Friday, July 18, 2014

ቋሚ ሲኖዶስ ለፓትርያርኩ ከፍተኛ ማስጠንቀቂያ ሰጠ
  • አስቸኳይ የቅዱስ ሲኖዶስ ምልዓተ ጉባኤ ለመጥራት ታቅዶ ነበር፡፡
  • ፓትርያርኩ በአ/አበባ የአድባራት አለቆች ዝውውት ስሕተት መፈጸማቸውን አምነዋል፡፡
  • ‹‹የቤተክርስቲያንን ሥራ ይጎዳል በሚል እንጂ ተመራጩ ነገር ከእሳቸው ጋር(ፓትርያርኩ) ጋር መሥራት ማቆም ነበር፡፡›› የቋሚ ሲኖዶስ አባል የተናገሩት

  • ፓትርያርኩ ከአሁኑ መንገዳቸው ካልተጠቆማቸው ፤ ስህተታቸው ካልተነገራቸው ቤተክርስቲያኒቱን አደጋ ላይ ሊጥሏት ይችላሉ፡፡


አንድ አድርገን ሐምሌ 12 2006 ዓ.ም፡- 
በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ሕግን የመተርጎምና የማስፈጸም መብት ያለው ቋሚ ሲኖዶስ ፤ ውሳኔዬን አክብረው አላስከበሩኝም ፤ ጠብቀው አላስጠበቁኝም ላላቸው ብጹዕ ወቅዱስ ፓትርያርክ አቡነ ማትያስ ከፍተኛ ማስጠንቀቂያ መስጠቱ ተገለጸ፡፡


ቋሚ ሲኖዶሱ ፓትርያርኩን ያስጠነቀቀው ፤ ባለፈው ሳምንት ረቡዕ ባካሔደው ሳምንታዊ ስብሰባ ወቅት ነው፡፡ የቤተክህነቱ የፋክት ምንጮች  እንደተናገሩት  የማስጠንቀቂያው መንስኤ ፤ አቡነ ማትያስ ምክራቸውን ለስልጣነ ፕትርክናቸው አይመጥኑም ከተባሉ ግለሰቦችና የቤተ ክርስቲያኒቱን ተቋማዊ ክብርና ነጻነት በመጋፋት ከሚወቀሱ አካላት ጋር ግንባር በመፍጠራቸው ፤ የቅዱስ ሲኖዶስን ውሳኔንና ልዕልና የሚጻረር ተግባር በየጊዜው በመፈጸማቸውና የቅዱስ ሲኖዶስ አባላቱን ክፉኛ በማሳሰቡ ነው፡፡

ከፍተኛ ገቢና አገልግሎት አቅም ባላቸው የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ገዳማትና አድባራት ሙስናንና ብልሹ አሰራርን በመዋጋት የተመሰገኑ አለቆችን ከሓላፊነት በማንሳት በተመለከተ አገልጋዩና ምዕመኑ ላቀረባቸው ጥያቄዎች ተገቢ ምላሽ ባልሰጡበት ኹኔታ ፤ የቋሚ ሲኖዶሱን ውሳኔ በመጻረር በአቡነ ማትያስ ትእዛዝ የተፈጸሙ ዝውውሮች ፤ ቋሚ ሲኖዶሱ ሳይወስንና የሚመለከታቸው አካላት ሳያውቁ ልዩ ጸሐፊያቸውን በማንሳት በሌላ መተካታቸውና የመሳሰሉት ጉዳዮች የቋሚ ሲኖዶሱ አባላት ከፓትርያርኩ ጋር በከፍተኛ ደረጃ የተጠየቁባቸው ዐበይት ነጥቦች እንደነበሩ ምንጮች አስታውቀዋል፡፡

በስብሰባው ላይ ለፓትርያርኩ ጥያቄ ያቀረቡት የቋሚ ሲኖዶስ አባላቱ ፤ ሳይገባቸውና ደረጃቸውን ሳይጠብቁ ‹ፓትርያርኩን ያማክራሉ› ያሏቸውን ግለሰቦች ስም በመጥቀስ ‹ከማን ጋር ነው የሚሰሩት? ማንን ነው  የሚሰሙት ? ከእኛ ጋር ይሰራሉ ወይስ አይሠሩም ?  › በሚል ጠንክረው እንደጠየቋቸው በምንጮቹ መረጃ ተመልቷል፡፡

አቡነ ማትያስ ስማቸው በሊቃነ ጳጳሳቱ ከተጠቀሱት ሰዎች ጋር የሚመክሩትና የሚሠሩት ‹አላማዬን ስለሚያስፈጽሙልኝ ነው›› በማለት አቋማቸውን ለመከላከል ቢሞክሩም ‹‹ አገልጋዩና ምዕመኑ የሚዘረፍበትና የሚሰቃይበት ዓላማ ሊኖርዎት አይችልም›› በሚል ጠንካራ ምላሽ እንደተሰጣቸውና በኹኔታውም መደንገጣቸው ተሰምቷል፡፡

 ‹‹የቤተ ክርስቲያንን ሥራ ይጎዳል በሚል እንጂ ተመራጩ ነገር ከእሳቸው ጋር(ፓትርያርኩ) ጋር መሥራት ማቆም ነበር፡፡›› ማለታቸውን የተጠቀሰላቸው አንድ የቋሚ ሲኖዶስ አባል ፤ ቋሚ ሲኖዶሱ ፓትርያርኩ በአጋጣሚው በብጹአን አባቶችና በወዳጆቻቸው ጭምር ቢመከሩም ሊያርሙት ስላፈቀዱትና ከሚገኙበት አሳሳቢ የአሰራር ኹኔታ አንጻር የቅዱስ ሲኖዶስ አስቸኳይና ድንገተኛ ጉባኤ ስብሰባ ለመጥራት የሚገደዱበት ደረጃ ላይ ደርሶ ነበር ማለታቸው ተነግሯል፡፡

አቡነ ማትያስ በቋሚ ሲኖዶስ አባላቱ በተጠየቁባቸው ጉዳዮች ስሕተት  መፈጸማቸውን አምነው መቀበላቸውና  ‹‹ከእኛ ጋር ይሰራሉ ወይስ አይሰሩም›› በሚል በቁርጥ ተጠይቀውበታል ለተባለው አዎንታዊ መልስ መስጠታቸው ፤ በቃለ ጉባኤውን የአስቸኳይ ስብሰባ ጥሪ ለጊዜው እንደገታው ጠቁመዋል፡፡ ቋሚ ሲኖዶሱ የቅዱስ ሲኖዶሱን ልዕልናና የቤተ ክርስቲያኒቱን መብትና ጥቅሞች ከመሰል ተግዳሮቶች የማስጠበቅ ርምጃውን በተተኪ ተለዋጭ አባላቱ አጠናክሮ እንደሚቀጥልበትም አስታውቀዋል፡፡

በተያያዘ ፓትርያርኩ የቅዱስ ሲኖዶሱን ውሳኔ በመጋፋት ስሕተት መፈጸማቸውን አምነው ከተቀበሏቸው ርምጃዎቻቸው መካከል ፤ ብልሹ አሰራርንና ሙስናን በመዋጋት የአገልጋዩና ምእመኑ ከፍተኛ ተቀባይነት ማትረፋቸው የሚነገርላቸው የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ደ/ጽጌ ቅ/ዑራኤል ቤተ ክርስቲያን አስተዳዳሪ ዝውውር ዋንኛው ነው ተብሏል፡፡
በደብረ ጽጌ ቅዱስ ዑራኤል ቤተ ክርስቲያን፣ የደብሩ ካህናት፣ ሠራተኞች፣ የሰንበት ትምህርት ቤት አባላትና  ምእመናን  የደብሩ አስተዳዳሪ መልአከ ብርሃናት ቀሲስ ክብሩ ገብረ ጻድቅ ወደ ሌላ ደብር መዛወራቸውን በተመለከተ ተቃውሟቸውን ሰላማዊነት በተሞላው አኳኋን ሲያሰሙ


ምንጭ፡- ፋክት መጽሔት ሐምሌ 12 2006 ዓ.ም 

1 comment:

  1. በእናንተ ዘንድ ያለውን የእግዚአብሔር መንጋ ጠብቁ እንደ እግዚአብሔር ፈቃድ በውድ እንጂ በግድ ሳየሆን በበጎ ፈቃድ እንጂ መጥፎውን ረብ በመመኘት ሳይሆን ጎብኙት ለመንጋው ምሳሌ ሁኑ እንጂ ማኅበሮቻችሁን በኃይል አትግዙ የእረኞችም አለቃ በሚገለጥበት ጊዜ የማያልፈውን የክብር አክሊል ትቀበላላችሁ 1ጴጥ.5÷1-4::

    ReplyDelete