Monday, June 16, 2014

‹‹የተቀደሰችው ደጅ ከዚህ በላይ መርከስን ማስተናገድ የለባትም›› መምህር ተስፋዬ ሸዋዬ

 • ኢትዮጵያ እና ኦርቶዶክሳዊት ተዋሕዶ ሃይማኖት ተለያይተው አያውቁም፡፡
 • ኦርቶዶክሳዊት ቤተ ክርስቲያን ኢትዮጵያ ከነበራት የቀድሞ ስፋትዋ ቢያንስ አሁን ባለችበት ቅርጽና ይዘት እንድትቆይ በማድረግ ባለውለታ ናት እንጂ ሀገር ያደኸየች አይደለችም፡፡
 • ድርሳንና ገድላትን የሚነቅፏቸው ከርዕይ ያልደረሱ ጣዕመ ጸጋ ያልቀመሱ ዐይኑ ግንባር ሆኖ እንደተፈጠረው የጤሜዎስ ልጅ በርጤሜዎስ ግንባር የሆነ ዐይነ ነፍሳቸው በክርስቶስ ጣት ያልተዳሰሰ በመለኮት ምራቅ ያልራሰ ሰዎች ናቸው፡፡
 • …. ከባለቤቱ የእግር ሰላም አንዲት ጠብታ እንዳይቀርባት በፍቃዷ ከግብጽ ጳጳሳትን ስታስመጣ ኖራለች፡፡ ያስገደዳት አልነበረም የአባቶቻቸውን ቃል ውሉድ በፍቅር ሲጠብቁት ኑረዋል እንጂ ከግብጻውያን ያገኝችው ትምህርት የለም፡፡


(አንድ አድርገን ሰኔ 9 2006 ዓ.ም)፡-
በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን ውስጥ ከሃይማኖቷ ፤ አስተምህሮዋ እና ቀኖና ውጪ የሆኑ ድርጊቶች በመስፋፋት ላይ ይገኛሉ፡፡ ይህን ድርጊት በሚመለከት መምህር ተስፋዬ ሸዋዬን እንደ አንድ የእምነቱ ተከታይ ግለሰብ ያላቸውን ሃይማኖታዊ አስተያየት ለፎከስ መጽሔት ሰጥተው ነበር፡፡ የዚህንም ቃለ መጠይቅ ምላሽ እንደሚመለከተው አቅርበነዋል፡፡

ፎከስ፡- የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ እምነት መቼ እና እንዴት ተጀመረ?
መምህር ተስፋዬ፡- ኢትዮጵያ ሀገረ እግዚአብሔር የምትባልበት ምክንያት በሦስቱም ሕግጋት ታውቀው ስለነበረ ነው፡፡ እነዚሁ ሕገ ልቡና ፤ ሕገ ኦሪት እና ሕገ ወንጌል ናቸው፡፡ ሕገ ኦሪት ስትሰራ ኢትዮጵያዊቷ ከሙሴ ጋር ነበረች፡፡ ከእርሷ ወገን የምትቆጠር ንግሥት ሳባም ከሰሎሞን ጋር የነበረውን ጥበበ እግዚአብሔር ለማየት ወደ ኢየሩሳሌም እንደሄደች ከዚያም ልጇ ሕገ እግዚአብሔር በራሱ በእሳት ጣት የተጻፈበትን ጽላት በዘመኗ እንዳመጣ የሚያገለግሉ ካህናትም አብረው እንደመጡ ተደጋግሞ የነገለጸ ነው፡፡ በዚህም ምክንያት በአጸደ ነፍስ ሳለች ባለቤቱ ያላቸውን ባልሰሙ ትውልድ ላይ የመፍረድ ስልጣን የሰጣት ናት፡፡ ከዚያን ጊዜ ጀምሮ የወልደ እግዚአብሔር ሰው  መሆን በኢትዮጵያ ሲጠበቅ ቆይቷል፡፡ አዳምንና ልጆቹን ከፍዳና ከመርገም ከዘላለም ኩነኔ ሊታደግ በሁለት ወገን ዘላለማዊት ድንግል ከሆነች ከእመቤታችን ከቅድስት ድንግል ማርያም ከሥጋዋ ሥጋ ከነፍሷ ነፍስ ነስቶ በመዋሕድ እንደኛው ሰው ሥጋም ሆኖ በተወለደ በሁለተኛው ዓመቱ ከአዳም በፊት የገነት በር ለተከፈተለት  በቀኙ ለተሰቀለው ሰው ቃል ኪዳን በመግባት በግብጽ በኩል ወደ ኢትዮጵያ በመጣ ጊዜ መልኩን ዐይታ በሕጻን አንደበቱ ያስተማራትን ትምህርት የሠራላትን ገቢረ ተዓምራት አስተውላና ተረድታ የባሕርይ አምላክነቱን አምና በክብር አስተናግዳዋለች፡፡ መንፈስ ቅዱስ በጽርሀ ፅዮን በወረደ ጊዜ ለመገኝቷ  አቡነ ዘበሰማያት በቋንቋዋ በግዕዝ ተጽፎ መገኝቱ ምስክር ነው፡፡ ከዚያን ጊዜ ጀምሮ ኢትዮጵያ እና ኦርቶዶክሳዊት ተዋሕዶ ሃይማኖት ተለያይተው አያውቁም፡፡

 ፎከስ፡-የተዋሕዶ እምነት ቀኖና እና አስተምህሮን እንዴት ይገልጹታል ?
መምህር ተስፋዬ፡-  የኢትዮጵያ ኦርቶዶክሳዊት እምነት በአምስቱ አዕማደ ምስጢርና በጸሎተ ሃይማኖት እንደተገለጸው ነው፡፡ በምስጢረ ሥላሴ የማይታይና የማይመረመር  ሁሉን ማድረግ የሚችል የሚሳነው ፈጽሞ የሌለ ሰማይና ምድርን ፤ የሚታየውንም የማይታየውንም ፤ ሥነ ፍጥረት ሁሉ የፈጠረ ይቅርታው እና ቸርነቱ የማይወሰን ፤ መጀመሪያውና መጨረሻው የማይታወቅ ፤ ለዘላለም የሚኖር አንድ አምላክ አለ፡፡ እርሱም በስም ፤ በአካል ፤ በግብር  ሦስት በባሕርይ በሕልውና እና በመለኮት ግን አንድ ቅዱስ ይባላል፡፡ በአንድ መለኮት ግን አንድ አምላክ ይባላል፡፡በሦስት ግብራት አብ ወላዲ አስራጺ ይባላል ወልድ ተወላዲ መንፈስ ቅዱስ ሰራጺ ይባላሉ፡፡ አብ በስሙ በአካሉ በግብሩ አብ ነው ፤ ቢወልድ ቢያሰርጽ እንጂ አይወለድም፡፡ አይሰርጽም ወልድም በስሙ በአካሌ በግብሩ ወልድ ነው ቢወልድ እንጂ አይወልድም፡፡ አይሰርጽም አያሰርጽም ፤ መንፈስ ቅዱስም በስሙ በአካሉ በግብሩ መንፈስ ቅዱስ ነው ቢሰርጽ እንጂ አይወልድም አይወለድም አያሰርጽም  የማይከፋፈሉ ሦስት የማይጠቀለሉም አንድ የሆኑ አብ ወልድ መንፈስ ቅዱስ በባህርይ  ፤ በህልውና ፤ በመለኮት ፤ በፈቃድ ፤ በምልአት ፤ በስፋትና በርቀት ይህን በመሳሰሉ ሁሉ የማይቀዳደሙ ትክክል ናቸው፡፡ አንድ አምላክ ይባላሉ ሦስት አማልክት አይባሉም ብሎ ማመን ነው፡፡

በምስጢረ ሥጋዌውም አለም ሳይፈጠር ከአብ ባሕርይ ያለ እናት የተወለደ የእግዚአብሔር ቃል ወልድ ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ እኛን ከፍዳና ከመርገም ከዘለዓለም ኩነኔ ለማዳን በኋለኛው ዘመን ከእመቤታችን ከቅድስት ድንግል ማርያም ያለ አባት እንበለ ዘርዓ ብዕሲ ተወለደ ከኃጢያት በስተቀር ሰው የሚሰራውን ሁሉ እየሠራ አደገ፡፡ ስለእኛ ሕግንሁሉ ፈጸመ መከራም ተቀበለ ፤ ተሰቀለ ሞተ በሦስተኛውም ቀን መግነዝ ፍቱልኝ መቃብር ክፈቱልኝ ሳይል ከሙታን ተለይቶ ተነሳ በአርባኛውም ቀን ወደ ሰማይ መንበሩ አረገ ዳግመኛም ተመልሶ ይመጣል በሕያዋንና በሙታንም ላይ ይፈርዳል ለመንግሥቱም ፍጻሜ የለውም ብሎ ማመን፡፡

ምስጢረ ጥምቀቱም ወልድ ዋሕድ በተለየ አካሉ ሁለት ልደትን መወለዱን አምኖ በሥላሴ ስም በመጠመቅ የሥላሴ ልጅነት መቀዳጀት መቻሉን ማመን ነው፡፡

በምስጢረ ቁርባንም በጸሎተ ሀሙስ ለሐዋርያት እንደተናዘዘላቸው በሥጋዬ በደሜም ታገኙኛላችሁ እንዳላቸው በቅዳሴ ጊዜ ህብስቱን ተለውጦ ሥጋ ፤ መለኮት ወይኑም ተለውጦ ደመ መለኮት መሆኑን አምኖና ተቀብሎ ዘለዓለም በሕይወት መኖር መቻሉን ማመን ነው፡፡

በምስጢረ ትንሳኤ ሙታንም ክርስቶስ ዳግመኛ በግርማ መለኮት በይባቤ መላእክት እንደሚመጣ በሕያዋንና በሙታንም እንደሚፈርድ በጎ ለሠሩ ርስቱን መንግሥተ ሰማያትን እንደሚያወርስ ክፉ ለሠሩትም ለዲያቢሎስና ለሰራዊቱ በተዘጋጀ የዘላለም እሳት እንደሚዘጋ ማመን ነው፡፡

ሌላው ደግሞ በፈቃዱ ሥራ የተሠራላቸውን ታቦትን የባለቤቱ ስሞች የተጻፈበት በቅርጽ ስለሆነ ለስሙ ጉልበት ሁሉ ይንበረከካል አንደበት ሁሉ ይገዛል ስለሚል የሚገባውን ክብር መስጠት ነው፡፡

ስለ እመቤታችንም ፈጥኖ የሚገዛ የባሕርይ አምላክ የባሕርይ ሊቀ ካህናት ፤ የባህርይ ሊቀ ነቢያት እና የባሕርይ ንጉሠ ነገሥት ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ዘለዓለም በድንጋሌ ሥጋ በድንጋሌ ነፍስ ጸንታ ሳለች በማህጸኗ መለኮትና ትስብእት ርስ በርሳቸው ባደረጉት ተዋሕዶ አምላክ ሰው ሆኖ ሰውም አምላክ የሆነባት  ስለሆነች ይህ ደግሞ ከስነ-ፍጥረት  ወገን ለማንም የማይደረግ ስለሆነ ስሟም በሰማይና በምድር በመዓትም በምህረትም  የሠለጠነ መሆኑን  በሁሉ ነገሯም ራሱን እንድትመስለው ስላረጋት አስቀድሞ በልቡ አስቦ ለክብሯ ይህንን አለም በውስጡም የያዘውን ሁሉ  ስላዘጋጀላት ለርሷም የሚገባትን ክብርና ፍቅር መስጠት ነው፡፡

መስቀልም ዓለምን ለማዳን ባለቤቱ በላዩ በተሰቀለ ጊዜ ሥጋው ስለነጠበበት ደሙም ስለተንጠባጠበበት ይህም ማለት በደመ መለኮት የተቀደሰና  ልብሱም ደመ መለኮት ስለሆነ ለርሱም ተገቢውን ክብርና ፍቅር መስጠት ነው፡፡

ስለ አበው ስለ ነቢያት ፤ ስለ ሐዋርያት ፤ ስለ ጻድቃን ፤ ስለ ደናግል ፤ ስለ መነኮሳት ፤ ስለ ማኅረ ቅዱሳን ሰማያውያን ሁሉ አስቀድሞ በኦሪት ትዕዛዜን ለሚፈጽሙ እስከ ሺህ ትውልድ ይቅርታን የማደርግ ነኝ  ባለው በየጊዜውም ከምርጦቼ ከቅዱሳኖቼ ጋር ኪዳንን አደረግሁ ምህላንም ተማማልሁ ብሎ ባረጋገጠው ቃል ከደጋጎቹ ባንዱ ስም ለጠማው ውኃ ላጠጣም ዋጋው አይጠፋበትም ባለው መታሰቢያቸውንም እስከ ዘለዓለም አክብሮ መገኝት ነው፡፡

ስለ ቤተ ክርስቲያንም በራስዋ በክርስቶስ በክፉና በደግ መካከል ለመለየት የመጨረሻዋ ባለስልጣን ስለሆነች ቅድስት እናታችን ብለን የሚገባትን ክብር መስጠት ነው፡፡ ይህን ሁሉ አምኖ በምግባር በትሩፋት በንጽህና በቅድስና  በእግዚአብሔር ፊት  መቆም እንዲገባ አውቆ ተግቶ መፈጸም የታዘዘ ነውና ማንም በከንቱ ባይሳለቅ ጥሩ ነው፡፡

ፎከስ ፡- ብዙዎች የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ እምነት ጥንታዊ ፤ ባህላዊና ልማዳዊ አስተሳሰብ ያጠቃታል ይላሉ፡፡ ይህ አባባል በእርስዎ አመለካከት ምን ያህል እውነተኛ ነው?

መምህር ተስፋዬ፡- ፈጽሞ ሀሰት ነው ፤ ልማዳዊና ባህላዊ አስተሳሰብ የተባለው የቱ ነው ? አስቀድሞ እንዳልኩት ሦስቱንም ሕግጋት ከክቡር እግዚአብሔር ተቀብላ በየሰዓታቸው ሠርታባቸዋለች፡፡ ኦሪትና ነቢያት የተናገሩትን ልፈጽም መጣሁ እንጂ ልሽር አልመጣሁም  ባለው መሠረት መቅደሷን በደብተራ ኦሪት ቅርጽ ሠርታ ምስጢራትን ስታከናውንበት ኑራለች፡፡ መስዋዕተ ኦሪትን በሐዲስ በክርስቶስ ክቡር ሥጋና ቅዱስ ደም ትሠዋለች ታሳርጋለች በጥምቀት የሥላሴ ልጅነት ታድላለች በቅዳሴ አሐዱ አብ ቅዱስ አሐዱ ወልድ ቅዱስ አሐዱ ውእቱ መንፈስ ቅዱስ ብላ የቅድስት ሥላሴን አንድነት ሦስትነት ታውጃለች በአበው ማኅበረ ነቢያት ፤ በማኅበረ ሐዋርያት ፤ በማኅበረ ጻድቃን ሰማዕታት ፤ በማኅበረ ደናግል ወመነኮሳት በአጠቃላይ በማኅበረ ቅዱሳት ሰማያውያን እግዚአብሔር የገለጸውን ኃይሉን የገባውን ኪዳኑን አምልታ አስፍታ ታጎላለች፡፡ “ክብር ለሚገባው ክብር ስጡ መታዘዝ ለሚገባው ታዘዙ” በተባለው አምላካዊ ቃል መታሰቢያቸውን ሳታጠፋ ታከብራቸዋለች እንጂ በዘመናቸው ሰይጣነ ቅናት አድሮባቸው እንደገፏቸውና እንደተጣሏቸው ሰዎች በመዋዕለ እረፍታቸው አትገፋቸውም፡፡ በአጸደ ሥጋ ከዚህ ዓለም ስላለፉ አይረቡም አይጠቅሙም አትልም፡፡ የሚጠሏቸውን በምድር ከበረከቱ በሰማይ ከመንግሥቱ እንደሚለያቸው አጠንክራ ታስተምራለች፡፡ ከዚህ ሌላ ምን ባሕልና ልማድ አላት ይላሉ ?

ፎከስ፡- የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ እምነት በኢትዮጵያ ለኢትዮጵያ ብቻ ነው የሚል አስተሳሰብ የሚያራምዱ ወገኖች አሉ፡፡ በዘህ አስተያየት ላይ እርስዎ ምን ይላሉ ?

መምህር ተስፋዬ፡- በባሕል በሥርዓት በአንዳንድ ነገር እንለያይ እንጂ ከግብጽ ፤ ከሶርያ ፤ ከሕንድና ከአርመን ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን ጋር አንድነቱን ሦስትነቱን የወልደ እግዚአብሔርን ሰው መሆን በማመን አንድ ነን፡፡
 ፎከስ፡-የተዋሕዶ እምነት አስተምህሮ የተመሰረተው በመጽፍ ቅዱስ ላይ ሳይሆን በአዋልድ መጻሕፍት ላይ ነው የሚሉ ምን መልስ ይኖሮታል?

መምህር ተስፋዬ፡- አዋልድ መጻሕፍት ራሳቸው መሠረታቸው መጽሐፍ ቅዱስ ነው ከዚያ የተቀዱ ናቸው፡፡ ወደ መንበረ ክብሬ ካረግሁ በኋላ ከባሕርይ አባቴ ከአብ ወጥቶ የሚመጣላችሁ መንፈስ ቅዱስ ሁሉን ይገልጽላችኋል በእኔም ያጸናችኋል ካለው ከቃሉ የወጡ አይደሉም፡፡ በተለይ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ከምታምንባቸውና ከምታስተምራቸው መንፈስ ቅዱስ ከገለጻቸው እውነቶች አይጣረሱም፡፡ መጻፍ እስከተቻለ ድረስ ለማስፋት ላመጉላት ከመጣራቸው በስተቀር፡፡ በአንዲት የክርስትና ሃይማኖት ሊኖሩ የሚገባቸው ነገሮች ሁሉ ተካተውባቸዋል፡፡ የሚጠሏቸው የራሳቸውን ተረታ ተረት እየጻፉ ሰው እንዲስት የሚጥሩ ደካሞች ናቸው፡፡
 ፎከስ፡- በድርሳን በገድል በተዓምር ላይ የተገለጹ ታሪኮች ከመጽሐፍ ቅዱስ ጋር በተለይም ከወንጌል ጋር ይጋጫሉ ?

መምህር ተስፋዬ፡- በጭራሽ አይጋጩም ፈጥኖ የሚገዛውን ሥመ ሥጋዌው ኢየሱስ ክርስቶስ የሆነውን የባሕርይ አምላክ አምኖ በፍቅር በትህትና ጸንቶ መገዛት ምን ያህል ዋጋ እንዳለው ይገልጻሉ፡፡ የሚነቅፏቸው ከርዕይ ያልደረሱ ጣዕመ ጸጋ ያልቀመሱ ዐይኑ ግንባር ሆኖ እንደተፈጠረው የጤሜዎስ ልጅ በርጤሜዎስ ግንባር የሆነ ዐይነ ነፍሳቸው በክርስቶስ ጣት ያልተዳሰሰ በመለኮት ምራቅ ያልራሰ ሰዎች ናቸው፡፡

የቁስጥንጥንያ ከሀዲያንና ሐሳውያን በየጊዜው እየተነሱ በዘሩት የሐሰት ትምህርተ ታሽተው ሃይማኖታቸውን ፈረጅያቸውን አንጠልጥለው የመጡ መነኮሳትና አጫፋሪዎቻቸው ይህች ቃል ሥጋ መሆኑን የምታምን የምታስተምር መንፈስ ቅዱስ ምስክሯ የሆነን ሃይማኖት አፍነው ፍጥረታዊውን ተረታ ተረት እንዲላማ ቢያደርጉም ትጥላቸዋለች እንጂ አትወድቅላቸውም፡፡ በማይከፈል ሦስትነታቸው በማይጠቀለልም አንድነታቸው ፍትሑ ርቱዕ ሥላሴ እንዲፈርዱባቸው ልባቸው ያውቃልና ክርስቶስን በሕግ በአምልኮ በሚያውቁት ምዕመናን ሕዝበ ክርስቲያኑ አይቀበላቸውም አይከተላቸውም፡፡
Fokse:- በዚህ ዘመን የሃይማኖት መምህራን በዝተዋል የእምነት ተቋማትም እንደ አሸን ፈልተዋል ፡፡ የዚህ ክስተት መነሻ ሃይማኖታዊ መልስ ይኖረዋል ብለው ያስባሉ ?

መምህር ተስፋዬ፡- በመጨረሻው ዘመን ወንጌል ለፍርድ በዓለም ሁሉ ትሰበካለች ተብሏል፡፡ ሳይላኩ ተልከናል ሳይታዘዙ ታዘናል ፤ ሳይማሩ ተምረናል የሚሉ በመንፈስ ቅዱስ የሚያብሉ መንፈስ ቅዱስንም ያበለ የሚያስመስሉ  ሀሳውያን እንደሚበረክቱም ቅዱሳት መጻሕፍት ተባብረው አስረድተዋል፡፡ ነገር ግን እንዳያስቷችሁ ተጠንቀቁ ብለውም አስረግጠው ተናግረዋል፡፡

ፎከስ፡- በተዋሕዶ እምነት ስለ ሃይማኖት አባቶች ስለ ሰባኪያን መንፈሳዊ ሚና ሃላፊነት የተደነገገ ሕግ ይኖራል ? ካለ ቢገልጹልኝ ?
መምህር ተስፋዬ፡- ከኢትዮጵያ ኦርቶዶክሳዊት ተዋሕዶ እምነትና ሥርዓት ጋር ሳይገናዘብ ከሩማንያ በተቀዳ ቃለ ዓዋዲ ተሸፋፍኖ እንጂ የላትም ያለው ማነው ? ማንም ቢሆን ከአራቱ ወንጌላትና ከሥርዓት መጻሕፍቷ ያልተማረ እንዳይሾም ታዛለች ፤ ተሾሞም ከመንፈሳዊ ተልዕኮ ውጪ በሌላ የማይረባ ነገር ተጠምዶ ቢገኝ ይሻር ትላለች፡፡ እንደዛሬው ሁሉ ሕዝበ ክርስቲያኑን እየበተናችሁ ደሞዝና የወሎ አበል እንዳይቀርባችሁ ስለ ገንዘብ ስበኩ አትልም፡፡ ወይም ስለ ክርስቶስ ሞተናል ያላችሁ መነኮሳት የቤተ ክርስቲያኗን ሃብት ይዛችሁ በገዳም ያሉትን መናንያንና መነኮሳት በረሃብ በእርዛት አጫጩ ፤ አቀጭጩ ልጆች ያላቸውን ካህናት ድሆችንም አስርቡ አትልም፡፡ ምዕመኑ ክርስቶስን እንዲረሳ በየበዓላቱ በሌላ ወሬ አደናግሩ አትልም፡፡ የትዕቢት ዘርፍ የሆኑ ዝሙትንና ስርቆትን ፤ ስስትምና ፍቅረ ነዋይም ፤ ቁጣና ቅናትም ፤ ምቀኝነትም አድማም ስድብም ሀሰትም ተንኮልም የሚያስሽሩ እንደሆኑ በሥርዓቷ አለ፡፡ ክቡር አምላክ ኢየሱስ ክርስቶስ በወንጌል ባስተማራት የንጽሕና ሥርዓት የምትመራ ናት፡፡

ዛሬ ዛሬ ንጽናቸው ያልጠበቁ ከሴት ያልራቁ የከተማ መነኮሳትና ሳያገቡ የሚልከሰከሱ ምስጢሯንም የሚያረክሱ አንዳንድ ዲያቆናት አገለገልን እያሉ እንደሚመጻቁት አይደለም፡፡ እነዚህን ሥርዓቷ በቤተ ክርስቲያን ካለ ተድላ ደስታ ይለዩ ይላል፡፡ በአጠቃላይ ማንም በሀሳቡ በነገሩ በሥራውም ሁሉ ተጠንቅቆ በንጽሕና እንዲራመድ የሚያዝና የሚያስገድድ ሥርዓት አላት፡፡

ፎከስ፡- የተዋሕዶ እምነት አስተምህሮ ከዘመንና ከሥልጣኔ ጋር አብሮ መጓዝ አቅቶታል የሚል አስተያየት ይሰነዘራል፡፡ በዚህ ላይ ምን ይላሉ ?

መምህር ተስፋዬ፡- በትክክሉ ሥርዓቷ ቢተገበር ከማንኛውም ዘመንና ሥልጣኔ ቀድሞ የሚገኝ ነው፡፡ ዛሬ ሰው በእለታዊ ነሮው የሚገለገልባቸው የማዕድ ፤ የንጸሕና የአሰራር ፤ የአነዋወር ሥርዓትና መገልገያዎችም ከትምህርቷ የፈለቁ ናቸው፡፡ አንድ ቄስ የጸሐይና የጨረቃ ግርዶሽ መቼ እንደሚከሰት እስከ ደቂቃዋ መናገር የሚችል ነው፡፡ ስለ ሰማይ በራሪዎች ስለምድርም ተሽከርካሪዎች ስለምልክትነታቸውም ገና ስትመሠረት ታውቃለች በሰማያት መካከል ጎጆ ስለ መሰራቱና መጨረሻውም በርሷ ዘንድ ግልጽ ነው፡፡ ሞባይል ሳይሰራ ስለ መንፈስ መላላክ ታስተምር ነበር ሌላም ሌላም ማለት ይቻላል ግን ይህ ሁሉ ሰው ነፍሱን ካጎደለ አይረባወም አይጠቅመውም ትላለች፡፡

ፎከስ፡- በጥያቄያችን ያልተካተተ አንባብያንን ስለ ተዋሕዶ እምት ግንዛቤ ያስጨብጣል ሀቁን ያሳውቃል የሚሉት ካለ ቢጨምሩ ?

መምህር ተስፋዬ፡- የኢትዮጵያ ኦርቶዶክሳዊት ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን በሁለት ወገን ዘለዓለም ድንግል ከምትሆን ከእመቤታችን ከሥጋዋ ሥጋ ከነፍስዋ ነፍስ ከአጽምዋ አጽም ፤ ከደሟ ደም ፤ ከጥፍሯ ጥፍር ፤  ከጸጉሯ ጸጉር ነስቶ በአጠቃላይ ከባሕርያዋ ባሕርይ ፤ ከአካሏ አካል ነስቶ  የተወለደውን ወልድ ዋህድ ማለትም  ከሁለት አካላት(መለኮትና ትስብእት) አንድ አካል ከሁለት ባሕርይ(አምላክነትና ሰውነት) አንድ ባሕርይ በመሆን አምላክ ሰው ቢሆን ሰውም አምላክ ሆነ ሰው በመሆኑም ጭማሪ ቅናሽ የሌለው የባህርይ አምላክ ነው ብላ ማመንን ከራሱ ከባለቤቱ በየበዓላቱ በኢየሩሳሌም እየተገኝች በምኩራብ ያስተማረውን ትምህርት የሰራው ገቢረ ተዓምራት ሠምታ ዐይታ በሕጻንነቱም በቤቷ አስተናግዳ ያመነች ናት፡፡ አንዳንዶች ስለተከፈላቸውና ስለሚከፈላቸውም መኅለቅ እንደሚቀባጥሩት አንደሚያወሩት አይደለም፡፡ ከሐዋርያትም መጠራት የኢትዮጵያ መጠራት ይቀድማል፡፡ ከባለቤቱ የእግር ሰላም አንዲት ጠብታ እንዳይቀርባት በፍቃዷ በግብጽ ጳጳሳትን ስታስመጣ ኖራለች፡፡ ያስገደዳት አልነበረም የአባቶቻቸውን ቃል ውሉድ በፍቅር ሲጠብቁት ኑረዋል እንጂ ከግብጻውያን ያገኝችው ትምህርት የለም፡፡ ዛሬም ከሌሎች የሚያሻት ነገር የለም፡፡
ኢትዮጵያም ከነበራት የቀድሞ ስፋትዋ ቢያንስ አሁን ባለችበት ቅርጽና ይዘት እንድትቆይ በማድረግ ባለውለታ ናት እንጂ ሀገር ያደኸየች አይደለችም ፤ ከአድዋ ድል ወዲህ ብዙዎች ቂም ይዘውባት በዶማ እጃችን እናፈርሳታለን እያሉ ይዝታሉ፡፡ በዚያን ወቅት ኢትዮጵያውያን በበዓል ሥራ አይነኩም ስለዚህ ጦርነቱንም በበዓል አድርጉት ተብለው ስለተሳሳቱ ሁለተኛም ቤተክርስቲያን ከምታስተምራቸው አንዱ የእግዚአብሔር ሀገር ስለሆነች ኢትዮጵያ ሰው ጠላቷን ቢገድል ቢሞት በዱር በገደል ቢወድቅ ቢጥል ካህናተ ሰማይ ይፈቱታል ዕዳ በደል የለበትም ስለምትል የተገኝው ድል ለአፍሪካውያንም ለዐረባውያን ከቅኝ ግዛት ቀንበር ለመላቀቅ ትግል እንዲጀምሩ ፈር ቀዳጅ ስለሆነ ቁጭት አለባቸው፡፡

የኛዎቹ ቢጽ ሀሳውያን ከዚያ የሚላላቸውን ፍርፋሪ ተስፋ በማድረግ በማይፈታ ጽኑ እሥራት ለመያዝና ለዘላለም ለመጋዝ ላይ የርግማን እሳት እያላሙ እያፋሙ ይገኛሉ፡፡ ኢትዮጵያ ወልድ ዋሕድ ከሚለው እምነቷ ሳትናወጥ እስከ ክርስቶስ ዳግም ምጽት ቆይታ ለልጆቿ ዋጋ እስከማሰጠት እንደምትጸና አስቀድሞ የተነገረ ነው፡፡ በሚሞት አፋቸው በሚፈርስም ሰውነታቸው ራሳቸውን ሞት አይነካሽ አስመስለው የማይነቀፈውን ሲነቅፉ ክህደታቸውን ለማስፋት ሲጣደፉ ቢታዩም ፡፡ በሕገ እግዚአብሔር እያስፈራሩ ሰውን ከባለቤተ ፤ በምድር ከረድኤቱ ፤ በሰማይም ተድላ ከተጎዘዞዘው እረፍት ካለባት የዘለዓለም መንግሥቱ ለመለየት ታጥቀው የተነሱ ናቸውና ሰው ሊያውቃቸው ይገባል፡፡ በእኛ እና በአርዮሳውያን ፤ በእኛና በልዮናውያን ፤ በእኛና በንስጥሮሳውያን በሌሎችም የተወገዙ ከሀዲያንና ሀሳውያን መካከል የአገላለጽ ልዩነት እንጂ የሃይማኖት ልዩነት የለም “መተው ነገሬን ከተተው” በሚለው መርህ እና መተው እንችላለን ግዘቱን አንስተን ከላይ የተጠቀሱትን ከሀዲያን ከቅዱሳን ወገን እንዳንደምራቸው ግን ሰው ይታዘበናል ይነቃብናል እስከዚያው ትምህርት በማመሳሰል ክህደቱን እያላመድን እንቆያለን የሚለውን አባባልና አካሄድ ሕዝበ ክርስቲያኑ ሊነቃበት ይገባል፡፡ በእኛና በእነርሱ መካከል እኛ ወደ እርሱ እንዳንሄድ አነርሱም ወደ እና እንዳይመጡ የማይታለፍ ታላቅ የውግዘት ገደል አለና ሕዝበ ክርስቲያኑ የተዋሕዶ ክርስትና አሻራ የሆኑትን አብያተ ክርስቲያናትን እንዲያንጽ ምስክር እንዳያቆይእመክራለሁ፡፡ የምን ቤተ ክርስቲያን ? ገንዘቡን ውሎ አበልና ለደመወዛችን አምጣ እንጂ እያሉ የሚያስቸግሩትንም እየተጋፋ ሕንጻ ቤተ ክርስቲያኑን መሥራት አለበት፡፡

በስልታቸው መንቃት አለበት ርሱን ለተኩላ እያስረከቡና እየበተኑ ስለ ገንዘቡ ቢሰብኩለት ጆሮ ሊሰጥ አይገባም፡፡ የቤተክርስቲያን ሀብቷ ምዕመን ሕዝቡ ነው ሌላ ሀብት አያስፈልጋትም፡፡ ያንኑ በሀብተ መንፈስ ቅዱስ በትምህርት በተአምራት ካጸናችው ትልቅ ግዳጅ መወጣት መፈጸም የሚችል ነው፡፡ እርሱ የቤተ ክርስቲያን ከሆነ በእርሱ እጅ ያለ ብስጥ ብስያጥ ለክብርዋ ያውለዋል በአጠቃላይ ሕዝበ ክርስቲያን እወቅ ወልድ ዋሕድ የምትል ሃይማኖትህን ነቅተህ ጠብቅ፡፡ የተቀደሰችው ደጅ ከዚህ በላይ መርከስን ማስተናገድ የለባትም ፤ አትችልም፡፡ ይህን የምናገር በውጭ ስላሉ አጽረ ቤተክርስቲያን አይደለም፡፡ በውስጥ ሁነው በውጭ ያሉትን ወደ ውስጥ ለማስገባት በር ለሚከፍቱና ሁኔታ ለሚያመቻቹትን ልጆቿ  በመምሰል እያጎሳቆሏት ያሉትን ሰው እንዲነቃባቸው እንዳይስትላቸው ስለማጠንቀቅ ነው እንጂ፡፡ ለብልህ ምዕመን ሕዝበ ክርስቲያን ብዙ መዘብዘብ አግባብ ሆኖ አይደለም፡፡ ሁሉንም ያውቀዋልና ሥጋንና ነፍስን ከሚያሳድፍ ነገር ራስን መለየት ይገባዋል፡፡ ከቤተ ክርስቲያን በሚለይ ውግዘት ከተያዘ ዘለአለም ከተድላ መንግሥቱ የተለየ ስለሚሆን ከቃኤልም መንገድ አምርሮ ይራቅ፡፡ የጥፋት ውሀ ከመጣበት ሰዶምና ጎመራ ከተገለባበጡባት ኃጥያት ይራቅ ስለማለት ነው፡፡


ወስብሐት ለእግዚአብሔር 

7 comments:

 1. ስለ ክርስቶስ ሞተናል ያላችሁ መነኮሳት የቤተ ክርስቲያኗን ሃብት ይዛችሁ በገዳም ያሉትን መናንያንና መነኮሳት በረሃብ በእርዛት አጫጩ ፤ አቀጭጩ ልጆች ያላቸውን ካህናት ድሆችንም አስርቡ አትልም፡፡

  ReplyDelete
 2. Kale heyewot Yaemalen Yagelgelot Zemnewon Yabzalen Amen

  ReplyDelete
 3. In the past several years I have heard many songs
  and sermons, read a few books, on how special
  Ethiopia is in God’s agenda and how dear and close
  the nation is to God.From the sermons and chapters of published books
  what I gathered is that the general theme is the
  same. They all state that Ethiopia, on account of
  Psalms 68:31, is very special. What, really, is
  special about Ethiopia? Is it the oft-repeated one
  verse? Or is it the forty plus times it was mentioned
  in the Bible? The overused verse ኢትዮጵያ እጆችዋን ወደ
  እግዚአብሔር ትዘረጋለች። And the Geez ኢትዮጵያ ታበጽሕ
  እደዊሃ ኀበ እግዚአብሔር - Ethiopia shall soon stretch out
  her hands unto God. (Ps. 68:31) has been so
  misused and overused that it lost its original intent
  and meaning.Some of my readers, especially those enamored by
  such sermons might have already labelled me as
  some sort of bigot. Therefore, I should make clear if
  I am a sort of anti-Ethiopia or some one carrying a
  prejudice. No, I am not both. I am an Ethiopian by
  birth and by psyche. ...

  ReplyDelete
 4. እግዚአብሔር እድሜና ጤና ይስጥልን። ግሩም ትምህርት ነው። ኃይለ ሚካኤል።

  ReplyDelete
 5. Is there any plan to visit S. Sudan refugees in Ethiopia? This is something the church needs to orginize real quick. No preaching or teaching. Just feed and let them drink the hungry and thristy, kiss their chucks, wash their legs, sit, talk, laught and cry with them. Then, when their suffering subsides, they will remember the blessings they received in Jesus name. They really need an honest help, not politically motivated one. They suffered way too long. My apologies for posting unrelated comment.

  ReplyDelete
 6. አንድ አድርገኖች ፡ እባካችሁ ይህን ቃለመጠይቅ ስለሰጡት አባት ሙሉ መረጃ ብትሰጡን ? ወይም ሌላ መረጃ የሚሰጠን ሰው ካለ? ማለት ስለሚያገለግሉበት ደብር…..

  ReplyDelete
 7. ድንቅ የሆነ ትምህርትና መረጃ አድርሳችሁናል፡፡እግዚአብሐር ይስጥልን፡፡ ቃለ ሕይወትን ያሰማልን፡፡

  ReplyDelete