Wednesday, May 28, 2014

ወርሀ ግንቦት ……….1983 ዓ.ም

  • ደርግ ለ17 ዓመት ብዙ ግፍና በደል ያደረሰባትን ቤተ ክርስቲያንን  በ1983 ዓ.ም ግንቦት ወር ላይ ምህላ እንድታደርግ  በደብዳቤ  ቤተክህነቱን  ጠይቆ ነበር፡ 

(አንድ አድርገን ግንቦት 20 2006 ዓ.ም)፡-  በቀደምት  አባቶቻችን  ዘመን  እንኳን  በሃገሪቷ  ለየት  ያለ ክስተት ፤ ረሃብ ፤ ቸነፈር ፤ ጦርነት  ሲነሳ  ቤተ ክርስቲያን  አዋጅ አውጃ  ጸሎት  ምህላ ታደርግና በረከትን ከእግዚአብሔር ከአምላካችን ታሰጠን እንደ ነበር በቀደምት ዘመና የተጻፉ ድርሳናት ይናገራሉ፡፡ ከ23 ዓመት በፊት በ1983 ዓ.ም በወታደራዊው መንግስት መጨረሻ  የስልጣን  ቀናት ህዝቡ  ከፍተኛ ጭንቀት ውስጥ  ወድቆ  ነበር፡፡  እያንዳንዱ  ቀን ሊያስከትል የሚችለው ነገር ፤ ይዞት የሚመጣውን እልቂት እና ችግር ማንም እርግጠኛ  ካለመሆኑ ጋር አንዱ ካንዱ ይሻላል  ብሎ ሊመርጣቸው ከማይችል  ከሁለት ኀይሎች  ጋርም  የተፋጠጠበት ወቅት ነበር ፡፡  በአንድ በኩል  ‹‹አለሁ አልሞትኩም›› እያለ የሚፎክረው  ወታደራዊ  መንግሥት  በሌላ በኩል  ደግሞ  ወደ ፊት  እየገፋ  የነበረው  ተቃዋሚ  ኃይል አካሄድ ብዙ ግልጽ  ስላልነበረ በወቅቱ የህዝቡን  ጭንቅ ይበልጥ አብሶት ነበር፡፡ 


በዚህ ሰዓት ሕዝቡ በሃይማኖቱ እየተሰበሰበ ምህላ ጸሎት በተለያዩ አብያተ ክርስቲያት ካለማም አዛዥነት ጀምሮ ነበር ፡፡ በየአብያተ  ክርስትያናት ህዝብ እየተሰበሰበ አለቀሰ   ተከዘ እግዚአብሔርን ይቅርታ  ጠየቀ ፡፡  ያንዣበበው የእልቂት ደመና ዞር እንዲል ተማጸነ ፡፡ በግንቦት ወር መግቢያ ጀምሮ በመንበረ  ጸባኦት ቅድስት  ሥላሴ  ቤተ ክርስቲያን  ታላቅ  የምህላ  ጸሎት  በይፋ  ተነገረና  በርካታ ህዝብ ፤ የዘመኑ ጥቂት ባለስጣናት እና  የቤተክህነት አግልጋዮች  ተገኙ፡፡  በዚህ እለት  አለቃ አያሌው  ታምሩ በቦታ ተገኝተው  እንዲያስተምሩ  ተጋበዙ ፤ ያስተማሩትም ትምህር በአጭሩ ይህን ይመስላል፡፡

‹‹ በህዝብና በአገር ላይ ያንዣበበው የጥፋት ደመና ይገፈፍ ዘንድ ህዝቡ ወደ እግዚአብሔር እያቀረበ ያለው  እግዚኦታ  አስፈላና  ተገቢም  ነው፡፡  ግን በተለይ የዛሬን  የጸሎት መርሀግብር  ያስያዙት  ባለስልጣናት  የት አሉ ? ዛሬ እንደ ነነዌ ሰዎች  በእግዚአብሔር  ፊት መውደቅ  ነው የሚገባን  ምክንያቱም  የመጣው  ፍርድ አበሳ እና ውድቀት ማንንም ከማንም ሳይለይ የሚያንገላታ  በመሆኑ   ነው፡፡ በአገራችን በጎ ነገር ይኖር ዘንድ ከዋና መሪ እስከ ዝቅተኛ ኑሮ ድረስ ያለው  ሕዝብ ከልባዊ  ጾምና ጸሎት  ጋር  በእግዚአብሔር  ፊት  ሊወድቅ ይገባል ››  በማለት አስተምረው ነበር፡፡ 




ደርግ ስልጣኑ አፈር ሊበላ ሲቃረብ ለ17 ዓመት ብዙ ግፍና በደል ያደረሰባትን ቤተ ክርስቲያንን ምህላ  እንድታደርግ  በደብዳቤ  ቤተክህነቱን  ጠይቆ ነበር ፡፡  ቤተ ክርስቲያኒቷም  ጥያቄውን ተቀብላ  ምህላ  አውጃ  በየአብያተ ክርስትያናት  እና  በገዳሞች  ብዙ የሰው ደም  እንዳይፈስ ፤  ሀገር ሰላም እንድትሆን  ፤ ሀገሪቱ  ላይ የሚመጣውን አደጋ አምላክ  እንደ ንፋስ  አንዲያሳልፈው በምህላ  ከምዕመን  ጋር በአንድነት  ጸለየች  ፤ አዲስ አበባም  ብዙ እልቂት  ሳይከሰት  በለሆሳስ  ሁሉን  ነገር  አለፈ መንግስት ወረደ መንግሥት ተተካ ፡፡


ምንጭ ፡- የአለቃ አያሌው ታምሩ ማስታወሻ መጽሐፍ 

1 comment:

  1. Selam,

    I appreciate your publication & your sharing it with me.

    I repeatedly asked if you could give me website or whatever where I can find Aleqa Ayalew's teachings.

    Would appreciate very much if you could take the trouble,

    Commander Assefa

    ReplyDelete