Sunday, October 12, 2014

የመቃብር ቤት ካሳ ጥያቄ ክስ



አንድ አድርገን ጥቅምት 02 2007 ዓ.ም
ሐረር ክልል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ነው፣ በክልሉ ጠቅላይ ፍርድ ቤትና በፌዴራሉ ጠቅላይ ፍርድ ቤት የሰበር ችሎት ፡፡ የክርክሩ መነሻ አንዲት ግለሰብ በሐረር ከተማ በሚገኘው ቅዱስ ሚካኤል ቤተ ክርስቲያን ግቢ ውስጥ የመቃብር ቤት ለመሥራት እንዲፈቀድልኝ ጠይቄ የመቃብር ቤት እንድሠራ ስለተፈቀደልኝ ለእኔና ለዘመዶቼ የቀብር ሥርዓት የሚፈጸምበት የመቃብር ቤት በብር 200,000 ሠርቼያለሁ፡፡ ሆኖም ቤተ ክርስቲያኗ ሃይማኖትሽን የለወጥሽ በመሆኑ በመቃብር ቤቱ ለመጠቀም አትችይም በማለት በግልጽ ደብዳቤ አሳውቆኛል፡፡ ስለዚህ የቤተ ክርስቲያኗ ተከታይ በነበርኩበት ጊዜ የሠራሁትን የመቃብር ቦታ ያለምንም ካሳና ግምት ለመልቀቅ የውል ግዴታ ያልገባሁ በመሆኑ የመቃብር ቤቱን ለመሥራት ያወጣሁትን ብር 200,000 ቤተ ክርስቲያኑ እንዲከፍል ይወሰንልኝ ስትል ክስ አቀረበች፡፡ ቤተ ክርስቲያኗ በበኩሏ በሰጠችው መልስ አመልካቿ የመቃብር ቤት መሥራቷን በማመን በሠራችው የመቃብር ቤት፣ የዘመዶቿ ሥርዓተ ቀብር ተፈጽሞ የዘመዶቿ አጽም አርፎበት ይገኛል በማለት ተከራክራለች፡፡ ካሳውን በተመለከተም ግለሰቧ ሃይማኖቷን የለወጠች በመሆኑ በመቃብር ቤቱ የመጠቀም መብት የላትም፣ የመቃብር ቤት ግምት ለመክፈል ያደረግነው ውል የሌለ በመሆኑ ክሱ የእምነቱን መሠረታዊ ቀኖናና አሠራር የሚፃረር በመሆኑ የመቃብር ቤት ግምት የመክፈል ኃላፊነት የለብንም በሚል መከላከያ መልስ አቅርባለች፡፡

የሐረር ከፍተኛ ፍርድ ቤት የግራ ቀኙን ክርክርና ማስረጃ ከመረመረ በኋላ ቤተ ክርስቲያኗ ግለሰቧ የሠራችውን የቤት ግምት የመክፈል ኃላፊነት አለበት በማለት መቃብር ቤቱ በባለሙያ ተገምቶ ብር 50,153.50 ቤተ ክርስቲያኗ እንድትከፍል ውሳኔ ሰጥቷል፡፡ ይግባኝ የቀረበለት የክልሉ ጠቅላይ ፍርድ ቤትም ይግባኙን ሰርዞታል፡፡ ጉዳዩ በመጨረሻ ለፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ሰበር ሰሚ ችሎት ቀርቦ የመጨረሻ እልባት አግኝቷል፡፡ ይህ ፍርድ በሰ// 85979 መጋቢት 13 ቀን 2005 .. የተሰጠ ነው፡፡
የሰበር ችሎቱ ፍርድ
ሰበር ችሎቱ መሠረታዊ የሕግ ስህተት የተፈጠረበትን የሥር ፍርድ ቤቶች ፍርድ ያስቀርባል በማለት መርምሮታል፡፡ ሰበሩ ግለሰቧ በቤተ ክርስቲያኗ ቅጥር ግቢ ውስጥ የሠራችውን የመቃብር ቤት ግምት እንድትከፍል ፍርድ ቤቶቹ የሰጡት ፍርድ ተገቢ ነው? ወይስ አይደለም? የሚለውን ጭብጥ በመመሥረት ፍርድ ሰጥቷል፡፡ በፍርዱ ዋና ትንተና እንደተገለጸው ማንኛውም ሰው የመረጠውን ሃይማኖት የመከተል መብት እንዳለው በመተንተን ቤተ ክርስቲያኗ ለግለሰቦች የጻፈችው ደብዳቤ ይህን የእምነት ነፃነት ሕገ መንግሥታዊ መብት እንደማይገድብ አረጋግጧል፡፡ በሌላ በኩል ግን ሰበር በሰጠው ትንተና የመቃብር ቤቱ ከግለሰቧ የቀደመ እምነት ጋር የተያያዘና እምነቷን በለወጠች ጊዜ ቀሪ እንደሚሆን አስምሮበታል፡፡ የሰበር ችሎት ዋና የትንታኔ ክፍል እንዲህ ይነበባል፡፡ 
‹‹… ተጠሪ አመልካች የሚያራምደውን ሃይማኖትና መንፈሳዊ አስተምህሮ በመተው የሌላ ሃይማኖት ወይም እምነት ተከታይ መሆኗ ካልተካደ ተጠሪዋ የኢትዮጵያ ተዋህዶ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን ተከታይ አማኝ የነበረች በመሆኑ ምክንያት አመልካች ሰጥቷት የነበረውን ክብር፣ መብትና ጥቅም በነበረው ሁኔታ እንዲቀጥልላት ለመጠየቅ አትችልም፡፡ ተጠሪ የሌላ እምነትና ሃይማኖት ተከታይ መሆን ስትጀምር ከአመልካች ጋር የነበራትን የሃይማኖትና የእምነት ትስስር መሠረት በማድረግ ነው፡፡ በአመልካች ቅጥር ግቢ ውስጥ ተጠሪ የመቃብር ቦታ የገነባችው ከአመልካች ጋር በነበራት ጥብቅ የሆነ ሃይማኖታዊና መንፈሳዊ ግንኙነት ምክንያት እንጂ በአመልካችና በተጠሪ መካከል በገንዘብ የሚተመን የኢኮኖሚያዊ ውልና ስምምነት መሠረት በማድረግ አይደለም፤›› በማለት የሠራችው የመቃብር ቦታ ከእምነቱ ተለይቶ የሚታይና የሚፈጸም ተራ የሆነ ውል ወይም የንብረት ግንኙነት ባለመሆኑ ቤተ ክርስቲያኗ የቤቱን ካሳ ግምት የመክፈል ግዴታ የለባትም ሲል የሥር ፍርድ ቤቶችን ፍርዶች ሽሯል፡፡ 

 From Ethiopian Reporter

No comments:

Post a Comment