Saturday, June 14, 2014

አባ ማትያት ፡- ከሕለተ ሙሴ ወደ ሕለተ ወርቅ


ከታደሰ ወርቁ
ቅዳሜ ሰኔ 7 2006 ዓ.ም ፋክት መጽሄት የተወሰ
  • አቡኑ ጉዱ ካሳን የሆኑ እስኪመስለን ድረስ የለውጥ አባት ተደርገው ተወሰዱ ፤ በቤተ ክርስያኒቱ ምሁራን ልጆች ተሳትፎ እየፈራረስ የነበረውን ጽመታዊ ቡድንን ከያለበት እየፈለጉ በማሰባሰብ ነፍስ ዘሩበት፡፡ቅዱስነታቸው ፤ ራሳቸውን ለአላስፈላጊ ተጽህኖ ያጋለጡበት ፈቃደኝነትና ዝግጁነት ቄሳራዊው ወገን ብቻ ሳይሆን ጽምታዊውም ቡድን ያልጠበቀው ምርኮ ኾነለት፡፡
  • ፓትያርኩ ቤተ ክርስቲያናችን ለመንፈሳዊ ተቋምነቷ የሚመጥኑ ሰዎች ሊመደቡላት እንደሚገባ ቢናገሩም በቅዱስነታቸው የሚታየው አቋም የለሽነትና አቅመ ቢስነት ከፍቶ አደባባይ ወጥቶ አሸማቃቂ ደረጃ ላይ ደርሷል፡፡
  • ቅዱስነታቸውን በክብረ-ክህነት ላይ አመንዝረው ፤ ከአባቶቻችን አዋራጆች ፤ ምሁራን ልጆቻቸውን በጠራራ ጸሀይ ለማስገደል ጭምር ከሚያሴሩ ፤ ቤተ ክርስቲያኒቱን በግላጭ ከሚዘርፉና ከሚመዘብሩ እንዲሁም ለመሰረተ እምነቷ  ፤ ለሥርዓቷ ፤ ለትውፊቷና  ታሪኳ ግድ ከማይላቸው አማሳኞችና ጽልመታዊ ኃይሎች ጋር የተሰለፉት ሕለተ ሙሴን ጠልተው ሕለተ ወርቅን በማፍቀር አባዜ ነው፡፡


(አንድ አድርገን ሰኔ 7 2006 ዓ.ም)፡-በአዲስ ፓትርያርክ ፤ ዋና ጸሐፊ እና ጠቅላይ ሥራ አስኪያጅ ሥራውን የጀመረው ቤተ ክህነት ባሳለፍነው ወርሀ ግንቦት አንደኛ አመቱን ይዟል፡፡ ይህው የአንድ ዓመት የሥራ ዘመን ገና ከጅምሩ ስለ ቤተ ክርስቲያኒቱ ተቋማዊ ለውጥ ብዙ የተለፈለፈበት ቢኾንም መሠረታዊ ችግሮቿን መፍታት ይቅርና አንዲት ክንድ አንኳን ፈቅ አላደረገውም፡፡ ዓመቱ ፤ በመልካም አስተዳዳር እጦት መንስኤ የኾኑት ብልሹ አሰራር - ሙስና- ጎጠኝነት ከየትኛውም ጊዜ በላይ ጎልተው የታዩበት ጊዜ ነበር ማለት ይቻላል፡፡

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ላለፉት ኻያ አንድ አመታት በርዕሰ አበውነት ‹ሲገዙ› የነበሩትን የብጹዕ ወቅዱስ አቡነ ጳውሎስን ሞትን አስከትሎ ስድስተኛውን ዘመነ ፕትርክና  የምደባ ያህል  የተረከቡት ብጹዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ  የቤተ ክርስቲያኒቱን ቀናኢ ሊቃውንትና ምእመናን ለዘመናት ሲያንገሸግሽ የቆየውን አድሏዊ አሠራር ፤ ጎጠኝነትና ሙስና በመጠኑም ቢኾን ይፈታሉ የሚል ግምት ተሰጥቷቸው ነበር፡፡


ይህም ያለምክንያት የተሰጠ ቅድመ ግምት አይደለም፡፡ ቅዱስነታቸው በአቡነ ጳውሎስ ዘመን ፕትርክና ይታዩ የነበሩትን  እነዚህን ችግሮች በማንሳት እንዲሁም በአቡነ ጳውሎስ ዘመን  ሊቃውንተ ቤተ ክርስቲያን ለሚጠይቋቸው የመብትም ሆነ ሌሎች ጥያቄዎች ተገቢ ምላሽ ማግኝት አለመቻላቸውን በየብዙኃን መገናኛ ማጋለጣቸው የመጀመሪያው  የቅድመ ነገር ምክንያት ነበር፡፡

በበዓለ ሲመታቸው ወቅት ንግግር ሲያደርጉ የቤተ ክርስቲያኒቱን ሊቃውንትና ምእመናን ብሶትና የዕለት ከዕለት ምሬት የተሰማቸው በሚመስል ሁኔታ  ትኩረት ሰጥተው ከሚንቀሳቀሱባቸው  የሥራ ዘርፎች  መካከል ፤ በዋነኝነት ሙስናንና ጎጠኝነትን መዋጋት እንደሚሆን መጥቀሳቸው ኹለተኛው የቅድመ ነገር ምክንያት ነበር፡፡

በዚህ ንግግራቸው ሳይወሰኑ ያስቀመጧቸውን ነጥቦች በቁርጠኝነት ወደ ስራ ለመለወጥ የተነሱ በመሚመስል አኳኋንና  በአምስተኛው ዘመነ ፕትርክና  ባልተለመደ ግለት ግንቦት 21 ቀን 2005 ዓ.ም በተካሄደው የቅዱስ ሲኖዶስ ምልዓተ ጉባኤ መክፈቻ ላይ ብልሹ አሠራርን ለማረምና ለማስወገድ የጸረ- ሙስና አብይ ኮሚቴ ፤ አስተዳደሩን በአዲስ መልክ ለማዋቀር የአስተዳደር ማሻሻያ አብይ ኮሚቴ ፤ የፋይናንስ አሠራር ስርዓት ለመዘርጋት ደግሞ የገንዘብ አያያዝ ማሻሻያ አብይ ኮሚቴ ፤ እንዲቋቋም የብዙኃን መገናኛ ጠርተው ማወጃቸው ሦስተኛ ቅድመ ነገር  ምክንያት ነበር፡፡ ቅዱስነታቸው በዚያ ታሪካዊ በሚመስል በኋላ ግን በብዙዎች ዘንድ ራስን ማስተዋወቂያ ተደርጎ በተወሰደው ስልታዊ ንግግራቸው ‹‹እነዚህን ሦስት መሰረታዊ እርምጃዎች የቤተ ክርስቲያኒቱን ጤናማ ሂደት የሚወስኑ እጅግ አስፈላጊ የሆኑ ርምጃዎች ናቸው፡፡ ስለዚህ የቀረበው ሀሳብ በአስቸኳይ ተግባራዊ እንዲሆን ቅዱስ ሲኖዶስ ቆራጥ ውሳኔ ሊሰጥበት ይገባል›› ካሉ በኋላ ‹‹ሥር ሰዶ የሚታየው አሳፋሪና አሳዛኝ አሠራር ሳይታረም ቢቀጥል ቤተ ክርስቲያኒቱ ከፍተኛ ችግር ውስጥ እንደምትወድቅ እኛንም በአመራር ላይ ያለነውን ብልሹነት ታሪክ እንዲወቅሰንና እንዲፈርድብን የሚያደርግ መሆኑን ልንገነዘብ ይገባል›› ሲሉም አስጠንቅቀው ነበር፡፡ አክለውም ‹‹በርምጃው ሥር ነቀል ለውጥ ለማምጣት ቆራጥነት ይጠይቃል ፤ በአጭር ጊዜ የተፈለገውን ለውጥ ለማምጣት የሚዳግት ቢሆንም የለውጡን መሠረት በአስቸኳይ ማስቀመጥና  አቅጣጫውን መቀየስ እጅግ አስፈላጊ መሆኑን ሊሰመርበት ይገባል›› ብለውም ነበር፡፡

ይህ አፍዓዊ መግለጫቸው ተከትሎም በቤተክህነቱ መዋቅራዊ ለውጥ ተደርጎ የአገልግሎት አሰጣጡ የቤተ ክርስቲያኒቱን ዋንኛ ተልእኮ ማስፈጸም የሚያስችል ይሆናል የሚል ግምት በብዙዎች  ዘንድ ተወሰደ፡፡ ቅዱስነታቸውም  በአንድ አመት በዓለ ሲመት አከባበር ሥነ-ሥርዓት ላይም ‹‹የዛሬ ዓመት የተናገርኳቸው ቃላት ኹሉ እንደጸኑ ናቸው ፤ አልተበረዙም ፤ አልተከለሱም ፤ እንዲያውም ከቅዱስ ሲኖዶስ አባላት ፤ ከሊቃውንተ ቤተ ክርስቲያን ከምእመናን ጋር በመሆን አጠነክራቸዋለሁ›› ከማለት አልፈው ለተቋማዊ ለውጡ በቁርጠኝነት የተነሱ በሚመስል ሁኔታ  በለውጡ ወሳኝ በሆኑ ጉዳዮች  ላይ የተለያዩ የጥናት ቡድኖች እንዲቋቋሚ በጎ ፍቃዳቸውን ያሳዩ መስለው ‹ተወኑ› ፡፡ በአንዶቻችን ዘንድ አቡኑ ጉዱ ካሳን የሆኑ እስኪመስለን ድረስ የለውጥ አባት ተደርገው ተወሰዱ፡፡

በኋላ ግን ኾነው የተገኙት መስለው የተናገሩትን ሳይሆኑ ከቅድስት ሀገር እየሩሳሌም እስከ አሜሪካ ኖረውታል የሚባለውን ምንነታቸውንና ማንነታቸውን ነው፡፡ መልካም አስተዳደር በማስፈን ኾነ ጎጠኝነትን ኾነ ጥቅመኝነትን መሠረት ያደረጉ አድሏዊ አሠራሮችን በማስቀረት ፤ ሙስናን በመዋጋትም ኾነ በቤተ ክህነቱ አገልግሎት አሰጣጥ ላይ የሊቃውንቱንና  የምእመኑን ቅሬታ የሚፈቱና አመኔታቸውን ያተረፉ ኾነውና በቅተው አልተገኙም፡፡

ይባስ ብለው ሞያዊ እውቀታቸውን ለቤተ ክርስቲያን እድገትና ደህንነት አስራት አድርገው ያቀረቡ ሙያተኞችን አግልለው ድጋፍ ነስተው ፤ ከቤተ ክርስቲያን ጥቅም ይልቅ የራሳቸውን ጥቅም ከሚያስቀድሙና  ለቤተ ክርስቲያኒቱ እድገትና ለውጥ የዘመናት እንቅፋቶች የሆኑ አማሳኞችና አድር-ባር ፖለቲከኞች ጋር ማኅበርተኝነት መስርተው ተገኙ፡፡ ርእሰ አበውነታቸውን ዘንግተው የስርዓቱ ጭቃ ሹምና ምስለኔ በመሆን የማይገባቸውን ሥልጣን ከሚገባቸው ነጥቀው  ከያዙት ፤ ድኻውን ካህን ባለፉት 23 ዓመታት ሲበዘብዙ እና ሲያሰቃዩት ከኖሩት ፤ የካህኑን ቤተ-ሰብእ ለዘመናት ከእጅ ወደ አፍ የሠቆቃ ኑሮ እንዲገፋ ካደረጉት ፤ ሊቃውንቱን በተዋራጅነት ፤ በድህነት ፤ በእርዛትና በበሽታ እየተሰቃዩ እና እየተጎሳቀሉ አስከፊ ኑሮ እንዲያሳልፉ ያደረገውን አማሳኝና አድር ባይ  ቡድን ጠባቂ ሆነው አረፉት፡፡

ከመንበረ ፕትርክና እስከ አጥቢያ አብያተ ክርስቲያናት  ድረስ ያለውን አገልጋይ ጭሰኛ አድርገው ያለዋስትና ከሥራው ሲያፈናቅሉት ከኖሩት ከመንበረ ፓትርያርክ ጅራፍ አውራጆችና በእልቅና ወንበር ከተቀመጡ የአጥቢያ ምሽሮዎች ጋር በመሆን ፤ የብዝበዛውን መረብ ይበልጥ ለማጠናከርና ምቹ ሁኔታ እንዲፈጠርላቸው የሚያስችላቸውን የስልጣን ከለላ በመስጠት ፤ የእነርሱ አገልጋይ እና የብዝበዛው ተባባሪ ሆነው እንዲታዩ አደረጓቸው፡፡ እውነተኛው አገልጋይ በዚህ የዘመናችን መልከኞች መብቱን ተገፎ ለብዝበዛ በመጋለጡ ከመላ ቤተሰቡ ጋር በችግር ሲማቅቅ ፤ እነርሱ የመዘበሩትን የቤተ ክርስቲያን ገንዘብ ቤተ ክርስቲያኒቱን ለማተራመስ ከሚጠቀሙት ጋር  ግንባር ፈጥረው ተገኙ፡፡

እንደ አምስተኛው ዘመነ ፕትርክና ሁሉ በስድስተኛው ዘመነ ፕትርክና ለቤተ ክርስቲያኒቱ ልዕልና ክብር የደከሙላትን መስዋዕትነት የከፈሉ ሊቃውንት ፤ ቢያንስ ፍትሀዊ አስተዳደር ሲጠብቁ ፤ የቤተ ክህነቱ የዘመናት አድ-ባይ ቡድንና የአጥቢያ አማሳኞች ግንባር ፈጥረው የፓትርያርክ አባ ማትያስ የአስተዳደራቸውን ባለሟልና ባለጊዜዎች በመሆን ለሹመት ፤ ለሽልማቱ እና ለጥቅማ ጥቅሙ በመጀመሪያ ረድፍ ተሰለፉ፡፡ ሊቃውንቱ ለቤተ ክህነቱ ባይተዋርና የበይ ተመልካች እንዲሆኑ የሚያደርጉ ጸረ-ምሁራን ፤ ጸረ-ሊቃውት አስተሳሰቦች ፤ አቋሞችና ድርጊቶች መታየታቸው ቀጥሏል፡፡

በቤተ ክርስያኒቱ ምሁራን ልጆች ተሳትፎ እየፈራረስ የነበረውን ጽመታዊ ቡድንን ከያለበት እየፈለጉ በማሰባሰብ ነፍስ ዘሩበት፡፡ በመንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ቤተ ክህነት ጽ/ቤት የስብከተ ወንጌል እና ሐዋርያዊ ተልእኮ መምሪያ ከኢትዮጵያ መጽሐፍ ቅዱስ ማኅበር ጋር በመተባበር የካቲት 21 እና 22 በአዘጋጁት ሀገር አቀፍ የስብከተ ወንጌል የምክክር ጉባኤ ወቅት ቅዱስነታቸው አድርገውት በነበረው ንግራቸው ላይ ‹‹ከዩኒቨርሲቲ ተመርቀው ቤተ ክርስቲያንን እንምራ እያሉ ነው ፤ ቤተ ክርስቲያኒቱ ትውፊትና ስርዓት አላት ፤ እንዲህ ማለት አይችሉም ፤ በባይሎጂ እና በኬሚስትሪ እንቀድስ ይላሉ›› የሚለውን ክሥና ወቀሳም ይህንን ያረጋገጠ ነበር፡፡

ይኽውም ከመንፈሳዊነትና ሞያዊነት ይልቅ በጥቅመኝነትና ጎሰኝነት የተሳሰሩ አማሳኞች በፓትርያርኩ አስተሳሰብ ላይ የፈጠሩት የጸረ መንፈሳዊነትና የጸረ ምሁርነት ተጽህኖም የተጋለጠበት ከመሆኑም በላይ ‹‹ቤተ ክርስያኒቱን በሰለጠ እና በተማረ ኃይል አንቀሳቅሳለሁ ሙስናንና ብልሹ አሰራርን አስተካክላለሁ ፤ ታማኝነት ፤ አቀኝነትና  ተጠያቂነትን አሰፍናለሁ›› ዓይነቱና የመሳሰለው ንግግራቸውም ‹‹ሥር በሰደደ ችግር መፍትሄ አማራጭ መስለው ራሳቸውን ያስተዋወቁበት ፤ ከውስጥ እምነታቸው ያልመነጨና የተጫናቸው›› መሆኑም የተረጋገጠበት ኾኗል፡፡

‹‹ቅዱስ ሲኖዶስም ከምንም በላይ በራሱ መተማመን አለበት ፤ ከእግዚአብሔር በታች  እምነቱ እና ትውክልቱ በቤተ ክርስቲያን ላይ መሆን አለበት ፤ ቤተ ክርስቲያኒቱም ነቅቶ እና ተግቶ የመጠበቅ ሓላፊነት አለበት››  ብለው በዓለ ሲመታቸውን የመከሩት ቅዱስነታቸው ፤ ራሳቸውን ለአላስፈላጊ ተጽህኖ ያጋለጡበት ፈቃደኝነትና ዝግጁነት ቄሳራዊው ወገን ብቻ ሳይሆን ጽምታዊውም ቡድን ያልጠበቀው ምርኮ ኾኖለታል፡፡ በርዕሰ መንበርነት ለሚመሩት ቅዱስ ሲኖዶስ እና በብዙ ሚሊየን የሚልቁ አገልጋዮችና ምዕመናን በርእሰ አበውነት የተሰየሙበት መንበረ ተክለሃይማኖት ፤ ከውስጣዊ እና ውጫዊ ግለሰባዊ እና ቡድናዊ  ጣልቃ ገብነትን ተከላክለው መመሪያውንና ውሳኔውን በማስፈጸም ልዕልናውን ማስከበት ተስኗቸው እየዳከሩ ይገኛሉ፡፡

ቅዱስነታቸው ግንቦት 21 2005 ዓ.ም በመጀመሪያ ጊዜ ለመሩት የቅዱስ ሲኖዶስ ምልዐተ ጉባኤ መክፈቻ ላይ ባደረጉት ንግር ፡- ‹‹የቤተ ክርስቲያኗ አስተዳደር  ሒደት ሲመረመር ግን  እጅግ የተንዛዛ ቢሮክራሲ የሰፈነበትና  የሰው ኃይል አመዳደቡም ከመሠረታዊ  ተልእኮ ፤ ተግባርና እቅድ ጋር ያልተቀናጀ ከመሆኑ በላይ የሰራተኛው አቀጣጠርና የስራ ችሎታ ፤ ዕውቀትንና ልምድን እንደ መስፈርት ወስዶ የተፈጸመ ባለመሆኑ የሰራተኛው ቁጥር ከሚያስፈልገው በላይ ወጥቶ ይታያል ፤ ወደ ውስጥ ገባ ብሎ ሲመረመርም በወገንተኝነትና በሙስ የተቀጠረ መሆኑንና እንዲሁም አፈጻፀሙ የተለያዩ የስነ ምግባር ብልሹነት በስፋት የሚያንጸባርቅ ሆኖ ይስተዋላል፡፡ ይህ ከቤተ ክርስቲያኒቱ ክብርና ቅድስና ጋር የማይጣጣም ሂደት በመሆኑ ሁኔታው ለማረም ቅዱስ ሲኖዶስ አስቸኳይ እርምጃ ሊወስድ ይገባል፡፡›› ማለታቸው ይታወሳል፡፡

እጅግ የሚያሳዝነውና የሚያሳፍረው ግን ፤ በዚህ መልኩ በራሳቸው አንደበት የጠቀሷውን የቤተ ክርስቲያኒቱን መሰረታዊ የአስተዳደር ችግር ይፈታል ተብሎ ተስፋ የተጣለበትን የተቋማዊ ለውጥ ግስጋሴ በአማሳኙ ቡድን አባላት ጎትጓተኝነት ፤ በሙሰኛ የደኅንንት  ነን ባይ ግለሰባዊ አጋፋሪነትና የራሳቸው የቅዱስነታቸው ሽንፍ ስነ ልቦና በወለደው  ተንበርካኪነት የተነሳ የተገታ መስሎ ይታያል፡፡ ቅዱስ ሲኖዶስ ለተቋማዊ ለውጥ ጥናቶች የሰጠውን ይሁንታንና የአፈጻጸም አቅጣጫዎች በአማሳኞቹ ምክር ማገት ሳይበቃቸው ይባስ ብለው የቤተ ክርስቲያኒቱን የተቋማዊ ለውጥ እድሎችና ተስፋዎች ሲያመክን ከኖረው ጽልመታዊ ሃይል ጋር  በጎጠኝነት ተሰልፈዋል፡፡  በዚህም ሳቢያ በአመራራቸው ላይ ቅሬታና እምነት ማጣት እየተባባሰ ሲሄድ ይታያል፡፡ ፓትያርኩ ቤተ ክርስቲያናችን ለመንፈሳዊ ተቋምነቷ የሚመጥኑ ሰዎች ሊመደቡላት እንደሚገባ ቢናገሩም በቅዱስነታቸው የሚታየው አቋም የለሽነትና አቅመ ቢስነት ከፍቶ አደባባይ ወጥቶ አሸማቃቂ ደረጃ ላይ ደርሷል፡፡ ጥቂት በማይባሉ ሰራተኞችና አገልጋዮች ዘንድ ደግሞ አቅመ ቢስነቱ እና አቋመ ቢስነቱ ንቀትና ጥላቻን ከማስከተሉም በላይ ፤ የቀድሞውን ፓትርያርክ በደል አስረስቶ ዘመነ ፕትርክናቸውን ብዙዎች እንደ መልካም ትዝታ የሚያወጉትና የሚጨዋወቱበት ኾኗል፡፡        

በዘንድሮ የግንቦት ቅዱስ ሲኖዶስ ምልዓተ ጉባኤ  ስብሰባ ቅዱስነታቸው ከምልዓተ ጉባኤው ቁጥጥር ውጪ የሆኑበት  አግባብ ከቤተ ክርስቲያኒቱ  የአደረጃጀትና የአሰራር ለውጥ ተቃዋሚ አማሳኞች ጋር የፈጠሩት ቁርኝት በገሐድ  ያረጋገጠ ከመሆኑም በላይ  ከሕለተ ሙሴ ወደ ሕለተ ወርቅ  ውላጤ የማድረጋቸው ትእምርት  ተደርጎ ሊወሰድ ይችላል፡፡  የምዕራብ ሸዋ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ብፁእ አቡነ ኤጲፋንዮስ በምልዓተ ጉባኤው መካከል ቆመው ቅዱስነታቸውን  ‹‹ ገና አንድ ዓመት ሳይሞላዎት  ለምነው አብረው ይስሩ ያሏቸውን  ሊቀጳጳስ በመገፍተር  ኃይልዎን ማሳየትዎ እንዴት ነው ? ሥራ ሆኖ የሚቀጥለው ከወዲሁ እንዴት ነው ? የሚገፋው ? ›› ብለው መናገራቸው በራሱ በእውንነት  ከወሰድነው  ፓትርያርክ አባ ማትያስ ከሕለተ ሙሴ ወደ ሕለተ ወርቅ መሸጋገራቸውን ያረጋግጥልናል፡፡

በዚህ አውድ ሕለተ ሙሴ የእወነተኛና ቸር እረኝነት ትእምርት ሲሆን ሕለተ ወርቅ ደግሞ የአጤያዊ አምባገነንነት ትእምርት ነው፡፡ በመጀመሪያው ራስን ስለመንጋው አሳልፎ መስጠት  ፤ ራስን መካድና መስቀል መሸከም ፤ ስለ ቤተክርስቲያን ክብርና ልዕልና መስዕዋት መሆን  ፤ ስለገቡት ቃልና ሃላፊነት ፤ ስለ ስርዓተ አበውና ቀኖና መታመን ፤ በራስ ቅድስና ሌሎችን መቀደስ  ፤ በመልካም አርአያነት በምእመናን ዘንድ መታፈር ፤ በጥብአት አጥፊ ሹማምንትን መገሰጽ ፤ በብሔራዊ በአህጉራዊ እና አለም አቀፋዊ ተደማጭነት ሲኖርበት  በሁለተኛው ደግሞ ስለ መንበር መንጋውን አሳልፎ መስጠት ፤ ለራስ አጤያዊ ስርዓት መቆርቆርና መስቀሉን ከባሕርያዊ እሴቱ አርቆ እና አውጥቶ በጌጥነት መጠቀም  ፤ ስለ ራስ ክብርና ዝና መጨነቅ ፤ ቃለ-አባይ ሆኖ መገኝት ፤ ከስርዓተ አበውና ቀኖና ቤተ ክርስቲያ በላይ ግላዊ ደማዊ እና  ሥጋዊ ፍቃዳትን አግዝፎ መታየት ፤ ተኣምኖን በቤተ መንግሥቱ ማድረግ ፤ የቅጥረኝነትንና የተላላኪን አገልግሎት መስጠት አለበት፡፡

ቅዱስነታቸው ፤ ከሕለተ መሴ ወደ ሕለተ ወርቅ ውላጤ አድርገዋል ስንል  በመጀመሪያ የዘረዘርናቸውን የሕለተ ሙሴ መገለጫዎችን በፈቃዳቸው ትተው በሁለተኝነት የዘረዘርናቸውን የሕለተ ወርቅ  መገለጫዎችን ገንዘብ አድርገዋል ማለታችን ነው፡፡ ይህ ደግሞ ከአምልኮተ እግዚአብሔር  ወደ አምልኮተ ጣኦት መሔድ በአመንዝራነት የማስቆጠሩን ያህል ከሕለተ ሙሴ ወደ ሕለተ ወርቅ ውላጤ ማድረግ በክብረ ክህነት እንደማመንዘር ይቆጠራል፡፡

በታሪካችን እንኳን ሰማዕተ ጻድቅ ብጹዕ አቡነ ጰጥሮስና ብጹዕ አቡነ ሚካኤል ሕለተ ወርቅን ተጸይፈው ሕለተ ሙሴን አፍቅረው ለቤተ ክርስቲያን ክብርና ልዕልና ፤ ለአገርና ለሕዝብ ነጻነት በኦርቶዶክሳዊ ጥብዐት ሰማዕት ሲኾኑ  ፤ ሕለተ ሙሴን ትተውና ቀብረው ፤ ሕለተ ወርቅን ወድደውና አፍቅረው የአገር ዳር ድንበር የደፈረውን ፤ ሉአላዊ ክብራችንና ልዕልናችንን የገፈፈውን ፤ ሕዝባችንን በቦንብ ያቃጠለውን ፤ ገዳማትንና አድባራትን ያጋየውን የፋሽስት ጦርን ያስተናገዱ ሌሎችም ነበሩ፡፡ ዛሬ በቤተ ክርስቲያናችን እየኾነ ያለው በቅርጽ ሳይሆን በይዘት አንድ ነው፡፡

ቅዱስነታቸውን በክብረ-ክህነት ላይ አመንዝረው ከአባቶቻችን አዋራጆች ፤ ምሁራን ልጆቻቸውን በጠራራ ጸሀይ ለማስገደል ጭምር ከሚያሴሩ ፤ ቤተ ክርስቲያኒቱን በግላጭ ከሚዘርፉና ከሚመዘብሩ እንዲሁም ለመሰረተ እምነቷ  ፤ ለሥርዓቷ ፤ ለትውፊቷና  ታሪኳ ግድ ከማይላቸው አማሳኞችና ጽልመታዊ ኃይሎች ጋር ተሰልፈው በመጀመሪያዎቹ ገጾች የጠቀስናቸውን የድፍረት ጥፋቶች እንደፈጸሙና ከገቡት ቃል በተቃራኒው እንዲቆሙ ኃይልና ብርታት የሆናቸው ይህው የትላንት ደዌያችን ፤ ሕለተ ሙሴን ጠልቶ ሕለተ ወርቅን በማፍቀር አባዜ ነው፡፡

የቅዱስነታቸው በዚህ አሳዛኝና አሳፋሪ ኹኔታዎች ውስጥ መገኝት ቤተ ክርስቲያናችን ተዘርዝረው በማያልቁ  ከተከማቹ አስተዳደራዊ ችግሮች  ጋር እንድትተበተብ እንድትቀጥል እያደረገ መኾኑ እሙን ነው፡፡ እነዚህ ችግሮች እንዲቃለሉ ሳይሆን እንዲወሳሰቡና እንዲጠልቁ ከአገሪቱ የፖለቲካ እውነታ ጋር የሚመጋገበው ቅዱስነታቸው ሕለተ ወርቅነትን  ብቻ ሳይሆን የቅዱስ ሲኖዶሱን አካላትና አሠራር በመቆጣጠር ቤተ ክርስያኒቱን የቆብ ደሴት ለማድረግ የተያያዘው አቅጣጫ ጭምር ነው፡፡    

በዚህም የተነሳ የቤተ ክርስቲያናችን አስተዳደር ከቀናነትና ከጽናት እየራቀ እንጂ እየቀረበ የሚሄድ አልሆነም፡፡ ዛሬ ቤተ ክርስቲያናችን አስተዳደራዊ እና መዋቅራዊ ሕይወት  ፤ ይህን አቅም በተግባር ላይ ለማዋል በሚችሉ ኃይሎች እጅ እንዲሆን አላበቃውም፡፡ የቤተ ክርስቲያኒቱን የላዕላይና ታህታይ መዋቅር ሥልጣን የተቆጣጣሩት ጥቁር ራሶችም ፤ ከቤተ ክርስቲያን ጥቅም በፊት የራስን ስልጣን ለማስቀጠልና ከዚህ ስልጣን የሚገኝ ጥቅም በሙሉ እያግበሰበሱ ለመኖር ቆርጠው የተነሱ ኃይሎች በመሆናቸው ፤ ሕለተ ወርቅነትንም ሆነ የቆብ ደሴትነትን መግራት አልቻሉም፡፡ ለዚህ እንዴት እንደበቃን በሚገባ መረዳት ተመሳሳይ የሆነ ወይም የከፋ ውድመት በቤተ ክርስቲያናችን ላይ እንዳይደርስ ለመከላከል ያስችለናል የሚል እምነት አለኝ፡፡

የሥርዓትና የትውፊት ግምጃ ቤት እያሉ ፤ ያለፈውን ዘመን ታላቅነቷን እና ልዕልናዋን ብቻ እየተረኩ ፤ ነገር ግን ቤተክህነቱ ያለበትን ድቅድቅ ጨለማ እና ስልጣኔ አልባ ሕይወት ፤ የመንፈሳዊ እና አስተዳደራዊ ልዕልና መላሸቅ  እንዳለዩ ሆኖ ማለፍ የሚቻልባቸው ዘመናት ያበቃ ይመስለናል፡፡

ቤተ ክርስቲያን ከረጅም ውጣ ውረድ ፤ ብዙ ችግርና ፈተና ከሞላው ታሪኳ በእነዚህም ታሪኮች ውስጥ አባቶች ያሳዩት ተጋድሎና  ለሀገሪቱ ከከፈሉት መስዋዕትነት ጋር የማይመጥን አስተዳደራዊ እና ልማታዊ ደረጃ ላይ መገኝቷ  ፤ እጅግ የሚያንገበግበው ልሂቃዊው ትውልድ መምጣቱንም ማጤን ያስፈልጋል፡፡  ይህ ትውልድ በአንድ በኩል በሀገሩ እና በቤተ ክርስቲያኑ የቀደመ ታላቅነት እና ነጻነት የሚኮራ ፤ በሌላ በኩል ደግሞ በቤተ ክህነቱ የሚታየውን የጎጠኝነት ፤ ብኩንነት ፤ ብልሹ አሰራር እና ምዝበራ በመሳቀቅ ለመፍትሄ እየተጋ ያለ ትውልድ ነው፡፡ ቅዱስነታቸው በጎሳዊ ፤ ጥቅማዊ እና ፖለቲካዊ ተዛምዶ ለሕለተ ወርቅ ያስገበረው የአማሳኞች ስብስብ ተቋማዊ ለውጥን ከጎጠኝነትና ጥቅመኝነት ጋር እያገናኝ የጸረ ሙስና ትግል አንድነት ለመከፋፈል ቢጥርም እነዚህ ኦርቶዶክሳዊያን ኃይሎች ከየትኛውም ጎሳ ሊመዘዝ የሚችል የትውልድ ታሪክ ያላቸው መኾኑ ፤ ኹሉም በጋራና በአንድነት ቤተ ክርስቲያናቸውን ከተጋረጡባት አደጋ ለመጠበቅ በቅተዋል፡፡

ከዚህ አኳያ አንድ ነገር እርግጠኛ መሆን ይቻላል ፤ ጎጠኞችና ስግብግቦች ዛሬ ፓትርያርኩን ከብበው ሕለተ ሙሴነታቸውን አውርደው ለሕለተ ወርቅ የዳረጓቸውና  የቤተ ክርስቲያናችንን የትርምስ አጀንዳ የሚቀርጹት አማሳኞች ከሀዲነታቸውንና ሌብነታቸውን ለመሸፈን የሚጠቀሙበት የጎሳ ፖለቲካ  ማጭበርበር በዝምታ የማይታለፍበት ዘመን እየቀረበ ስለመኾኑ!!

በመጨረሻም ለቅዱስነታቸው ግንዛቤ አንድ ነገር ላስቀምጥ፡፡ ፀሮቻቸው በሕይወት አሉ፡፡ ግን በቤተመቅደስ አይኖሩም፡፡ ልጆቻቸው ግን በቤተመቅደሱ በሕይወት ልዕልና የድኾች ከተማ በሚሉት ዓይነትና ኹኔታ በእውነትና በትሩፋት አጊጠው ይኖራሉ፡፡


ቸር ሰንብቱ

6 comments:

  1. መመካር ጠፋ ማለት ነው ?

    ReplyDelete
  2. andadirgen እግዚአብሔር ይቅር ይበላቹ።ኣባቶች ላይ የድፍረት ቃል መናገር ለማንም ኣይበጅም። ልቦና ይስጣቹ

    ReplyDelete
  3. awey betekehnet!1

    ReplyDelete
  4. Enen yemigermegn yemimenan fetena alemaleku. Be alem fetena, beras dikmetna mignot fetena, bemenafiqan fetena, yibas bilo be Abotoch FETENA????!! Minew egziabhere betareqen hulachinim Egzio enbel. Ebakachihu kirstianoch wede Egziabhere enmeles, yesew haTi'at mawrat yibkan.
    PRAY FOR GOD!!!
    welete Amanuel

    ReplyDelete
  5. ሰላም ጤና ይስጥልኝ።

    አቶ መለስንና አባ ጳውሎስን ባንድ ላይ ሲያሰናብት እግዚአብሔር መልእክት ነግሮናል። መቅሰፍትነቱ ግልጽ ነበር።
    ያላወቅነው ግን ሌላ መልእክት አለ። ሁለት ወሳጆችን በንድ ላይ ወስዶ ኃይማኖቱን የቀየረ የሃገር መሪና አገሩን የቀየረ የሃይማኖት መሪ ባንድ ላይ ለምን ሰጠን? የዚህ ነገር ሚስጢሩ ምንድን ነው? ኃይማኖታችን ስንተው አገራችን አጣን ነው? አገራችን እንድናገኝ ኃይማኖታችን እናግኛት ነው? እኛ የነዛን ኃይማኖት ስንወስድ እነሱ የኛን አገር ወሰዱ ነው? ሚስጢሩ ምን ይሆን? ለብዙ ጥያቄዎች መልስ እዛ ውስጥ ያለ ይመስለኛል።

    ምስጋና ለመድኃኔዓለም።
    ኃይለሚካኤል

    ReplyDelete
  6. Ye hulachen hatiyat bezat nw betekerestiyanen le fetena yedaregat!!! Esti hulachenem wede Fetari enetseley?????

    ReplyDelete