጠያየቅ።

     መቼም ኢትዮጵያ በክርስትናውም ታሪክ ውስጥ ስሟ ከፊት ጎልቶ የሚነገርላት ናት። ለምሳሌ በመፅሐፍ ቅዱስ ውስጥ ስሟ ተደጋግሞ የተነገረላት ሀገረ- እግዚአብሔር ናት በሚል ትታወቃለች። እየሱስ ክርስቶስ ሲወለድ ሰባ ሰገሎች ለክብሩ መገለጫ ወርቅ፣ እጣን፣ ከርቤ፣ የከበሩ ማዕድናት ይዘው ወደ እስራኤል እንደሔዱ ሁሉ፣ በወቅቱ ኢትዮጵያን ሲያስተዳድር የነበረው ንጉስ ባዜንም ወደ እስራኤል ሔዶ የጌታን መወለድ ተመልክቶ የመጣ ሰው መሆኑ ይነገራል። የፅላተ-ሙሴ መቀመጫ በሆነች ሀገር፣ አድባራትና ገዳማት ከታላላቅ ታሪኮቻቸው ጋር ባበቡባት ጥንታዊት ምድር ላይ ዛሬ ዛሬ እየተከወኑ ያሉ እምነቶች ቆም ብለን “ምን አይነት ክርስትና ነው እያራመድን ያለነው” ብለን እንድንጠይቅ ያስገድደናል። በዚህች ሀገር ውስጥ በአሁኑ ወቅት የተደናበሩ ፈረንጆች ሁሉ እየመጡ ኢትዮጵያዊያንን ከሰይጣንና ከደዌ እየፈወስን ነው በማለት በየማምለኪያ ቦታው ዶክመንተሪ ፊልሞች እየሰሩ እያሳዩን ይገኛሉ። አሁንም የኢትዮጵያ ሰይጣን ብዛቱ እና የሚያጠምቀውና የሚያስወጣው ሰውም እንዲሁ የትየለሌ እየሆነ በመምጣት ላይ ነው።
   
  ሰይጣንን ከሰው ላይ ለማባረር አቅም ያላቸው እነማን ናቸው? ዘፋኞች? ወታደሮች? አማኞች?. . ኧረ እነማን ናቸው? የእምነት ተቋማት ራሳቸው ጠንካራ አቋም ሊኖራቸው ግድ ይላል። ዛሬ ዝም ብለው የሚያዩት ይህ ጉዞ፣ ነገ ሌላ ቅርጽና ስርዓት ይዞ ብቅ ይላል። ከፊት ያለው ፈተና ከባድ ይመስላል።

     በአጠቃላይ አንባቢዎቼን የምጠይቀው ነገር እስኪሰከን ብለን እኛ ማንም ተነስቶ በቀደደው ጎዳና የምንፈስ ነን ወይ?

9 comments:

 1. እግዚአብሔር ይስጥልኝ። እንደውም እኔ በግሌ እያልኩ የነበረው ሰይጣን ይህን ያህል ታዞላቸው ከተንበረከከላቸው ለምን እሱን አራሱን ከአምላክ ያስታርቁትና በሀገራችን ጤነኛና ማይኩም ደግሞ የእግዚአብሔር ድንቅ ስራው የሚነገርበት ቢሆንልን። የቅዱሳን አምላክ አእምሮአችንን ይመልስልንና ማስተዋሉን ይስጠን አሜን።

  ReplyDelete
 2. men ydareg "anbasa syreze yzenb mchwech yhonal "yalwet abaw abatocha zem blew mesalachu ych agera egezabher ytbalechen ysntwe sadkan ager ysent gedamatna adbarat ager yseta meder nech ymelat tweled eraswen ylmenem tgadlw khenat ylalachw fawsen ymelew mmettachew tytachaw new .lhwlewm egezabher amlek lebanacwe mlesw lnshan endyabkachew enslylchw alen hulachenem balenebat egezabher amlak orthodox twhedow emntachenn kmnafkan sara ytabkelen amen!!

  ReplyDelete
 3. Why you always write unnecessary things, sorry if you are on the write side why don't you preach God words.....our Orthodox church is becoming a political pitch! I Please almighty God bless Ethiopia!!!!

  ReplyDelete
 4. Bewnet Egziabher yakbirilin.Bezih guday betekirstian endelealaw gize chel bila yemitalf kehone,ahun yetejemerew niqnaqem endew legizew bicha kehone,yichin kidist betekirstian mefencha new yemiyaderguat.Kibr yistilin !

  ReplyDelete
 5. ወይ አለማስተዋል! ትገርማላችሁ ስታሳፍሩ ወይ ክርስትናችን!
  መናፍቁን ስታነጻጽሩ ትንሽ እንኳን አታፍሩም???
  ድሮም አዛኝ ቅቤ አንጓች አሉ አያቴ?

  ReplyDelete
 6. እግዚአብሔር አገልግሎትህን ይባርክልህ ፡፡ እውነትክን ነው ዛሬ በሀገራችን የሀይማኖቻችን ጉዳይ ለሰማያዊ ቤት ሳይሆን ለምድራዊ ቤት /ኑሮ/ ሀብት መሰብሰቢያ ሆናለችና እኛ ኦርቶዶክሳውያን ልናስተውል ይገባናል፡፡ የቤተ-ክርስቲያን አባቶችም በጎቻቸውን ሊጠብቁ ይገባል እላለሁ፡፡

  ReplyDelete
 7. በመጀመሪያ መምህር ግርማ ለዘመናት ከቤተ ክርስቲያን ያልጠፉ በእግዚአብሄር ትምህርትርም ሆነ በአገልግሎቱ ከቤተስኪያኑ ያልተለዩ መሆኑ ግልፅ ነው ። ትናንት የመጡ አስመስለህ ማውራትህ ይገርማል ፤ ከ13 ዓመት በላይ ቤተክርስቲያኑን ሲያገለግሉ አንድ ፍራክ ሳይቀበሉ ከንቱዋችሁን በከንቱ መልሱ የተባለውን በተግባር ያሳዩ አባት ናቸው ይህን ለማረጋገጥ ድንገት የውሸት ክስ መስርተህ ቤታቸውን 15 ቀን ስትበረብር ያሁሉ የቃልቻ የመተት እንዲሁም የወርቅ የዶላር ክምር ብታገኝ ኖሮ በደስታ ፈንድቀህ ከጥበቡ ወርቅዬ ጋር ባመሳሰልካቸው ነበር አይ የስም መመሳሰል። አጋንንትን ማውጣት ለካህናት ለተመረጡት እንደሚቻል ስታስተምር አልነበረ እንዴ? ሁሉም እንደየስጦታው ያገለግላል ስትል አልነበር እንዴ? መንፈስን መመርመር የእናንተ ስራ ነበር ታዲያ ለምን ፊት ለፊት አትሄድም ለምን ጓሮ ጓሮ ትምሳለህ እሳቸው ባደባባይ እያሉ? ድሎት እና ምቾት ቢፊልጉ እንደ አብዛኛዎቻችሁ ውጭ ሀገር ተዝናንተው መኖር ይችላሉ መቼም በዚህ አንጣላም። ግን እውነቱ እንደሱ አይደለም። መምህር በሚገባ አስተምረዋል ከፈለክ ያስተማሩት ገብተህ ማየት ትችላለህ ሁሉ በግልፅ ነው ። ጌታንም አጋንንት ሲያወጣ ይሄ ጠንቋይ መተተኛ ብለውታል ስለዚህ ምንም አይደንቅም ብዙ ህዝብ የኦርቶዶክር እምነቱን እንዲያጠነክር ምክንያት ሆኑ እንጂ ሰንካላ አልሆኑም። በጋራ ላልከው ጥሩ ነበር ለእናንተ እንድታምኑ ምንም እንኳ እግዚአብሔር ምንም የሚሳነው ነገር የለም እያላችሁ ብታስተምሩም በቤቱ በስሙ እና በቅዱሳኑ የሚከናወነውንም ብታዩ አላመናችሁም እና አመፃ ትውልድ መሆናችሁን አረጋግጠናል። እስኪ ህድና ጥያቄዎችህን በአደባባይ ህዝቡ ፊት ጠይቃቸው እንደ ሾካካ በየፌስ ቡኩ ሀሜት ከምትደረድር።

  ReplyDelete
 8. እነደ መናፊቃን አፍ እንጂ መስሚያ ጆሮና ማግናዘቢያ አእምሮ የላቸውም ሁልጊዜ በውሸት መኖር ይፈልጋሉ መርዘኛ ቅናተኛ ስለሆኑ ስጦታቸውማ የመምህር ግርማ ከእግዚያብር ነው እድሜ ጤና ይስጥልን ይህን መርዘኛ ማህበር ልቦና ይስጥልን!!!

  ReplyDelete
 9. በመጀመሪያ መምህር ግርማ ለዘመናት ከቤተ ክርስቲያን ያልጠፉ በእግዚአብሄር ትምህርትርም ሆነ በአገልግሎቱ ከቤተስኪያኑ ያልተለዩ መሆኑ ግልፅ ነው ። ትናንት የመጡ አስመስለህ ማውራትህ ይገርማል ፤ ከ13 ዓመት በላይ ቤተክርስቲያኑን ሲያገለግሉ አንድ ፍራክ ሳይቀበሉ ከንቱዋችሁን በከንቱ መልሱ የተባለውን በተግባር ያሳዩ አባት ናቸው ይህን ለማረጋገጥ ድንገት የውሸት ክስ መስርተህ ቤታቸውን 15 ቀን ስትበረብር ያሁሉ የቃልቻ የመተት እንዲሁም የወርቅ የዶላር ክምር ብታገኝ ኖሮ በደስታ ፈንድቀህ ከጥበቡ ወርቅዬ ጋር ባመሳሰልካቸው ነበር አይ የስም መመሳሰል። አጋንንትን ማውጣት ለካህናት ለተመረጡት እንደሚቻል ስታስተምር አልነበረ እንዴ? ሁሉም እንደየስጦታው ያገለግላል ስትል አልነበር እንዴ? መንፈስን መመርመር የእናንተ ስራ ነበር ታዲያ ለምን ፊት ለፊት አትሄድም ለምን ጓሮ ጓሮ ትምሳለህ እሳቸው ባደባባይ እያሉ? ድሎት እና ምቾት ቢፊልጉ እንደ አብዛኛዎቻችሁ ውጭ ሀገር ተዝናንተው መኖር ይችላሉ መቼም በዚህ አንጣላም። ግን እውነቱ እንደሱ አይደለም። መምህር በሚገባ አስተምረዋል ከፈለክ ያስተማሩት ገብተህ ማየት ትችላለህ ሁሉ በግልፅ ነው ። ጌታንም አጋንንት ሲያወጣ ይሄ ጠንቋይ መተተኛ ብለውታል ስለዚህ ምንም አይደንቅም ብዙ ህዝብ የኦርቶዶክር እምነቱን እንዲያጠነክር ምክንያት ሆኑ እንጂ ሰንካላ አልሆኑም። በጋራ ላልከው ጥሩ ነበር ለእናንተ እንድታምኑ ምንም እንኳ እግዚአብሔር ምንም የሚሳነው ነገር የለም እያላችሁ ብታስተምሩም በቤቱ በስሙ እና በቅዱሳኑ የሚከናወነውንም ብታዩ አላመናችሁም እና አመፃ ትውልድ መሆናችሁን አረጋግጠናል። እስኪ ህድና ጥያቄዎችህን በአደባባይ ህዝቡ ፊት ጠይቃቸው እንደ ሾካካ በየፌስ ቡኩ ሀሜት ከምትደረድር።

  ReplyDelete