Thursday, February 6, 2020

የመንግሥት ይፋዊ ጦርነት‼

(በዲ/ን ብርሃኑ አድማስ)
(አንድ አድርገን ጥር 29 2012 ዓ.ም) ፡- ትናንት ሌሊት ላይ በአዲስ አበባ 24 አካባቢ በኦርቶዶክሳውያን ላይ በመንግሥት የተፈጸመው ሽብር በእጅጉ አሳዛኝ እና አሳፋሪ ነው።  ነገሩ በሌሉት የተደረገው ጉዳዩ ሕግ ለማስከበር ሳይሆን መንግሥት ከቤተ ክርስቱያናችንና ከኦርቶዶክሳዊያን ጋር ይፋዊ ጦርነት መጀመሩን ለማወጅ ይመስላል፡፡

በሕልም ዐለም ውስጥ ያሉ የሚመስሉኝ ኦርቶዶክሳውያን ምንም ያህል ቢሉለት ለእኔ እስከሚገባኝ ድረስ ይህ መንግሥት ጸረ ኦርቶዶክስ መሆኑ ግልጽ ከሆነልኝ ሰነባብቷል።  አንዳንዶቹ ባለሥልጣናት ምንም ያህል ቢያስመስሉም እውነታውን ሊደብቁት አልቻሉም።  በርግጥ ማስመሰላቸው የማይታወቅባቸው አደገኛ ጸረ ኦርቶዶክሶች እንደሚኖሩም እጠረጥራለሁ።  ነገር ግን ጌታ በወንጌል የማይገለጥ የተከደነ ነገር የለም እንዳለ ለጊዜው ነው እንጂ ሁሉም ግልጥ የሚሆንበት ጊዜ ሩቅ አይሆንም። የዚያን ጊዜ ደግሞ በሰፈሩት ቁና መሰፈር የማይቀር መሆኑ የተፈጥሮ ሕግ ነው።


የከተማው ምክትል ከንቲባ ሐዘንዎን መግለጥዎ ከልብ ከሆነ ሐዘን ቤት በመሔድ ፋንታ በተግባር ሊያሳዩን የሚገባዎ ብዙ ተግባራት አሉ። 

1) ምንም ያህል የሕግ ጥሰት ቢኖር በሌሊት እንደ ይፋ ጦርነት በተደረገው እዝ የመጀመርያው ተጠያቂ ስለሆኑ ትእዛዝ በተቀበሉት ከማላከክ ይልቅ እርስዎና የውሳኔውና የትእዛዙ ተሳታፊዎች በይፋ ይቅርታ ከመጠየቅ ጀምሩ።

2) ያሠራችኋቸውን በሙሉ ያለ ምንም ቅድመ ሁኔታ ፍቱ። የታሠሩት ምንም የተለየ ወንጀል አልሠሩም። ቤተ ክርስቲያን ስለተገኙ እና በሕግ ሰበብ የሕግ ጉልበት ተጠቅሞ እንደ ሌባ በሌሊት የመጣን አካል ለመከላከል ከመሞከራቸው በቀር ያደረጉት የለምና ልቀቋቸው።
 
3) ካዘዛችሁና የልባችሁን ካደረሳችሁ በኋላ ይህን ያህል ሰው ይዘናል (ሳይያዝም ሊሆን ይችላል) በማለት ፋንታ ተመትተው የቆሰሉትን አሳክሙ።

4) ያወደማችሁትን መልሳችሁ ቦታውን በሕግ አስረክቡ።
 
5) በዚህ ሽብር መሰል መንግሥታዊ ጦርነት ከሐሳብ እስከ ውሳኔ የተሳተፉትን አካላት ከሥልጣናቸው ወርደው በሕግ ተጠያቂ ይደረጉ። ያን ጊዜ መንግሥት ለሕዝብ ማሰቡን መናገር ይችላል። ከዚህ ውጭ እኔን የሚገባኝ ከስውርና ከውስጥ ለውስጥ ጥቃት ወደ ይፋዉ ጦርነት መሸጋገራችሁ ብቻ ነው።

ክቡር ከንቲባ ሆይ መንግሥትና ሕዝብን ለማጣላት ያሰቡ አካላት ሲሉ መናገረዎ ደግሞ ጭራሽ ሌላ ጥቃት ለመፈጸም የሚያስቡ መሆንዎን ከማሳየት ያለፈ ፋይዳ የለውም። የመንግሥት ምንነት አልገባኝ ብሎ ካልሆነ በቀር እውነት እልዎታለሁ ለዚህ መንግሥት ከራሱ በላይ ጠንካራ ጠላት የለውም።

No comments:

Post a Comment