ይህ ጽሁፍ በጋዜጠኛ ተመስገን ደሳለኝ የተጻፈ ሲሆን ፤ ሳንቆርጥና ሳንቀጥል ከመጽሄቱ ላይ
ያገኝነውን እንዲህ አቅርበነዋል ፤ አንባቢ ጽሁፉን የራሱ ሚዛን ላይ ማስቀመጡ ለራሱ ትተናል ፤ ጋዜጠኛው በአቅሙ የቻለውን
ያህል ካለበት ነባራዊ ሁኔታ ፤ ከሰማውና ካሳለፈው በመነሳት ነገን ለመጠቆም ጥረት አድርጓል….
ተመስገን ደሳለኝ
(ፋክት መጽሄት መስረም 25 2006 ዓ.ም)፡- የኢሕአዴግ ታጋዮች የመንግሥት ‹‹ጠንካራ ይዞታ›› የሚባሉ ከተሞችን ሳይቀር መቆጣጠር ችለዋል፤ ወደ አዲስ አበባም የሚያደርጉት ግሥጋሴም ፕሬዝዳንት መንግሥቱ ኃይለማርያምን ሳይቀር እንቅልፍ ነስቷል፡፡ በአንዳች ተኣምር ግሥጋሴውን መግታት ካልቻሉ በጥቂት ወራት ውስጥ ሁሉም ነገር ታሪክ እንደሚሆን በማወቃቸው መላ በማፈላለጉ ላይ ተጠምደዋል፡፡ በዚህን ጊዜ ነበር(የሐሳቡ አመንጪ ተለይቶ ባይታወቅም)፣
‹‹ለዩኒቨርስቲ ተማሪዎች አጭር ሥልጠና ሰጥቶ ከሀገሪቱ ሠራዊት ጎን ማሰለፍና የ‹ወንበዴውን ጦር› ማድረሻ ማሳጣት›› የሚለው ሐሳብ
እንደ መፍትሔ የተወሰደው፡፡
እናም መንግሥቱ ራሳቸው ተማሪዎቹን በዩኒቨርስቲ አዳራሽ ሰብስበው እንዲህ ሲሉ አፋጠጧቸው፡-
‹‹እነርሱ (ኢሕአዴግና ሻዕቢያን ማለታቸው ነው) ለእኩይ አላማቸው ከእረኛ እስከ ምሁር ሲያሰልፉ እናንተ ምንድን ነው የምትሠሩት?
በሰላማዊ ሰልፍና በስብሰባ ብቻ መቃወም ወይስ ወንበዴዎቹ እንዳደረጉት ከአብዮታዊ ሠራዊታችነ ጎን ቆማችኹ የአገሪቱን ህልውና ታስከብራላችሁ?››
ይህን ጊዜም አስቀድሞ በተሰጣቸው መመሪያ ከተማሪው ጋራ ተመሳስለው በአዳራሹ የተገኙት የደኅንነት
ሠራተኞችና የኢሠፓ ካድሬዎች ‹‹ዘምተን ከጠላት ጋራ መፋለም እንፈልጋለን›› ብለው በስሜትና በወኔ እየተናገሩ በሠሩት ‹ድራማ›
ተማሪው ትምህርት አቋርጦ እንዲዘምት ተወሰነ፤ አዲስ አበባ ዩኒቨርስቲም ተዘጋ፤ ተማሪዎቹም ለወታደራዊ ሥልጠና ደቡብ ኢትዮጵያ ወደሚገኘው
ብላቴ የአየር ወለድ ማሠልጠኛ ከተቱ፡፡
……….ከመላው ዘማቾች አሥራ ሁለት የሚኾኑ ተማሪዎች ተሰባስበው ሲያበቁ በየቀኑ ካምፓቸው አቅራቢያ
ወደሚገኘው ሚካኤል ቤተ ክርስቲያን በመሄድ ከመዐቱ ይታደጋቸው ዘንድ ፈጣሪያቸውን በጸሎት መማጠን የሕይወታቸው አካል አደረጉት፤
ከቀናት በኋላም በአንዱ ዕለት አንድም ለመታሰቢያና ለበረከት ፤ ሁለትም ስብስቡ ሳይበተን ወደፊት እንዲቀጥል በሚል ዕሳቤ ‹‹ማኅበረ ሚካኤል›› ብለው
የሠየሙትን የጽዋ ማኅበር መሠረቱ፡፡ . . . ይሁንና ከመካከላቸው አንዳቸውም እንኳ በ1997ዓ.ም በ‹ፓዌ መተከል› ዞን የተደረገውን
የመልሶ ማቋቋም ሠፈራ ፕሮግራም እንዲያመቻቹ በዘመቱ ተማሪዎች ከተመሠረተውና ከተለያዩ የጽዋ ማኅበራት ጋራ በመዋሐድ የዛሬውን
‹‹ማኅበረ ቅዱሳን›› እንደሚፈጥሩ መገመት የሚችሉበት የነቢይነት ጸጋ አልነበራቸውም፤ የሆነው ግን እንዲያ ነበር፡፡
‹ማኅበረ ቅዱሳን›
የ‹‹ማኅበረ ሚካኤል›› መሥራቾች ከተማሪ ጓደኞቻቸው ጋራ ‹‹ይለያል ዘንድሮ የወንበዴ ኑሮ››ን
እየዘመሩ የገቡበት ወታደራዊ ሥልጠና ተጠናቅቆ ወደ ጦር ሜዳ ከመግባታቸው በፊት አማፅያኑ አሸንፈው የመንግሥት ለውጥ በመደረጉ ሥልጠናቸውን
ሳይጨርሱ ወደየመጡበት ተመለሱ፡፡ ሆኖም ለውጡ በተካሄደ በዓመቱ እነርሱን ጨምሮ በአምላካቸው፣ በጻድቃን፣ በሰማዕታትና በመላእክታት
ስም የተመሠረቱ የተለያዩ ማኅበራት ከአቡነ ጎርጎርዮስ አስተባባሪነት በጠቅላይ ቤተክህነት ግ ተሰብስበው
ወደ አንድ እንዲመጡ መደረጉ ሊጠቀስ የሚገባው ልዩነት ባይፈጥርም ፤ ስያሜው ግን ብርቱ ክርክር አስነሳ፡፡ በአዳራሹ
ከተገኙ ጳጳሳት አንዱ የሆኑት አቡነ ገብርኤልም ‹‹ማኅበረ ቅዱሳን ብየዋለሁ›› ብለው ውጥረቱን አረገቡት፡፡ እቱም ግንቦት
ሁለት ቀን አስራ ዘጠኝ ሰማኒያ አራት ዓመተ ምህረት እደነበር ተጽፏል፡፡
ዓላማው ምንድን ነው?
ማኅበረ ቅዱሳን ሲመሠረት ‹ዓላማዬ› ብሎ የተነሣው አራት መሠረታዊ ጉዳዮች ላይ ማተኮር
መሆኑን በተለያዩ ጊዜ ለህትመት ባበቃቸው ድርሳናቱ ገልጿል፡፡ እርሱም ‹‹ትምህርተ ሃይማኖት፣ ሥርዐተ እምነት፣ ክርስቲያናዊ
ትውፊትና የሀገሪቱ ታሪክ ተጠብቀው ለትውልድ እንዲተላለፉ ማስቻል›› የሚሉ ናቸው፡፡
ማኅበሩ ከመሰሎቹ የተለየ ጥንካሬ እንዲኖረው ያስቻለው ዓላማውን ከግብ ለማድረስ በዋናነት በሀገሪቱ የተለያዩ ዩኒቨርስቲዎችና ኮሌጆች የሚማሩ ተማሪዎችን አባል ማድረጉ ላይ ተግቶ መሥራቱ ነው፡፡ ዛሬም ድረስ መስፈርቱ እያገለገለ እንደሆነ ይታወቃል፤ ይህ ሁኔታም ይመስለኛል አንዳንድ ጸሐፍት ማኅበሩን ‹‹የቤተ ክርስቲያኗ የዩኒቨርስቲ እጅ›› እንዲሉት ያስገደዳቸው፡፡
የሆነው ኾኖ ማኅበሩ በምሥረታው ማግሥት በሃይማኖቱ የመጨረሻውን ሥልጣን በያዘው ቅዱስ ሲኖዶስ
ዕውቅና ተሰጥቶት በጠቅላይ ቤተ ክህነት የማኅበራት ማደራጃ ሥር እንዲሆን ተደረገ፡፡ በ1985 ዓ.ም. ደግሞ መተዳደርያ ደንቡን
አጸደቀ፡፡
የግጭት ጅማሬ
ማኅበሩ ደንቡን ባጸደቀ ሰሞን ከመንግሥት ጋር ብቻ ሳይሆን ‹‹ሕገ ቤተክርስያንን ባፋለሰ
መንገድ በፓትያርክ ተሸመዋል›› በማለት ከተቃወማቸው አቡነ ጳውሎስ ጋር አይንና ናጫ ሆነ፡፡ እያንዳንዱ እቅስቃሴውም አራንሺ
ገ/መድህን ይመራው በነበረው የጸጥታ ክፍል ስር ወደቀ፡፡
አንዳንድ የኢሕአዴግ አመራሮች በብላቴ
ከተመሠረተው ‹‹ማኅበረ ሚካኤል›› ጋራ በማያያዝ የማኅበሩን መሪዎች አልፎ አልፎ ‹‹ተረፈ ደርግ›› እና ‹‹መዐሕድ›› እያሉ ከማሸማቀቅ
ባለፈ ብዙም ጫና አያደርጉባቸውም ነበር፡፡ ዛሬ ማኅበሩን በመንግሥት ጥቁር መዝገብ በቁጥር አንድ ጠላትነት እንዲሰፍር ካደረጉት
ልዩነቶች(ያለመግባባቶች) መካከል ዋናዎቹን በአዲስ መሥመር እጠቅሳለሁ፡፡
ኢሕአዴግ የአገሪቱን ምሥረታ ከዐፄ ምኒልክ ዘመን የሚጀምር የመቶ ዓመት ማድረጉ ማኅበሩ ዓላማዬ
ከሚለው ‹‹ታሪክን ጠብቆ ለትውልድ ማስተላለፍ›› ጋራ መታረቅ አለመቻሉ ያስከተለው ውጥረት የመጀመሪያው ነው፡፡ ማኅበሩ ‹‹የኢትዮጵያ
ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ›ን ታሪክ 2000 ዓመት ወደኋላ ሄዶ ማስላቱ ብቻውን፣ ‹‹አንዲት ኢትዮጵያን በመፍጠር ስም ምኒልክና ተከታዮቹ
ያስፈኑትን ጭቆና በጠመንጃ ለማስወገድ በረሃ ገባን›› ከሚሉት የህወሓት መሥራቾች ጋራ ሊያጋጨው መቻሉ የሚጠበቅ ነበር፡፡ ጉዳዩን
ከለጠጥነው ደግሞ ‹‹ማኅበሩን በ1980ዎቹ አጋማሽ እንደ ስጋት ይመለከተው የነበረውን ‹የሸዋ ፊውዳል› ወደ ሥልጣን ለማምጣት ያደፈጠ
ተቃናቃኝ አድርጎ ፈርጆት ነበር›› ወደሚል ጠርዝ ሊገፋን ይችላል፡፡ በነገራችን ላይ፣ በፖሊቲካው መንገድ ለሹመት የበቁት አቡነ
ጳውሎስም እስከ ኅልፈታቸው ድረስ ማኅበሩ በሸዋ ተወላጅ ጳጳስ ሊተካቸው የሚያሤር ይመስላቸው እንደነበር ይነገራል፡፡በጥቅሉ በኢሕአዴግና በማኅበረ ቅዱሳን መካከል የርእዮተ ዓለም (በብሔር እና በኢትዮጵያዊነት ላይ የተመሠረተ) ልዩነት መኖሩ ላለመግባባቱ መነሾ ነው፡፡
ሌላው የቅራኔያቸው መንስኤ ፣ በወርኃ ሚያዝያ 1993 ዓ.ም ፕሮፌሰር መስፍን ወልደ ማርያምና ዶ/ር ብርሃኑ ነጋ ከአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ ተማሪዎች ጋራ ሰብአዊ መብትንና አስተዳደራዊ ጉዳዮችን በተመለከተ የግንዛቤ ማስጨበጫ ውይይት ባደረጉ ማግሥት፣ በዋናው ግቢ ከተቀሰቀሰው ተቃውሞ ጋራ የሚያያዘው ሁነት ነው፡፡ በወቅቱ ተማሪዎቹ በሰላማዊ መንገድ ላቀረቡት ጥያቄ የጸጥታ አስከባሪዎች የኃይል ምላሽ መስጠታቸው ጉዳዩን ከቁጥጥር ውጭ አደረገው፡፡ ድብደባውና ማሠቃየቱ ከአቅም በላይ የሆነባቸው የተወሰኑ ተማሪዎችም ከመንበረ ፓትርያርኩ በአጥር ወደሚለየው ቅድስት ማርያም ቤተ ክርስቲያን ሸሽተው ይገባሉ፡፡ በአካባቢው የነበሩ የጸጥታ ሠራተኞችም የግቢውን በር ይቆልፋሉ፡፡ይሁንና የአቡኑን ድጋፍ ያገኙ ፖሊሶች ተማሪዎቹንም በኃይል አስወጥተው ደብድበው አሰሯቸው፤ ድርጊቱንም ማኅበረ ቅዱሳን በልሳኖቹ (‹ሐመር› መጽሄትና ‹ስምዓ ጽድቅ› ጋዜጣ) የቤተክርስቲያኗን ለሸሸ መጠለያነት ታሪክ አጣቅሶ አጠንክሮ መቃወሙ ከመንግሥት ጋራ በአደባባይ ቅራኔ ውስጥ ከተተው፡፡
ሌላው ቅራኔአያቸውን ያጦዘው ክስተት ደግሞ በአቶ ተፈራ ዋልዋ በ1998 ዓ.ም ወርኃ ጥቅምት በደቡብ ዩኒቨርሲቲ ለሚማሩ ተማሪዎች ‹‹መንግሥትና አብዮታዊ ዴሞክራሲ››
በሚል ርእስ ሥልጠና በተሰጠበት ወቅት ኦርቶዶክስን ‹‹የነፍጠኞች ፊት አውራሪ››፣ ጥምቀቱንም ‹‹በውሃ መንቦጫረቅ›› ብሎ ማጣጣሉ ሲኖዶሱን
ግድ ባይሰጠውም፣ ማኅበረ ቅዱሳንን አስቆጥቶ መልስ እንዲሰጥ ያደረገበት ኩነት መፈጠሩ ነበር፡፡
የመዋቅሩ ስፋትና የውጥረቶቹ ጡዘት
የማይቆጣጠረውን የተደራጀ ኃይል አጥብቆ ለሚፈራው ኢሕአዴግ፣ የማኅበሩ መዋቅር እየሰፋ መሄድ ስጋት
ላይ ጥሎታል፡፡ አባላቱ የዩኒቨርስቲ ወይም ኮሌጅ ምሩቃን መሆናቸው ከገጠር እስከ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ቢሮ ድረስ የራሱ ሰዎች እንዲኖሩት
አድርጓል፡፡ የአገዛዙም ጭንቀት ‹‹ይህ ኃይል አንድ ቀን በተቃውሞ ፖሊቲካ ሊጠለፍ ይችላል›› የሚል ነው፡፡ ይህንንም የሚያረጋግጠው
አቶ ኣባይ ፀሃየ መስከረም 2002 ዓ.ም. የማኅበሩን አመራር በሲኖዶስ ጽ/ቤት ባነጋገረበት ወቅት ግንባሩን መደገፍ እንዳለባቸው የገለጸበት መንገድ ‹‹ኢሕአዴግ ገለልተኛ የሚባል ነገር
አይገባውም›› የሚል መሆኑን ስናስታውስ ነው፡፡
በምርጫ 97 ዋዜማም አቶ መለስ የሃይማኖት ተወካዮችን ሰብስ ወደ ፖለቲካው እንዳይገቡ
ባስጠነቀቀበት መድረክ ተመሳሳይ አቋም ታይቷል፡፡ በወቅቱ
የብስራተ ገብርኤል አስተዳዳሪ የነበሩት አባ ኪሮስ መለስን ‹‹ከምስራቅ ይነሳል የተባለው ቴዎድሮስ እርስዎ ኖት›› ሲሉ
አወድሰው ነበር ፡፡ አባ ተክለሚካኤል የተባሉ መስፈሳዊ መሪ ደግሞ (በ2003 ዓ.ም ህይወታቸው ሲያልፍ ‹አቡን› ተብለው
ነበር) ከአባ ኪሮስ ፍጹም በተቃራኒ መልኩ ‹የሩሲያው ቭላድሚን ፑቲን በሃይማኖታዊ በዓላት ላ ይሳተፋሉ ፤ ያስቀድሳሉ ፤
ለሃይማኖታቸውም ይቆረቆራሉ ፤ እርስዎ ግን የህን ሲዲርጉ አይስተዋልም››
በማለት ወቀሳ አዘል አስተያየት አቅርበው ነበር፡፡ መለስ በበኩሉ ለውዳሴውም ሆነ ለወቀሳው ትኩረት የሰጠ በማይመስል አኳኋን
እንዲህ በማለት ነበር በጅምላ የሸረደዳቸው ‹‹ እውነተኞቹን በገዳም ያሉትን መነኮሳት በርሃ እያለሁ አውቃቸዋለሁ››፡፡ ይህ
የመለስ ሽርደዳ ዓላማ ወደ ተቃውሞ ጎራ ሊሳቡ ይችላሉ ብሎ የጠረጠራቸውን የቤተክርስያኒቱ መሪዎችንና ማኅበረ ቅዱሳንን ‹‹ለእኛ
ካልወገናችሁ ‹የቄሳርን ለቄሳር› አስተምህሯችሁን መከተል ግዴታችሁ ነው አሊያም ሃሳዊ ናችው›› የሚል መልዕክት ማስተላለፍ
ይመስለኛል፡፡
.
የሆነው ሆኖ በኢህአዴግ እና በቅንጅት መካከል በድኅረ ምርጫ የተፈጠረውን አለመግባባት ቤተ ክርስቲያኗ የቄሣርን ለቄሣር ብላ ለማንም ሳትወግን ዕርቅ እንዲፈጠር መሸምገል እንዳለባት ማኅበሩ በልሳኖቹ መወትወቱ የተገላቢጦሽ አገዛዙን አስኮረፈው፡፡ በአናቱም ከአማራ ክልል የተላከው ሪፖርት፣ ‹‹በገጠር ያሉ የማኅበሩ አባላት ለተቃዋሚዎች ቀስቅሰዋል›› ማለቱ ውጥረቱን አንሮታል፡፡
በሌላ በኩል መንግሥት ለሦስተኛ ጊዜ ባካሄደው የሕዝብ ቆጠራ ‹‹የክርስቲያኑ ብዛት 33 ሚልዮን
ነው›› ማለቱ፣ ‹‹45 ሚልዮን ነው ›› ከሚለው ማኅበረ ቅዱሳን ጋር አለመግባት ውስጥ ከትቶት እንደነበር ይታወሳል፡፡
የኢሕአዴግ ክሦች
ኢሕአዴግ በ1999 ዓ.ም በጅማ በሻሻ ቅዱስ ገብርኤል ቤተ ክርስቲያን ውስጥ ካህናትና ምእመናን
‹‹የእስልምና እምነት ተከታዮች ናቸው›› በተባሉ አንገታቸው በስለት ተቆርጦ መገደላቸውን የሚያሳየውን ፊልም በሲዲ አባዝቶ ያሰራጨውም
ኾነ ከጭፍጨፋው ጀርባ የመንግሥት እጅ አለበት የሚል የስም ማጥፋት ዘመቻ የመራው ማኅበሩ ነው ብሎ ያምናል፡፡
ከዚህ በተጨማሪ በአዲስ አበባ ‹‹ኢትዮጵያ የክርስቲያን ደሴት ናት››፣ በጎንደር ‹‹ጎዶልያስ››
(የእግዚአብሔር ጦር) የሚል ጽሑፍ የታተሙባቸው ቲሸርቶች አዘጋጅቶ ያሰራጨው ማኅበረ ቅዱሳን ነው ሲል ይከሳል፡፡ በነሐሴ ወር 2005
ዓ.ም በፌዴራል ጉዳዮች ሚኒስቴር ሚኒስትር ዶ/ር ሽፈራው ተክለ ማርያም ስም ‹‹የአክራሪነት/ጽንፈኝነት ዝንባሌዎችና
መፍትሔዎቻቸው›› በሚል ርእስ የተሰራጨው ሰነድ ክሡን፡-
‹‹ኢትዮጵያ
የክርስቲያን ደሴት ነች፤ አንድ አገር አንድ ሃይማኖት ወዘተ ጉዳዮችን በማቅረብ በአንድ በኩል የሃይማኖት ብዝኃነትን የሚፃረር፣
በሌላ በኩል ደግሞ አገራችን የሃይማኖት ብዝኃነት መኾኗን የሚቃወም አካሄድ ነው፤›› ሲል ያጠናክረዋል፡፡
(በነገራችን ላይ ከጥቂት ዓመት ወዲህ በጥምቀት በዓል
ታቦታቱ የሚያልፉበት መንገዶች አጽድተው ቀይ ምንጣፍ የሚያነጥፉ እና አደባባዮችን በባንዲራ የሚያስጊጡ በርካታ ወጣቶች እንዳሉ ይታወቃል፡፡ ኢህአዴግ
ይህ መነሳሳት አልሸባብ በአፍሪካ ቀንድ አካባቢ የሚያደርገውን የመስፋፋት ሙከራ ይገድባል የሚል እነት ቢኖረውም ፤ ከወታደራዊ መርጃ
እና ከደህንንቱ እንቅስቃሴ ከቁጥጥር እንዳይወጣም ሆነ እዳይደበዝዝ
የሚከታተል ቡድን በስውር ማዋቀሩን ሰምቻለሁ)
የኦቦይ ስብሃት ኩዴታ
በ2001 ዓ.ም ፓትርያርኩ አቡነ ጳውሎስ ከሹመታቸው በኋላ ለመጀመሪያ ጊዜ ከሲኖዶሱ አባላት ጠንካራ ተቃውሞ አጋጥሟቸው እንደነበር ይታወሳል፡፡ ይኹንና ከዚህ ንቅናቄ ጀርባ አቡነ ሳሙኤልናና ሁለት የማኅበረ ቅዱሳን የስራ አስፈጻሚ አባላትን የያዙት ኦቦይ ስብሃት ነጋ እንደነበሩበት ለጉዳዩ ቅርብ ከነበሩ ሰዎች አረጋግጫለኹ፡፡ አቦይ ስብሃት ‹‹አቡነ ጳውሎስ ለኢሕአዴግ ዕዳ ነው›› ብለው መደምደማቸው ለኩዴታ እንዳነሣሣቸው ይነገራል፡፡ በወቅቱ በተፈጠረ
አንድ አጋጣሚም ለሴራው የ‹መና› ያህል ነበር፡፡ ነገሩ እዲህ ነው ፓትርያርኩ ወደ ውጭ ሀገር የሚያደርጉት ጉዞ የሲኖዶስ
ይሁንታ ማግኝት እንዳለበት ሕገ ቤተክርስቲያን ይደነግጋል፡፡ ይሁንና በዚያ ሰሞን አቡነ ጳውሎስ እንደለመዱት ለማንም ሳያሳውቁ
ጣልያን የሚደረገውን የ‹ጂ20› ሀገራት ስብሰባ ላይ ለመገኝት ይሄዳሉ፡፡ ሲኖዶስም ባልተጠበቀ ሁኔታ ድርጊቱን ይቃወማል፡፡ ከቀናት
በኋላም (የፌደራል ጉዳዮች ሚኒስትር ተወካይ ባሉበት) በሲኖዶስ ስለ ድርጊታቸው ማብራሪያ የተጠየቁት አቡነ ጳውሎስ ‹‹እኔ
በሕገ ቤተክርስቲያን አላምንም›› የሚል ምላሽ በመስጠት ጉዳዩን ጭራሽ ሰማይ ጥግ ያደርሱታል፡፡ በዚህ ከመጠን በላይ የተበሰጩት
አቡነመልከጸዴቅ ‹‹እርስዎ የጦር ጀኔራል ኖት›› የሚል ኃይለ ቃል እስከመናገር ደርሰው ነበር፡፡
የሆነው ሆኖ የኦይ ስብሃት ፖለቲካዊ ድጋፍ ይዘው ፤ አጋጣሚውን በረቀቀ መንገድ የተጠቀሙበት
አቡነ ሳሙኤል እለቱን ፓትርያርኩን ከአስተዳደራዊ ስራ አውጥቶ በ‹ባራኪነት› ብቻ ወስኖ የሚስቀምጣቸውን ፍኖተ ካርታ
ያዘጋጃሉ፡፡ ይሁንና ሃሳቡ ውሳኔ ሳያገኝ ቀኑ በመምሸቱ ለማግስት
ቀጠሮ ተይዞለት ይለያያሉ ፤ ግና ሁሉም አባቶች ‹በማታ እንግዳ› ተጎብኝተው ነበር፡፡
አቡነ ሳሙኤል ከተመረኮዙት የጠነከረ የፖለቲካ ኃይል ያለውን ወገን ያየዙት ፓትርያርክ ፤ ከምሽቱ 4 ሰዓት በኋላ ወደ ጳጳሳቶቹ ማደሪያ በርካታ የደህንነት
ሰራተኞችን አሰማርተው ከፍተኛ እንግልትና ማስፈራሪያ አደረሱባቸው
፤ በተለይ ደግሞ በስብሰባው ላይ ጠንካራ ተቃውሞ ያቀረቡት አቡነ መልከጸዲቅ ከዛው ከፓትርያርኩ ቤተመንግስት ከሚገኝው ማደሪያቸው
በኃይል ኢሚግሬሽን ግቢ ወስደው
አሰቃይተዋቸዋል(ዘግይቶ ሕይወታቸው ያለፈው ከዚሁ ጋር
በተያያዘ እንደሆነ ሰዎቻቸው ይናገራሉ)፡፡ የኩዴታው መሪ አቡነ ሳሙኤል ወደ ስብሰባው አዳራሽ ለመሄድ ማልደው ከመኝታቸው
ቢነሱም መመርካታ የፖሊስና የደህንነት ሰዎች ተከበው ከቤታቸው ወደየትም መንቀሳቀስ እንደማይችሉ ይነገራቸዋል፡፡ በወቅቱ
በአካባቢው ከነበረ ሰው ባገኝሁተ መረጃ መሰረት አቡነ ወደ አቦይ
ስብሃት ስልክ ደውለው ስለ ክስተቱ አማክረዋቸዋል ፤ ያደረጉት
ንግግር ይህን ይመስላል
አቡነ ሳሙኤል ፡- የታጠቁ ሰዎች ከበውኛል ወደየትም መሄድ አልቻልኩም››
አቦይ ስብሃት ፡- ዝም ብለህ ሂድ
አቡነ ሳሙኤል ፡- አንገልሃለን እያሉኝ ነው እኮ
አቦይ ስብሃት ፡- ይግደሉህ
አቡነ ሳሙኤል ፡- ሹፌሬን አግደው የመኪና ቁልፍ ነጥቀውታል
አቦይ ስብሃት ፡- በእግርህ ሂድ
ይሁንና አቡነ ሳሙኤል መሄድ ሳይችሉ ቀሩ ፤ ስብሰባው እርሳቸው በሌሉበት ተካሄደ ፤ በውጤቱም ፓትርያርኩ አሸነፉ፡፡ በወቅቱ መንግሥት ማኅበረ ቅዱሳንን
የሴራው ጠንሳሽ አድርጎታል ፈርጆታል፡፡ በግልባጩ ማኅበሩ የእቅስቃሴው ተቃዋሚ መሆኑን የተረዱት ስብሃት ነጋ ጥርስ እንደነከሱበት ይነገራል፡፡( በነገራችን ላይ
የአቦይ ስብሃት እቅድ ቢሳካ ኖሮ ተያይዘው በሚነሱ
አለመግባባችን በመጠቀም ማኅበሩን መምታትንም የሚያካትት ነበር፡፡)
የዋልድባ ጉዳይ
በመንግሥትና በማኅበረ ቅዱሳን መካከል የነበረውን አለመግባባት ወደላቀ ጠርዝ ያደረሰው በዋልድባ
ገዳም አካባቢ ይቋቋማል የተባለው የስኳር ፋብሪካ ጉዳይ ነው፡፡ በገዳሙ የሚኖሩ ምእመናንን ጨምሮ በርካታ የእምነቱ ተከታዮች ያሰሙትን
ተቃውሞ ችላ በማለት ወደ ሥራ ለመግባት በሞከረው መንግሥት ላይ የተነሣው ተቃውሞ ተጠናክሮ ቀጠለ፡፡ ይኹንና ሥርዐቱ ገዳሙ ላይ
አልደርስም ብሎ ሲከራከር፣ ቤተ ክህነትም የማጣራት ሥራ መሥራቱን ገልጦ ‹‹ምንም ዐይነት ችግር የለም›› ብሎ ከመንግሥት ጎን ቆመ፡፡
ማኅበረ ቅዱሳን ጉዳዩን ቦታው ድረስ ሄዶ የሚያጣራ አምስት አባላት ያለው ቡድን ወደ ዋልድባ ላከ፡፡ ቡድኑ አጥንቶ ባቀረበው ሪፖርት፡- ‹‹16.6 ሄክታር መሬት ከገዳሙ ተወስዷል፤ ወደፊት ገዳሙን የውሃ መጥለቅለቅ ያሰጋዋል . .
.›› የሚል ሪፖርት ለመንግሥት አቅርቧል፡፡ በተቃራኒው ደግሞ የዶ/ር ሽፈራው ሰነድ የማኅበሩን ጥናት እንዲህ ሲል ኮንኖታል፡- ‹‹መንግሥት በሃይማኖታችን ጣልቃ ገብቷል በሚል ገሃድ ፍላጎትና ድብቅ አሠራር ካላቸው የውጭ ቡድኖች ጋራ በማበር ሰላምን አደጋ ውስጥ የማስገባት፣ ሕገ መንግሥታዊ ሥርዐቱን በሃይማኖት ሽፋን ለመናድ ይንቀሳቀሳሉ፡፡ በቅርብ በነበረው የፓትርያርክ ምርጫና በዋልድባ ገዳም ዙሪያ የተፈጠረው ዝንባሌ የነዚህ ፍላጎቶች ማሳያ ነው፡፡››
የፓትርያርኩ ኅልፈት
በ2004 ዓ.ም መጨረሻ አቡነ ጳውሎስ ማለፋቸው ሌላ ፍጥጫን አስከትሏል፡፡ ማኅበሩ
ስደተኛውን ፓትርያርክ አቡነ መርቆሬዎስን ከአሜሪካ አምጥቶ ወይም እንዳሻው የሚያሽከረክረውን ጳጳስ መንበሩ ላይ ለማስቀመጥ
ምርጫው በሚፈልገው መንገድ እንዲጠናቀቅ በርትቶ እየሠራ ነው የሚለው ወቀሳ የመንግሥት ቁጣን የበዛ አድርጎታል፡፡ የጠቀሱት
ሰነድም ውንጀላውን በገደምዳሜ ገልጾታል፡- ‹‹በእስልምናም
ይሁን በክርስትና ሃይማኖቶች ሽፋን የሚደረገው የአክራሪነት/ጽንፈኝነት እንቅስቃሴ በዋናነት እየነጣጠረ የሚገኘው የተቋማቱን የበላይ
አመራር ዕርከኖች መቆጣጠር ነው፡፡››
ናዳው እየመጣ ነው?
ባለፉት ሁለት ዓመታት የእስልምና እምነት ተከታዮች
‹‹መንግሥት በሃይማኖታችን ጣልቃ አይግባ›› በሚል የጀመሩትን ትግል ተከትሎ አገዛዙ ማኅበረ ቅዱሳንንም ደርቦ የመምታት ዕቅድ
እንዳለው የሚጠቁሙ ምልክቶች ታይተዋል፡፡ የኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች ጽ/ቤትን በሚኒስትር ማዕርግ የሚመራው አቶ ሬድዋን ሑሴን፣ ‹‹መንግሥት ጉዳዩን በሰላም ቢጨርሰው የተሻለ
ነው›› ሲሉ ምክር ለመለገሥ ለሞከሩ የምዕራብ አገሮች ዲፕሎማቶች፣ ‹‹የአወሊያን ቡድን በዚህ መልኩ ሳናበረክከው ቀርተን
መጅሊሱን እንዲወስድ ብናደርግ፣ ነገ ደግሞ ማኅበረ ቅዱሳን ‹ሲኖዶሱን አምጡ› ቢለን ምን መለስ ይኖረናል?›› ሲል የሰጠው ምላሽ ይህንኑ የሚመለክት ነው፡፡
የፌዴራል ጉዳዮች ሚኒስቴር መ/ቤት ባለፈው ዓመት
ወርኃ የካቲት ‹‹ለሃይማኖት ተቋማት የተዘጋጀ›› ብሎ ያሰራጨው ሰነድ ማኅበረ ቅዱሳን እና መብታቸው እየጠየቁ ያሉ የእስልምና
እምነት ተከታየች የጥቃቱ ዒላማ እንደኾኑ ያሳያል፡፡ ሂደቱን በመምራትም ኾነ በማስፈጸም ከፌዴራል ጉዳዮች ሚኒስትር ጀርባ ኾኖ
በዋናነት የሚሠራው የፀረ ሽብር ግብረ ኃይል እንደኾነ ይታወቃል፡፡
በአንድ ወቅት ዶ/ር ሽፈራው ተክለ ማርያም
‹‹የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት የፖሊቲካ ርብርብ ሜዳ አይኾኑም፤ የመንግሥት መሥሪያ ቤቶችም ከማንኛውም ሃይማኖታዊ እንቅስቃሴ
ነጻ መኾን አለባቸው›› ያሉበት ዐውድ ‹‹በዩኒቨርስቲዎች የአካዳሚ ትምህርትን ተገን በማድረግ እምነትን ማስፋፋት አይቻልም››
በማለት ማኅበሩ እንደ ቀድሞው አባላቱን ለማስተማር የሚችልበትን ኹኔታ የሚያግድ ነው፡፡
በ2006 ዓ.ም በዩኒቨርስቲዎች ይተገበራል የሚባለው አለባበስንና አመጋገብን የሚመለከተው መመሪያም ራሱን የቻለ አደጋ አለው፡፡ እንዲሁም የሃይማኖት ማኅበራት
ዓላማቸውን አሳውቀው እንዲመዘገቡ የሚያስገድደውን ሕግ በምክር ቤት ለማጸደቅ ዝግጅቱ ተጠናቋል፡፡ መዝጋቢው ክፍል ማኅበራቱን በፍርድ
ቤት ከማስቀጣት እስከ ማፍረስ የሚያደርስ ሥልጣን እንደሚሰጠው ምንጮቼ መረጃ አድርሰውኛል፡፡ ይበልጥ የመንደነግጠው ደግሞ በዚህ
መልክ ማኅበራቱን ከጠለፉ በኋላ ማንም ሰው ‹‹ቅዱስ ቃሉን›› ለመስበክ ፈቃድ ማግኘትን ግዴታ ለማድረግ መታቀዱን ስናነብ ነው፡-
‹‹የሰባክያን/ዳኢዎች ሚናን የበለጠ ለማጎልበትና የተጠያቂነት ሥርዐት ለመትከል እያንዳንዱ የሃይማኖት ተቋም የራሱን መምህራን የሚለይበትን የመታወቂያ ሥርዐት ሊያበጅና በዚህም የክትትል ሥራ እንዲሠሩ መደገፍ ይቻላል፡፡››
ሰነዱ ወደ መንፈሳዊ ኮሌጅ የሚገቡ ተማሪዎችንም መልምሎ
የሲኖዶሱን፣ የማኅበረ ቅዱሳንን፣ የመጅሊስን. . .አመራርነት የመያዝ ዕቅድ እንዳለው በዘወርዋራ ይጠቁማል፡፡ የፌዴራል ጉዳዮች
ሚኒስቴር በ2004 ዓ.ም ባዘጋጀው የሥልጠና ማንዋል ላይም ‹‹በኦርቶዶክስ ክርስትና መድረክ አክራሪው ኃይል ማኅበረ ቅዱሳን ነው›› ሲል መፈረጁ ይታወሳል፡፡ ከዚህ ጎን ለጎንም የማኅበረ ቅዱሳንን ግቢ ጉባኤ በማዳከም፣ ከሰንበት
ት/ቤቶች፣ ከሰበካ ጉባኤና ከሀገረ ስብከት ሥራ አስኪያጆች ጋራ በማጋጨት፣ በካህናት በማስወገዝና በመሳሰሉት ተጠቅሞ ሊያፈርሰው እንደተዘጋጀ መረጃዎች ይጠቁማሉ፡፡
በጥቅሉ ሰነዱ ማኅበረ ቅዱሳንን ‹‹በሃይማኖት ሽፋን
የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ሃይማኖት መንግሥታዊ ሃይማኖት መኾን ይገባዋል በሚል በአቋራጭ በአቋራጭ የፖለቲካ መሣርያ ለማድረግ የሚንቀሳቀስ››
ሲል ይኮንነዋል፡፡ ‹‹የአክራሪነትና ጽንፈኝነት ምንጩን ለማድረቅ እየተሠራ የሕግ የበላይነትን የማስከበር
ሥራም ጎን ለጎን መፈጸም ያለበት ነው፤›› ሲል ጥቁምታ ይሰጣል፡፡
መፍትሔው ምንድን ነው?
ከላይ በጥቅሉ እንደጠቀስኩት የ22 ዓመታቱ ሂደት የሚያስረግጠው፣ የኢሕአዴግን ማንኛውም ዓለማዊም ኾነ ሃይማኖታዊ ተቋማት ነጻነት ያለማክበሩ ብቻ ሳይኾን ቀስ በቀስ ህልውናቸውን ለዘላለሙ ለማጥፋት በሙሉ ኃይሉ እየሠራ እንደኾነ ነው፡፡
የሆነው ሆኖ የማኅበረ ቅዱሳን ሰዎች ተቋቸውን ለመከላከል ከሕዝበ ሙስሊም እቅስቃሴ የተሻለ የሚመርጡት
መንገድ ያለ አይመስለኝም፡፡ በዚህመንገድ ተጉዘው ሕዝበ ክርስያኑን ሕዝባዊ ንቅናቄ ፈጥሮ በመከራው ጊዜ የደረሰለትን ‹‹የእምነቱን ዘብ እንዲታደግ›› ጥሪ ማስላለፍና
ማነሳሳት ይጠበቅባቸዋል፡፡
ማኅበሩ በእስልምና ሃይማኖትና በተከታዮቹ ላይ ያለውን ከተጨባጭ እውነታ ጋር የሚረሱ ምልከታዎቹን
እና ለፍትሃዊው ሕዝበ ሙስሊም ያሳየውን ዝምታ በመግራት የራሱን ህልውና እጅግ በፍጥነት ለመታደግ መሞከር ይኖርበታል፡፡፡ ከሥርዐቱ የፖሊቲካ ዘዬ እንደተረዳነው ቀስ በቀስ እየተረዳነው በመጣው አፈና ላይ ማኅበሩ አንገቱን ቀብሮ፣ ጣልቃ
ገብነቱን ቸል ብሎ የማንገራገሩ አካሄድ፣ በአንድ ክፉ ቀን በመጅሊሱ የተፈጸመው ታሪክ በራሱም ላይ መደገሙ አይቀሬ እንደኾነ ለመናገር
ነቢይ መኾንን አይጠይቅም፡፡ በርካታ ምዕመናን መኖራቸው ፤ ዓለማዊ የትምህርት ተቋማት የረገጡ ከተሜ ወጣቶች በማኅበሩ ውስጥ መብዛታቸው
የመውጫ መንገዱን በአመራሩ ላይ ይጥለዋል ‹‹ለትላንት አናረፍድም፤
ለነገ አንዘገይም›› እንዲሉ የቤተ ክርስቲያኗ ሊቃውንት፡፡
Hi its awesome &outstanding issues,thanks god ,I can't wait that day.here days come,thanks god again.they goon pay it.
ReplyDeleteYou guys are the one you goon take
ReplyDeleteresponsibility for the lost &misleading
of the orthodox church members.even for the conflict between government and church members you drag to hell
Those they don't know about their religion doctrine and your point of view .
but god he look after you.may be he comes to punish ,clean his house &he make straight up everything.I can't wait
that day.to MK
yhe yezet egziabhiyer yrdan.
ReplyDelete