አንድ አድርገን
መስከረም 28 2007 ዓ.ም
(ወንድወሰን ውቤ)
ሩሳዊያን የሶሻሊስት አብዮትን ተከትሎ ቤተክርስቲያንን አንይ አሉ። ያው እምነት የለሹ ሥርዐት በሩሲያ ኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያን ላይ የግፍ በትሩን በጭካኔ አሳረፈ። ካህናቱ ተጨፈጨፉ፣ ተሰደዱ። እግዚአብሔርን ማመን ወንጀል ሆነ። ብዙ አብያተክርስቲያናት ተዘጉ። በምትካቸው የቦልሸቪክስ ፓርቲ ጽሕፈት ቤቶች ተከፈቱ። በስታሊን እግር የተተካው ክሩሽኔቭ ሞስኮ ውስጥ የሚገኝ አንድን ግዙፍ ካቴድራል እንዲፈርስ ያዛል። አፍራሾቹ ማፍረሱን ከጉልላቱ ጀመሩት።
ክሩሽኔቭ ከጥቂት ዓመት በኋላ በቤተክርስቲያን በኩል ሲያልፍ ያ ካቴድራል ከጉልላቱ የተወሰነ ክፍል ፈርሶ ቀሪው ግን አሁንም ድረስ እንደቆመ ያየል። መኪና አስቁሞ ወደ ቤተክርስቲያኑ ዘለቀ። ውስጡ አሮጊቶችና ጥቂት አዛውንቶች ብቻ ነበሩ። ገብቶ እየተዘዋወረ አያቸውና። “ግዴለም እንዳይፈርስ! እነዚህ በቅርቡ ሙተው ያልቃሉ ያኔ ቤተክርስቲያኑን ሙዚየም እናደርገዋለን” ብሎ በእብሪት ተናግሮ ወጣ። አንዲት እናት እጁን ያዝ አደረጉትና “ስማ ልጆቻችንን ከዐይኖቻችሁ ሰውረን እያስተማርን ነው። እናንተ ስታልፉ የፈረሰውን እነሱ ያንፁታል!” አሉት በኃይለ ቃል። ስቆባቸው ወጣ። የሴትዮዋ ቃል ግን ትንቢት ነበር። በ1989(በኛ አቆጣጠር በ1982 ዓ.ም.) ሶሻሊዝም ሲወድቅ የክሩሽኔቭ የራሱ ልጅ ቁሞ አባቱ ያስፈረሰውን ቤተክርስቲያን ጉልላት አሠራ። ዛሬ ሌኒን የለም፣ ክሩሽኔቭም የለም…የለም! ደርግም እንዲሁ ይፎክር ነበር። ነገም ዛሬ ማዕተብ ለማስቆረጥ የሚፎክሩብን አይኖሩም። ቤተክርስቲያን ግን ትኖራለች። መሠረቷ፣ ራስ ጉልላቷ ክርስቶስ ነውና።
የኛዎቹ ባለሥልጣናት ቤተክርስቲያንን በመወረፍ ነው የፖለቲካ ሀ ሁ የሚጀምሩት። አፉን የዚች አገር ባለውለታ በሆነችው ቅድስት ቤተክርስቲያን ላይ ያልከፈተ፣ አፍራሽ ኃይል ለማዘዝ፣ ትፍረስ ለማለት የዶዘር ማዘዣ ለመፃፍ የሚፈጥነው ባለሥልጣን መብዛቱ ይገርማል።
ሩሲያዊያኑ የእምነት የለሹን ሶሻሊስታዊ አመለካከት መበስበስ ተረድተውታል። ወደ ልባቸው ተመልሰው ቤተክርስቲያኗን ሕዝቡን የሚያስተሳስሩበት የአንድነት ምዕቀፍ አድርገው ተጠቀሙባት። እነሆ በድኅረ-ሶሻሊዝም የወንጀለኞች፣ የጎበዝ አለቆች መናኃሪያ የነበረችው ሩሲያ ዛሬ ልዕለ ኃይልነቷን ዳግም እያሰመለሰች ነው። የትናንት ፌዴሬሽኗ አካላት የነበሩት የምሥራቅ አውሮፓ አገራት ተመልሰው ወደ ጉያዋ እየገቡ ነው። መሪዎቿ ቤተ ክርስቲያንን ይቅርታ ጠይቀው፣ ልጅነታቸውን በንሥሐ አድሰው ማተባቸውን አስረዋል። ለዚህ የፑቲን ትውልድ ተመስጋኝ ነው።
ቭላድሚር ፑቲን አሁንም ያሠሩት ማተብ በልጅነታቸው ክርስትና ሲነሡ የታሰረላቸው ማተብ ነው። የኛዎቹ ደግሞ ሊያውልቁን ይፎክራሉ። ሰውዬው ማተብ ማስቆረጥ የረጅም ጊዜ ዕቅዳቸው አካል መሆኑን አምልጧቸው ተናግረውታል።ይችን ቤተክርስቲያን የሚጠብቅ መንፈስ ቅዱስ አፍን ከፍቶ ፊትን ጸፍቶ ማናገር ያውቅበታል። ከዚች ቤተ ክርስቲያን ማሕፀን የተወለዱ የሥልጣን አቻዎቻቸውን ግዴለሽነት ፣ ባስ ሲልም ቀድመው እነሱ አውልቀውት ስላዩ የብዙኃኑ መልስ ምን ሊሆን እንደሚችል ግድ አልሰጣቸውም። ስህተቱ እዚህ ላይ ነው።
ትልቁ የዚህ መንግሥት ባለሥልጣናት ችግር ከታሪክ ጋር መጣላታቸው ነው። ስለተጣሉም ከታሪክ አይማሩም።በ17ኛው ክፍለ ዘመን ወደ ኢትዮጵያ የመጡት የካቶሊክ ሚሲዮናዊያን (Jesuits) “ንጉሡ ዓፄ ሱስኒዮስ ከኮተለከ ሌላው ዕዳው ገብስ ነው” የሚል የስህተት ስሌት አስልተው ገቡ። መጨረሻ ግን የራሳቸው ሰው “ETHIOPIANS would rather die than submit to the new religion” ብሎ እስኪመሰክር ድረስ ማተባቸውን ከመቁረጡ በፊት አንገታቸውን እንዲቆረጥ የቆረጡ መሆናቸውን አሳይተዋል። እኔም እንዲህ እላለሁ፡-
እኔም የአባቶቼ ልጅ ነኝ!!!
No comments:
Post a Comment