Thursday, October 16, 2014

የወቅቱ አጀንዳ ፡- ሕገ ወጥ ሰባኪያንን እና አጥማቅያንን መቆጣጠር

 አንድ አድርገን ጥቅምት 6 2007 ዓ.ም ፡ -

በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ጥቅምት 5 ቀን 2ዐዐ7 . የተጀመረው የሰበካ መንፈሳዊ ጉባኤ እንደቀጠለ ይገኛል፡፡ እስከ አሁን 24 አህጉረ ስብከቶች ሪፓርቶቻቸውን አቅርበዋል፡፡ ጉባኤው ከተነጋገረበት አንዱ ጉዳይ ‹‹ሕገ ወጥ ሰባኪያንን እና አጥማቅያንን መቆጣጠር›› የሚል መሆኑን ለማወቅ ተችሏል፡፡በሥርዐተ ቤተ ክርስቲያን ማጥመቅ የሚችለው የቅስና ሥልጣነ ክህነት ያለው አባት ብቻ ነው፡፡ ቅስና የሌለው ሰው አያጠምቅም  አያናዝዝም   አይባርክም /ፍት....አን.3 .21/  ቅዱሱን ቅባት  መቀባት የሚችለው የክህነት ሥልጣን  ያለው ብቻ ነው፡፡  /ያዕ.5÷14/  ሀብተ መንፈስ ቅዱስ በገንዘብ  አይሸጥምና አጥማቂው ካህን መማለጃ መቀበል አይገባውም፡፡ /....አን.7/ አሁን ግን እየተመለከትን እና እየታዘብን ያለነው ሕገ ወጥ ሰባኪያንና ሕገ ወጥ አጥማቂያን የማህበረሰቡን ችግር በመረዳት ጥረው ግረው በወዛቸው የምድርን ፍሬ ከማግኝት ይልቅ  በብልጣ ብልጥ አካሔድ የአባቶችን ኪስና የእናቶችን መቀነት መፍታት ላይ መዝመታቸውን ነው፡፡

 ቅድስት ቤተ ክርስተያን ባሕረ ጥበባት ስንዱ እመቤት ሆና ሳለ ለግል ጥቅማቸው የሚንቀሳቀሱ አንዳንድ ግለሰቦችና ቡድኖች በየጊዜው ብቅ እልም እያሉ ምእመናንን በማደናገር እያወኳት ይገኛሉ፡፡ በተጨማሪም በውጭ ሀገርና በሀገር ውስጥ በሚገኙ የቤተ ክርስቲያን አካላት ባልሆኑ አስተማሪዎቻቸው የተሰጣቸውን ተልእኮ በመያዝ ‹‹መልካም የሆነው ትምህርት እንዳይኖር አብዝተው ይተጋሉ›› እንዳለው ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ ቅድስት ቤተ ክርስቲያናችንን የወንበዴዎች ዋሻ ለማድረግ ሌት ተቀን ከውጭ እየገፉ በቤተ ክርስቲያን መዋቅር ውስጥ ለሆዳቸው ባደሩ አጋዦቻቸው አማካይነት እየተደገፉ ስልታቸውን በመቀያየር የቤተ ክርስቲያንን ትምህርት ሳያውቁ ለዘመናት የኖረችው ቤተ ክርስቲያን ሐዋርያዊ ተልእኮዋን በተገቢ ሁኔታ እንዳትወጣ እያደረጉ ይገኛሉ፡፡

ይህን የሕገ ወጥ አጥማቂያንን  አካሄድ የተመለከተው ጠቅላይ ቤተ ክህነት  ‹‹አገልግሎት›› ብለው ለሚያጠምቁበት አብያተ ክርስቲያናት አስተዳዳሪዎች ሕገ ወጥ ሥራቸውን ለማስቆም ያስችለው ዘንድ ደብዳቤ ቢጽፍም ሰዎቹ ቤተ ክርስቲያናትን እየቀያየሩ ከ‹‹ማጥመቅ›› ሥራቸውን ሲገቱ አልታየም፡፡ እነዚህ ሰዎች ተከታዮቻቸውን ወደ ግለሰብ አፍቃሪነትና ሲልቅም አምላኪነት እያሸጋገሯቸው ይገኛሉ፡፡ ተከታዮቻቸውም ከስርዓተ ቅዳሴ ይልቅ የ‹‹አጥማቂዎቹን›› የማጥመቅ ሂደት የማረካቸው ፤ ስርዓተ ቅዳሴው የሚረዝምባቸው ፤ ለመገረምና ለመደነቅ ራሳቸውን አዘጋጅተው የሚመጡ ሰዎች ከመሆናቸው በተጨማሪ የተዘጉ አብያተክርስቲያናት ፤ በተኩላ የሚወሰዱ ምዕመናን ፤ በየቦታው ስለ እምነታቸው ብለው ዋጋ እየከፈሉ ከሚገኙ ክርስቲያኖችን ከማሰብ እና የመፍትሄ አካል ከመሆን ይልቅ ‹‹አጥማቂያቸው› በሚሰሩት ሕገወጥ ሥራ ስማቸው ሲነሳባቸው የእግር እሳት ያህል ዘልቆ የሚሰማቸው ሰዎችን እየተመለከትንና እያፈራን እንገኛለን፡፡


በቅርቡ አጥማቂው በእስራኤል ሀገር ባካሄዱት ‹‹ጉባኤ›› በሕዝብ ፊት መተት አስደርገሻል ተብያለው ፤ በ‹‹አጥማቂው›› ሰው ምክንያት ስሜ ጠፍቷል ያለች አንዲት ምዕመን ጉዳዩን ወደ ፖሊስ ዘንድ ይዛ መሄድ በመቻሏ ‹‹አጥማቂውም›› በፍርድ ቤት ክስ ከመመስረቱ በፊት ሀገሪቱን ለቀው ሊወጡ ችለዋል፡፡

የሰበካ መንፈሳዊ ጉባኤ አባላትም በተኩላ ከሚወሰደው ምዕመን ቁጥር ያልተናነሰ ደጋፊዎችን ያፈሩ የራሳቸው ዝና ፤ ሀብትና ንብረት የሚያስጨንቃቸው ሕገ ወጥ አጥማቂያንና ሰባኪያን ጉዳይ አጽንኦት ሰጥተው መወያየት መቻላቸው ሊያስመሰግናቸው ይገባል፡፡ ወደፊትም ይህ አካሄድ መስመር እንደሚይዝ ተስፋ አለን፡፡

ከዚህ በፊት እንዲህ ሆኗል…….

የዛሬ ሁለት ዓመት አንድ ሰው ከሰሜኑ ክፍል ይነሳና የማጥመቅ ስራውን እያከናወነ  ወደ ምስራቅ ክፍል ሐረር መንገድ አሰበ ተፈሪ ጉዞውን ይቀጥላል፡፡ አሰበ ተፈሪ ሲደርስ የማጥመቅ ጸጋ እንዳለው ለቤተ ክርስቲያን አባቶች እና ለአካባቢው ሊቀ ጳጳስ አስረድቶ ፤ የማጥመቅ አገልግሎት እንዲሰጥ ሕጋዊ ፍቃድ አግኝቶ ሰዎችን ሊያጠምቅ ስራውን በይፋ ይጀምራል፡፡ ቅዳሜ እና እሁድ ከቅዳሴ በኋላ ስራውን ሲጀምር ለመጠመቅም ሆነ ለመመልከትም የመጡ ሰዎች እያጓሩ ፤ እየጮሁ መውጣት ጀመሩ ፡፡ መንፈስ ተብዬው ሲለፈልም ‹‹ሟርት ነኝ›› ፤ ‹‹መተት ነኝ›› ፤ ‹‹እገሌ ነኝ›› ማለቱን ቀጠለ፡፡ ማነው ያደረገብህ ? ተብሎ ሲጠየቅ ፤ የሚታዘዘው መንፈስ የደብሩን አስተዳዳሪ ፤ ቄሶችን ፤ ዲያቆናትን ፤ መምህራንን ስም መጥራት ተያያዘው ፡፡ በቦታው ያለው ሰው ግራ ገባው ፤ ግማሹ ‹‹ይሄ ሰውዬ ትክክለኛ እጥማቂ አይደለም ፤ እነዚህን ዲያቆናትና ፤መምህራንን  እናውቃችዋለን ንፁህ ናቸው›› ሲል ፡፡ ሌላው ክፍል ደግሞ ‹‹ያው መንፈሱ እኮ ተናገረ ፤ ከዚህ በላይ ምስክር አያሻንም›› ብለው ስማቸው የተጠራውን ቀሳውስ ዲያቆናት ፖሊስ አስጠርተው አፍሰው እስር ቤት ከተቷቸው፡፡ ይህ ሰው መሰል ተግባሩን በተለያዬ ቦታዎች ውስጥ እየዞረ በመስራት መሰል ነገሮች በሶስት ቤተ ክርስትያኖች ላይ ተከሰተ፡፡ ቀሳውስቱ ፤ ዲያቆናቱ ሁሉም ዘብጥያ ወረዱ፡፡

በዚህ ሁኔታ ማን ይቀድስ? ማንስ ቀድሶ ያቁርብ?  በቦታው  የተከሰተው ነገር  በጣም አስቸጋሪ ሆነ   የአካባቢው  ምእመን  ‹‹ቀሳውስቱንና  ዲያቆናቱን ደግመን ማየት አንፈልግም››  ስላለ የአካባቢው  ሀገረ  ስብከት  አስተዳዳሪ ሊቀ ጳጳስ  መንፈሱ መሰከረባቸው የተባሉትን አባቶች ወደመጡበት ማሰናበት እና አዲስ አገልጋዮችን በማምጣት ሂደት ውስጥ ቤተክርስቲያን ከአንድ ወር በላይ ተዘጋች ፤ ለምዕመኑ ሲሰጥ የነበረው የቀድሞ አገልግሎትም ተስተጓጎለ፡፡ ይህ በእንዲህ እያለ ይህ ሰው ብር መሰብሰቡን ማጥመቁን የከለከለው አካል አልነበረም፡፡ አንዳንድ ቦታ ላይ እሱን ለመጋበዝ እስከ 7000 ሺህ ብር ድረስ ከምዕመናን ይሰበሰብና በጉባኤ እንዲገኝ ይደረግ ነበር፡፡  ብዙም ሳይጓዙ በአካባቢው በረሀ ላይ ያሉ አብያተ ክርስቲያናት በጧፍ እጥረት አገልግሎቱ ማከናወን ሲገዳደራቸው እየተመለከቱ ለአንድ ሕገ ወጥ አጥማቂ ግን 7,000 ብር በቀናት ጊዜ ውስጥ እንዴት መሰብሰብ እንደቻሉ ለተመለከተ እጅጉን ይገረማል፡

ይህ በእንዲህ እያለ ሰውየው ሌላ ቦታ ላይ ተጋብዞ ለማጥመቅ ሥራ ሄደ ፤  በቦታው ላይ የተከሰተው ነገር ከአሰበ ተፈሪው የተለየ ነበር፡፡ ቤተ ክርስቲያኗ ባልታወቀ ምክንያት ከዓመታ በፊት ተቃጥላ ነበር ፤ በወቅቱም በቁጭት የአካባቢውም ምዕመን የተቃጠለቸውን ቤተክርስቲያን መሥራት ችሎ ነበር ፡፡ ይህ ‹‹አጥማቂ›› ነኝ ባይ እዚች ቤተ ክርስቲያን ላይ እያጠመቀ ሳለ አንዱ መንፈስ የያዘው ሰው ይነሳና መለፍለፍ ይጀምራል፡፡‹‹ቤተ ክርስቲያኗን ያቃጠላት መምህሬ ‹እገሌ› ነው›› ብሎ መሰከረ፡፡ ምዕመኑ እውነት መስሎት ያን መምህር ካልገደልነው ብሎ ተነሳ፡፡ በመሀል አንድ አባት ይነሱና እረፉ ‹‹መንፈስን ሁሉ አትመኑ›› ነው የተባለው፡፡ አንተም ማጥመቅህን አቁም ፤ ‹‹በችግር የተያዙትን እስራታቸውን እግዚአብሔር ይፍታ ስንል አንተ ደሞ ሌላ ብጥብጥ አመጣህብን›› ብለው በሰላም ወደመጣበት ሸኙት፡፡ 

ለቤተ ክርስትያን መቆርቆራችን ባልከፋና ጥሩ ሆኖ ሳለ እንዴት ለቤተ ክርስቲያን እንደምናስብ  አለማወቃችን ደግሞ ሌላ ችግር እየፈጠርን መሆኑን ተገንዝበነው አናውቅም፡፡  አሁንም የአካባቢው ሰው አቃጠለ የተባለውን መምህር ይዘው ለፖሊስ አስረከቡ ፡፡ ፖሊስም እስኪጣራ ብሎ መምህሩን አሰረው ፤ ፖሊስ ምንም አይነት ተጨባጭ ማስረጃ ስላላገኝ መምህሩን ፈትቶ ሀገር ለቆ እንዲሄድ አሰናበተው፡፡ ህዝቡም ‹‹ቤተክርስቲያናችንን አቃጥለህብናልና አይንህን እንዳናይህ ››  ብለው አይንህን ለአፈር አሉት፡፡

ይህ ሁሉ እየሆነ ማስተዋል የሚችል ሰው በመጥፋቱ በሌላ ጊዜ ፤ ሌላ ቦታ ላይ ‹‹አጥማቂው›› መንፈስ ያወጣል ፤ ተዓምረኛ ነው ሲባል የሰሙ ምዕመኖች ይምጣልን ብለው በጠየቃቸውን ብር ከማሕበረሰቡ ላይ ፤ ከአላፊ አግዳሚው ላይ መሰብሰብ ይጀምራሉ ፡፡ በወቅቱ የ‹‹አጥማቂው›› ማንነት ለማወቅ ሰው አይነ ልቦናው አልበራለትም ነበር  ፤ ራሱ መተተኛ ሆኖ ሳለ በመተት የተያዘ ሰው እፈታለሁ ፤ ከዲያቢሎስ ቁራኛነት እገላግላችዋለሁ ብሎ ማውራትና ማጥመቁን ተያይዞታል ፡፡በዚህ ሁኔታ ሳለ አባቶች ተሰብስበው መከሩ ፡፡ እንቢ አይመጣብ ቢሉ ‹‹የራሳችሁ ጉድ እንዳይወጣባችሁ›› ነው ይባላሉ፡፡ ይምጣ ቢሉ ደግሞ ቤተክርስቲያኗን ፈትቶ ፤ ያሉትን ካህናት እንዲባረሩ አድርጎ ፤ ምዕመኑን ለሌላ እምነት አሳልፎ ሊሰጥ ነው፡፡ ግራ የሚገባ ነገር ሆነ ፡፡ አባቶች ተሰብስበው መከሩ እንዲህም አሉ ፡- ‹‹በሚቀጥለው  እሁድ ጠዋት መምጣት ይችላል ፤ ነገር ግን እኛ ለሊቱን ሙሉ ድርሳናትንና ዳዊትን እንድገም ፤ ደግመን ጸሎት እናድርግ ፤ መልካ መልኮችን እናድርስ ፤ ከዛ እኛ በማኅበር ሆነን ባደረግንበት ፀበል እሱ መጀመሪያ ይጠመቅ ፤ ከዚያ እኛ ሁላችንም እንጠመቃለን ፤ ከዛ ምዕመኑን ያጠምቃለል ›› ብለው ቃለ ጉባኤ ይዘው ተፈራርመው ፤ ወስነው ስብሰባንውን ዘጉ፡፡ 

‹‹አጥማቂው››  ምን እንደተባለ ማን ይንገረው ባልታወቀበት ሁኔታ ቅዳሜ ለእሁድ አጥቢያ በሕብረት ሆነው አባቶች ካህናት ቃል የገቡትን አድርገው ‹‹አጥማቂው››ን ቢጠብቁት ሊመጣ አልቻለም፡፡ ሳይመቸው ቀርቶ ይሆናል  በማለትሌላ ቀጠሮ ያዙለት ፤ አሁንም ሊመጣ አልቻለም ፡፡ የቀረበትን ምክንያት ሲጠይቁት ውሃ የማያነሳ ምክንያት አቀረበላቸው፡፡

ጥቂት ምዕመን በብልሀት ቀስ እያሉ የ‹‹አጥማቂው›› ማንነት ስለገባቸው ገፍተው ከአካባቢው አባረሩት፡፡ ይህ ሰው ይህን አይነት ስራ ደቡብ አካባቢ ሲሰራ ሌባና አጭበርባሪ መሆኑ ታውቆ በእስር ቤት እንደሚገኝ ከጊዜ በኋላ ተሰማ፡፡ እኛ ይህ ሰው በአንድ ቦታ ላይ ብቻ ያደረገውን ብቻ እናውቃለን ፤ ከዚህ በፊት ምን ያህል ቤተ ክርስቲያን ይበትን? ፤ አሁን ምን ይስራ? ፤ በአሁኑ ሰዓት ምን እያደረገ እንዳለ  የምናውቀው ነገር የለም፡፡

እኛ አይናችን ታውሯል ፤ እናያለን አንመለከትም ፤ እንሰማለን አናዳምጥም ፤ ፡፡ እነሱም እየዞሩ ቤተ ክርስቲያን ያፈርሳሉ ፤ ቤቱን ይፈታሉ ፤ ተከታዮችን ያፈራሉ ፤ ደጋፊዎችን ያደራጃሉ ፤ የእግራቸውን እጣቢ እንደ ጸበል ጻዲቅ ለምዕመኑ ያከፋፍላሉ ፤ የቻይናን ዘይት ቅባ ቅዱስ ብለው ይሸጣሉ ፤ በጆንኛ ሙሉ መቁጠሪያ ለገበያ ያቀርባሉ ፤ ጉባኤያቸውን በሲዲ አድርገው አቀነባብረው ለኛው ይሸጣሉ፡፡

የአካባቢው አባቶች ጠይቀን እንደተረዳነው ፡- ‹‹ይህው እሱ በዚያን ጊዜ አጠምቃለሁ ብሎ ውሀ የረጨባቸው ሰዎች አሁንም ይጥላቸዋል ፤ ምን እንዳሰፈረባቸው እግዚአብሔር ይወቀው ፤ እሱ ሳይመጣ በፊት ጤነኞች ነበሩ ፤ እሱ ካጠመቃቸው በኋላ ግን በሽታ ላይ ጥሏቸው ሄደ ፤ አንዳንዶቹ ቤተክርስቲያን እየመጡ እየተጠመቁ እየተሸላቸው ነው ፤ አንዳንዶቹ ግን አሁን በሽተኞች ናቸው››  ብለዋል ፡፡


አሁን ላይ ሁለተኛ ቀኑን የያዘው ጉባኤ ‹‹ሕገ ወጥ ሰባኪያንን እና አጥማቅያንን መቆጣጠር›› በሚል አጀንዳ ላይ መነጋገር መቻሉ ጉዳዩ ምን ያህል አሳሳቢ እንደሆነ ያመላክታል፡፡ አሁኑ ላይ ይህ ጉዳይ መንገድ ካልተበጀለት ፤ መፍትሄ ካተቀመጠለት የቤተ ክርስቲያኒቱ ጳጳሳት አባቶች ፤ የአብያተክርስቲያናት አስተዳዳሪዎችና  ምዕመናንና ሥራቸውን በአግባቡ ባለመስራታቸው ፤ ሃላፊነትና ግዴታቸውን በአግባቡ ባለመወጣታቸው ምክንያት አሁን ላይ በሚያስቆጩ ለተኩላ ተላልፈው ከተሰጡት ምዕመናን ቁጥር በላቀ በእነዚህ ሕገ ወጥ ሰባኪያንና አጥማቂያን እንደ በግ የሚነዳው ምዕመን ቁጥር ሊበልጥ የማይችልበት አንዳች ምክንያት አይኖርም፡፡

ማስተዋሉን ይስጠን


10 comments:

  1. ማስተዋሉን ይስጥህ ወዳጄ!

    ReplyDelete
  2. በማለዳ መያዠ ቁጥር 2 ብታነብ ይሄን ሁሉ ባልፃፍክ ነበር፡፡ ለምንድነው በዚህ ጉዳይ ያተኮርክ አባቶች አጀንዳ ያላደረጉት አንተ አጀንዳ የምታደርገውስ ስለምንድነው፡፡ ምን እናንተ ሰው ለምን አሜሪካ ይሄዳል ኢትዮጵያ የተባረከች ሃገር እያለችለት እያላችሁ አስተምራችሁ አሁን ምእመናን ትታችሁ ኑራችሁ አሜሪካ አድርጋቹሃል፡፡ እዚህ እያስተማሩ ህሙማን እየፈወሱ ትምህርተ ድህነት በሚሰጡ አባት ለምን ምቀኝነት አደረብህ፡፡ በሃይማኖት ያደራችሁ እነጂ ለሃማኖት ያደራችሁ አለመሆናችሁ ተረድተናል:: እግዚአብሔር ይማርህ ለእውቀት ለግርማ ሞገስ… ብለህ የተዋረስከው መንፈስ ካለ ጉባኤው መጥተህ እንድታስወጣው ብየ እመክርሃለው

    ReplyDelete
  3. Amen egziabher yirdan tibeb mastewalun yadilen

    ReplyDelete
  4. Why you didn't put your name and picture if you rally have genuine love for Ethiopian people. Instead of talking in the dark. You can also mention every one who involved in this unethical activities.
    I think there is a difference between sprinkling the holy water and Baptism.
    I wish I see you when you open your mouth more to oppose the demolishing of Monasteries like Waldba, the expansion of Mosques, and Khat, drug and prostitution culture.

    ReplyDelete
  5. Memiher girman lemekawem ebakachihu bemereja yehun .yalebeleza malazen new!!!!

    ReplyDelete
  6. gobez neqa belu yhe dregets MKn lemetlef beswur yemadeba mehonun ewequ

    ReplyDelete
  7. Replies
    1. እግዚአብሔር እምነታችን ያጽናልን በደነዚህ ዓይነት ሰዎች በጣም ተምታተናል፡፡

      Delete