Monday, July 21, 2014

ወላይታ ፡ የፓትርያርክ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ተክለ ሃይማኖት መገኛ


(አንድ አድርገን ነሐሴ 15 2006 ዓ.ም )፡-  ዳግማዊ ምኒልክ (ሕዝቡ በፍቅር እምዬ ይላቸው ነበር) ኅዳር ፳፯ቀን ፲፰፻፹፰(1888).. ወላይታ ከጦና ዋና ከተማ ደልቦ ደረሱ፡፡ እዚኽ የመገኘታቸው ምስጢር የወላይታው ንጉሥ ጦናአልገብርም› ብሎ በመሸፈቱ እሱን ለማረም ነበር፡፡ “…አገር ከጠፋ በኋላ ሲያቀኑት ያስቸግራል፡፡ ገንዘብም በግድ ካልሆነ በቀር በፈቃድ የሰጡት አያልቅም፡፡ አገርህን አታጥፋ፡፡ግብርህን ይዘኽ ግባ፡፡ ብለው በሽምግልና ቢሞክሩም መልሱ እምቢታ በመሆኑ አጤ ምኒልክ ዳሞት ተራራ ላይ ያሰፈሩትን ጦራቸውን አዘው በአንድ ጊዜ ወላይታን አስጨነቋት ፣ ንጉሥ ጦናም ቆስለው ተማረኩ፡፡የሚገርመው ግን መፍቀሬ ሰብዕ እና የዲፕሎማሲ ሰው የሆኑት አጤ ምኒልክአይ ወንድሜን እንዲያው በከንቱ ሕዝብ አስጨረስክብለው የንጉሥ ጦና ቁስል እንዲታጠብና እንዲታከም ካስደረጉ በኋላ የተማረከው የባላገሩ ከብት እንዲመለስ አድርገው ፣ ንጉሥ ጦና እስኪያገግሙ በእግዚአብሔር ቸርነትና ብርቱ በሆነው ተጋድሎአቸው የረቱት ጠብቀው የወላይታን ሕዝብ ሰብስበው “…እንግዲህ ወዲህ የሚያስተዳድርህ ልጄ ወዳጄ ጦና ነውና ተገዛለት፡፡ አውቆ ሳይሆን ሳያውቅ እኔን የበደለ መስሎት ሰው አስጨረሰ እንጂ ከድሮም ከአያቶቻችን ቂም የለንምና መልሼ እሱን ሾሜልሃለው፡፡እንግዲህ ወዲህ ብታምጽ በራስህ ዕወቅ፡፡ ግብሬን አግባ፡፡…” የሚል አዋጅ አስነግረው የወጉዋቸውን ጦናን ሾመው ጥር ፲፩ ቀን አዲስ አበባ ገቡ፡፡(አጤ ምኒልክ መጽሐፍ በጳውሎስ ኞኞ)


እምዬ ሚኒሊክ ንጉስ ጦና ጀግና በመሆናቸው ለንጉስ የሚደረገውን ክብር  ባለመንፈግ ወደ አዲስ አበባ እንዲመጡ ካደረጓቸው በኋላ  እጅግም ስላከበሯቸው የክርስትና አባት ኾነው መልሰው የወላይታ አገረ ገዥ አድርገው ሾመዋቸዋል ፡፡ ከዚያን ጊዜ በኋላ የካዎ ጦና የልጅ ልጆች ከሸዋ መኳንንት ልጆች ጋር በጋብቻ የተሳሰሩም ነበሩ ፤ ይህ ማለት የካዎ ጦና ዘር የኦርቶዶክስ ተዋህዶ እምነት ተከታይ በመሆናቸው ከመኳንንት ልጆች ጋር ጋብቻ መፈጸም ይችሉ ነበር ማለት ነው፡፡ ንጉሥ ጦና ከዚህ ዓለም በሞት ሲለዩ አዲስ አበባ በዓለ ወልድ ቤተ ክርስቲያን አስከሬናቸው አርፎ በአሁኑ ወቅት መቃብራቸው በቤተ ክርስቲያኑ መግቢያ በስተቀኝ በኩል ይገኛል ፤ ከዚያን ጊዜ በኋላ የወላይታ ህዝብ አብዛኛው ክፍል የኦርቶዶክስ ተዋህዶ እምነት ተከታይ ነበር፡፡ (አሁን ግን ተገላቢጦሽ ሆኖ እናገኝዋለን)




ወላይታና ንግሥና  …
የፓቶሎሚ(ሞቶሎሚ) የተባለው የወላይታ የሁለተኛው ማላ ሥርወ መንግስት 11ኛ ንጉሥ ኃይለኛ ስለነበረ ቡልጋ ላይ ዘምቶ  በምርኮ ብዙ ሰዎችን ይዞ ሲሄድ የአቡነ ተክለ ሃይማኖትን እናት እግዚእ ሐርያን በጊዜው ይዞ ሄዶ ነበር ፡፡ “እግዚእ ሐርያን ግን የወታደር ጭፍሮች በማረኳት ጊዜ አክብረው ይዘዋት ሄዱ ፡፡ ለጌታችን ለንጉሡ ሚስት ትሆናለች ብለው፡፡ እጅግ መልከ መልካም ነበረችና”( ይህ  ገድለ ተክለሃይማት ላይ ሰፍሯል ) ፤ እግዚእ ሐርያን ካዎ ፓቶሎሚ ለማግባት አስሞሽሮ ካስቀመጠበት የጣኦት ቤት ቅዱስ ሚካኤል አውጥቷቸው ወደ ቡልጋ ከተመለሱ በኋላ ከባለቤታቸው ከካህኑ ከጸጋ ዘአብ መጸነሳቸውንና አቡነ ተክለሃይማኖት መወለዳቸውን ገድሉ ላይ ሰፍሮ ይገኛል ፡፡

 “ያን ጊዜ ድንገት ከሰማይ መብረቅ በረቀ ፤ ብልጭልጭታ ሆነ ነጎድጓድ ተሰማ ፤ ዓለሙን ሁሉ ተነዋወጠ ፤ ቅዱስ ሚካኤል ወርዶ ከመካከላቸው አንስቶ በክንፉ ታቅፎ ወሰዳት ፤ ከዳሞት ዞረሬም በሶስት ሰዓት ወሰዳት ፤ በመጋቢት በ22 ቀን ጸጋ አብ ከቤተመቅደስ ገብቶ ሲያጥን ለሷ ሲለምን ከቤተመቅደስ አግብቶ ከዚያ ትቷት ወደ ሰማይ አረገ ፤ ከነጎድጓዱና ከመብረቁ ፍርሃት የተነሳ ሞተለሚ ደነገጸ አእምሮውን አጣ” ይላል፡፡ (ገድለ ተክለ ሃይማኖት 12፤136)

ንግሥናና ወላይታ አንድ ሺህ  እድሜ ርዝማኔ አላቸው ፤ በታሪክ ፓቶሎሚ ተብሎ የሚጠራው በገድለ ተክለ ሃይማኖት ደግሞ ሞቶሎሚ የሚባለው ንጉሥ እዚው ቦታ ነግሶ እንደነበር ይነገራል ፤ ወላይታና አካባቢዋ በንጉሥ መተዳደር የጀመረችው ከአስርት መቶ አመታት በፊት ነበር ፤ በጊዜው ነገሥታት ካዎ የሚል ቅድመ መጠሪያ ነበራቸው ፤ ካዎ ማለት በወላይትኛ ንጉሥ ማለት ሲኾን ቡሻሻ ማለት ደግሞ አልጋ ወራሽ ማለት ነው ፤ ወጋ ማለት ትልቅ ወይም ኃይለኛ ማለት ነው፡፡ እንዲሁም ጦሶ ማለት እግዚአብሔር ማለት ነው፡፡


ክርስትናን አልቀበልም ለሌላውም እሾህ እሆናለው ያለው የወላይታው ንጉሥ ሞተለሚ ጻድቁ አባታችን ተክለ ሃይማኖት በእግዚአብሔር ቸርነትና ብርቱ በሆነው ተጋድሎአቸው ሲረቱት ፍስሐ ጽዮን በተባለው ስማቸው ተማርኮ ስማቸውን እስከመለመን ደረሶ ነበር፡፡ አባታችን ተክለ ሃይማኖትምየመንግሥትህንም እኩሌታ ብትሰጠኝ ስሜን አልሰጥህም፡፡ነገር ግን በፈጣሪዬ ብታምን ያለዋጋ እሰጥሃለው ስላሉት ቃላቸውን ሰምቶ ፣ አምኖና ተጠምቆ ክርስትናን ተቀብሏል፡፡ታዲያ ይኽን የመሰለ ደጋግ ሥራ የተሠራባት ወላይታ በባዶ እግር ይሔዱ የነበሩትንና በወር ደሞዛቸው የሙት ልጆችን ያሳድጉ የነበሩ ፍጹም ባሕታዊ ጸዋሚና ተኃራሚ የነበሩትን  የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ፓትርያርክ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ተክለ ሃይማኖትን ብታስገኝ ምን ይደንቃል? ወላይታ ዛሬም ከተሐድሶ መናፍቃንና ፕሮቴስታንት ጋር አንገት ለአንገት እየተናነቁ ሥርዓተ ቤተ ክርስቲያንንና የዳሞትን በረከት የሚያስጠብቁ ብዙ የሰንበት /ቤት ወጣቶች ሞልተውባታል፡፡ ከነዚህ አንደኛዎቹ ደግሞ የወላይታ ደብረ ገነት ቅዱስ ጊዮርጊስ ቤተ ክርስቲያን //ቤት ወጣቶች ናቸው፡፡

ፈረንጆቹ ድመትን በጨለማ ቤት ውስጥ መፈለግ በራሱ አስቸጋሪ ነው፡፡ በተለይ ደግሞ ድመቷ ጥቁር ከሆነች ይላሉ፡፡ በአስቸጋሪ ላይ ሌላ አስቸጋሪ ማለት ነው፡፡ በወላይታም እንዲህ አይነት ነገር ይታያል በየሜዳው የሚታየው የፕሮቴስታንቱ ጩኸት አንድ አሰቸጋሪ ነገር ሆኖ ሳለ የውስጥ ባንዳው የተሐድሶው ጉዳይ ደግሞ ሌላው ችግር ነው፡፡ በቦታው ተገኝተን እንደተለመከትነው የቅዱስ ጊዮርጊስ ቤተ ክርስቲያን  //ቤት ወጣቶች የሸሸውን ለማምጣት ያለውን ለማበርታት ትጉህና ታታሪ ሆነው ክርስቲያናዊ ግዴታቸውን በአግባቡ እየተወጡ ይገኛሉ፡፡

‹‹እግዚአብሔር ቤተ ክርስቲያንን ይጠብቅልን››


2 comments:

  1. እግዚአብሄር እንዲህ የሚጽፉ እጆችን ያብዛልን!!
    ነገር ግን ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ተክለሃይማኖት 3ኛ እንጅ 2ኛ ፓትርያርክ አይደሉም፡፡ቀዳማዊው አቡነ ባስልዮስ ናቸው፡፡2ኛው ፓትርያርክ አቡነ ቴዎፍሎስ፡፡አቡነ ተ/ሃይማኖት 3ኛ፡፡ስለዚህ ጽሁፉን በዚህ መልኩ አስተካክሉት፡፡ያቀረባችሁልን ታሪክና ወቅታዊ ሁኔታ መልካም ነው፡፡ይልመድባችሁ፡፡

    ReplyDelete
  2. ፈረንጆቹ “ ድመትን በጨለማ ቤት ውስጥ መፈለግ በራሱ አስቸጋሪ ነው፡፡ በተለይ ደግሞ ድመቷ ጥቁር ከሆነች ” ይላሉ፡፡ በአስቸጋሪ ላይ ሌላ አስቸጋሪ ማለት ነው፡፡ በወላይታም እንዲህ አይነት ነገር ይታያል በየሜዳው የሚታየው የፕሮቴስታንቱ ጩኸት አንድ አሰቸጋሪ ነገር ሆኖ ሳለ የውስጥ ባንዳው የተሐድሶው ጉዳይ ደግሞ ሌላው ችግር ነው፡፡ በቦታው ተገኝተን እንደተለመከትነው የቅዱስ ጊዮርጊስ ቤተ ክርስቲያን ሰ/ት/ቤት ወጣቶች የሸሸውን ለማምጣት ያለውን ለማበርታት ትጉህና ታታሪ ሆነው ክርስቲያናዊ ግዴታቸውን በአግባቡ እየተወጡ ይገኛሉ፡፡
    በርቱ ደ/ገነቶች ።መቸም ቢሆን የማይዝል ክድ የማይረታ ኃይል እንዳላችሁ እተማመናለሁ {ገ/ስላሴ ነኝ}

    ReplyDelete