በሠዓሊ አምሳሉ ገ/ኪዳን አርጋው
(አንድ አድርገን ግንቦት 16 2005
ዓ.ም)፡- በነገረ ሃይማኖት ውስጥ እስከ አሁን ድረስ ሆኖ እንዳየነው፣ እንደሚያታወቀው፣ እየሆነም እንደምናየው ከባለቤቱ ከመድኀኔዓለም
ክርስቶስ አንሥቶ መትሕተ ፈጣሪ መልዕልተ ፍጡራን በሆነችው በቅድስት ድንግል ጽዮን ማርያም፣ በቅዱሳን መላእክት፣ በአበው ጻድቃን
ሰማዕታት /ቅዱሳን/ በሁሉም ላይ ክሕደት ወይም ኑፋቄ ያልተነሣበት ማንም የለም፡፡ በወላዲተ አምላክ ላይም ከሚነሡ ኑፋቄዎች ሁሉ
የከፋውና ከባዱ ኑፋቄ ደግሞ ይህ ከላይ በርእስ የተጠቀሰው የኑፋቄ ወይም የክሕደት ዓይነት ነው፡፡ ክሕደት ወደነው አይመጣም በቦታና
በጊዜም አይወሰንም፡፡ አሳች ሰይጣን እስካለ ጊዜ ድረስም ይቀጥላል፡፡ የሥጋ ሞት ለሰው ልጆች ሁል ጊዜ እንግዳ እንደሆነ ሁሉ የነፍስ
ሞት ኑፋቄ ወይም ክሕደት ደግሞ ሁል ጊዜ እንግዳ ነው፡፡
ምንም እንኳን ክሕደት ወይም ኑፋቄ
በየዓይነቱ እንደሚነሡ እንደሚመጡ ከክርስቶስ ጀምሮ ደቀ መዛሙርትም በወንጌልና በየመልእክቶቻቸው አስቀድመው ያስጠነቀቁና ያሳሰቡ
ቢሆንም ጉዳዩ በቅዱሳት መጻሕፍት በግልጽ ይቀመጥም አይቀመጥ ኑፋቄ ወይም ክሕደት ያልተነሣበት የጉዳይ ዓይነትም የለም፡፡ የእግዚአብሔር
ቃል ወይም መጽሐፍ ቅዱስ በቁሙ የምሥጢር መጽሐፍ እንደሆነ ይታወቃል፡፡ ሲናገርም በቀጥታ ግልጽ ባለ ቋንቋ ከመናገር ይልቅ በምሳሌ
ማስረዳትን ይመርጣል፡፡ ወንጌልን ስናነብ ማለትም የጌታን ትምህርት ያየን እንደሆነ ያለ ምሳሌና ምሥጢር የተናገረው ቃል የለም ማለት
ይቻላል፡፡ አስቀድሞ ‹‹አፌን በምሳሌ እከፍታለሁ›› ተብሎ ተጽፏልና፡፡
ይህ ያነሣነው ርእሰ ጉዳይም እንደ
ሌሎቹ ዋና ዋና ጉዳዮች ሁሉ ከጆሮ ይልቅ ለልብ ከተተው ነገረ ሃይማኖቶች አንዱ ነው፡፡ ይህም በመሆኑ ሰዎች ሲሰነካከሉበትና ሲወድቁበት
ይታያል፡፡ ምንም ቢሆን ግን ቅንና ንጹሕ ልብ ያላቸው ሰዎች ምሥጢሩ የቱንም ያህል የተሠወረ ቢሆንም የተሠወረው ለሚጠፉት እንጂ
ለሚድኑት አይደለምና ንጹሕና ቅን ልባቸው እየተመሩ ከመሠናከል ይድናሉ ይተርፋሉ፡፡ጠማማውን ክፉውንና የድፍረቱን መንገድ ከመምረጥ
ይታቀባሉ፡፡
አሁን ችግሩ ያለው ክፉ፣ አኬተኛ፣
ጠማማ፣ ዐመጸኛና ዕቡይ ልብ ባለው ሰው ላይ ነው፡፡ እንዲህ ዓይነት ልብ ያለው ሰው ደግሞ ምንም እንኳን ጉዳዩ በበቂ ደረጃ በግልጽ
የተጻፈና የተነገረ ጉዳይ ቢሆንም ጠማማ አኬተኛና ዐመፀኛ ልብ ያለው ሰው ከክፋቱና ከጥመቱ ከዐመፃውም የተነሣ ቀና ቀና ነገር አይታሰበውምና
አማን በአማን ብሎ ለመቀበል ወይም ለማመን ይሳነዋል፡፡ ስለሆነም ጉዳዩ ያለው ነገረ ሃይማኖቱ በግልጽ በመጻፉና ባለመጻፉ ላይ ሳይሆን
የልባችን ቀናነት ወይም ጠማማነት፣ ደግነት ወይም ክፉነት፣ ትሁትነት ወይም ዐመፀኛነት፣ አማኝነት ወይም ተጠራጣሪነት ላይ ነው፡፡
ጻድቅ፣ ቅን፣ ትኁትና ንጹሕ ልብ ያለው ማንኛውም ክርስቲያን የተማረም ይሁን ያልተማረ እንኳንና በወላዲተ አምላክ ላይ ይቅርና በማንም
ሰው ላይ የሚያጎድፍ ነገር ማድረግ አይቻለውም፡፡ ክፉ ዐመፀኛና ጠማማ ልብ ያለው ሰው ደግሞ እንኳንና ቅዱሳኑን ባለቤቱን ልዑል
እግዚብሔርን ከመዝለፍ፣ ከመንቀፍ፣ ከመተቸት ጨርሶም ከመካድ ወደ ኋላ እንደማይል ታዝበናል ተመልክተናልም፡፡
አሁን ለዚህ ኑፋቄ በተለመደው መንገድ
እንዴ ምን ነው? ጠቢቡ ሰሎሞን መኀ.4፥12 ‹‹ወዳጄ ሆይ ሁለንተናሽ ውብ ነው ነውርም የለብሽም፡፡›› በመኀልየ መኀልይ ወይም
የመዝሙሮች መዝሙር በሆነው መዝሙሩ እንዲያ ያወደሳትና ያመሰገናት ማንን ሆነና ፣ንጽሕናዋን ሲናገር እኮ ነው፤ ጥንተ አብሶ ወይም
የውርስ ኀጢአት እንደሌለባት ሲናገር አይደለም እንዴ?እሺ ይሄ ማለት ካልሆነ ሌላ ታዲያ ምን ማለት ነው?፡፡ ቀጥሎም እኅቴ ሙሽራዬ
የተቆለፈ ገነት የተዘጋ ምንጭ የታተመ ፈሳሽ ናት፡፡›› መኃ. 4 ፥ 7 ብሎ ያወደሳት ማንን ሆነና? ኧረ ለመሆኑ ከአምላክ እናት
በላይ ማን ኖሮ ጠቢቡ ለሌላ ለማን እንዲህ ዓይነት ቅኔና መዝሙር ይቀኛልና ነው ለእሷ እንዳልሆነ የምታስቡት? እሺ ለእሷ ካልሆነ
በሉ ሌላ ለማን? ጥቀሱልን?
ልበ አምላክ ዳዊትም በመዝ.44፥9
ላይ ‹‹በወርቅ ልብስ ተጎናጽፋ ንግሥቲቱ በቀኝህ ትቆማለች፤ ልጄ ሆይ ስሚ እዪ ጀሮሽንም አዘንብይ፤ ወገንሽንም የአባትሽንም ቤት
እርሽ፤ ንጉሥ ውበትሽን ወዷልና፤ እርሱ ጌታሽ ነውና፡፡›› ብሎ ስለ ድንግል ስለ ወላዲተ አምላክ ከተናገረው ጥቅስ ላይ “ወገንሽን
የአባትሽንም ቤት እርሺ” ማለቱ ምን ማለት ነው?፡፡ ይሄን ማለቱ እኮ አንቺ ከወገኖችሽ የተለየሽ ነሽ ወይም ከአዳምና ከሔዋን ጀምሮ
በዘር የሚተላለፈው የውርስ ኃጢአት ወይም ጥንተ አብሶ የለብሽም ከዚያ ጠብቆሻል፣ ለይቶሻል ፣ አንጽቶሻል(ከጉድፈት በኋላ ሳይሆን ሳትጎድፍ አስቀድሞ
ከመጉደፍ አነጻት)ሰውሮሻል፣ ታድጎሻል፣ ማለቱ አይደለምን ?፡፡ ይሄን ማለቱ ካልሆነ ወገንሽን የአባትሽንም ቤት እርሽ ማለት ታዲያ
ምን ማለት ነው? እንዲህ ዓይነቱን ምሥጢር መረዳት ካልቻላቹህማ ምኑን የእግዚአብሔርን ቃል(መጽሐፍ ቅዱስን) ተረዳቹሁት? ቃሉስ
ምኑን ሕይወት ሆናቹህ? እያልኩ መልስ ከመስጠት ይልቅ ምንም እንኳ ቃሉ ማለዳ ማለዳ ሁሌም አዲስ ቢሆንም ትንሽ ለየት ባለ መንገድ
ነገሩን ለማሳየት መሞከሩን መርጫለሁ፡፡ ይህ ኑፋቄ ያለባቸው ሰዎች በአምላክ እናት ላይ ጥንተ አብሶ ስለመኖሩ የሚናገር ወይም የሚያረጋግጥላቸው
ጥቅስ ከመጽሐፍ ቅዱስ አንዲትም እንኳ የለም፡፡ በጣም የሚገርመው ነገር እውነቱ እንዲህ በሆነበት ሁኔታ ከየት አምጥተው የአምላክን
እናት ጥንተ አብሶ አለባት እንደሚሉ ነው፡፡ ያው ቀደም ሲል እንደገለጽኩት ከእኪተኛው ልቦናቸው አፍልቀው መሆኑ ነው፡፡
እንደዚህ ዓይነት ኑፋቄ ያለባቸው ሰዎች የሚጠቅሱት አንድ ሌላ ቃል አለ ሳይገባቸውና
ተሠውሮባቸው፡፡ እሱ ምንድ ነው? ቅዱስ ያሬድ በድርሰቱ “አንጺሖ ሥጋሀ ኀደረ ላዕሌሃ” ሥጋዋን አንጽቶ አደረባት ብሏል እና ይሄን
ማለቱ ጥንተ አብሶ አለባት ማለቱ ነው ብለው ለራሳቸው በመተርጎም የክሕደት ማጥ ውስጥ ተነከሩ፡፡ እውነቱ ግን እንዲህ አይደለም፡፡
ልዑል እግዚአብሔር የሰውን ልጅ የፈጠረ አንድ ጊዜ ነው፡፡ እሱም አዳምን በፈጠረባት ጊዜ፤ አባታችን አዳምን ከአራቱ ባሕርያተ ሥጋና
ከሦስቱ ባሕርያተ ነፍስ ፈጥሮታል፡፡ ከዚያ በኋላ ግን ሔዋንን ከአጥንቱ ከአዳም አጥንት፤ ሌሎቻችንን ደግሞ ከአብራኩ ከአዳም አብራክ
ከሔዋን ማሕፀን በክሂሎቱ በፈቃዱ ፈጥሮናል ይፈጥራልም፡፡ ከአዳም ሌላ ማለትም ከአዳም ውጭ ከላይ ከገለጽኩት መንገድ ውጭ የፈጠረው
የሰው ዘር የለም ሁሉም የለበሰው የአዳምን ሥጋ ነው፡፡ የአዳም ሥጋ ደግሞ ወይም እስከ ድንግል ያለው የሰው ዘር በአዳም በደል
ምክንያት ሁሉ የውርስ ኀጢአት የሰለጠነበት ነው፡፡ ወላዲተ አምላክም የአዳም ልጅ እንደመሆኗ መጠን እንደ ሌሎቹ የአዳም ልጆች ሁሉ
ያ የውርስ ኀጢአት ሊኖርባት ይችል ነበረና የአዳም ልጅ በመሆን ወይም ጥንተ አብሶ ያለበትን የአዳምን ዘር ሥጋ በመልበስ ወይም
ከእርሱ ዘር በመወለድ ብቻ ከሚወረስ የውርስ ኃጢአት ወይም ጥንተ አብሶ አንጽቶ ወይም ጠብቆ ወይም ታድጎ ወይም አድኖ አደረባት
ለማለት አንጺሖ አለ እንጂ ያደፈ ሆኖ ኖሮ ያንን ያደፈውን አንጽቶ አደረባት ለማለት አይደለም፡፡
አሁን ይህች ቃል አንጺሖ የምትለዋ
ቃል ጥሩና እንዲህ ያለ ኑፋቄ ወይም ክሕደት ካለባቸው ሰዎች ጋርም ልታግባባን ወይም ልታስታርቀን የምትችለው ቃልም እሷው ራሷ ናት፡፡
አንጺሖ ሲል አንጽቶ ማለቱ ነው፣ ትክክል ነው፣ ያግባባናል፡፡ ቁም ነገሩ ያለው እዚህ ላይ ነው፡፡ እንዳነጻት ካወቁ ልዑል እግዚአብሔር
ንጹሕ አካሏን ፈልጎታል፡፡ ሽቶታል ማለት ነው፡፡ ንጹሕ አካሏን ከፈለገው ደግሞ ቀድሞውን እግዚብሔር አንዲያድፍ ወይም እንዲጎድፍ
የሚተወው ወይም የፈለገው ስለምንድን ነው? የአምላክ ከወላዲተ አምላክ መወለድ እንደ እንግዳ ደራሽ እንደ ውኃ ፈሳሽ እንዳልሆነ
ይታወቃል፡፡ ዓለም ሳይፈጠር ገና በአምላክ ልቦና ታስባ ትኖር ነበርና ወይም ደግሞ በሰው ሰውኛው ገና ለአዳም በአምስት ቀን ተኩል
ከልጅ ልጅህ ተወልጄ አድንሃለሁ ብሎ ቃል ኪዳን ከገባለት ጊዜ ጀምሮ ከእርሷ እንደሚወለድ የሚታወቅ ነገር ነበር፡፡ ይህ ማለት ደግሞ
አምላክ ከድንግል የመወለዱ ነገር ድንገት የሆነ ነገር አይደለም ማለት ነው፡፡ በመሆኑም እግዚአብሔር ከድንግል መወለዱ በድንገት
ካልሆነ ማደሪያውን በኋላ ሊያነጻት ነገር እስኪያድፍ እስኪጎድፍ የሚጠብቅበት ምን ምክንያት አለው? ለማንጻት ለማንጻት ቀድሞውንም
ገና ሳያድፍ እንዳያነጻት ምን ይከለክለዋል? ከእርሷ እንደሚወለድ አስቀድሞ እንደማወቁ መጠን ማደሪያውን ሁለነገሯን አዘጋጅቶ፣ አሰናድቶና
አንጽቶ ማለትም ቀድሞ ከነበረው ሰው በመሆን ብቻ ከሚታደፍበት ልማድ አንጽቶ ሰዓቱ ሲደርስ አድሮባታል ከሥጋዋ ሥጋ ከነፍሷ ነፍስን
ነስቶ ተወልዶባታል፡፡ ነቢየ እግዚአብሔር ኢሳይያስ 1፥9 ‹‹የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር ዘርን ባያስቀርልን ኖሮ እንደ ሰዶም በሆንን
እንደ ገሞራም በመሰልን ነበር፡፡›› ያለው ለዚህ ነው፡፡ ከዚያ የውርስ ኀጢአት ነጻ የሆነች ወይም የነጻችና ለእርሱ ማደሪያነት
የበቃች የተገባች ዘርን ባያስቀርልን ኖሮ አምላክም አይወለድም ነበር፡፡ እርሱ ባይወለድ ኖሮ ደግሞ እጣ ፋንታችን ዕድል ተርታችን
ሰዶምና ገሞራን መሆን ነበር፤ ማለቱ ነው፡፡ “ልዑል ማደሪያውን ቀደሰ” ያለው ቅዱስ ዳዊትም ከዚህ ተነሥቶ ነው፡፡ መዝ.45፥4
በመሆኑም የአምላክ ሰው መሆን እንደ
እንግዳ ደራሽ፣ እንደ ውኃ ፈሳሽ ካልሆነ፤ እግዚአብሔር በባሕርይው ንጹሕ ነውና ንጹሕ ነገርን ይወዳል ወይም ንጹሕ ነገርን ነው
የሚወደው ካልን፤ እግዚአብሔር እንደፈጣሪነቱ በሁሉም ነገር ላይ ሁሉንም ነገር የማድረግ ሥልጣን ኃይልና ችሎታ አለው ካልን ማለትም
በአዳም ልጆች ላይ በዘር በሚተላለፈው በውርስ ኃጢአት ወይም በጥንተ አብሶ ላይ ጭምር ያሻውን የማድረግ ሥልጣን አለው ካልን፡፡
የድንግልን ሥጋ በኋላ ሊወለድባት ወይም ሊያድርባት ሲል ሊያነጻው ነገር እስኪያድፍ የሚጠብቅበት ምን ምክንያት አለው? አድፎ ከሚነጻ
ሰውነት ይልቅ ከጅምሩ የነጻ ወይም ያላደፈ ሰውነት እንደሚሻለው ስለማያውቅ ወይም የሚሻለውን የማያውቅ ነው ማለታቸው ይሆንን? ወይስ
ልዑል እግዚአብሔር በጥንተ አብሶ ላይ ምንም የማድረግ ኃይልና ሥልጣን የለውም ማለታቸው? እኛስ አምላካችን ስሙ ለዘለዓለም የከበረ
የተመሰገነ ይሁንና ንጹሐ ባሕርይ እንደመሆኑ መጠን ፍጹም ንጹሕ የሆነ ነገርን ይወዳልና አሁንም ክብር ምስጋና ይግባውና ፍጹም ንጹሕ
ቅዱስ አድርጎ ባዘጋጀው በድንግል ሥጋ ላይ ያደረ ወይም የተወለደ ነው፡፡ የእኛስ አምላካችን በውርስ ኃጢአት ወይም ጥንተ አብሶን
ጨምሮ የሚቀር ነገር ሳይኖር በሁሉም ነገር ላይ ፍጹም ሥልጣን ያለው አምላክ ነው ያለን፡፡ እናቱ ቅድስት ድንግል ጽዮን ማርያምም
ክብር ምስጋና ይግባትና የኛስ እናታችን ምንም ምክንያት እንከን የሌለባት ፍጹም ንጽሕት ቅድስት ናት፡፡
እግዚአብሔርን እንደ እግዚአብሔርነቱ
የሚያውቅ፣ የሚያምን የሚረዳ ማለትም ከስፋቱ እሰከ ጥልቀቱ ፣ ከግዝፈቱ እስከ ርቀቱ እንዲህ ነው ብለን ልንገልጸው የማንችለውን
ይህንን የምናየውና የማናየው የምናውቀውና የማናውቀው ዓለማት ሁሉ የእጁ ሥራ የሆነ ወይም የፈጠረና ፈጥሮ የሚገዛ፣ ለኃያልነቱ ምሳሌ
የሌለው፣ እንዲህ ነው ተብሎ ሊነገር ሊገለጽ የማይቻል፣ ጅማሬና ፍጻሜ የሌለው፣ ፍጹም ገናና፣ ፍጹም ክቡር፣ ለኀይላት፣ ለሥልጣናት፣
ለመናፍስትም ፍጹም አስፈሪና አስደንጋጭ የሆነ አምላክ መሆኑን የሚያውቅ፣ የሚያምንና የሚረዳ ክርስቲያናዊ ልቦና ወይም ኅሊና ያለው
ሰውና ይህም አምላክ ከቅድስት ድንግል ማርያም እንደተወለደ የሚያምን የሚቀበል ሰው ለእርሱ ማደሪያነት የምትገባው ደግሞ ምን ያህል
የንጽሕናዋ ነገር ሊናገሩት የማይቻል፣ ቅድስናዋ ወደር የሌለው ልትሆን እንደምትችል ወይም እንደሚገባትና እርሱ እራሱም ለመለኮታዊ
ክብሩና ንጽሕናው ሲል በዚህ ደረጃ እንደሚያዘጋጃት ምንም ዓይነት ምስክር ሳያሻው ከቅን፣ ትኁት፣ ንጹሕና ጻድቅ ልቦናው ተረድቶ
ያምናል ይቀበላል፡፡
እመቤታችንን በጥንተ አብሶ ወይም
በውርስ ኃጢአት የሚጠረጥር ሰው በእርግጠኝነት እግዚአብሔርን እንደ እግዚአብሔርነቱ አያውቀውም አያምነውምም፡፡ በመሆኑም በውጭ ካሉት
መናፍቃን እስከ ውስጥ ካሉት ከሐዲያን ልብሳቸውና ቆባቸው እንጂ ልባቸው ክርስቲያን ያልሆነ ያልጰጰሰ ወይም ያልመነኮሰ፣ ቆዳቸው
እንጂ ልባቸው ያልተቀባ፣ ሳይጠሩ የመጡ፣ ሰይጣን ለተልእኮው ያስገባቸው፣ የዲያብሎስ የግብር ልጆች እንደሆኑ ቅዱሱ ሐዋርያ ዮሐንስ
በራዕዩ ተናግሯል “እግዚአብሔርንም ለመሳደብ፣ ስሙንና ማደሪያውንም፣ በሰማይ የሚያድሩትን ሊሳደብ አፉን ከፈተ” ራዕ.13፥6
‹‹ዘንዶውም ወደ ምድር እንደ ተጣለ ባየ ጊዜ ወንድ ልጅ የወለደችውን ሴት
አሳደዳት ከእባቡም ፊት ርቃ አንድ ዘመን ዘመናትም የዘመንም እኩሌታ ወደ ምትመገብበት ወደ ሥፍራዋ ወደ በረሀ እንድትበር ለሴቲቱ
ሁለት የታላቁ ንሥር ክንፎች ተሰጣት እባቡም ሴቲቱ በወንዝ እንድትወሰድ ሊያደርግ ወንዝ የሚያህልን ውኃ ከአፉ በስተኋላዋ አፈሰሰ፡፡
ምድሪቱም ሴቲቱን እረዳቻት፤ ምድሪቱም አፏን ከፍታ ዘንዶው ከአፉ ያፈሰሰውን ወንዝ ዋጠችው ዘንዶውም በሴቲቱ ላይ ተቆጥቶ የእግዚብሔርን
ትእዛዛት የሚጠብቁትን፣ የኢየሱስም ምስክር ያላቸውን፣ ከዘርዋ የቀሩትን ሊዋጋ ሔደ፡፡ በባሕርም አሸዋ ላይ ቆመ” ዩሐ ራእ
12÷13-18 ክርስቲያኖችና መናፍቃንም ይህ ጥቅስ ለማን አንደተነገረ ያለ ልዩነት ይስማማሉ ወይም ስለ ወላዲተ አምላክና ስለ አማኑኤል
እንደሆነ ያምናሉና የሚያነታርከን ነገር አይኖርም ማለት ነው፡፡ እንዲህ ከሆነ ዘንዳ የጥቅሱን ትርጉም በስሱ እንይ፡-
ዘንዶ የተባለው በጊዜው አንድ ልጇን
ሊገልባት ሲያሳድዳት የነበረው ሄሮድስ ሲሆን ፍጻሜው ግን በሰው ልጆች ልቦና ላይ እንክርዳድ ወይም ክሕደት ኑፋቄ የሚዘራ ዲያብሎስ
ነው፡፡ ‹‹እባቡም ሴቲቱ በወንዝ እንድትወሰድ ሊያደርግ ወንዝ የሚያህልን ውኃ ከአፉ በስተኋላዋ አፈሰሰ፡፡›› ይህም ማለት በጊዜው
ድንግል ልጇን ሰይጣን ካደረበት ከሄሮድስ ሠይፍ ለማትረፍ በረሃውን አቋረጣ ወደ ግብጽ በተሰደደች ጊዜ ሰይጣን አድሮበት የሚያሠራው
ሄሮድስ ያደረሰባትን መከራ ሲናገር ነው፡፡ ፍጻሜው ግን እባቡም ወይም ዘንዶውም ሴቲቱ በወንዝ እንድትወሰድ ሊያደርግ ወንዝ የሚያህልን
ውኃ ከአፉ በስተኋላዋ አፈሰሰ ማለት ዲያብሎስ በመናፍቃን አንደበት አድሮ በቅድስተ ቅዱሳን ላይ የክሕደት፣ የኑፋቄ፣ የንቀት፣ የዘለፋና
የስድብ ቃልን አፈሰሰ አወጣ ተናገረ ማለት ነው፡፡ “ምድሪቱም ሴቲቱን እረዳቻት ምድሪቱም አፍዋን ከፍታ ዘንዶው ከአፉ ያፈሰሰውን
ወንዝ ዋጠችው” በጊዜው ሄሮድስ ሕፃኑን ይዞ ለመግደል ያሳድዷት የነበሩትን የሄሮድስን ሠራዊት እርሷን ለመያዝ በሚያሳድዷት ጊዜ
ግዑዛን ሣር ቅጠሉ ሁሉ ለፈጣሪው ለአማኑኤልና ለእናቱ ተገን እንደሆነ፤ ለሄሮድስ ሠራዊት ግን ጣርና ጋር እንዳበዛባቸውና ከዚህም
የተነሣ ሊይዟቸው እንዳልቻሉ ሲናገር ሲሆን ፍጻሜው ደግሞ ምድሪቱም ሴቲቱን እረዳቻት አፍዋን ከፍታ ዘንዶው ከአፉ ያፈሰሰውን ወንዝ
ዋጠችው ማለት ምድር የተባለው የሰው ልጆችን ማለትም ምዕመናንን ነው፡፡ ዘንዶው በመናፍቃን ልቦናና አንደበት አድሮ የሚያፈሰውን
የስድብ፣ የዘለፋ፣ የክሕደትና የኑፋቄ ቃል ምዕመናን ሰምተው እንዳልሰሙ በልቦናቸው ሳያሳድሩ ንቀው በማለፍና በኑፋቄው ባለመሰናከል
ባለመውደቅና ባለመመረዝ ቅድስት ድንግል ማርያምን የሚገባትን ያህል ክብር በመስጠት የዘንዶውን ድካም ከንቱ ያደርጋሉና፡፡ “ዘንዶውም
በሴቲቱ ላይ ተቆጥቶ የእግዚአብሔርን ትእዛዛት የሚጠብቁትን፣ የኢየሱስም ምስክር ያላቸውን፣ ከዘርዋ የቀሩትን ሊዋጋ ሄደ በባሕርም
አሸዋ ላይ ቆመ” ዘንዶውም በሴቲቱ ላይ ተቆጥቶ ማለት ድንግል ከአምላክ በተሰጣት የማማለድ፣ የማስታረቅ፣ የመራዳት ጸጋና በረከት
በልጇ ስም አምነው የተጠመቁትን ክርስቲያኖችን ወይም ምእመናንን ትራዳለችና፣ ትደግፋለችና፣ ታነሣለችና፡፡ በዚህ አገልግሎቷ ዲያብሎስ
ተቆጥቶ “የእግዚአብሔርን ትእዛዛት የሚጠብቁትን” አለ የአንዲቱ ቤተ ክርስቲያን ልጆች ዐሥርቱ ትእዛዛትን፣ ስድስቱ ቃላተ ወንጌልን
ሳይለዩ ሳይነጥሉ ይጠብቃሉና፤ “የጌታ ኢየሱስም ምስክር ያላቸውን” አለ ‹‹በሰማያት ያለውን የአባቴን ፈቃድ የሚያደርግ እንጂ ጌታ
ሆይ ጌታ ሆይ የሚለኝ ሁሉ መንግሥተ ሰማያት የሚገባ አይደለም፡፡ በዚያ ቀን ብዙዎች ጌታ ሆይ ጌታ ሆይ በስምህ ትንቢት አልተናገርንምን
በስምህስ አጋንንትን አላወጣንምን በስምህ ብዙ ተአምራትን አላደረግንምን ይሉኛል፡፡ የዚያን ጊዜም ከቶ አላውቃችሁም እናንተ ዓመፀኞች
ከእኔ ራቁ ብየ እመሰክርባቸዋለሁ፡፡›› አለ ጌታ በወንጌል ማቴ.7፥21-23፡፡ስሙን ከጠሩ ከዚያም አልፈው በስሙ ተአምራትን የሚያደርጉትን
እንዴት አላውቃቹህም ይላቸዋል ያልን እንደሆነ ዛሬ ክርስትና ሃይማኖት ነኝ የሚለው ቁጥሩ ከ30 ሽህ ካለፈ ቆይቷል ይሄ ሁሉ ጌታ
ሆይ ጌታ ሆይ ባይ ነው ከዚህ ሁሉ ሃይማኖት ነኝ ባይ ግን ክርስቶስ ኢየሱስን በትክክለኛ ማንነቱ የምታምን የምትገልጽ የምትመሰክር
አንዲቷ ብቻ ናት ፡፡ ቃሉም የሚለው አንድ ሃይማኖት አንዲት ጥምቀት አንድ ጌታ በመሆኑ ኤፌ.4፣5 ስለሆነም የተቀሩት
ሁሉ የሚጠሯቸውና የሚሰብኳቸው የሚያምኑባቸውም ኢየሱሶች ሐሰተኞች ኢየሱሶችን ወይም ክርስቶሶችን ማቴ.24፣24 እና ኢየሱስ ነኝ
ብሎ የሚመጣውን አውሬውን ነው ፡፡ሰይጣንም ለክፋቱ ለተንኮሉ ለዓላማው በእነኝህ ሐሰተኞች ክርስቶሶች ስም ተአምራትን ያሠራቸዋል፡፡በመሆኑም
ነው የድንግል ልጅ መድኃኔዓለም ክርስቶስ በስምህ ትንቢት አልተናገርንምን ፣በስምህ አጋንንትን አላወጣንምን፣ በስምህ ብዙ ተአምራትን
አላደረግንምን ሲሉት ከቶ አላውቃቹህም እናንት ዓመፀኞች ከእኔ ራቁ ብሎ የሚመሰክርባቸው ፡፡ ዘንዶው የተቆጣው
በሴቲቱ ላይ ነውና የሚዋጋውም የእግዚአብሔርን ትእዛዛት የሚጠብቁትን፣ የኢየሱስም ምስክር ያላቸውን፣ ከዘርዋ የቀሩትን ነውና “ከዘርዋ
የቀሩትን” አለ የወላዲተ አምላክ የሥጋ ዘመድ የሆኑትን ማለት ሳይሆን የጌታችንን የአምላካችንን የመድኃኒታችንን የኢየሱስ ክርስቶስን
በሐዋርያው ዮሐንስ አማካኝነት ለክርስቲያኖች ሁሉ ከጌታ ለእኛ የተሰጠችንን የመስቀሉ ሥር የእናትነት ስጦታና በልጅነታችንም እንንከባከባት
እንጠብቃትም ዘንድ የጣለብንን የአደራ ቃል ተቀብለን ወላዲተ አምላክን እናታችን ያደረግንና የእናትነት አገልግሎቷን የምናገኘውን
እሷም ልጇ ኢየሱስ ክርስቶስ በወንጌላዊው ዮሐንስ እማካኝነት ‹‹እነሆ ልጅሽ›› በሚለው አምላካዊ ቃል በተሰጣት የእናትነት አደራ
ልጆቸ የምትለንን እንደ ልጅ የምትንከባከበንን የምታገለግለንን ማለት ነው፡፡ እንደሚታወቀው ልጅነት ወይም የክርስቶስ ወገንነት የሚኮነው
የሚገኘው በዘር ኃረግ ሳይሆን እሱን በማመን የሚገኝ ነውና፡፡ በመሆኑም ወላዲተ አምላክን ትምክህታቸው ያደረጉትንና ንጽሕናዋን ቅድስናዋን
የሚያውቁትንና የሚያምኑትን እናታችን የሚሏትን የአንዲቱን ቤተ ክርስቲያን የተዋሕዶ ልጆችን ( የእግዚአብሔርን ትዕዛዛት የሚጠብቁትን
፣ የኢየሱስም ምስክር ያላቸውን ፣ከዘሯ የቀሩትን ) ተብሎ የተነገረላቸው የዚህች ቤተክርስቲያን ልጆች ብቻ ናቸው ፡፡ ቀደም ሲል
በቀረበው ማብራሪያ መሠረት ከዘሯ ያልተቆጠረ የኢየሱስ ምስክር የለውምና ፣የእግዚአብሔርን ትዕዛዝ የሚጠብቅ አይደለምና ፡፡ እነዚህንም
ሊዋጋ ሔደ በባሕርም አሸዋ ላይ ቆመ አለ፡፡ አሸዋ በእምነት ያልጸና ተጠራጣሪና የከሐዲ ልብ ምሳሌ ነው፡፡ “ቃሌን ሰምቶ የሚያደርገው
ሁሉ ቤቱን በዓላት ላይ የሠራ ልባም ሰውን ይመስላል፡፡ ዝናብም ወረደ ጎርፍም መጣ ነፋስም ነፈሰ ያንም ቤት ገፋው በዓለት ላይም
ስለተመሠረተ አልወደቀም፡፡ ይህንም ቃሌን ሰምቶ የማያደርገው ሰው ሁሉ ቤቱን በአሸዋ ላይ የሠራ ሰነፍ ሰውን ይመስላል፡፡ ዝናብም
ወረደ ጎርፍም መጣ ነፋስም ነፈሰ (ሰውን ከእግዚአብሔር የሚለዩ ፈተናዎች ኑፋቄ ክሕደት መከራ ደረሰበት) ያንም ቤት መታው ወደቀም
አወዳደቁም ታላቅ ሆነ /በእምነት የጸና አይደለምና ኑፋቄ ክሕደት አለበትና ወደቀ አወዳደቁም የከፋ ሆነ/›› ማቴ.7፥24-27
በመሆኑም በባሕር አሸዋ ላይ ቆመ
አለ በመናፍቃን ልቦናና አንደበት ላይ አደረ ክርስቲያኖችን ያሳድድ፣ ይዋጋ፣ መከራም ያደርስባቸው ዘንድ ማለቱ ነው፡፡
እናም ክርስቲያኖች ይህ ኑፋቄ ምን
ያህል ከባድና አጋንንታዊ መሆኑን ቤተ ክርስቲያን ከሐዋርያት ባገኘችው ትምህርት ካረጋገጠች ቆይቷልና በዚህ ጉዳይ ላይ ምንም ዓይነት
ብዥታ የለባትም፡፡ ከዘንዶው አፍ በሚፈሰው ኑፋቄ እንዳንመረዝ የወላዲተ አምላክ ረድኤት የልጇ ጥበቃ አይለየን አሜን፡፡ ይቆየን
ወስብሐት ለእግዚአብሔር ወለወላዲቱ
ድንግል ወለ መስቀሉ ክቡር አሜን፡፡
I beg you in the
name of Zion Mary to Email and Blog it ,to share it to Twitter and Facebook .
thank you so much
ሠዓሊ አምሳሉ ገ/ኪዳን አርጋው
amsalugkidan@gmail.com
ሠዓሊ አምሳሉ ገ/ኪዳን አርጋው ጽሁፉን አላበሰልኅሁም : ጥያቂ ያስነሳብሃል
ReplyDelete1 "አንጺሖ ሥጋሀ ኀደረ ላዕሌሃ” በድንብ አለተተረጐምም የራስህን ሀሳብ ነው የተናገርህ
2 የክርስቶስ ሞት ለድንግል ማርያም ያስፈልጋታል ወይ?
3 "ጌታዬ መዳሀኒቴን "ሉቃ 1 አልተመለከትኃውም
በአጠቃላይ ጽሁፉ ከካቶሊክ እምነት ጋር ይመስላል አስብበት