Friday, May 30, 2014

የቤተ ክህነቱ ጨለምተኛ ምሁራዊ ድባብ ፡ Cynical Intellectual Atmosphere

                                                              
                                                              በታደሰ ወርቁ ተጻፈ
 • ዛሬ ሊቃውንቱ የቤተክርስቲያኗ መቁሰል አልታይ ብሏችዋልና ቤተክርስቲያን አለቃ አያሌውን ከሙታን መንደር ትጣራለች፡፡

(አንድ አድርገን ግንቦት 23 2006 ዓ.ም)፡- በዚህ ዐውድ(Context)ምሁር የምለው ከቤተ ክርስቲያኒቱ የአብነት ትምህርት ቤቶች ሊቅነታቸውን ያስመሰከሩ ፤ ከመንፈሳዊ ኮሌጆች የተመረቁ እንዲሁም በቤተ ክርስቲያኒቱ ዙሪያ ጥናትና ምርምር አድርገው የጥናት ወረቀቶቻቸውን ያበረከቱ ፤ መጻሕፍትን ያሳተሙትን ጭምር ነው፡፡ በጥቅሉ በቤተ ክርስቲያኒቱ በአዕምሮ ሥራ ላይ የተሰማሩትን ነው፡፡

በዚህ መልኩ ያስቀመጥናቸው ሊቃውንት ቁጥር በአንጻራዊነት እያደገ ቢሄድም በቤተ ክርስቲያኒቱ እና በምእመኑ ውስጥ ቀድሞ የነበራቸው ቦታና የኑሮ ደረጃ በማሽቆልቆል ላይ ይገኛል፡፡ አንዳንዶቹም ሊቃውንት በቤተ ክርስቲያኒቱ  አገልግሎታቸውን እየሰጡ ቢሆኑም  በአሁን ጊዜ በቤተ ክርስቲኒቱ ውስጥ እንደሚታየው የቀድሞውን የመንፈስ ልዕልና እና ሐሳባዊ መሪነት አጥተዋል፡፡ ለመኖር የሚያስፈልጋቸውን ከማድረግ በተረፈ ምሁር የሚያሰኛቸውን ተግባር የሚፈጽ አሉ ብሎ ለመናገር አያስደፍርም፡፡

በተለያዩ አዝማናት የቀሰሙትን በጎ እውቀት ከምእመኑ ሕይወትና ከቤተ ክርስቲያኒቱ አገልግሎት ግንኙነት ያለው ፤ የምእመኑንና የቤተ ክርስቲያኒቱን የአግልግሎት ሕይወት ለመቀየር የሚውል መሆኑ ቀርቶ ዝም ብሎ የኑሮ መደጎሚያ ብቻ አድርጎ መውሰድ በእጅጉ ይታይባቸዋል፡፡ይህ ደግሞ እውቀትን ለእውነትና ለቤተ ክርስቲያኒቱ መሠረት እምነት ፤ ቀኖናና ትውፊት ወገንተኛ መሆን ቀርቶ የበለጠ ዋጋ ለከፈለ የጥፋት ኃይል ሁሉ በሚፈለገው ዓይነት ተለክቶና ከሐሰት ጋር ተለውሶ የሚሸጥ ሸቀጥ አድርታል፡፡


ሊቃውንቱ ‹‹እኔ ንጹሕ ነኝ ፤ ምንም አልሆንም ፤ የቤተ ክርስቲያኒቱ ሙያተኛ ነኝ ፤ ሥራዬን እየሠራ ነው” በሚል ራሳዊ አቋም መንጋውን የተኩላ ሲሳይ አድርገውታል፡፡ ቤተ ክርስቲያኒቱ የ‹‹አጉራ ዘለሎችና ጆቢራዎች›› መፈልጫ እንድትሆን ፈቅደዋል የሚሉ ወቀሳዎችም ይቀርቡባቸዋል፡፡ ወቀሳውም የደረት ንግግር አለመሆኑን ልብ ይሏል፡፡

ሁኔታውን ክፉና ጨለማ የሚያደርገው ምሁራኑ አሁን ያሉበት ደካማ ሁኔታ ብቻ ሳይሆን ይህንን ለማሻሻል ያላቸው ወኔ እና የሌሎች እህት አብያተ-ክርስቲያናት ምሁራን አሁን ያሉበት ደረጃ ላይ ለመድረስ የሚወስድባቸው ጊዜ ስናሰላ ነው፡፡

በቤተክርስቲያኒቱ ትምህርተ መሠረት የሊቃውንት ድርሻ ‹‹የዓለም ብርሃንና የምድር ጨው›› መሆንም ጭምር ነው፡፡ ይህንን ታላቅነት በድርሻቸው ሲታደሉት በደካማነታቸውና በሓላፊነት ሽሽታቸው ብርሃንነታቸውን ወደ ጨለማ ፤ ጨውነታቸውን ወደ አልጫነት በመለወጣቸው ኃላፊነታቸውንና ብርኩናቸውን አውጥነው የጣሉ ይመስላሉ፡፡

በእርግጥ ብዙዎች የምሁርነታቸውን ሚና በሚገባ መደላደል(Stabilization) እንዳልተጫወቱ አሳምረው ያውቁታል፡፡ዕውቀታቸውን የቤተ ክርስቲያኒቱን ውሳኔ ሰጪ አካል ለመምከር አለመቻሉንም ሁሉም ይረዱታል፡፡ ውሳኔ ሰጪዎቹም የ‹‹ሊቃውንት ምክር›› ብለው ሲጠይቁ የሚያገኙት እውነቱን ሳይሆን ሊቃውቱ ውሳኔ ሰጪውን አካል ያስደስተዋል ብለው የሚያስቡትን ‹‹እውነት›› ብቻ እንደሆነም ይገነዘባሉ፡፡
አሁን ባለው የቤተ-ክህነቱ ሁኔታ እጅግ የሚያሳዝነው የእነኚህ ኃይሎች(የውሳኔ ሰጪው እና የምሁራን) በተናጠል መዳከም ብቻ ሳይሆን ይህንን ድክመት በመገንዘብ ለቤተ ክርስቲያኒቱ ሲባል በጋራ ለመሥራት አለመቻላቸውና የመሥራም ፍላጎት ፍንጭ አለመታየቱ ነው፡፡

የሁለቱም ኃይሎች እርስ በእርስ የጎሪጥ መተያየት ፤ ቅንነት በተሞላውና ገንቢ በሆነ መልኩ መተቻቸት አለመቻል ወይም ለመደጋገፍ አለመመሞከር ተቋሟን ‹‹የነጋ አድርሶች›› ስብስብ እንድትሆን አድርጓታል፡፡ ሕግ የሚጣስላቸውና ሕግ የሚጣስባቸው ሰዎች ጥርቅምም እንድትሆን አብቅቷታል፡፡

ይልቁንም በጽንፈኛነት የአንዱን ድክመት ማጉላትና ይህን የጽንፈኛነትን አቋም በየጎራው በማስተጋባት ‹‹እኔ የበለጠ አሳቢ ፤ ከእኔ የተለየው ሁሉ ግን የቤተክርስቲያ አጥፊ ነው›› ብሎ በመኩራራት እና በዚህም እንጀራ ለመጋገር መሞከር በእጅጉ የሚዘወተር ነው፡፡ ይህ ደግሞ ቢያንስ በግል ደረጃ የግብዝነትና የአድርባይነት (Opportunist) መገለጫ ፤ ሲያልፍ ደግሞ ቤተ ክርስቲያቱን ሊጎዳ የሚችል እኩይ ድርጊት ነው፡፡  

ይህ ሁሉ የእውቀትና የሞራል ተገናኝ ቀጠናዎች(Inter-Zone) የሚያመጡትን የሥነ ልቡና ቀውስ ለመከላከል በሚመስል ሁኔታ በቤተ-ክህነቱ ሊቃውንተ ዙሪያ ጨለምተኛ ምሁራዊ ድባብ(Cynical Intellectual Atmosphere) የተንሰራፋ ይመስላል፡፡ 

ነገሮችን በዕውቀትና በሃይማኖት ከመጋፈጥ ይልቅ ፍጹም ሥር በሰደደ ወሬና ሐሜት ማለፍ ፤ አጥፊ የቤተ-ክህነቱን ሹማምንት እነርሱ ሳያውቁ በየመሸታ ቤቱ ወይም አንድ አይነት ሀሳብ በሚያስቡ ቡድኖች  መካከል ማማት ፤ የሚደረጉ ጥረቶች መጨረሻ መጥፎ ይሆናሉ ብሎ ማመን ፤ ለለውጥ ሳይጥሩ ሌላው የሚያደርገውን የለውጥ ጥረት ማጣጣል ፤ በቤተ ክርስቲያኒቱ ክፉና ጎጂ ክስተት እንዳይመጣ ‹‹ አኔ ምን ማድረግ አለብን?›› ብሎ በመጠየቅ በምሁርነት ማድረግ የሚገባቸውን ከማድረግ ይልቅ ክፉ ነገር ሲመጣ ‹‹አላልኳችሁም›› ብሎ በጨለምተኛ ምሁርነት መመጻደቅ የቤተ-ክህነቱ ምሁራዊ ድባብ የሆነ ይመስላል፡፡በቤተ ክርስያኒቱ ደረጃ ውድቀት ሊያመጡ የሚችሉ መሠረታዊ ችግሮችን እያዩና እየተገነዘቡ  ለምእመኑ እይታና ውይይት ማቅረብ ምሁራዊ ግዴታ ከመሆኑ በላይ የኦርቶዶክሳዊነት ግዴታ ሳይሆን እንደ የዋህነትና አላዋቂነት የሚቆጠሩበት ጨለምተኛ ምሁራዊ ድባብ ያለበት ቤተክህነት ባለፉት በ22 ዓመታት ውስጥ ያፈራን ይመስላል፡፡

ከዚህ ቢብስም በምዕመኑ ፊት ትክክለኛ የሆነውንና የሚመስለን ነገር መናገር በተለይም ይህን ነገር መንግሥትን የሚጎነትል ከሆነ አንድም የተናገርነው ጀብደኝነት አሊያም ‹‹ ሰውየው የመንግሥት ሰላይ ሳይሆን አይቀርም›› ተብሎ የሚያስጠረጥር ደረጃ ላይም እየተደረሰ ነው፡፡

እንዲህ አይነቱን ምሁራዊ ጨለምተኝነት ለተጣለባቸው ፍርሃትና ስንፍና መደበቂያ የሚያደርጉት ብዙዎች ናቸው፡፡በዚህ ምክንያት እውነተኛው የቤተ ክርስቲያኒቱ የሊቅነት ስሜት ጠፍቶ ምሁርነቱ ርካሽና የማይከበር እየሆነ ይገኛል፡፡ በአንድ በኩል የምሁርነቱ ደረጃ እየወረደ ፤ በሌላ በኩል የቆራጦቹ ቤትና የነጻዎቹ ሊቃውንት ቤተ ክርስቲያን እየተዋረደች ትገኛለች፡፡ እነዚህ ምሁራን ‹‹ሆዷን ለቆረጣት የራስ ሕመም መድኃኒት የማዘዝ›› ያህል እየታየባቸው ነው፡፡

ይህ ሁሉ ተደራርቦ የፈጠረው ‹‹የምሁራዊ ቅሌት›› ስሜት ሊቃውንቶቻችን በቤተ-ክህነቱ ውስጥ በጉልህ የሚታዩትን መሠረታዊ ችግሮች(የቀኖና ቤተ ክርስቲያን ጥሰት ፤ የቤተሰብ አስተዳደር እጦት ፤ ሙስናና ጎጠኝነት) የሚያሳዩ መስታወቶች ፤ የቤተ ክርስቲያኒቱን መሠረተ እምነት ፤ ሥርዓተ አምልኮ ሐዋርያዊ ትውፊትና አስተዳደራዊ ድርጁነት ቀጣይነት የሚጠቁሙ ዘመን ተሻጋሪ ኃይል መሆናቸው ጥርጣሬ አሳድሯል፡፡

እንደ ማኛው ተራ ምዕመን በቤተ-ክህነቱ ‹‹ገዥ መደቦች›› አድርጉ የተባሉትን ሁሉ በተንበርካኪነት (submissive) የሚያደርጉ ፤ ባሳለፍነው ዘመነ ፕትርክና እንደታየው የቤተ ክርስቲያኒቱን መብት በቤተ-ክህነቱ ‹‹ገዥ መደብ›› ጎን የመቀመጥ ክብር መቀዳጀትን የመረጡ ይመስላሉ፡፡ ለራሳቸውና ለሊቅነታቸው ብዙ ክብር የሌላቸው ፤ አቅመ ቢስ የቀንድ አውጣ ኑሮ ነዋሪዎች ናቸው የሚለው የብዙዎች አስተያየት እየሆነ ይገኛል፡፡

ሊቃውንቶቻችን የቤተ-ክህነቱ ፖለቲካ ሳበዳቸው ‹ገዥዎች› ጋር ሲርመጠመጡ መቃናት የሚገባው ሁሉ ይበልጥ እየጎበጠ መሄዱና ቤተ-ክርስቲያኒቱም የምትተማመንበት የታሪክ ምስክርና ታጋይ መጥፋቱም በጉልህ ታይቷል፡፡ አንዳንዶች እንዲያውም ‹‹ነጻ የወጣ ነፍስ›› የሌላቸው እስኪመስል ድረስ ሕሊናው ላይ አንጥፈው ተቀምጠዋል፡፡

እርግጥ ከላይ የጠቀስኳቸው በሊቃውንቶቻችን ዘንድ የሚታዩት ምሁራዊ ጨለምተኝነት እና ክትያው(Consequences) እነዚህ ሊቃውት በሚኖሩባቸውና በሚሠሩባቸው አካባቢዎች በሚደርስባቸው ቤተ-ክህነታዊ ‹‹ገዥ መደብ›› እና ‹‹መንግሥታዊ›› ገዥ መደቦች ነን ባዮች ተጽዕኖ ምክንያት የመጡና ከፍተኛ አስዋጽኦ ያደረጉባው እንደሆኑ አይካድም፡፡

ይሁንና እንደ ጥንቶቹ ሊቃውንት ነጻ ምሁራዊ ድባብ በሌለበትም የቤተ ክርስቲያቱ ማኅጠነ ልቦና(Think Thank) በመሆን ምእመኑን በአንዲት ቤተ ክርስቲያን ሐሳብ መርተው በሚፈለገው የሞራልና የመንፈስ ልዕልና ማብቃት ባለመቻላቸው ከወቀሳ አይድኑም፡፡

ዛሬ ቤተ ክርስቲያ ከእነሱ የበለጠ አለቃ አያሌውን ከሙታን መንደር ትጣራለች ፡፡ የቤተ ክርስቲያኗ መቁሰል አልታይ ብሏችዋልና፡ ለዛሬ የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን መሰረታዊ ችግሮች ‹‹ ያለ አቡነ ተክለሃይማኖት ያለ አቡነ ፍሊጶስ ደብረ ሊባኖስ ምንድን ነች ? ያለ አቡነ እየሱስ ሞዐ ያለ አቡነ ክርስቶስ ሞዐ ደብረ ሀይቅ ምንድን ነች ? ያለ አቡነ ኤዎስጣቲዎስ ያለ አቡነ ፊሊጶስ ደብረ ባዚን ምንድን ነች ? ›› ያሰኙንን አይነት ሊቃውንት አጥብቀን እንፈልጋለን ፡፡ 

ሊቀ ካህናት ማንትሴን ፤ ሊቀ ስዩማን እገሌን ፤ መጋቢ ሐዲስ ፤ መጋ ብሉይና ሊቀ ማእመራንን እንትናን እናከብራቸዋለን ፡፡ ለዛሬይቱ ቤተ ክርስቲያን ደዌ መድኀኒት መሆን ካልቻሉ ክእነርሱ ይልቅ መድኀኒት መሆን የቻለውን ጨዋን እንመርጠዋለን፡፡

እንዲህ ካለ ምሁራዊ ጨለምተኝነት ወጥታችሁ በቦታሁ ተገኝታችሁ ቢሆን ኖሮ ያልጠገገውንና ከቶውንስ በላይ በላዩ የሚጨማመርበትን የቤተ ክርስቲያኒቱን ቁስል እኛም በየጋዜጣው ፤ በየመጽሔቱና በየብሎጉ የምንሞጫጭር የቤተ ክርስቲያን ልጆች በየብዕራችን ባንጓጉጠው ደስ ይለን ነበር፡፡ ዳሩ ግን ‹‹ውኃንም ድንጋዩ ስለሚያጮኽው›› ጥሩ ትንፋሽ ለመሳብ ፋታ አልተገኝም፡፡ ቤተ ክርስቲያቱና ምእመኑ ተራ በተራ አንድ ጊዜ በመሐል አገር ፤ ሌላ ጊዜ በደቡብ ፤ አንድ ጊዜ በሰሜን ሌላ ጊዜ በምእራብና በምሥራቅ ኢትዮጵያ በኩል በገዛ እረኞቻቸው ሲወጉና ሲደሙ ብዕር አብሮ ይጮኻል፡፡ ያ የእረኞች አጥቂነት የባለቅኔውን ፤ የደራሲውን ፤ የፖለቲከኛውን ፤ የምሁሩን አንጀት ያላውሳል፤ ሐሞቱን ፤ የቀረች ውሳኔን ይነካካል፡፡ ያስጮኻል፡፡

ቤተ ክርስቲያኒቱን እያጠፋ ያለው መዋቅር አርበድባጅ (Shock detachment) ቡድንም አይደለም፡፡ የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያንን አንድነት ፤ ክብርንና ሉዓላዊነት  እየተፈታተነና ከዚህ ተስፋ መቁረጥ ደረጃ (አንዳንዶችን) ያደረሰው ቤተ ክርስቲያቱን ለመጠበቅ ፤ ለመንከባከብ ፤ ለማዳን የምሁራን ቆራጥነት የማጣት ጉዳይ ነው፡፡

በቅዱስ ሲኖዶስ ጥንካሬና ችሎታ ላይ እንዳንተማመን በብዛት የምናየው በሲኖዶስ በኩል ችሎታ ማጣትንና ችሎታ ካላቸው የሊቃውንት ኃይል ጋር የበለጠ እየተለያየ መሄዱን ነው፡፡ ከቅዱስ ሲኖዶስ ውጪ ባሉ አደረጃጀቶች ላይ እምነታችንን እንዳናሳርፍ የቤተ-ክህነቱን አርበድባጅ ቡድን መቋቋም ቀርቶ በራሱ ለመቆም የሚችል አደረጃጀት ያለበት ሁኔታ አይደለም፡፡ ይህን ሁኔታ ለማስቀረት የቤተ-ክህነቱ ጨለምተኛ ምሁራዊ ድባብ መቀየሩ ወሳኝነት አለው፡፡ መቀየር ማለት ሊቃውንቱ በቤተ- ክርስቲያኒቱ የመሠረተ እምነት ፤ የሥርዓተ አምልኮና ትውፊት መፋለሶች ላይ እውቀትን መሠረት ያደረገ ሂሳዊ አስተሳሰብ በነጻነት ማራመድ ፤ የቤተክህነቱን መዋቅራዊ አርበድባጅ ቡድን ያለ አንዳች መሸማቀቅ መገሰጽ ፤ ቤተ ክርስያኒቱ ያለችበት ነባራዊ እውነታ ከአጠቃላይ ዓለም አቀፍ ሁኔታ ተገንዝቦ መፍትሔዎችን ማስቀመጥ ማለት ነው፡፡

እናም በዚህ መልኩ ጨለምተኛ ምሁራዊ ድባቡ እንዲለወጥ ከተፈለገ ቅዱስ ሲኖዶስ ይከተል የነበረውን ኋላ ቀር አሰራር ለውጦ ፤ ከትንሽ ቡድን ጉጠኝነት (Sectarianism) ወጥቶ ፤ የተለያዩ ምሁራን አቅፎ እና የፖሊሲ ማውጣት ላይ አማክሮ ምእመኑን ለሚፈልገውበጎ አላማ የሚያነሳሳበት መንገድ መቀየስ አለበት ፡፡ ይህ ነው ከቅዱስ ሲኖዶስ የሚጠበቀው ‹‹ኦርቶዶክሳዊነት››፡፡

በሊቃውንት በኩል ደግሞ ከላይ የጠቀስኩትን ፤ የቤተ ክርስቲያን ልጅነት ከልቡ ወስዶ ፤ በቤተ ክርስቲያኒቱ ጉዳዮች ላይ በድብቅና በሹክሽክታ ሳይሆን በግልጽና ሓላፊነት በሚሰማው መልክ በመሳተፍ ፤ ያሉትን መንፈሳዊ የትምህርት ተቋሞቻችንን እያጠናከረ ፤ የሌሉና የሚያስፈልጉትን እየፈጠረ የቤተ ክርስቲያን ልጅነት መብቱን በቀናኢነት የሚጠብቅ ፤  ግዴታውን በአግባቡ የሚወጣ መሆን ይገባዋል፡፡

ከዚህ በኋላ የቤተ ክርስቲያኒቱን ሊቃውንት ልንማጸን የምፈልገው ወደ ኋላ ተመልካችነቱን አቁመውና ረስተው በወደፊቱ ላይ ያተኩሩ ዘንድ ነው፡፡ ታዲያ ይህ ሲባል ካለፈው ታሪካችን ሳንማርና ሳንታረም ዘግቶና ለማኅደር አስረክቦ አይደለም፡፡

ባለፉት 22 ዓመታት የሚያሳፍርና ለአድማጭ ግር የሚያሰኝ የታሪክ ሸክም የተፈጸመ ይመስለናል፡፡ የወደፊቱን ተመልካች (Future Oriented) ሊቃውንቶቻችን እነዚህን የታሪክ ሸክም ነቁጥ በምራዊ ቅኝት ሊያሳዩን ይገባል፡፡ በጥናትና ምርምር ታግዘው ቤተ ክርስቲያኒቱ አሁን ያለችበት ሁኔታ ምን ይመስላል ? የቤተ ክርስቲያኒቱ ሁኔታዎች አሁን ባሉበት አቅጣጫ ከቀጠሉ ከተወሰኑ ዓመታት በኋላ ምን መልክ ይኖራቸዋል? በጎ ለውጥ ለማጣት ቅዱስ ሲኖዶስ ካህናቱና ምእመኑ አንዳድ የአቅጣጫ ማስካካከያዎችን በአንድት ቢያደርጉ በቤተ ክርስቲያቱ የሚታየው ለውጥ ምንድነው? ይህ ተግባራዊ እንዲሆን ከቅዱስ ሲኖዶስ አባላት ፤ ከሊቃውተ ቤተ ክርስቲያን ፤ ከአገልጋዮችና ምዕመናን ምን ይጠበቃል ? ለሚሉት መሠረታዊ ጥያቄዎች መልስ መስጠት ይጠበቅባቸዋል ፤ ቤተ ክርስቲያቱ ካለችበት አዙሪት ለመውጣት አስፈላጊውን መስዋዕትነት ለመክፈል የሚዘጋጅ እውነተኛ ‹‹ኦርቶዶክሳዊ››  ምሁራዊ መኅበረሰብ እንዲዳብር መታገል የሚጠበቅባቸው ጊዜ ላይ እንገኛለን፡፡
6 comments:

 1. እኛም ከእውነተኞቹ አባቶቻችንና መምህራኖቻችን ጎን በመሆን በፆም፤በፀሎት፤በሃሳብ፤በገንዘብ፤በእውቀት፤……በሁሉም ነገር ልንረዳቸውና ልንደግፋቸው ይገባል፡፡እኛም የሚጠበቅብንን ድርሻ መውሰድ አለብን፡፡ እግዚአብሔር ቤተክርሰቲያናችንን ይጠብቅልን፡፡

  ReplyDelete
 2. እኛም ከእውነተኞቹ አባቶቻችንና መምህራኖቻችን ጎን በመሆን በፆም፤በፀሎት፤በሃሳብ፤በገንዘብ፤በእውቀት፤……በሁሉም ነገር ልንረዳቸውና ልንደግፋቸው ይገባል፡፡እኛም የሚጠበቅብንን ድርሻ መውሰድ አለብን፡፡ እግዚአብሔር ቤተክርሰቲያናችንን ይጠብቅልን፡፡

  ReplyDelete
 3. Yes I agree We lost ...............

  ReplyDelete
 4. Yes I agree we lose ...

  ReplyDelete
 5. Fantahun muche rikashe muhirinegn bayi seyitani

  ReplyDelete