Tuesday, June 3, 2014

‹‹ወእጨጌ ዘመንበረ ተክለ ሃይማኖት››



 (አንድ አድርገን ግንቦት 26 2004 ዓ.ም)፡-
ፕሮፌሰር ታደሰ ይባላሉ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የታሪክ ፕሮፌሰር  ሲሆኑ የዩኒቨርሲቲው የመጻሕፍት ዝግጀት ተቋም ዳይሬክተርና ዋና አዘጋጅ በመሆን አገልግለዋል፡፡ በአሜሪካ ሀገር በኮኔል ፤ ኖርዝዌስት ዩኒቨርሲቲ ኢሊኖይ ስቴት ዩኒቨርሲቲ በጎብኝ ፕሮፌሰርነት ከማስተማር በተጨማሪ በሳባቲክና ፈቃዳቸውን  በፈረንሳይ ሀገር ባሳለፉት ዓመት በታዋቂው ኮሌዥ ዲፍራንስና በፓሪስ ዩኒቨርሲቲ እየተጋበዙ ጥናታዊ ጽሑፎችን ያደረጉ ምሁር ናቸው፡፡ እኚው ፕሮፌሰር በጦቢያ መጽሔት ቅጽ 5 ቁጥር 10 1990 ዓ.ም በአምስተኛው የፕትርክና ዘመን ለብጹዕ ወቅዱስ አቡነ ጳውሎስ የተሰጠውን ‹‹ወእጨጌ ዘመንበረ ተክለ ሃይማኖት››ን ማዕረግ አሁንም የቀጠለው መጠሪያ በሚመለከት ተጠይቀው የመለሱት መልስ ለማስቃኝት ወደድን ፡፡ ከዚህ ጋር በተያያዘ ‹‹ሊቀ ጳጰስ ዘአክሱም›› የሚለው መጠሪያ ላይም ውዝግብ እንደነበር የምናስታውሰው ነገር ነው፡፡


ጦቢያ፡- ፓትርያርኩ(አቡነ ጳውሎስ) ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ባላቸው ማዕረግ ላይ ‹‹ወእጨጌ ዘመንበረ ተክለ ሃይማኖት›› እየተባሉ መጠራት ጀምረዋል፡፡ ‹‹እጨጌ›› ምን ማለት ነው? በመጠሪያው መጠራታቸው ተገቢ ነው ?

ፕሮፌሰር ታደሰ፡- ‹‹እጨጌ›› የሚለው ማዕረግ ስም በደብረ ሊባኖስ ገዳም በጻድቁ በአቡነ ተክለ ሃይማኖት መንበር  ተተክተው ይሰሩ የነበሩ ብዙ ቅዱሳን አባቶች ለምዕታት ዓመታት ሲጠሩበት የቆዩበት ስም ነው፡፡ ማዕረጉ ግን በአንድ ገዳም አበ ምኔትነት ብቻ የሚወሰን ሳይሆን ቀደምት ጳጳሳት ከግብጽ ይመጡ በነበረበት ዘመን ከጳጳሳቱ ቀጥሎ በሁለተኛ መንፈስ አባትነት የተመደበው ቅዱስ ኢትዮጵያዊ የሚጠራበት ስም ነበር፡፡ ለገዳሙ አስተዳደር ከበታች ‹‹ጸባቴ›› የተባለ እንደራሴ  እየተሸመ እጨጌውን በበላይነት በአገር አቀፍ ደረጃ ይሰራ ነበር፡፡

በተለይ በአጼ ዘርዓ ያዕቆብ ዘመን ጀምሮ የደብረ ሊባኖስ መሪ የገነነ ስም እያገኝ ሄዷል፡፡ ከውጭ የሚመጡት ጳጳሳት የሀገር ቋንቋ  የማይናገሩ ፤  የሕዝቡን ባህልና ወግ የማያውቁ  ፤ በአስተርጓሚ ክህነት ለመስጠት ብቻ የመጡ ባይተዋሮች ስለነበሩ እጨጌው ትልቅ ስልጣን ነበረው፡፡
ታዲያ የአሁኑ ፓትርያርክ(አቡነ ጳውሎስ)  በቅዱስ ሲኖዶስ ውይይት እንዲደረግበት ቀስቅሰውና ፤ በሃሳቡ ጓደኞቻቸውን አሳምነውና ሁሉም አስፈላጊነቱን ተስማምተው በማዕረጉ ቢጠቀሙበት ይህንን ያህል ጉዳት ያለው አይመስለኝም፡፡(ቅዱስ ሲኖዶስ ሙሉ ስምምነት ላይ አልደረሰበትም) እንዲያውም እንደማስታውሰው ብጹዕ ወቅዱስ አቡነ ባስልዮስ በመጀመሪያ ላይ ይጠቀሙበት የነበረ ይመስለኛል፡፡ከመጰጰሳቸው በፊትም ቢሆን እጨጌ ገብረ ጊዮርጊስ ተብለው ለብዙ ዓመታት አገልግለውበታል፡፡ ታዲያ ሲጰጵሱ በመሸጋገሪያው ዘመን  ላይ ማዕረጉን ደርበው መያዛቸው የፖለቲካ ትርጉም ያለው ይመስለኛል፡፡ ከእርሳቸው በኋላ ሌላ እጨጌ እንዳይሾም ፤ የማዕረጉ ታሪካዊነት ያበቃለት መሆኑን ፤ ሌሎች ሹመት ፈላጊ መነኮሳትም ማዕረጉን እንዳይመኙት ለማበከርም ጭምር ነበር፡፡ ከዚያ በኋላ ግን ብጹዕ ወቅዱስ አቡነ ቴዎፍሎስም እንኳን ሲጠቀሙበት አላስታውስም፡፡

ለማንኛውም ጉዳዩ አሁን ጥያቄ የበዛበት የቅዱስ ሲኖዶስ ዋና ዋና አባላት እንኳ በቅድሚያ በመነጋገር መሉ ለሙሉ ተስማምተው ፓትርያርኩ እንዲጠቀሙበት በግልጽ ባለመስጠታቸው ይመስለኛል፡፡ይሁንና  በማዕረጉ ባይጠቀሙበትም ያላቸው ታላቅ መንፈሳዊ ስልጣን ቅንጣት ያህል እንኳን አይቀንስባቸውም፡፡ ቢጠቀሙበትም ከስማቸው ረዘም ባለ ማዕረግ ዝርዝር ሲታጀብ ሊገኝ ከሚችለው እርካታ ሌላ ምንም አይጨምርላቸውም፡፡ የአቡነ ጳውሎስ ሙሉ መጠሪያ ስማቸው ‹‹ብፁዕ ወቅዱስ ዶክተር አቡነ ጳውሎስ ቀደማዊ ፓትርያርክ ርዕሰ ሊቀነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ ሊቀ ጳጳስ ዘአክሱም ወእጨጌ ዘመንበረ ተክለ ሃይማኖት የዓለም አብያተ ክርስቲያናት ምክር ቤት ፕሬዝዳንት፣ የዓለም ሃይማኖቶች ለሰላም የክብር ፕሬዝዳንት ፣ የዓለም የሰላም አምባሳደር  . . .. . .›› ነበር፡፡

 ብዙ ነገር የዳሰሱበትን ሙሉ ቃለ ምልልሱን ሌላ ጊዜ እንመለስበታለን

No comments:

Post a Comment