(አንድ አድርገን ግንቦት 23
2005 ዓ.ም)፡- ‹‹ ከምሽቱ 1፤30 ላይ አንድ ሞቅ ያለው የተበሳጨ ጀብራሬ አቡነ ጴጥሮስ ሃውልት ላይ ሽንቱን እየሸና ‹አንተ ድንጋይ ጓደኞችህ ተመችቷቸው
በማርቼዲስ ሲንሸራሸሩ ይህው አንተ ድንጋይ ሆነህ ቀረህ ድንጋይ አሸናብሃለሁ › ሲል በልጅነት ደም ፍላት ዘልዬ ከጀብራሬው
ጋር ግብ ግብ ገጠምኩኝ ፡፡ ድንጋይ አይደለም፡ ‹ድንጋይ ነው› በሚል
በቡጢም ተቃመስን ፡፡ ከስብሰባው የተበተኑ ሰራተኞች ገላገሉንና እየተበሳጨሁ
ቤቴ ገባሁ፡፡ ሌሊቱን አልተኛሁም፡፡ ጴጥሮስ ሕያው ነህ ለማለት ፤
ጴጥሮስ ድንጋይ አይደለም ለማለት ይመስለኛል ‹ጴጥሮስ ያችን ሰዓት› ስጭር አደርኩ ›› ጸጋዬ ገብረ መድህን
ሃሙስ ሚያዚያ 24 ቀን 2004
ዓ.ም ጠዋት ሳተና የሆኑ ወጣቶችና ጎልማሶች የአቡነ ጴጥሮስን ሃውልት
ልክ እንደ አስቸጋሪ ኮርማ በገመድ ጠልፈው አንዳች የሚያህል ክሬነር አስረው ከነበረበት ለመንቀል ደፋ ቀና ይላሉ፡፡
አላፊ አግዳሚው ወጪ ወራጁ እንደ ዘበት እያየ ያልፋል፡፡ ከፊሉም ሞባይሉን አውጥቶ
ፎቶ ሊያነሳ እና ሊቀርጽ ይሞክራል፡፡ ‹‹የሰውየው›› (ሁነኛ ሰው) ሃውልት (የእኛ የእውነተኝነት) ዋቢ ከውስጥ በአቡጀዲ ተጠቅልሎ
፤ ከውጭ በጣውላ ተጠፍንጎ ፤ በብረት ዘንግ ተደግፎ ሊነቀል ትዕዛዝ ይጠብቃል፡፡
የአዲስ አበባ ፖሊሶች ከመርካቶ
፤ ከፒያሳ ፤ ከጊዮርጊስ እና ከወደ አስኮ መስመር የሚመጣውን ሕዝብ እንደ ከብት በንቃት ያግዳሉ ፤ ሰው ወደ አደባባዩ እንዳይቀርብ
፡፡ የመኪናው መጨናነቅ ፤ ከመንገዱ መዘጋትና ከበዓል ዋዜማው ጋር ተዳብሎ ጭንቅንቅ ሆኗል፡፡
አጠቃላይ ሁኔታውን ሲታይ የአንድ ታላቅ ሐዋርያ አርበኛ ሐውልት ሳይሆን የአካባቢው ሰዎች ተሰባስበው
አንድ የፋሲካ ኮርማ ለቅርጫ የሚጥሉ ነው የሚመስለው ፤ ለፋሲካ ነዲያንን ሊመግቡ ፤ ‹ ገመዱን ሳብ አድረገው ወደዛ እንዳታሳልፍ ፤ ሰዎቹን መልሳቸው መኪናው እንዳንይቀሳቀስ ‹‹ ዜሮ አራት እባክህ ከወዲያ
መኪኖችን ዝጋልኝ›› ከፖሊስ መገናኛ የሚደረግ የቃላት ልውውጥ ቅንጅት የሌለው ትርምስምስ….
ወይም ደግሞ የኛ የሀበሾች ሸጋ
አርአያ ፤ ታላቅ የሀገር አርበኛ ፤ ‹‹ለፋሽስት ኢጣልያል ፤ ለጠላት ፤ አልገዛም ፤ አትግዙን ፤ አልንበረከክም እንዳታንበረክኩ
እንኳን እናንተ የሀገሬ ሰዎች ይቅርና መሬቷም እንዳትቀበለው እንዳትገዛ ገዝቻለሁ..›› ብለው ለራሳቸው ጸንተው ወገንን አጽንተው ሕይወታቸውን የሰው ጉምቱ የእግዜር
ሰው መታሰቢያ ሃውልት የሚነሳ ሳይሆን ፤ አንድ ስልስት ከወጣ በኋላ የሚፈርስ የለቅሶ ድንኳን ሥነ ስርዓት ይመስላል፡፡
‹‹ ገመዱን ሳበው ወጥር፤ አላላ
፤ ወርውር ፤ እረባካችሁ ችካሉን ምታ ፤ አታቀላፋ ፤ ..›› ምናን ቃላት ሲሰማ ይህን የሚያህል ብሔራዊ ጉዳይ የእንቶኔን ዕድር
ድንኳን የማፍረስ ያህል ቅልል አለብኝ፡፡ በዚሁም ሀገር እና አስተዳደሯም ጭምር አብሮ ቅልል አለብኝ
፡፡ ሰዎቿም የማታከብር ሀገር ወትሮም ቀላል ነች፡፡
መጀመሪያ ሀውልቱ ባልተነቀለ ፤
ባልተነሳ ፤ ሌላ አማራጭ በተፈለገ ፤ ልክ እንደ ሌሎች ልዕልና ያላቸው ሀገራት የጋራ ማንነት የተገነባባቸው ታሪካዊ ቅርሶች መጠበቅ
፤ መንከባከብ ፤ ግድ ከሆነም አማራጭ ከከፋ ቢያንስ በብሔራዊ የክብር ስነ ስርዓት በአግባቡ ለጊዜው ማንሳት ፤ የተወከሉበትን አላማ
እና ራዕይ ዋጋ መስጠት ፣…እንጂ..
ምናልባት አቡኑ አርበኛ በእኔ ትውልድ
አንዳንድ ወጣቶች ‹ ለጣልያን አድረን ቢሆን ኖሮ ፤ ይህን ጊዜ ሀገር ትለማ ነበር › ብለው እንደሚያስቡት ቅዥት መንግሥትም ስህተት
ሰርቷል ብሎ አቂሞ ይሆን እንዴ? ልማት አደናቃፊ አድርጎ … ‹‹ሕዝቤ ሆይ እግዚአብሔር ብርሐን ነው ፤ ነጭ ነው ፤ ጣልያንም ነጭ ነው ፤ እናም ሐገራችንን ሊያቀና ከእግዚአብሔር
የተላከልንን ፋሽስት ጣሊያን ትቀበሉት ዘንድ ቡራኬዬን ሰጥቻለሁ›› ማለት ነበረባቸው … ባንዳዎች እንዳደረጉት፡፡
‹‹ይህው አንተ ድንጋይ ሆነህ ቀረህ
ድንጋይ አሸናብሃለሁ ገደኞችህ ›› ሲል የጀብራራው ድምጽ ይሰማኛል፡፡ ሃውልቱ ከመሬቱ ከስሪቱ እንደ አሮጌ
አጥር ሲወልቅ ፤ በወቅቱ እና በቦታው የፌደራሉ ባንዲራ የለ ፤ የክልል ባንዲራ የለ ፤ ኢትዮጵያ አርበኞች ተወካዮች የሉም ፤ የኢትዮጵያ
ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን ካህነታ የሉም ፤ የተለያዩ የሃይማኖት አባች የሉም ፤ የሀገር ሽማግሌዎች የሉም ፤ ሰፊው ሕዝብ
የለ ፤ ቄሱም ዝም መጽሀፉም ዝም ፡፡ በቃ ዝም ዝም ‹ ልክ አሮጌ
ቤት እንደሚፈርስ ሁሉ ፤ ትልቅ ጠቀሜታ እና እና እሴት ያለው የእውነት
፤ የታሪክ ፤ የማንነት አሻራ ሲፈርሱ
አፍራሹ አካል የለም ፡፡ የተወከለው ሕዝብም አያውቅም ፤ አያይም አይሰማም፡፡
‹‹አንት ድንጋይ ጓደኞችህ ተመችቷቸው በማርቼዲስ ሲንሸራሸሩ ይህው አንተ ድንጋይ ሆነህ ቀረህ ድንጋይ አሸናብሃለሁ
› እንዲል የጀብራሬው መንፈስ አስተዳር ውስጥ ገብቶ ፤ ጀብራራ መርሃ ግብር ተፈጽሟል፡፡ አቡነ ጣልያን ያቀረበላቸውን ማማለያ ተቀብለው
ቢሆን ኖሮ ፤ እኛም ኢትዮጵውያን የጣሊያን ባሪያ ሆነን ነበር ፤ እርሳቸውም ኢትዮጵያና የጥልያን እህት ቤተ ክርስቲያኖች ፓትርያርክ
ሆነው ፤ ከጣልያን ዘመናዊ አውቶሞቢል መጥቶላቸው ፤ ምናልባትም ዛሬ ሃውልታቸው በቆመበት ቦታ ላይ የፋሽስት ግራዚያኒ ሃውልት ቆሞ
‹‹ ግራዚያኒ አደባባይ›› በመርሴዲስ ፍልስስ ብለው ሊንሸራሸሩ ፤
እና ‹‹ጥልያን የመጣው የኢትዮጵያን ሕዝብ ከድንቁርና ሊያወጣ ነው ፤ ሴቶች በእልልታ ወንዶች በጭብጨባ አንደዜ ተቀበሉት›› ብለው
በየቤተክርስቲያኑ ሊሰብኩ …. ወይ ነዶ ! ሁነኛው ሰው ግን ይህን
አላደረጉትም ፤ አልታለሉም ለእውነት ሲሉ ለሕዝብ ሲሉ ለሀገር ሲሉ
ሕይወታቸውን ከፈሉ፡፡
አሁን ከረፋዱ 4፡30 ሰዓት ሆኗል
፤ ክሬኑ የአቡኑን ሃውልት መነቅነቅ ጀምሯልን፡፡ ልክ አንድ ተራ አጥር የመንቀል ያህል (ይህ ሃውልት ለሚወክለው መንፈሳዊ እና ሞራላዊ እሴት ዋጋ አልተሰጠውም ፡፡ ክሬኑ ሃውልቱን ያማስላል ፤ ነቅነቅ
ነቅነቅ ወዝወዝ ወዝወዝ እያደረገ ከተቀበረበት መሬት ላይ ሥሩ ሥሩ እንዲለቅ የጠነከረውን መሬትን የሟሟሟት ስራ ሂደት ላይ ነው፡፡
5፡40 ሰዓት ላይ ሃውልቱ ተመንግሎ
ወደ ላይ ተንጠለጠለ፡፡ ከዚያም አንድ እንደ ዘንዶ የረዘመና የተነጠፈ
ቆሻሻ ካሚዮን ላይ ደገፍ አድርገው ጫኑት፡፡ ምናልባት መኪናው እንኳን
ታጥቦ ቢቀርብ ፤ ምናልባት ተራ ፊልም ሲመረቅ የሚነጠፍ ቀይ የክብር
ምንጣፍ ቢኖረው ፤ በቃ ምንም የለ ፤ ክብር የለ ፤ ድማሜ የለ ፤
የመንግሥት ተወካይ የለ ፤ከንቲባው የሉ ፤ ካህናቱ የሉ ፤ …የአቶ መለስ ዜናዊ ፎቶ ብቻ ከአስፋልት ማዶ ተሰቅሎ ይታዘባል…
ፋሽስት ጣሊያን የአክሱምን ሃውልታችንን
ሲወስድ የነበረው ስሜት ድባብ ምን ይመስልነበር … (የምታውቁ ግለጹልን).. እኔ ግን አንድ ጣልያን ኢምባሲ በሹፌርነት ይሰራ የነበረ ጓደኛዬ ‹‹ አዲስ አበባ የሚመደቡ የጣሊያን ኢምባሲ ሰዎች በፒያሳ አቡነ ጴጥሮስ ሃውልት አቅራቢያ ፤ በአራዳው ጊዮርጊስ የሚኒልክ ሃውልት አቅራቢያ ፤ በአራት ኪሎ
እና በስድስት ኪሎ ሃውልቶች ዙሪያ ማለፍ አይፈልጉም ፤ አይፈቅዱም ፡፡ ውርደታቸውን ሽንፈታቸውን ህጸጻቸውን ያመላክታቸዋልና፡፡
እነኚህ ሃውልቶች በሆነው መንገድ ይነሳ ዘንድ የጋለ ፍላጎት ነበራቸው ፤ እጃቸውም ረጅም ነው›› ሲል ያወጋኝን አልደብቃችሁም፡፡
እናም ቪቫ ጥልያን ! እዛ በጣልያን
መሬት ለጨፍጫፊው ጄነራል ግራዚያኒ ሃውልት ታቆማለህ ፤ መናፈሻ ትሰይማለህ ፤ እዚህ ለኢ-ፍትሃዊነት አልንበረከክም አትንበርከክ ያሉ የሰማዕቱ ፣መታሰቢያ ሃውልት በልማት ሰበብ እንደ አረም ይነቀላል፡፡ ለግራዚያኒ የቆመለትን ሃውልት ለመቃወም በሃገራቸው አዲስ አበባ የሰማዕታት
ሃውልት የተሰበሰቡ ዜጎች በጅምላ ይታሰራሉ፡፡ ቪቫ ሚኒሊክ በአልክበት ቅላጼ ፤ ቪቫ ጥልያን እላለሁ ፤ አንተ የጎበጠው ታሪክህን ታቃናለህ ፤ እኛ የቀናው ታሪካችንን እንነቅላለን
፤ እናከስማለን፡፡
የአቡነ ሃውልት የሚወክለው ታላቅ
መንፈሳዊ ዕሴት ዋጋ የሚሰጥ መንግሥት ለወራት ከአጠገቡ ጥልቅ ጉድጓድ
ሲቆፍር - ሲነቀንቅ አቧራውን የሚከልል ዳስ እንኳን አልጣለለትም
፡፡ መቼም የዚህን ጉዳት ቀራጺያን የቅርስ ባለሙያዎች እና አርክቴክቶች ዘርዝሩት…
6፡00 ሰዓት ሲሆን አፍራሽ ግብረ
ኃይሉን ማን እንደተቆጣው እንጃ
! ድንገት ሃውልቱን አንጠልጥለው ወደ ነበረበት መሬት በክሬን ምርኩዝት ደገፍ አድርገው አቆሙት፡፡ ለአፍታ እንቅስቃሴያቸው ተገታ፡፡ ምን እንደሆነ ምክንያቱን ተሯሩጠን
ጠየቅን ፤ ሃውልቱ ያለምንም ‹‹ኦፊሲላዊ ሥነ ስርዓት›› እና የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን በቦታው ተገኝታ ቡራኬዋን
አለማስተላለፏ እንዲሁም ሽግሌዎቹ የኢትዮጵያ አርበኞች በቦታው አለመገኝታቸው በፈጠረው ቅራኔ ትዕይንቱ እንዲደገም ተወስኗል አሉን
፤ ልክ እንደ ተውኔት ቴአት…ዘይገርም
‹‹አንት ድንጋይ ጓኞችህ በመርሴዲስ ይምነሸነሻሉ አንተ ግን እዚህ
ሃውልት ሆነህ ቀረህ›› እንዲሉ የሎሬት ጸጋዬ ገብረ መድህን ጀብራሬ፡፡ ይኽው ከዓመታት በኋላ ብዕረኛው ጸጋ ተሸነፈ የጀብራው መንፈስ
እንደ ደመና በአዲስ አበባ ሰማ ላይ ናኝ፡፡
አዲስ አበቤ ምን እየሆነ እንዳለ ፤ ምን እየተደረገ እንዳለ የምታውቅ
አትመስም ፤ ከፊሏ ጾመ ሕማማት ላይ ናት ፤ ሌላዋ የፋሲካ ዶሮ እና ሽንኩርት ታሯሩጣለች
፤ አታክልት ተራ…. ከፊሏ በሌሎች ጉዳዮች ተጠምዳለች፡፡ በመንገድ ላይ ያለችው ቀረብ ብላ ምንድነው? እያለች እንደ መዝናኛ በሞባይሏ
ቀርጻ ታልፋለች ፤ ትላንቷ እየፈረሰ እንዳለ ልብም ያለች አትመስም፡፡
ዘወር ብዬ ባየው ኋላዬን አጣሁት
አወይ
የሰው ነገር….. ነገሬን ናፈቅኩት ዛሬን ሳልኖርበት እንዲል የመሸበት መንገደኛ …
እኩለ ቀን እንዳለፈ የማርሽ ሙዚቃ አባላት በፈጥኖ ደራሽ ቦታው ላይ
ደረሱ፡፡ ቶሎ በነፍስ ድረሱ ተብለው መምጣታቸው ይታወቅባቸዋል ፤ ሱሪ ባንገት ! ቆየት ብሎም የአዲስ አበባ መስተዳደር የበታች
ሃላፊዎች (ክቡር ከንቲባ የሉበትም) ስብስብ በማዘጋጃ ቤት የጓሮ በር ብቅ አሉ፡፡ እንደገና ቆየት ብሎም ካህናቱም ጸሎታቸውን አሳርገው
መጡ፡፡ እናም በፊት ለፊት ገጽ የማታዩት የድጊቱ መራሄ ድርጊት ‹‹ዳይሬክተሮች›› ትዕዛዝ የተጠናቀቀው ክብር የለሽ ትዕይንት እንደገና
ተደገመ፡፡
እናም ስድስት ሜትር ከሃያ አምስት የሚረዝመው የእምነበረድ ሃውልት
፤ ዘጠኝ ነጥብ ሶስት ቶን የሚመዝው ንቅል ሃውልት ከነ ወጥ ፍልፍል ድንጋይ መሠረቱ እንደገና ሲነሳ ተጨበጨበ ፤ ጭብጨባ .. ጭብጨባ
… ግርማ ሞገስ የሌለው ጭብጨባ… ማርሽ ሙዚቀኞች ‹‹ሞቅ አደረጉት›› ድድድው..ድድድው… ድድድ…
ኡፍ..
አዚህ ላይ የጂጂ ስንኝ ትዝ አለኝ
ትናገር አድዋ
አድዋ ዛሬ ናት አድዋ ትላንት
መቼ ተነሱና የወዳደቁት
ምስጋና ለእነሱ የአድዋ ጀግኖች…
ለዛሬ ነጻነት ላበቁኝ ወገኖች..
የተሰጠኝ ሕይወት ዛሬ በነጻነት
ሰው ተከፍሎበታል ከደምና ከአጥንት
እናም የእኛ እውነትን ፤ ታማኝነትን ፤ ሀገር-ሕዝብ ወዳድነትን ፤
በኑሯቸው ሕይወታቸውን ከፍለው ያስተማሩን ባለታሪክ የአቡነ ጴጥሮስ መታሰቢያ ሃውልት እደ አረም ተነቅሎ ፤ እንደዋዛ ፤ እንደዘበት
፤ በፒያሳ አድርጎ በአራት ኪሎ አድርጎ ወደ ብሔራዊ ሙዚየም አመራ፡፡ በዚያው አረፈ… እዚያስ እንዴት ይሆን መክረሚያው ማን ያውቃል….?
በጌታቸው ወርቁ
በስተመጨረሻ የሎሬት ጸጋዬ ገብረመድህን
ጀብራሬ ከኢህአዴግ ጋር ተመሳሰሉብኝ…..
ከ‹‹አንድ አድርገን››
የአቡነ ጴጥሮስ ነገር ከተነሳ አይቀር
ስለ አክሱም በእድሜያችን ያየነውን ነገር ለመናገር ግድ አለኝ ፤ እንደ ነገሩ ድግሪዬን የጨረስኩት ከሀረማያ ዩኒቨርሲቲ ነበር ፤
ሀረማያ ወደ ሀረር ሲሄዱ ከ20 ኪሎሜትሮች በፊት ትገኛለች ፤ ሃረማያ ብዙ ነገሮችን የያዘች ቦታ ነች ፤ በጣልያን ጊዜ የአክሱም
ሃውልት እንዴት እንደተወሰደ መረጃ ከፈለጉ ወደ ቦታው ማምራት ብቻ በቂ መሆኑን ልነግርዎት እፈልጋለሁ ፤ በጊዜው በ1929 ዓ.ም
ገደማ ከጣልያም አንድም ለጦርነት አንድም ነዳጅ ለማውጣት በግዳጅ
ከመጡ ሰዎች አንዱ የጆርጅ አባት አንዱ ናቸው፡፡ ጆርጅ ማለት ከአለማያ ከተማ ወደ ሃረማያ ዩኒቨርሲቲ ሲሄዱ መሃል ቦታ ላይ ትልቅ
ጋራጅ ያለው ትውልደ ጣልያናዊ ነው ፤ የተወለደው እዚህው ኢትዮጵያ ውስጥ ቢሆንም ሙሉ ነገር ከአባቱ መውረስ ችሎ ነበር ፤ እኔም
የጣልያን ሃውልት እንዴት ከኢትዮጵያ እንደወጣ ያወኩት ከጆርጅ አማካኝነት ነው ፤ በጊዜው ጆርጅ የሚነግረኝ ሁሉ ተረት መስሎኝ ነበር
ነገር ግን የሚያወራኝ ከፎቶ ጋር የተገናዘበ መሆኑን ስለገለጸልኝ በአይኔም ስለተመለከትኩኝ ላምነው ችያለሁ ፤ የአክሱም ሃውልት
ከኢትዮጰያ የወጣው በአንድ ምሽት አማካኝት መሆኑን ግልጽ አድርጎ አስረድቶኛል ፤ የአክሱም አካባቢ ሕዝብ ማታ ያየውን ሃውልት ጠዋት
ሲነጋ ማየት አልቻለም ነበር ፤ ሃውልቱ ተነቅሎ መንገድ ጀምሮ ነበር ፤ መንገዱም በመረብ ወንዝ አድርጎ እሱን መሸከም የሚችል መርከብ
በቀይ ባሕር ይጠብቀው ነበር ፤ እኛ በዘመናችን በአውሮፕላን የተመለሰልንን
፤ ጠቅላይ ሚኒትር አቶ መለስ ዜናዊ ‹‹ አክሱም ለጋምቤላ ምኑ ነው፣…›› ያሉትን ሃውልት በምን አይነት መኪና እንደወጣ
ማስረጃውን በአይኔ ልመለከት ችያለሁ ፤ እኔ ያየሁትን ግን የኢትዮጵያ ባሕልና ቱሪዝም ሚኒስቴር ወይም ሌላው ጉዳዩ ይመለከተኛል
ያለው ተቋም ማስረጃው እጁ ላይ ያለ አይመስለኝም ፤ የአክሱም ሃውልት ከኢትዮጵያ ሲወጣ ቀኑ ሰዓቱ እና መርሃ ግብሩ ቀድሞ በጣሊያኖች የተጠነሰሰ ነበር፡፡ ሃውልቱም ምን ያህል ኪሎ እንደሚመዝን ተገምቶ ስንትም
ቦታ መከፈል እንዳለበት ተሰልቶ ፤ መኪናም ተዘጋጅቶለት ነበር ፤ የተጫነበትም መኪና ፎቶዎች እኛ በታሪክ ባናውቀውም በእነ ጆርጅ
ቤት ውስጥ በምድረ አለማያ በባቲ ከተማ ውስጥ ይገኛል ፤ ከዚህ በተጨማሪ
የጣልያኑ ወታደር የነዳጅ አውጪ ባለሙያ እና የመኪኖች ጥገና ባለሙያ ልጅ ጆርጅ ለታሪክ ተመራማሪዎች የሚጠቅሙ በርካታ የኢትዮጵያም
ይሁን የአለም መረጃዎች ቤቱ ውስጥ ይገኛሉ፡፡ የሁለተኛው ዓለምን ጦርነት የተመለከተ 12 ጥራዝ ያለው መጻህፍትም ተመልክቻለሁ….
ለማንኛውም ይሆናልን ትተት ነበር ብለን በልበ ሙሉነት መናገር ያስችለን ዘንድ ስለ አክሱም ሃውልት አወሳሰድ በፎቶ የተደገፈ ማስረጃ
፤ በወቅቱ ስለተጀመረው የኦጋዴን አካባቢ የነዳጅ ጉዳይ ፤ እና መሰል ታሪካችንን በሃረማያ በባቲ ወረዳ በአንድ ቤት ውስጥ ይገኛሉ…. ይህን ሁሉ የኋላ ታሪኬን ያሳየኝ እና የነገረኝ ጆርጅ ከዚህ አለም በሞት መለየቱን በቅርብ ሰምቻለሁ…
እሱ ቢለይም ልጆቹ ጋር ጥቂት ነገሮች ይኖራሉ ብዬ አስባለሁ…… ይህን
ሰነድ ባገኝው ለትውልድ አስቀምጣለሁ ይጠቅመኛልም ያለ ወደ ቦታው ቢያመራ ጆርጅ በህይወት ቢያልፍም ትንሽ ለታሪካችን ጭማሪ የሚሆን
ነገር ያጣል ብዬ አልገምትም፡፡
ቸር ሰንብቱ
No comments:
Post a Comment